ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ – ክፍል 1


መጻሕፍት በማዘጋጀት ሒደት ውስጥ እድሜ ወሳኙ ነገር ነው

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ መምህር ፣ ሰባኬ ወንጌል ፣ ጸሐፊ ፣ አርታኢና ሐያሲ ናቸው:: ከመንፈሳዊ አገልጋይነታቸው በተጨማሪ የፊዚክስ ዲፕሎማ ፣ የሥነ ጽሑፍ ዲግሪን የፊሎሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: የጃንደረባው ሚዲያ የሰንበት ቃለ መጠይቅ እንግዳ ናቸው:: ከጠያቂው ጋር ባላቸው ቅርበት አንቱታውን ትተው በጃንደረባው ሠረገላ ላይ የሚከተለውን ተጨዋውተዋል:- 

ጃንደረባው :- ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ወደ መጻሕፍት ሥራው ለምን አይመለስም? ከ”በዓላት” ከ”ሁለቱ ኪዳናት”ን ከ”ትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ”ን ከመሳሰሉ በሳል መጻሕፍትና ጠንካራ መጣጥፎች ወዲህ በወጥ የመጽሐፍ ሥራ የማያስነብበን ለምንድን ነው የሚል ወቀሳ እየቀረበብህ ነው:: ምን ትላለህ?

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- እውነት ነው ወቀሳው በተለያየ ጊዜ እና ሁኔታ ሲቀርብ እመለከታለሁ። በማኅበራዊ ሚዲያ በየአጋጣሚው አስተያየት ከመስጠት አንሥቶ ርእሰ ጉዳይ አድርገውም የጻፉብኝ እንዳሉ አውቃለሁ። የሚገርመው ግን ይህ አይደለም። ለዚሁ ጉዳይ ብቻ ብለው ሥራዬ ብለው ቢሮ ድረስ መጥተውም ያሳሰቡኝ፣ ያነጋገሩኝም አሉ። 

አንዳንዶቹ ደግሞ ማሳተሚያ ፈርተህም ከሆነ እናስብበታለን እስከማለትም የደረሱ አሉ። እውነቱን ለመናገር ከምገምተው እና ከምጠበቀው በላይ ነው ጥያቄው። ጥያቄም ብቻ አይደለም በርከት ያለ ወቀሳም ጭምር አለው። ከምር ተቆጥቶ “ይህን ዐቢይ ጾም እቤቴ ልዝጋብህ” ያለኝም ወንድምም አለ። አንድ ታዋቂ ጸሐፊ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ ብሎ አንድ ጉዳይ አንሥቶ አንተ ይህን ይህን ጻፈው እንዲህ እንዲህ ያለውን እኔ አስሸ ላሟላልህ እና እባክህን አሳብህን ለኅትመት አብቃው ብሎ ተማጽኖኝ ያውቃል። 

እውነት ለመናገር ከማልጠብቃቸው ሰዎች ሁሉ አስገራሚ ማሳሳበቢያዎች፣ ጥያቄዎች፣ ወቀሳዎች ከዚህም አልፎ ምክሮች እና ተግሣጾች እስካሁን ድረስ አላቋረጡልኝም። በዚህ መልክ የምገልጸውም ብዙዎች በዚሁ መንገድ ያልተደረገ መስሏቸው የቀናነት ሀሳባቸውን ይዘው እንዳይደክሙ ከረዳ ብዬ እንጂ ያን ያህል አስፈላጊ ሆኖ አልነበረም። የሆነው ሆኖ እስካሁን አልተሳካም። የዚህ ሁሉ ጉድለቱ ከእኔ ብቻ ነው። በቅንነት እና ያለኝን እንዳካፍል በማሰብ ይህን ላደረጉ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። 

ይህንኑ ማድረግ እያሰቡ በተለያየ ምክን ያት ላልተቻላቸውም እንዳደረጉት ቆጥሬ አመሰግናለሁ። ስለወደፊቱ ከመናገሬ በፊት ግን ከመጻሕፍት አንጻር ካለኝ የሕይወት ትስስር ጋር በተገናኘ አንዳንድ ጉዳዮችን ማንሣት ያለብኝ ይመስለኛል።  

ጃንደረባው :- ለመሆኑ ከመጻሕፍት ጋር ያለህ ትውውቅ እና ትስስር እንዴትና መቼ ተጀመረ?

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- ነገሩ ተያያዥ እና ረዥም ቢሆንም እኔ ቆረጥ አድርጌ አቀርበዋለሁ። 

ከቤተሰቤ እንደተረዳሁት ገና ሳልወለድ እናቴ ታምማ ከቀበሌያችን ሦስት ሰዓት ያህል ብቻ የሚወስድ ርቀት ላይ ታሪካዊዋ የሐረጊት ኪዳነ ምሕረት ገዳም አባቴ ወስዷት ነበር። በዚያ ቆይታዋ በተደረገላት ነገር እና ባየችው ምልክት በዚያ ወቅት ቤተ ክርስቲያንን እንዳገለግል ገና ሳልወለድ ለኪዳነ ምሕረት ተስላ ኖሯል። በወቅቱ የነበሩት የገዳሟ የዕቃ ቤት ጠባቂም እስከማስታውሰው ድረስ ስማቸው አባ ገብረ ሥላሴ ይባሉ ነበር። እና እርሳቸውም ክርስትና የማነሣው እኔ ነኝ ብለው ነበር ብለውኛል። በርግጥ ቤተሰቦቼ ቀደምው በገቡት ሌላ ቃልኪዳን ምክንያት ለእርሳቸው ባይሰጡኝም እርሳቸው ግን የእኔ ልጅ ነው እያሉ በሔድን ቁጥር ሁሉ ይንከባከቡኝ ነበር። እና ትልልቅ የብራና ጭራቸውን እየተቀበልሁ መጻሕፍቱን ሁሉ እንደማንኛውም ልጅ ይህ የእኔ ነው ይህም የእኔ ነው እል እንደነበር ነግረውኛል። 

ይልቁንም ማስታወስ ከጀመርሁበት ጊዜ ያለውን ሁኔታ ወደ ኋላ ተመልሼ አሁን ሳስበው የመጻሕፍት ነገር ጽንሱን የወሰዱሁት ያን ጊዜ ነው ማለት ይቻላል።
ዕድሜዬ ለትምህርት ሲደርስም ያስገቡኝ ያው በአጥቢያችን ያሉ ታዋቂ የአቋቋም መምህር ጋር ነበር። መርጌታ ፍስሐ ይባሉ ነበር። እዛ ከፊደል ገበታ አንሥቼ ዳዊት ደግሜ እንዳገና ንባብ ላይ እያደላደልኩ ሳለ በቀበሌያችን የአስኳላ (የዘማናዊ) ትምህርት ቤት ተከፈተ። 

ከዚያ በአካባቢው የነበሩ የደርግ ባለሥልጣናት ይመስሉኛል በቅድሚያ የቄስ ተማሪዎች ወደ ዘመናዊው ትምህርት እንዲገቡ ግዳጅ ሲያመጡ ተለቅ ተለቅ ያሉት ዜማ እና አቋቋም ይማሩ የነበሩት እና ይህን ያልፈለጉት ደቀ መዛሙርት ወደ ሌሎች ጉባኤ ቤቶች የደርግን ግዳጅ ሸሽተው ሔዱ። አንዱ የእኔ ታላቅ ወንድም ነበር። እኔ ግን ለደርጉ የጥያቄ መመለሻ ተደርጌ ተሰጠሁና ወደ አስኳላው ገባሁ እና በዚያው ቀረሁ። 

በርግጥ በኋላ እንደነገሩኝ አባቴን ደርግ እንደገባ ለንግሡ ሥርዓት ይረዱ ይሆናል ብሎ ያሰባቸውን ወይም በሌላ ምክንያት አላውቅም ይዟቸው ሲሔድ እና በኋላም በእሥር ቤት በቆዩበት ወቅት ለቤተሰብ የሰጡት አደራ የእኔን መማር ጉዳይ ስለነበር መማሬ ላይቀር ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን የጀመርሁት በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው።

ጃንደረባው :- ታዲያ ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መቼ እና እንዴት ተመለስህ?

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ:- ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመማር በሔድንበት የእስቴ ወረዳ ከተማ በሆነችው መካነ ኢየሱስ ሁለት ነገሮች ተከሰቱ። በነገርህ መካነ ኢየሱስ የሚለው አሁን አንድ የፕሮቴስታንት ዲኖሚኔሽን ሆኖ ነው የሚታወቀው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ይህ ስም የታላቁና የታሪካዊው እስቴ የሚገኘው ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ስም ነው። እነርሱም ስሙን የወሰዱት ከዚያ ስለነበር በወቅቱ በንጉሡ ዘመን ተከሠው መጠነኛ ካሣ ከፍለው ስሙን ግን ይዘውት እንደቀሩ ሰምቻለሁ። እና ትምህርት ቤታችንም ስሙ መካነ ኢየሱስ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የሚባለው። ታዲያ አንደኛው ከእኔ ጋር ቄስ ትምህርት ቤት አብሮኝ ይማር የነበረው ጓደኛዬ እና ወንድሜ ዲያቆን ያየህይራድ ተስፉ ጋር ከአንደኛ እስከ አምስተኛ አብረን ተምረን ከስድስት እስከ ስምንት ከተለያየን በኋላ ዘጠነኛ ክፍል ላይ አንደገና እዚህ ከተማ ተገናኘን። 

በተለያየንበት ወቅት እርሱ የሰንበት ትምህርት ቤት የሚባል ጀምሮ መጥቶ ስለነበር በኋላ ላይ አንድ ቀን አስታውሳለሁ በጥቅምት ወር ለውኃ ዋና አንድ ቸና የሚባል ወንዝ ወርደን ውለን ስንመለስ መንገዳችን ላይ ከተማው ውስጥ ከበሮ ሲመታ ሰማን። ለካስ ሰንበት ትምህርት ቤቱ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ቢሮ ውስጥ ባለ አዳራሽ ኖሯል የሚካሔደው። ታዲያ ያየህይራድ ያውቅ ስለነበር ወሰደን። 

እስከማስታውሰው ድረስ ስንገባ ከፍ ያሉ ሰዎች ስንሔድ እኛ ሳንሆን አንቀርም። ተሳስቼ ካልሆነ በቀር ከዚያ በፊት የነበሩት በብዛት ከእኛ በዕድሜ የሚያንሱ ሕጻናት ነበሩ። እና ያ የተውኩት የቤተ ክርስቲያን ትስስር ድንገት እንደገና ተመለሰ። እኔ ከዚያ በፊት በአማርኛ የተጻፈ የሃይማኖት መጽሐፍ ስለመኖሩም አላውቅም። ሌላው ቀርቶ ለመርጌታ ፍስሐ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መካነ ሰማዕት ገላውዴዎስ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሸለሟቸው ታላቅ ወንድሜ በአድናቆት ሲያወራ ት ዝ ይለኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ መጽሐፍ ይሁን ሌላ ነገር ይሁን ግ ን ምንም አላውቅም ነበር። በአማርኛ የጽሎት መጽሐፍ ሁሉ መኖሩን ያወቅሁት ከዚያ በኋላ በአንድ አጋጣሚ ነበር።

ታዲያ እዛ የሰንበት ትምህርት ቤት የሚያስተምረው ደግሞ ቄስ ጸዳሉ ሹምዬ የሚባል ካህን ነበር። እውነት ለመናገር ከዚያ በፊት ቤተ ክርስቲያን የምንሔድ ዳዊትም ግእዙ የነበረኝ ቢሆንም ሰንበት ትምህርት ቤት ስንሒድ ትልልቆች ስለነበርን ሁሉ ነገር ያስደንቀኝ ነበር። አሁን ሳስበው ቀሲስ ጸዳሉ በዚያ ዘመን እንዴት እንደዚያ ጎበዝ መምህር መሆኑ እስካሁን ያስገርመኛል። እርሱ ቅኔ አዋቂ ስለነበር ሊሆን ይችላል ታሪክ በጣም ያውቃል። ጎበዝ አስተማሪ ነው። ብቻ ትልቅ ፍቅር እና ፍላጎት በልባችን ውስጥ አሳደረብን። በዚያውም ላይ በወረዳ ቤተ ክህነቱ የነበሩ በጣም ትልልቅ ሰዎች ነበሩ። እነ መላከ ሕይወት አለቃ መለሰ ኃይሉ፣ መለአከ ገነት መርጌታ ጌትነት በየነ፣ እነ መርጌታ ልብሰወርቅ ደርሶ እነ መርጌታ ነቅዐ ጥበብ የሚባሉ ትልልቅ እውነተኛ አባቶች አይለዩንም ነበር። የሚገርመው የእነዚህንም ሆነ የሌሎች ያልጠራኋቸውን ትልቅነት ግን የተረዳሁት አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ታላቁን የመጻሕፍት መምህር እና መናኒውን የኔታ ኃይለ ሚካኤል አገኘንና እና ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደገና ተመልሼ መጣሁ። ከዚያ እርሳቸው ጋር ደግሞ በርካታ መጻሕፍት ስለነበሩ የተውኳቸውን ትምህርቶች ከመማር ጎን ለጎን መጻሕፍቱን በማንበብ ሳላውቀው ከመጻሕፍት ጋር እውነተኛ እና ተግባራዊ ወዳጅነት ጀመርሁ ብዬ የማስበው እዚያ ነው። የአቡነ ጎርጎርዮስ መጻሕፍትን፣ መርሐ ጽድቅ ባሕለ ሃይማኖትን፣ መጽሐፈ ሥነ ፍጥረትን፣ አእማደ ምሥጢርን፣ የአቡነ መልከጼዴቅ የስብከት ዘዴን፣ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያሳተማት መዝገበ ሃይማኖት ይመስለኛል ርእሱ እና የመሳሰሉትን ያነበብሁት በዚያ ጊዜ ነው። ሌላው ቀርቶ ቁራንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት እዛው የኔታ ኃይለ ሚካኤል ጋር ነበር። እንግዲህ እስቴ የተፈጠረው አንዱ መሠረታዊ ነገር ይህ ነው። ከመጻሕፍት ጋር ጥሩ ትውውቅ ጀመርሁ የምለው በዚህ ጊዜ ነው።

ጃንደረባው :- መጻሕፍት ወደ ማዘጋጀት እንዴት መጣህ? በምን ምክን ያት?

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ደግሞ ግጥሞችን እየጻፍኩ ሰልፍ ላይ አነብብ ነበር። ለአንዳንድ የተለዩ ጉዳዮችም ታዝዤ ግጥም አዘጋጅ ነበር። እንዲያውም የድራማ ድረስትም አንድ ጊዜ ብቻ ቢሆንም ጽፌ ተሠርቶም ነበር። በሰንበት ትምህርት ቤቱም ማስተማር የጀመርነው ወዲያው ነበር። ከዚህ የተነሣ መድረክ መምራት እና የተለያዩ ሓላፊነቶችን መለማመድ በጊዜ ጀመርን፣ በእነዚህ ምክንያቶች አንዳንድ አስተማሪዎች ደራሲ ልሆን እንደምችል ሲነግሩኝ ውስጤ እየተቀበለው መጣ።

በኋላ ግን አንድ አስደንጋጭ ነገር ገጠመኝ። እርሱም የአሥራ ሁለተኛ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ስንወስድ የአማርኛ ቋንቋ ፈተና ምንባቡ ላይ ለፈተና የመጣው የንባብ ይዘት ስለደራሲዎች የሚናገር ነበር። እና እዛ ምንባብ ላይ አንድ ሰው ደራሲ ለመሆን ዕድሜው አርባ ዐመት ቢሞላው ጥሩ ነው የሚል ነገር ሳነብብ ፈተናውን ትቼ ደነገጥኩ። እኔ ደራሲ ለመሆን ቋምጬ ያለሁ ሰው ቁጭ ብዬ እድሜዬን ሳሰላው ከግማሹ ገና ፈቅ አላልኩም። ለዚያውም እኛ በደርግ እና ኢህአዴግ ጦርነት ሁለት ዓመት አቋርጠን ስለቆየን እንጂ ያ ባይሆን ደግሞ የበለጠ ያንስ ነበር። እውነት ለመናገር እዛው ፈተናው ላይ ሆኜ ለራሴ ይህን ያህልስ እኔ አልጠብቅም ብዬ መልስ ሰጥቼ ባልፍም ስለመጻሕፍት መጻፍ እና ስለእድሜ ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ግን እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ የማይጠፋ ነገር አስቀምጦብኝ ቀረ። ይህ ጉዳይ እስካሁን ላሉት አንዳንድ ጉዳዮቼ አስተዋጾ ስላለው ነው ያነሣሁት ።

ሁለተኛው ደግሞ ያው እኔ መጀመሪያ ፊዚክስ ዲፕሎማ ነው የተማርኩት። በእኛ ጊዜ እስከ ሦስት ነጥብ ሁለት (3.2) ድረስ ያመጣነው ወንዶች ከዚያ በፊት እንደነበረው ለዲግሪ አልተፈቀደልንም። ኢህአዴግ መንግሥት እንደሆነ ስለነበር እኛ ያለንበት ክልል ይህ እድል አልተሰጠንም። በኋላ እንደሰማሁት ሌሎች ክልሎች ተጎድተው ኖረዋል ተብሎ ለአንዳንዶቹ በ2.6 ሁሉ ዲግሪ ሲገቡ እኛ ደግሞ ወደ ዲፕሎማ ነው እንድንገባ የተደረገው። በኋላ ብዙዉ በተለያየ መንገድ ቢማርም። እኔም ሁለት ዓመት ቆይቼ እንደገና አድቫን ስታንዲንግ በሚባል እድል ለዲግሪ ገባሁ። በዚያ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ሰፊ አገልግሎት እንሰጥ ነበር። ታዲያ በ1992/93 ይመስለኛል “ሰዓታት በመቅደሱ ሚዛን ሲመዘን” የሚል አንድ የተሐድሶዎች መጽሐፍ ወጥቶ አነበብኩኝ። በወቅቱ አዲስ የሚወጣን መጽሐፍ ሁሉ ተከታትዬ የማስገዛ እና የማነብብ ነበርሁ። 

በዚህ ጊዜ በጣም አዘንኩ ተናደድሁና መልስ መስጠት አለብኝ ብዬ ተነሣሁ። በዚህ ምክን ያት አዲስ አጀንዳ አዘጋጅቼ ቢጋር አውጥቼ መጻፍ ጀመርሁ። በዚህ ጊዜ ለአንዳንድ ጉዳዮች ተጨማሪ የማጣቀሻ መጻሕፍትን ፈልጌ ሳነጋግር አዲስ አበባ ሔደህ እነ ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራውን እና ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ብትጠይቅ ታገኛለህ አሉኝ። እውነቱን ለመናገር ያን ጊዜ የፊዚክስ ተማሪ እንደመሆኔ መጠን ገና የማጠቀሻ መጻሕፍት አጠቃቀስን እንኳ ስለማላውቅ ዝኒ ከማሁ ራሱ የመጽሐፍ ዓይነት ነበር የሚመስለኝ። በዚህ ምክንያት ክረምት አዲስ አበባ መጥቼ ይህን ሀሳቤን ሳቀርብ ዲያቆን ዳንኤል ሀሳቡን ከተቀበለ በኋላ የራስህን እየሠራህ ለእኛም አንድ ቡክሌት ብትሠራልን የሚል ሀሳብ አቀረበልኝ። 

ያን ጊዜ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ላይ የገሃንም ደጆች የሚል ርእስ ያለው ተሐድሶን የሚያጋልጥ ጽሑፍ ይወጣ ነበር። ታስታውስ ከሆነ ያን ጊዜ ተሐድሶ የገነነበት አንዱ ወቅት ነበር። እነ አባ ብእሴ አባ ዮናስ የሚባሉ መንኮሳት በኤግዚቪሽን ማዕከል ከፐሮቴታንት ኮንፈረንስ ተገኝተው ሲዘልሉ የሚያሳየው ፊልም የተሠራጨበትም ወቅት ነበር። እኔም ሀሳቡን ተቀበልሁ። በኋላ እርሱ ለእኔ በየቀኑ ጽ/ቤት የምሔድበት የታክሲ ወጭ ለማስፈቀድ ጉዳዩን ሥራ አስፈጻሚ ላይ ሲያቀርብ የወቅቱ ዋና ጸሐፊ የነበረው ዲያቆን ዓባይነህ ባሕርዳር ለሥራ ሲመጣ በሁለት አጋጣሚዎች አይቶኝ ስለነበር አይ እርሱ የተሻለ ነገር መሥራት የሚችል አቅም ያለው ስለሆነ ብሎ ሌላ ሃሳብ ያቀርባል። ሀሳቡም መርጌታ ሃየሎም የሚባሉ አንድ መምህር የዕብራዉያን አንድምታ ለሚለው የተሐድሶዎች መጽሐፍ የመልስ መጽሐፍ አዘጋጅተው ማኅበሩ እንዲያሳትምላቸው ሰጥተው ኖሯል። ያ ረቂቅ ግን ለኅትመት ሳይበቃ ሊያዩት በወሰዱት ሰዎች እጅ ላይ ጠፍቶ ኖሯል። 

በዚያ ዘመን ጽሑፍ የሚዘጋጀው በወረቀት ስለሆነ እና እንዳሁኑ ሶፍት ኮፒ የሚባል ስለሌለ ከጠፋ ጠፋ ነው። አዘጋጁ ደግሞ ወይ አሳትሙ ወይ ጽሑፌን አምጡ እያሉ አስጨንቀዋቸው ኖሯል። ስለዚህ ዓባይነህ ይህን ጭንቀት ለመገላገል ሲል በዕብራዉያን መልእክት ላይ አንድ ወጥ ሥራ በአራት ወራት ውስጥ እንደሠራ ሥራ አስፈጻሚውን አስወሰኖ በጀትም ተፈቅዶለት ታዘዝኩኝ። እኔም የመጣሁበትን ትቼ የማኅበሩን የቤት ሥራ ወስጄ ከሰኔ እስከ ጥቅምት አጋማሽ ይመስለኛል ያው የምታውቀውን ሁለቱ ኪዳናት የሚባለውን ሥራ ሠረቼ ተመለስኩ። እኔ የጀመርኩት ሥራ ግን እንደተጀመረ ቀረ። ከዚያ ወደ ባሕርዳር ተመለስኩ። ሆኖም ይህ ሥራ ሌላ ጉዳይ ይዞ መጣ። 

ይኸውም አዲስ አበባ መጥቼ ማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ በመደበኛ አገልጋይነት እንዳገለግል ከፍተኛ ጫና አመጣና ወደዚህ መጣሁ። በዚህ ምክን ያት እኔም በሕይወቴ አንድም ቀን ቤተ ክርስቲያንን አሁን በማደርገው መንገድ ማለትም ሰባኪ ሆኜ እየተዟዟርኩ እና ጽሑፎችን በመጻፍ አገለግላለሁ ብዬ አስቤ የማላውቀው ሕይወት ውስጥ ገባሁ። ስለዚህ ከከፊዚክስ አስተማሪነት፣ ምናልባትም ተመራማሪነት ወይም በሳይንሱ ዓለም ከመኖር ጎትቶ እናቴ ለኪዳነ ምሕረት ወደ ተሳለችው ስለት የመለሰኝ ወይም ደግሞ የሕይወቴንም አቅጣጫ የቀየረው ራሱ ነገረ መጻሕፍት ነው ማለት ነው። የሚገርመው አሁን ወደዚህ ከተመለስሁ በኋላ እናቴ ወደዚያ ወደ ዐለማዊው ገብቶ ቀረ በላ ትጨነቅ እንደነበረ አንድ የአክስቴ ልጅ የነገረኝ በቅርብ ነው። ያነሣሁትበት ዋና ዓላማ ግ ን ከመጻሕፍትም ጋር እንዳልለያይ ሆኜ መታሰሬን በዚሁ አጋጣሚ ለማሳወቅ ሳይሆን አሁን ሰው በሚጠብቀኝ መንገድ ላለመጻፌ ሁለቱም ነገሮች እስካሁንም ተጽእኗቸው ያልለቀቀኝ በመሆኑ ነው።

ከላይ የተጠቀሱት መጻሕፍት እንግዲህ ከሁለቱ ኪዳናት ጀምሮ እውነት ነው በእኔ የተዘጋጁ ናቸው። እንደምትለው በሳል እና ጠንካራ ባይሆኑም በጻፍኩበት ወቅት ላደርግ የምችለውን አድርጌ ያዘጋጀኋቸው ናቸው። ልቦለድ ባይሆኑም ያስደነገጠኝ ዕድሜ ላይ ከመድረሴ በፊት የተዘጋጁ በመሆናቸው አሁን እኔ የምደሰትባቸው መጻሕፍት አይደሉም። አሁን ከእነዚያ የተሻለ ነገር ለማዘጋጀት መቻሌን ባላውቅም እውነቱን ለመናገር የእነዚያ መጻሕፍት ክፍተቶችን ባየሁ ቁጥር አንዱ ት ዝ የሚለኝ ግ ን የዕድሜው ነገር ነው። እውነቱን ለመናገር መጻሕፍትን በማዘጋጀት ሒደት ውስጥ ዕድሜ አንዱና ወሳኙ ነገር መሆኑን እኔም በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ እፈልጋለሁ። ይህን ስል የተባለው ዕድሜ የግድ ለሁሉም ሰው የሚያስፈልግ ነው ለማለት ሳይሆን ቢያንስ ወደዚያ ዕድሜ የሚጠጋ ብስለት የሚጠይቅ መሆኑን ግ ን መዝለል የሚቻል አይመስለኝም። ከዚህ ዕድሜ በፊት ጥሩ የጻፉ አሉ፤ የሚጽፉም ይኖራሉ። ሆኖም ወደ ተፈለገው ዕድሜ ሳንደርስ የምንሠራው ሥራ በዕድሜው ሆነን ከምንሠራው ሥራ ይልቅ ውሱንነቱን መጉላቱ የሚቀር አይመስለኝም።

ዞሮ ዞሮ ግን ሕይወቴን ወደ መጻሕፍት እና አገልግሎት ያመጣው ከላይ የተነሣው ጉዳይ ነው። ጉዳይ ደግሞ በአጠቃላይ ከተሐድሶ እና ከለውጥ ጋር በተያያዘ መጻፍ እንዳለብኝ አምኜ ሁኔታውን አሳድጌ ይዤው ረዘም ላሉ ጊዜያት ተጨማማሪ ማስረጃዎችን ሳፈላልግለት ኖሬያለሁ። ተጽፎ በመውጫው ጊዜ ደግሞ እኔ ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች እየጎተቱኝ እስካሁን አልቻልኩም። እግዚአብሔር ከፈቀደ ግ ን አሁን ጊዜው እየቀረበ ይመስለኛል።  

ጃንደረባው :- እድሜው አሁን በቂ ነው ለማለት ነው?

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- ዕድሜውማ አሁን ብዙ አለፈ፣ አሁን ደግሞ ሌላ ችግር መጣ። አሁን ደግሞ የትናንቱ ጉልበት የለም። አዲስ አበባ እንደመጣሁ ምን አልባት ያኔ ሰውም ስለማያውቀኝ እና ብዙም የሚያዋክብ ነገር ስላልነበረብኝ ሊሆን ይችላል፣ ጤነኛ በሆንኩባቸው ዕለታት ሁሉ በቀን ከአሥራ አራት እስከ አሥራ አምስት አሥራ ስድስት ሰዓት ድረስ ለንባብ ፣ ለአርትዖት እና ለጽሑፍ አውል ነበር። አሁን ያን ማድረግ የምችል አይመስለኝም።

ጃንደረባው :- በፊሎሎጂ ክፍለ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪህን እጅግ አመርቂ በሆነ ውጤት እንዳጠናቀቅህ እናውቃለን:: እንዴት ወደዚያ ትምህርት ልትገባ ቻልክ? ፊሎሎጂ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ያለው ፋይዳ ምንድን ነው? በአግባቡስ ልትጠቀምበት የምትችለውእንዴት ነው?

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ :- የሚገርመው ነገር ያው አዲስ አበባ መጥቼ ቀጥታ የመጻሕፍት ሥራ ላይ ነው የተመደብኩት ። እንደመጣሁ ከሠራሁት አንድ መጽሐፍ ቀጥሎ በወቅቱ የግቢ ጉባኤያት መማሪያ መጻሕፍት ይዘጋጁ ስለነበር እዚያ ኮሚቴ ውስጥ መጀምሪያ አርታኢ ነበርሁ። የኮሚቴው ሰብሳቢ የነበረው ዲያቆን ዳንኤል ወደ አሜሪካ ለስድስት ወር ሲሔድ ሙሉ በሙሉ ሓላፊነቱ ወስጄ ሥራውን ተረከብኩ ማለት ይቻላል። በዚህ ምክን ያት በኋላ ዘግይተው ከታተሙት ሁለት የታሪክ መጻሕፍት በቀር ሌሎቹን በሙሉ አርትዖት የሠራሁላቸው እኔ ነበርሁ። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ወስጄ መሥራት ይጠበቅብኝ ነበር። ለዚህ ሲባል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ እና የተግባቦት ትምህርት ተማርሁ። በኋላ ሐመር መጽሔት ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኜ ስመደብ አንዳንድ የጥንት ታሪካዊ ቦታዎችን ሠርቼ ነበር። 

አስታውሳለሁ የጣና ቂርቆስ አንዱ ነበር። በሐመረ ተዋሕዶም ተመሳሳይ ቀደም ያሉ ታሪካዊ ሁኔታዎችን ያለ አቅሜ ተደፋፍሬ ጽፌባቸው ነበር። ታዲያ በኢትዮጵያ ጥናት ታዋቂ ከሆኑ ምሁራን አንዱ የሆነው ፕሮፌሰር ሺፈራው አንብቧቸው ኖሮ አንድ ቀን አስጠርቶኝ አበረታታኝ እና በታሪክ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪ እንደሠራ አሳሰበኝ። ይህን ያለበትን ምክን ያት አሁን ላያስፈልግ ይችላል ብቻ ምክሩን እኔም ከልቤ ወስጄ ታሪክ ልማር ስወስን ትምህርት ሚንስቴር አዲስ እበባ ዩኒቨርስቲ በዋናነት አዳዲስ ለሚከፈቱ ዩኒቨርስቲዎች ላይ የሚመደቡ መምህራንን በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ እንዲያስተምር ታዘዘና በተለይ አንዳንድ የትምህርት ዘርፎች ትምህርት ሚኒስቴር ከሚመድባቸው ውጭ የማይቀበሉ ሆኑ። በዚህ ምክንያት እኔም ታሪክ መማር የማልችል ሆነ። በኋላ ምን ልማር ብዬ መልሼ ፕሮፌሰር ሺፈራውን ሳማክረው ተቀራራቢ የሆነውን ፊሎሎጂን እንድማር መከረኝ። በርግጥ ከዚያ በፊት አንዳንድ ተማሪዎችም እንድማር አሳስበውኝ ነበር። በዚህ ምክን ያት ነው ፊሎሎጂ ያጠናሁት::

ፊሎሎጂ ከገባሁ በኋላ ግ ን እንኳን ተማርሁ ብዬ ተደስቻለሁ። ሞያው በአጭሩ ድርሳናት ላይ ወይም ማንኛውም ቀደምት የጽሑፍ ሥራዎች ላይ የሚጠና ጥናት ነው። ዋናውና ተቀዳሚ ተግባሩ አንድ ነው ማለት ይቻላል። ይኸውም የጥንት ጽሑፎች በእጅ እየተጻፉ በእጅ እየተገለበጡ ብዙ ዘመናትን ሲሻገሩ ብዙ ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል። ምክን ያቱም በእጅ የሚገለብጥ ሰው ምን ያህል ስሕተት ሊሥራ እንደሚችል ፎቶኮፒ ከመምጣቱ በፊት ኖት ሲገለብጥ የኖረ ተማሪ ሁሉ በቀላሉ ሊረዳው ይችላል። መስመር እንዘላለን፣ ገጽም ልንደርብ እንችላለን። ደግመን ልንጽፍ እንችላለን። ቃላት እንሳሳታለን። እጅግ በርካታ ስሕተቶችን ልንፈጽም እንችላለን። ታዲያ እንዲህ ያለው ስሕተት አንድ ጊዜ ብቻ የሚያጋጥም ላይሆን ይችላል። ብዙ ጊዜ ነው። ይህን ደግሞ በብዙ መቶ ዐመታት እና ሺሕ ዐመታት ስትወስደው አንድ ድርሰት ኦሪጅናሉ ምን ያህል ተጠብቆ ድርሶን ይሆን የሚል ጥያቄን ያስነሣል። 

ይህም ብቻ አይደለም በዘመን ብዛት ውስጥ ደግሞ የሥላጣኔ ለውጥ ለመሳሌ የእጅ ጽሑፍ አጣጣል ( Calligraphy የሚባለው) ለውጥ ስለሚከሰት የኋላ ገልባጭ ብዙ ነገሮች ላይ ሳያውቀው ችግር ሊፈጥር ይችላል። ለምሳሌ ከ500 ዓመታት በፊ የነበረው የ “ከ” አጻጻፍ የአሁኑን “ለ” ሊመስል ይችላል። በዚህ ምክን ያት የዚህ ኝዛቤ የሌለው አንድ ሰው አንድ የዚያ ዘመን ድርሰት ቢገለብጥ “ኬላ” የሚለውን “ሌላ” ወይም ከዚህ የተለየ አድርጎ ሊገለብጠው ይችላል። ትርጉም ከሠራ ደግሞ ከዚህ የተለየ እና የበዛ ስሕተቶችን ሊፈጽም ይችላል። 

ስለዚህ ፊሎሎጂ ማለት ከብዙ ዐመታት በፊት የተጻፈ አንድ ጽሑፍ ሲገለበጥ እና ሲተረጎም የገጠሙትን ይህን መሰል ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናት ውደ ጥንታዊነቱ የቀረበ አድርጎ ማዘጋጀት ወይም ማሳተም ማለት ነው። ይህ ኅትመት ነው ክሪቲካል ኤዲሽን የሚባለው። ይህን ሲያደርግ እጅግ ብዙ አድካሚ ሥራዎችን ይሠራል። ከዚህ ውጭ የሆኑ የተርጉም፣ የትንተና እና መሳሰሉትን ተጓዳኝ ጥናቶችን ሁሉ የሚሠራ ቢሆንም ዋናው ሥራው ግን ይህን ክሪቲካል ኤዲሽንን ማዘጋጀት ነው ማለት ይቻላል።

ሥራው በዚህ መንገድ ግልጽ ሆኖ ከሆነ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገር ምን ያህል አስፈላጊ ሥራ መሆኑን ለመራድት ብዙ የሚያስቸግር አይመስለኝም። እንዲያውም በዓለም ላይ ራሱ በዘመናዊ መንገድ የተጀመረውም መጽሐፍ ቅዱስ ግልበጣ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ነበር። ሌላው ቀርቶ ታሪኩንም ስናጠና ባሕላዊ በሆነ መንገድ አሁንም የጀመሩት የቤተ ክርስቲያን መምህራን ናቸው። ለምሳሌ ያህል የእስክንድርያው ኦሪገን ሄክሳፕላ የሚባለው መጽሐፉ ለዚህ ተጠቃሽ ነው። ሄክሳፕላ ማለት ባለስድስት አምድ ጽሑፍ ማለት ነው። እርሱ ያድረገው ምንድን ነው በዘመኑ የተለያዩ ግልባጮች ያላቸውን መጻሕፍት ችግር ለማቃለል ሲል ዕብራይስጡን በግሪክ የሚተረጉም አንድ አምድ፣ አድርጎ ሌሎቹን የተለያዩ ግልባጮች አድርጎ መስመር በመስመር የተለያዩ ግልባጮችን በማቅረብ ሠርቷል። 

ይህ የሠራው የዛሬ 1800 ዐመት ገደማ መሆኑን ስናስብ በሥራውም በሀሳቡም እንደነቃለን። በኋላም ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ አፈውርቅም በዳዊት ትርጓሜው ላይ የተለያዩ ግልባጮችን እያመጣ ያነጻጽራል። አሁን በእኛ ትርጓሜ ራሱ እንዲህ የሚል ንባብም አለ የሚል አገላለጽ ዳር እስከ ዳር ሞልቷል። እንዲህ ብሎ ያቀናል እያሉ ሁሉ ሰዋስው ያርማሉ። እንዳለ የሊቃውንቶቻችን ሥራዎች ብናያቸው በራሳቸው መንገድ ፊሎሎጂስት ናቸው ማለት እንቺላለን። ስለዚህ ፊሎሎጂ ለቤተ ክርስቲያን ምን ይጠቅማለ ከማለት ያለፊሎሎጂ ምን ልንሥራ እንችላለን ብሎ መጠየቅ ሳይቀል አይቀርም።

በአሁኑ ጊዜ ተሐድሶዎች፣ የታሪክ አጣማሚዎች፣ ሌሎችም ሳያውቁ የሚስቱ ሰዎችን ችግር በአግባቡ ለመፍታት ከተፈለገ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአግባቡ የሥራ ክፍል ሁሉ አቋቁማ ባለሞያዎች አሰባስባ በመጻሕፍቷ ላይ የሚነሱባትን ጥያቄዎች ልታቃልላበችወ ከሚያስችሏት ሞያዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ፊሎሎጂ ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሰዎች ለፖለቲካ ትኩሳት የሚቀሰቅሱባቸው እንደ ራእየ ማርያም ያሉት እና ሊሎችም ብዙ ድርሳናት ችግሮቻቸው የመጀመሮኢያዎቹ የደራሲዎቹ ሳይሆን የገለባጭ እና የተርጓሚዎች እንደሆነ ይታመናል። ገድለ ተክለ ሃይማኖትን የመሉ ብዙ ዐይነት ቅጂዎች ያላቸው ችግሩ ይሄው የገለባጮች እና የተርጓሜዎች እንጂ የመጀምሪያ ድርሰቱ ሊሆን አይችልም። አሁን ከዚህ በላይ ማለት አይቻልም እንጂ ብዙ ነገሮችን ማንሣት ይቻላል። ስለዚህ ሞያው የተፈጠርው እርሷ ውስጥ እንደሆነው ሁሉ አሁን ራሱ ለሌሎች ሊጠቅም የሚችለውም ከእርሷ በኋላ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። እኔ እስከሚገባኝ ድርስ ፊሎሎጂ ከቤተ ክርስቲያናችን ፊት ቅድሚያ የሚያስፈልገው ተቋም ሁሉ አይታየኝም። ይህ ማለት ግ ን እርሷ በአግባቡ ጥቅም ላይ ብታውለው የሌሎቹን ችግር ሁሉ እግረመንገዱን ይፈታል ለማለት እንጂ አገልግሎቱ ትንሽ ነው ለማለት አይደለም። በነገራችን ላይ ከሮም ካቶሊክ አንሥቶ ሌሎች ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናትም ሞያውን በአግባቡና በደንብ ተጠቅመውበታል።

ይቀጥላል … 

Share your love

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *