በቤተ ክርስቲያናችን “መጻሕፍተ መነኮሳት” በሚል ዐቢይ ርእስ ሥር የሚታወቁና በሦስት ሶርያዉያን አባቶች ስም የተሰየሙ መጻሕፍት አሉ። እነዚህም መጻሕፍት፦ ማር ይስሐቅ ፥ ፊልክስዩስ እና አረጋዊ መንፈሳዊ በመባል ይታወቃለ። በምንኩስና እና ገዳማዊ ሕይወት ዙሪያ የተጻፉና ከውጪ ቋንቋዎች በየጊዜው የተተረጎሙ ብዙ መጻሕፍት እያሉ እነዙህ ሦስቱ ብቻ “መጻሕፍተ መነኮሳት” ተብለው ለምን እንደ ተመረጡ ግልጽ አይደለም።
ለምሳሌ ከግሪክ ቋንቋ የተለያዩ መጻሕፍት በየጊዜው በተመለሱበት በአክሱማዊው ዘመነ መንግሥት (ከ4-6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) የተተረጎመው “ሥርዓት ዘአዘዘ መልአከ እግዚአብሔር ለአባ ጳኵሚስ” 1 ፥ እንዱሁም ከ14-16ኛው መቶ ክ/ዘመን ባሉት ጊዜያት ውስጥ ከአረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎሙት ፦ “ዜና አበው ቅዱሳን ዘትሰመይ ገነተ” 2 ፣ “ዜና አበው ክቡራን አው አርብዓ ዜና ዘትሰመይ ገነተ መነኮሳት”3 ፣ “ገድለ አበው ቅዱሳን አው ገነተ መነኮሳት”4 ፣ “ነገረ አበው ቅዱሳን”5 እና “ራእይ ወምእዳን ዘአባ ነቢዪድ ዘደብረ ሲሀት”6 በመባል የሚታወቁት መጻሕፍት በውስጣቸው የያዘትን የገዳማውያን ቅዱሳን አባቶች አባባል (ብሂል)፣ ዜና (ገድል) እና የብሕትውና መልእክቶች ስንመለከት እነዚህ ሁሉ የመጻሕፍተ መነኮሳት አካል መሆን ነበረባቸው ለማለት ያስችላል።
“ማር ይስሐቅ” በሚል ርእስ የሚታወቀው መጽሐፍ፣ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ660-680 ድረስ የነነዌ ጳጳስ የነበረው የምሥራቅ ሶርያ መንፈሳዊ አባት (St. Isaac theSyrian) ድርሳናትን (ascetical homilies)7 በመጠኑ የያዘ ነው። በሶርያ ቋንቋ “ማር” ማለት “ጌታ” ማለት ሲሆን ይህ የክብር ስም ለጳጳሳት የሚሰጥ ነው። ለዚህ ነው ይህን በመከተል የመጽሐፉ ተርጓሚ “ማር ይስሐቅ” የሚለውን ርእስ የመረጠው። ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ የብህትውናን እና የጽሞና (ውስጣዊ ፀጥታ) ሕይወት በጣም የሚወድ አባት ስለ ነበር በጵጵስና መንበሩ ላይ ለ5 ወራት ያህል ብቻ ከቆየ በኋላ፣ መንበሩን ትቶ ኢራን ውስጥ ወደ ምትገኘውና “ራባን ሻቡር” ተብላ ወደ ምትታወቀው ገዳም ገብቶ ቀሪ ሕይወቱን እንዳሳለፈ ይነገርለታል። የቅዱስ ይስሐቅ ጳጳስ ዘነነዌ ድርሳናት ለማንኛውም ክርስቲያን መንፈሳዊ ሕይወት በጣም ጠቃሚ ከመሆናቸው የተነሳ በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ታዋቂነትን አትርፈዋል።
የምሥራቅ ሶርያ መነኮሳት ከማር ይስሐቅ ሥራዎች መካካል 35 ምእራፎችን የያዘ መጽሕፍ ከሶርያ ቋንቋ ወደ ግሪክ ከተረጎሙ በኋላ ይኸው መጽሐፍ በ11ኛው መቶ ክ/ዘመን ከግሪክ ወደ አረብኛ ተተርጉሟል8።
በመጨረሻም የመጻሕፍተ መነኮሳት መቅድም እንደሚነግረን ማር ይስሐቅ በአፄ ገላውድዎስ ዘመነ መንግሥት (1533-1551 ዓ.ም) “ሰሊክ ዘደብረ ሉባኖስ” በተባለ መነኮሴ ከአረብኛ ወደ ግእዝ ተመልሷል9። የግእዙ ትርጉም 34 አንቀጾች ያሉት ሲሆን “በእንተ አርምሞ (ስለ ዝምታ)” የሚል ርእስ የተሰጠው አንድ የመጨረሻ ድርሳን ይጨምራል። አንቀጾቹ በውስጣቸው፦ ፍቅረ እግዚአብሔር፣ ሥርዓተ ምጽዋት ፥ ከኃጢአት መታቀብ፣ ጾም እና የእንባ ጸጋ (ሥጦታ)፣ በእግዚአብሔር የሚገኝ ሀሴት፥ በጸሎት የተለጎመ አንደበት፥ ነዳያንን (ድኾችን) መውደድ ፣ ዓለምን መናቅ ፣ ትሕትና እና ይቅርታ ፣ ኃጢአትን ማሰብ እና ንስሐ፣ የነፍስ ንጽሕና ፣ መንፈሳዊ ተጋድሎ እና ዝማሬ ፣ አርምሞ (ዝምታ) ፣ ጽሙና (seclusion) ፣ የዝሙት ፍላጻ ፣ በትዕቢት ምክንያት የሚመጣ ፈተና ፣ የሥጋ የነፍስ እና የልብ ንጽሕና ፣ ኅሊናተ እኩያት (evil thoughts) ፣ ትዕግሥት እና ቅድስና የተሰኙ ንኡሳን አርእስቶችን ይዘዋል።
በመጻሕፍተ መነኮሳት ውስጥ ከሚገኙት ሦስት መጻሕፍት መካከል “ፊልክስዩስ” የሚል ርእስ የተሰጠው መጽሐፍ “መንበግ” ተብሎ በምትታወቀው ቦታ ጵጵስና ተሹሞ የነበረው ሶርያዊ ቅዱስ ፊልክስዩስ እንደ ጻፈው የመጽሐፉ መቅድም ይናገራል10። መቅድሙ ወደ ግሪኩ ትርጉም ቀረብ ባለ መልኩ “ፊልክስዩስ” ማለት “መፍቀሬ አኃው – የወንድሞች ወዳጅ” ማለት እንደሆነ ይነግረናል11። በመቅደሙ የተጠቀሰው የምዕራብ ሶርያ አባት Philoxenus of Mabbug (A.D. 450-523) ሲሆን የኬሌቄዶንን ጉባኤ የተቀበሉ ወገኖችን በመቃወምና የእኛን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ “Oriental Orthodox Churches” በመባል የሚታወቁት፦ የግብጽ ፣ አርመን ፣ ምዕራብ ሶርያ እና ማላንካር (የሕንድ) አብያተ ክርስቲያን የተቀበሉትን የቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያን ነገረ ክርስቶስ አብራርቶ በመጻፍ የሚታወቅ አባት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በመንፈሳዊ ሕይወት ዙሪያ የጻፋቸው ድርሳናት 12 አሉት ፤ እነዚህም ድርሳናት እስካሁን ድረስ ወደ ግእዝ አልተተረጎሙም። የተለያዩ ሊቃውንት በጥናቶቻቸው እንዲረጋገጡት በእኛ ቤተ ክርስቲያን “ፊልክስዩስ” በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ፥ ዳዲሾ ዘኳታር13 (Dadisho Qataray) የተባለና በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ የምሥራቅ ሶርያ (East Syrian/ Assyrian) መነኮስ ያዘጋጀው አንደምታ ነው። “ገነተ መነኮሳት” በመባል የሚታወቅና “ይሩማሲስ እና ጰላድዮስ”14 ያሰባሰቡት15 ወደ ግእዝ የተተረጎመ መጻሕፍ በእኛ ቤተ ክርስቲያን እንዳለ ሁሉ ፥ ይኸው መጽሐፍ ቀደም ብሎ (በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) “ኢናኒሾ” በተባለ የምሥራቅ ሶርያ መነኮስ ወደ ሶርያ ቋንቋ ተተርጉሞ ነበር። ዳዲሾ ዘኳታር በኢናኒሾ ትርጉም ላይ የጻፈው አንደምታ (commentary) በዓለም አቀፍ ደረጃ Dadisho Qaṭraya’s Compendious Commentary on the Paradise of the Egyptian Fathers በመባል ይታወቃል።16
ነገር ግን በምሥራቅና በምዕራብ ሶርያ አብያተ ክርስቲያን መካከል በነገረ ክርስቶስ (Christology) ላይ አለመግባባት ስላለ የምዕራብ ሶርያ ምሁራን የምሥራቅ ሶርያ አባት የሆነውን የዳዲሾን ስም ከመጽሐፉ ርእስ በማስወገድ በራሳቸው አባት (በፊልክስዩስ ዘመንበግ – Philoxenus of Mabbug) ተክተውታል።17 ለዚህ ነው በእኛም ቤተ ክርስቲያን የዳዲሾ ዘኳታር አንድምታ “ፊሌክስዩስ” በመባል የሚታወቀው። ይህ መጽሐፍ በአፄ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግሥት (1336-1364 ዓ.ም) ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1340-1380 ዓ. በነበረውና ካልእ ሰላማ(ብርሃነ አዜብ ወይም ካህነ አዜብ) በመባል በሚታወቀው ግብጻዊ ሊቀ ጳጳስ ከአረብኛ ወደ ግእዝ ተተርጉሟሌ።18
የዳዲሾ ዘኳታር አንደምታ፦ የጰላድዮስ ታሪክ ፣ ታሪከ መነኮሳት ዘጰላዴዮስ (Palladius)፥ታሪከ መነኮሳት ዘይሩማሲስ (Jerome) እና ብሂለ አበው (Apophthegmata) በተሰኙ 4 ክፍሎች የተከፈለ ነው። በጥያቄና መልስ (ተስእሎ ወአውሥኦ) መልኩ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ ወንድሞች መነኮሳት ለአንድ አረጋዊ አባት ያቀረቡትን መንፈሳዊ ጥያቄዎችንና መልሶቻቸውን ያካተተ ነው። የግእዙ ትርጉም አከፋፈል ወደ እንግሊዝኛ ከተተረጎመው ጋር ይመሳሰላል ፤ ነገር ግን የግእዙ አራተኛ ክፍል፦ የጸሎት ትጋት ፣ ስለ ተጋድሎ ሥርዓት ፣ ስለ ፍቅር እና ምሕረት ፣ ስለ ትሕትና ፣ የዝሙት ፈተና ፣ ስለ ንስሐ ፣ የተአምራት ሥራዎች ፣ አምልኮአዊ ራእዮች እና ስለ ሁሉም የትሩፋት ምግባሮች በሚል ንኡሳን አርእስቶች ተከፋፍሏ19።
የዚህ አጭር ጽሑፍ ዋነኛ ርእስ ያደረግሁት “አረጋዊ መንፈሳዊ” በ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ እና ልብን በሚመስጡ መንፈሳውያን ጽሐፎቹ የሚታወቀው የምሥራቅ ሶርያ መነኮስ አባ ዮሐንስ ዘዳልያታ ነው። የግእዙ ተርጓሚ “ሳባ” የሚለውን የሶርያ ቃል ይዞ ይህንኑ ቃል “አረጋዊ/ሽማግሌ” ብሎ በመተርጎም፣ እንዱሁም መጽሐፉ በዋነኝነት ስለ መንፈሳዊ ፍጹምነት ስለሚናገር ለመጽሐፉ “አረጋዊ መንፈሳዊ” የሚል ርእስ ሰጥቶታል። በእንግልዘኛም “The Spiritual Elder” በመባል ይታወቃል። ነገር ግን የመጽሐፉ ደራሲ መጠሪያ ስም John of Dalyatha (ዮሐንስ ዘዳልያታ) ነው። ስለዚህ የዚህ መጽሐፍ ሙሉ ርእስ፦ “አረጋዊ መንፈሳዊ ዘድረሰ አባ ዮሐንስ ዘዳልያታ” ቢሆን የተሻለ ነበር።
ግልጽ ባልሆነ መልኩ የመጽሐፉ መቅድም አረጋዊ የሚባለው አባት “ደብረ ኮኖብዮስ” የምታባል ገዳም ውስጥ የመነኮሰ ዮሐንስ የሚባል ወንድም እንደ ነበረው ይናገራል።20 ስለሆነም አረጋዊን እና ዮሐንስን ሁለት የተለያዩ ሰዎች ያደርጋቸዋል። ነገር ግን በሶርያ “ዮሐንስ ሳባ – Yōḥannān Sābhā” (ዮሐንስ አረጋዊ) ወይም ዮሐንስ ዘዳልያታ በመባል የሚታወቀው እ.አ.አ. ከ690-780 ድረስ በዙህ ምድር የኖረው ያው አንድ ሰው ነው። አረጋዊ መንፈሳዊ ከአረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎመው በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት (1500-1533ዓ.ም) ነበር።21
በኢራቅ ሰሜናዊ ምሥራቅ ግዛት የተወለደው ዮሐንስ (Yōḥannān) በአቃራቢያው የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፥ የሥርዓተ ቅዳሴ እና የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጽሑፎች እየተማረ አደገ።
ከመነኮሰ በኋላ ቱርክ ድንበር አጠገብ በምትገኘው ቃርዱ ገዳም ውስጥ ለተወሰኑ ዓመታት ኑሯል። አብዛኛውን የሕይወቱን ጊዜ ያሳለፈው ግን ከገዳሙ አበምኔት ፈቃድ ካገኘ በኋላ ገዳሙን ለቆ ዳልያታ (የወይራ ቅርንጫፎች) በተሰኙ ተራሮች ላይ ጸጥታ በሰፈነበት የብህትውና ኑሮ ነው።22 የዚህ አባት ድርሳናት እና መልእክታት ከአምላኩ ጋር እውነተኛ ኅብረት (theosis/ሱታፌ አምላክ) ማግኘት የሚፈልግ አንድ ክርስቲያን ሊጓዛቸው የሚገባቸውን መንፈሳዊ ደረጃዎችን እና በመጨረሻ የሚጎናጸፋቸውን ጸጋዎች ውብ በሆነ አገላለጽ ያትታል።
የእኛ አበው መተርጉማንም ከሁለቱ መጻሕፍተ መነኮሳት በተለየ መልኩ “አረጋዊ መንፈሳዊ” የመንፈሳውያን አርበኞችን መንፈሳዊ ጸጋ እና በመጨረሻ የሚደርሱባቸውን መዓርጋት እንደሚናገር ጠቁመዋል።23 ስለዚህ አባ ዮሐንስ ዘዳልያታ የኖረውን እና የደረሰበትን መንፈሳዊ መዓርግ (የብቃት ደረጃ) ነው በድርሳናቱ የጻፈልን። በቅድስና ካጌጠው ውብ እና መንፈሳዊ ሕይወቱ የተነሳ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ ኅብራት (መልኮች) ይገለጹለት ነበር።
ለምሳሌ በ30ኛው ድርሳኑ መሥዋዕተ ቅዳሴ እያቀረበ ሳለ በአምሳለ በግዕ እና በሕፃን መልክ ጌታ እንደ ተገለጸለት ይናገራል፡- “እቀድስ ዘንድ በጀመርኩ ጊዜ ስለ ሁሉ ቤዛ ራሱን የሠዋ ጌታን በማይመረመር ብርሃን በበግዕ፥ እንዱሁም በሕፃን ምስል አየሁት . . . ሳየውም ደነገጥሁ፤ አደነቅሁም። ልቦናዬ ተለወጠ፥ ነፍሴና ሥጋዬም በፍቅሩ እንደ እሳት ተቃጠለ። ከዚህ ድንቅ ነገር የተነሣ የምሠራውን አላወቅሁትም። ሌቡናዬ በፍቅሩ ስለ ተቃጠለ መልኩ ያማረ ጌታን አቅፈው ዘንድ ወደድሁ።”24
መንፈሳዊ ጸጋ የበዛለት አረጋዊው መነኩሴ አባ ዮሐንስ የተጠመቁ ክርስቲያኖች የሚጠብቃቸውን የክብር ትንሣኤ ለመነሣት በንስሐ እና እንባ፥ በጾም እና በጸሎት፥ ዝምታ በተሞላበት አንክሮ (አድናቆት) ያጌጠ መንፈሳዊ ሕይወት ሊኖራቸው እንደሚገባ በአጽንኦት ይናገራል። ለዚህም ነው 36 ምዕራፎች ያሉት የአረጋዊ መንፈሳዊ ድርሳናት አንድ ክርስቲያን ከጨለማ ገዢዎች ጋር ያለበትን መንፈሳዊ ውጊያ ተረድቶ የዲያቢሎስን ሽንገላ እየተቃወመ (ኤፌ6፡10-19) በእንባ በታጀበ የንስሐ ሕይወት የአምላኩን ፊት መፈለግ እንዳለበት በሰፊው የሚናገሩት። አርባ ስድስቱ የዮሐንስ ሳባ መልእክታት በግል መንፈሳዊ ጉዳይ ላይ የተጻፉ ቢመስልም በዋነኝነት የመንፈሳዊው ሰው ነፍስ ውበት ላይ ያተኩራል። አረጋዊ መንፈሳዊ በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ ከድርሳናት እና መልእክታት በተጨማሪ “አርእስተ አእምሮ” በሚል ርእስ በሦስት ክፍል የተከፈለ እና የሥላሴን ነገር የሚናገር ትምህርተ ሃይማኖት ይዟል።
በዚህ አጭር ጽሑፍ ስለ አባ ዮሐንስ ሳባ (አረጋዊው አባ ዮሐንስ) ድርሳናት ዝርዝር ሐተታ ማቅረብ ባይቻልም የመጽሐፉን ደራሲ ማንነት እና ከሌሎች መጻሕፍተ መነኮሳት ጋር ያለውን ኅብረት በመጠኑ ለማሳየት ሞክሬአለሁ።
ሁላችንም መጽሐፉን አንብበን ለመጠቀም ያብቃን!
የግርጌ ማስታወሻዎች :-
- ይህን የመነኮሳት የጾምና የጸሎት ሕግ ሰብስቦ የያዘ የአንድነት ገዳማዊ ኑሮ መመሪያ በግእዝ ሥነ ጽሑፍ የተካነው ጀርመናዊ ሊቅ አውጉስቶ ዲልማን ከሌሎች የተለያዩ ድርሳናትና ጽሐፎች ጋር አሳትሞታል።SeeAugusto Dillmann, Chrestomathia Aethiopica (Lipsiae, 1866) pp. 57-69
- Patericon aethiopice, ed. Victor Arras (Corpus Scriptorum Christianorum Orientalium (CSCO),Vol. 277-278, Scriptores Aethiopice 53-54) Louvain, 1967.
- Quadraginta historiae monachorum, ed. Victor Arras (CSCO, Vol. 505-506, Scriptores Aethiopice85-86) Louvain,1988.
- Geronticon, ed. Victor Arras (CSCO, Vol. 476-477, Scriptores Aethiopice 79-80) Louvain,1986.
- Collectio monastica, ed. Victor Arras (CSCO, Vol. 238-239, Scriptores Aethiopice 45-46) Louvain,1963.
- Abb Nabyud de Dabra Sihat: Visions et conseils ascétiques, ed. Robert Beylot (CSCO, Vol.377, Scriptores Aethiopice 70) Louvain,1976.
- The Ascetical Homilies of Saint Isaac the Syrian, trans. D. Miller (Boston: Holy TransfigurationMonastery) 1984.
- Tedros Abraha, “Isaac of Ninive, Filoxenus of Mabbug and John S[a]ba: Three FundamentalNames to Ethiopian Monasticism, Theology and Spirituality”, Harp 29 (2014) p.138.
- “ማር ይስሐቅ፡ መቅድም” መጻሕፍተ መነኮሳት፡ ማር ይስሐቅ ፤ ፊልክስዩስ (ገብረክርስቶስ) ፤ አረጋዊ መንፈሳዊ (አዲስአበባ፡ ተስፋ ገብረሥላሴ ማተሚያ ቤት፡ 1988 ዓ.ም.) ገጽ 2.
- “ፊልክስዩስ፡ መቅድም” መጻሕፍተ መነኮሳት፡ ማር ይስሐቅ፤ ፊልክስዩስ (ገብረ ክርስቶስ)፤ አረጋዊ መንፈሳዊ (አዲስ አበባ፡ ተስፋ ገብረሥላሴ ማተሚያ ቤት፡1988 ዓ.ም) ገጽ 9.
- Philexenus የሚለው የግሪክ ቃል Lover of foreigners (የውጭ ሰዎች/የእንግዶች ወዳጅ) የሚልትርጉም አለው።
- The Discourses of Philoxenus of Mabbug, trans. Robert A. Kitchen (Collegeville, MN: Cistercian Publications, 2013).
- ይህ አባት እስካሁን ድረስ “ኳታር” በመባል የምትታወቀው አገር ተወላጅ ነው። የራባን ሻቡር ገዳም መነኮስ ሲሆን “ገነተ መነኮሳት” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ እና በአባ ኢሳይያስ ዘአስቄጥስ ድርሳን ላይ በጻፋቸው አንድምታዎች ይታወቃል።
- እነዚህ ሊቃውንት በእንግሊዝኛ Jerome and Palladius በመባል ይታወቃሉ።
- “ፊልክስዩስ፡ መቅድም” (ተስፋ ገብረሥላሴ ማተሚያ ቤት፡ 1988 ዓ.ም) ገጽ 8.
- ለምሳሌ በእንግሊዘኛ እና ጋርሹኒ ቋንቋዎች የተዘጋጀዉን መጽሓፍ ይመልከቱ። Dadisho Qaraya’s Compendious Commentary on the Paradise of the Paradise of the Egyptian Fathers in Garshuni, eds. And trans. Mario Kozah, Abdulrahim Abu-Husayn and Suleiman Mourad (New Jersey: Gorgias Press, 2016).
- Witold Witakowski, “Filekseyus, the Ethiopic Version of the Syriac Dadisho Qatraya’sCommentary on the Paradise of the Fathers”, Rocznik Orientalistyczny 95/1 (2006) p.286.
- “ፊሌክስዩስ፡ መቅድም” (ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት፡1988ዓ.ም) ገጽ 8.
- የክፍል አራትን መነሻ እና በውስጡ የያዟቸውን ጥያቄዎችና መልሶች ፊሌክስዩስ (ተስፋ ገብረ ሥሊሴ ማተሚያ ቤት፡ 1988 ዓ.ም.) ከገጽ 67-246 ያለውን ይመልከቱ።
- “አረጋዊ መንፈሳዊ፡ መቅድም” መጻሕፍተ መነኮሳት፡ ማር ይስሐቅ፤ ፊሌክስዩስ (ገብረ ክርስቶስ) ፤ አረጋዊ መንፈሳዊ (አዲስ አበባ፡ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያቤት፡ 1988 ዓ. ም.) ገጽ 3.
- አረጋዊ መንፈሳዊ ፤ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት፡1988 ዓ.ም.፤ገጽ 371.
- See “Introduction,” The Letters of John of Dalyatha, trans. Mary T. Hansbury (New Jersey:Gorgias Press, 2006) p. vii.
- “አረጋዊመንፈሳዊ፡መቅድም” (ተስፋገብረሥላሴማተሚያቤት፡1988 ዓ.ም) ገጽ 6.
- አረጋዊ መንፈሳዊ (ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት፡1988 ዓ.ም) ገጽ 168-169.
- የ34ኛውንድርሳን ሙሉ ይዘት አረጋዊ መንፈሳዊ (ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት፡1988 ዓ.ም.) ከገጽ 189-196ይመልከቱ።
መጽሀፈ መነኮሳት ከላይ የተጠቀሱትን ብቻ ነዉ የሚይዘው ወይስ ሌሎችንም ይጨምራል ?
እጅግ ደስ የሚያሰኝ እና በጣም ጥሩ የሆነ ነገር ነው የምትሰሩት በተለያዩ መጽሐፍትም ብትቀጥሉበት ጥሩ ነው በሌላው በኩል ግን ስለ ገዳማት እና አድባራት የሚዳስስ ዝግጅቶችን ጽሑፎችን ብታዘጋጁ እና ስለ ኢትዮጵያ አድባራትና ገዳማት እንድናውቅ ብታደርጉን መልካም ይመስለኛል።በተረፈ የምትሰሩት ሥራ ሁሉ እጅግ እጅግ የሚያስደስት ነው የብርሃን እናት ትስጥልን🙏🙏🙏
መድኃኔ አለም ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ በመጣ ጊዜ ዘወትር የምንናፍቅለትና በተስፋ የምንጓጓለትን የህይወትን ቃል ፥ ብዙዎችን በሳበውና በማረከው ጥዑም አንደበቱ ያሠማልን ፥ ከእርሱ ጋራም ለዘለአለም ይኖሩ ዘንድ የተስፋይቱን አዲሲቷን ሰማይና አዲሲቷን ምድር መንግስቱን ያውርስልን ። አገልግሎቶን ይባርክልን ።
በእውነት ነው የምሎት ፥ ስለ እነዲዝህ አይነት ነገር ምንም እውቀቱ አልነበረኝም ። እኒህም መጻህፍት ከየት ይምጡ አይምጡ ፥ ብቻ መምህራን ሲጠቅሷቸው ነበር ይምሰማው ። አሁን ግን ቢያንስ ማን እንደጻፋቸውና መቼ እንደተጻፉ እውቅናው አለኝ ። እናመሠግናለን መምህር 🙏🙏🙏
ስለጸሐፊዎቹ እንድንረዳ እንድናውቅ ስላደረገን እናመሰግናለን።
በጥቂቱ ስለ መፃሕፍቱ ይዘት ተጠቅሷል እና ሚገልፁት መነኮሳት ብቻ ሳይሆን ሰብዐ አለምም ለፈፅሙት ሊተገብሩት ሚገቡ ጉዳዮችን ነው እና ለምን መፅሐፈ መነኮሳት ተብለው ተጠሩ?
መልካም ነው ተመችቶናል
እግዚአብሔር ይስጥልን ፣ ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
ከተቻለ ቢያንስ አንዱን መፅሐፍ በሶፍት ኮፒ ብታጋሩን?
እግዚአብሔር ይስጥልን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ስለ ሰባቱ የጸሎት ጊዜ ማብራሪያ ብትሰጡን
በጣም ነው የወደድኩት። አሪፍ ጽሁፍ ነው። ወደ ሰረገላው ለመቅረብ ለመጠየቅ እንደ እናንተ ለማገልገል እናፍቃለሁ። በጸሎት አስቡኝ። መምህራችን ቃለ ህይወት ያሰማልን። እንደ መደበኛ ጽሁፍ ብቻ ሳይሆን እንደ ጥናታዊ ጽሁፍ ነው ያነበብኩት። የPhiloxenus of Mabbugንን ጸረ ኬልኪዶን ሲሉት ስለምሰማ ማንነቱን ለማወቅ በጣም እፈልግ ነበር እና የኛ ፊሊክሲዮስ መሆኑን ሳውቅ በጣም ደስ ብሎኛል።
በሚቀጥለው ዶ/ር ቀሲስ መብራቱ ስለ Miaphysite, Monophysite and Dyephysite ልዩነት ቢጽፉልን ብዬ እመኛለሁ።
ይቅርታ ተመለስኩ. . እነዚህ ጽሁፎች በEmail እንዲደርሱን ቢደረጉ መልካም ነው።