በትሕትና ማደግ

ስለብዙ ነገር መጻፍ ይቻላል፤ ስለትሕትና ግን ለመናገር እና ለመጻፍ በኛ ደረጃ ላለ ድፍረት (ጥቂት ትዕቢት) ይፈልጋል። ትሑት ልትሆን ትችላለህ ግን ትሑት እንደሆንክ ባሰብክ ሰዓት ትህትናህን አጥተኸዋል። ትህትናን ከባድ የሚያደርገው ያ ነው። ትሁት እንደሆንክ እያሰብክ ትሁት መሆን አትችልም። ትህትና በመሆን ብቻ የሚገለጽ መንፈሳዊ ፍሬ ነው።

ዴቪድ በድቢል እንዲህ ይላል “ታዋቂ መሆን እፈልጋለሁ ምክንያቱም ስለታዋቂነቴ ትሁት መሆን እሻለሁ። ግን ምንድነው የኔ ትህትና በዚህ ወጥመድ ውስጥ ተቀርቅሬ?” ለዚህ ነው ትህትናን እንዳገኘናት መቼም እርግጠኛ የማንሆነው። ትሁት ለመሆን እንፈልጋለን ከዛ ያን ትህትና በማሳየት እንታበያለን። በስክሩቴፕ ደብዳቤው ሉዊሲ እንዲህ ይላል ወርምውድ የተባለው ሰይጣን አዲሱ ክርስቲያን ትሁት እየሆነ መምጣቱን ለታላቁ ሰይጣን ሲነግረው፣ ታላቅየው ሰይጣን ለወርሙድ ያለው ይሄን ነበር፤ “ወርምውድ እውነት ነው ታማሚህ (አዲሱ ክርስቲያንን ነው) መቼም ትሁት እንዲሆን ልትፈቅድለት አይገባም፤ ትሁት ሆነ ማለት እቅዳችንን ሁሉ ማሳካት አንችልም ማለት ነው። ስለዚህ ሂድ ትህትናውን አሳየው፣ ትሁት እንደሆነ ግለጥለት፤ ስለትህትናው ይወቅ ፥ መኖሩ የታወቀ ትህትና ትህትና መሆኑ ያበቃለታል።”

አንድሪው መሬ እንዳለው ከትዕቢቶች ሁሉ በላይ የከፋው በቅድስናችን መታበይ ነው። ብዙዎቻችን ያለምንም ምክንያት ትሁት እንደሆን እናስባለን ምክንያቱም ትሁት የሚመስሉ ቃላቶችን ስለተጠቀምን ወይም አንገታችንን ስላቀረቀርን ወይም ትዕቢትን ስለተጠየፍን፤ እውነታው ግን ትዕቢተኞች በሆንን መጠን በሌሎች ላይ የሚታይን ጥቂቷን ትዕቢት ራሱ መታገስ አንችልም። ዊሊያም ሎ እንዳለው ትህትናን መለማመድ ከፈለግህ ትዕቢተኛ እንደሆንህ ማወቅ እና ማመን ያስፈልጋል፤ በሕይወትህ ሁሉ በዚህ በሽታ የተጠቃህ ነህና።

በትህትና ማደግ

አሁን ውይይታችንን እንጀምር ፥ ትዕቢተኛው በዚህ ለሚመስሉት የጻፈው በሚል መነሻ። መጀመሪያ ግን ለምን በትህትና እንደግ ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ትዕቢት እንዴት የከፋ ነገር ነው ፥ ትህትናስ በፈጣሪያችን ዓይን እንደምን ያማረ ነው?

• 2ኛ ሳሙ 22፥28 “አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፤ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ።”

• ኢሳ 66፥2 “ እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።”

• መዝ 107፥6 “እግዚአብሔር ትሑታንን ያነሣል፥ ኃጢአተኞችን ግን እስከ ምድር ድረስ ያዋርዳል።

• ምሳ 3፥34 “በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።”

• ትን.ሚክ 6፥8 “ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወጅ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?”

• ማቴ 18፥4 “እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው።”

• ሉቃ 14፥11 “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።”

• ኤፌ 4፥2 “በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤”

• ያዕ 4፥10 “በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።”

• 1ጴጥ 5፥5 “እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”

የቤተክርስቲያን አባቶችም በተግባራቸው እንደገለጡት ከመካከላቸው ታላቅ ሆኖ የሚወጣው ሁልጊዜ ለራሱ ዝቅተኛ ቦታ ያለው ነው። ራሱን ከልቡ ያነሰ እንደሆነ የሚያስብ አባት በእግዚአብሔር ከሌሎች ሁሉ አበው ተለይቶ ሲከብር ተጽፎ አንብበናል። አውግስጢኖስ እንዳለው “አንድ ታዋቂ የንግግር ጥበብ አዋቂ  በንግግር ትምህርት ውስጥ ትልቁ ሕግ ምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ ፥ መናገር አለ። ሁለተኛው ትልቁ ሕግስ ቢባል መናገር አለ አሁንም። ሦስተኛውስ ተብሎ ሲጠየቅ ፥ ሦስተኛውም መናገር ነው አለ። እኔንም በክርስትና ትልቁ ሕግ ምንድነው ብትሉኝ፣ ሁለተኛውም ሦስተኛውም ሁልጊዜ ትህትና ነው የምላችሁ” ይላል።

ዊልያም ሎ እንዳለው ሃይማኖትን ከትህትና ውጪ መኖር ማለት ከዓይን ውጪ ማየት እችላለሁ እንደማለት ነው ወይም ሳይተነፍሱ በሕይወት እቆያለው ብሎ እንደማሰብ ነው ይላል። በጥልቀት ካሰባችሁበት ሰው ያለትህትና እግዚአብሔርን ማወቅ አይችልም። ከፍ ያለውን ለማየት ዝቅ ማለት ያስፈልጋል። አባታችን ሆይ የሚለው የጸሎቶች ሁሉ አውራ ሲጀምር በሰማያት ያለኸው አባታችን ብሎ ነው የሚጣራው። መቼስ እግዚአብሔርን ከደመናት በላይ አስቀምጠነው ፥ ቦታን (space) ከሱ በላይ በሚያደርግ ሀሳብ እየጸለይን እንዳልሆነ ይገባናል።  እርሱ ከየትኛውም ስፍራ በላይ ግዙፍ ነው ፥ ሰማያት ይጠቡታል። በርግጥ ደግሞ እርሱ ረቂቅ ነው በዚህም ልባችንን ዙፋኑ ማድረግ ይቻለዋል። በሰማይ እንዳለው ሁሉ በጥልቁ ሲዖልም እሱ በዛ አለ። ያለእርሱ ምንም ነገር ሕልውና የለውምና። ነገር ግን “በሰማያት ያለው” የምንለው የኛን በዝቅተኛው ምድር ማለትም በውድቀት እና ውርደት ስፍራ ላይ ሆነን የሱን የፍቅር ከፍታ አንጋጠን እያየን ስለሆነ ነው ፥ ያን ሰማያዊ አባት ነው ዝቅ ብለን የምንጠራው። እሱ ሁልጊዜ ከላይ ነው፤ ከፍቅር ዝቅ ብሎ፣ ከፍትሕ ወርዶ፣ ከምሕረት ጎድሎ፣ ከኃይል ተቀንሶ፣ ከምልዓት አንሶ አያውቅም። እኛ ግን ከምድር ነው ይሄን ጥሪ የምናቀርበው። የኢዮብ ምሬት ከኢዮብ ወዳጆች መልካም ቃላት በላይ የተወደደው እኮ ለዚህ ነው፤ ኢዮብ ከቆመበት ሥፍራ ሆኖ እግዚአብሔርን ጠራው፤ ከሕመሙ፣ ሕመሙ ካስከተለበት ቁጣ፣ እጦቱ ካመጣበት የስሜት ጉስቁልና ሆኖ እግዚአብሔርን ጠራው ፥ ከምድር ሆኖ። አላስመሰለም፣ ልቡ ተከፍቶ አንደበቱ አልመረቀም፣ ምሬት ውጦት አድናቆት አፉን አልሞላም። ካለበት ሆኖ እግዚአብሔርን ጠራው። ወዳጆቹ ግን ይሄ ታላቅ ምስጢር ተሰውሮባቸው ሳለ ፥ እንደሚያውቁ አስመሰሉ፣ ኢዮብን እግዚአብሔር እንደሚናገረው ከታላቅ ዙፋን ተናገሩት፣ ፈርተው ሳለ ከፍርድ ወንበር ከማስመሰል ከፍታ ተናገሩ። ምድር ላይ ከሆንን ከምድር እንጥራው፣ ተናደን ሳለ ከእርጋታ ከፍታ፣ ጥላቻ ወርሶን ሳለ ከፍቅር ከፍታ፣ በቀል አንዶን ሳለ ከሀሰት የምህረት ፋፋቴ አንጥራው ፥ ከአለንበት እንጀምር።

ትዕቢት ግን ከከፍታ ለማየት ስለሚሞክር ፥ ጌታችን ከገለጠልን ሰማያዊ አባት ጋር መገናኘት ይሳነዋል። ራሱን በከፍታ አስቀምጦ ስለሚናገር የእግዚአብሔርን ከፍታ ማየት እና ማግኘት አይችልም። ለዚህ ነው ነቢዩ ኢሳይያስ (57፥15) እንዲህ ያለው “ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል። የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ።” ጌታችንም በተራራው ላይ ስብከቱ ከዚህ ዝቅታ የሚጸልዩ ብቻ ወደ ከፍታው መንግስቱ እንደሚገቡ ነግሮናል “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።” (ማቴ 5፥3)። ውርደትን ትዕቢት እንደምትቀድማት ሁሉ ትህትናን ከፍታ ይከተለዋል። (ምሳ 11፥2)።

የትዕቢት መሠረት ራሳን ከሌላው ጋር ማነጻጸር እንደሆነ ሁሉ፤ ትዕቢት ሌሎችን የመብለጥ ጥማት ነው። ከባልንጀራህ በላይ ሀብታም የመሆን ጥማት፣ ከባልንጀራህ በላይ ጎበዝ የመሆን ጥማት፣ ከባልንጀራህ በላይ ታዋቂ የመሆን ጥማት፣ ከባልንጀራህ በላይ ትሁት የመሆን ጥማት፣ ከባልንጀራህ በላይ ጻድቅ የመሆን ጥማት፣ ከባልንጀራህ በላይ ታዋቂ የመሆን ጥማት እንደሆነ ሁሉ ፥ ትህትናም ራስን የማነጻጸር ውጤት ነው። ከማን ጋር? በልቡ የዋህ እና ትሁት ከሆነው ከጌታችን ጋር። በርሱ ፊት እንዴት ደቃቅ እንደሆንን የማወቅ ውጤት ነው፣ የኛ የሆነ እና ከርሱ ያልተቀበልነው ምንም ምን እንደሌለ የማወቅ ውጤት ነው። ማንነታችንን ገልጦ በሚያያው በሱ ፊት ከፍቅሩ ውጪ ምንም የምንመካበት ነገር እንደሌለን ራሳችንን ከሱ ጋር በማነጻጸር የምናውቅበት ውጤት ነው። ሁሉን ከእሱ እንደተቀበልን ካመንን ስለየትኛው ነገር ነው የምንታበየው? ሁሉ ከኛ ሊወሰድ እንደሚችል ካመንን እንዴት በራሳችን ሁሉን እንዳልተቀበልን እንመካለን?

ይሄን ስናስተውል የዛኔ እሱን እንፈራለን ፥ ያለእርሱ ፈቃድ በኛ ላይ ምንም ማድረግ የማይችሉትን ደግሞ ከመፍራት እንቆጠባለን። ምክንያቱም ትዕቢት ማለት አንድም ያለአግባብ የዋለ ፍርሃት ማለት ነው። ፍርሃት ቦታውን ሲስት ትዕቢትን ይወልዳል። ኃያሉን እግዚአብሔር መፍራት አቁመን ደካማውን ሰው ስንፈራ ትዕቢት ይወለዳል። በሰዎች ፊት ጎድሎ የመታየት ፍርሃት ነው ትዕቢትን የሚወልደው። ሰዎች እውነተኛ ማንነታችንን ቢያውቁ ወይም እንደማንም መሆናችንን ቢረዱ ይንቁናል ወይም ከኛ ይርቃሉ ወይም የምንፈልገውን ነገር አይሰጡንም የሚለው ፍርሃት ነው አንደኛው የትዕቢት ምንጭ።

ነገር ግን በጸጋው ብዛት ፥ በምህረቱም ጥልቀት ልጆች እንድንሆን የጠራን እግዚአብሔርን ስንመለከት፤ እኛ ስለራሳችን ከምናውቀው ደካማነት በላይ፣ ትላንት እና ዛሬ የበደልነውን ብቻ አይደለም ወደፊትም እንደምንበድለው እና እንደምንክደው እያወቀ የሚወደን አምላክ እንዳለን ሲገባን የዛኔ ከዚህ አግባብ ያልሆነ ፍርሃት እንላቀቃለን።

ለዚህ ነው ትህትና ማለት ከፍርሃት መላቀቅ ማለት የሚሆነው። በሰዎች ፊት አንሶ ያለመታየት እና የመናቅ እና የመጠላት ፍርሃት ሲለቀን ነው ትህትናን ገንዘብ የምናደርገው። ይሄ ግን በእርሱ የምህረቱ ብዛት በጸጋው የሚቻል እንጂ በኛ ጥረት ብቻ አይደለም። ጸጋው ወደ ትህትና እንደሚመራን ሁሉ የክርስቶስን ጸጋ ለመቀበል ደግሞ ትህትና ያስፈልጋል። ማለት ትህትና ነው ጸጋው እንዲሰራ የሚያደርገው። ጸጋው ነው ትሑት እንድንሆን የሚያደርገን።  ትህትና ነው ጸጋውን እንድንቀበል የሚያስችለን።

በአዲስ ኪዳን ላይ ስለእምነታቸው በጌታችን የተደነቁ ሰዎች ፥ ትሕትና ነበር ለእምነታቸው መደነቅ ምክንያት የሆነው። ወደ ቤቴ ልትገባ አይገባህም ያለው መቶ አለቃ ፥ ጌታ ያደነቀለት እምነቱን ነበር ፥ መቶ አለቃው ግን ራስን የማዋረድ ተምሳሌት ነው፤ ራሷን ከውሾች ጋር አንድ በማድረግ የወዳደቀ ምግቦች ለውሾች እንደሚሰጠው ለርሷም የርሱ የምህርት እጅ ሊዘረጋ እንደሚገባ የለመነችው ያቺ ከነናዊት ሴትም ፥ እምነትሽ ታላቅ ነው የተባለችው። ይሄም የሰው ልጅ በማመን ብቻ ትህትናን እንደሚለብስ ሲነግረን ነው ፥ ግን ደግሞ በትህትና ብቻ ነው ወደ ፍጹም እምነትም የምንደርሰው።

የሚወዱትን አምላክ ሳይሆን እውነተኛውን አምላክ ለማየት የፈቀዱ ሰዎች ነበሩ እነዚህ የአዲስ ኪዳን አማኞች። የምንፈልገውን አምላክ ሳይሆን እውነተኛውን አምላክ ለማየት ስንፈቅድ እና በእርሱ ላይ ምንም ምን መብት እንደሌለን ስናውቅ ነው ያ ትሕትና መስራት የሚጀምረው። ጸሎታችን እሱን ለመቀየር ሳይሆን እኛን ለመለወጥ ሲሆን እናየዋለን። እሱ በሰማያት ነው ያለው እኛ ነን ከጥልቁ መውጣት የሚያሻን። ከእኔነት ጥልቀት፣ ከወረድንበት ውርደት ወደ ማይቀየረው እንዲቀይረን ስንማጸን ነው  እሱን የምናውቀው። የዛኔ ጌታችን እንዴት ያለ ትሁት እንደሆነ ይገባናል። ለትህትናዋ በፍጥረት መኃል ወደር የሌላትን የድንግል ማርያም ማሕጸን ውስጥ ለማደር ፍቃዷን ጠየቀ፤ ከኃጢአት ጠብቆ ለራሱ ማደሪያነት ያቆየውን ሰውነት ለመግባት ፍቃድ ጠየቀ። ራሱ ያበጃጀውን ሰውነት እንደ እንግዳ እና እንደ ባዕድ ልግባበት ብሎ መልዕክተኛ ላከ። ይሄ እንዴት ያለ ትሕትና ነው? እንዴት ያለ ሰውን ማክበር ነው ፥ እርሱ የሆነውን ጥቂቱን ብንናገር አከበርነው እንናለን እኛን ግን ከሚገባን በላይ ሰጠን። ከሚመጥነን በላይ ወደደን። ይሄ ለሸክላ የሚገባው ክብር አልነበረም። ድንግል ማርያምም ይሄ የፈጣሪ ትህትና ቢደንቃት ፥ እንዲህ ያለ ክብር ለባሪያው ምንድነው ብላ አደነቀች። “ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በተነ ፥ ትሑታንን ግን ከፍ አድርጓል” አለችን ፍጥረት መድረስ የሚችለው የመጨረሻ ከፍታ ላይ የወጣችው ድንግል ማርያም።

ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ ይሄን ከላይ ጀምሮ የተገለጸውን እንዴት በሚገርም ውበት እንዳስተማረን እንይ “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድስ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤” (ፊል 2፥3፡11)። በሰዓቱ እንዲያከብረን ፥ ራሳችንን እንደጌታችን እናዋርድ። መዋረድን እንደመቀማት ላለመቁጥር እንጸልይ። በጊዜው ከፍ እንዲያደርገን ፥ በጊዜዬአችን ፈልገን እንዋረድ። መርጠን ዝቅ እንበል።

በመጨረሻ ለዚህ ጽሑፍ ትልቅ ግብአት የሆነኝ መምህር ትህትናን ለመለማመድ እንድንችል ማድረግ ስላለብን ደረጃዎች የዘረዘረውን ልጥቀስና ላብቃ፤

1) ለሌሎች ትችት እንዴት እንደምንመልስ እናስተውል፤

ብዙ ጊዜ “የማንረባ እና ደካሞች፣ ከንቱዎች እንደሆን” እንናገራለን፤ ግን ማንም እንደዚያ እንደሆንን ቢያምን እና ያን መልሶ ቢነግረን ይከፋናል። እንናደዳለን። ትሑት ሰው ግን ግሳፄ እና ትችት የሚገቡት እንደሆነ ያውቃል፤ ራሱ የተናገረው እውነት ስለሆነ ሌሎች ሲነግሩትም አይከፋውም።

ሰዎች ሲተቹን እና ሲገስጹን የመጀመሪያው መልሳችን መሆን ያለበት “አመሰግናለሁ። አስብበታለሁ። ልክ ልትሆኑ ትችላላችሁ።” ይሁን መልሳችን። ራስን ነጻ እና ንጹህ ከማድረግ ሱስ እንላቀቅ። ትችትን በደስታ እንቀበል። አንሽሸው።

2) ለሰዎች ትዕቢት የምንመልስበትን መንገድ እናስተውል፤

ዊልያም ሎ እንዳለው በትዕቢት የተሞላ ሰው የሌሎችን የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል ትዕቢት መታገስ አይቻለውም። የሌሎች ትዕቢት ሲመረን ያ ሰው ለኛ ቦታ ስለሌለው ይሆናል። ይሄም በዛ ሰው ፊት መዋረዳችን ነው ያመመን። ለዚህም ይሆናል ትዕቢተኛን በቀላሉ ማወቅ የምንችለው ፥ ለኛ ትዕቢት ቦታ ስለማይኖረው። እንዲህ ያለው ሰው ሲገጥመን የትህትና መማርያ እናድርገው::

3) ለመከራ እና ለመናቅ የምናሳየውን ባህሪ እናስተውል፤ 

ትሑት ሰው ባሪያ ሆኖ ሳለ ከጌታው የተሻለ ክብርን አይሻም፤ የትኛውም ባሪያ ከጌታው የበለጠ ሊከበር ሊወደድ አይገባውና። ጌታችን ከተሰቃየ፣ መከራንም ከተቀበለ፣ በሰዎች ፊት፣ በአለቆች ፊት ከተናቀ ለኛ እሱ ከተቀበለው በላይ ክብር መፈለግ ትዕቢት ነው። ጆርጅ ማክዶናልድ እንዳለው “የሰው ልጅ (ጌታችን) እስከሞት ድረስ የተሰቃየው ፥ እኛ ሰዎች እንዳንሰቃይ ሳይሆን የኛ ስቃይ እንደእርሱ እንዲሆን ነው።” ከሱ ስቃይ ጋር ስቃያችን እንዲቆጠር ነው። ስለዚህ በዚህ ምድር ክብርን መፈለግ ከጌታችን በላይ ለመሆን መመኘት ነው።

4) ከማን ጋር እንደምንገጥም እናስተውል፤

ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ትዕቢተኞች አትሁኑ ፥ ከእናንተም ከሚያንሱ ጋር ለመወዳጀት ፍቀዱ እንዳለው፤ ይሄንንም ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ባሪያ ከሆነው ከአናሲሞስ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መስርቶ እንዳሳየን ፥ ከኛ በሁሉ ነገር ዝቅ ካሉ ሰዎች ጋር ለመወዳጀት እንጣር። ከተከበሩ፣ ከታወቁ፣ ከአዋቂ ሰዎች ጋር ለመታየት፣ ፎቶ ለመነሳት ከመጣር ያላነሰ ከኛ ከሚያንሱ፣ ማህበረሰብ ቦታ ከማይሰጣቸው ሰዎች ጋር ለመሆን እንፍቀድ።

5) ከጌታችን ትምህርት ወስደን ፥ ከኛ ክብር በታች የሆኑ ተግባሮችን ለመስራት እንፍቀድ፤ 

ሌሎች መስራት የማይፈልጉትን እንስራ። ሰዎች የሚሸሹትን አገልግሎት እናገልግል። ቆሻሻ መጥረግን፣ ማስተናገድን፣ ለታናናሾች የተተውትን አገልግሎት ሆን ብለን እንምረጥ። ይሄን ነው ዝቅ ብሎ እግር ያጠበው ጌታችን ያስተማረን። ይሄን ደግሞ ለታይታ አናድርግ፤ ይሄን የማያደርጉትንም እኔ እንደነሱ አይደለሁም በሚል ትዕቢት ላለመመልከት እንጣር።

6) በሌሎች ውድቀት እና ኃጢአት ፃድቅነታችሁን ስትለኩ ራሳችሁን ከያዛችሁት፤ የራሳችሁን ደካማነት እና ኃጢአት የበለጠ አስቡ።

7) በጌታችን እና በቅዱሳን ስም በድብቅ በጎ ነገርን ለሰዎች አድርጉ፤ ከዛም ለማንም አትናገሩ፤ በድብቅ ይጽና ለዘላለም። ያን ማድረግ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በፍጥነት ትደርሱበታላችሁ።

8) ለሰዎች ስንል የውሸት ገጽታ ግንባታን ከማድረግ እንቆጠበ።

ባዚል ፓስካል እንዳለው ባለን ሕይወት እና በራሳችን አንረካም፤ ስለዚህ በሰው አዕምሮ ውስጥ ሀሳብ ወለድ (imaginary) የሆነ ሕይወትን  መኖር እንሻለን። በዚህም ምክንያት መብለጥ፣ ማንጸባረቅ እንፈልጋለን። ይሄን ሀሳብ ወለድ (imaginary) ማንነት ለመጠበቅ እንደክማለን በዚህም ለእውነተኛው ማንነታችን ቦታ የለንም። ርጋታ፣ ደግነት፣ እውነተኝነት ባህሪያችን ከሆነ ያን ማንነታችንን ለሰው ለማሳወቅ እና ከሀሳብ ወለዱ ማንነታችን ጋር ለማጣበቅ እንተጋለን። እነዚህን መልካም ባህሪያችንን ከራሳችን ለይተን ከሀሳብ ወለዱ ማንነታችን ጋር እናስተሳስረዋለን። ጀግና ለመባል ፈሪዎች መሆንን እንመርጣለን። የከንቱ ማንነታችን መገለጫው አንዱ በአንዱ ብቻ መርካት አለመቻላችን ነው። ስለዚህ እውነተኛ ማንነታንችንን እንክደዋለን። ለክብራችን ለመሞት እንወዳለን።

9) ምክር እና ሀሳብ ከመስጠት እንቆጠብ፤ 

ዘሎ የመምከር እና ሰውን የማቃናት ፍላጎታችንን እንግታ። ከዛ ይልቅ አጠገባችን ባለው እና በሚያወራን ሰው ላይ እናተኩር። አጠገባችን ያለው ሰው ሕይወት ያለውን ውበት እናድንቅ። በተለይ ሰዎች ችግራቸውን ሲነግሩን የኛ ሀሳብ ልዩ ስለሆነ አድርገን አናስብ። መደመጥ ፈልገው እንደሆነና፣ ብንችል በጸሎታችን እንድናስባቸው ይሁን እንጂ ለመምከር አንፍጠን።

10) የምስጋና ሕይወትን እንምራ። አመስጋኝነት ትሕትና የሚበቅልበት ለም አፈር ነው።

11) መታዘዝን እንማር ፥ ራስን መስጠት እንለማመድ። መታዘዝ የሚፈልጉትን ማድረግ አይደለም። እሱማ ሕጻናትም የሚወዱትን እንዲያደርጉ ሲነገራቸው ያደርጋሉ። የማንወደውን እና የማንፈልገውን ማድረግ እንጂ።  

12) ሰዎችን እናክብር ፥ ለእውቀታቸው እና ለስብዕናቸው እውቅና እንስጥ፤  

ሰዎችን በመተቸት እና በማዋረድ የእኛን ክብር በድብቅ ከፍ ከማድረግ ይልቅ ለሰዎች እውቀት፣ ስብዕና፣ አገልግሎት እውቅና እንስጥ። እንዴት የእነሱ ማንነት እና ትምህርት እኛን እንደለወጠን በይፋ እንግለጽ። በሌሎች ስኬት የመቅናትን ቅርምት እንዋጋ።

13) ትሕትናን አንፍራው፤ 

ትሕትና የጸጋ በር ነው፣ ትሕትና የክብር ዙፋን ነው፣ ትህትና የከፍታ መቅድም ነው፣ ትህትና የዓለማት ጌታን ወደእኛ የሚያቀርብ ሠረገላ ነው፤ ስለዚህ እንዲህ እያልን እንጸልይ “ጌታ ሆይ ምንም ቢወስድ ፥ ምንም ቢፈጅ ትሑት አድርገኝ።”

Share your love

19 አስተያየቶች

  1. እጅግ በጣም አስተማሪ ነው። ለመተግበርና ለመኖር እንድንችል እግዚአብሔር ያግዘን!
    ቃለ ሕይወትን ያሰማልን! መንግስተ ሰማያትን ያዋርስልን!

  2. እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ሕይወትን ያሰማልን! መንግስተ ሰማያትን ያዋርስልን

  3. “ጌታ ሆይ ምንም ቢወስድ ፥ ምንም ቢፈጅ ትሑት አድርገኝ።”

    ቃለ ሕይወትን ያሰማልን!

    • “ጌታ ሆይ ምንም ቢወስድ ፥ ምንም ቢፈጅ ትሑት አድርገኝ።”
      የህይወትን ቃል ያሰማልን!

  4. …የሚወዱትን አምላክ ሳይሆን እውነተኛውን አምላክ ለማየት የፈቀዱ ሰዎች ነበሩ እነዚህ የአዲስ ኪዳን አማኞች።
    ቃለ ሕይወትን ያሰማልን!

  5. • ሉቃ 14፥11 “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።” ከልጅነቴ ጀምሮ የማውቀው ይሄን ነበር ። ሌለውን እንዳውቅ ስላረጋቹኝ አመሰግናለሁ ።🙏🙏🙏

  6. ቃለ ሕይወት ያሰማልን። የትህትናን ጸጋ ለሁላችን ያድለን። ይሄን ክፉ ትዕቢት ያሳድልን መድኀኔዓለም።

  7. የሰማነውን በዕዝነ ልቦናችን ይደርብን፡፡ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡

  8. እንደ ችርነት ነው እንደኛ ሃሳብ መች ትህትና ላይ መድረስ እንችላለን፡፡
    አለማመኔን እርዳው ጌታ ሆይ!
    ቃለ ሕይወትን ያሰማልን! አሜን!!!

  9. የአገልግሎት ዘመናችሁን ይባርክልን፣ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፣ ተስፋ መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን!

  10. እግዚአብሔር ይመስገን ትልቅ ትምህርት ነው ያስተማሩን. ቃለህይወትን ያሰማልን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *