የበረኸኛው መልስ

ቆዳ አገልድሞ ፀጉሩን አንጨፍሮ በሄኖን ሸለቆ ወደሚጮኸው ሰው ሰው የሚያየውን ልይ ብዬ መጣሁ። የገባውን በቃል ያልገባውን በውኃ እያጠመቀ ይሸኛል። ደግሞ ጠያቂዎች መልሱን የሚፈሩትን ጥያቄዎች ይጠይቁታል፡፡ ይህ የሰው ጠባይ ይደንቃል። ጥያቄ ሲፈጠርበት መልሱን ይፈራል፤ የማይኖረውን መልስ ለመስማት ይጠይቃል። ሁሉንም ግን አያቆምም፤ መጠየቁንም፣ መፍራቱንም፣ አለመኖሩንም!

የተሰበሰቡት አብዛኞቹ አብርሃም አባት አለን በሚል የሚመኩ ስለነበሩ ይህ በረኸኛ ቀን መቅረቡን ነገራቸው። አብርሃም ሰው መሆኑ ካበቃ ቆይቷል። አብርሃም ሀሳብ፣ ፍልስፍና፣ ቅኝት፣ ውበት፣ ሕይወት፣ ወዘተ . . . ሆኗል አብርሃም። አብርሃም ቀርቶ አብርሃምነት ተተክቷል፡፡ 

አብርሃምነት ደግሞ አለማወቅንና የማይታወቀውን ማመን፣ በተስፋ መጽናት፣ በወጣትነትህ ከሚስትህ ገረድ በሽምግልናህ ከሚስትህ መውለድ፣ ለፈጣሪህና ለሚስትህ ቃል በመታዘዝ መሐል መሰነግ፣ ወንድምን መውደድ፣ ያለህን ምርጡን ብቻ ሳይሆን ምንም መተኪያ የሌለውን ነገር ሳታንገራግር መስጠት፣ ፈጣሪህን ላለማሳዘን ሕግን መተላለፍ ኃጢአትን መሥራት እንኳ ቢሆን አለማመንታት፣ ሕሊናህን የመጨረሻ ደስታዬና ተስፋዬ ላልከው መቃብር አድርገህ ብቻህን ማማጥ፣ የፈጣሪህ ሥውር ሸንጎ አማካሪ መሆን፣ በወገብህም የፈጠረህ ነገ የሚሆነውን ተሸክመህ መኖር፣ ድንኳንህ አርያም አንተም ቅድመ ሥጋዌ የልዑሉን አካል ለመዳሰስ መብቃት ነው አብርሃምነት። ከዚህ ተለይተው የደረቁ ነበሩ አብርሃም አባት አለን የሚሉ። አባቶቹ ወደ ሓሳብን፣ ፍልስፍናን፣ ሕይወትን፣ ቅኝትን ፣ ወዘተ . . . ወደ መወከል ወደ መሆን መሻገራቸውን ያላስተዋለ ልጅ ቅርንጫፍ ሊሆን አይችልም።

ይህ ቢያስደነግጣቸው ምን እናድርግ? አሉት። ጥንታዊቷን እያወቋት የማይኖሯትን መልስ ደገመላቸው፤ ባልንጀራን እንደራስ መውድድን! ሁለት ልብስ ያለዉ ለሌለው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ በማለት።

ቀራጮችም በጠይቁት ያንኑ ደገመላቸው፤ ባልንጀራን እንደራስ መውደድን! ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ ሲል።

ጭፍሮችም ምን እናድርግ? ቢሉት አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ ባልንጀራን እንደራስ መውደድን ደግሞ አስተማራቸው፤ በማንም ግፍ አትሥሩ ፣ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፣ ደሞዛችሁ ይብቃችሁ በማለት።

ለጥቆ እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። መንሹ በእጁ ነው፤ አውድማውን ፈጽሞ ያጠራል፤ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል ሲል ሰምቼ ከእግር ጥፍሬ እስከ ራስ ጠጉሬ የሚነዝር ስሜት ተሰማኝ። እኔ በዚያ ቃል ስቃጠል ሰዉ ግን ለውኃው ጥምቀት ይጋፋ ነበር፡፡ በረኸኛውም እንደ እያንዳንዱ መረዳት መሻቱን እየፈፀመ ሸኘው።

ከጀንበሯ ማቆልቆል ጋር የሕዝቡም ቁጥር አቆለቆለና በመጨረሻ በረኸኛው የልቡን ሐቅ ይዞ ብቻውን በረሃው መካከል ቀረ። ይቺን ሰዓት ነበርና የጠበቅሁ ወደርሱ ቀረብሁ። በአሸዋውና በጠጠሩ ላይ ስራመድ የእግሬን ዳና ቢሰማም ቀና ብሎ ለማየት አልተጨነቀም። እኔም የልቤን ለመጠየቅ ፈቃድ መጠየቅ አለስፈለገኝም። እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ በብዙ መቶዎች ዓመታት አንዴ ቢበዛ ሁለቴ የሚያጋጥም ክስተት ነው። ከአእምሮ የሚፈልቅ ጥያቄን ሁሉ እንዳቅሙ መልስ ያገኝለታል፤ የልብን ጥያቄ መመለስ የሚችሉ ልዩ ክስተት የሆኑ ሰዎች ግን እንደ ልብ አይገኙም። ለዚህ ነው ብዙ ሰው አእምሮው ነቅቶ ልቡ ሞቶ የሚኖረው፤ መልስ ስለማያገኝ።

ቀረብ ብዬ ተቀመጥሁ። ፊቱ ላይ ብርቱ ትካዜ ከታላቅ ደስታ ጋር ሲታገል አየሁት። ቃሉ ብቻ ሳይሆን ፊቱ ራሱ ቀጥሎ ሊሆን ያለውን ይተነብያል፡፡ ዕንባና ሳቅ፣ ኀዘንና ደስታ፣ ጥላቻና ፍቅር፣ ሞትና ሕይወት፣ ጨለማና ብርሃን፣ መለያየትና አንድነት፣ ወዘተ . . . ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚቀላቀሉበት ቀን ቀርቧል፤ የጊዜውን መልክ መለየት ለቻሉ።

መምህር አንዲት የልብ ጥያቄዬን እንድትመልስልኝ ነው ይህን ያህል ሰዓት ደጅ የጠናሁ አልኩት ንግግር ለመጀመር።

ዘመናቸውን ሙሉ የልባቸውን ጥያቄ ተሸክመው ያለፉ አሉና በጊዜ አትመዝነው አለኝ። አሁን ግን . . . አለና ፊቱ በጨለማው እንደ ፀደይ ጨረቃ ፈክቶ ሳይጨርሰው ዝም አለ። የሰሰተው ነገር በልቡ እንዳለ ያስታውቃል። የተሰወረች ዕንቊ አይቶ እስኪገዛት የቸኮለ ግን ምሥጢሯ ወጥቶ እንዳያጣት የሰጋ ሰውን መሰለኝ።

አላዋቂነቴን እርዳው! ግና መምህር የሙሴ ሕግ ተሰጥቶናል፤ ከአባቶቻችንም የወረዱ ብዙ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ መልካም ሥርዓቶች ተሠርተውልናል። ነገር ግን የባሕርያችን ድካም ደግሞ ወደ ኋላ ይስበናል። ጾም ይበዛብናል፣ ጸሎት ያታክተናል፣ ስግደት ያደክመናል፣ ሕጉን ለመፈጸም ዝለት በርትቶብናል፣ ሌላም ሌላም መጥቀስ እችላለሁ። ከዚህ የተነሣ የነፍስ ደስታ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ሰንሰማ ከመደሰትና ከመጽናናት ተስፋንም ከመያዝ ይልቅ ኀዘን፣ ወቀሳ፣ ተስፋ መቁረጥ ይጫነናል። ከዚህ ማረፍ እንዴት ይቻላል? 

የማንኖረውን ለምን እንሰማለን? የምንሰማውንስ መኖር ለምን ያቅተናል? ወይስ ሕጉ ቀድሞም የተሰጠን መፈጸም እንደማንችል እየታወቀ ነው? በማለት የልቤን ጭንቀት ተነፈስኩ። ቀና ብሎ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሩቅ እንደሚያይ ሰው ቀርቦ አየኝና “አንተ የፍቅርህን ያህል ፈጽም የተቀረውን ለባለቤቱ ተወው። በፍቅር በሚፈጸም ነገር ውስጥ ግዴታ የለም፣ ልግም የለም፣ ትምክህት የለም፣ እርካታ የለም፣ ድካም የለም፣ ፍርሃት የለም፣ ስጋት የለም፣ አበዛሁ የለም፣ አጎደልሁ የለም፣ ምስጋናንም ወቀሳንም መጠበቅ የለም:: በፍቅር በሚፈጸም ሕይወት ውስጥ ያለው ፍቅር ብቻ ነው:: የምትፈፅማቸውን ነገሮች ሕግ ወይም ሥርዓቶች ናቸው የሚለውን ትተህ ፍቅርን ብቻ አሰብ። የፍቅርህን ያህል ኑር! ከፍቅርህ አቅም በላይ ምንም መፈጸም አይቻልህም። ብትፈፅመው እንኳ ወይ ከማማረር አልያም ከትምክህት ሲያልፍም ከልማድ አይነፃምና ከንቱ ድካም ይሆንብሃል። እኔ በበረሃ የኖርኩ በረሃው አብሬው ለመኖር ከምፈልገው ጋር ለመሆን አመቺ ስለ ሆነልኝ እንጂ በረሃው ምቹ ስለሆነ አይደለም። ፍቅር ጊዜን ቦታንና ሁኔታን ሌላው ቀርቶ ራስህንም የማስረሳት አቅምና ባሕርይ አለው። ይህን ጥበብ ካላወቅህ ከልዑሉ ጋር ለመኖር የምታደርገው ጥረት አታካች ይሆንብሃል። በፍቅር ወጥን በፍቅር ፈጽም። በፍቅር ለተያዘ ልብ ሁሉ ይቻላል! አለኝ። ይህን የበረኸኛውን መልስ ሰምቼ የተገናኘንበት ቦታ ተለየሁት:: ዓይኑም መንፈሱም ስላልተከተሉኝ እጅግ ጥልቅ ኀዘን ተሰማኝ። ወደ መንደሬ ስመለስ ሰው ለምን መልሱን የሚፈራውን ጥያቄ ይጠይቃል? ለምንስ የማይኖረውን መልስ ለመስማት ይጠይቃል? እያልሁ እደነቅ ነበር።

ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

10 አስተያየቶች

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን!!

    ”በፍቅር በሚፈጸም ነገር ዉስጥ ግዴታ የለም”!!

  2. የምትፈፅማቸውን ነገሮች ሕግ ወይም ሥርዓቶች ናቸው የሚለውን ትተህ ፍቅርን ብቻ አሰብ። የፍቅርህን ያህል ኑር! ከፍቅርህ አቅም በላይ ምንም መፈጸም አይቻልህም። ብትፈፅመው እንኳ ወይ ከማማረር አልያም ከትምክህት ሲያልፍም ከልማድ አይነፃምና ከንቱ ድካም ይሆንብሃል።

  3. “ሰው ለምን መልሱን የሚፈራውን ጥያቄ ይጠይቃል? ለምንስ የማይኖረውን መልስ ለመስማት ይጠይቃል?”

    ቃለ ህይወት ያሰማልን፤ ረጅም እረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥልኝ።

  4. ሁሌ በኣካል ኖረን በመንፈስ እንዳንጠፋ እንዲህ ኣይነት ኣባቶችን ከመካከላችን ኣያጥፋብን።

  5. “ሰው ለምን መልሱን የሚፈራውን ጥያቄ ይጠይቃል? ለምንስ የማይኖረውን መልስ ለመስማት ይጠይቃል?”

    ቃለ ህይወት ያሰማልን፤ ረጅም እረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥልኝ።

  6. እሜን እግዚአብሔር መስገን ትልቅ ትምህርት ነው ያስተማሩን ለፈጣሪ በፍቅር መገዛት ደስ ይላል. ቃለህይወትን ያስማልን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *