ማይታወቅ አምላክ (Ἄγνωστος Θεός)

ክርስትና በመላው ዓለም መሰበክ ከጀመረ ከዐሥር ዓመት በላይ ቆየት ብሎ ወደ ሐዋርያት ተልእኮ ከተቀላቀሉት የጌታችን ምስክሮች ደቀመዛሙርት አንዱ ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአሕዛብ ዘንድ ስሜን የሚሸከም ምርጥ (ኅሩይ) ንዋይ የተባለ የተጠራበትን ተልእኮ እስከ መጨረሻው ዳርቻ ለማድረስ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የወንጌልን ቃል በቃል፣ በጽሑፍና በተግባር አዳርሷል፡፡ የሐዋርያው የወንጌል ተልእኮ ለእኛ ትውልድ ትልቅ መልእክት አለው፡፡ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ተልእኮ ልዩ ከሚያደርጉት አንዱ በዘመኑ ለነበሩት የዕውቀት ደረጃዎች፣ የማኅበራዊና ባህላዊ ክስተቶች፣ የቋንቋና የአገዛዝ ሥርዓቶች ትኩረት በመስጠት አገልግሎቱን እየመጠነ የፈጸመ ታላቅ ተልእኮ መሆኑ ነው፡፡

የሐዋርያው የወንጌል ተልእኮ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ በመላው የግሪክ ወሮም ግዛት ለሚኖሩ ከልጅ እስከ አዋቂ የእድሜ ክልል ላላቸው ነዋሪዎች፣ የወቅቱን የሥልጣኔ ትምህርት ለተማሩም ላልተማሩም፣ ለባለሥልጣኖቹም ሆነ ሥልጣን ለሌላቸው፣ ለአይሁድ ሊቃውንትም ሆነ ሕግ እናውቃለን ብለው ለሚመኩ ፈሪሳውያን፣ ለብሉይ ኪዳን ተርጓሚዎችም ሆነ ለጸሐፍት፣ ለወታደሮችም ሆነ ለልዩ ልዩ ባለሙያዎች፣ በዘመኑ የረቀቀ የፍልስፍና ትምህርት እንከተላለን ለሚሉት ሳይቀር እንደየዕውቀትና ሥልጣን ደረጃቸው፣ እንደየማኅበራዊ ኑሮ ክፍላቸው የሚሆን ትምህርት ማስተማሩ እና የወንጌልን ዕውነት ማሥረጹ፣ የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብርና ጌትነት በአስደናቂ የቋንቋና የንግግር ችሎታ መግለጹ ለእኛ ትውልድ ትልቅ አርኣያነትና ምትክ የሌለው አንድምታ አለው፡፡

ያለንበት ዘመን በመላው ዓለም ማለት ያቻላል በርካታ መንፈሳዊና ቁሳዊ፣ ዓለማዊና አምላካዊ፣ ምድራዊና ሰማያዊ፣ ትምህርቶች በየቦታው ሳይለያዩ የሰፈኑበት፣ ዕውነቱ ከሐሰቱ ፣ የሚጠቅመው ከማይጠቅመው፣ በአንድነት ተዘበራርቆ፣ ተሰበጣጥሮ የሚገኝበት ነው:: 

በአንድ የቴሌቪዥን ሥርጭት ወይም በአንድ የመረጃ ማሰራጫ የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች፣ የማኅበራዊ ፍልስፍናዎች፣ ወቅታዊ ዜናዎች በልዩ ልዩ ቋንቋና አገላለጽ፣ ምንም ልዩነት ሳይደረግባቸው ፍርዱ ለሰሚና ለተመልካች ተብለው ይቀርባሉ:: የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ሊያገኛቸው የሚገቡ የመረጃ አቅርቦት ፍትሐዊነትን ለማሳካት ሲባል መንግሥታት ለሁሉም እኩል እድል በመስጠት አንዱ አንዱን ሳይነቅፍ፣ ሳይተችና በሌላው ላይ ተጽኖ ሳይደርግ የራሱን ትምህርት መግለጽ እንዲችል መብት በመስጠት ፣ በማቻቻልና በማከባበር ላይ የተመሠረተ መድረክ በዓለም ላይ በመፈጠሩ ሃይማኖቱን በጥልቀት የተረዳ፣ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር በቃልና በሕይወት መግለጽ የሚችል፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቀት ክህነት በተጨማሪ የዘመኑን አስተሳሰብ የተረዳ አገልጋይ ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ ሳንወድ በግድ በዓለማዊ ፍልስፍናም ሆነ ከእኛ ባዕድ በሆነ ትምህርት ተጽዕኖ ሥር መወደቃችን አይቀርም፡፡

ለዚህ የቅዱስ ጳውሎስን ምሳሌ መከተል ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከጌታችን ዕርገት ጥቂት ዓመታት ቆይቶ በፍልስፍና ትምህርት የበለጸገች፣ የገናኖቹ የግሪክ መንግሥታት መናኽሪያ፣ የዛሬው የምዕራባውያን ሥልጣኔ ምንጭ ተደርጋ ወደምትወሰደው እና በዘመኑ የዕውቀቶች ሁሉ ቁንጮ ወደ ሚገኘባት ወደ አቴና ደረሰ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በአቴና ሌሎች ደቀመዛሙርትን ሲጠብቃቸው ሳለ፥ በከተማው ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት። ስለዚህም በምኵራብ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በየቀኑም በገበያ ከሚያገኛቸው ጋር ይነጋገር ነበር። (የሐዋ17፡17)፡፡ 

በዚህ ዘመን ገናና የነበሩ ሁለት የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ደቀመዛሙርት በአቴና ነበሩ፡፡ እነርሱም ኤፊቆሮስ ወገንና ኢስጦኢክ የተባሉት ፈላስፎች ሲሆኑ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጋር ተገናኙ። ቅዱስ ጳውሎስ በሚያስተምርበት ጊዜም አንዳንዶቹ “ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል?” አሉ፤ ሌሎችም የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው። “አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል” አሉ። (የሐዋ 17፡18)

ኤፊቆሮስ እና ኢስጦኢክ የተባሉት ፈላስፎች እነማን ናቸው? ቅዱስ ጳውሎስስ እነዚህን ፈላስፎች እንዴት ሊገናቸው ቁርጥ ውሳኔንን ወሰነ? የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ኤፊቆሮስ ያላቸው የቀድሞው የግእዝ ስያሜን በመያዝ ሲሆን በራሳቸው አጠራር Epicureanism ኤፒሬክሬንዝም ይባላሉ፡፡ እነርሱም እንደ ፕላቶ (አፍላጦን)፣ አሬስቶትል (አርስጣጣሪስ)፣ የመሰለ የፍልስፍና ትምህርትን ባስተማረ ኤፒኩረስ በተባለ ፈላስፋ ከክርስቶስ ልደት 307 ዓመታት በፊት የተጀመረ ትምህርት ነው፡፡ የዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በየዘመኑ በነገሡ የግሪክ ነገሥታት ተሰሚነት የነበራቸው፣ ከግል ጥቅማቸው ይልቅ ለማኅበረሰብ ጥቅም የሚያደሉ ያንንም በማድረግ ደስታ የሚሰማቸው፣ ደስታም የሕይወታቸው ዐቢይ ትርጉም አድርገው የሚያምኑ ተናጋሪዎችና በየጊዜው የአቴና ነዋሪዎችን በሕይወት ፍልስፍና እየማረኩ አዳዲስ ነገሮችን የሚያስተምሩ ነበሩ፡፡ 

በተጨማሪ በዚሁ አኳያ የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ኢስጦኢክ ብሎ ያስቀመጣቸው ሌሎቹ የፍልስፍና ቡድኖች እንዲሁ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ተወዳጆች በኤስጦይኮች ዘንድ ግን ባላንጣዎች የነበሩ ፈላስፎች ነበሩ፡፡ ከሮም፣ ወይም ከአረብ ወይም ከአፍሪካ ወደ አቴና ለሚመጣ ለመጤ ትምህርት ግን ተባብረው መልስ ይሰጡ ነበር፡፡ Stoicism (ስቶይሲዝም) የሚባለው የአሕዛብ የፍልስፍና ትምህርት የተመሠረተው በአቴና ከተማ ነዋሪ በነበረው በዜኖ ነው፡፡ ዘመኑም ከክርስቶስ ልደት 300 ዓመት በፊት ነበር፡፡ የእነዚህ ፈላስፎች ትምህርትም ከፍትሕ መጉደል የሚመጣው የአጥፊነት ባሕርይ የሰውን የተረጋጋ አኗኗርና ዘለቄታዊ ደስታ ስለሚነሱ የሰው ልጅ እነዚህ ነገሮች በግሉ ለማስወገድ የተረበሸ ስሜትንና የተመሰቃቀለ የአእምሮ ፍትሕንና ሚዛናዊ ያልሆነ አስተሳሰብን መለማመድ የለበትም ይላሉ፡፡

እነዚህ ፈላስፎች እና የፍልስፍና ትምህርት ቤታቸው ከክርስትና ሦስት መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ ናቸው፡፡ ባላቸው ቅድምናም ይሁን ተሰሚነት በዘመናቸው በነበረውም ኅብረተሰብ የአዋቂዎች ሁሉ ዳርቻ ተደርገው መወሰድ ለቅዱስ ጳውሎስ አስፈሪ አልነበረም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህ የአቴና ጠበብት ለመጋፈጥ ያስቻለውን ወኔ ከየት አገኘ ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የመጀመሪያው ምንም እንኳ የቦታ ርቀት ቢወስነው የእነዚህ ፈላስፎች ትምህርት ለኢየሩሳሌምና ከኢየሩሳሌም ውጭ ለነበሩ አይሁድ እንግዳ አልነበረም ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹን የፍልስፍና ደቀመዛሙርት በአይሁድ የታልሙድ ድርሰቶች ሳይቀር የታወቁ ነበር፡፡ 

ይልቁንም ዕብራውያን የትርጓሜ መጻሕፍት የኤፊቆሮስ ትምሀርትና ተከታዮች (አፒቆሮስ) ወይም መ*#* በማለት ይጠሯቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ከታዋቂው የረበናት ወገን ምሁር ገማልያል ሥር የተማረ ስለነበር ስለ እነዚህ ሰዎች በመጠኑ ሊያውቅ ይችላል፣ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ የቋንቋ ችሎታው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህ ፈላስፎች የሚናገሩትን የግሪክ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የሚፈላሰፉበትን የዕውቀት ቋንቋ ሳይቀር ያውቅ ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ ግን መሠረታዊ ትምክህቱ በክርስትና ያገኘው የሐዲስ ኪዳን ዕውቀትና በጌታን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለው ትምክህት ነው፡፡ ስለሆነም የክርስትና ትምህርት ዓለም ለሚያነሣው ጥያቂ ብቁ መሆኑን ከመረዳት አልፎ በተግባር አሳይቶበታል፡፡

ይልቁንም ሐዋርያው የሚያስተምረው የትምህርት ርቀት ከእነርሱ ፍልስፍና በላይ ስለሆነና የሚረዱትም ስላልመሰላቸው በትምህርቱ የተገረሙት እነዚህ ፈላስፎች ቅዱስ ጳውሎስን ይዘውት “ይህ የምትናገረው አዲስ ትምህርት ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ ይቻለናልን? በጆሮአችን እንግዳ ነገር ታሰማናለህና፤ እንግዲህ ይህ ነገር ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ እንፈቅዳለን” ብለው አርዮስፋጎስ ወደ ተባለው ስፍራ ወሰዱት። (የሐዋ ሥራ 17፡20)

ሐዋርያውን ወደ አርዮስፋጎስ የወሰዱበት ዋና ምክንያት የአቴና ሰዎች ሁሉና በዚያ የኖሩ እንግዶች አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር በሌላ ጉዳይ አይውሉም ነበርና ነው። (የሐዋ ሥራ 17፡21)፣ አርየስፋጎስ (Areopagus) የሚለው ቃል ከሁለት የግሪክ ቃላት የተገኘ Areios (Ἄρειος) (ትርጉም ቋጥኝ/ፀሐይ) እና Pagos (Πάγος) ምኩራብ፣ ሸንጎ ማለት ነው፡፡ በጥንታዊቷ ግሪክ የፍርድ ሸንጎ በመሆን አገልግሏል፡፡ ስለዚህ በዚህ ኮረብታማ አካባቢ በየቀኑ አዳዲስ የፍርድ ውሳኔዎች ከመሰማት በላይ የተለያዩ የግሪክ ጥንታውያን የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ደቀ መዛሙርት እና መምህራኖቻቸው የፍልስፍና ትምህርታቸውንም ያሰሙበት ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስን ወደዚህ ቦታ የወሰዱበት ምክንያት ግን የተናገረውን ልዩ ትምህርት ለመሰማት ከመፈለግ ያላለፈ ነበር፡፡ 

ምናልባትም የትምህርቱ አዲስነት ብቻ ሳይሆን ከእነሱ የተሸራረፈና በተፈጥሮ ምረምርና መላምት ላይ የተመሠረተ ፍልስፍና የሚያፈራርስ የአዲስ ኪዳን ብሥራት ወንጌልን ይዞ በመሄዱ ባልተገባ ስሕተት ወንጅለው ፍርድ ለማሳለፍ ጭምር መሆኑ ወደ ሸንጎ በመውሰዳቸው ይታወቃል፡፡

የክርስቶስ ሐዋርያ ስሙን በአሕዛብ ዘንድ ይሸከም ዘንድ የተመረጠ፣ በሰይፍ ስለት ፊት ቆሞ የጽድቅ አክሊሉን የተቀበለ ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም ዓለማዊው ፍልስፍና እና የአቴና ባለ ሥልጣናት ግርማ ሳያስፈራው በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ 
“የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ :- ለማይታወቅ አምላክ (Ἄγνωστος Θεός) የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ” አላቸው፡፡ (የሐዋ ሥራ 17፡ 22-23)

ቅዱስ ጳውሎስ የእነዚህ ፈላስፎች የትምህርት መሠረት በሚገባ የተረዳ መሆኑን የሚያሳየው ዐቢይ ጉዳይ በመጀመሪያ የተናገረው ‹‹አማልክትን እንደምትፈሩ›› የሚለው ሐረግ ነው፡፡ አንድ ሐዋርያ ትምህርቱን ከመጀመሩ በፊት የሚያስምራቸውን ሰዎች የዕውቀትና የኑሮ እንዲሁም የአምልኮትና የአስተሳሰብ ሁኔታ በሚገባ መረዳት አለበት፡፡ 

ሐዋርያው በመጀመሪያ በከተማዎ የሞላውን የብዝኀ አማልክት ሥርጭት እና ለአማልክቱ ሕዝቡ፣ ሹማምንቱና ሊቃውንቱ ያላቸውን መሠጠት በሚገባ ተረድቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአብዛኛዎቹ የግሪክ የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለአማልክት የሚሰጠውን ከበሬታ ከትምህርታቸው ተረድቷል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርቱን ከመጀመሩ በፊትም ከተማዋን ተዘዋውሮ መጎብኘቱን ‹‹በከተማዋ የማምለኪያ ቦታዎች ማለፉን›› ገልጧል፡፡ ከማለፍም አልፎ ተርፎ መሥዋዕት ወደሚቀርብላቸው የአማልክት ምስሎች ሲመለከት አንድ ምልክት ቀልቡን ስቦታል፡፡ ይኽውም ምልክት በመስቀል ላይ የተሰቀለ ሰው ምስል ያለበት መንበር እና ከመንበሩ ሥር የተጻፈው ጽሑፍ ነው፡፡ 

ጉዳዩ እንዲህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ አቴና ከመድረሱ ዐሥር ዓመት በፊት የአቴና ፈላስፎች በእሥራኤል አንድ ከሰማይ የወረደ ደግ መምህር ተነሥቶ ብዙ መልካም ነገሮችን እንዳደረገ ከዚያም ክፉ ሰዎች ሰቅለው እንደገደሉት፣ እሱም ከሞታን እንደተነሣ ሰምተው ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ስለዚህ ሰማያዊ ደግ ሰው አምላክነት፣ በአስደናቂ ተአምርና በተዋሕዶ ምሥጢር በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን፣ የመሰከረላቸው፣ የጌታችንን ትምህርቱን፣ የፈውስ ተአምራቱን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱን፣ የመንፈስ ቅዱስን መላክ የነገራቸው ስለሌለ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ መሰቀሉን በሰሌዳ ብርሃን፣ አይተው ነበርና ያንኑ ቅርጽ ሠርተው የማይታወቅ አምላክ ብለው በመጻፍ ለሌሎች አማልክቶቻቸው እንደሚያቀርቡት ያለ መሥዋዕትን ያቀርቡ ነበር፡፡ 

በግሪኮች የማያውቋቸውን አማልክት፣ ወይም ከሌላ ዓለም የሰሟቸውን አማልክት፣ በርግጥ የተመደ ነበር ግን ይህንን በተለየ መልኩ የማይታወቅ አምላክ ያሉትን የተሰቀለውን የክርስቶስን ምስል ከማምለክ አልፈው የማይታወቅ አምላክን ወይም በማይታወቅ አምላክ ስም (Νὴ τὸν Ἄγνωστον፤ ኔ ቶን አግኖስቶን) እያሉ ይምሉበት ጀምረው ነበር::

ሐዋርያው ያንን ሲመለከት “እኔ እናንተ የማይታወቅ ያላችሁትን አምላክ አውቀዋለሁ፣ ሳታውቁት የምታመልኩትንም አውቃችሁ እንድታመልኩት አስተምራችኋለሁ” አላቸው፡፡ ሐዋርያው በዚህ ጉዳይ ትምህርቱ ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ ሲል ብዙ ምሥጢርን ነግሮናል፡፡ እነዚያ ግሪኮች የአቴና ሰዎች አማልክትን ከመፍራት አንፃር ብቻ የማያውቁትንም አምላክ ምስሉን አቁመው ያመልካሉ፡፡ ስሙን አያውቁትም፣ ትምህርቱን አልሰሙም፣ በተአምራቱ ከሥጋ ደዌ አልተፈወሱም፣ በትምህርቱ ከነፍስ ቁስል አልዳኑም፣ በጥምቀቱ ልጅነትን፣ በትንሣኤው ተስፋን አላገኙም፡፡ ግን የማይታወቅ አምላክ ብለው መሥዋዕት ይሰዋሉ፣ ይምላሉ ቃልኪዳን ይገባሉ፡፡ 

ወደኋላ እንመለስበታለን አንጅ ይህ ለእኛ ትልቅ ትምህርት አለው፡፡ ስሙን ከማወቅ አልፈን ክርስቲያን ተብለን እየተጠራንበት አቤት ካላልን፣ ትምህርቱን እያነበብን፣ እየሰማንና እያሰማን ካልተለወጥን፣ ከዓለማዊ የሥጋ አስተሳሰብ ሳንወጣ፣ የመንፈስ ልጅነትን ሥራ ሳንሠራ፣ ለትንሣኤ የሚያበቃንን ምግባር ስንቅ ሳንይዝ እንዲሁ በአካላዊ አፍአዊ እንቅስቃሴ ከተወሰንን ዛሬ የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ለአሕዛብ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ያስፈልገናል፡፡  

እኔ ክርስቶስን እንደመሰልኩት እናንተም እኔን ምሰሉ ብሎ የክርስቶስን ምስል በሕይወቱ ቁመና ሥሎ አምላኩን በመምሰል ለሚያስምራቸው ሁሉ የክርስቶስ ምስል በሕይወቱ መስታወት የሚገለጽ ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ የግሪክ ፈላስፎችን የሦስት መቶ ዓመታት ረቂቅ ፍልስፍና ሳያስፈራው ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። (የሐዋ ሥራ 17፡24- 27)

ሐዋርያው በዚህ ትምህርት የሁሉ መገኛ ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ እንጅ ብዙ አማልክት አለመሆናቸውን፣ እሱም ከሰዎች ሕይወት ርቆ በጠባብ ቤት ብቻ ተወስኖ በዚያ አትክልትና ፍራፍሬ ሻማና ጧፍ እየቀረበለት በትናንሽ ሥጦታዎች ብቻ እየተገለገለ የሚኖር ሳይሆን በሰዎች ሕይወት ውስጥ የልጅነት ሀብትን ሰጥቶ፣ እሱ የዘላለም አባት ሆኖ፣ የሚመለክ፣ በቅዱሳን ሕይወት ለዘለዓለም እያበራ የዘለዓለም መንግሥትን የሚያወርስ አምልክ ሰዎችንም ከአንድ ዘር ፈጥሮ ያበዛ ሁሉንም በጊዜና በቦታ ወስኖ እርሱ ግን ዘለዓለማዊ እና በሁሉ ቦታ የሰፍኖ የሚኖር፣ አምላክ መሆኑን ተናገረ፡፡ 

ይህንን ያለበት ሁለት ምክንያች አሉት፡፡ በሁለቱ የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ትምህርት መሠረት “ቁስ አካል፣ አማልክትም ሆኑ ነፍስ ከአንድ ነጠላ ሕዋስ የተፈጠሩ ናቸው” ብሎ ያምናል” ይሁን አንጅ የአማልክት ነፍስ ከረቂቅ አካላቸው ጋር እንዳታመልጥ ሆና የተሰፋች ስለሆነች አማልክት ለዘላለም ይኖራሉ የሰው ነፍስ ግን ከግዘፍ አካሉ ጋር ያላት ግንኙነት የላላ ስለሆነ ነፍስን ለዘለዓም ይዞ መቆት አይችልም ስለዚህ ሰው ይሞታል ዳግመኛም አይነሣም” ብለው ያምናሉ፡፡ 

በተጨማሪም “ደስታን የሕይወት መለኪያ አድርጎ መውሰድ በሥነ ምግባር የታጀበ፣ ያልተወሳሰበ ሕይወት የትልቅ ደስታ ምንጭ ነው” ብለው ያስተምራሉ፡፡ “ምኞትን መቀነስ ፍላጎትን መግታት፣ ከአካላዊ ደስታ ይልቅ የሥነ ልቦና ደስታን መሻት፣ ለሰው ልጅ የሕይወት ትርጉም ብቻ ናቸው እንጅ ቁስ የተባለ ሁሉ በቦታና በጊዜ የተወሰኑ በመሆኑ የደስታ ምንጭ ሊሆን አይችልም” ይላሉ፡፡ 

ቁስ አካላት ከተወሰነላቸው ጊዜና ቦታ ውጭ መሆን አይችሉም እድሜያቸው በጊዜ እንቅስቃሴአቸው በቦታ የተገደበ ነው፡፡ ሰው በራሱ ቁሳዊ ነው ነፍሱ ስትለየው ሕይወትን ያቆማል፣ ሌሎቹ ቁስ አካላት የራሳቸው የሆነ ገደብ አላቸው አማልክት ከቁሳዊ ሰዎች ጋር በነፍስ ይዛመዳሉ፣ እነሱ ግን ነፍስ ከረቂቅ አካላቸው ጋር እጅግ የተጣበቀች ስለሆነች ዘለዓለማውያን ናቸው፡፡ አማልክትንም የምንፈራው እነሱ የማይሞቱ ስለሆነና እኛ ሞት አጥብቀን ስለምንፈራ ነው ይላሉ፡፡

ሁለቱ ትምህርት ቤቶች በብዙ ጉዳዮች የሚለያዩ ሲሆን በእነዚህ ትምህርቶች መጠነኛ መቀራረብ አላቸው ስለዚህ ሐዋርያው ለእነዚህ ፈላስፎች ሊያስተላልፍ የፈለገው እጅግ ብዙ ረቂቅ ትምህርት ቢኖርም ዋናዎቹና ከላይ በግልጽ የምናያቸው አንደኛው “ሰዎች ከአምላክ ጋር ዝምድና ካላቸው አምላክን ከእነሱ አሳንሰው በወርቅና በብር ወስነው ማስቀመጥ እንደሌለባቸው” ሲሆን፡፡ ቅኔያቸውንም ሳይቀር በመጥቀስ “ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን። እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም” (የሐዋ ሥራ 17፡ 28-30) ሲል የሥነ ፍጥረቱ በጊዜና በቦታ መወሰን የፈጣሪ ፈቃድ እንጅ የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት የማነስ ጉዳይ አለመሆኑን በመግለጽ ክርስትና ከአቴና ፍልስፍና የተሻለና ፍጹም የሆነ የሥነ ፍጥረት ትንታኔ እንዳላት በማሳየት ፈላስፎቹን ከነተከታዮቻቸው መማረክ ነው፡፡ 

ዕብራዊው ቅዱስ ጳውሎስ የአሕዛብን በጥንታዊ የግሪክ ቋንቋ ቅኔ ውስጥ የተደበቀ ፍልስፍናና ትምህርት ሳይቀር ፈትቶ ሰው ከፈጣሪ ጋር ያለውን ዝምድና በምሥጢረ ሥጋዌ አስተማረ፡፡  
ስለዚህ ሐዋርያው ቀጥሎ እንዲህ አለ እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል። አላቸው፡፡ (የሐዋ 17፡31)

ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው የቅዱስ ጳውሎስ የትንሣኤ፣ የእውነተኛ ፍርድ፣ የአምላክ ኃያልነት ትምህርት በእነዚህ ፈላስፎች ዘንድ እጅግ የማይወድ ይልቁንም የሰውን ልጅ ደስታ ከሚፈታተኑት ነገሮች ውስጥ ሁለቱ ትላልቅ ጉዳዮች የአማልክት ፍርሃትና የሞት ጭንቀት ናቸው ብለው ስለሚያምኑ ሊሰሙት አልፈለጉም፡፡ በተለይ ስጦይቆች ስለ ፍርድ እጅግ ይጨነቃሉ፣ ፍርድ ከተዛባ ደስታ አይኖርም ስለዚህ ሕይወት ግቧን አትመታም ይላሉ፡፡ ኤፌቅጠሮሶች ደግሞ ስለሞት መጨነቅ እና ማሰብ ደስታን ይፈትናል፣ ተስፋ ያስቆርጣል ብለው ስለሚያምኑ ስለተንሣኤ መመራመር አይፈልጎም፣ በትምህርታቸው ነፍስ ከሥጋ ከተለየች በኋላ ተመልሳ የመዋሐድ ዕድል የላትም ይላሉ ስለዘህ ትንሣኤ ሙታንን አያምኑም፣ ከዚህ የተነሣ የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ ጉዳዩ ያልገባቸው ወይም የትንሣኤ ሙታንን ማመን ማለት ከአሁን ቀደም አምነው ሲያስተምሩት የነበረውን የፍልስፍና ትምሀርት በሙሉ የሚያፈራረስባቸው ስለመሰላቸው አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን በአዲስ ኪዳን ትምህርት የተመሰጡት በይበልጥም ወደ ውስጥ ገብተው ለመመርመር ፍላጎት ያላቸው ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት። (የሐዋ 17፡ 33)፡፡ 

ቅዱስ ጳውሎስ ባስተማረበት በዚህ ቀን ወዲያው ያመኑ ነበሩ፣ ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠትና በማፌዝ የዘገዩ ነበሩ፣ በሦስተኛ ደረጃም ደግመን እንሰማሃለን ብለው ቀጠሮ የሰጡ ነበሩ፡፡ በወንጌል ተልእኮ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሊገጥመን ይችላል፡፡ ጌታችን በቅዱስ ወንጌል አንዳስተማረን በገር መሬት ላይ እንደወደቀ ዘር ወዲያው ሰምተው በቃሉ ተማርከው ራሳቸውን የሚለውጡ ይኖራሉ፣ አንዳንዶቹ ካስተማርነው ትምህርት ላይ ሲያጉረመርሙ፣ ሲተቹ፣ ሲከራከሩ በአለት ወይም በጭንጫ ላይ እንደወደቀ ዘር ሳይጠቀሙበት ወይ በአእዋፍት ተለቅሞ ወይም የትችትና የፌዝ ቁጥቋጦ ውጦት የሚቀር ይኖራል፣ አንዳንዶች ደግሞ ቆይ እስኪ በደንብ እናጢነው ብለው ወደ ቤታቸው ይዘውት የሚሄዱም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮ መንፈሱን የረበሸውን የአማልክት መንጋ ገሥፆ ከመካከላቸው ወጣ። አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ። (የሐዋ ሥራ 17፡ 33-34)

በእኛም ዘመን የማያውቀውን በማምለክ፣ የሚያውቀውን ደግሞ የማይታወቅ በማለት መሥመር በሚያስለቅቁ ትምህርቶችና ልምዶች የተወጠረ ብዙ ሰው አለ፡፡ በተለይ ከምዕራቡ ዓለም በሚፈጠረው የባህል ወረራ፣ በዓለማዊና ቁሳዊ ሐሳብ የሚባክን፣ ዘመናዊው እና ሳይንሳዊ ተብሎ የሚታወቀው ዕውቀት ይበቃኛል ብሎ የሚመካ፣ የዚህ ዓለም ገዥ የተባለው ገንዘብ የደስታ ሁል ምንጭ የፈለጉትን ለማድረግ ቁልፍ መሣሪያ አድርጎ የሚቆጥር፣ መልካም የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር ለማግኝት በረሀብ የሚቃትት፣ ዕውነቱንም ሐሰቱንም አንድ ላይ ሰምቶ በመካከል የቆመ፣ በሥነ ምግባር ሥነ ልቦና ሁከት የሚሠራውን ክፉ ሥራ የራሱ መገለጫ አድርጎ የሚታበይ እና ብዙ ዓይነት ሰው ያለበት ትውልድ ነው፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደየአካባቢው የጎሉበት፣ የግልና ጋራ ፍላጎቶች የተምታቱበት ብዙ የኅብረተሰብ ክፍል አሁንም አለ፡፡ 

ስለዚህ በቋንቋ የበሰሉ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተካኑ፣ ዘመናዊው ዓለም የደረሰበትን ሥልጣኔና የማኅበራዊ ክንውን ደረጃ የተረዱ፣ ሌላውን የሚያከብሩ፣ የራቸውን የሚጠብቁ የወንጌል ልዑካን ያስፈልጉናል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአቴና ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ሊቃውንትና ደቀመዛሙርት አድናቂዎችና ተከታዮች ፊት እንዲናገር ሞገስ የሆነው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ አገልግሎታችንን ይባርክልን ያስፋልን፡፡

አኮቴት ለስሙ::

ማስታወሻ :- መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የኢኦተቤ የውጪ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ ናቸው::

Share your love

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *