መሆን እና መኖር

ቅዱስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር ተራራ የጌታችን መልኩ ተለውጦ ሲያበራ፤ ልብሱም በምድር አጣቢ ሊያነፃው ከሚችለው በላይ ነጭ ሲሆን፤ ሙሴና ኤልያስም መጥተው ከጌታ ጋር ሲነጋገሩ አይቶ የመጣለትን ሀሳብ የገለጠበት ቃል ነው ” በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው”።

አባቶች ቢርበንና ቢጠማን ሙሴ መና እያወረደ ውሃ እያፈለቀ፤ ጠላት ቢነሣብን ኤልያስ እሳት አውርዶ እያጠፋ፤ አንተ ደግሞ ብንታመም እየፈወስኸን ብንሞት እያነሳኸን በዚህ መሆን መልካም ነው ማለቱ እንደ ሆነ ይተረጉማሉ። 

ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ንግግሩ በዚያ ሥፍራ ብንገኝ ልናስበውና ልንመኘው የምንችለውን  ሁላችንን ወክሎ  ስሜታችንን ነው የተናገረው። ለሥጋችንና ለስሜታችን ምቾትና ደስታ የሚሰጥ ቦታ መሆን የሁላችን ምኞት ነው:: ቢሆንልን መሆን የምንፈልግ የት ይሆን? አሁን ያለንበት ቦታና ሁኔታ ውስጥ ያለነውስ ተመችቶን ወይም ያን ሆነን መኖርን አምነንበት ነው?

በእውነታው አንድ ነገር መሆንና (ሆኖ መገኘትና) የሆነውን መኖር እጅግ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ከትንሹ ብንጀምር በተሰማራንበት ሙያ ባለሙያ መሆንና ሙያውን መኖር ይለያያል። አንድ ሰው ፖሊስ ቢሆን ዩኒፎርም ለብሶ በሚንቀሳቀስበት የሥራ ሰዓቱ ወንጀል እየተከላከለ ከሥራ ውጭ ነኝ ብሎ ባሰበበት ሰዓት ወንጀል ሲፈፀም አይቶ በግዴለሽነት ካለፈ ፖሊስ ሆነ እንጂ ሙያውን አይኖረውም፡፡ የሕክምና ባለሙያስ ሙያውን መኖር ያለበት የት ይሆን? ብዙዎቻችንን የምንደስተው በ “መሆን” አችን እንጂ የሆነውን ስለ “መኖር” ተጨንቀን አናውቅም። መሆን ውስጥ ያለው ደስታና ምቾት ሲሆን መኖር ውስጥ ግን የሚጠብቀን ተግባርና ኃላፊነት ነው። ብዙዎቻችን ጌታ እግዚአብሔርን የምንለምነው የለመነውን ነገር እንድንሆን እንጂ የሆነውን እንድንኖረው አይደለም።

ትዳር የምንለምን ባል/ሚስት ስለ መሆን አብዝተን እንለምናለን የለመነውም ይሰጠናል። ትልቁ ችግር መሆን የለመነውን ለመኖር ፍላጎቱ፣ ዝግጁነቱና ቁርጠኝነቱ ስለሌለን በ “መሆን” ገነት የመሰለን ሕይወት በ “መኖር” ደረጃ ሲዖል ይሆንብናል። ስለዚህ ብዙዎቻችን ባል/ሚስት መሆን ችለናል ፤ ያልቻልነው ነገር ቢኖር ባል/ሚስት ሆነን መኖር ነው። ባል/ሚስት መሆን ምቾት አለው። ከቤተሰብ ጭቅጭቅ፣ ከጓደኞች የነገር ጉንተላ፣ ከማኅበረሰብ ሐሜት፣ ከዕድሜ ጋር የጎሪጥ ከመተያየት፣ ሰው ሁሉ በፈሰሰበት ቦይ መፍሰስ አለመቻል ከሚፈጥረው ጭንቀት፣ ወዘተ . . . ያሳርፋል። ባልነት/ሚስትነት የሚጠይቀውን መኖር ግን ያደክማል፤ ያታክታል። በመሆኑም ሚስትህን ባልሽ ነኝ ከማለትህ በፊት ባልነትን መኖርህን ጠይቅ፤ ባልሽን ሚስትህ ነኝ እኮ ከማለትሽ በፊት ሚስትነትን መኖርሽን ጠይቂ፤ ሁለቱ ለየቅል ነው:: መሆን ከብዶ አያውቅም የሆነውን መኖር እንጂ !!!

አባት/እናት መሆንም እንዲሁ ደስታና የኅሊና ምቾት አለው፤ ከምላስ ያድናል። ወላጅነትን መኖር ግን ስንቶቻችንን አታክቶን ልጆቻችን እንደ ምድረ በዳ አበቦች በክረምቱ ዝናምና በፀሐይ ብርሃን ብቻ አድገው እንዲፈኩ አስመኝቶናል። የመሆንና የመኖር ልዩነቱ አይጣል!!!

ከፍ ወዳለ ሀሳብ ሰንሄድ ሰው መሆንና እንደ ሰው መኖር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ሰው ለመሆን የፃፍነው ማመልከቻ፣ ያወጣነው ወጪ ወይም የደከምነው ድካም የለም። እኔ ስለ ራሴ እስከማስታውሰው ድረስ ሰው ያልነበርኩበት ጊዜን አላስታውስም። ስፀነስም ስወለድም ሰው ተብዬ እውቅና ተሰጥቶኛል፡፡ ሁላችንም እንዲሁ ነን። የሁላችንም ችግር ደግሞ ሰው መሆንን መኖር አለመቻላችን ነው:: ዳዊት ሰው የሆነውን ልጁን ሰሎሞንን “ልጄ ሆይ ሰው ሁን!” ያለዉ ሰውነትን ኑረው ሲለው ነው። ፈረስን ፈረስ ሁን፤ አንበሳን አንበሳ ሁን፤ እባብን እባብ ሁን ልንለው አንችልም። ምክንያቱም የሆኑትን ይኖሩታልና። ሰው ግን በመጀመሪያ የሆነውን የማወቅ ጸጋ ስለተሰጠው ማለት ፈረስ ፈረስ፣ አንበሳ አንበሳ፣ እባብም እባብ ምን መሆኑን አያውቁም፤ ሰው ግን ሰው መሆኑን ስለሚያውቅ። ሁለተኛ ሰው የሆነውን የመኖርም ሆነ ያለመኖር አቅም ስላለው ሌሎቹ ግን ስለሌላቸው የሆነውን በተግባርና በኃላፊነት እንዲገልጥ (እንዲኖር) ይጠየቃል፤ ይነገረዋል። የሆነውን በመኖር ካልገለጠው ግን የሆነውንም ያጠፋዋል።

የበለጠ ከፍ ወዳለው ስናልፍ ደግሞ እኛ ክርስቲያን ሆነናል። ክርስቲያን የመባል ቀጥተኛ ፍቺ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ማለት ነው። በመሆንና በመኖር ግን ትርጒሙ ይለያያል። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ማንም ሊነጥቀን አይችልም። ሲፈርድብን እንኳ እንደ ልጅ ነው:: ለፍርድ የሚያበቃን ግን የሆነውን አለመኖራችን ነው። 

እንደ እውነቱ ይህን ጽሑፍ ከምናነበው ውስጥ ክርስቲያን በመሆኑ የሚከፋና “ምን አቅብጦኝ ነው ክርስቲያን የሆንኩት” የሚል ወይም በአቅፋቸው ወስደው ያስጠመቁትን የሚረግም እንደሌለ እተማመናለው። ክርስትና ግን ክርስቲያን ከመሆን ባለፈ መኖርን ባትጠይቀን ምንኛ መልካም ነበር?! የምንልም ቁጥራችን ቀላል አይሆንም። እንደው በመሆን ብቻ ያቺ መንግሥት ብትወረስ ምን ነበረበት?! ግን የሆንከውን “መኖር” የሚል ግዴታ ተከተለው። 

አሁንም እናስተውል አብዛኞቻችን ክርስቲያን ለመሆን ምንም አልደከምንም:: ማስታወስ ከምንችልበት ጊዜ አንስቶ ክርስቲያን ያልነበርንበት ጊዜ ትዝ አይለንም። የሚገርመው ክርስትናን መኖር የቻልንበት ጊዜንም እንዲሁ አናስታውስም። ክርስቲያን መሆንንም በመታወቂያ ደረጃ ያልተውነው በዚህ መሆን ለእኛ መልካም መስሎ ስለታየን እንጂ መኖር ለሚጠበቅብን ቁርጠኛ ስለሆንን አይደለም። በክርስትና አስተምህሮ የሰማነው አምላክና እርሱን ከበው በሚኖሩ ቅዱሳን ዙሪያ ስለ መሆን የሰማነው ትርክት የሰጠን ምቾት ስላለ በዚህ መሆን መልካም ነው ብለን እናስባለን። ከገናናው ክብር ግን የሆነውን መኖር እንዳለብን የሚያስገነዝበው “እርሱን ስሙት” የሚለው ቃል ሲመጣ ለ “መኖር” ወድቀን እንደ ሞተ ሰው እንሆናለን፤ ሁሉን ወደ መኖር ያመጣው እጅ እስኪዳስሰን ድረስ።

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

12 አስተያየቶች

  1. በዚህ ዘመን የሆኑት በሕይወት የመግለጡ በመኖት የመገለጡ ነገር ቀጥ ያለ ዳገት የመውጣት ያህል ከዘማ በከፈ እርቆኛል…አቤቱ እኔን ደካማውን አስበኝ

    ክቡር ቀሲስ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን

  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን የሁላችን ችግር የሆነውን ሀሳብ ነው ያነሱልን የዚህ ሁሉ ነገር መነሻው እግዚአብሔርን በውስጣችንን አለመክተታችን ነው።ከፈጣሪ በላይ የኛ ምኞት በውስጣችን ተሰግስጓል

  3. በጣም ጥልቅ የሆነ ትምህርት ነው መምህራችን በትኩረት ካላነበብነው አይገባንም በትኩረት ካነበብነው የምናውቀውን በትኩረት እንድንኖርው ያጋድለናል።
    ቃለ ህይወት ያሰማልን በእድሜ በፀጋ ይጠብቅልን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *