መጽሐፈ ዘፍጥረት የአምስተኛውን ቀን ፍጥረታት ሲተርክ “እግዚአብሔርም አለ፡- ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፤ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈርም በታች ይብረሩ” በማለት ይጀምራል፡፡ ዘፍ 1፡20 አእዋፍ ጌታ እግዚአብሔር ከውኃ ከፈጠራቸው መካከል ናቸው፡፡ ከውኃ ተፈጥረው የተሰጣቸው ተፈጥሯዊ ጸጋ ደግሞ “ከምድር በላይ” እንዲበርሩ ነው፡፡ በዚህ የዘፍጥረት ተረክ ውስጥ ጌታ እግዚአብሔር ስለ እኛ ሕይወት ምን ታላቅ ምሥጢር ሊነግረን እንደ ወደደ ለማየት እንሞክራለን፡፡
ከምድር መጥቀው እንዲበርሩ የተፈጠሩት አእዋፍ የተገኙ ከውኃ መሆኑ፤ ውኃ የጥምቀት ከውኃ የተገኙትም የጥሙቃን (የክርስቲያኖች) ምሳሌ ናቸው ይሉናል አበው፡፡ ጌታችን ስለ ምሥጢረ ጥምቀት ለኒቆዲሞስ ሲነግረው “ከሥጋ ተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ፡፡ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምጹንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” ብሎታል፤ ምሥጢሩን ለጊዜው ሊረዳው ባይችልም፡፡ ዮሐ 3፡6-8 ከመንፈስ የተወለዱ ሁሉ በምን ደረጃ ሊኖሩ በአዲስ ተፈጥሮ ከውኃና(በሚታይ) ከመንፈስ እንደ ተወለዱ አበሠረን፡፡
በዚህ ማዓርግ በአዲስ ተፈጥሮ ከብረን ሳለን በእኛ ዘንድ የሚታየው ሕይወት ምን እንደሚመስል የአእዋፍን ተፈጥሮ በመመርመር ለማየት እንሞክር፡፡
የአእዋፍን አኗኗር በሦስት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡
፩. ክንፍ እያላቸው ፍጹም ከምድር መነሣትና መብረር የማይይሉ እንደ ሰገኖ (ሰጎን)ያሉ፤
፪. ከምድር ለመነሣት የሚውተረተሩ መልሰው ግን የሚወድቁ እንደ ዶሮ ያሉ፤
፫. ከምድር መጥቀው መብረር የሚችሉ፤ እንደየ ደረጃቸው በቅርብ ከፍታ ከሚበርሩ ጀምሮ በዓይነ ሥጋ ለማየት እስኪያዳግት ድረስ በአስደናቂ ከፍታ ላይ እስከሚወጡ እንደ ንስር ያሉ በማለት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡
ሁሉንም በየተራ ምሳሌነታቸውን ለማየት እንሞክር፡-
፩. ክንፍ እያላቸው ፍጹም ከምድር መነሣትና መብረር የማይችሉ እንደ ሰገኖ (ሰጎን) ያሉት ችግራቸው የሰውነታቸው ክብደት ለመብረር እንቅፋት መሆኑ ነው፡፡ ክርስቲያኖችም በተለያየ ሸክም ኅሊናቸው (ልቡናቸው) ከከበደ መድረስ የሚገባቸው ልዕልና ነፍስ ላይ መገኘት ፈጽሞ አይችሉም፡፡
መንፈሳዊ ልዕልናን ገንዘብ እንዳያደርጉ የመጀመሪያው ሸክም ኃጢአት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እናንት ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ያለን ለዚህ ነው፡፡ ማቴ 11፡28 የኃጢአት ሸክምን ከልብ በሆነ ንስሐ ማስወገድ በክንፈ ጸጋ መጥቆ ለመብረር የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ ኃጢአት ከምድር እንዳንነሣ ቁልቁል የሚስብ Gravity ነው፡፡ ክብደት በጨመረ ቁጥር ወደ ላይ ለመውጣት ያለው ዕድል እየጠበበ ትግሉ ደግሞ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
ሁለተኛው ሸክም ምድራዊ ሀሳብ ነው፡፡ ጌታችን በወንጌል “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና” ሲል አስጠንቅቋል፡፡ ሉቃ 21፡34-36 ጨምሮም “. . . በኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፡፡ በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናል” ማቴ 24፡36-42
ዛሬ በንስሐ ሕይወት እንመላለሳለን ብለው በድፍረት የሚያስቡ እንኳ ከዚህ ሸክም ያልተላቀቁ ናቸው፡፡ ሰው ከነፍሱ በላይ ነገ ለሚፈርስ ሥጋ ብዙ ይደክማል፡፡ የቀን ሀሳቡ የሌት ቅዠቱ ስለ መብልና መጠጥ ነው፡፡ የሌለው ለማግኘት ያለው ለመጨመር ይባዝናል፡፡ የድንግልናን ምሥጢር ለክርስቶስም ራስን ሙሽራ አድርጎ የማቅረብንም ክብር ጠንቅቃና አጉልታ በምታስተምር ቤተክርስቲያን እየኖረ ያላገባው/ችው ትዳር የመያዝ ሀሳብ ዕረፍት ነስቷቸዋል፡፡ የልባቸው ምኞት ተፈጽሞላቸው በትዳር የሚኖሩም ክብደቱ አስጨንቋቸዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ “ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው፡፡ በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ፡፡ ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፤ እኔም እራራላቸዋለሁ” ይላል ስለ ትዳር ማሰብና በትዳር መኖር ያለውን ሸክም ሲገልጽ፡፡ 1 ቆሮ 7፡27-35 (ይህን ያለበትን ምክንያት ለመረዳት ሙሉውን በጥንቃቄ ማንበብ)
ሦስተኛው ሸክም ዓለምን መውደድና ምኞት ነው፡፡ ዓለምን መውደድ የሚለው ሀሳብ ብዙ ነገሮችን ያካትታል፡፡
በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ዐውድ በሰው ዘንድ ለሚኖር ተቀባይነት መድከም፣ በልጦ መታየት፣ ክብር፣ ዝና፣ ገንዘብ፣ ዕውቀት፣ ሥልጣን. . . እና የመሳሰሉት ብለን ካላለፍነው ሁሉን ለመዘርዘር ጊዜ ያጥርብናል፡፡ የሰው ሀሳቡ በምድራዊ ምኞት ተገርኝቶ ሲያዝ ልቡናው ይከብዳል፡፡ የሚሻለውን ለመምረጥና ለመከተልም ማስተዋል አይኖረውም፡፡ ጌታችን በወንጌል “የሰውነት መብራት ዓይን ናት፡፡ ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል” ይለናል፡፡ ማቴ 6፡22 ይህን የተረጎመ አንድ ሊቅ በአማርኛ “ዓይንህ ጤናማ ብትሆን. . .” የሚለው በግሪኩ ሲነበብ “ዓይንህ simple ብትሆን. . .” (ቀላል ከሚለው ቀጥተኛ ትርጉም ይልቅ የእኛ መተርጉማን ጤናማ ያሉት በእውነት የተሻለ ቃል ነው) ሕይወትን ቀለል አድርገህ ትኖራለህ፤ ይህም ከምኞት ሸክም ያድንኃል፤ ክበደ ልቡናህም በመንፈሳዊ ሕይወትህ በክንፈ ጸጋ ለመብረር እንቅፋት አይሆንብህም ሲል ነው ብሎ ተርጉሞታል፡፡ ቀለል ያለ ኑሮ ማለት ከፉክክር የራቀ ለሰው አስተያየት (ሙገሳም ሆነ ነቀፌታ) በማይጨነቅ ማንነት የሚገለጥ ሕይወት ማለት ነው፡፡
ዮሐንስ ወንጌላዊም በመልእክቱ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፤ ማንም ዓለምን ቢወድድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም” ይለናል፡፡ ከፍቅረ እግዚአብሔር በላይስ ወደ ላይ በክንፈ ጸጋ መጥቀን እንድንወጣ የሚያደርግ ምን ይኖራል? 1 ዮሐ 2፡15-16
ጌታችን ደቀመዛሙርቱ የሆንን ሁላችን ከሸክም ነጻ የሆነ ሕይወት እንድንኖር ከማስተማሩም በላይ ሥጋዊ ሸከም ቀርቶ በመንፈሳዊነት ስም እንኳ የሚጫንን ሸክም ተቃውሟል፡፡ ፈሪሳውያን ከተዘለፉበት ምክንያት አንዱ በሌሎች ሸክም መጫናቸው ነው፡፡ “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፤ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም” ብሏል፡፡ ማቴ 23፡4-5 እርሱ ግን “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ. . . ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” ብሎናል፡፡ ማቴ 11፡29 ቤተክርስቲያንን ከጌታችን አደራ የተቀበሉ ሐዋርያትም መንጋውን ሲያስተዳድሩ “. . . ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ፤ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና . . .” ሲሉ እናያቸዋለን፡፡ የሐዋ.ሥራ 15፡22-29 በራሳችን ላይ ፈቅደን በጫነው ሸክም ብንኖር ግን ተጠያቂነቱ የእኛው ነው፡፡
፪. ሁለተኞቹ ነገደ አእዋፍ ከምድር ለመነሣት የሚውተረተሩ መልሰው ግን የሚወድቁ በእንዲህ ያለው ምልልስ የሚኖሩ እንደ ዶሮ ያለ ሕይወት የሚኖሩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ይኽኛው ምድብ ከመጀመሪያው ምድብ የሚሻሉ የሚመስሉት በመሞከራቸው ነው፡፡ ሀሳባቸው አልፎ አልፎና ጽናት በሌለው ሁኔታ ቢሆንም ጨርሶ በምድራዊ ሀሳብ ተገርኝቶ የተያዘ አይደለም፡፡ ኃጢአትን ከመሥራት መታቀብ ባይኖርም እንኳ ጸጸት የሚጎበኘው ኅሊና አላቸው፡፡
የእነዚህ ትልቁ እንቅፋት የሚያጡትንና የሚያተርፉትን አለማወቅ፣ ልማድና በተጋድሎ አለመጽናት ናቸው፡፡ ይህም ሕይወታቸውን በየትኛው አቅጣጫ መምራት እንዳለባቸው ቁርጥ ውሳኔ ላይ እንዳይደርሱ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡ እግዚአብሔርን በመምሰል መኖር ማትረፊያ መሆኑን በፍጹም ልባቸው ለመቀበል ይከብዳቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ፤ ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” በማለት የሚመክረው እንዲህ ላሉት ነው፡፡ 1 ጢሞ 4፡8 በመሆኑም የክርስትና ሕይወታቸው ወቅታዊ (seasonal) ነው፡፡
የጾም ወራት ሲሆን፣ በሕይወታቸው ከባድ ነገር ሲገጥማቸው ወይም በሆነ አጋጣሚ የሰሙት ስብከት ሙቀቱ እስኪለያቸው ድረስ ፍጹም የተሰበረ መንፈስ ሊታይባቸው ይችላል፤ ግን አይቆይም፡፡ ፈቃዳቸውን ወደ መፈጸም ሲመለሱ የቆዩበትን ለመርሳት ብዙም አይቸገሩም፡፡
በዚህ የሚገኙት ሌላው ቀርቶ በአገልጋይነት ደረጃ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንደ ዶሮ በጩኸታቸው ሌሎችን የሚቀሰቅሱ እነርሱ ግን በቆሙበት የሚያንቀላፉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በድቅድቅ ጨለማ መቀጣታቸው እንደማይቀር ከተናገረ በኋላ ምክንያቱን ሲያስቀምጥ “እነዚህ ውኃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው፡፡ ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፤ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ፡፡ ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፡፡ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል፡፡ አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትዕዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና፡፡ ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤ ደግሞ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል” ብሏል፡፡ 2 ጴጥ 2፡17-22
በዮሐንስ ራእይ 3፡15 በሌላ ምሳሌ ትኩስ ወይም በራድ አለመሆን ተብሎ የተገለጠ ሕይወት አደገኛነቱ ለመዳን ያለው ተስፋ እጅግ የመነመነ መሆኑ ነው፤ መተፋትን ያስከትላል፡፡ ትልቁ እንቅፋቱ ደግሞ ከቃለ እግዚአብሔር፣ ከንስሐ፣ በአጠቃላይ ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር የሚኖር ጎጂ መላመድ ነው፡፡ ምናልባት ለቤተመቅደሱ ቅርበትና በዚያ ከሚያገለግሉ ጋርም መልካም መግባባት ሊኖረን ይችላል፡፡ ራሳችንን ሳንሰጥ ያለንን ግን በመለገስ ላንታማ እንችላለን፡፡ ይህም በብዙዎች ዘንድ ከሚያሰጠን ሞገስ የተነሣ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለሟል የሆንን መስሎ እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል፡፡ የምንኖረው ሽንገላ የበዛበት ሕይወት ባይተዋር ቤተኞች መሆናችንን እስክንረሳ ያደርሰናል፡፡ በዚህ ደረጃ ካለነው ይልቅ ከላይ በቁጥር አንድ የተጠቀሱት በንስሐ ተመልሰው የቅድስና ሕይወትን ለመኖር የተሻለ እድል ይኖራቸዋል፤ ቢያንስ ልማድ ፍርሃታቸውን አልነጠቃቸውምና፡፡
፫. ከምድር መጥቀው መብረር የሚችሉ፤ እንደየ ደረጃቸው በቅርብ ከፍታ ከሚበርሩ ጀምሮ በዓይነ ሥጋ ለማየት እስኪያዳግት ድረስ በአስደናቂ ከፍታ ላይ እስከሚወጡ እንደ ንስር ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ራሳቸውን ክደው፣ ፈቃዳቸውን ሰውተው፣ ሕይወታቸውን ወደ ኋላ ከሚስባቸው የትኛውም መጣበቅ (attachment) ራሳቸውን ነጻ አድርገው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ፈቃዱን ለመኖር መጨከን በእነርሱ ዘንድ አለ፡፡ የሕይወታቸው ብርሃን የምድር አሕዛብ እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ ያስገድዳል፡፡ እውነትን ያውቋታል ይኖሯታልም፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው” የሚሉ ናቸው፡፡ ገላ 2፡ 20-21 ሁል ጊዜም የኋላቸውን እየተዉ ወደ ፊት የሚዘረጉ እንጂ በደረሱበት የሚጽናኑ አይደሉም፡፡ ለሚበልጠው ጸጋ መቅናትና ትሕትና መጥቀው የሚበሩባቸው ሁለቱ የጸጋ አክናፍ ናቸው፡፡
የመንግሥቱ ምሥጢር ስለ ተገለጠላቸውና ጥበባቸውን በሞኝነት፣ ኃይላቸውን በድካም፣ ልዕልናቸውን በውርደት፣ ቅድስናቸውን በዕብደት ስለ ሠወሩ፤ ሁሉን በሚያውቀው ዘንድ ታውቀው በዘላለማዊው ልቡና ስለ ተሣሉ፤ የሕይወታቸው ምሥጢር የክብራቸው ድንበር ሥጋዊ ደማዊ አእምሮን ስለሚረታ ስለ እነርሱ ምን እንል ዘንድ ይቻለናል? የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ተውሰን “መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል፤ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም” ከማለት በቀር!!! 1 ቆሮ 2፡15
ማሳረጊያ የምናደርጋት በመብረሯ ወፍ ብለን የምንጠራት በባሕርይዋ ግን አጥቢ እንደ ሆኑ እንሰሳት የሆነችዋን የሌሊት ወፍን ነው፡፡ ይህቺ ፍጥረት በሌሊት ስትንቀሳቀስ ዓይኗ ማየት ስለማይችል እንቅስቃሌዋን የምትወስነው ከራሷ የምታወጣው የድምጽ ሞገድ ከፊቷ ካለ ማንኛውም ነገር ጋር ተጋጭቶ በሚሰጣት ነጥሮ በሚመጣ ድምጽ (Echo) በመመራት ነው፡፡ የሌሊት ወፍ በዚህ ጨለማ ዓለም በራሳቸው መረዳት በመታመን ለመጓዝ ለሚሞክሩ ሰዎች ምሳሌ ትሆናለች፡፡ ለሰዎች የተገለጸው እውነተኛውና የመጨረሻ እውቀት ክርስቶስ ነው፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ያለን ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ 8፡12 ክርስቶስን ሳያውቁ ከራሳቸው ኅሊና የሚወጣ የሀሳብ ሞገድን እየተከተሉ በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው፡፡ እንደ ራስ ድምጽ አታላይ ነገር የለም፡፡ እንኳን ክርስቶስን ባለማወቅ ጨለማ ለወደቁ ቀርቶ እርሱን በማወቅ ለምንኖር እንኳ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ለሰው የራሱ ድምጽ መጥፎ ሆኖ ተሰምቶት አያውቅም፡፡ ወጥመዱም ያ ነው፡፡
በራሳቸው መረዳት የሚመሩት ሰዎች መልካምነት ሊኖራቸው ይችላል፤ ሰውም በዚህ ከፍ ያለ ሥፍራን ስለሚሰጣቸው የመብረራቸው ምሥጢርም ይኸው ነው፡፡ ክርስቶስን ባለ ማወቅ ጨለማ ውስጥ እስከ ቆዩ ድረስ ግን መልካምነታቸው የሚረባቸው ነገር አይኖርም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው መልካም ሰዎች እንድንሆን አይደለም በቅድስና እርሱን ወደ መምሰል እንድናድግ እንጂ፡፡ የልጁን መልክ የሚመስሉ ብቻ ናቸው በአባት ዘንድ ለመታየት የሚበቁ፡፡
በዘመኑ የተያዘ ሃይማኖት አልቦ መንፈሳዊነት ወይም መንፈሳዊነትን ከሃይማኖት ለመነጠል የሚደረግ ሩጫ ፍጻሜው በጨለማ ከመዳከር ያለፈ ወደ ዘላለማዊው ብርሃን የሚያደርስ አይደለም፡፡ የብርሃን ልጆች ከጨለማ ልጆች የሚለዩበት የመጀመሪያው መሥፈርት ሃይማኖት ነው፡፡ ጌታችንም “መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ያለ ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ 14፡6 ዛሬም ሠልጥኖ የምናየው ሁለቱ ከጥንት የክርስትና ተቃራኒ የሆኑ መንገዶች ናቸው፤ አይሁዳዊነትና ግሪካዊነት! አይሁዳዊነት ምልክትን መሻት ሲሆን ግሪካዊነት እውቀትን መከተል ነው፡፡ እናምናለን የሚሉት ምልክት በመሻት ጠቢባን ነን የሚሉት ደግሞ እውቀትን በመከተል ይጠፋሉ፡፡ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን!” መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት ተብሎ የተገለጠ ብርሃን ነው፡፡ ብርሃን ሃይማኖት ነው፤ ሃይማኖትም ክርስቶስ ነው፡፡ 1 ቆሮ 1፡18-31
ሰው በብዙ ውሳጣዊና ውጪያዊ ምክንያት እንዲሁም ዓላማ መልካም ሰው ሊሆን ይችላል፤ ከሃይማኖት ውጪ ግን ቅዱስ መሆን ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ቅድስና ቅድስናን በሚሰጥ ነው፡፡ በግብጽ በረሃ ለብዙ ዓመታት የኖሩት ኢትዮጵያዊው ባህታዊ አቡነ አብደል መሢህ “ልግስና በዝቷል ክርስቶስ ግን የለም” የሚለው አባባል መንፈሳዊነትን ከሃይማኖት ለይቶ ቅድስናን በመልካም ሰውነት ተክቶ ለመኖር የሚደክምን የዘመኑን ሰው ለመግለጽ የተጠቀሙበት ድንቅ ቃል ነው፡፡
ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::
https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL
ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::
ቃለ-ሕይወትን ያሰማልን!
ራሴን የቱጋር እንዳለሁ እንድመለከት አድርጎኛል:: ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህር::
ቃለ-ሕይወትን ያሰማልን!
ቃለ ህይወት ያሰማልን ።🙏🙏🙏
ቃለ ሕይወት ያሰማልን ኹልጊዜም ወደ ትክክለኛው መንገድ እንድንኼድ የሚያደርጉን አባቶችን ስለሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን
ቃለሕይወት ያሰማልን
ሰው በብዙ ውሳጣዊና ውጪያዊ ምክንያት እንዲሁም ዓላማ መልካም ሰው ሊሆን ይችላል፤ ከሃይማኖት ውጪ ግን ቅዱስ መሆን ፈጽሞ አይቻልም፡፡
ቃለ-ሕይወትን ያሰማልን መምህር!
ቃለ-ሕይወትን ያሰማልን መምህር!
ቃለ ህይወት ያሰማልን
Kale hiwot yasemalen… egnanm yanebebnewn wede hiwot lemekeyer yabkan