መጽሐፈ ጦቢት በደስታ የሚጠናቀቅ ታሪክ ያለበት መጽሐፍ ነው። ታሪኩ እንደ ልዩ የሥነ ጽሑፍ ድርሰት አንባቢውን በሀሳብ ዓለም ውስጥ እንዲዋኝ የሚያደርግ ነው። በሐዲስ ኪዳን ቀጥታ ሲጠቀስ ባናገኝም ከሐዲስ ኪዳን መጻሐፍት ጋር በእጅጉ የተያያዘ የነገረ መለኮት አሳቦች አሉት። ታሪኩ የሰው ልጅ በመከራ ዘመን እንዴት መኖር እንዳለበት እና የእግዚአብሔር ሰዎች በመከራ ውስጥ ሲሆኑ በምን አይነት አኗኗር ሕይወታቸውን ሊመሩ እንደሚገባ ከጥልቅ ምክሮች ጋር ያስነብበናል። በዚህ ጽሑፍ በመጽሐፈ ጦቢት የተገለጠው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በጥቂቱ እንመለከታለን።
መጽሐፈ ጦቢት የሚጀምረው ከነገደ ንፍታሌም የዘር ሐረግ የጦቢትን ትውልድ ቆጥሮ ነው። እንደ ስሙ ጦቢት የመልካም ቤተሰብ መሪ ነው። ሚስቱ ሐና ስትባል ጦቢያ የተባለ ልጅም ወልደዋል። በግዞት ምድር ጦቢትን በመጽሐፉ እንተዋወቀዋለን። በእርግጥም የጦቢት ማንነት ክፉ ዘመንን ለማለፍ ሊኖረን የሚገባ የሕይወት ስንቅ የያዘ ነው።
በፋርስ ወዳለች ወደ ነነዌ ከወረደም በኋላ እግዚአብሔርን ማሰብ የሕይወቱ መሠረት አደረገ። ለእግዚአብሔር ሕግ በመገዛት ለወንድሞቹ ምጽዋትን ያደርግ ነበር። ከአምልኮተ ጣኦት ራሱን ለይቶ ወገኖቹ ሁሉ በተማረኩበት ዘመን ሊበሉ የማይገባውን እህል ሲበሉ እርሱ ግን ከአሕዛብ እህል እንዳይበላ ሰውነቱን ጠበቀ። በበዓለ መጸለት እና ሠዊት ብቻውን ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ ለአምላኩ መሥዋዕትን ያቀርብ ነበር። አብረውት ለተሰደዱት ወገኖቹም ምጽዋትን ያደርግ ነበር። በጽድቅና በቅንነት እውነተኛ ሆኖ የኖረ ሰው ነውና በግዞት በመከራ ዘመን ቢሆንም ከእርሱ የሚጠበቁትን መልካም ነገሮች ሁሉ ለመያዝ የጣረ ሰው ነበር።
በፋርስ ወዳለችው ወደ ነነዌ ከተማረኩ በኋላ እግዚአብሔር ለጦቢት በንጉሱ ስልምናሶር ፊት ሞገስን ሰጠው። አለቃ አድርጎም ሾመው። ስልምናሶር ሞቶ ልጁ ሰናክሬም በነገሰ ጊዜ የጦቢትን መልካም ስራ በተለይ ደግሞ የሞቱ ሰዎችን ይቀብር እንደነበር በሰማ ጊዜ ገንዘቡን ወርሶ ሞት ፈረደበት። ጦቢት ለሃምሳ አምስት ቀናት ተደበቆ ቆየ ንጉሱ ሰናክሬም እንደሞተ ልጁ እስራደን እንነገሰ በሰማ ጊዜ ጦቢት ከተደበቀበት ወጥቶ ወደ ቤተሰቦቹ ተመለሰ።
ጦቢት ወደ ቤተሰቦቹ ከተመለሰ በኋላ በዓለ ጰንጠቆስጤን ለማክበር በማዕድ ተቀመጠ። እግዚአብሔርን በማሰብ በበዓል ደስታን ሊያደርግ ልጁን ጦቢያን ወደ መንገድ ወጥቶ ከወገኖቻቸው ሰው ይዞ እንዲመጣ ላከው። ልጁ ጦቢያ ሲመለስ ግን ክፉ ዜና ነው ይዞ የተመለሰው።
“አባቴ! ከወገኖቻችን የተገደለ አንድ ሰው አገኘው ሬሳውም በገበያ ወድቋል” አለው። ጦቢት የሞተ ሰው በገበያ ወድቆ እርሱ ሊመገብ አልወደደም። እህሉን ሳይቀምስ የሞተን ሊቀብር ወጣ። (አስከሬን አፈር ሳይቀምስ እህል አንበላም የሚባለው ትውፊት ከዚህ የመጣ ነው)
በዓሉ ወደ ኀዘን ደስታውም ወደ ለቅሶ ተመለሰ። አለቀሰለት ፀሐይ በገባች ጊዜም መቃብር ቆፍሮ ቀበረው። ይህን የተመለከቱ ጎረቤቶቹ ተሳለቁበት:: እርሱ ግን ንጉሥ የገደለውን በመቅበር ንጉሡን ሳይሆን እግዚአብሔርን ፈርቷልና። ጦቢት በዚህ ተግባሩ ወደ ሞት መቅረብን አልፈራም። ለሞቱ ሰዎች የሚደረግ እንክብካቤን ሬሳዎችን ሰብስቦ እርቃናቸውን ሸፍኖ በሥርዓት በመቅበር በእምነት ለሰው ልጅ ሊሠጥ የሚገባውን ክብር በምሕረት ተግባሩ አስተማረ።
በዚያች ምሽት ጦቢት ረክሷል:: የማንጻት ሥርዓትን ሳይፈጽም ወደ ቤቱ ገብቶ ማደር አይችልም ነበር። በቅጽሩም አዕዋፋት እንዳሉ አላስተዋለም ነበርና ፊቱን ገልጦ በውጪ ተኝቶ ሳለ ኩሳቸውን ዐይኑ ላይ ጣሉበት። ዐይኑ በልዞ በጽኑ ታመመ። ወደ ባለ መድኃኒቶች ቢሄድም የረባ የሚጠቅመውን መድኃኒት አላገኘም። ለሁለት ዓመታትም ዐይኖቹን አጥቶ ከቤቱ ተቀመጠ።
ሚስቱ ሐና ወጥታ በሰዎች ቤት እያገለገለች ለቤተሰብ ገንዘብ ማምጣት ጀመረች። ከደሞዟ ጭማሪ አንድ የበግ ግልገል ተሰጧት ወደ ቤት ይዛ ስትመጣ ጦቢት አላመናትም:: የተሰረቀ ከሆነ መልሺ የተሰረቀ መመገብ ተገቢ አይደለም አላት። ሚስቱ ሐና “ጸሎትና ምጽዋትህ ወዴት አለ? እነሆ በላይህ ያለው ሁሉ ታወቀ” አለችው። አስጨናቂ ንግግር ነው። ጦቢት አዘነ አለቀሰ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ።
ሐና ለባሏ ጥሩ ነገር ያደረገች ይመስላል ጠንካራ አንደበቷ ጦቢትን ወደ ጸሎት መርቶታል። ጻድቅ ሰው ነውና በመከራ ውስጥ ሆኖ በጸሎቱ ‘አንተ ፍትሐዊ አምላክ ነህ’ በማለት በመከራ ጊዜ በእምነት ልመናውን አቀረበ ። በጸሎቱ ስለ እርሱ ብቻ አይደለም ስለህዝብ እና ስለ አባቶቹ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ምሕረትን ለመነ ዘለዓለማዊ ዕረፍትን ጠየቀ።
ታዲያ ጸሎቱ ብቻውን ወደ እግዚአብሔር አልደረሰም በክፉ ንግግር ምክንያት ወደ አምላኳ በጸሎት እየጮኸች ከነበረች ሣራ የምትባል ሴት ጋር እንጂ።
እንደ ጦቢት ስትጸልይ የነበረች በሜዶን ክፍል በጣኔስ የራጉኤል ልጅ የሆነች ሣራ የምትባል ሴት ነበረች። አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን አድሮባት ሰባት ባሎቿን ገድሎ በኀዘን ውስጥ የምትኖር ነበረች። በአባቷ ቤት ውስጥ ያሉ አገልጋዮችም በእርሷ ምክንያት በተፈጠረው ኀዘን ‘እንደ ባሎችሽ አንቺም በሞት ሂጂ’ ብለው ተናገሯት።
ሣራ ወደ ሰገነት ወጥታ ወደ አምላኳ ጸለየች። እግዚአብሔር የሁለቱን ሰዎች ጥሪ ሰማ። ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሩፋኤልን ወደ እነርሱ ላከ። ሩፋኤል የስሙ ትርጓሜ እግዚአብሔር መድኃኒት ነው ማለት ነው። ሐኪም የሚያስፈልገው ለታመመ እንጂ ለጤነኛ አይደለምና ጌታ አይሁድን ከታመሙበት የዕውቀት ጨለማ እና አለማመን አህዛብን ደግሞ ከጣዖት አምልኮ ለማዳን ወደ ዓለም እንደመጣ ጌታውን በሚመስል አመጣጥ መልአኩ በሰው አምሳል ስሙ አዛርያ ተብሎ የጦቢትን ዐይኑን ለማብራት ሣራን ደግሞ ከጋኔን ሊያድናት በመካከላቸው ተገኘ።
ጦቢት በጸሎት እግዚአብሔርን ከጠየቀው በኋላ ልጁን ጦቢያን ጠርቶ መከረው። ምክሩ ጥልቅ ወላጆች እንዴት ለልጆቻቸው አርአያ ያለው ህይወትን እንደሚያወርሱ የሚያስተምር ምክር ነው።ጦቢት በስጋ ዐይኑ ማየት ባይችልም ልጁን እንዴት በሕይወት ብርሃን እንደሚገኝ ይመክረዋል። ጦቢያም እንደአዘዝከኝ አደርጋለው ብሎ ከተቀበለ በኋላ አባቱ በሜዶን ክፍል በራጌስ ከገባኤል አደራ ያስቀመጠውን ገንዘብ እንዲያመጣለት ይልከዋል። ሀገሩን የሚያውቅ በመንገድም አብሮት የሚጓዝ ሰው ሲፈለግ በቅርብ አዛርያ ተብሎ በሰው አምሳል ቅዱስ ሩፋኤል ተገኘ። ክፍያም ተስማምተው መንገዳቸውን ጀመሩ። እናቱ ሐና የልጇን መሄድ ጠልታዋለች በእንባ ጦቢትን ለምን ልጁን እንደላከው ወደ ሩቅ ሀገር እየከሰሰች ጦቢት በእምነት ሆኖ ተመልክቷልና የእግዚአብሔር መልአክ እንደሚጠብቀው እየነገረ ያጽናናታል።
ቅዱስ ሩፋኤልና ጦቢያ ጉዟቸውን በቤት ውሻቸው በመታጀብ ከጀመሩ በኋላ ምሽት ላይ ከፈሳሽ ውሀ አጠገብ ደረሱ። ጦቢያም ሊታጠብ በወረደ ጊዜ ዓሣ ተጠጋው ቅዱስ ሩፋኤልም ‘ይህን ዓሣ ያዘው’ አለው። ይዞ ወደ ምድር አወጣው። ሥጋውንም ከተመገበ በኋላ ልቡን ጉበቱን ሐሞቱን እንዲይዘው ነገረው። ሰይጣንን ድል ለማድረግ ይጠቀሙበታል። ጦቢያ ለአባቱና ለወደፊት ሚስቱ ለሣራ መድኃኒት መያዙን ገና አላወቀም። ጉዞአቸውን ቀጠሉ ወደ ራጉኤል በደረሱ ጊዜ ወደ ቤት ገብታ ልጁ ሣራ በደስታ አስተናገደቻቸው። ቅዱስ ሩፋኤል ጦቢያን ሣራን እንዲያገባት ነገረው። ሰባት ባሎችዋን አስቀድሞ የገደለባትም ጋኔን በጸሎት እና የዓሥውን ልብና ጉበት በማቃጠል ሲጨስ ተሸንፎ እንደሚጠፋ ነገረው፡። ጦቢያም መመሪያውን ተቀብሎ እንደተባለው አደረገ ጦቢያና ሣራ በሰላም ተጋቡ።
የሰርጉ በዓል ከተጠናቀቀ በኋላ አባቱ የላከውን የአደራ ገንዘብ ለማምጣት መንገዳቸውን ቀጠሉ። ጦቢያ አሁን ሚስቱ ሣራን የአባቱን የአደራ ገንዘብ ይዞ ከመልአኩ ጋር በመዘግየቱ በጣም ያስቡና ይጨነቁ ወደነበሩት ወላጆቹ ተመለሰ። መልአኩ በነገረው መሠረት የአባቱን ዐይኖች በዓሣ ሐሞት ኳላቸው። ከአራት ዓመታት በኋላም ዓይነ ብርሃኑን አገኘ። ደስታ ሆነ እግዚአብሔር ድንቅ ስራን በመካከላቸው ሠርቷልና አመሰገኑ። የተፈጸመው ይህ ድንቅ ስራ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ አስቀድሞ የተነገረ ምሳሌ ነው።
ዓሣ በግሪክ ቃሉ ሲተነተን ይህን ይወክላል። ΙΧΘΥΣ Ιησούς (Jesus-ኢየሱስ) Χριστός (Christ- ክርስቶስ) Θεού (God’s-የእግዚአብሔር ) Υιός (Son-ልጅ) Σωτήρ (Saviour-መድኃን)” ክርስቲያኖች በመጀመሪያዎቹ ክፍለ ዘመናት ጌታችንን ለመወከል ቃሉን ይጠቀሙበት ነበር። ዓሣው ለሁለቱ ሰዎች መድኃኒት እንደሆናቸው ማዳን እና ድል በዓሥ በተመሰለው በኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሆኑ ምሳሌ ነው።
በመሸ ጊዜ የደረሱበት ውሃ በአንድ ቦታ ረግቶ ያለ ውሃ ሳይሆን ሂያጅነቱ የሚጠቁመው ፈሳሽ ውሃ ነው። ሕይወት ያለበት መሆኑን ለመጠቆም ነው። መድኃኒት የሆነው ዓሣ – ኢየሱስ ክርስቶስ በፈሳሽ ውሃ ከተመሰለው የህይወት ምንጭ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ ምሳሌ ነው። ይህ የውሃ ፈሳሽ በህይወት የተመላ እንደሆነ ለመጠቆም ጥንታውያን ስዕሎች በዓሣ ሙላት ይስሉታል።
ለመድኃኒትነት የተመረጡትን የዓሥው ብልቶች ልብ እና ጉበት ከደም ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ደም በመሥዋዕት ስርዐት ላይ ያለው ስፍራ ትልቅ ነው። በመሥዋዕቱ ላይ የሰው ህይወቱ በደም ተወክሏል (ዘሌ 17:11)። በመሥዋዕቱም ዋና ጉዳይ ሕይወታችንን ወደ እግዚአብሔር ማቅረባችን ነውና ደም ከመሥዋዕቱ ጋር ተነጣጥሎ አይነገርም።(ዕብ 9:22) በእነዚህ ከደም ጋር ግንኙነት ባላቸው ብልቶች ነው ሣራ ላይ ያደረውን ጋኔን ድል የተደረገው። በደሙ የኃጢአትን ስርየት ያገኘንበትን (ቆላ1:13) በደሙ ፈሳሽነት እኛን ከሰይጣን ባርነት ነጻ የወጣንበት ለክርስቶስ የማዳን ሥራ ምሳሌ ነው። መጤሱም ፣ ዕጣን ምሳሌነቱን ጨምረን እንመለከታለን። ዕጣን የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የተወደደ መሥዋዕት ሆኖ ለአባቱ የቀረበ።
ሌላው የዓሣው አካል የጦቢትን ዐይን ለመፈወስ የተጠቀሙበት ሐሞት ነው። ሐሞት የቅዱስ ወንጌል ምሳሌ ነው። ሐሞት ቆምጣጣ ነው።የክርስቶስን ቅዱስ ወንጌል የተቀበሉት በመከራ ውስጥ እንደተቀበሉት ማሳያ ነው።በብዙ ትዕግስት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በግርፋት፣ በእስር፣ በግፍ፣ በህመም፣ በጾም…የተሰበከ ወንጌል ነው።”(ሐዋ 4:18 2ኛ ጢሞ 3:12) በዓለም ሳለን የወንጌልን በመከራ ውስጥ የምንኖረው ቢሆንም እኛን ወደ ዘለዓለማዊ ብርሃን የምንመራበት ነው።
በአጠቃላይ በመጽሐፉ የምንመለከተው ምስል ላይ ስናተኩር -አባት-ልጅ-መልዕክተኛ-ወንጌል-ሰርግ-ፍጥረት። በትክክል እዚህ ምን እንረዳለን? ይህ መጽሐፍ በክርስቶስ የማዳን ሥራ በትንቢታዊ ምሳሌነት አባት በላከው ልጅ የተፈጸመ ተግባር በልጅ በተያዘ የድል ዜና ወንጌል ። በወንጌል መጨረሻም የምናገኘው ሰርግ። ከዚህ ሁሉ ስራ ጋር የፍጥረት መከተልን መስማማትን እንመለከትበታለን። በእውነት መጽሐፈ ጦቢት ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰበከበት መጽሐፍ ነው።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
የጦቢትን ዐይን ያበራው ቸሩ መድሃኔዓለም የእኛንም 0ይነ ልቦና ያብራልን ፤ ቅዱስ ስጋውና ክቡር ደሙን ለመቀበል የበቃን የተዘጋጀን ያድርገን። ቃለ ህይወት ያሠማልን።
ቃለ ህይወትያሰማልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያስምዕ ለነ
ቃለ ህይወት ያሰማልን።!!
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
Kalhetewaten yasmalen manegesta samayaten yawerselen
አሜን ቃለ ሕይወት ያሰማልን የአገልግሎት ዘመን ያርዝምልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን!
ማቃለል ህይወትን ያሰማልን
ቃለ ህይወትን ያሰማልን
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን። በእውነት በመጽሐፈ ጦቢት ውስጥ ያለውን የጌታችንን የማዳን ሥራ የሚያሳይ ትንቢት በዚህ መልክ መቅረቡ ያስደስታል። እንዲሁ የመልአኩን የቅዱስ ሩፋኤልንም ተዓምር እንድናስታውሰው በተጠናቀረ መንገድ የቀረበ ጽሑፍ ነው። አንብበን ደግሞ ለሕይወት ያድርግልን🙏💐
ቃለ ህይወትያሰማልን