ኑሮን ስለ ማቅለል

ኑሮን ስለ ማቅለል

| ጃንደረባው ሚድያ | መጋቢት 2016 ዓ.ም.|

✍🏽 ቀሲስ ታምራት ውቤ

“ሰው ለምቾትና ለተቀማጠለ ሕይወት ራሱን አሳልፎ ሲሰጥ ለንስሓ ያለው ቁርጠኝነት ይቀንሳል፡፡ ”

(ፍና ቅዱሳን – ገጽ 51)

ብዙ ጊዜ በምቾት የተቀማጠለ ሕይወትን እና ኑሮን ቀለል ባለ (በዘመናዊ ዘይቤ) መኖር የሚሉትን ሃሳቦች ቀላቅለን እናያቸዋለን ፡፡ ነገር ግን ሁለቱ ሃሳቦች የሚለያዩ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም እኛ እየኖርን ያለነው (ለመኖር የምንጥረው) የትኛውን ዓይነት ኑሮ ነው? በአካል፣ በነፍስና በአስተሳሰብ መኖር የሚገባንስ እንዴት ነው? 

መልስ፦ ሰው ለምቾትና ለተቀማጠለ ሕይወት ራሱን አሳልፎ ሲሰጥ ለንስሓ ያለው ቁርጠኝነት ይቀንሳል? እውነት ወይም ሐሰት መሆኑን ለማወቅ ሩቅ መሔድ አይጠበቅብንም ራሳችንን ማየት እንጂ። አበው “ዝናም ዘነበ ቢለው፥ በየደጅህ እየው” እንዲሉ በየራሳችን ሕይወት ስናየው እውነት ነው ምቾትና የተቀማጠለ ሕይወት ምን ያህል ለንስሐ ልምሾ እንደሚያደርገን ማየት እንችላለን። 

እስቲ ተጠየቁ ፦ 

በዘመኑ ቋንቋ በዚህ በዚያ ብሎ ማለት ሰርቆ ፣ አጭበርብሮ ፣ ጉቦ ተቀብሎ፣ ደሀ አስለቅሶ የተቀማጠለ ሕይወት ይጀምርና ሲጠየቅ የሰው ሕይወት ተፍትፎ ያገኘውን፤ ተፍ ተፍ ብዬ የሠራሁትና ያገኘሁት ነው የሚል ሰው ንስሐ ሊገባ ሲመጣ፤ ይህንን ሁሉ ነገር ያገኘሁት ሰርቄ ነው ሲል፤ በል  እውነት ከልብህ ንስሐ መግባት ከሆነ የፈለከው “የወሰድከውን መልስ ፥ የበደልከውን ካስ” ቢባል ያ ሰው ተመልሶ ይመጣል? 

መልሳችን፦ አይመጣም ነው። ስለዚህ ለጥያቄው መልስ ተሰጥቷል ማለት ነው!

አሁን ደግሞ ሻል ያልን ነን፤ በቤቱ እንኖራለን የምንል ለንስሐ እንመጣና ምን አጠፋችሁ? ስንባል፥ “እንዲህ አድርገን ፣ እንዲህ አድርገን . . . ” ስንል በሉ እመቤታችን በጸሎቷ በምልጃዋ እንድትቆምላችሁ ውዳሴዋን እየደገማችሁ ስድሳ አራት ስገዱ ስንባል ምንድነው መልሳችን?  የዚህን ጊዜ የችግር ብዛት መምዘዝ ይጀመራል ፤ እንዲህ ሆኜ፣ በዚህ ወጥቼ ፣ በዚህ ወርጄ . . . ማለት እንጀምራለን። የወገባችንን ጤንነት የሚያረጋግጥ ኃጢአት ሠርተን ለንስሐ የመጣነው ሁሉ ቀኖናው ሲሰጠን ለመስገድ ጉልበቴን ወገቤን እያልን ለእኛ የሚስማማን ቀኖና እንዲሰጠን ለማሳመን እንጥራለን። ጨከን ሲባልብን ደግሞ እሳቸው ጋር አለመሄድ ነው እንላለን። ለምን? ሲባል እሳቸው ያከብዳሉ እንላለን። 

በነገራችን ላይ አሁን እኮ አባቶች ካህናት  ንስሐ የሚሰጡን በድርድር ነው። ይህንን ብንላቸው አይፈጽሙትም በዚያው ይቀራሉ ብለው በመስጋት አባብለው ይዘውን ነው እንጂ በመጽሐፉ የተደነገገውን ተከትለው አይደለም። አያችሁ ለዚህ ያበቃን ቅምጥልነት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ  “ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፥ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤ ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት” (1 ጢሞ 5: 5-6 ) እንዳለ በጠዋት ተነስታ ጥሩ ነገርን ወደ አፍዋ ማለት የለመደችን ቅምጥል ሴት ጾም ስናዛት ይፈትናታል። ስለዚህ አባብለን ነው ሁሉን የያዝነው። 

ቴክኖሎጂን ፣ ሌላ ሌላውንም በመጠቀም ኑሮን ማቅለል ጥሩ ነው። እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፦ ኑሮን ማቅለል ለምን? ኑሮ እንዲቀልላችሁ የምትፈልጉት ለምንድ ነው?

ላለመድከም የሚል መልስ ከጉባዔው ሲመለስ ፤ ጉባዔው አባብሎ የመለሰውን መልስ አባታችን “ለስንፍና እንዲመቸን ነው” ብለው አሰተካከሉን ። አባቶቻችን ሰባት ዋና ዋና ኃጢአቶች ብለው ከሚሏቸው ውስጥ ስንፍና አንዱ ነው።

ሰነፍ ሰው የኃጢአት መደብር ነው። ሰነፍ የሆነ ሕሊናውም ሰውነቱም ሥራ የፈታ ሰው የሚሄደው ኃጢአትን ወደ መሥራት ነው። አስተውሉ! ድሮ ሕይወት ከባድ በነበረበት ጊዜ ሰው ጭንቀቱ ፣ ሓሳቡ ሁሉ ኑሮውን ለማሸነፍ ነው። አሁን ግን ኑሮ ቀለል ሲል ጭንቀቱ ጠፋ። አሁንም ልብ ብላችሁ ራሳችሁ ታዘቡ እስቲ ፤ ኑሮን አቀለልን ስንል አንዱ በጣም ያቀለልነው ነገር ቢኖር ኃጢአት የመሥራት መንገድን ነው። ልክ ኑሮን ያቀለልነውን ያህል ኃጢአት የመሥራትንም መንገድ ቀላል አድርገነዋል። 

📙 አንድ መጽሐፍ ሳነብ እንዲህ ይላል፦ “ነፃ መሆን መልካም ነው ፥ ነፃ የሆንከው ግን ከምንና ለምን እንደሆነ ጠይቅ” ይላል። በአሜሪካን የጥቁሮች ታሪክ ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ነፃ ከወጡ በኋላ ነፃነታቸውን ምን እንደሚያደርጉት እና ምን እንሁን ብለው እንደጠየቁት እና ግራ እንደገባቸው ፥ የተወሰኑት ደግሞ ተመልሰው ወደ ጌቶቻቸው እንደሄዱት  እንዳንሆን ነፃ የምንሆነው ከምንና ለምን እንደሆነ በደንብ መገንዘብ ያስፈልጋል። 

ጌታ እግዚአብሔርም ሰው ነፃነቱ ግራ ሊያጋባው እንደሚችል ስለሚያውቅ እንዲህ ብሏል:- “አንተም ወንድምህን ዕብራዊውን ወይም ዕብራዊቱን ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግሉህ በሰባተኛውም ዓመት ከአንተ ዘንድ አርነት አውጣው። ከአንተም ዘንድ አርነት ባወጣኸው ጊዜ ባዶውን አትስደደው፤ ነገር ግን ከመንጋህ፥ ከአውድማህም፥ ከወይንህም መጥመቂያ ትለግስለታለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ባረከህ መጠን ትሰጠዋለህ። አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደ ነበርህ አምላክህም እግዚአብሔር እንዳዳነህ አስብ፤ ስለዚህ እኔ ዛሬ ይህን ነገር አዝዝሃለሁ። እርሱ ግን አንተንና ቤትህን ስለወደደ፥ ከአንተም ጋር መልካም ስለ ሆነለት፦ ልወጣ አልወድድም ቢል፥ አንተ ወስፌ ወስደህ በቤትህ በር ላይ ጆሮውን ትበሳዋለህ፥ ለዘላለምም ባሪያ ይሆንልሃል። በሴት ባሪያህ ደግሞ እንዲሁ ታደርጋለህ።”  

(ዘዳግ 15: 12-17) (ዘጸአ 21: 2-6 )

እኔና እናንተም አንዳንድ ጊዜ እንዲሁ ነው። እረፍት ነው የናፈቀኝ በጣም እንደው እረፍት ወጥቼ እንልና ከመሥሪያ ቤት አሥራ አምስት ቀን እረፍት ሞልተን ወጥተን በሦስተኛው ቀን ምን እንደምናደርገው ግራ ይገባናል። ከዚያ በኋላ እቤት ውስጥ በሆነው ባልሆነው መነጋገርና መጨቃጨቅ እንጀምራለን። ይህንን የምናደርገው ማድረግ ፈልገን ሳይሆን እረፍቱን እንዴት አንደምንጠቀምበት ስላላወቀን ነው። ስለዚህ ሊያርፍ የወጣው ሰው ወደ መሥሪያ ቤት ሲመለስ ተደብሮ፣ ደክሞት ፣ ዝሎ፣ የሥራ ፍላጎቱ ሞቶ ነው ። 

📣 አንድ ነገር ከመጠየቃችሁ በፊት ለምን እንደፈለጋችሁት ግን እርግጠኛ ሁኑ!

♦️ ሀብት ፈልጎ ሲያገኝ ምን እንደሚያደርገው ግራ የሚገባው ሰው አለ፤

♦️ ትዳርን ፈልጎ ሲሰጠው ምን እንደሚያደርገው ግራ የሚገባው ሰው አለና፥ ሌላም ሌላም እንዲሁ ።

✍️  አሁንም ሕይወታችንን ማቅለል ነው አልን ። እሺ ብሎ አቀለለው። የኑሮን መቅለል ለምን ፈለግነው? ለምን እንደምትፈልጉት እርግጠኛ ሁኑ ! ብዙ ነገር ጠይቀን እግዚአብሔር የሚያዘገይብን ያንን የጠየቅነውን ነገር ለምን እንደ ፈለግነው  እርግጠኛ እስከምንሆን ነው። እርግጠኛ ሆናችሁ መልስ ስትሰጡ ይሰጣችኋል። እርግጠኛ ሆናችሁ ካልነገራችሁት ግን ጌታ እግዚአብሔር እንድትጠፉበት ብሎ አይሰጥም። ይህን ልብ በሉ!

📌📌 አስተውሉ! እስካሁን ያየናቸው ሁሉ ክርስትና ሕይወት ነው እንዳልን እንድንኖርባቸው የሕይወት መመሪያ ነው እየተማርን ያለነው እንጂ ሌላ አይደለም። ስለዚህ በየእለት የሥጋ ሕይወታችሁ ላይ አምጡና ተጠቀሙበት ። አንድ ሰኞ የምትማር ልጄ ለምን እንደሚማሩ ለተጠየቁት ጥያቄ መልስ እንዲህ ብላ መልሳለች:- “እኔ የመሰለኝ ዝም ብሎ ስብከት ልማር የመጣሁ ነበር የመሰለኝ ፥ ግን አሁን እዚህ ከመጣሁ የተማርኩት የሕይወት ፍልስፍናን ነው። በዚያ የሕይወት ፍልስፍና ከባድ ቢሆንም ለመኖር እያተገልኩ ነው “

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

20 አስተያየቶች

  1. ቀሲስ አዲስ ርዕስ ያልተሰማ ጉዳይ እያመጡ ስለሚያስተምሩን እናመሰግናለን🙏ከዚህ በላይ ቤ/ክንን የሚያገለግሉበት ፀጋ ይስጥልን

  2. ለቀሲስ ቃለ ህይወት ያሰማልን። ትምህርቱ በጣም አስተማሪ እና ራሴን እንዳይ አድርጎኛል።

  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን በእድሜና በፀጋ ይጠብቅልን አሜን

  4. የስራ ሰዓቴ ጠዋት 3- ምሽት 4 ስለነበር ሰለቸኝ። እርግጠኛ የሆንኩት በእሱ ብቻ ነው። መሰላቸቴን። ስለዚህ ሌላ ስራ እየሰራሁ ልማር ብዬ ከለቀኩ አንድ ወር አለፈኝ። በመልቀቄ አልጸጸትም ከለቀኩ በኋላ ያልኩትን አንዱንም አለማረጌ ግን የለቀኩት ምን እንደፈለኩ በደንብ ሳላጤን ነበር ያሰኘኛል።

    ቃለ ህይወት ያሰማልን አባታችን። እኛም በተማርነው ፍሬ እንድናፈራ ይርዳን። አሜን።

  5. ቃለ ህይወት ያሰማልን በድሜ በጸጋ ይጠብቅልን መምህር
    ለኔ ቀጥታ የተነገረኝ ነው የመሰለኝ ።

  6. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህር። በነገራችን ላይ በመምራችን የተጻፈውን “ፍና ቅዱስን” መጽሐፍን እያነበብኩት ነው እና በጣም ሕይወት የሆነ መጽሐፍ ስለሆነ ያላነበባችሁት እንድታነቡት እመክራለው

  7. [url=https://samoylovaoxana.ru/v-sochi-zaderjan-peterbyrjec-streliavshii-iz-vnedorojnika/]В Сочи задержан петербуржец, стрелявший из внедорожника[/url] или [url=https://samoylovaoxana.ru/izrailskii-myzei-iskysstvovedeniia/]Израильский музей искусствоведения[/url]

    [url=https://samoylovaoxana.ru/tag/podvodnyj-gorod/]подводный город[/url]

    https://samoylovaoxana.ru/tag/pokorenie-elbrusa/

    Ещё можно узнать: [url=http://yourdesires.ru/vse-obo-vsem/1705-kto-izobrel-spichki.html]в каком году изобрели спички[/url]

    Семейный отдых

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *