ከእርጋታውና እኔንም እንደ አዋቂ ከመቁጠሩ ሳይወጣ “ስለ ቀደሙት ሰዎች ሕይወት ሁሉን የመስማት ዕድል አግኝተሃል? የኖረውንስ ልማድ እንዳለ የመቀበል ግዴታ ተጥሎብሃል? አንተን ፈጣሪ ሲፈጥርህ መልክህ፣ አሻራህ፣ ድምፅህ ከአንተ በፊት የነበሩትን አይመስልም። ከአንተም በኋላ አንተን የሚመስል አይመጣም። ሌሎችን በማይመስል መልክህ መኖር ካልተቸገርህ ሌሎችን በማይመስል ማንነት መኖር ለምን አትችልም? ሁሉ የኖረውና የሚኖረው የራሴ ለሚላቸው ብቻ እየሰጠ ቢሆንም አንተ ለምን ለሁሉ በመስጠት ተለይተህ አትገለጥም? ልዩ ሆነህ ተፈጥረህ ልዩ ነገር ማድረግን ለምን እንደማይቻል ትቆጥራለህ? ልዩ ሆኖ ከመፈጠርና ልዩ ሆኖ ከመኖር የቱ ይከብዳል?” ሲለኝ ዓይኖቹ ሀሳቤን ቀድመው የሚያነቡ ይመስል ነበር።

ሀሳቡን ለመመርመር ሞከርሁ። ግን ሀሳቡ የሚመረምር እንጂ የሚመረመር አልነበረም፡፡ በሀሳቡ ያለኝን አክብሮት በዝምታዬ ገልጬ አንዱን የሥጦታ ዕቃ አነሳሁ። ልዩ ኅብር ያለው የከበረ ነገር ነው። በሕይወቴ እንዲህ ያለ የሚያምር ነገር አይቼ አላውቅም። በአንገት የሚጠለቅ ልዩ ሀብል፡፡

“ይህን መውሰድ እፈልጋለሁ” አልሁት። እርሱም “ከመግዛትህ በፊት ምን መሆኑን ማወቅ ይኖርብሃል” ሲል ጠንከር ብሎ መለሰልኝ። “የአንገት ሀብል መሆኑ ይታየኛል። ከዚያ የተለየ ምን አለው?” ስል የማየውን ሊያብራራልኝ ከሞከረ ሊሰማኝ የሚችለው ንዴት ከወዲሁ እየተሰማኝ ጠየቅሁት።

“ይህ ሀብል እንደምታየው መሀሉ ላይ ቀይ የከበረ ፈርጥ አለው። ይህ ፈርጥ ‘ፍቅር’ ይባላል። በአንገት ዙሪያ የሚሆነው ሀብል ደግሞ ‘ራስን መካድ’ ከተባለ የከበረ ማዕድን የተሠራ ነው። ይህን ከገዛህ የምታጠልቀው ለራስህ ነው። ሀብሉ ሰውነትህን ከነካበት ቅፅበት ጀምሮ ለሌሎች እንጂ ለራስህ አትኖርም፤ የራስህን አትፈልግም፤ መሠጠትህም ለሁሉ ይሆናል። ብዙ ነገሮች ትርጉማቸው ይቀየርብሃል። ትሰጣለህ እንጂ አትፈልግም፤ ለሌሎች ስለመሙላት እንጂ ስለ ጎደለብህ ነገር አታስብም፤ በጥንካሬያቸው ከመጠቀም ይልቅ ድክመታቸውን

ታግዛለህ፤ ከስኬታቸው ይልቅ በውድቀታቸው ወራት ልትደግፋቸው ትገኛለህ። ስለ ሌሎች ስትል ደስታህን ለኀዘን፤ ጌትነትህን ለባርነት፤ ደም ግባትህን ለጥፋት፤ ክብርህን ለውርደት ትሰጣለህ። እኔ ባይነት በሚፈጥረው ልዩነት ውስጥ ራስህን አታገኘውም። እኔ ባይነትህን ታጣዋለህ አንተነትህ ግን አይጠፋም። ከገባህ አትወጣም፤ ከጀመርህ አትቆምምና አስበህ ወስን!!!” አለኝ።

ንግግሩን ሲያጠቃልል ሀብሉን የያዘው እጄ ሲዝል ተሰማኝ። የተቀበልሁት ማንነቴ ሲቀየር፤ የለመድሁት ጥቅም ሲቀር፤ የምሳሳለት ክብር ሲሻር ታወቀኝ። ታዲያ ምን ቀረኝ? ብዬ አሰብሁ።

“እስከ ዛሬ ከብዙ ሰው ጋራ በፍቅር ኖሬያለሁ። አንተ ስለ ፍቅር የምትነግረኝና የለመድነው የምናውቀው ፍቅር አንድ አይደለም። ፍላጎቴ፣ ጥቅሜ፣ ክብሬና ማንነቴ ተቀባይነት የማያገኝና የማይከበርልኝ ከሆነ ምኑን ፍቅር ሆነ? መፈቀሬንና ማፍቀሬንስ በምን አውቃለሁ?” ስል የማይመስል ነገር በሚል ንቀት ተናገርሁ።

“ማፍቀርህን ለሌሎች በመኖርህ ታውቀዋለህ። ለእነርሱ ስትል በምትከፍለው መሥዋዕትነት ትገልጠዋለህ። የምትከፍለው መሥዋዕትነት ፍቅርህንም ሊያካትት ይችላል። ስለ መፈቀር ግን ለምን ታስባለህ?”

“መፈቀሩን ማወቅ የሁሉ ደስታ ስለሆነ ይመስለኛል ” ስለ በጥርጥር መለሰሁ።

እርሱም “ደስታህን አንተ ለሌሎች በሚሰማህና በምታደርገው ላይ ከማፅናት ይልቅ ለምን ሌሎች ስለ አንተ በሚሰማቸውና በሚያደርጉልህ

ላይ ትመሠርታለህ?” ሙግቱ ጠነከረብኝ።

“እንዲህ ማሰብና መኖር ለማን ይቻለዋል? እንዲህ ሆኖ የኖረ ዓለም ከተፈጠረ እስከ ዛሬ አልተሰማም” በማለት አገነገንሁ።

“ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በምድር ፊት ተበትነው የኖሩ የሰው ልጆችን ታሪክ ሁሉ የመስማት ዕድሉ ነበረህ? በእያንዳንዱ ጎጆ ማን እንዴት እንደኖረ ምን ያህል ታውቃለህ? አንድ ሰው አልተነገረለትም ማለት ታሪክ የለውም ማለት አይደለም። በተጨማሪም ደጋግመህ የምታነሣው ስለ አለመቻል ነው፡፡ ያንተን መቻልና አለመቻል በሌሎች አቅም ለምን ትለካለህ? ቀድመህ ከተሸነፍህስ መቻልህን እንዴት ታውቃለህ? ሰዎች ሆነው ለሰው አይቻለውም የሚባልን የፈጸሙ እንዳሉ አልሰማህምን?” አለኝ በኀዘኔታ።

“ግን ‘ኮ ፍቅር የሚባለው ከሁለቱም ወገን ሲሆን ነው። ከአንዱ ብቻ ሲሆን ላፍቃሪውም ለተፈቃሪውም ምቾት ይነሳል” አልኩኝ አለማወቄን ወደ መቀበል ከፍታ እየወጣሁ።

“በዚህ ዓለም ከተፈጸሙ ታላላቅ ስህተቶች አንዱና ዋናው ነገሮችን ከመሠረታዊ ባህርያቸው ፈፅሞ የማይገናኝ ትርጉም መሥጠት ነው። የዚህ ዋና ተጠቂ ከሆኑት መካከል የመጀመሪያው ፍቅር መሆኑ በብዙዎች ንግግር ይታያል። አንተ ፍቅር ብለህ የጠራኸው በእኔ ባይነት (Ego) መታወርንና ሌሎችን የፍላጎታችን አገልጋዮች ለማድረግ ጭምብል ማጥለቅን ነው። በዚህም ራስህን በሌሎች ለመመለክ ጣዖት አድርገህ ታቀርባለህ። 

በውዳሴያቸው፣ በሸንፈታቸው፣ ራሳቸውን ፍጹም ለአንተ በማስገዛታቸው ሐሴት ታደርጋለህ። ያ ጎድሏል ብለህ ስታሰብ ማንነትህን ትቀይራለህ። የፍቅርን መሠረታዊ ባሕርይ ከተረዱ ሰዎች አንዱ እንዲህ ገልጾታል ‘. . . ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፤ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፤ የራሱን አይፈልግም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቆጥርም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፤ ሁሉን ያምናል፤ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፤ በሁሉ ይጸናል . . .።’ ለመሆኑ አንተ ፍቅር ብለህ የጠራኸው ከእነዚህ የቱን ይዟል? ወዳጄ የምታፈቅረው ከመፈለግህ በፊት ፍቅርን ፈልገው። ፍቅርን ማግኘት ከቻልህ የምታፈቅረው አታጣም!”

“አንተ የተከበርህ ሰው የምትነግረኝ ነገር ለመቀበልና ለመኖር ከባድ ቢሆንም ለሕይወት ብርሃን የሚሆን እውነት መሆኑን ማስተባበል ግን አይቻልም” ስል ተናዘዝሁ።

“ከፈጣሪ የተሰጡንን ጸጋዎች ባህርያቸው ሳይበረዝ መቀበል ካለመቻል በላይ ርግማን የለም። ሰው ፈጣሪ የሰጠው ቀላል ሸክም ከብዶት ራሱ የፈጠረውን ከባድ ሸክም ተሸክሞ የሚኖር ምስኪን ነው። ደግሞም የሕይወት ብርሃን የሆነውን እውነት መረዳትና መኖር ቀላል ሕይወትን በሚመርጡ ሰዎች ዘንድ አይታወቅም። ሕይወትን መኖር ማለት የህልወና አለመቋረጥ አይደለም፡፡ ልባቸው ደም መርጨት ሳያቆም የሞቱ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ማወቅ ከአስተዋዮች አይሠወርም።”

“አንተ ታላቅ ሰው ከአንተ ይህን ድንቅ እውነት የሰሙ ጀሮዎቼ ቡሩካን ናቸው፡፡ ግን በዚህ ዓለም ከላይ የገለፅህልኝን ሕይወት የኖራት አንድ ሰው ስንኳ መኖሩን እጠራጠራለሁ። በርግጥ ይህቺን ሕይወት የኖራት አንድ ሰው ልጠቅስልኝ ትችላለህ?”

“ሁልጊዜ ተከታይ የመሆን ሕይወትን ለምን ትመርጣለህ? የምታስበው ሀሳብ፤ የምትኖረው ሕይወት ትክክል ለመሆኑ ቀድሞ የነበረ መሆኑን ማስረጃ ለማቅረብ ለምን ትጥራለህ? አንተ ከተከታይነት መንፈስ ተላቀህ የአንድ ነገር ጀማሪ ለመሆን ለምን ትፈራለህ?

ለማንኛውም በዘመን አድማስ ልዩ ነገርን የገለጡ አብሪ ኮከቦችን አልፌ አልፌ ልጠቅስልህ ብችልም የሰው ልጅን አጠቃላይ ታሪክ ከላይ ባብራራሁልህ ሁኔታ ተገልጦ የቀየረ ግን አንድ ብቻ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ እርሱ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ከዘመናት በፊት የወሰናትን ሕይወት ገለጣት፤ ሕያው ሆኖም ይኖራል።” ሲል የቃሉ ኃይል ነፍሴን ናጣት።

“አንተ የተወደድህ ሰው እባክህ ንገረኝ እርሱ ማነው? ካገኘሁት ይህቺን ሕይወት አገኝ ዘንድ ያለኝን ሁሉ ራሴንም ጭምር ስንኳ ቢሆን እተዋለሁ። እባክህ ንገረኝ እርሱ ማነው?” ስለ ማለድሁት።

እርሱም ዓይኖቼን በፍቅር እያየ መለሰልኝ “የምናገርህ እኔ እርሱ ነኝ!”

ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው::  ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist)  ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::

https://www.youtube.com/@EpiphaniaTube

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

5 አስተያየቶች

  1. እንዳላነብ የሚከለክልኝ ምንድን ነው?
    አምላከ እስር ኤል ልዑል እግዚአብሔር ለቀሲስ ታምራት ጸጋውን ያብዛልውዎች፣ለጃን ሚዲያ ብርታቱን ይስጣችሁ!
    የቀሲስ መጽሐፍ ካላቸው ጠቁሙን!

  2. እጅግ በጣም ድንቅ ጽሁፍ ነው፣ “የምናገርህ እኔ እርሱ ነኝ!”
    እድሜ ይስጥልን አባታችን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *