በጃንደረባው ሠረገላ ላይ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ያደረጉት ቆይታ ክፍል አንድን በዕለተ ቅዳሜ አስነብበን ነበር:: ዘለግ ያለውን ክፍል ሁለት የመጨረሻ ክፍል ውይይት እነሆ:-
ጃንደረባው :- በሥነ ጽሑፍ ተማሪነትህ ወቅት የተረዳኸውና ለቀሪ የጸሐፊነት ዘመንህ ቅርጽ አስይዞኛል የምትለው የምታስታውሳቸው ነገሮች ምንምን ናቸው?
ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- እኔ ወደ ሥነ ጽሑፍ የመጣሁት ከፊዚክስ ትምህርት እና ከሥራ ዓለም ስለነበር ፍልስፍናውን ተጠምቼ ነው የተማርሁት ማለት እችላለሁ። በእኔ ግንዛቤ ሥነ ጽሑፍ ያልገባቸው ጥቂት የሥነ ጽሑፍ መምህራንም ገጥመውኝ ትቼ ለመውጣት ሁሉ ተፈታትኖኝ ነበር። እንዲህ ያለው ችግር በሁሉም የትምህርት ዘርፍ ሊያጋጥም የሚችል ቢሆንም ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ስለ ዕድል ተጠይቆ በአንድ መጽሔት ላይ እንደመለሰው እድል ይሁን አድሎ አላውቅም እንጂ እዛ ያሰቀራቸው ባላውቅም አንዳንድ አስተማሪዎች ትምህርቱን እንዳቋርጥ የተፈታተኑኝ መሆኑን መርሳት አልችልም። ሆኖም ከብዙ ጥሩ መምህራን ደግሞ ብዙ ቁም ነገሮችን አግኝቼበታለሁ። ለአንተ ጥያቄ ግን አራት ነገሮች ላይ በአጭሩ ብናገር በቂ ሊሆን ይችላል።
የመጀመሪያው የሥነ ጽሑፍን ፍልስፍና ላይ ግንዛቤ መያዝ ራሱ ትልቅ ነገር ነው። ሰዎች መጻሕፍትን ወይም ሌሎች ጽሑፎችን ዝም ብለው በማንበብ ብቻ የነገሮችን ምንነት በአግባቡ እንደማይረዱ በደንብ አውቄበታለሁ። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እጅግ በርካታ ነገር ይታተማል። አነበብን ብለው የሚነግሩኝንም ሆነ የሚጠይቁኝን ሰዎች ስሰማ ደግሞ ያለው ችግር ቁልጭ ብሎ ይታየኛል። ለምሳሌ የሚት ልቦለድ መጻሕፍትን የታሪክ መጻሕፍት አድርጎ የሚከራከር፣ የሚመርቅ የሚረግምም ሰው ሞልቷል። እንዲያውም አሁን የሚት መጻሕፍት ገበያ የደራበት ዘመን ስለሆነ ብዙ ዝባዝንኬ እየታተመ ገበያውን እየመራው ነው ማለት ይቻላል። ገበያው አሳስቦኝ ሳይሆን ሰው አሳዝኖኝ ነው የማነሣው። እንዲያውም አንዳንዶች ከኢንተርኔት የለቃቀሙትን የሚያስፈራ የኮንሳፓይራሲ እና መሰል ድሪቶ አሳትመው ብዙዉን ሕዝብ ባያነብ ሊኖረው ከሚችለው ጤነኛ አእምሮ በታች ሁሉ ሳያወርዱት አልቀሩም። በታሪክ እና በሌሎች ሥራዎች ጨምረህ ከደካማ ፖለቲከኞቻችን ማጣመም ጋር ስታየው ችግራችን ሁሉ መብቀያው ይህ ብቻ እስኪመስል ድረስ ያስፈራሃል። ለእኔ እንደሚገባኝ ይህ የሥነ ጽሑፍ ሀ ሁን ካለመገንዘብ የሚመጣ ችግር ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ስለንባብ ምንነት ራሱ መገንዘብ በጣም አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነገር ይመስለኛል።
በተለይም ስለነቂስ ንባብ ስታውቅ ብዙ ጠንካራ ሥራዎችን በማንብበ ብዙ ምሥጢራትን፣ ፍካሬያትን ለማወቅ በር ይከፍታል። ንባብ ክህሎት መሆኑን ከማውቅ ጀምሮ እንደማንኛውም ክህሎት ስትለምደው ቢያስቸግርም በኋላ ግን በቀላሉ የሚመለስ መሆኑ ራሱ ትልቅ ጠቃሚ ነገር ስለሆነ ለሕይወት ብዙ ይጠቅማል። ስለንባብ ታውቃለህ ማለት ስለመጻሕፍትም ታውቃለህ ማለት ነው። ልክ ሐኪም በሽተኛን በማየት በሽታውን እንደሚገምተው ትንሽ ጠያይቆ ደግሞ ግምቱን እያጠናከረ ሂዶ እንደሚያውቀው የንባብን ሁኔታ አውቆ ወደማንበብ የሔደም ሰው እንዲሁ ይመስለኛል። ምርቱን ከገለባ ለመለየት አይቸገርም። የንባብ ክህሎት እና የንባብ መንገዶችን ማወቅ ሰፊ ጥቅም ያለው ነው።
ሦስተኛ ራሱ ስለ ጽሑፍ ወይም ስለመጻፍ እና ስለ አጻጻፍ መንገዶች ማወቅ ነው። ይህም እጅግ መሠረታዊ ነገር ነው። በነገራችን ላይ ሞያዊ ነገሮችን በጽሑፍ የማቅረብ ችሎታን ለማዳበር በየመስኩ ባሉ ሥነ ዘዴዎች የሚሰጠው እንደተጠበቀ ሆኖ ይህኛው ግን ለሁሉም የሚያስፈልግ መሠረታዊ ነገር ይመስለኛል። ጽሑፍ በራሱ የተለየ (Sacred) ነገር ነው። እንጀራ ለመብላት የሚጻፍ ተራ ነገርም አይደለም። ለብዙዎች እንደሚመስለው አንድ ነገር ሞንጨር ምንጨር አድርገህ ገቢ የሚታቀድበት ተራ ሸቀጥ አይደለም። ጽሑፍ እጅግ የተከበረ ነገር ነው። በእውነቱ ይህን ማወቄ ብቻ ያስደስተኛል።
የምትጽፈው በዓላማ አንድ ለውጥ ለማምጣት ነው እንጂ ይጽፋል ተብሎ ለመደነቅም አይደለም። ጽሑፍ ተፈጥሮአዊ እና ጤናማ ሲሆን ብዙዎችን የሚፈውስ መድኃኒት ነው። ካለበለዚያ ግን የተበከለ መደኃኒት ነው ማለት ትችላልህ ። የተበከለ መድኃኒት በሽተኛውን ሊያድን አይችልም። እንዲያውም አባብሶ ሊገድለው ይችላል። ጽሑፍም ልክ እንደዚህ ነው ማለት ትችላለህ ። አሁን በእኛ ሀገር ያለውን ሁኔታ ስታየው አንዱ ችግሩ ከዚህ የተነሣ ነው። አጋነንከው ካላልከኝ የጽሑፍን ምንነት፣ ጥቅም እና ጉዳት ሳያውቁ የሚጽፉ ሰዎች ማለት ኒውክለር የታጠቁ አሸባሪዎች ማለት ናቸው። በእኛ ሀገር ሁኔታ ደግሞ ይህ ሆኗል ማለት የሚቻል ይመስለኛል። በሃይማኖቱም፣ በታሪኩም፣ በፍልስፍናውም፣ በሌላውም እንዲህ ያለ ችግር ውስጥ እንዳለን ይመስለኛል።
ዐራተኛው እና ለአሁኑ ውይይታችን የመጨረሻው ደግሞ ስለ ትርጉም (Translations) ያገኘሁት ግንዛቤ ነው። እንደምታውቀው በተለይ የእኛ ቤተ ክርስቲያን አብዛኛው እንዲያውም በጣም ከጥቂቶች በቀር ማለት ይቻላል መጽሐፍ ቅዱሳችን ጨምሮ መጻሕፍቶቻችን የተተረጎሙ ናቸው። እኛ ሀገር የተደረሱ እና የተዘጋጁ ወጥ ሥራዎች ብዙ ናቸው ማለት አይቻልም። ቅድሚያውን የሚወስዱት የምሥጋና ሠራዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ። ከቅዱስ ያሬድ እና ከአባ ጊዮርጊስ ሥራዎች ጋር ሌሎችም ቀላል የማይባሉ የምሥጋና ሥራዎች አሉን።
በተለይም ቅኔ እና አቋቋም ከዳበሩ በኋላ ለዚሁ ለማኅሌቱ ሲባል የመልክእ ድርሰቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በርካታ ሆነው ተዘጋጅተዋል ማለት ይቻላል። ከዚያ ወጭ አንጻራዊ ስፋት የሚኖራቸው የገድላት እና የድርሳናት መጻሕፍት ናቸው። በዚህ ዘርፍም ብዙ የትርጉም ሥራዎች ቢኖሩም እነዚያን ተከትለው ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ወጥ ሥራዎችም አሉን። እንደ ሦስተኛ የምወስዳቸው በቁጥር አናሳ ቢሆኑም የዕቅበተ እምነት ሥራዎችም አሉን። ከዚህ ውጭ ያለው ግን በሙሉ የትርጉም ሥራ ነው።
ከዚህ አንጻር ቀደም ብዬ ስለፊሎሎጂ ጥቅም ስናገር እንዳነሣሁትም ከዚህ ጋር የተያያዙ እንደ የትኛውም ሀገር እና ቤተ ክርስቲያን የራሳችን ችግሮች አሉብን። ሌላው ቀርቶ የሥነ ጽሑፋችን መንገድ ቢጠና የሚጀምረው ከትርጉም ነው። ከዚህም ሁሉ በላይ አሁን በዓለም ላይ ራሱ ትልቅ የዕውቀት እና የመረጃ ልውውጥ ያለው በትርጉም ሥራ ነው። እኛም ሀገር እንደ አቅማችን ብዙ ሥራዎችን እየተረጎምን ነው። ይህ እውነታ ፊታችን ላይ ሆኖ ስለትርጉም ምንነት፣ ዘዴዎቹ እና ከዚህ የተያያዙ ችግሮች ስለሚፈቱበት መንገድ ግንዛቤ ሳይኖረን መሥራት እንዴት ያለ ጉድለት መሰለህ ። ሌላው ቀርቶ ብዙ ሥራዎቻችን ትርጉሞች ከሆኑ ስለተርጓሚዎች ዕውቀት ልምድ እና ስለእነርሱ ታሪክ ያለን መረጃ በጣም አናሣ የሆነው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል። እንዲሁ እንደዋዛ ቀዳማዊ ምኒልክ ሲመጣ ከርሱ ጋር አብረው ስለመጡ ሌዋውያን እና ስላመጧቸው መጻሕፍት ቢነገርም ስለመተርጎማቸው ወይም አለመተርጎማቸው ግን ከግምታችን ያለፈ ተጨባጭ ማስረጃ የለንም።
በትርጓሜው ላይ እነርሱ አመጡልን ይላል እንጂ በምን እንደተቀበልናቸው አይናገርም። በኋላ ደግሞ ስለዘጠኙ ቅዱሳን እናነሳለን። ከዚያ ቀጥሎ ስሙ ጎልቶ የሚነሣው መተርጉም ሰላማ ነው። ከዚያ ውጭ የእኛ ሊቃውንት ስለነበራቸው ሚና አልፎ አልፎ በየምዕላዱ ከምናገኘው በቀር የተደራጀ ሥራ የለንም። ወደ እነዚህ ሀሳቦች ሁሉ እንደመጣ እና ለማደርጋቸው አነሥተኛ ነገሮችም ትልቅ ግንዛቤ ፈጥሮልኛል የምለው ስለትርጉም እና ሰለሙያዊ ጉዳዮቹ በሥነ ጽሑፍ ትምህርቴ ወቅት ከወሰድኳቸው ኮርሶች ስለሆነ እነዚህን መዝለል ያለብኝ አልመሰለኝም። በዚሁ አጋጣሚ የሥነ ትርጉም መምህሬ የነበረውን እና በአሁኑ ጊዜ ካናዳ ኦታዋ የሚገኘውን መምህሬን ገዛኸኝ ጌታቸውን ማመስገን እፈልጋለሁ።
ጃንደረባው:- ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍትን ለሚጽፉ ሰዎች ቢከተሉት ብለህ የምትመክረው ፍልስፍና ምንድን ነው? ለመጪው ዘመን ምን ምን ዓይነት መጻሕፍት ቢጻፉ ይጠቅማሉ ትላለህ?
ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- በእኔ እምነት ምንም ሊታለፉ የማይችሉ የምላቸው አራት ነገሮችን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል። የምትጽፈበትን ጉዳይ፣ የምትጽፍለትን አካል፣ መሠራታዊ የሥነ ጽሑፍ ክህሎትን፣ እና መሠረታዊ ኦርቶዶክሳዊውን የሥነ ጽሑፍ መንገድ ማወቅ የግድ ይመስለኛል። በእኔ ግምገማ እራሴ የሠራኋቸውን ሥራዎች ጨምሮ ወደ ኋላ ሒጀ ስመለከት እንዚህ በጉልህ ጎድለው ይታዩኛል።
የምንጽፈበትን ጉዳይ ማወቅ የሚለውን ሳነሣ ይህን ሳያውቅ ማን ይጽፋል የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። እውነቱን ለመናገር ግን እንዲያውም መሠረታዊ ችግራችን ይህ ይመስለኛል። እንዲያውም ለስሟ መጥሪያ ቁና ሰፋች ዓይነት የሚጽፈውን ትቼ ነው። እንደዚያ ያለውን ጻፈ ሳይሆን ሸቀጠ ብንለው ይሻላልና። ደግሞም ብዙ ሸቃጮች ሞልተውናል። ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ጽሑፍ የሚወለደው በአንድ ጉዳይ ላይ ሰዎች ተገቢ ዕውቀት እያዳበሩ ሲመጡ በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ ውሱንነቶች፣ ጉድለቶች፣ ስሕተቶች ወይም ደግሞ አዳዲስ ተጨማሪ ጉዳዮች እንዳሏቸው ይሰማቸዋል። ያን ጊዜ ያን ማካፈል ግዴታ ይሆንባቸዋል፤ ወይም ደግሞ እራሱ ጉዳዩ ፈንቅሏቸው ሊወጣ ያስቸግራቸዋል። በመማር ፣ በማስተማር እና በመመራመር የሚኖሩ ሰዎች የሚጽፉትም በዚሁ መንገድ ነው።
በዚህ ምክንያት እውነተኛ ጸሐፊዎች ብዙ መጻሕፍትም አይኖሯቸውም። ወይ በመንፈስ ቅዱስ አዲስ ድርሰት የሚሰጣቸው ወይም በፍልስፍና በነገሮች ሁሉ ላይ ያልተቋረጠ ጥያቄ እያነሡ ያንን በመመለስ አዲስ ነገር አለን የሚሉ ፈላስፎች ካልሆኑ በቀር አዋቂዎች በጥንቃቄም ስለሚያዘጋጁ ብዙ መጻሕፍት አይኖሯቸውም። የማይኖሯቸውም ስለአንድ ጉዳይ ሊኖር የሚገባውን ተገቢ ዕውቀት ምን እንደሆነ ወደ ማወቅ ስለሚደርሱ ለጉዳዩ ባለቤትነት ላላቸው ሰዎች ሁሉ ቅድሚያ ስለሚሰጡ ያንን ይጠብቃሉ እንጂ ብድግ እያሉ ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም በሚል አባባል ራሳቸውን አያጽናኑም። ስለዚህ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
በእኛ ቤት ያሉ መጻሕፍትም የዚህ ውሱንነት አለባቸው ስል ዝም ብዬ አይደለም። ሌላው ቀርቶ በዘመናችን ላሉ በርካታ ሃይማኖታዊ የአስተምህሮ ችግሮች ክፍተቶች የሚታዩት ሌሎች ጠንክረው ሳይሆን እኛ ከሚገባው በታች ሆነን ስለምንገኝ ነው። የዚህ ችግር ዋናው ምክንያት ደግሞ የምንጽፍበትንም ሆነ የምንናገርበትን ጉዳይ በአግባቡ ስለማናውቅ ነው ብዬ አስባለሁ።
ሁሉንም ያነሣኋቸውን በዚህ መንገድ ለማብራራት ጊዜ ሊወስድ ይችላል። የመጨረሻው ላይ ግን ትንሽ ማለት ያለብኝ ይመስለኛል። ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ጽሑፍ የምንለው በጽሑፍ የሚተላለፍን ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ መሆኑን በማስታወስ ይህን ጉዳይም በደንብ ማጤን ተገቢ ነው። ያው እንደሚታወቀው የኦርቶዶክሳዊ የአስተምህሮ መንገዶች ሊተገብሩ ከማይችሉት አሁንም ዋና ዋና የምላቸውን ማስታወስ ይኖርብኛል። የመጀመሪያው ከዘመናዊ ፍልስፍና እና ሥነ ጽሑፍ እድገት ጋር በሌላው ዓለም የገነነው ተጠየቃዊ አመክንዮ ልበለው መሰል እንግሊዝኛ Deductive reasoning የሚለው የማይሠራ መሆኑን ማስታወስ እፈልጋለሁ።
ለምን ብዙ ሰዎች ያወቁ የነቁ እየመሰላቸው በዚህ መንገድ ብዙ ስሕተቶችን ያመጣሉና። ይህንን ከዚህ ሞያ ጋር ቅርበት ለሌላቸው ሰዎች በቀላሉ ላስረዳ መሰል። ዲዳክቲቭ ሪዝኒንግ የሚባለው ከሁለት መነሻ ሀሳቦች ተነሥቶ የምንደርስበት ማጠቃለያ ነው። ለምሳሌ አበበ ሰው ነው። ሰው ሁሉ ደግሞ ሟች ነው። ስለዚህ አበበ ሟች ነው የሚል ማጠቃለያ ላይ መድረስ ዐይነት ነው ዲዳክቲብ ሪስኒንግ የሚባለው መንገድ። ታዲያ ይህ እውነት አይደለ ወይ ምን ችግር አለው የሚል ሰው እንዳይኖር ይህ ሁል ጊዜም በሃይማኖት እንዴት እንደማይሠራ ላስረዳ። በብሉይ ኪዳን ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ነበር። እመቤታችን በብሉይ ኪዳን ዘመን ተወልዳለች ። እነዚህ ዐረፍተ ነገሮች በየራሳቸው እውነት ናቸው። ሆኖም ከዚህ ተነሥተህ ግን ስለዚህ እመቤታችን ኃጢአት ነበረባት ብትል ትሳሳታለህ። ለዚህ ነው ይህ መንገድ አይሠራም የምንለው።
የዚህ ዓይነት መንገድ ፈጠራቸው ብዬ ክማስበው አንዱን ማንሣትም እችላለሁ። እመቤታችን መንፈሴ በአምላኬ በመድኃኒቴ ደስ ይላታል ብላለች ። ከዚህ ንግግር ጌታ እንዳዳናት መመስከሯን መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ከአዳናት ኃጢአት ነበረባት ማለት ነው የሚሉ ሰዎች ገጥመውኝ ያውቃሉ። እንዲህ የሚሉ ሰዎች ዲዳክቲቭ ሪስኒንግ ምን እንደሆነ ባያውቁ ከዚህ ዓለም ከተማሩት ትምህርት ተነሥተው አስተሳሰባቸው በተሠራበት የፍልስፍና መንገድ መናገራቸውንና ይህንን እንደማይጠየቅ ተፈጥሮአዊ ዕውቀት አድርገው በመውሰዳቸው የሚሳሳቱት ስሕተት ነው። ብዙ ምሳሌዎችን እና ጉዳዮችን ማንሣት ቢቻልም ነገሩን በዚህ መተው ይቻላል።
ዲዳክቲቭ ሪስኒንግ ለሃይማኖት ለምንድን ነው የማይሠራው የሚልጥ ጥያቄ ካለ መልሱ በአጭሩ በሃይማኖት የሚሠራማ ከሆነ ሃይማኖት ተራ የሰዎች ግኝት ፍልስፍና ብቻ ነው ማለት ነው። የማንቀበለው ግን ሃይማኖትን ከፍልስፍና ለማስበለጥ ባለ ተራ ፍላጎት ወይም ግብዝነትም አይደለም። ሲጀመር ሃይማኖት ከተፈጥሮ እና ከተፈጥሮአዊ ሥርዓት የሚሻገረውን መለኮታዊ ሃይል እና አሠራሩን በማመን የምትኖርበት ሕይወት ነው። ይህ ባይሆን ተአምር የሚባል ምንም ነገር ሊኖር አይችልም፣። ተአምርን ተአምር የሚያሰኘው ከተፈጥሮ ሕግ ባሻገር የሚፈጸም በመሆኑ ነውና። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ከተጻፈባቸው ምክንያቶች አንዱ እግዚአብሔር ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ የሚሠራ መሆኑን ማስተዋወቅ እና በኋላ ለመዳናችን የሚፈጽማቸው ነገሮች በተፈጥሮ ሕግ መሠረት የማይሠሩ መሆናቸውን አስቀድሞ በማሳወቅ ማዘጋጀት ነው።
ዲዳክቲቭ ሪስኒንግ የማይሠራው ለዚህ ነው። ዲዳክቲቭ ሪስኒንግን ተጠቅመው ሃይማኖታቸውን ማስተማር የጀመሩ አካላት የደረሱበትን የክፍፍል ብዛት ዓይነት እና ምስቅልቅልም በዓይናችን በግልጽ የምናየው ነው። ስለዚህ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ጸሐፊ ይህች ጉዳይ በተለይ በመሠረታዊ የሃይማኖት ዶክትሪኖች ላይ ከተገለጠው ወጥቶ ወደዚህ መንገድ ከሔደ በግልጽ የክህደት ጎዳናን እየጀመራት ነው ማለት ይቻላል።
ሁለተኛው እና ልክ እንደዚሁ አስፈላጊው ነገር መላምታዊ ወይም ግምታዊ ወይም ደግሞ የግለሰቡ መረዳት የተጫነውን አተረጓጎም (Speculative Theology) ውስጥ እንዳይገባ አሁን መጠንቀቅ ነው። ይህኛው በብዙዎች የተሻለ ይታወቃል ብዬ አስባለሁ። ሆኖም በብዙ ስብከቶቻቸን እና በብዙ መጻሕፍትም ላይ እነዚህን ችግሮች አስተውላለሁ። በነገራችን ላይ የእኛ ሊቃውንት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በጣም ጠንቃቆች እንደሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ለምሳሌ አዲስ ነገር ካሰማህ ከየት አገኘኸው ከማን ሰማኸው የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ። ይህም በግምት በልብወለድ እና በአእምሮ ሥሪት ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ በገለጸው እውነት ብቻ እንድንጓዝ ጠብቆ ኖሯል። እነዚህን ሁለቱን መጠንቀቅ ለማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ መሠረታዊ ነው ብዬ አምናለሁ።
ሦስተኛው የሀሳብ ሥርቆትን (plagiarism) የሚመለከት ጉዳይ ነው። ይህን ጉዳይ ማንም እንዲያደርገው የማይፈቀድ፤ አድርጎትም ሲገኝ ከፍተኛ ውርደት የሚያከናንብ በጣም ጸያፍ ድርጊት ነው። ኦርቶዶክሳውያን ጸሐፊዎች ይህን በተመለከተ በደንብ መገንዘብ ያለብን ነገር ያለ ይመስለኛል።
ከብዙ ትዝብቶቼ አንዱ ብዙ ጸሐፍት ፣ ሁሉንም አይደለም፣ ለሚጠቀሙባቸው ምንጮች ወይም ሃሳቡን ላመጡባቸው ጸሐፍትም ሆነ መጻሕፍት ተገቢውን ዕውቅና እየሰጡ ነው ብዬ አላምንም። አትስረቅ የሚል ሕግን የምናስተምር ሰዎች ምንም እንኳ አብዛኛው ነገር ባለማወቅ ቢሆንም በዚህ የምንወቀስ መሆን የለብንም። ስለዚህ ለምንጮቹ ተገቢውን ዕውቅና መስጠት እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች አንዱ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መጠቆም የሚያስፈልግ እንደሆነ አምናለሁ። ይህ የሚደረግባቸው ደግሞ ራሱን የቻለ ሥነ ዘዴም ስላለው ያንንም አሟልቶ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው።
አባ ገብረሃና እንዲህ ብለዋል እየተባለ እንደሚነገረው በጽሑፍ ወቅት ዮሐንስ አፈወርቅ ወይም አባ ጊዮርጊስ እንዲህ ብሏል ብሎ መጻፍ ተገቢውን ዕውቅና መስጠት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። እንዲህ ያለው አገላለጽ እንዲያውም ቅቡልነትን ለማግኘት የሚደረግ ማሳሳቻ ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል። ስለዚህ ይህን ችግር በአግባቡ ለማቃለል እንዲህ ያሉ መሠረታዊ ነገሮችን ለማወቅ የትምህርትም ሆነ የሥልጠና ዕድል ያልነበራቸው ሰዎች እንዲህ ያሉትን ሁኔታዎች ሊያሳውቅ የሚችል መሠረታዊ ሥልጠናዎችን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ብዬ አስባለሁ።
ጃንደረባው :- እንደ ሥነ ጽሑፍ ባለሙያነትህና እንደ ሃይማኖት መምህርነትህ ከብዙ ጸሐፍት ጀርባ የማማከርና የአርትዖት ሚና በመወጣት በመጻሕፍት ጥራት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለህ ይታወቃል:: በዚህ ጸሐፍትን የማርታት ሥራህ ወቅት ምን ታዘብህ?
ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- እውነቱን ለመናገር ብዙ ነገሮችን ለመታዘብ ችያለሁ። እነዚያን አሁን እዚህ ማንሣት ብዙም የሚጠቅም አይመስለኝም። ፈጽሞ ዝም ላለማለት ያህል ግን አንድ ሁለት ነገሮችን ልበል።
አንደኛው በዙ ሰው ከፍተኛ የሆነ የመጻፍ ፍላጎት እያዳበረ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ጥሩ ነገር ቢሆንም ችግሮችም አሉበት ። እንዲያው ጻፈ ለመባል ብሎ ነው ለማለት ሳይሆን ዕውቀትን የሚገልጽበት መንገድ አድርጎም ወስዶት ሊሆን ይችላል፣ ብቻ መጻሕፍትን የመጻፍን ምክንያት በአግባቡ ሳያውቀው የመጻፍ ፍላጎት ብቻውን አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል ነው ይህን የምፈራው። ሁለተኛ ደግሞ አቅሙ እና ሀሳቡ እያላቸው የሥነ ጽሑፍ የክህሎት ችሎታው ባለመኖሩ መጻፍ የሚገባቸው ሰዎችም ሳይጽፉ እንደሚያልፉም ታዝቢያለሁ። ሌሎቹ ብዙ አስፈላጊ አይመስሉኝም። ሰዎች ሲደርሱ ቢያውቋቸው ብቻ የሚጠቅሟቸው ናቸው። ቢነገሩም ጉዳት እንጂ ጥቅም አይጨምሩምና።
ጃንደረባው :- በመጽሐፍ ጀርባ ወይም መግቢያ ላይ የሚሠጡ አስተያየቶችና መቅድሞችንም ትጽፋለህ:: ይዘታቸው ምን ሊሆን ይገባል ብለህ ታምናለህ?
ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- ይህ ራሱን የቻለ ሞያዊ ነገር አለው። በእኔ እምነት ሦስት ነገሮችን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ መቅድም ማለት ከስሙ እንደምንረዳው ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባትህ በፊት ልታውቀው ወይም ልታስታውሰው የሚያስፈልግህ ነገር ነው። መቅድሙ በርግጥም ቀድሞ መገኘት ያለበት ነገር መሆን አለበት ። መግቢያም መግቢያ መሆን አለበት ። በአንዳንድ ጽሑፎች ላይ መግቢያዎችን ሳይ መግቢያ ሳይሆኑ መዝጊያ ሆነው የሚያጋጥሙበት ጊዜ አለ። ይህ እንግዲህ መግቢያ የሚባል መኖሩን እንጂ መግቢያ ራሱ ምን መሆኑን ካለማወቅ የሚመነጭ ይመስለኛል።
እንዲያውም በአንድ ወቅት አንድ ሰው “መግቢያ የሌለው ሰው መግቢያ ሊጽፍ አይገባውም” ብሎ ጽፎ አይቼ ተገርሚያለሁ። አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ነገሮች ራሱ አዋቂነት መስለዋቸው እያዳነቁ ሲያወሩ ሰምቼ ተገርሚያለሁ። እንዲህ ያለው ነገር ምን ይመስለኛል መሰለህ። በእኛ ሀገር ውስጥ እስካሁን ራቁታቸውን የሚኖሩ ሰዎችን እንደ ትልቅ ነገር ለዓለም ቱሪስቶች በኩራት ለማስተዋወቅ እንደሚደረግ ማስታወቂያ ነው የማየው።
እስኪ ተመለክት ራቁትነት እንደ ጥሩ ባህል ሲቀነቀን። ማሰልጠኑ ማልበሱ ቢቀር ማፈሩ እንዴት ይቀራል በእውነት ። ሌላው ቀርቶ ከጎብኝዎቻችን አንዳንዶቹ ከእንስሣት ብዙም ያልራቅን ለመሆናችን እንደማስረጃ ፈልገውት የሚያዩን ስለሚመስለኝ በጣም ያሳፍረኛል። ይህንንም ልክ እንደዚህ ነው የማፍርበት ለማለት ነው። ሰው መጽሐፍ ጽፌያለሁ ብሎ ተነሥቶ የሚያሳፍረውን እንኳ አለማወቁ በእጅጉ ያስገርማል። አስደናቂው ደግሞ የአድናቂው ነገር ነው። ይህ ሁሉ ያለንበትን ጌታ በወንጌል ያለውን የእውር ለእውር መመራራት ነገር የሚያስታውስ ነው። እንግዲህ ብዙዎቻችን ከታወርን ያው ጭል ጭል ይልልኛል ያለ እየመራ ወስዶ አንዱ ገደል ውስጥ መጨመሩ የማይቀር ነው። በአንዳንዶች ዘንድ እየሆነ ያለውም እንደዚህ ነው ማለት ይቻላል።
ስለዚህ መቅድሞች እና ቀዳሜ ቃሎች ስማቸውን በሚገልጽ ወደ ኋላ ያለውን ይዘት ለማንበብ በር የሚከፍቱ እንድናነበው እና ዕውቀት እንድንገበይ የሚያግዙ መሆን አለባቸው ብዬ አምናለሁ።
ሁለተኛው እና ከላይኛው ጋር የሚሔደው ደግሞ ከጉዳዩ ጋር ባልተገናኘ መዘብዘብ የለባቸውም። አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ሳያውቁ ከመጽሐፉ ጭብጥ የሚቃረኑ መሆንም የለባቸውም። አንድ ጊዜ አንድ ሰው እንዲህ ያለ የተቃረነ ነገር አድርጎ ተመልክቼ ታዝቤያለሁ። ሰውየው ደግሞ ተምሪያለሁ የሚል መሆኑ የበለጠ እንዳዝን አድርጎኛል። እንደሚመስለኝ አስተያየት መስጠቱን እንደመከበር ከመውሰዱ ባለፈ መጽሐፉንም ገረፍ ገረፍ አድርጎ እንጂ በመሠረታዊነት ይዘቱን ለመረዳት እንኳ የቻለ አይመስለኝም።
ሦስተኛው በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ሥራዎች እንዲመጡ የሚጠቁሙ እና ፍንጭዎችን የሚያሳዩ ቢሆኑ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ። ከዚህም ጋር አላማቸው የተጻፈውን ማስነበብም ጭምር ስለሆነ የይዘት ዳሰሳ በማይመስል መልኩ ጽሐፉን ማስተዋወቅ እና ባልተጋነነ መንገድ ሆኖ አንባቢውን ለንባብ ቢያነሣሱ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ።
ይህ የሚደረገው ግን እንደ አስለቃሽ ሰዎችን ሆድ በተሳሳተ መንገድ ለማነሣሣት አይደለም። እንደዚህ ከሆነ እንዲያውም ባይደረግ ይሻላል። እንዲህ የሚደረግበት መሠረታዊ ምክንያት ሌላ ከፍ ያለ አላማ ያለው ነው። መጽሐፍ ማለት ሀሳብህን እምነትህን እቋምህን ሰዎች ገዘተውልህ በዚያ ዙሪያ እንዲሰባሰቡ እና ተሳስቷል ወይም አይጠቅምም ብለህ ከምታስበው ወጥተው ይጠቅማል ወዳልክው እንዲመጡ ብለህ የምታዘጋጀው እንጂ ቅድም እንዳልኩት ምን አለ ተብሎ ለመሸቀጥ የሚደረግ አይደለም።
ስለዚህ መቅድም ወይም ቀዳሜ ቃል ጸሐፊው ያን ያሚያደርግበት እውቀቱ የሚጠቅም መሆኑን ካመነ አንባቢዎችን በተመጠነ መንገድ የሚያግባባው ያን ሀሳብ ስለሚቆምለት እና የሀሳቡን አሸናፊነት ስለሚፈልገው እንጂ ለማሻሻጥ እና ለወዳጅነት ብሎ አይደለም። የሚያሳዝነው ግን አሁን እየሆነ ካለው አብዛኛው ለሰዎቹ እንጂ ለሀሳቡ አይመስለኝም። ምክንያቱም ብዙ አስተያየት ሰጪዎች ሀሳቡን በአግባቡ ስለመረዳታቸው እንኳ የሚያጠራጥር ሁኔታ እንደገጠማቸው የሚናገሩ ሰዎች እየበረከቱ መጥተዋልና። የሚገርምህ እኔንም ለእነዚህ ለነዚህ መጻሕፍት የሰጠኸው ከአንተ የሚጠበቅ አይደለም ብለው የወቀሱኝ ሰዎችም አሉ። እንዲያውም አንድ ጊዜ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር አንድ ኮርስም የሰጠኝ ወዳጄም መምህሬም ደውሎ እንዴት አንተ አስተያየት የሰጠኸበት መጽሐፍ ግዙ ተብሎ ባነር ይለጥፍለታል አለኝ። እንደ አጋጣሚ የወጣው የምረቃው ማስታወቂያ እንጂ የሽያጭ ማስታወቂያ ባለመሆኑ ተረፍኩ።
ጃንደረባው:- ማስተዋወቅ ችግር አለው?
ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- ሀሳቡን ማስተዋወቅ ወይም በሪቪው እና በመሳሰለው ማስተዋወቅ ይችላል። እያልኩ ያለሁትም ስለዚሁ ጉዳይ ነው። መቅድምና የጀርባ ሽፋን ላይ የሚሰጥ አስተያየትም ዋና አላማው መጻሐፉን በሀሳቡ ማስተዋወቅ ነው። ከዚህ በላፈ ትልልቅ ባነር እና የመሳሰሉትን ማድረግ ግን እንደሸቀጥ ማሰተዋወቅ ስለሆነ ለመጻሕፍት በጣም ጸያፍ ነው። በሀሳቡ የማይታወቅ እና የማይሸጥ መጽሐፍ ከሆነ አንድ ችግር አለው ማለት ነው። በርግጥ በሁኑ ጊዜ መጻሕፍት እየተሸጡ ያሉት በተሳሳተ መንገድ በሸቀጥ ባህል ስለሆነ ደኅናዎቹን ማስተዋወቅም ግዴታ እስከመሆን ደርሶ ሊሆን ይችላል። ዋናው የተነሣንበት ጉዳይ መቅድምን የተመለከተ ስለሆነ በሀሳቡ ማስተዋወቅ ተገቢ ነው ፤ ይህንም ሊያደርግ ይችላል ለማለት ነው።
መቅድምን፣ ቀዳሜ ቃልን እና የሽፋን አስተያየቶችን ሁሉ እንዲሁ የሸቀጥ ማስታወቂያዎች ማስመሰል ግን ቢያንስ አዋቂዎች እንዳይገዟቸው የሚያደርግ አስነዋሪ ተግባር መሆኑን ለማስታወስ ያህል ነው። መግቢያ በሌላ ሰው ሲጻፍ ግን ጥልቅ የሆነ ሥራ ሊሆን ይችላል። በተለይም በምርምራዊ መንገድ ለተሠሩ ሥራዎች ብዙ ነገሮች የሚቀርቡበት ስለመጻፉ በቻ ሳይሆን በመስኩ ላይ ስላለ ወቅታዊ ሒደቶች እና መጽሐፉ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በምን ሒደት እንዳለፈ ብቻ ሳይሆን አንባቢው በንባብ ወቅት የሚገጠሙትን በይዘቱ ውስጥ ያሉትን ብዙ ነገሮች ሁሉ የሚያስተዋውቅ አድካሚ ሥራ ነው። ስለዚህ መግቢያ የሚያስገባ ሁኖ ወይም የነገረንን ስንገባበት እንድናገኘው ተደርጎ የተዘጋጀ መሆን አለበት ። ለምሳሌ አንድ ብዙ ቁስ ወይም ዕቃ ያለበት ቤት ገብተህ እቃዎችን ማምጣት ቢኖርብህ ቤቱን የሚያውቀው ወይም ዕቃዎቹን ያስቀመጠው ሰው የቱን የት ማግኘት እንዳለብህ ፣ እንዳይሰበሩብህ ወይም ሌላ ችግር እንዳይፈጠረብህ ምን ማድረግ እንዳለብህ አስረድቶ እንደሚልክህ ያለ ሥራን መሥራት የማይችል መግቢያን መግቢያ ነው ልትለው አትችልም። እንደዚህ ሆኖ መዘጋጀት አለበት ብዬ ነው የማምነው።
ጃንደረባው :- ከሰፊ የንባብ አድማስህ ለትውልድ የምታካፍለው የንባብ ልምድ ምክሮች (tips) ምን ምን ናቸው? ለሚያነቡ ሰዎችስ ምን ትመክራለህ?
ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- እውነቱን ለመናገር የንባብ አድማሴ ሰፊ አይደለም። ምናልባት ማንበብ ከሚወድዱት ሰዎች ልመደብ እችል ይሆናል። በርግጥም እኔ ፊልም፣ ሲኒማ፣ ኳስ፣ እና የመሳሰሉትን የማልፈልግ ሳልሆን የማላውቃቸው እና የማልወድድም ሰው ስለሆንኩ ሊሆን ይችላል ንባብን የምወድደው። ይህ መሆኑ ግን የአንባቢነት ካባን አያለብሰኝምና ለጥያቄው ተገቢው ሰው ላልሆን እችላለሁ። ይህን የምለው ከልቤ እና የእውነት ነው። ሆኖም ስለንባብ ከተረዳሁት አንዳንድ ነገሮችን ማለት እፈልጋለሁ።
የመጀመሪያው ንባብ ክህሎት መሆኑን ብዙ ሰዎች መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል። ይህም ማለት ልክ እንደ ውሃ ዋና፣ መኪና መንዳት፣ የመሳሰሉት ነው። ማለትም በማድረግ የምትለምደው እንጂ ስለንባብ በማወቅህ አንባቢ መሆን አትችልበትም። እንደዚያ ማለት ለምሳሌ የኳስ ተንታኞች ስለኳስ የሚናገሩበት እውቀት እንጂ ኳስ የሚጫወቱበት ክህሎት የላቸውም። ክህሎቱ ቢኖራቸው ኖሮ ይጫወቱ ነበር እንጂ አይተነትኑም ነበር። ምሳሌውን ያመጣሁት ክህሎትን በተግባር ተለማምደህ የምታመጣው እንጂ እንዲሁ አስፈላጊነቱን ሰምተህም ሆነ ዐውቀህ ሔደህ አንባቢ ለመሆን የሚቻል አይደለም።
ክህሎት መሆኑን ስናውቅ ግን ሁለት ነገሮችን አንረሳም። አንደኛ እንደማንኛውም ክህሎት ስትጀምረው አድካሚ ነው። ቅድም ያልናቸውን ሁሉ ለመልመድ አድካሚ ሂደት እላቸው። አንዳንዴ እንዲያውም ድካም ብቻ ሳይሆን የአካል መጎዳትም ሊያመጡ ይችላሉ። ስለዚህ እነዚያን ለመልመድ የሚፈልጉ ሁሉ ይህን አውቀው እና ተዘጋጅተው እንደሚገቡበት ንባብም እንዲህ ያለ ነገር ዝግጅት እና ትዕግሥት የሚፈልግ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። ክህሎቶች ከለመድናቸው ባኋላ ደግሞ በጣም ቀልለው የምናደርጋቸው ነው የሚሆኑት ።
ለምሳሌ ብስክሌት መንዳት አንደዚያ ነው። ስትለምደው ስትወድቅ ስትነሣ፣ ልብስህ ሲቀደድ፣ ስትጋጋጥ ሊሆን ይችላል። ከለመደከው በኋላ ደግሞ እግርን መሪው ላይ ሰቅሎ እስከመሔድ የሚያደርስ ቅልለት እና አስደሳችነት አለው። እውነት ለመናገር ንባብም እንደዚሁ ነው። ለመልመድ ሊያደክም፣ ሊያሰለች እና የማይቻል ሊመስል ይችላል። ከተለመደ በኋላ ግን በጣም ቀላል እና ማንኛውም ቦታ እና ጊዜ ላይ ሊደረግ የሚችል በጣም አስደሳች ነገር ነው። እውነቱን ለመናገር የዛሬ 15 ዓመት ለመጀመሪያ አውሮፓ በሔድኩበት ወቅት በተለይ ጀርመን አንዱ ያስቀናኝ ባሕላቸው ይህ ነበር። እንዲያውም እኔንም በተለይ በባቡር ስሔድ እንዳላፍር አድርጎኛል ማለት እችላለሁ። እነርሱ የሚያስቀኑኝ በተጨናነቀ ባቡር ውስጥ ቆመው እየሔዱ ሻንጣቸውን ተደግፈው የሚያነብቡት ነገር በጣም በጣም ያስገርመኛል። እውነተኛ ክህሎት እና ባሕል ሲሆን ለካ ያን ያክል ቀላል እና ሌላ ማሰብ እስከማትችል ድረስ አስደሳች ነገር ነው።
ሁለተኛው ጉዳዬ ውጤቱን በተመለከተ ነው። ያለ ንባብ አእምሮ ሊዳብር አይችልም። እንደሚባለው እኛ ኢትዮጵያውያን የማሰብ አቅማችን (IQ) ከሁሉም ዝቅ ያለ ነው ይባላል። እኔ በግሌ አምኛለሁ። ይህ የማሰብ አቅም የሚለካው ሰው በእድሚው ልክ ሊያስብ እና ሊያውቅ የሚገባውን እና አሁን ከሚያውቀው እና ከሚያስብበት ጋር በማነጻጸር የሚሠራ ስሌት ነው። ስሌቱ ፍጹማዊ ባይሆንም እንኳ በአንጻራዊነት ሲታይ ትክክል ይመስለኛል። አሁን ያለንበት ውጥንቅጥ፣ ግጭት፣ እልቂት፣ አለመደማምመጥ ፤ ሌላው የሚለውን በአግባቡ አለመረዳት፣ ሆነ ብሎ ማጣመም እና የመሳሰሉት ሁሉ ከማሰብ ኣቅም ውደቀት የሚመነጩ ናቸው። ለዚህ ምክንያት ተደርገው ከሚወሰድት አንዱና ዋናው የንባብ ባሕሉም ክህሎቱም ስለሌለን ነው ብዬ አስባለሁ። ስለንባብ የሚናገሩ ወይም የሚጽፉ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ ልክ የጂም ስፖርት ለሰውነትህ ጤናን ለአካል ጥንካሬን እና ለተክለ ሰውነትም መስተካከልን የሚሰጠውን ያህል ንባብ ደግሞ አእምሮን እና የማሰብ ችሎታን በዚያው መጠን የሚለውጥ እና የሚያስተካክል ነው። ልክ እንደ ጂሙ ጤናማ አስተሳስበን፣ የአቋም እና የአመለካከት ጤናማናትን ብስለትን እና ጥንካሬን ሊያላብሰን የሚችል ብቸኛው መንገድ ንባብ ነው።
የሚያነብቡ ሆነው የተሳሳቱ እና የሚያበላሹ ሰዎች አሉ አይደለም ወይ ልትል ትችላለህ ። የእነርሱ ችግር ንባብ ሳይሆን ሌላ ነው። ምን መሰለህ ። አንድ ሰው ባልበሰለ አእምሮ አንድን ነገር እንዲያምነው ከተደረገ (አስተውል እንዲያውቀው አይደለም ያለኩት እንዲያምነው ነው ያልኩት) እና ካመነበት ከዚያ በኋላ ያለው ንባቡ ያንን የሚያምንበተን ለማስረዳት ወይም ለመጠበቅ ወይም ያን ይደግፋል የሚምስለውን መርጦ በማውጣት ላይ የተጠመደ ነው የሚሆነው። እንዲህ ያሉ ሰዎች ማለት አድሏቸው፣ ችግራቸው ከንባባቸው የመጣ ሳይሆን ችግራቸውን፣ እምነታቸውን፣ አድሏቸውን ፣ ዝንባሌያቸውን እና ጥፋታቸውን በንባብ ለመደገፍ የሚያነብቡ ስለሆኑ ለንባብ ምሳሌ መሆን አይችሉም። ልክ በእምነት ብትወስደው የኔታ ገብረ ሕይወት ዘደብረ ጽጌ እንዳሉት ያለ ነው።
የኔታ ገብረ ሕይወት (የብዙ ሊቃነ ጳጳሳት የመጽሐፍ መምህር የነበሩት በረከታቸው ይድረሰንና እጅግ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን የተናገሩ ፈሊጥ ላይ የደረሱ አባት ነበሩ)። ። ብፁዕ አቡነ ኤልሣዕ እንደነገሩኝ እንዲህ ብለው ጠየቋቸው። የኔታ አንዳንድ ሊቃውንት ሲማሩ ሲያውቁ ተጠራጣሪ የሚሆኑት ትምህርት ወይም ዕውቀት ወደ መና***ነት ይወስዳል ወይ ብለው ይጠይቋቸዋል። እርሳቸውም አይ ትምህርትም ሆነ ዕውቀት ወይም ሊቅነት መ**ቅ አያደርግም። ነገር ግን ብዙዎች ባልበሰሉብት ወቅት ጂል መምህር ይገጥማቸውና ኑ*ፋቄ ይዘራባቸዋል። ኋላ እየተማሩ ሲሔዱ ከተማሩት ውስጥ ላመኑበት የሚስማማ የመሰላቸውን ስለሚናገሩ ሲማሩ የደርሱበት ይመስልላቸዋል እንጂ በመማራቸው ያመጡት አይደለም ብለዋቸዋል። የክፉዎች የተዛቡ ሰዎችም ንባብ ልክ እንደዚህ ነው። በማንበባቸው የደረሱበት፣ ያገኙት እና ያወቁት ሳይሆን ንባባቸውን ለብልሻታቸው እና ለመዛባታቸው መደገፊያ አድርገው ስለሚያቀርቡት ነው።
ስለዚህ ሳጠቃልለው በትትክለኛው መንገድ ሆነን የምናንበው ንባብ አእምሮአችንን ሀሳባችንን እውቀታችንን ብቻ ሳይሆን የምናውቅበትን የምንረዳበትን የምንተረጉመበትን መንገድ ሁሉ ስለሚያስተካክለው ብዙ ችግሮች በቀላሉ በመግባባት ሊፈቱ ይችላሉ። አኛ ሀገር በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት ችግሮችን መፍታት ያቃተንም እኮ ይህን ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ ስለማይታወቅ ሳይሆን ለዚያ የሚሆን የአእምሮ ሥሪት ላይ የደረሱ ሰዎች ስለማይመሩን ነው። የማስመሰል፣ ያውቃሉ የመባል፣ አድሎን ለመደገፍ ከሚደረግ ንባብ ባለፈ መሠረታዊ የዕውቀት እና የንባብ ሥሪት የተገነባ አእምሮ ሲመጣ ግን እስክንናገርም አይጠብቁም። ራሱ አእምሮአቸው ያስገድዳቸዋል። ስለዚህ ንባብ የብዙ ችግሮች መፍቻ መንገድ መሆኑን ከማወቅ ባለፈ ክህሎት መሆኑን እና ይህ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተገንዝበን የንባብ ባህላችንን እንድናዳብር ነው ማሳሰብ የምፈልገው።
ጃንደረባው:- ከሃይማኖት መምህርነትና ከጸሐፊነትና በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ካለህ እጅግ ወሳኝ አስተዋጽኦ በመነሣት የመጪው ዘመን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምን እንዲመስል ትመኛለህ? ለወጣት አገልጋዮችስ ምን ትመክራለህ?
ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- አስተዋጽዖ የሚለውን አቆይተነው ወደ ነገሩ ላምራ። ይሄ ከባድ ነገር ግን በጣም አስፈላጊ ጥያቄ ነው። እውነቱን ለመናገር እንደማንኛውም ሰው እኔም ምኞቶች ሕልሞች እና ሀሳቦች አሉኝ። በአጭሩ የምለው ግን የመጪው ዘመን አገልግሎት ተገቢ ዕውቀት እና ሕይወት ሊመራው ይገባል። እውቀት ያለው ሰው እኮ ሲያጠፋም ያፍራል። ሲታወቅበትም ይደነግጣል። አሁን አኮ ብዙ ነገሮች ላይ ሐፍረት እንኳ ተሟጥጦ የጠፋ ነው የሚመስለው። ስለዚህ ለዚያ ምቹ የሆኑ ተቋማት መገንባት አለባቸው ብዬ ነው የማስበው። ይህን የምለው ዝም ብዬ አይደለም። አስተያየትን ዘርዝሮ እንዲህ ቢደረግ እንዲያ ቢሆን እያሉ መስጠት ይቻላል፣ ትርጉም ይሰጣል ብዬ ግን አላስብም።
ምክንያቱም ይሥራ የምንለው ወይም እንዲሠራው የምንፈልገው ወይም ደግሞ ለዚያ በሚሆን ቦታ ያለው ሰው ለዚያ የሚገባው ሁኔታ ላይ ሳይሆን ዝርዝር ጉዳይ መናገር ጥቅም አለው ብዬ አላስብም። ይልቁንስ እኒያ አካላት ያን እንዲያውቁ የሚረዳ አሠራር ወይም አካሔድ ነው መምጣት ያለበት ። እውቀት ይምራው ማለት ይህ ነው። ሰውየው ዕውቀት እንዲኖረው ሳናደርግ ወይም ዕውቀቱ ያለው ሰው እንዲያግዝ ሳይመቻች መናገር ትርፉ መተቻቼት፣ መራራቅ ከዚያም መጠላላት እና ተስፋ መቁረጥ የሚሆን ይመስለኛል። ስለዚህ ለዚያ የሚሆኑ ተቋማትን ማጣናከር፣ መፍጠር ተገቢውን የሰው ሀብት ማፍራት ማብዛት እና እድሉን መፍጠር ነው ብዬ አስባለሁ።
ጃንደረባው:- ከንባብ ከትምህርት ብዙ ሀገር ከመጎብኘት በአጠቃላይም ከሕይወት የተማርከው የሕይወት ፍልስፍናህ ወይም ይህ መመሪያዬ ነው የምትለው ጽንሰ ሃሳብ ካለ ብትነግረን::
ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ:- እውነቱን ለመናገር የተለየ የምለው የሕይወት ፍልስፍናም ሆነ መንገድ የለኝም። ያን ያክል ያስፈልጋል ብዬም አላስብም። ከሆነም እንደ ስማችን በተግባር ክርስቲያን መሆንን ነው በአግባቡ መለማመድ ያለብን ብዬ ነው የማምነው። እስካሁን ባለኝ መረዳት ክርስቲያን ከመሆነ የተሻለ የአኗኗርም ሆነ የአሠራር ልቀት ኖሯቸው ያስቀኑኝ አላጋጠሙኝም። እውነተኛ ክርስቲያን ብንሆን እንደ መጀመሪያዎቹ ክፍለ ዘመናት ዓለም ሁሉ እንደሚከተለን አልጠራጠርም። አሁንም የማየው ይህንኑ ነው። ሰዎች ክርስቲያኖችን ክርስቲያኖች ሆነው ባገኟቸው ቁጥር ሁሉ የየትኛውም ዓለም ሰዎች ሊከተሏቸው እና ሊመስሏቸው ሲፈልጉ ነው ያስተዋልኩት ። ስለዚህ እኔ እንደሚገባኝ ክርስቲያን ለመሆን የምጣጣር ስለሆንኩ ከዚህ የተለየ ምንም የሕይወት ፍልስፍና የለኝም፣ እንዲኖረኝም እልፈልግም።
ብዙ ሰዎች እንደ ሕክምና ትእዛዝ የሆነ ቀላልና ቅደም ተከተላዊ የሆነ አዲስ ነገር (a kind of prescription) እንደሚፈልጉ እረዳለሁ። እርሱም ቢሆን ግን ተጽፏል። አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ብዙ ቦታ መዞር ፣ ገዳማትን ማየት፣ የበቁ ሰዎችን ማግኘት፣ … የመሳሰለው አይደለም የሚጠቅመን። እነዚህ በራሳቸው የበረከት ምንጮች ቢሆኑም ወደ ምንፈልገው የሚወስደን እና ከብዙ ጭንቀት የሚገላግለን አንድ ነገር ነው። እርሱም ትእዛዛትን መፈጸም ነው። በዚህ ከሔድን ከበቁት ጋርም ብዙ ሳናንከራተት እንገናኛለን። ሩቅ ሳንሔድም ከገዳማት ጋር እንተሳሰራለን። ስለዞርን ሳይሆን በሚያደርሰው መንገድ ስንሔድ ብቻ ነው እነዚህን ሁሉ አግኝተን መጠቀም የምንችለው። ጌታ እኔ መንገድ ነኝ ካለ ሌላ መንገድ ለምን ያስፈልጋል። ጌታ እኔ መንገድ ነኝ ያለው እኮ ሥላሴን ስለማወቅ እና ማመን ወይም ስለድኅነታችን ቤዛነቱ በቻ ሳይሆን በተግባር ለምንሔድበት ሕይወትም ለማሳየት ወይም ለአርአያም ስለመጣ ነው።
እርሱ ወሀቤ ሕግ ሆኖ ሳለ ሕግን ፈጽሞ ካሳየን ለመንፈሳዊ ሕይወት ሌላ መንገድ አለ ማለት እንደ ኑፋቄ የማየው ነገር ነው። እርሱ በሥጋዌው እና በቅዱሳንም በመገለጥ ካሳየው ውጭ ምንም የተሻለ መንገድ የለም። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ለማስረዳት ያህል እንናገረው ብለን ካልሆነ ቀላሉም ብቸኛውም መንገድ ትእዛዛትን በመፈጸም ወደ ተሻለው እና ደጋግሞ እንዳለው ከዓለም የማይገኘው ሰላም ወደሚገኝበት መንገድ መገስገስ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ፍልስፍናም፣ መንገድም፣ ልምድም ፣ ይጠቅማል ብዬ ብዙ አላስብም። እርሱን ብንለማመደው እንዴት መልካም ነገር ነበር።
ቃለሕይወት ያሰማልን ረጅም ዕድሜን ያድልዎት ውድ መምህራችን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን እግዚአብሔር በክብር ያኑሮት መምህራችን ።
እኛም ጥሩ እንድንሆን ይርዳን
ቃለ ህይወት ያሰማልን ።