አቤቱ የሚያሰቃዩኝ ምንኛ በዙ?

ብዙዎች በእኔ ላይ ቆሙ፡፡ ብዙዎች ሰውነቴን አምላክሽ አያድንሽም አሏት፡፡

አንተ ግን አቤቱ መጠጊያዬ ነህ፡፡ ክብሬንና ራሴንም ከፍ ከፍ የምታደርገው አንተ ነህ (መዝ. 3፡1)

ነቢዩ ዳዊት ክፉ ቀን ቢገጥመው የጸለየው ጸሎት ነው፡፡ መራራ ቀናት ሀገር ያስለቅቃሉ፡፡ ከዙፋን ያወርዳሉ፡፡ ማቅ ያስለብሳሉ፡፡ ለብቻ ያነጋግራሉ፡፡ መራራ ቀናት እንደ ጣፋጮቹ ቀናት ፈጥነው አያልፉም፡፡ ያስቸግራሉ፡፡ ዳዊት መራራ ለቅሶን እያለቀሰ ይህንን መዝሙር የዘመረው ሳኦል ሲያሳድደው ፣ ጎልያድ ሰይፉን መዝዞ ሲመጣበት በነበረ ጊዜ አይደለም፡፡ ዳዊት አቤቱ የሚያስጨንቁኝ ምንኛ በዙ ብሎ መራራ ቃላትን የተናገረው ወደ ዙፋን ከወጣ በኋላ ነው፡፡

ዳዊት አደገ ፤ በሳኦል ፈንታ ተሾመ ፣ ሚስት አገባ ፤ ልጆች ወለደ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በኋላ አስጨናቂ ቀን በዳዊት ላይ መጣ፡፡ ልጁ አቤሴሎም በጠላትነት ተነሣበት፡፡ ኤሎፍላውያን ቢሆኑ ይዘምትባቸዋል፡፡ እነ ሳኦል ቢሆኑ ተከታትሎ ያጠፋቸዋል፡፡ የገዛ ልጁ ፣ የአብራኩ ክፋይ ሕዝቡን አሳምጾ አባቱን ሀገር አስጥሎ አሳደደው፡፡

የእኛም ሕዝብ ዛሬ ላይ እንደ ዳዊት ያለ መከራ ነው የገጠመው፡፡ የሚያሰቃዩት በዙ፡፡ ብዙዎች በራሱ ላይ ቆሙ፡፡ አምላክሽ አያድንሽም እያሉ የገነባውን መቅደስ አፈረሱ፡፡ የሚያሳድዱት ኤሎፍላውያን ቢሆኑ በዘመተ ፣ ፣ እነ ጎልያድም ቢሆኑ ወንጭፉን ይዞ በተጋደለ ፣ እነ ሳኦልም ቢሆኑ ቁርጡን አውቆ ጫካ ገብቶ በታገለ ነበር፡፡ ግን እነ አቤሴሎም ናቸው፡፡ ከአብራኩ የተከፈሉ ፤ ከማዕዱ እየበሉ ያደጉ ፣ አብረውት ሀገር ፣ ቤት የተጋሩ፡፡

እነዚህን ምን ማድረግ ይሻላል? ዳዊት ያልተዋጋው ‘አቤሴሎም ልጅ ነው እውቀት ቢጎድለው ነው’ ብሎ ነው እንጂ ስለማይችል አልነበረም፡፡ ዳዊት አርበኛ ነው፡፡ ነብር በጡጫ ፣ አንበሳ በእርግጫ መስበር የሚችል ፤ የጦር መላ ያለው ጀግና ነው፡፡ ሳይዋጋ ዝም ያለው መልስ ከእግዚአብሔር ነው ብሎ አስቦ ነው፡፡ የሸሸ ሁሉ የተሸነፈ አይደለም፡፡ ዝም ያለ ሁሉ ኃይል በውስጡ የሌለው አይደለም፡፡

በመጨረሻ አሸናፊው ዳዊት ነው፡፡ አቤሴሎሞች የሸሸላቸው ሁሉ የተሸነፈ ፣ የማይመለስ ፣ የማይችል ፣ ከዚህ በኋላ አከርካሪው የተሰበረ ስለሚመስላቸው ሚስቱን ፣ ርስቱን ፣ ቤቱን ሀብቱን ሁሉ ይወርሳሉ፡፡ ዳዊት የተመለሰ ቀን ግን ሬሳቸውም አይመለስም፡፡ አቤሴሎም ዳዊትን ባሳደደው ቀን ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ የዳዊትን የአባቱን አልጋ አረከሰ፡፡ ሚስቱን ዙፋኑን ወረሰ፡፡ ዳዊት ሲመለስ ግን አልተገኘም፡፡ ነፍሱ በምድረ በዳ እንደወደቀች ቀረች፡፡ መጨረሻው አያምርም፡፡ እነ አቤሴሎምን ሥልጣን ሲይዙ አለማያውቁበት ግፉን አታብዙ በሏቸው፡፡ 

ዳዊትም ‘ተነሥ አቤቱ አምላኬ አድነኝ ፤ የጠላቶቼን መንጋጋ መትተሃልና የክፉዎችንም ጥርስ ሰብረሃልና’ እያለ ይመለሳል፡፡ መዝ. 3፡7     

Share your love

9 አስተያየቶች

  1. አንተ ግን አቤቱ መጠጊያዬ ነህ፡፡ ክብሬንና ራሴንም ከፍ ከፍ የምታደርገው አንተ ነህ (መዝ. 3፡1) ቃለ ህይወት ያሰማልን

  2. አጭር ግን እጅግ ድንቅ ወቅታዊ ስብራታችንን የሚጠግን ትምህርት ነው፣ የሕይወትን ቃል ያሰማልን።

  3. “ሳይዋጋ ዝም ያለው መልስ ከእግዚአብሔር ነው ብሎ አስቦ ነው”
    መለስ ከ እግዚአብሔር ነው የምንልበትን ተግስት ይስጠን🙏

    መምህር ቃለ ሕይወት ያሰማልን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *