ወደ ላይ መውጣትን ማን ይጠላል? ከሁሉ በላይ መሆንንስ የማይሻ ማን ነው? ስለሌሎች መዳን ለሚጨነቁ ሰዎች ካልሆነ በቀር ከልዕልና ወደ ትሕትና መምጣት ከባድ ነው። ዲያብሎስ እንጦርጦስ የወረደው ክብር ቢጎድልበት ነው። አዳም ወደዚህ ዓለም የመጣው ከገነት ቢሰደድ ነው። ናቡከደነፆር በሕይወት ሳለ ዙፋኑን ለልጁ ለዮርማሮዴቅ የለቀቀው ሰው መሆን ቢሳነው ነው ዳን 4÷33። ማንኛውም ሰው ወደ መቃብር የሚወርደው ነፍስ ቢለየው ነው።
ወዶ ፈቅዶ የወረደ ማነው?
መውረዱ ለሌሎች ወደ ላይ መውጣት ምክንያት ይሆን ዘንድ የወረደ ማነው? እንዲህ ያለ መውረድን የወረደ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እንጅ ሌላ ማንም የለም። ራሱን በፈቃዱ ዝቅ አደረገ። ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ የሰው ባሕርይ በላይ በሰማይ ቦታ አግኝቶ ታየ።
እንዲህ ነው መውረድ!
አንተን ፍለጋ የወረደውን አምላክ ከፍ ካለው ምንጣፍህ ወርደህ ፈልገው። ወደ ታች በወረደ ጊዜ ያገኘው የሰውን ባሕርይ እንጅ የመላእክትን ባሕርይ አልነበረምና ከላይ ያለውን የመላእክትን ባሕርይ ሳይሆን የታችኛውን የሰውን ባሕርይ ተዋሐደ። ወንድሜ! እግዚአብሔር እንዲዋሐድህ ከላይ ልሁን አትበል። ዝቅ ባልህ ቁጥር ለእግዚአብሔር ቅርብ ትሆንለታለህ።
እግዚአብሔር አድሮብህ እስኪያነሣህ ድረስ እነሣለሁ አትበል። የፈጀውን ያህል ዘመን በታችኛው ዓለም ብትቆይ እንጅ በራስህ ጥረት ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ሊሰጥህ አይችልም። የሰው ልጅ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስምን የተቀበለው፣ ጉልበት ሁሉ እንዲሰግዱለት የሆነው፣ መኳንንት ደጅ ከፍተው የተቀበሉት እግዚአብሔርን ደጅ ጸንቶ በተደረገለት መነሣት ነው።
እንዲህ ነው መውረድ!
መውረድን ካወቅንበት ዕርገትን አናጣትም። ከዕርገት የሚቀድመው መውረድ ነው። “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” ዮሐ 3÷13 ተብሎ ተጽፏልና።
ከእግዚአብሔር ጋር የሚያርጉ ከእግዚአብሔር ጋር የወረዱ ሰዎች ናቸው። እግዚአብሔር ለሰው ብሎ ከወረደ ሰውም ለእግዚአብሔር ብሎ መውረድ አለበት። ስለእግዚአብሔር ብለህ ውረድ ከድሆች ጋራ ተቀመጥ።
ስለ እግዚአብሔር ብለህ ውረድ የበደሉህን ሰዎች በደላቸውን ተውላቸው።
ስለ እግዚአብሔር ብለህ ውረድ የሚሰጡህ ለሌላቸው ራስህን ስጣቸው።
ስለ እግዚአብሔር ብለህ ውረድ አንተ ሙተህ ሌሎችን አድናቸው።
የዓለም ብርሃን አንተ ነህ ብሎ ቢሾምህ÷ ጊዜ ስትቀጥር መውረድ ተስኖህ ስንቶቹ ዕውራን ሁነው ቀሩ።
በዚያ መንገድ ማለፍ ሲገባህ ዘኬዎስ ሾላ ላይ እንደተሰቀለ ‘’ፈጥነህ ውረድ” የሚለው ጠፍቶ ይሄው እስካሁን አለ። በኢያሪኮ መንገድ ያሉ ዕውራን አሁንም እግዚአብሔርን አላዩም። የሚድኑ ሰዎች ባሉበት መንገድ ሳይሆን ላንተ በሚስማማህ መንገድ ብቻ ነው የምትጓዘው። ታዲያ እግዚአብሔር ካንተ ጋር እንዴት ሊሠራ ይችላል?
መጽሐፍ የምትጽፈው ለብልጽግና፣ መዝሙር የምትዘምረው ለዝና፣ የቤተ ክርስቲያንን ሹመት የምትፈልገው ለዕውቅና የምታደርገው ሁሉ ሰዎችን ማዳንን ማዕከል ያደረገ አይደለም። አንተ ቀትር ነው ብለህ ተኝተህ ሣምራዊት የሕይወት ውኃ ሳትቀዳ ተመለሰች። ‘’ከኃጢአተኞችና ከቀራጮች ጋር ይበላል’’ ይሉኛል ብለህ ስንት ቀራጮች ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ሲገባቸው የራስህን ክብር በማስቀደምህ ብቻ ከነኃጢአታቸው በሞት ተወሰዱ? እግዚአብሔር ስላንተ ከወረደ አንተም ልትወርድ ይገባሃል።
አውቃለሁ! የኛ ሰው ከወረዱለት መስቀል ያሸክማል፣ ጋኔን አለበት ብሎ ይሳደባል፣ ከተራራ ላይ ቁልቁል ካልወረወርሁ ይላል፣ ግሩም ትምህርት ብታስተምሩትም ትምህርቱን ሳይሆን እናንተን ወደ መመርመር ይዛወራል፤ ማን አስተማረው፣ ከየት ተማረው፣ ይህ የጠራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? እናትና አባቱንስ እናውቃቸው የለም? ማለት ያበዛል። ከወረዱለት መቃብር ሳያገባ የማይመለስ ክፉ ሰው በዓለም ላይ መኖሩን ረስቸ አይደለም። ጥቂት ቢሆኑም ዓለም እስካሁን ሳያልፍ የሚጠባበቃቸው ወደፊት የሚመጡ ጻድቃን ስላሉ ለእነርሱ ብየ ነው እንጅ።
ዓለም የሚኖረው ለጥቂት ጻድቃን ሲባል ነው እንጅ ስፍር ቁጥር ስለሌላቸው ኃጥአን ተብሎ አይድለም። ጥቂት ጻድቃን ባይኖሩማ ሰዶምና ገሞራን በሆንን ነበር። ብዙ ኃጥአን ይረግጡኛል ብለህ ጥቂት ጻድቃንን ወርደህ ከማዳን እንዳትዝገይ። ተጉህ ገበሬ አሳምሮ ባረሰው መሬት ላይ የእንክርዳድ መብቀል ይገርማል! የገበሬው ዓላማ ለስንዴው እንዲስማማው እንጅ ለእንክርዳዱ ብሎ አልነበረም። አጥር ያጠረው ጠባቂ የሾመው ለስንዴው ብሎ እንጅ ለእንክርዳዱ አልነበረም። እንዲያውም ለስንዴው ብሎ ታግሦ እንጅ ለእንክርዳዱ ሲል በእርሻው ላይ እሳት መልቀቅ ያምረዋል። ግ ን ምን ይደረጋል ለስንዴው ሲባል በተጠበቀ እርሻ ውስጥ እንክርዳዱም ይኖራል። የግፉን መብዛት የክፉዎችን ክፋት አይተው የዚህን ዓለም ማለፍ የሚመኙ በዙ ናቸው። ነገር ግ ን ወደፊት የሚመጡ አሁንም ያሉ ጥቂት ጻድቃን ስላሉ ለእነርሱ ሲባል ተጠብቆ መቆየቱ አይቀርም። ሰባኪው የሚሰብከው እነዚህ ጥቂት ጻድቃን እንዳይቀሩበት ነው። ሥጋውና ደሙ የሚዘጋጀው ለጥቂት ጻድቃን ምግብ እንዲሆን ነው። ካህን የሚሾመው እነዚህ ጻድቃን ቁልፍ አጥተው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሳይገቡ እንዳይቀሩ ነው።
ባሕታዊ በረሀ የሚወርደው፣ በምድረበዳ የሚወድቀው ጥቂት ጻድቃን ስላሉ ነው።
ዛሬም ራሳቸውን ዝቅ ካደረጉ ከትዕቢት ዙፋን ከወረዱ መምህራን ጋር የሚሠራው የጻድቃን ልደት ስላልተቋረጠ ነው። ዓለም በኀዋ ላይ በሚንሳፈፍበት ዘመን ከአፈር ጋር የተደባለቀ እንጀራ በልተው፣ አፈር ለብሰው፣ አፈር መስለው የሚያስተምሩ መምህራን መኖራቸው የጥቂት ጻድቃን ትውልድ እንዳይቋረጥ ነው። እስር ቤት ከወረዱ ሐዋርያት ጋር ይሠራ የነበረው ክርስቶስ በዙፋን ላይ ከነበሩ ነገሥታት ጋር ሲሠራ አላየነውም። ክርስቶስ ደረቱን በወርቅ መታጠቂያ ታጥቆ በተገለጠለት ጊዜ ዮሐንስ በድንጋይና በድንጋይ መካከል ታስሮ ተጥሎ ነበር። በወርቅ ምንጣፍ ለተቀመጡት ራሱን ያልገለጠ አምላክ በተናቀ ስፍራ ለተጣለው ዮሐንስ ራሱን መግለጡ ይደንቀኛል። በኛ ፍቅር ምክንያት የወረደው አምላክ በሱ ፍቅር ምክንያት ስንወርድ በመከራ ያከብረናል።
እንዲህ ነው መውረድ!
ለኃጢአት ሳይሆን ለጽድቅ
በማጣት፣ በስንፍና ምክንያት ሳይሆን እግዚአብሔርን ይቅርታ ለመጠየቅ ለመብላት ለመጠጣት ሳይሆን ለጾም ለጸሎት ቃሉን ለመፈጸም በመትጋት
ራሱን ከፍ ከፍ ያደረገ ይዋረዳል፤ ራሱን ዝቅ ያደረገ ግ ን ይከብራል
ሉቃ 14÷11
ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ሰኞ የሚነበቡ ይሆናል::
ብዙዎቻችን ልበ ደንዳኖች ስለሆንን መውረደ እና መዋረድን በጣም መለየት የከበደን ዘመን ላይ ነን። እንደው እግዚአብሔር በምህረት እያየን እንጂ ለመመራትም አስቸጋሪዎች ጭምር ነን