የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን የሕግ (Law)፥ የታሪክ (History)፥ የጥበብ (Wisdom) እና የትንቢት (Prophecy) በማለት በአራት ይከፍሏቸዋል። ከእነዚህ መካከል የጥበብ መጻሕፍት የተሰኘው ጎራ ውስጥ የሚመደበው፥ የጥበብን አስፈላጊነት እና የስንፍናን ወይም የሞኝነትን ጥቅም የለሽነት አጉልቶ የሚያሳየው መጽሐፈ ምሳሌ (ዕብ፡ ሲፍር ሚሽሌ) ተጠቃሽ ነው። ይህ መጽሐፍ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ኑሮን ለመኖር የሚረዱ እና ከክፋት መንገድ የሚጠብቁ ምክሮችን በምሳሌዎች መልክ አንድ ላይ አዋቅሮ የያዘ መጽሐፍ ነው። የአይሁድም ሆነ የክርስትናው ትውፊት እንደሚያስረዳው ከሆነ፥ መጽሐፉን የጻፈው እግዚአብሔር ከሁሉ ይልቅ ጠቢብ እንዳደረገው የተነገረለት (1 ነገ 4፡30) የዳዊት ልጅ፥ የእስራኤልም ንጉሥ የነበረው ጠቢቡ ሰለሞን ነው።

የዚህ መጽሐፍ ዋና ዓላማ በመጽሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ (ምሳ 1፡1-6) ላይ ተጠቅሷል። ጸሐፊው ጠቢቡ ሰለሞን እንደሚነግረን ከሆነ፤ መጽሐፈ ምሳሌ አላዋቂ ለሆኑት እውቀትን እንዲገልጥ፥ በእድሜ ላልበሰሉት እውቀትንና ልባምነትን እንዲሰጥ፥ እንዲሁም ጥበበኛ የሆኑትን የበለጠ ጥበበኛ እንዲያደርግ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። በአጠቃላይ መጽሐፉ የሰው ልጅ ከየትኛውም የእውቀት እና የጥበብ ደረጃ ላይ ተነስቶ፤ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ የሆነውን እግዚአብሔርን መፍራትን (ምሳ 1፡7) መሠረት በማድረግ ሕይወቱን እንዴት በብልሃት መምራት እንዳለበት መንገድ የሚያሳይ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሁለት ጫፍ ተደርገው የሚነጻጸሩ ነገሮችን ማግኘት የተለመደ ነው። በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥም እንዲህ አይነቱ ንጽጽር ይታያል። መጽሐፈ ምሳሌ በአንዱ ጫፍ ጥበብን እና ጥበበኛን፥ በሌላው ጫፍ ደግሞ ሰነፍ እና ስንፍናውን አስቀምጦ ይመዝናል፤ የሁለቱንም መንገድ እና ውጤታቸውንም ያሳየናል። ዕብራይስጡ የሰነፍ እና ስንፍና ዓይነቶችን የሚገልጽበት የተለያዩ ቃላቶች ቢኖሩትም፤ ሁሉም ሲተረጎሙ ግን ‘ሰነፍ’ ወይም ‘አላዋቂ’ በሚል ተጠቅልለው ስለተተረጎሙ፥ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለመገንዘብ ከባድ ያደርገዋል። በመሆኑም ልዩነታቸውን ለማየት እንዲያስችለን፥ ሰነፍ እና ስንፍናን ለመግለጽ ከዋሉ ቃላቶች መካከል ሦስት ቃላት ላይ ትኩረት እናደርጋለን። እነዚህም ከሲል (כְּסִיל)፥ ኤዊል(אֱוִיל) እና ናቫል (נָבָל) የተሰኙት የዕብራይስጥ ቃላት ናቸው። እነዚህ ቃላት ምንም ስንኳ ‘ሰነፍ’ ተብለው ቢተረጎሙም፤ የተለያዩ የሰነፍ እና የስንፍና ዓይነቶችን እንደሚከተለው ያሳያሉ፦ 

  1. ስሜት የሚመራው ሰነፍ፦ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሰነፍ ዓይነት በዕብራይስጥ ከሲል (כְּסִיל) ተብሎ የተገለጸው ነው። ይህ አይነቱ ሰነፍ በዋነኛነት የሚመራው በእውቀት ወይም በጥበብ ሳይሆን በስሜቱ ነው። ስሜቱ እንዳመጣለት ይጓዛል፥ ከስሜቱ ባሻገር አርቆ ማሰብ አይሆንለትም፥ ራሱን ማስደሰት ላይ ብቻም ያተኩራል። ይህ አይነቱ ሰነፍ እውቀት እና ጥበብ ካለበት የራቀ ነው። በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ አያውቅም። መዝሙረኛውም “አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ትልቅ ነው፥ አሳብህም እጅግ ጥልቅ ነው፤ ሰነፍ (ከሲል) ሰው አያውቅም” (መዝ 91፡6) በማለት እንዲህ አይነቱ ሰነፍ የእግዚአብሔርን ሥራ ከማወቅ የራቀ እንደሆነ ይናገራል። ይህ ሰነፍ ከእውቀት እና ጥበብ መራቁ ብዙ መዘዝ ያስከትልበታል። የዝምታን ጥቅም ስለማይገነዘብ ሐሜተኛ (ምሳ 10፡18) ይሆናል፥ ክፉ የማድረግን ጉዳት ስለማያውቅ ክፉ ማድረግ ጨዋታ (ምሳ 10፡23) ይመስለዋል፥ የትእግስትን ጥቅም ስለማይረዳ ነገሮችን ሳያስብ እንደመጣለት ያደርጋል (ምሳ 13፡26)፤ ጥበብ ስለሌለው ሕይወቱን የሚመራው ያለ ዓላማ ነው (ምሳ 17፡24)፤ በዚህ ሁሉ ምክንያትም ወላጆቹም (ምሳ 17፡21) ሆነ ለሥራ የሚቀጥረው ሰው (ምሳ 26፡10) በእርሱ ያዝኑበታል። ወሬም ቁምነገር የለውም (ምሳ 12፡23)፥ እንዲያውም ንግግሩ ጥፋትን ያስከትላል፤ መጽሐፍ ቅዱስም “የሰነፍ (ከሲል) አፍ ለራሱ ጥፋት ነው፥ ከንፈሩም ለነፍሱ ወጥመድ ነው።” (ምሳ 18፡7) ይለናል።

    መጽሐፍ ቅዱስ ከእንደዚህ አይነት ሰነፍ ሰው ጋር ብዙ ጊዜን አብረን እንድናሳልፍ አይመክርም። ጠቢቡም “ከሰነፍ (ከሲል) ሰው ፊት ራቅ፥ ከእርሱ ዘንድ የእውቀት ከንፈርን አታገኝምና” (ምሳ 14፡7) የሚለው ለዚህ ነው። ሆኖም ግን፥ ከሌሎች ሰነፎች ይልቅ ለመማር እድል ያለው ይህ ‘ከሲል’ በሚለው ቃል የተወከለው ሰነፍ ነው። ጠቢቡ ሰለሞንም ራሱን ጠቢብ አድርጎ ከሚያስብ ሰው ጋር አነጻጽሮ “ለሰነፍ (ከሲል) ተስፋ አለው” (ምሳ 26፡12) ይላል። በቃሉ ከሚቸኩል ሰው ጋርም አነጻጽሮ ተስፋ እንዳለው (ምሳ 29፡20) ይናገራል። የእግዚአብሔርን ሕግ የሚሽረው ከእውቀት ማጣት እና ለስሜት ተገዢ በመሆኑ ስለሆነ፥ በጥንቃቄ ካስተማሩት ጠቢብ እስከመሆንም ሊበቃ ይችላል። ተመክሮ አልሰማ የሚል ከሆነ ግን፥ “በሰነፍ (ከሲል) ጆሮ አንዳች አትናገር፥ የቃልህን ጥበብ ያፌዝብሃልና።” (ምሳ 23፡9) የሚለውን ሰምቶ መራቅ የተሻለ ይሆናል።

  2. ተቆጪው ሰነፍ – በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሰነፍ አይነት በዕብራይስጡ ኤዊል (אֱוִיל) ተብሎ የተገለጸው ነው። ይህ ሰነፍ መጀመሪያ ላይ ካየነው ሰነፍ የባሰ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ የእግዚአብሔርን ሕግ የማይጠብቀው ካለማወቅ ሳይሆን ሆን ብሎ ነው። የእግዚአብሔርን ሕግ ያውቃል፥ ነገር ግን የራሱ መንገድ የተሻለ እንደሆነ ያስባል። ይህንንም ጠቢቡ ሰለሞን ሲገልጽ “የሰነፍ (ኤዊል) መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት” (ምሳ 12፡15) ይለናል። ይህ ሰነፍ የወላጆቹን ተግሳጽ ይንቃል (ምሳ 15፡5)፥ በዚህም ምክንያት በተጣመመ መንገድ መጓዝን ይለምዳል። በአጠቃላይ ጥበብና ተግሳጽን የሚንቅ (ምሳ 1፡7) ማንነትንም ይላበሳል። በዚህ ምክንያት ከጥበብ እጅግ በጣም የራቀ ይሆናል፤ “ጥበብ ለሰነፍ (ኤዊል) ከፍ ብላ የራቀች ናት” (ምሳ 24፡7) የተባለውም ለዚያ ነው። በሀገራችን “በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ” እንደሚባለው፥ ይህ የሰነፍ አይነትም ዋና መታወቂያው አፉ አለማረፉ፥ ክርክር መውደዱ እና ንግግሩ ለከት ማጣቱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም “አፉ ለጥፋት ይቀርባል” (ምሳ 10፡14)፥ “ከክርክር ይጣመራል” (ምሳ 20፡3)፥ “በአፉ የትዕቢት በትር አለ” (ምሳ 14፡3) እያለ ወደ ጥፋት ስለሚመራው አንደበቱ ይነግረናል። ሌላው መታወቂያው ደግሞ ቁጣው ነው። ቁጣው ቶሎ የሚታወቅ (ምሳ 12፡16) ሲሆን፥ የቁጣውን ከባድነት መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽም “ድንጋይ ከባድ ነው፥ አሸዋም ሸክሙ ጽኑ ነው፤ ከሁለቱ ግን የሰነፍ (ኤዊል) ቁጣ ይከብዳል።” (ምሳ 27፡3) ይለዋል። 

    መጽሐፍ ቅዱስ ከእንዲህ አይነት ሰነፍ ፍጹም እንድንርቅ ይመክራል። ይህንን የሰነፍ አይነት ከስንፍናው ማላቀቅ እጅግ ከባድ እንደሆነ በአስገራሚ አገላለጽ ሲያስረዳ “ሰነፍን (ኤዊል) በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው፥ ስንፍናው (ኢዌሌት) ከእርሱ አይርቅም።” (ምሳ 27፡22) ብሎ ይመክረናል። የዚህ ሰነፍ ስንፍናው በኃጢአት ላይ እስከማፌዝ (ምሳ 14፡9) ድረስ እንደሚደርስ ስንገነዘብ፥ በእርግጥም ከባድ ስንፍና ውስጥ እንዳለ እንረዳለን። በዚህ ከባድ ስንፍናውም ምክንያት እድሜ ዘመኑን ለጠቢብ ተገዢ ይሆናል (ምሳ 11፡29) መጨረሻውም ጥፋት ነው።

  3. ነውረኛው ሰነፍ – በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሞኝ ወይም የሰነፍ አይነት ደግሞ በዕብራይስጡ ናቫል (נָבָל) ተብሎ የተገለጸው ነው። ይህ የሰነፍ አይነት ‘ሰነፍ’ የሚለው መጠሪያ ብቻውን በሚገባ አይገልጸውም፥ ምክንያቱም ከስንፍናም ባለፈ ቃሉ አሳፋሪ መሆንን፥ ስድነትን፥ ነውረኝነትን እና በግብረገብነት እጅግ ወርዶ መገኘትንም ይጠቁማል። ይህ ሰነፍ ከሰው አልፎ ፈጣሪንም አይሰማም፤ ከዚህም ተሻግሮ ፈጣሪ እንደሌለ ሆኖ ይኖራል። መዝሙረኛው ንጉሥ ዳዊት ስለዚህ ሰነፍ ሲናገር፥ “ሰነፍ (ናቫል) በልቡ፦ አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጎሰቆሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም።” (መዝ 14፡1) ይላል። በዚህ ክፍል “አምላክ የለም” ይላል መባሉ፥ የፈጣሪን መኖር መካዱን (Ideological Atheism) ከማሳየት ይልቅ፥ ፈጣሪ ለጽድቅም ሆነ ለኩነኔ ግድ እንደሌለው፥ “ምንም ብንሠራ ፈጣሪ ግድ የለውም” የሚል አይነት አሳብን እንደሚያንጸባርቅ፥ በአጭሩ ፈጣሪ እንደሌለ ሆኖ ኑሮውን እንደሚገፋ (Practical Atheism) የሚያስረዳ ነው። 

    በኦሪት ዘዳግም ላይ ታላቁ ነቢይ ሙሴ “ደንቆሮ (ናቫል) ብልሃተኛም ያልሆንህ ሕዝብ ሆይ” (ዘዳ 32፡6) ብሎ እስራኤልን ጠንከር ባለ ተግሳጽ በገሰጸበት ክፍል ላይ፥ ናቫል የሚለው ቃል ‘ደንቆሮ’ ተብሎ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ እናገኛለን። በዚያው ክፍል ላይም እግዚአብሔር እስራኤልን “በማያስተውል (ናቫል) ሕዝብ አስቆጣቸዋለሁ።” (ዘዳ 32፡21) ሲል ናቫል የሚለው ‘አለማስተዋል’ ተብሎ ተተርጉሟል። ይህ አይነቱን ሰነፍ እጅግ አደገኛ የሚያደርገው፥ ከላይ እንዳነሳናቸው ሁለት የሰነፍ አይነቶች ካለማወቅ በማጥፋት ወይም እያወቀ በማጥፋት እና በመበደል ብቻ አያቆምም። ከዚህ አልፎ ሌሎች ሰዎችን ወደ ክፋት መንገዱ ለማምጣትም ይጥራል። “ተናግሮ የሚያናግር፥ ስቶ የሚያስት” የሚባለው አይነት ማለት ነው። ይህ አይነቱ ሰነፍ በእግዚአብሔር ላይም ቢሆን ከማሾፍ አይመለስም፤ የጥበብ ቃልንም ቢነግሩት ያሾፋል። ምግባሩ የከፋ፥ ልቡም የደነደነ ስለሆን፤ ለዚህ አይነት ሰነፍ መፍትሔው “እግዚአብሔር ሆይ፥ ልቡን አቅናለት” ብሎ መጸለይ ብቻ ይሆናል።

    እግዚአብሔር ከክፉው መንገድ ራሳችንን እንድንጠብቅ ብቻ ሳይሆን በመልካሙ መንገድ እንድንሄድም ቅዱስ ቃሉን ሰጥቶናል። የኃጢአት እና ስንፍና መንገድ ምን እንደሚመስል አውቀን ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናል። በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ፥ “ጥበብ በጎዳና ትጮኻለች፥ በአደባባይ ድምጽዋን ከፍ ታደርጋለች፤ በአደባባይ ትጣራለች፤ በከተማይቱ መግቢያ በር ቃልን ትናገራለች” (ምሳ 1፡19-20) ተብሏል። 

ራሳችንን ከስንፍና ለማራቅ ለጥበብ ጥሪ በጎ ምላሽ ሰጥተናት ይሆን? 

“እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ” (ኤፌ 5፡15)

ማስታወሻ:- መምህር ፍሬሰንበት ገብረ ዮሐንስ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የዕብራይስጥ መምህር ሲሆኑ የጃንደረባው ሚዲያ ቋሚ ዐምደኛና ማኔጂንግ ኤዲተር ናቸው::

Share your love

3 አስተያየቶች

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *