ሙሴና ሚካኤልን ፍለጋ

እስራኤል በፈርዖን አገዛዝ እጅግ ተጨንቀዋል:: “በግብፅም ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነሣ” (ዘጸ. 1:8) ከተባለበት ዘመን ጀምሮ የእስራኤል እናቶች የዕንባ ጅረት ፤ የእስራኤል ሕፃናት የደም ጎርፍ አልቆመም::  ዮሴፍን የማያውቁ ፈርዖኖች አይነሡ እንጂ የተነሡ እንደሆነ “ግብፅን ያቀናነው እኛ ነን” ብትል ስለ ዮሴፍ ውለታ ብትተርክ የሚሰማህ የለም:: ሕፃናት አለቁ ብትል “ለግብፅ ፒራሚድ ሥራ ይጠቅማል” ትባላለህ እንጂ የሚሰማህ የለም:: ፈርዖን ነፃነት ሲጠይቁት “ጠግባችሁ ነው” ብሎ ምግብ የሚቀንስና ሥራ የሚጨምር ጨካኝ መሪ ነበር:: (ዘጸ. 5:18)

+++

እንደምንም አለፈ:: ይህንን የጨለማ ዘመን አሳልፎ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብፅ ባርነት ነፃ ባወጣበት በዚያ ታላቅ ዕለት ግን ይህ ሆነ:: 

፳ኤል ከባርነት ተላቅቀው ከግብፅ ከወጡና ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ንጉሥ ፈርዖን ሒድ ብሎ የለቀቀው ሕዝብ ጉልበት ቆጨው:: በቁጣ ነድዶ ሠራዊቱን አስከትቶ በፈጣን ሠረገላ እየጋለበ መጣባቸው:: ከፊታቸው ደግሞ የሚያስፈራ ባሕር ተደቅኖአል::  ሕዝቡ ግን የፈረደበት ሙሴ ላይ በቁጣ ጮኹበት::  

መጽሐፈ መቃብያን “ያንን ሁሉ ሕዝብ ሲጠብቅ ያልተበሳጨ ሙሴን አስበው” እንደሚል እንደ ሙሴ ትሑትና ታጋሽ መሪ መቼም ታይቶ አይታወቅም:: (2 መቃብያን 11:1) መቼም ሙሴ ለእስራኤል ያልሆነው ነገር አልነበረም:: “ሕዝቤን ከምታጠፋ እኔን አጥፋኝ” የሚል መሪ ከሙሴ በቀር የት ይገኛል? “የአንተ ሥልጣን ሳይነካ ሕዝቡን ልደምስሰው” ሲባል ሥልጣኑ ይቅርብኝ ሕዝቡን ከምትደመስስ ከሕይወት መጽሐፍ ስሜን ደምስስልኝ  ሲል የሚገኝ መሪ ከወዴት ይገኛል? (ዘጸ. 32:32) “ሥልጣኔን ለማቆየት ምንም ያህል ሕዝብ ቢያልቅ ይሻላል” ብለው የሚያስቡ መሪዎች ዓለምን በሞሉባት ዘመን ፣  ሕዝቦች ስለ መሪዎች ሥልጣን ሲባል ደማቸው እንደ ጎርፍ በሚፈስስበት ዘመን ሆነን ስናስብ  “ሕዝቤ ከሚጠፋ እኔ ልጥፋ” የሚል መሪ በነበራቸው እስራኤል እንቀናለን:: 

እስራኤል ግን የሙሴ መሪነት አልታያቸውም:: ከፈርኦን ነፃ መውጣት ቢፈልጉም ለሙሴም መታዘዝ አይፈልጉም:: እሱን መቃወም የጀመሩት ገና ግብፃዊውን ገድሎ እስራኤላዊውን ባዳነባት ማግሥት ነበር:: 

ሁለት እስራኤላውያን ሲጣሉ ያየው ሙሴ “ለምን ወንድምህን ተመታዋለህ?” ብሎ ሊሸመግል ሲሞክር 

“በእኛ መካከል ዳኛ አድርጎ ማን ሾመህ?” ብለው አፈጠጡበት:: (ዘጸ. 2:14) ለካስ የወንድማማችን ጸብ እዳኛለሁ ብለህ መነሣት ራሱ አደገኛ ነገር ነው!? “ወንድማማቾች ናችሁ አትጣሉ” ማለት ለካ ዋጋ ያስከፍላል:: እናም ይህ ሙከራው ሙሴን ለስደት ዳረገው:: ሕዝቤን አድናለሁ ብሎ ራሱ ስደተኛ ሆነ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “እስራኤል ለምን ቁስሌን አከምክልኝ ብሎ ሐኪሙን የሚቆጣ  በሽተኛ ይመስላሉ” እንዳለው ሙሴ ለወገኔ ልቁም ባለበት ዕለት ስደተኛ ሆነ:: 

እስራኤል ከዚያ ወዲያ ሙሴ ላይ ምን ያላደረጉት አለ? ሆኖም ልክ በዚያች ባያት ዛፍ ላይ እሳት ሲነድባት እንዳልተቃጠለች እስራኤላውያንም ሙሴ ላይ ለዓመታት ቢነድዱም አላቃጠሉትም:: የተቀደሰውን ጽላት እስኪሰብር ድረስ ቢያማርሩትም ተስፋ አልቆረጠባቸውም::

በዚህ የመሻገር ቀንም “በግብፅ መቃብር ጠፍቶ ልታስፈጀን ነው?” “ከሞት ባርነት በስንት ጣዕሙ?”  እያሉ እስራኤል በኤርትራ ባሕር ዳርቻ ሙሴን በቁጣ እየጮኹ አስጨነቁት::

መሪነት ከባድ ነው:: ያንን ሁሉ ድንቅ ነገር አድርጎ እግዚአብሔር ነፃ ሲያወጣቸው ሙሴ ለእነርሱ ቤዛ ሆኖ ተሹሞ ብዙ ዋጋ ከፍሎአል:: ውለታውን ረስተው አፋጠጡት::

“ሙሴም ለሕዝቡ፦ አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ፡ አላቸው” 

ሙሴ ሕዝቡን ከጩኸታቸው ሲያረጋጋ ሳለ የእግዚአብሔር ድምፅ ወደ ሙሴ መጣ 

“ሙሴ ሆይ ለምን ትጮኽብኛለህ?” አለው::

ልብ አድርጉ የጮኸው ሕዝቡ ነው ሙሴ አረጋጋ እንጂ ቃል አልተናገረም:: ሆኖም ሙሴ አፉ ዝም ቢል ልቡ ይጮኽ ነበር:: ከእስራኤል ጩኸት ይልቅ የሙሴ ዝምታ እግዚአብሔር ጆሮ ደረሰ:: እግዚአብሔር ኤልያስ እንዳላገጠባቸው የአሕዛብ አማልክት በጩኸት ብዛት የሚሰማ አምላክ አይደለም:: በትዕቢትና አመፅ ከሞላበት ጩኸት ይልቅ በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ዝምታ እግዚአብሔር ጋር ይጮኻል:: 

የእስራኤል ጩኸት ፍርሃት ይነዛል:: ልናልቅ ነው የሚል ሽብር ይፈጥራል:: የሙሴ ዝምታ ግን ባሕር ይከፍላል::

ጌታ ሆይ ጩኸታችን አልሆነልንም:: ዝምታችንን ሰምተህ ሀገራችንን ከከበባት ጥፋት ታደግልን:: የሚጮኹብን ሳይሆን የሚጮኹልን ሙሴዎችን አብዛልን::  የእኛ መጨቃጨቅና ጠብ ባሕር አይከፍልም::  የእኛ ጩኸት ከመነካከስ በቀር አያሻግርም:: በአርምሞ የሚለምኑህን በእኛ ፊት ዝም አሉ የምንላቸው በአንተ ፊት ግን የሚጮኹትን ሰምተህ ታደገን::

ሙሴ ባሕሩን መታው:: የኤርትራ ባሕር በዝምታ ተከፈለ:: የመሪዎች ሥራ ባሕሩን መምታት እንጂ ሕዝቡን መምታት አይደለም:: በትር የተሠጣቸውም ባሕር ከፍለው ሕዝቡን እንዲያሻግሩ እንጂ ሕዝቡን እንዲያስቸግሩ አይደለም:: ይህ የገባው ሙሴ ሕዝቡን ትቶ ባሕሩን መታው::  ራሔል ስለ ልጆችዋ ያለቀሰችው ዕንባ እስከ ራማ ደርሶ የኤርትራን ባሕር ከፈለ:: 

[የራሔል ዕንባ እስከ ራማ ተሰማ ሲባል ስሰማ የድንግል ማርያም ዕንባ የት ድረስ ይሰማ ይሆን? እላለሁ:: “እመቤታችን ሆይ ስለ እኛ ስለልጆችሽ እባክሽን አልቅሺ:: የራሔል ዕንባ ራማ ከደረሰ የአንቺ ዕንባ የት ሊደርስ ነው? በየበረሃ እየወደቀ ስላለው ልጅሽ ስለሞተለት ወንድም እባክሽን ለምኚ:: ሙሴ በወንድሙ አሮን በትር ባሕርን ከፈለ:: ሳይተክሏት የለመለመችው የአሮን በትር  ድንግል ሆይ የኃጢአታችን ባሕርስ የተከፈለው ባንቺ አይደለምን? አሁንም የመከራችን ባሕር የማትከፍይልን ለምንድን ነው? ያሰኘኛል]

በሙሴ በትር ባሕሩ ተከፈለ:: የኤርትራ ባሕር (ቀይ ባሕር [በግሪኩ erythos ማለት ቀይ ነው]) እጅግ ባለ ታሪክ ባሕር ነው:: ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደረቅ ሆኖ ፀሐይ ያየውና ግማሽ ሚልየን የሚሆን ሕዝብ በመካከሉ ተራምዶ ያለፈበት ይህ ባሕር እንንደ ግድግዳ የቆመ ብቸኛው የዓለማችን ባሕር ነው:: 

በዚህ ባሕር እስራኤል ሲሻገሩ ፈርኦን ከነሠራዊቱ ሰጠመ:: በእግር የሔዱት የተሻገሩትን ባሕር በሠረገላ የሔዱት አቃታቸው:: የኤርትራ ባሕር ለእስራኤል ትንሣኤ ሲሆን ለፈርኦን ግን መቃብር ሆነ:: ፈርኦን ደንግጦ መመለስ የነበረበት ባሕሩ ሲከፈል ሲያይ ነበር:: ፈርኦንን ያደቆነ ሰይጣን ግን ባሕር መካከል ሳያቀስስ አልለቀቀውም:: እግዚአብሔር ሲቀጣ በፍትሐዊነት ነው:: ሕፃናት እያረደ ወደ ባሕር የጨመረው ፈርኦን የእርሱም ሞት ውኃ ውስጥ ሆነ:: ጎልያድ ብዙዎችን በገደለባት በገዛ ሰይፉ እንደሞተ ፈርኦንም ብዙዎችን በገደለበት ውኃ ሞተ::

በትዕቢቱ “እግዚአብሔር ማን ነው?” ብሎ ነበርና እግዚአብሔርን በዚያ ባሕር ተዋወቀው:: እሱ ሲሰጥም እስራኤል በኩራት “እግዚአብሔር ማን ነው? ” ለሚለው የፈርኦን ጥያቄ ከባሕር ማዶ ሆነው መልስ ሠጡ “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው” አሉ:: እስራኤል በኤርትራ ባሕር መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ “በባሕርና ደመና ተጠመቁ” ተብሎላቸዋል:: ፈርኦን ግን እስራኤል በተጠመቁበት ጠበል ውስጥ ሰጠመ:: 

የኤርትራ ባሕር እንደ ባቢሎን እሳት ለአንዱ መዳኛ ለሌላው መሞቻ ሆነ:: እስራኤልም በእሳቱ እንደዳኑት እንደ ሠለስቱ ደቂቅ በባሕሩ ዳኑ ግብፃውያንም በእሳቱ እንደሞቱት እንደ ባቢሎናውያን በባሕሩ ሞቱ:: በሁለቱ  ታሪኮች ላይ ነገሩን ያስፈጸሙት ደግሞ ብርሃናውያኑ ሚካኤልና ገብርኤል ነበሩ:: 

የኤርትራን ባሕር ሲሻገሩ ከሙሴ ሌላ እስራኤልን ሲመራ የነበረ አንድ ሰማያዊ ጠባቂም ነበረ:: እርሱም የእስራኤል ጠባቂ (advocate of Israel) በመባል የሚታወቀው ቅዱስ ሚካኤል ነበር:: 

“በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ” ዘጸ 14:19 እንዲል ቅዱስ ሚካኤል እስራኤልን ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን ዐምድ እየተመሰለ በመንገድ መራቸው::

እኛም ያጣነው ሙሴንም ሚካኤልንም ነው:: እኔን ከሕዝቤ ያስቀድመኝ የሚል ሙሴ እና እኔ ላብራላችሁ የሚል ሚካኤል እንሻለን:: በእርግጥ የቀን ደመና የሌሊት ብርሃን ሆኖ የሚቆም ጠባቂ ከሚካኤል በቀር ወዴት ይገኛል? “ከሚካኤል በቀር የሚያጸናኝ የለም” ያለው ገብርኤል ያለ ምክንያት አልነበረም:: እውነትም ሁሉ ነገር በጨለመበት በዚህ ዘመን የሚያበራ መንገድ መሪ ያስፈልገናል:: 

ቅዱስ ሚካኤል ሲጨልም ከማብራት ፀሐይ ሲከርር ከማጥላት በቀር አንዳች ያልተናገረ ሲጠብቅ የማይታይ ውለታ ቁጠሩልኝ የማይል ቅዱስ ጠባቂ ነው:: ይህንን ከእስራኤልም ታሪክ የመልአኩን ጥበቃ ከቀመስን ልጆቹም ታሪክ መረዳት ይቻላል:: ሊቁ ቢቸግረው የመልአኩን በዝምታ የተሞላ ጠባቂነት ቢያይ “አንተኑ ሚካኤል መና ዘአውረድከ” “ሚካኤል ሆይ መናን ያወረድኸው አንተ ነህን?” ብሎ እየጠየቀ ያደንቃል:: እያበሩልህ አበራንልህ የማይሉ እየመገቡ አበላንህ የማይሉ ሚካኤላውያን ከወዴት ይገኙ ይሆን? 

እኛ ዛሬም ድረስ ያለነው ከባሕሩ ዳርቻ ላይ ነው:: ሁሉም መሻገር ይፈልጋል:: ከእኛ መካከል እንደ ፈርኦን ሰጥሞ የሚቀር ይኖራል:: እንደ እስራኤል የሚሻገር ይኖራል: :  ቅዱስ ሚካኤል ሆይ ለእኛም ድረስልን:: ይህንን ክፉ ዘመን በክንፎችህ አሻግረን:: መናው ይቅርብን መና ሆኖ ከመቅረት ግን ታደገን::

Share your love

22 አስተያየቶች

  1. ቅዱስ ሚካኤል ሲጨልም ከማብራት ፀሐይ ሲከርር ከማጥላት በቀር አንዳች ያልተናገረ ሲጠብቅ የማይታይ ውለታ ቁጠሩልኝ የማይል ቅዱስ ጠባቂ ነው:: ይህንን ከእስራኤልም ታሪክ የመልአኩን ጥበቃ ከቀመስን ልጆቹም ታሪክ መረዳት ይቻላል:: ሊቁ ቢቸግረው የመልአኩን በዝምታ የተሞላ ጠባቂነት ቢያይ “አንተኑ ሚካኤል መና ዘአውረድከ” “ሚካኤል ሆይ መናን ያወረድኸው አንተ ነህን?” ብሎ እየጠየቀ ያደንቃል:: እያበሩልህ አበራንልህ የማይሉ እየመገቡ አበላንህ የማይሉ ሚካኤላውያን ከወዴት ይገኙ ይሆን?

    ቃለ ሕይወትን ያሰማልን መምህር

    • ቃለ ህይወት ያሰማልን

      እድሜህን ያርዝምልን🙏🏾🙏🏾🙏🏾🙏🏾🙏🏾

  2. አሜን አሜን አሜን ቃለ ሕይወት ያሰማልን የአገልግሎት ዘመን ያርዝምልን መምህር

  3. የቀን ደመና የሌሊት ብርሃን ሆኖ የሚቆም ጠባቂ ከሚካኤል በቀር ወዴት ይገኛል? “ከሚካኤል በቀር የሚያጸናኝ የለም” ያለው ገብርኤል ያለ ምክንያት አልነበረም። ቃለ ህይወት ያሰማልን ።

  4. “እመቤታችን ሆይ ስለ እኛ ስለልጆችሽ እባክሽን አልቅሺ:: የራሔል ዕንባ ራማ ከደረሰ የአንቺ ዕንባ የት ሊደርስ ነው?…”

    እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
    በርቱልን

  5. “በእርግጥ የቀን ደመና የሌሊት ብርሃን ሆኖ የሚቆም ጠባቂ ከሚካኤል በቀር ወዴት ይገኛል?”

    ቃለ ህይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያት ያውርስልን መምህር

  6. ሙሴ ባሕሩን መታው:: የኤርትራ ባሕር በዝምታ ተከፈለ:: የመሪዎች ሥራ ባሕሩን መምታት እንጂ ሕዝቡን መምታት አይደለም:: በትር የተሠጣቸውም ባሕር ከፍለው ሕዝቡን እንዲያሻግሩ እንጂ ሕዝቡን እንዲያስቸግሩ አይደለም::

  7. “በትዕቢትና አመፅ ከሞላበት ጩኸት ይልቅ በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ዝምታ እግዚአብሔር ጋር ይጮኻል:: ” ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምሕር።

  8. መምህራችን ሁሌም ትምህርቶ ድንቅ ነው! ይገርመኛል የሰው አጠራጣር! በምን አይነት አጋጣሚ ወደሰንበት ት/ቤት እንደመጡ የሆነ ጊዜ ያወሩት ሁሌ ትዝ ይለኛል። እግዚአብሔር ያውቅበታል። ለኛም መክሊታችንን አውቀን በፀጋው ብቻ ታምነን በትህትና በቤቱ እንድንቆይ ይርዳን! የሊቀ መልዓኩ ምልጃና ረድኤት አይለየን! የአመት ሰው ይበለን!

  9. ቃለ ሕይወት ያሰማልን፣ አስበ መምህራንን ያድልልን መምህራችን። በእውነት እስራኤልን 40 ዘመን የመራ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እኛም በምልጃው የምናምን ልጆቹን ይጠብቀን፣ ይህን የመከራ ዘመን እስራኤልን ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ እንዳሻገረ ያሻግረን🙏💐

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *