የጽሙና ጊዜ አለህ?

በጸሎት ጊዜ ሐሳቡ እየተበተነበት የተቸገር አንድ ደቀ መዝሙር ወደ አረጋዊ አባት ሄዶ ስለሆነው ነገር ይነግራቸዋል። እኛም አረጋዊ ልጁን በምሳሌ ሊያስተምሩት ስለ ፈለጉ ከፊቱ ውኃ አመጡ። ከዚያም በውኃው ላይ ጠጠር በመወርወር ልክ የሚርገበገብ ሞገድ ሲፈጠር ያን ደቀ መዝሙር ፊቱን በውኃው ውስጥ እንዲያይ ጠየቁት። ተማሪውም በውኃው ውስጥ ጥላ የሚመስል ነገር እንጂ መልኩን ማየት እንዳልቻለ ነገራቸው። ቀጥለውም አረጋዊው ውኃው እስኪረጋጋ ጠብቀው “አሁንም መልሰህ ተመልከት?” አሉት። አየ፤ “አሁን ልክ እንደ መስታወት ውኃው ፊቴን እያሳየኝ ነው” አላቸው። አረጋዊውም “ልጄ ሆይ፣ አንተም እንዲሁ ሂድና ራስህን አረጋጋ። ያን ጊዜ በጸሎትህ ውስጥ መጽናናትን ታገኛለህ” አሉት። (Paradise of the holy fathers) 

የቆርቆሮና የብረት ጩኸት ጋጋታ ባለበት ውብና ለስላሳ የሆነውን የዋሽንት ድምጽ መስማት የሚቻለው ማን ነው? ሁከትና ረብሻ በሚነግስበት፣ የማይቋረጥ ግፊያና አለመረጋጋት ባለበት የሰዎች ግርግር ውስጥ ሆነህ እንዴት የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ ልትሰማ ትችላለህ? የእግዚአብሔርን ድምጽ በአውሎ ነፋስ ፋጨት፣ በምድር መናወጥ፣ በሚያስገመግም የእሳት ድምጽ ውስጥ አታገኘውም። እርሱ የሚናገረው ከእነዚህ ሁሉ በኋላ በሚሆነው “ትንሽ የዝምታ” ጊዜ ነው።(1ኛ ነገ 19፥12) 

ልክ የመድኃታችንን የልብሱን ጫፍ በስውር ነክታ ከቁስሏ እንደ ተፈወሰችው ሴት፣ አንተም የነፍስህን ቁስል ለማድረቅ በመቅደሱ የሞላውን የጌታን የልብሱን ዘርፍ በምሥጢር የምትዳስስበት የብቻ ጊዜ ያስፈልግሃል?  

ከእሾህ ወይን ከኩርንችትም በለስ እንደማትለቅም፣ ራስህን ከዚህ ዓለም ሁከት የምትለይበት ጊዜ ሳይኖርህ እውነተኛ የነፍስ መጽናናትን ልታገኝ አትችልም። ለዚህም ነው ጌታችን በወንጌል “ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ፤ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ” በማለት ያስተማረን። ላዘነችው ነፍስህ መጽናናትን፣ ለልቡናህ ዕረፍትን ትፈልጋለህ? ስለ ኃጢአትህ የምታፈሰው የንስሐን እንባስ ትሻለህ?  እንግዲያውስ ከሰው ርቀህ በርረህ ወደ ፈጣሪ የምትሄድበት የጽሙና ጊዜ ይኑርህ። 

የእስራኤል ልጆች የመላእክትን እንጀራ የተመገቡት ቆነጃጅቱ በሚዘፍኑበት እና ለጣዖት የሚቀርብ ዳንኪራ በነገሠበት ግብጽ አይደለም። ሰማያዊውን መና ያገኙት ግብጽን ጥለው ከወጡ በኋላ በበረሃ ሳሉ ነው። አብርሃም ታላቅ ሕዝብ የሚሆንበትን ጽኑዕ ቃልኪዳን የተቀበለው ያደገበትን አገር እና የአባቱን ቤት ጥሎ በመውጣቱ ነው። አንተስ እንደ እስራኤል ልጆች መላእክት እንዲመግቡህ፣ እንደ አባታችን አብርሃምስ ታላቅ ሕዝብ መሆን ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ዛሬውኑ ከግብጽ የምትሸሽበትን ዕቅድ ያዝ። የአባትህን ቤት ትተህ ለጥቂት ጊዜ ፈቀቅ የምትልበትንም ገዳም አስስ። 

ጌታን ያጠመቀውና ለብዙዎች በብርሃኑ ደስ የሚያሰኝ “የሚነድ መብራት” የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ ሁሉ በፊት ብቻውን ከአምላኩ ጋር በበረሃ ነበር። የሐዲስ ኪዳኑ ባለ ራእይ ቅዱስ ዮሐንስ እነዚያን ሁሉ ሰማያዊ ምሥጢራት የተመለከተው ብቻውን በፍጥሞ ደሴት ሆኖ ነው። ስሙን በአሕዛብ፣ በነገሥታቱና በእስራኤል ልጆች ሁሉ ፊት ይሸከም ዘንድ የተመረጠው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ከሁሉ አስቀድሞ ግን የመረጠው አምላኩ መንፈሳዊውን ኃይል ያስታጥቀው ዘንድ የገዛ ድክመቶቹን ተሸክሞ ብቻውን ወደ አረብ በረሃ ገስግሶ ነበር። 

ያንተስ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በመንፈስ የምትጎለምስበት በረሃህ ፣ እንደ ወንጌላዊው ዮሐንስ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን የምትዘከርበት ፍጥሞ ደሴትህ፣ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ በነፍስ ታድሰህ የምትወጣበት አረባዊ ገዳምህ  የት ነው? መቼ መቼስ ወደዚያ ትወርዳለህ?

Share your love

45 አስተያየቶች

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር እውነት ነው ::ሰው ለራሱ የጥሞና ጊዜ ያስፈልገዋል እራሱንም ፈልጎ ለማግኘት ይረዳዋል

  2. 🥺🥺 ሁሌም ወደምትናፈቀን ወዳዛች ቅድስት አርምሞ ይመልሰን……ቃለህይወትን ያሰማልኝ🙏

  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን።በእግዚአብሄር አምነን እስከ መጨረሻዎ ህቅታ ድረስ የምንታመን ያድርገን።

  4. እፁብ ነው የማናያቸውና የማናስባቸውን ነገሮች እንድናስብ እየረዳችሁን ነው። መድሃኔ ዓለም በመንግስቱ ያስባችሁ።

  5. ቃለ ህይወት ያሰማልን::
    እያሰብኩት ያለ ርዕሰ ጉዳይ ነው የተፃፈው
    ፈጣሪ ከዚህች ግርግር አለም ይልቅ ስላም እና እርጋታ ወደሰፈነበት ቤቱ ይሰብስበን!

  6. ቃለ ህይወት ያሰማልን፤ በእድሜ በጸጋ በቤቱ ያኑርልን።
    በተማርኩት እንድኖር አምላክ እስራኤል ይርዳኝ። አሜን።

  7. እግዚያብሄር ጥበብ፣ ማስተዋልን፣ እና መረጋጋትን ያድለን። ቃለ ህይወት ያሰማልን

  8. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን; በዕድሜ በጤና በቤተክርስቲያናችን ይጠብቅልን ያኑርልን

  9. ቃለህይወትን ያሰማልን እናመሠግናለን:: Enezi menfesawi tshufoch betam girum nefsn yemiyadsu menfesaw ke rasachn endntarek yemiyaregu nachew::So, jandereba generation can you please change those journals into a voice and post it in a youtube So that people can Listen these God’s word when he/she is not in a comfort zone to read. Please Try to think about this Thanks God bless you all.

  10. ይህን በነፍስ ታድሰን የምንወጣበት የጥሞና ገዳም እንድናገኝ ወደዚያም ወርደን እንድንጠቀምበት እግዚአብሔር ይርዳን!!!

  11. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህራችን በጣም የሚገርም ሀሳብ ነው ፀሎት በመፅሀፍት ከማንበባችን በፊት በአምላካችን ፊት ቆመን ሀሳባችንን መሰብሰብ እንድንችል መፀለይ አለብን ሀሳባችንን የሚሰርቁን የምናያቸው የምንሰማቸው ብቻ ሳይሆኑ ውስጣችን ጭምር ይረብሸናል ፈጣሪ መንፈስ ቅዱሱን ልኮ ልቦናችንን ህሊናችንን ይሰብስብልን።

  12. በጣም ጥሩ ዕይታ ና ምልከታ ነው ። በርታ ወንድሜ ። ቃለ ሕይወት ያሰማልን ።

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *