ይህን ጥያቄ ብዙዎቻችን በተለያዩ ምክንያቶች ልንጠይቅ እንችላለን። በተለይ ሕይወታችንን ከባድ ያደረጉብን ፈተናዎች አልርቅልን ሲሉ፤ አስጨናቂ የኾኑ ነገሮች አልሸሸን ሲሉን። ክፉ ሥራን ለማቆም አስበን ያቃተን ሲመስለን፣ ተምረን ሐሳባችን አላሳካ ያለን ሲመስለን፣ ሥራ ፈልገን ስናጣ፣ ሰዎች ተገቢውን ክብር አልሰጥ ብለው ሲንቁን ወይም ያስፈልገናል ያልናቸውን ነገሮች ማግኘት ሲያቅተን በጽኑ ቍዘማ ውስጥ ኾነን ለምን ተጠርኹኝ? ባልፈጠር ይሻል ነበር! የማልጠቅም ስለ ኾንኹኝ ራሴን ማጥፋት አለብኝ። እያልን ብዙ ግራ መጋባት ውስጥ የምንገባ ጥቂት ሰዎች አይደለንም። ለመኾኑ ለምን እንደ ተፈጠርን በአግባቡ የምንረዳ ስንቶቻችን ነን? እግዚአብሔርስ ከእኛ የተፈጠርንለት ዓላማ እያገኘብን ይኾን? እውነተኛውን የሕይወት ዓላማስ ተገንዝበን ያን ለማሳካት የምንኖር ምን ያህል ነን? ብዙዎቻችንስ የሕይወት መሠረታዊ ዓላማ ምግበ ሥጋ፣ ልብስ ሥጋ እና መጠለያን ማግኘት ነው ብለን አንድ ራሱን እንደ ቻለ ሃይማኖት አልተቀበልንምን? ሳይንሳዊስ በኾነውስ መንገድ መሠረታዊ የሕይወት ፍላጎቶች እኒህ ናቸው በመባሉ ምክንያት የሕይወትን ፍጹም ስኬት እኒህን ነገሮችን በማግኘትና በማጣት ላይ አልመሠረትንምን? እንግዲህ ተስፋ መቍረጥ፣ ፍጹም ጭንቀት ውስጥ መግባት፣ ራስንም ለማጥፋት ማሰብ በእጅጉ እያጠቃን ያለው በመሠረታዊነት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን መሠረታዊ የሕይወት ዓላማ ባለማወቃችን ምክንያት ነው። ለመኾኑ ለምን ተፈጠርን? ሦስት የተፈጠርንበትን ዓላማዎች በአጭሩ እንመልከት።
አንደኛው የተፈጠርንለት ዓላማ ፍቅር ነው። እግዚአብሔር እኛን የፈጠረን ከእኛ የሚያገኘው አንዳች ነገር ኖሮት አይደለም። ወይም እኛን ባይፈጥረን የሚያጣው ምንም ነገር አይኖርም። የእርሱ ክብርና ምስጋና በፍጥረት ላይ ጥገኛ የኾነና በፍጥረቱ መኖርና አለመኖር የሚጨምርና የሚቀንስ ነው ተብሎ ፈጽሞ አይነገርለትም። በባሕርይው ምንም ዓይነት ጉድለት የለበትምና። በመኾኑም እኛን የፈጠረን ፍጹም ስለ ኾነው ፍቅሩና ቸርነቱ መኾኑን ልብ እንላለን። በእርሱ ዘንድ ሦስትነቱ ከአንድነቱ ጋር የተስማማው ዘላለማዊ በኾነ ፍቅር ነው። እርሱ ራሱ ፍቅር ስለ ኾነ ከፍቅር ውጭ ኾኖ ኖሮ አያውቅም። የአካል ሦስትነት የባሕርይ አንድነቱን የማይከፋፍለው፤ የባሕርይ አንድነትም የአካል ሦስትነትን የማይጠቀልለው በእርሱ ዘንድ ስላለ ዘላለማዊ ፍቅር ነው። እኛንም የፈጠረንና እንድንኖርም የሚፈልገው ስለ ፍቅር ነው። አዳምን “ከዚህች ዛፍ ፍሬ አትብላ” ብሎ የከለከለው አዳም ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር በመታዘዝ ይገልጥለት ዘንድ ነው። እግዚአብሔር አዳምን ስለ ፍቅር ብሎ እንደ ፈጠረው አዳምም ለእግዚአብሔር ስለ ፍቅር ብሎ ይገዛለትና ትእዛዙን ይጠብቅ ዘንድ ተገቢ ነው። ዕፀ በለስ የፍቅር ምልክት ናትና። ትእዛዙም ለአዳም የተሰጠው አዳም ትእዛዝ በመጠበቅ ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ይገልጽ ዘንድ ነው። ጌታ በወንጌል “ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለ የሚጠብቀውም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ” ይላል፤ ዮሐ 14፥21። እንግዲህ ይህን የፍቅር ትስስር መሠረት አድርገን እንኖር ዘንድ የተፈጠርን ፍጡራን መኾናችንን እናስተውል።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ “በሥላሴ ውስጥ ያለው አንድነት በሰዎችም ዘንድ እንዲኖር በማቀድ እግዚአብሔር በሰዎች ተፈጥሮ ውስጥ በተለያየ መንገድ ፍቅርን ተክሏታል።” ይልና ቀጥሎ ስለ ምን እግዚአብሔር የሰውን ዘር በሙሉ ልክ እንደ አዳም ከምድር አፈር አላበጃቸውም? ስለ ምንስ እንደ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ አድርጎ አልፈጠራቸውም? ስለ ምንስ ከእርሱ የሚገኙ ልጆችን በየጥቂቱ እንዲያድጉ አደረጋቸው? ስለ ፍቅር ሲል እንዲህ አደረገ። በመውለድና በመወለድ ሂደት ውስጥ በሚፈጠረው ጥብቅ የኾነ ቍርኝት ፍቅር ሥር ሰዳ ትመሠረታለች። ይህቺም ፍቅር ሰዎች ኹሉ ፍጹም ወደ ኾነ አንድነት ታመጣቸዋለች። ቀጥሎ ስለ ምንስ እግዚአብሔር ሔዋንን ሲፈጥራት ልክ እንደ አዳም ከምድር አፈር አልፈጠራትም? ነገር ግን ከአካሉ አስገኛት? ብሎ ይጠይቅና ስለ ፍቅር ብሎ ይህን አደረገ ይለናል። ሊቁ “አንድ በሰውነታችን ጥልቅ ውስጥ የታተመ እኛ የማንረዳው ነገር ግን ከእኛ ተፈጥሮ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ፍቅር አለ” ይላል። (ሽመልስ መርጊያ (መ/ር)፣ 8ኛዋ ቀንና ሌሎችም፣ 2008 ዓ.ም፣ ገጽ 112)። እንግዲህ በዚህ ኹሉ መንገድ በእርጋታ ስንመለከት የሕይወት ዓላማው ፍቅር መኾኑን መገንዘብ እንችላለን። አካላዊ ቃል ሰው የኾነበት መሠረታዊ ምክንያትም ከዚህ የሕይወት ዓላማ ውጭ በኃጢአት ምክንያት የሄድነውን መልሶ ወደ ቀደመው አኗኗር ሊያመጣን ነው። ስለ ፍቅር ፈጠረን፣ ስለ ፍቅር ንስሓችንን ተቀበለ፣ ስለ ፍቅር ሰው ይኾንልን ዘንድ ቃል ገባ፣ ስለ ፍቅር ሰው ኾነልን፣ ስለ ፍቅር ብሎ የእኛን መከራ ተቀበለ።
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፦ “ክፉ አኗኗርህን የምትተውና ወደ እግዚአብሔር የምትመለሰው ቅጣትን ከመፍራት የተነሣና ከቅጣት ለማምለጥ ብቻ ስትል ካልኾነ፣ ወይም ደግሞ የመልካምን ነገር ዋጋ ለማግኘት ብቻ ስትል (እንደ ምንደኛ) ከማድረግና የመልካም ምግባር ሕይወትን በሒሳባዊ ስሌትና ጥቅምን በሚያብሰለስል ራስ ወዳድ ሕሊና የምትለውጥና የምትነግድ ከመኾን ነጻ መውጣት እውነተኛ ፍጹምነት ይህ ነው። ኹሉም ነገር ለኛ የተዘጋጀና የተጠበቀልን ስለ መኾኑ የተነገረንን ተስፋ አምነህና ተማምነህ የሚያጨንቅህና የሚያሳስብህ ነገር ኹሉ ከእግዚአብሔር ፍቅር እንዳትለይ ብቻ ሊኾን ይገባል፤ የሕይወት ታላቁ መዳረሻና የዳርቻ ፍጻሜ ከኾነው በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ከመኖርና በእርሱ የተወደደ ከመኾን የሚበልጥ አንዳችም ነገር የሌለ መኾኑን አስተውለህና ተረድተህ ብትኖር ታላቁ ፍጹምነት ማለት ይህ ነው።” እያለ እንዴት መኖር እንዳለብን ይመክረናል። (ያረጋል አበጋዝ (ዲ/ን)፣ መድሎተ ጽድቅ ቅጽ አንድ፣ 2007 ዓ.ም፣ ገጽ 116-117)። የሕይወት መዳረሻ ሊኾን የሚገባው ቅዱስ ጎርጎርዮስ እንዳለው በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ መኖር ነው። የተፈጠርነው ስለ ፍቅር እንደ ኾነ ኹሉ ልንኖርም የሚገባን ስለ ፍቅርና በፍቅር ነው። ክርስቶስን እኛን እስከ መስቀል ሞት የወደደን እኛ እርስ በእርሳችን በፍጹም እንዋደድ ዘንድ ነው።
ሰለሞንም “በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው” የሚለን ለዚህ ነው፤ መኃ 2፥4። በስተመጨረሻም ስለ ፍቅር እንኖር ዘንድም ትእዛዝን ሰጠን። ይኸውም፦ “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህቺ ናት” ብሎ አዘዘን፤ ዮሐ 15፥12። የሕይወት ዓላማው ይህ ከኾነ የክርስቶስን ፍቅር ረስተን እንዴት ራስን ስለማጥፋት እናስባለን? ወንድሜ ሆይ! ራስን ማጥፋት የሕይወትን ዓላማ መቃረን መኾኑን ልብ በል። አዳም ለትልቅ ቅጣት የተዳረገው የፍቅርን አቅጣጫ በመገልበጡና የሕይወት ዓላማ ከኾነው ፍቅር በመውጣቱ መኾኑን አስተውል። ያን በማድረጉስ ምን ያህል ጉዳት እንደ ደረሰበት ልብ በል። እንግዲያውስ ለጊዜው የመጣብህን ፈተና ተቋቁመህ የተፈጠርህለትን ፍቅር በሕይወትህ ለመግለጥ ብትጥር ምን ያህል ደስተኛ እንደምትኾን፥ ስለ ፍቅር የኖሩትን ሐዋርያትን በማሰብ ተረዳ! በፍቅር ስለ ፍቅር የምትኖር ከኾነ ማንኛውም ምድራዊ ነገር ሊያናውጽህ አይችልም። ኹል ጊዜም ቢኾን ፍቅርን የሕይወትህ መርሕ አድርገህ ተጓዝ።
ኹለተኛ የተፈጠርንለት ዓላማ መቀደስ ነው። ይህን የሕይወት ዓላማ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ኹኑ” ኦሪ ዘሌ 19፥2። የቅድስናን ሕይወት የሕይወታችን መርሕ እናደርግ ዘንድ ራሱ ባለቤቱ ጠርቶናል። ስለ ቅድስና ለመኖር መትጋት የሚጠበቅብን መኾኑን ልብ እንበል። የሞስኮው ፊላሬት የሕይወትን ዓላማ አስመልክቶ፦ “እያንዳንዱ ክርስቲያን ለራሱ ቅዱስ ለመኾን አስፈላጊና አበረታችን ነገር መፈለግ አለበት። ያለ ተጋድሎና ቅዱስ የመኾን ተስፋ የምትኖር ከኾነ፤ አንተ ክርስቲያን የኾንኸው በስም ብቻ ነው እንጂ በባሕርይው አይደለም። ነገር ግን ከቅዱስነት ውጭ ኾኖ ማንም ሰው ጌታን ሊያየው አይችልም፤ ይኸውም ማለት ዘለዓለማዊ ክብር ሊያገኙ አይችሉም ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው ኃጥአንን ሊያድን ነው ማለት ተገቢ ነው 1ጢሞ 1፥15። ነገር ግን ኃጢአተኛ ኾነን ሳለ የዳንን እንደ ኾነ አድርገን ካሰብን ራሳችንን እናታልላለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጥአንን ያደነው ቅዱሳን የመኾኛ መንገዱን በመስጠት ነውና።” ይላል። (St. Philaret of Moscow, Sermon of September 23, 1847)። ይህ የሊቁ አገላለጽ መኖር የሚገባን ቅዱሳንን ለመኾን መኾኑን በአጽንዖት የሚያሳስብ ነው። ክርስቶስ አምላካችን ሰው ኾኖ የተገለጠበት መሠረታዊ ምክንያትም እኛን ከኃጢአት አውጥቶ ወደ ቅድስና ለማስገባት ነውና። “ከእኔ ተማሩ” ብሎ መናገሩ በወንጌል መዘገቡ የእርሱን የአርአያነት ሥራ መሠረት አድርገን እንድንቀደስ ሲጋብዘን ነው።
ሰማዕቱ ኦንፊራይ ጋጋሉክ ቅድስና ኹላችንም የተጠራንለት የሕይወት ዓላማ መኾኑን ሲገልጽ፦ “ቅዱስነትን ማግኘት አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት የመነኮሳት ጒዳይ ብቻ አይደለም። ቤተሰብ ያሏቸው በዚህ ዓለም በተለያዩ ሞያዎች የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ለቅድስና ተጠርተዋል። ስለ ፍጽምናና ቅድስና የተሰጡ ትእዛዛት የተሰጡት ለመነክሳት ብቻ ሳይኾን ለሕዝብ ኹሉ ነውና።” ይላሎ። (Hieromartyr Onuphry Gagaluk)። ስለዚህ ኹላችንም የተጠራነው ለቅድስና መኾኑን ልናስተውል ይገባል። ውድ ወንድሜ ሆይ አንተ የተጠራኸው ለቅድስና መኾኑን አስተውል። ወጥረው የያዙህ እና ራስህን ወደ ማጥፋት ገፍተው የሚወስዱ ጒዳዮች ላይ ከምታተኩር ይልቅስ ስለ ሕይወትህ መቀደስ አስብ። በዚህ ዓለም ምንም ነገር አሌተሳካልኝም አትበል፤ የሕይወት ዋና ዓላማው መቀደስ ነውና፥ አኹን ከዚህ ሰዓት ጀምረህ ወደ ቅድስና መግባት እንደምትችል አስተውል። እኔ ረክሻለሁኝ ክፉን ነገር ማቆም አልችልም አትበል ይልቅስ በመስቀል ላይ በሕይወት መጨረሻ ላይ ወደ በጎነት የተቀየረው የቀኙኝ ሽፍታ አስበው። በመጨረሻዋ ሰዓት ወደ መልካምነት ሲመጣ ጌታም በፍቅር እንደ ተቀበለው አስተውል። አንተም እንዲህ መኾን የምትችል መኾንህን ከልብህ አምነህ አሐዱ ብለህ ጀምር።
ቴኦፋን እንዲህ ይላል፦ “የሕይወታችን ሥሙር መጨረሻው ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት መኖር ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ሥግው የኾነው በኃጢአት ምክንያት ውድቀን ያጣናትን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረችንን አንድነት ሊመልስል ነው። የእግዚአብሔር ልጅ በኾነው በኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ጋር ኅብረት ወደማድረግ እንገባል፤ ስለዚህም የሕይወትን ዓላማ እናገኛለን።” ይላል። (St. Theophan the Recluse, Letters to various people, 24)። እንግዲህ ይህ ሊቅ ደግሞ የሕይወት ዓላማው ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረንን ኅብረት ማግኘት ነው። ከእግዚአብሔር ከተለየን ከእውነተኛ የሕይወት ዓላማ ውጭ ኾነናል ማለት ነው። በምንም መንገድ ቢኾን ከእርሱ እቅፍ ልንወጣ አይገባንም። እግዚአብሔር ኹል ጊዜም አብረነው እንድንኾን ይፈልጋል። ኃጢአተኛ ነኝና እንዴት ከእርሱ ጋር መኖር እንችላለሁኝ አትበል፤ ይልቅስ ከእርሱ ጋር መኾንን ከውስጥህ ፈልጋት ያሌ እርሱ ራሱ ከኃጢአትህ አንጽቶ ካንተ ጋር መኾኑን ይገልጽልሃል። የሰርቢያው ኒቆላስ ደግሞ “ሰዎች ወደ ጦርነት የሚገቡት በጦርነቱ ለመደሰት ሳይኾን ከጦርነቱ ለመዳን እንደ ኾነ ኹሉ እኛም ወደዚህ ዓለም የገባነው በዚህ ዓለም ለመደሰት ሳይኾን ከዚህ ዓለም ለመዳን ነው። ሰዎች ወደ ጦርነት የሚገቡት ከጦርነቱ በላይ ስለ ኾነ የኾነ ጉደይ ነው እንዲሁም እኛም ወደዚህ ጊዜያዊ ሕይወት የገባነው ከዚያ በላይ ስለ ኾነ ጉዳይ ነው፤ ይኸውም ዘላለማዊ ሕይወት ነው። ወታደር ወደ ቤቱ መመለስን በደስታ እንደሚያስብ ኹሉ፤ ክርስቲያኖችም የሕይወታቸውን መጨረሻና ወደ አባታቸው ዓለም ወደ መንግሥተ ሰማያት መመለሳቸውን ሳያቋርጡ ያስባሉ።” ብሎ በምሳሌ ጥሩ አድርጎ በሕሊናችን ውስጥ የሕይወትን ዓላም በሥዕል መልክ ይቀርጽብናል። (St. Nicholas of Serbia, Thoughts on Good and Evil)።
ሦስተኛ የተፈጠርንለት ዓላማ ምስጋና ነው። ምስጋና በአንደበት ብቻ የሚቀርብ ነገር ሳይኾን በተግባራዊ ሕይወትም የሚቀርብ ጉዳይ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ “… ነገር ግን ምስጋና ሲባል እንዲሁ በቃላት ብቻ የሚቀርብ እንዳይመስላችሁ። ከቃላት በላይ በምግባር ለእግዚአብሔር ምስጋና ይቀርባል። ንጹሕ ምስጋና ይሄ ነውና እግዚአብሔርን በሕይወታችን እናመስግነው። መልካም ምግባርን እየሠራን ስናመሰግነው አባታችን ክብሩ ከፍ ከፍ ይላል። ስለዚህ ነጻ ከወጣንበት ቀንበር በመሸሽ ለአባታችን ንጹሕ ምስጋናን እናቅርብለት። … ስለዚህ በአንደበታችን ብቻ የምናመሰግነው አንኹን፤ ነቢዩ “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፤ በከንፈሮቹም ያከብረኛልና፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው” ብሎ እንደ ተናገረው እንዳይኾንብን ነጻ ከዘጣንባቸው ቀንበሮች አብዝተን በመሸሽም ጭምር እንጂ” ይላል። (ገብረ እግዚአብሔር ኪደ (ተርጓሚ)፣ ሰማዕትነት አያምልጣችሁ፣ 2007 ዓ.ም፣ ገጽ 145)። እኛና መላእክት የተፈጠርነው ስሙን ለማመስገን ክብሩን ለመውረስ ነው። የፈጠረንን አምላክ ኹል ጊዜም ቢኾን በማንኛውም ዓይነት ኹኔታ ውስጥ ብንኾን ልናመሰግነው ይገባናል። ጻድቁ ኢዮብ በዚያ ኹሉ መከራ ውስጥ ኾኖ “እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይኹን” ማለቱን አስተውል፤ ኢዮ 1፥21። በረሀብም፣ በችግርም፣ በሕማም፣ በስደትም፣ በኀዘንም በሌሎችም ኹኔታ ውስጥ ብንኾን እግዚአብሔር ላይ ልናማርር አይገባም፤ ይልቍንስ ኹሌም ልናመሰግነው ይገባል እንጂ። እንግዲህ ወዳጆች ሆይ! የሕይወት ዓላማው ምስጋና ከኾነ፤ ፈጣሪን ልታመሰግነው ይገባል እንጂ ራስህን ስለ ማጥፋት በማሰብ ልታሳዝነው ይገባልን?
ከክፉ ሕሊናት ለመጠበቅ አንዱ የሚያስፈልገን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በምስጋና መጥራት መኾኑን ልብ ልንል ይገባል። አባ ወቅሪስ እንዲህ አለ፦ “በሕሊናት እኲያትና በፈቃዳተ ሥጋ በሁከትና በመበጻበጽ መንፈስ ላይ እያለሁ ወደ አባ መቃርዮስ ሄድኩኝና ‘አባቴ ሆይ፣ ሕይወቴን እመራበትና እኖር ዘንድ ቃልን ንገረኝ’ አልኹት። አባ መቃርዮስም ‘የመርከቡን ገመድ ከመልህቁ ጋር አጥብቀህ እሰረው፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ቸርነትም መርከቧ በዚህ በዲያብሎሳዊ ማዕበልና ሁከት እንዲሁም በዚህ በከንቱው ዓለም ጥልቅ ጨለማ መካከል በደኅና ታልፋለች አለኝ።’ እኔም ይህ መርከብ ምንድን ነው? የመርከቡ ገመድስ ምንድን ነው? መልህቁስ ምንድን ነው? አልኹት። አባ መቃርዮስም እንዲህ አለኝ፦ “መርከብ ልብህ ነው፣ እርሱን ጠብቀው። የመርከቡ ገመድ ደግሞ መንፈስህ ነው፤ ቅዱሳንን በሚዋጓቸው ሁከቶችና ዲያብሎሳዊ ማዕበሎች ላይ የሚሠለጥንባቸውና ጸጥ የሚያደርጋቸው ወደብ ከኾነው መልህቅ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እሰረው። በእያንዳንዱ እስትንፋስ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ማረኝ፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አመሰግንሃለሁ” ማለት ቀላል አይደለምና። አዳኝ የኾነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በመጥራትና ገንዘብ በማድረግ ስንጸና የዲያብሎስን ማዕበል ጸጥ ያደርግልናል።” እንዲል። (ዘውዴ ገ/እግዚአብሔር (B.Th, PGD፣ የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ምሩቅ)፣ ታላቁ ቅዱስ መቃርዮስ፣ 2004 ዓ.ም፣ ገጽ 144-145)።
እንግዲህ ሳናቋርጥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! አመሰግንሃለሁ” ብለን ስንጣራ እርሱ በኃይሉ በልቡናችን እየተቀጣጠለ ያለውን ራስን የማጥፋት ስሜት ያርቅልናል። ኹል ጊዜም ቢኾን እግዚአብሔርን ማመስገን ራስን የማጥፋት ክፉ ሐሳብን ያርቅልናል። የእግዚአብሔርን ስም በየዕለቱ ማመስገን የክርስትና ሕይወት ጥዑም ዜማ ነው። ክርስቲያናዊ ሕይወትም በእውነተኛና ባልተቆረጠ ምስጋና የተመላ ነው። አዳምን በገነት ሰባት ዓመት ያቆየው በምስጋና መኖሩ ነው፤ ከገነትም እንዲባረር ያደረገው በተግባራዊ ሕይወቱ በመታዘዝ እግዚአብሔርን ከማመስገን ውጭ ራሱን ማድረጉ ነው። አካላዊ ቃልም ሥጋ ማርያምን ተዋሕዶ ሰብእናችንን ያከበረው በፍጹም የማይቆረጥ ምስጋና ሕይወታችንን እናጣፍጣት ዘንድ ነው። ከምጽአትም በኋላ የምንገባው ወደ ከበረው የቅዱሳን መላእክት የምስጋና ሕይወት ነው። ስለዚህ ሕይወታችን በምስጋና ውኃ ውስጥ በተመስጦ ልትኖር የተሰጠችን መኾኗን እናስተውላለን።
በማግሰኞ ውዳሴ አምላክ ላይ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው “ታጋሽ ሆይ፣ ለአንተ ምስጋና ይገባል። የምትችል፣ የምትጠብቅ ሆይ፣ ለአንተ ምስጋና ይገባል። ሰውን ይቅር የምትል ሆይ፣ ለአንተ ምስጋና ይገባል። ቸር ሆይ፣ ለአንተ ምስጋና ይገባል። ብቻህን ጥበበኛ የኾንህ ሆይ፣ ለአንተ ምስጋና ይገባል። ነፍስና ሥጋን ያሳመርህ ሆይ፣ ለአንተ ምስጋና ይገባል። ለደጎችና ለክፉዎች ፀሐይን የምታወጣ ሆይ፣ ለጻድቃንና ለኃጥአንም ዝናምን የምታዘንም ሆይ፣ ለአንተ ምስጋና ይገባል። የሰውን ልጅ ጠባይ ኹሉ እንደ አንድ ሰው አድርገህ ሕዝቡን ኹሉ የምትመግበው ሆይ፣ ለአንተ ምስጋና ይገባል። የሰማይ ወፎችን አራዊቱን፣ እንስሳቱን፣ እንደ ታናናሽ ወፎች የሚሞቱ ፍጥረታትን ኹሉ የምትመግበው ሆይ፣ ለአንተ ምስጋና ይገባል።” እያለ እግዚአብሔርን ያመሰግናል። (ተስፋ ሚካኤል ታከለ (ተርጓሚ)፣ ውዳሴ አምላክ፣ 2010 ዓ.ም፣ የማግሰኞ ቍ 1)። ስለዚህ እግዚአብሔርን ወደ ማመስገን ሕይወት እንመለስ፥ ከክፉ ሐሳብም ሕሊናችንን እንጠብቅ፣ እግዚአብሔር በቸርነቱ እውነተኛውን የሕይወት ዓላማ ተረድተን እንኖር ዘንድ ይርዳን አሜን።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
አሜን አሜን አሜን ቃለ ሕይወት ያሰማልን
እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ኹኑ” ኦሪ ዘሌ 19፥2። የቅድስናን ሕይወት የሕይወታችን መርሕ እናደርግ ዘንድ ራሱ ባለቤቱ ጠርቶናል። ስለ ቅድስና ለመኖር መትጋት የሚጠበቅብን መኾኑን ልብ እንበል። አሜን
አሜን ቃል ሕይወት ያሰማልን
አሜን ቃል ሕይወት ያሰማልን
አሜን!
Amen !!! kale hiwot yasemalin.
Amen Kale hiwot yasemalegn
ቃለ ህይወት ያሰማልን።
Amen.
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፣ አስበ መምህራንን ያድልልን። ፍቅር፣ መቀደስ እንዲሁም ምስጋና ብለው ስለ ሕይወታችን ዓላማዎች ያስተማሩን ትምህርት ጥልቅ እና መሳጭ ነው። እኛም በእውነት እኒህን እያሰብን በመንገዱ እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን🙏💐
ፍቅር, ቅድስና እና ምስጋና
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፣
ጥያቄ
በቀጣይ ስለ መክሊት እና አገልግሎት ቢቀርብልን እላለው
ክብረት ይስጥልኝ
ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
ፍቅር ቅድስና ምስጋና
ቃል ህይወትን ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
አሜን!! ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ማረኝ፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አመሠግንሃለው።
kale hiwot yasemaln.