‘ሴቶችም ደግሞ በሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፡፡ ከእነርሱም በገሊላ ሳለ ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ መግደላዊት ማርያም ፣ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳም እኅት ማርያም ሰሎሜም ነበሩ፡፡ ከእነርሱም ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የወጡ ሌሎች ብዙዎች ሴቶች ነበሩ’ ማር. 15፡40-41
ይህ የእናቶችን ብርታት ፣ ጽናትና ጉብዝና የሚያመለክት ንባብ ነው፡፡ በመንፈስ ያልበረቱትን እናቶች የሚያበረታ ንባብ ነው፡፡ እነዚህ እናቶች የሚመሰገኑ ናቸው፡፡ ችግር በሌለበት ሰዓት ሁሉ ወዳጅ ፣ ሁሉ ወገን ነው፡፡ ጌታ የታመሙትን በሚፈውስበት ፣ የተቸገሩትን በሚረዳበት ፣ የተራቡትንም በሚያጠግብበት ሰዓት ብዙ ወዳጆች ፣ ብዙ ተከታዮች ነበሩት፡፡ እንዲያውም በሁለት ዓሣና በአምስት እንጀራ አጥግቦ ካበላቸው በኋላ የሚነግሥ መስሏቸው በግራና በቀኝ መቀመጥን ጠይቀውት ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንጀራ እንዲያበላቸው በባሕርና በየብስ ፣ በታንኳና በእግር በፈረስ ይፈልጉት ነበር፡፡ ዛሬ ግን መከራ ሲደርስበት እነዚያ ሰዎች አሁሉ አልነበሩም፡፡ አንዳቸውስ እንኳ! እነዚህ እናቶ ግን የሚያቀርባቸው ባያገኙም ‘የት ነው የሚወስዱት? ምን ሊያደርጉት ነው?’ እያሉ በሩቅ ይከተሉት ነበር፡፡ ፈርተው ሳይሆን ተከልክለው ታግደው ነው፡፡
ሲወድቅ ይወድቃሉ ፤ ሲገረፍ ያማቸው ነበር፡፡ እነዚህ እናቶች የተከተሉት ከገሊላ ጀምሮ ነው፡፡ ሌሎችም ብዙ ስማቸው ያልተጠቀሰ እናቶች ነገር ግን የሚወዱትና የሚሳሱለት እስከ ቀራንዮ ድረስ አብረው ወጥተዋል፡፡ በዚያ አስጨናቂና አስፈሪ ሰዓት ጴጥሮስ እንኳን አላውቀውም ብሎ በካደበት ሰዓት ሴቶቹ ተከተሉት፡፡ መከራውን የመዘገቡለት ያልፎከሩት ፣ አለን አለን ያላሉት ናቸው፡፡
ኋላ ታረመ እንጂ እንዲሁ እንደ ጴጥሮስ አለን አለን የሚሉና የሚፎክሩ ተግባር ላይ ግን የሌሉ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ዛሬም አለንልሽ የሚሏትና የሚረዷት በውስጥ ያሉት ሳይሆኑ በሩቅ ያሉት ናቸው፡፡ ሰው እንዲያያቸው ሳይሆን እግዚአብሔር እንዲያያቸው በምሥጢር ቤተ ክርስቲያንን የሚረዱ አሉ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ጋር አብረው ቤተ ክርስቲያንን የሚያሙና የሚያደሙ ሰዎች አሉ፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያንን ‘የሚረዳት አለ ወይ? ችግርዋን የሚካፈላት አለ ወይ?’ ጭንቀትዋን የሚመዘግብላት ሰው እኮ ትፈልጋለች፡፡ የበሉትና የጠገቡት ሁሉ የተከተሉት ለጥቅማቸው ነበርና ጥለውት ጠፉ፡፡
ሃይማኖት በምክንያት ለጥቅም ሲል የሚከተል አያስፈልግም፡፡ ሁሉም ጌታን የተከተለው ለጥቅሙ ስለነበር ዓርብ ዕለት የተገኘ ሰው አልነበረም፡፡ እምነትን ለጥቅም ፣ ለተአምራት ብለን የተከተልን ከሆንን ወደፊትም የምከተል ከሆንን ትቅሙና ተአምራቱ ሲቀር እኛም እንቀራለን፡፡ መከተል እርሱን ብሎ ነው እንጂ! እርሱ እንዲሁ የሚወደድ አምላክ ነው፡፡
ለሰውም እንዲሁ ነው፡፡ ሰው ሲያገኝ ፣ ባለው ጊዜ ዘመድ ያልሆነው ሁሉ ዘመድ ነኝ ፣ ወገን ነኝ እያለ ይቀርበዋል፡፡ ለመብላት መሆኑ ነው፡፡ ሲያጣ ደግሞ ሁሉም ይበተናሉ፡፡ አናውቀውም ይላሉ፡፡ ሰው የሰውን ችግር ሲያይ እግሬ አውጪኝ ነው የሚለው፡፡ እንዲህ መሆን የለበትም፡፡ መድረስ የችግር ጊዜ ፣ የመከራ ጊዜ ነው… እንደነ መግደላዊት ማርያም፡፡
ጌታ በአጠገቡ ማንም ሰው አልነበረም፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ‘አምላኬ አምላኬ’ ያለው፡፡ ክርስትና አብሮ መታመም ፣ መታሰርና መገረፍ ነው፡፡ እነዚህ እናቶች ቆመው ያዩት መስቀል ላይ ሲያወጡት ፣ ሲወጉት ፣ ሆምጣጤ ሲያጠጡት ነበር፡፡ እነርሱም ተወግተዋል ፣ ኮምጣጤ ጠጥተዋል ፣ መስቀሉን ተሸክመዋል፡፡
ጉዞ ከገሊላ እስከ ቀራኞ ድረስ ነው፡፡ ሌሎቹ ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑት ገሊላ ላይ ቀርተዋል ፣ ናዝሬት ላይ ቀርተዋል፡፡ ዛሬም ብዙዎች ገሊላ ቀርተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዓርብ ላይ ያልነበረ ስለ እሑድ ሲነግሩት አይሰማም ፣ አያምንም፡፡ ሲሰቀልና ሲሞት ያልነበረ ስለ ትንሣኤው ብነግሩት ሊያምን አይችልም፡፡ ሐዋርያት መግደላዊት ማርያም ስለ ጌታ ትንሣኤ ስትነግራቸው ያላመኗት ዓርብ ዕለት ከጌታ ጋር ስላልነበሩ ፣ ቀራንዮ ስላልወጡ ነው፡፡
ግንቦት 11 1985 ዓ.ም. እንዳስተማሩት
ማስታወሻ :- በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በድንቅ ስብከቶቻቸው እና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሠረቷቸው ገዳማትና ትምህርት ቤቶች ፣ ባፈሯቸው መምህራንና መነኮሳት ለዘላለም የሚታወሱ ሊቀ ጳጳስ ናቸው::
ጃንደረባው ሚድያ የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን የቆዩ ወደ ጽሑፍ የተቀየሩ ስብከቶች ዘወትር አርብ ይዞላችሁ ይቀርባል::
በረከታቸው ይደርብን::
በጣም ደስ የሚል አቀራረብ ነው ቃለ ሕይወት ያሰማልን ለበለጠ አገልግሎት ያትጋልን ።
ይኼ የጃንደረባው ትምህርት ለኹሉም ሰንበት ተማሪዎችና በዓለም ላሉ ኹሉ አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች በቋሚነት ኮርስ ቢሰጥ በጣም ጥሩ ነው ። በጣም ያነቃል ከንባብ ፍቅር ያሲዛል እውቀትን ይመግባል ……ስለዚ ኹላችንም ይኼ ልምድ እንዲኖረን ለትውልድ እንድናሳልፍ ቢሰራበት።
የአባታችን በረከት ይደርብን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን