“አንቺ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ ተመለሽ፤ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ ተመለሽ” መኃ 7፥1 በኖኅ መርከብ ውስጥ ሆኖ ዐይኖቹ አሻግሮ ማየት የማይፈልግ ማን አለ? ከዚያ ሁሉ ጥፋት በኋላ ምድርን መልሶ ማየት ያጓጓል። ለዐርባ ቀናት ከሰማይ የወረደውና ከምድር የገነፈለው ትኩስ ውኃ የተራሮችን ራስ ሳይቀር የሚገሽር ትኩሳት የነበረው ውኃ ነው።
ማንም ቢሆን ለአንድ መቶ ሃምሳ ቀናት ምድርን ይዟት የቆየውን ውኃ መጉደል አለመጉደሉን በልቡ ማውጣት ማውረዱ አይቀርም። በዚህ መካከል የምድሪቱን ዕጣ ፋንታ ሊያሳውቅ የሚችል ታማኝ መልዕክተኛ ማግኘት እንዴት መታደል ነው? መዓቱ ቆሟል፤ በመርከቧ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ የምድሩን ፊት ማየት ይፈልጋሉ። በዚህ ጊዜ ነው ኖኅ ርግብን ምድሩን አይታ እንድትመለስ የላካት። መጀመሪያ ሄደች ለእግሯ ማረፊያ ስላላገኘች ተመልሳ መጣች፤ ምድሩ በውኃ ተሞልቶ ነበርና። ዳግመኛ ላካት የውኃውን መድረቅ ለማመልከት የወይራ ዝንጣፊ ይዛ ተመለሰች ከሰባት ቀን በኋላ መልሶ ላካት አልተመለሰችም። ኖኅም ምድር ከጥፋት ውኃ ማረፏን በዚህ አወቀና ከመርከቡ ወጣ።
ርግቢቱን ወደ ዓለም ልኮ ኖኀ ከመርከብ ወጣ። ለጥፋት ውኃ መምጣት ምክንያት የሆነው ኃጢአት መጉደሉን የምትናገረዋ ርግብ እመቤታችን እስከትመጣ ድረስ የዚህችኛዋ ርግብ አገልግሎት እስከዚህ ድረስ ስለነበረ ነው − መመለሷን ሳይጠብቅ ከመርከብ የወጣው። የኖኅ ርግብ ሳትመለስ በዚያው መቅረቷ እንደ ቁራ የምድሩ ነገር ስቧት አይደለም፤ እውነተኛው ሰላም የሚሰበክበት፣ የጥፋት ውኃ በሚጎድልበት ሳይሆን የሰው ልጅ ከኃጢአት የሚያርፍበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ ርግቢቱ አትመለስም።
ከዚያ በኋላ የተነሡ ነቢያት ይህንን ስለሚያውቁ ነው እንደ ኖኅ ዘመን ከሚበሩት አእዋፍ መካከል የሆነችውን ርግብ ሳይሆን ከሰዎች መካከል አንዷ የሆነችውን ርግብ ተመየጢ ተመየጢ ሲሉ የኖሩት። ከጥፋት ውኃ ሳይሆን ከኃጢአት መውጫ ጊዜው መድረሱን የምታበሥራቸውን ርግብ በሕይወተ ሥጋ መቆየት እስከቻሉበት ዘመን ድረስ ተመየጢ ተመየጢ እያሉ ደጅ ይጠኗታል። ርግቧ ካልተመለሰች ሰላም በምድር ላይ መታወጁን ማን ይናገራል? ቁራም አልተመለሰም። ሌላ መልዕክተኛም አልተገኘም።
መጥቀው ከሚበሩ ንስሮች ይልቅ ለሰላም አብሣሪነት የተመረጠች ይህች ርግብ እንዴት ያለች የተመረጠች ናት? ይህች ርግብ የእመቤታችን ምሳሌ ናት ብለው ሊቃውንት ተርጉመዋል። በሰሎሞን መኃልይ ላይ “ርግቤ መደምደሚያዬ” መኃ 5፥2 ተብላ የተጠራች እመቤታችንን ቅዱስ ኤፍሬም “ተፈሥሒ ኦ ማርያም ርግብ ሠናይት፤ በጎ ርግብ እመቤታችን ደስ ይበልሽ” ብሎ አመስግኗታል። ከዚህ አያይዞ የመልክአ ውዳሴ ደራሲ ደግሞ “ርግበ ገነት ጽባሓዊ፤ በምሥራቅ በኩል የተተከለችው የገነት ርግብ” ብሏታል። ከእመቤታችን ቀድመው ለእናትነት ቀድመው የተመረጡ ብዙ ቢሆኑም የሰላም አለቃ ክርስቶስን ለመውለድ ግን አልተቻላቸውም። በቅድስና የተመረጡ የታወቁ ሴቶችም ነበሩ የእመቤታችንን ያኽል በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ የታመነ የሰላም መልዕክተኛ ግን አልተገኘም።
በምድር ላይ የሚኖር ፍጥረት ሁሉ መምጣቷን እያሰበ ሲናፍቅ ነው የኖረው። በርግጥም በመጣች ጊዜ ክርስቶስን ይዛ በመገኘቷ መላእክት በምድር ላይ ለሚኖሩ ሁሉ “ለግዚአብሔር ምስጋና በሰማይ ይሁን በምድርም ሰላም” ሉቃ 2፥14 እያሉ አዋጅ ነገሩ። ስትጠበቅ የነበረችው የኖኅ ርግብ መጣችና ሰላምን ወለደችልን። ሰላም ከማንም ዘንድ የሆነችለን አይደለም፤ ሰላምን ተወልዳ ነው ያገኘናት ያውም ከሌላ አይደለም − ከእመቤታችን ነው።
ዛሬም የኖኅ ርግብ ሆይ! ተመየጢ ተመየጢ እንላለን።
ምድር እንደዚያን ጊዜው ሁሉ ሰላም የላትም። የሰላም ወሬ ሊያወራን የሚችል ማንም የለም። በያንዳንዱ ቀን ማለዳ መስኮታችንን ከፍተን የጥፋት ውኃ መጉደሉን የሚነግረን ሰው እንፈልጋለን ነገር ግን እስካሁን የነገረን የለምና ርግቢቱ እመቤታችን ሆይ እባክሽ ተመየጢ?
ይሆናል ብለን የላክነው ቁራ የምድርን በሬሳ መሞላት እንደ መልካም ነገር ሆኖለት ፊቱን ወደ እኛ አልመለሰም። ከኛ ጋር በነበረ ጊዜ በፊታችን ላይ ያየውን ጭንቀት ከኛ ተለይቶ ከወጣ በኋላ ረስቶት ሰላሙን ሊያበሥረን ወደኛ መመለስ አልፈለገም። ዛሬም የኛን ተሰብስቦ በአንድ ስፍራ መቀመጥ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዓለምን እንደፈለገ ብቻውን ከወዲያ ወዲህ ይመላልስባታል። ነገሮችን ሁሉ ለብቻው ሊጠቀምባቸው ወደደ። የመርከቧ ነዋሪዎች ተጨንቀዋልና ርግቢቱ ድንግል ማርያም ሆይ እባክሽ ተመየጢ?
ወይናችን እንዲያፈራ፤ አበባም በምድራችን ላይ እንዲታይ በመርከቧ ውስጥ ያለን እኛ ልጆችሽ ምድርን እንድንወርሳት ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ።
ሔሮድስ ሞቷል፣ አርኬላዎስ ነግሷል አልልሽም፤ እንዳልሞተ ታውቂአለሽ። አርኬላዎስ ብለን የሾምናቸው ሁሉ ሔሮድስ እየሆኑብን ተቸገርን። በኛ ዘመን በዳዊት ዙፋን የሚቀመጥልን፤ በልቡ እግዚአብሔርን መፈለግ ደስ የሚያሰኘው ንጉሥ እንኳን ባናገኝ በሔሮድስ ፋንታ ለይሁዳ የምንሾመው አርኬላዎስ ብንፈልግ አላገኘንም። የሕጻኑን ነፍስ የሚሿት ዛሬም አሉ አልሞቱም ግን ቢሆንም ተመየጢ!
ምድር የሞላት በግፍ የፈሰሰው የገሊላ አውራጃ ሕጻናት ደም ስለቆመ አይደለም ተመየጢ የምንልሽ ግፋችንን እንድታይልን ነው እንጅ። በኛ ዘንድ ስለልጆቿ የምታለቅስ ራሔል አሁንም እያለቀሰች ነው። ለቅሶም በራማ እየተሰማ ነው። ዋይታ በየደጁ አለ። ከሔሮድስ ቃል ተገብቶላቸው በገደሉት ሰው ልክ ሽልማት ሊቀበሉ የወጡት ገና አልተመለሱም። ግን ምን እናድርግ? ሰለ አባታሽ ስለ ኢያቄም፣ ስለ እናትሽ ስለ ሐና ብለሽ እመቤቴ ሆይ ተመየጢ?
ካልተመለስሽማ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ደራሲ፤ “ወእቀውም ዮም በትሕትና ወበፍቅር” ብሎ የሚቀድስ፤ እንደ ዘካርያስ የሚያጥን፤ እንደ ሙሴ ቅብዐ ክህነት የሚቀባን ካህን ከወዴት እናገኛለን? ስለዚህ ነው ተመየጢ የምንልሽ። እመቤቴ ሆይ! አባቶቻችንን እንደ ጥንቱ የልብሳቸውን ዘርፍ ዳስሰን መፈወስ አምሮናል፤ ጥላውን ሲጥልብን የሚፈውስ ካህን ያስፈልገናል፤ ጋኔን ማውጣትም በገንዘብ ሆነ፥ እኛን ድሆችሽን ከአጋንንት እስራት ማን ነጻ ያውጣን? ተአምራት ማድረግም ትንቢት መናገርም ለግያዝ ሆነ።
ገንዘብ ሳይቀበሉ ከለምጻችን የሚያነጹን እነ ኤልሳዕ ቢፈለጉ አይገኙም። ስለሌሉ ሳይሆን ቅብዝብዝነታችንና ምልክት ፈላጊነታችን ካጠገባችን አርቋቸው ይኸው ባጠገባችን የሉም። ግሩም በሆነው በቊርባኑ ፊት በቆመ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ “ጎሥዐ” ብሎ የሚያመሰግን ካህን ዐይናችን ፈለገ፤ ልባችን ተመኘ፤ ነገር ግን በምስጋና እና በውዳሴ “ጎሥዐ” ማለትን ትተው በልሳነ ሥጋ “ጎሳ” የሚሉት በዝተውብን እየተጨነቅን ነውና ተመየጢ?
የጴጥሮስ ጥላ የጳውሎስ ሰበኑ እመቤቴ ሆይ ቀራጩ ማቴዎስ ወንጌላዊ ተብሎ የተጠራው፣ ዐሣ አጥማጆቹ ወንድማማቾች ሰውን ወደ ማጥመድ የተለወጡት፣ ገበሬው ታዴዎስ፣ አትክልተኛው በርተሎሜዎስ ለዚህ መዐርግ የበቁት ባንች ነው። ሿሚውን ወለድሽላቸው፤ ታሪካቸውን የሚለውጠውን ወደ ዓለም አመጣሽላቸው። በእኛ ዘንድ ግን ነገሮች ሁሉ ተገለባብጠውብናል። ዓሣ አስጋሪ የነበሩት እነዚያ ወንድማማቾችም እንደገና መረብና መርከባቸውን ይዘው ወደ ገሊላ ባሕር ገብተዋል። ማቴዎስም ወደ ቀራጭነቱ ተመልሷል፤ ታዴዎስም ወንጌልን በገበሬ ዘር መስሎ ያስተምረናል ብለን ስንጠብቅ ዘር ወደ መዝራት ተመልሶ ዘሩን እየዘራ ነው።
በርተሎሜዎሶቻችንም ሰውን ተክለው ያጸድቁታል ብለን ተስፋ ስናደርግ ሰፊ እርሻ ከመንግሥት ተቀብለው አትክልት እየተከሉ እንደሆነ ሰማን እንግዲህ በዚህ ሰዓት የቀረን ብቸኛ ተስፋ ያንች መመለስ ነውና ርግቢቱ ሆይ! እባክሽ ተመየጢ?
ከመጣሽማ እንኳን ሰዎች መላእክት ይወርዳሉ። “ወሰላም በምድር” የሚለው ቅዳሴአችንም እውነት ይሆንልናል። ከመጣሽማ አባ ሕርያቆስም ለከንቱ ውዳሴ ሳይሆን በማብዛት ያይደለ በማሳነስ፤ በማስረዘም ያይደለ በማሳጠር ምስጋናሽን ያቀርባል። አድማጭ ሲኖር ዜማ የሚያስረዝሙ አድማጭ እንደሌለ ካወቁ ምስጋናሽን አስታጉለው የሚወጡ እነዚህን አናገኛቸውም ነበር።
ከመጣሽልንማ እንዚራ ስብሐቱን፣ አርጋኖኑን፣ ሰዓታቱን፣ ኆኅተ ብርሃኑን፣ ማኅሌተ ጽጌውን፣ አንቀጸ ብርሃኑን በስምሽ የሚደርሱልሽ አዲሶቹ አባ ጊዮርጊሶች፣ ቅዱስ ያሬዶች ይነሡልን ነበር። ይሄው አዲስ ድርሰት አዲስ ምስጋና የሚያሰማን አጥተን ስንት ጊዜ ሆነን። የዳዊት የሰሎሞን ርግብ ድንግል ማርያም ሆይ ተመየጢ ተመየጢ? እናይሽ ዘንድ ተመለሺ::
ማስታወሻ:- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ሰኞ የሚነበቡ ይሆናል::
” ሔሮድስ ሞቷል፣ አርኬላዎስ ነግሷል አልልሽም፤ እንዳልሞተ ታውቂአለሽ። አርኬላዎስ ብለን የሾምናቸው ሁሉ ሔሮድስ እየሆኑብን ተቸገርን። በኛ ዘመን በዳዊት ዙፋን የሚቀመጥልን፤ በልቡ እግዚአብሔርን መፈለግ ደስ የሚያሰኘው ንጉሥ እንኳን ባናገኝ በሔሮድስ ፋንታ ለይሁዳ የምንሾመው አርኬላዎስ ብንፈልግ አላገኘንም። የሕጻኑን ነፍስ የሚሿት ዛሬም አሉ አልሞቱም ግን ቢሆንም ተመየጢ! ”
ቃለ ሕይወት ያሰማልን ።
አንጀት አርስ።
“ሊቃውንት የተነሱ ቀን ደናቁራን ጆሮ ያጣሉ።”
ሊቁን ከክፉ እመአምላክ ትሰውርልን።
ደናቁራን የሚል ቃል የለም:: ደናቁርት (ደንቆሮዎች) ለማለትም ከሆነ ወንድሙን ደንቆሮ የሚል ፍርድ ይገባዋል ይላል:: ሳይሳደቡ ማመስገን ይቻላል::
ቃለ ህይወት ያሰማልን!!
እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
አዎ እመቤታችን ሆይ እባክሽ ተመየጢ
አሜን አሜን አሜን ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን
እረጅም ዕድሜ ከጤና ጋር ይስጥልን !!
ወቅቱን የዋጀ በድምፅ ቢቀርብ ደግሞ ለብዙ ያስተምረናል
የሕይወትን ቃል ያሰማልን በእድሜ በጸጋ ይጠብቅልን መምህር
❤️ ” እመቤቴ ሆይ ተመየጢ ” ❤️
ማርያም እባክሽ ነይልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን። “ከመጣሽማ እንኳን ሰዎች መላእክት ይወርዳሉ” ።
ቃለ ህይወት ያሰማልን!!
“ነገር ግን በምስጋና እና በውዳሴ “ጎሥዐ” ማለትን ትተው በልሳነ ሥጋ “ጎሳ” የሚሉት በዝተውብን እየተጨነቅን ነውና ተመየጢ?”
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ቃለህይወትን ያሰማልን!
😭 ተመየጢ
ቃለ ህይወት ያሰማልን!!