ክፍል ፫
ፐሊካን {ጳልቃን}
ፍቅር ሲሰጧቸው ፍቅር መመለስ የማይቻላቸው ገላግልት ያሏት ያልታደለች ወፍ ናት − ፔሊከን። የእኛ መምህራን በትርጓሜአቸው ጳልቃን ብለዋታል። ጫጩቶቿን እጅግ አድርጋ ትወዳለች፣ አብዝታም ትታቀፋቸዋለች። እነሱ ግን ሲበዛ አስቸጋሪዎች ናቸው። ገና ክንፍ ማውጣት ሲጀምሩ ጀምሮ ፊቷን በክንፋቸው ይጸፏታል። ገና ሳያድጉ እናታቸውንም አባታቸውንም መናቅ ማቃለል ይጀምራሉ። እነሱም መከራው ሲጸናባቸው በአፋቸው ጠቅተው በጥፍራቸው ወግተው ይገድሏቸዋል።
እንደ እፉኝት ልጆች እናታቸውን ገድለው በሕይወት እንዲኖሩ አይፈቀድላቸውም። እፉኝት በፀነሰቻቸው ልጆቿ ሆዷ ተቀዶ ትሞታለች። እነሱ ይኖራሉ እሷ ለዘለዓለም ትጠፋለች። እነዚህ ደግሞ በእናትና በአባቶቻቸው ላይ ሲነሣሱባቸው እናትና አባቶቻቸው ቀድመው ያጠፏቸዋል። ወይም አንዳንድ ጊዜ በረሀብ እስኪሞቱ ድረስ ጭው ባለው በረሀ ውስጥ ጥለዋቸው ይሸሻሉ፤ የፀና ክንፍ ኖሯቸው በረው፣ የበረታ ጥፍር ኖሯቸው ምድሩን ጭረው ራሳቸውን መርዳት አይችሉምና ረሀብ ሲጸናባቸው ይሞታሉ። በእርግጥ በመጨረሻ በተለይ እናታቸው የልጆቿ መሞት ስለሚያሳዝናት በሦስተኛው ቀን መጥታ ከክንፎቿ በታች ካለው ከአካሏ ደም አፍስሳ ትቀባና ታስነሣቸዋለች።
ፊሳልጎስ ስለዚህ ዎፍ የሚከተለውን መልእክት አስቀምጧል። “መፍቀሬ ደቂቅ ውእቱ በሕቁ ወሶበ ይወልድ ወልደ ይጸፍዑ ውሉድ ገጸ ወላድያኒሆሙ ወወላድያንሂ የኀድጉ በእንተዝ ወይርሕቁ እምዐቂበ ውሉዶሙ እስከ ይመውቱ ውሉድ ባሕቱ እምድኅረ ሣልስት ዕለት ትመጽእ እሞሙ ወታንጸፈጽፍ ደመ ገቦሃ መልዕልተ ውሉዳ እለ ሞቱ ወኮኑ ውዱቃነ ዲበ ምድር ወታነሥኦሙ፤ ልጆችን ፈጽሞ ይወዳል ጫጩቶቹም በተወለዱ ጊዜ የእናትና አባታቸውን ፊት ይጸፋሉ ወላጆቻቸውም እስኪሞቱ ድረስ ይተዋቸዋል ልጆቻቸውን ከመጠበቅም ይሸሻሉ ነገር ግን በሦስተኛው ቀን እናታቸው ትመጣለች ከጎኗም ሞተው መሬት ላይ በወደቁ ልጆቿ ላይ ደምን ታፈሳለች ታነሣቸውማለች።” የሚል ተጽፏል።
በፊሳልጎስ እንደተባለው ጳልቃን የጌታ ምሳሌ ነው። ገላግልቱ {ጫጩቶቹ} የአዳምና የሔዋን ምሳሌ ናቸው። በታሪኩ ላይ እንደተረዳነው ፍቅር የጎደለው ከልጆች እንጅ ከወላጆች አይደለም። ግልገሎቹ ጳልቃኖች ለሞት በሚያበቃ ቅጣት የተቀጡት በራሳቸው ስህተት እንጅ ከወላጆች አንዳች የጎደለ ነገር አልነበረም። አዳምና ሔዋንም የሞት ሞት እስኪፈረድባቸው ድረስ የደረሱት ገጸ መለኮትን ሲጸፉ ማለትም አምላክነትን ሲፈልጉ በመገኘታቸው ነው።
ሰውን በሕይወት የሚያኖረው የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። ሞት ማለት እኮ ሌላ ነገር እንዳይመስላችሁ − የእግዚአብሔርን ፍቅር ማጣት ነው። ገሀነመ እሳትም ማለት ከእግዚአብሔር ምሕረት መለየት ነው። አዳምን ከምድር አፈር የለየው እኮ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። በአፉ እስትንፋስ ሕይወትን ባይሰጠው ኖሮ ከምድር አፈር የተለየ መሆን የሚችልበት ምን ሊኖረው ይችላል? ምክንያቱም የተሠራው ከምድር አፈር ነውና። እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ ሕይወትን ያለ ዋጋ ስለሰጠው ከምድር የተሠራ ቢሆንም ብቸኛው የምድር ሠራተኛ ሆነ ዘፍ. 2፥5። የአዳምን እና የሳጥናኤልን ያኽል ጸጋ የተቀበለ ከፍጡራን መካከል ማን አለ? ነገር ግን ቀድመው ፊቱን የጸፉት ትንንሽ ጳልቃኖች አዳምና ሳጥናኤል ናቸው።
ፍቅር ሊሰጠው የማይገባ ሰው ይኖር ይሆን? አንዳንዱ ሰው ለባርነት ምክንያት የሚሆነው ነጻነቱ ነው። አንዳንዱ ደግሞ ነጻነቱ ከፍ ላለ ቅድስና ያደርሰዋል። ቀጭኔ ልጅ ትወልድና ዞራ በምላሷ ትልሰዋለች፤ ትንሽ ቆይታ ወደ ኋላ ትዞርና በኋላ እግሯ ትረግጠዋለች መነሣት የሚጀምረው ያንጊዜ ነው። ስትልሰው ያልተነሣውን ስትረግጠው ተነሣ። አንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር ፍቅር ንስሐ መግባት ሲሳነው በእግዚአብሔር ቁጣ ንስሐ ይገባል። በጣም የሚገርመኝ በዘመናት ሁሉ የተንከባከባቸው እስራኤል ያላመኑበትን ወደዚህ ዓለም ሰው ሆኖ በሥጋ በመጣ ጊዜ ያመኑበት በዘመናት ሁሉ የተቆጣቸው አሕዛብ ናቸው።
ባሕር ከፍሎ ያሻገራቸው፣ መና በደመና የጫነላቸው፣ ውኃ ከዓለት ላይ ያፈለቀላቸው፣ በንሥር ክንፍ ጭኖ ወደ ርስታቸው የመለሳቸው፣ ጠላት አጥፍቶ ደመና ጋርዶ የጠበቃቸው እስራኤል አላመኑበትም። በግብፅ ዘመን በባሕር ያሰጠማቸው ዘፀ. 14፥27፣ በባቢሎን ዘመነ መንግሥት አውሬ ያደረጋቸው ዳን. 4፥33፣ በፋርስ ዘመነ መንግሥት በለኪሶ ሜዳ ላይ በአንድ ቀን የጨረሳቸው ኢሳ. 37፥36 አሕዛብ ግን አመኑበት። በዚያች የጭንቅ ቀን በዕለተ ዐርብ ሊያድነው ሲከራከር ያየነው ከአሕዛብ ወገን የሆነውን ጲላጦስን እንጅ ከወገኖቹ ከእስራኤል አንዱን አይደለም።
ከነሱም መካከል የበለጠ ጸጋ ያላቸው አስቀድመው የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነው እናገኛቸዋለን። ከሰው ሁሉ መርጦ የሾመው የመጀመሪያው ሊቀ ካህናት በእስራኤል ታሪክ የመጀመሪያውን አምልኮተ ጣዖት አስጀመረ ዘፀ. 32፥4። የመጀመሪያው ንጉሥ ቅዱስ ዳዊት ለመጀመሪያ ጊዜ የባልንጀራን ሚስት ለመውሰድ ባልንጀራን የመግደል ሥራ ሠራ 2ሳሙ. 12፥7። መቅደሱን እንዲያገለግሉ የተሾሙት ሰዎች መቅደሱን እንደሚያፈርሱት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል ዮሐ 2፥19። ሰዎች በገበያ ተቀምጠው ያገኟትን የእግዚአብሔር ጸጋ ካህናት በቤተ መቅደስ ሆነው አላገኟትም። ይህን ባሰብሁ ጊዜ በጣም እደነቃለሁ።
ማቴዎስ የቀረጥ ቦታ ላይ ሆኖ ያየውን ክርስቶስን ማቴ 9፥9 ቀያፋ በቤተ መቅደስ ሆኖ ስለምን አላየውም? ዘኬዎስ እሱን ለማየት ከሾላ ላይ ሲወጣ ሉቃ 19፥1 የካህናት አለቆች ከፊቱ ሹልክ ሹልክ እያሉ መውጣት ለምን ፈለጉ? ዮሐ 8፥9። ዕውራኑ ዐይን ሳይኖራቸው በፊታቸው የሚያልፈው፥ ዐይን የሚያበራው ክርስቶስ መሆኑን ሲመለከቱ ዐይን የነበራቸው ሰዎች እንዴት ይህን ማስተዋል ተሳናቸው? ማቴ 20፥29። ይህንን እና ይህንን የመሰለውን ሁሉ ባሰብሁ ጊዜ ፍቅርህ የበዛላቸው ሰዎች ለምን ይክዱሃል? ብየ እግዚአብሔርን በሀሳቤ እጠይቃለሁ።
ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆን የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ሰኞ የሚነበቡ ይሆናል::
በጣም ጥሩ ትምህርት ነው ምሳሌዎችም አስተማሪዎች ናቸው ቃለ ህይወት ያሰማልን።
እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ሕይወት ያሰማልን
መምህራችን ቃለ ህይወት ያሰማልን ድንቅ የሆነ ጽሁፍ ነው በተለይም አምላካችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ያለውን ፍቅር በሚደንቅ እና ደስ በሚል መልኩ ስለገለጹልን እና ስላሳወቁን እግዚአብሔር ይስጥልን።ነገር ግን እንዲህ ያሉ ነገሮች ቀለል ባለ አማርኛ ቢገለጽ መልካም ነው።ምክንያቱም ይሄንን ጽሁፍ ለተለያዩ ሰዎች ለማጋራት ትንሽ አማርኛው ጠጠር ያለ ነው።እዚህ ሚድያ የሚለቀቁ ጽሁፎችን ለሌሎች ሰዎች ለማጋራት እሞክራለው ግን ትንሽ ካነበቡ በኋላ ሁሉንም ባነበውም አይገባኝም ብለው ይነግሩኛል።ስለዚህ ጀማሪውንም አዋቂውንም ያማከለ አገላለጽ ብትጠቀሙ መልካም ነው እላለሁ።
አመሰግናለው
ቃለ ህይወት ያሰማልን!!!
እናመሠግንአለን።
Very educational. Bless. I learn about the bible as well as new vocabularies from your writing. Thank you.
Kalehiwot yasemalen
ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህራችን።
“ስንጠላው እርሱ አብዝቶ ወደደን፤
ስለ ፍቅሩ ሞትን ገድሎ አዳነን፤
ባርነትን ኀጢአትን ከእኛ ጥሎ፤
ነጻ አወጣን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ።”
ማቴዎስ የቀረጥ ቦታ ላይ ሆኖ ያየውን ክርስቶስን ማቴ 9፥9 ቀያፋ በቤተ መቅደስ ሆኖ ስለምን አላየውም? ዘኬዎስ እሱን ለማየት ከሾላ ላይ ሲወጣ ሉቃ 19፥1 የካህናት አለቆች ከፊቱ ሹልክ ሹልክ እያሉ መውጣት ለምን ፈለጉ? ዮሐ 8፥9። ዕውራኑ ዐይን ሳይኖራቸው በፊታቸው የሚያልፈው፥ ዐይን የሚያበራው ክርስቶስ መሆኑን ሲመለከቱ ዐይን የነበራቸው ሰዎች እንዴት ይህን ማስተዋል ተሳናቸው? ማቴ 20፥29። ይህንን እና ይህንን የመሰለውን ሁሉ ባሰብሁ ጊዜ ፍቅርህ የበዛላቸው ሰዎች ለምን ይክዱሃል? ብየ እግዚአብሔርን በሀሳቤ እጠይቃለሁ። ekoooooo kale hiwetn yasemaln
እንስሳትን ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግበ ሥጋ የፈጠረልን አምላክ ሃልዎቱን ለእኛ ያለውን ፍቅር በእነሱ ሲያስተምረን መመልከትና ወደሱ አለመቅረብ መቻል ምንኛ ከባድ እንደሆነ በዚህ ጽሑፍ መመልከት እንችላለን። በእውነቱ ከእሱ እንዳንለይ ይጠብቀን እንደ እኛ ሳይሆን እንደ እርሱ ይጠብቀን ፊቱን አያዙርብን🙏
እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ህይወትን ያሰማልን እንድናስተውል የሚያደርግ ጽሑፍ ነው!!!
Kalehiwot yasemalen
ቃለ ህይወት ያሰማልን ቃሉን ሰምተን ተግባሪ ያድርገን
ቃለ ህይወት ያሰማልን።
ቃለ ህይወት ያሰማልን!!!