ካናዳዊው የግእዝ ሊቅ

መቻኮል ካልፈለግህና ቀስ ያለ ሒደት እንደሆነ ካመንህ ግእዝን መማር ቀላል ነው

 አውግስጢኖስ ዲክንሰን ካናዳዊ የኢትዮጵያ ጥናት ባለሞያ (Ethiopicist) ነው። በመካከለኛው ዘመን ጥናት (Medieval Studies) ሁለተኛ ዲግሪውን በዋተርሉ እና ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲዎች ሠርቷል። ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የታሪክ፣ የላቲን/ ሮማይስጥ እና የግእዝ ቋንቋ እውቀት አለው። 

እንግዳችን አውግስጢኖስ በአሁኑ ሰዓት በጀርመን ሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ በዓለም በግእዝ ቋንቋ እና ሥነ-ጽሑፍ ጥናት ቀዳሚ ናቸው ከሚባሉት ፕሮፌሰር አሌሳንድሮ ባውሲ እና ፕሮፌሰር ዴኒስ ኖስቲንቲን ሥር በኢትዮጵያ ጥናት የዶክትሬት ዲግሪውን እየሠራ ሲሆን፥ ትኩረት ያደረገውም በመልክእ ሥነ ጽሑፍ ላይ ነው። የጃንደረባው ሚዲያ የሰንበት ቃለ መጠይቅ እንግዳ አድርገን ጋብዘነዋል።

ጃንደረባው:- የጥናት መስክህን ከኮምፒውተር ሳይንስ ወደ ሜዲቫል ስተዲስ ቀይረሃል፡፡ ይህንን ለውጥ እንድታደርግ ያነሣሣህ ምን ነበር? በዚህ የጥናት መስክ ላይ ፍላጎት እንዳለህ እንዴት አውቀህ ልትወስን ቻልህ? ሒደቱን እስቲ አካፍለን?

አውግስጢኖስ ዲከንሰን:- ቀድሞውኑም ታሪክ ላይ ዝንባሌው ነበረኝ፡፡ አንድ ሰው በሙያ ዘርፉ ሊያደርገው የሚችለው ነገር ሆኖ ግን አይታየኝም ነበር፡፡ ሕፃን እያለሁ ኢልቦለድ የሆኑ የታሪክ መጻሕፍትን እና ትናንሽ ታሪካዊ ልቦለዶችን አነብ ነበር፡፡ በዓሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ስሆን ደግሞ ከአዳዲሶቹ ይልቅ ጥንታዊ ሥነ ጽሑፎች ምርጫዎቼ ነበሩ፡፡ ልጆች ታሪክ ላይ ፍላጎት ማሳየታቸው እንግዳ ነገር ባይሆንም እኔ ግን ስሞች ላይ ፣ ዓመትና ቀናት ላይ ፣ ታሪካዊ ክስተቶች ላይ እና ሰዎች ቸል ብለው የሚያልፏቸው ጥቃቅን ነገሮች ላይ ጭምር የማወቅ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ 

ዩኒቨርሲቲ ስገባ ኮምፒውተር ሳይንስን አታካችና የማያረካ ሆነብኝ፡፡ የጥናት ዘርፍ ስመርጥ የመካከለኛው ዘመን ጥናት መግቢያን (Introduction to Medieval Studies) መረጥሁ፡፡ ይህ ትምህርትም የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ የሚያስቃኝ ሳይሆን ዘርፉን እንደ ትምህርት ዘርፍ የሚያስተዋውቅ (በሥሩ ያሉትን ዘርፎችና የጥናት ዘዴዎችን የሚያጠና) ነበረ፡፡ ትምህርቱ በእውነትም የሚመስጥ ነበረ፡፡ ለማስተማር መሠጠት ያለው ፕሮፌሰር በማግኘቴም ዕድለኛ ነበርሁ፡፡

ስለ ድርሳናት፣ ስለፓሌዎግራፊ Palaeography (የጥንታዊ መዛግብት የአጻጻፍ መንገድና እድሜያቸውን መለያ መንገዶች የሚያጠና ዘርፍ)፣ ኮዲኮሎጂ Codicology (መዛግብትንና እርስ በእርስ ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠና ዘርፍ)፣ ኑሚስማቲክስ Numismatics (የሳንቲሞች፣ የገንዘብ ኖታዎችና የሜዳሊያዎች ጥናት)፣ ስለ ፊሎሎጂ Philology (የቋንቋዎችን ቅርጽ፣ ታሪካዊ አመጣጥ እንዲሁም የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያጠና ዘርፍ) ማውራት ለእኔ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ጨረፍታውን ብቻ ያየሁት ራሱን የቻለ ዓለም ሲሆን ከዚያ በኋላም ሙሉ በሙሉ ልሰምጥበት የምፈልገው ዓይነት ሆኖ አገኘሁት፡፡ ኮርሱ እየተጠናቀቀ ሲመጣ የጥናት መስኬን መቀየር እንዳለብኝ እጅጉን ተሰምቶኝ ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ ከዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች ጋር በዚሁ ፕሮፌሰር የሚመራ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ መሳተፌ ሙሉ ለሙሉ ቆርጬ እንድወስን አደረገኝ።  

ጃንደረባው :- ወደ ኢትዮጵያ ጥናትስ ትኩረት እንድታደርግ በቅድሚያ የሳበህ ነገር ምንድርን ነው? በጉዳዩ ላይ እንድታተኩር ምን አነሳሳህ?

አውግስጢኖስ ዲከንሰን:- በማእከላዊው ዘመን [በመካከለኛው ዘመን ፣ ከ5ኛው መቶ/ክ/ዘ – 15ኛው መቶ/ክ/ዘ] ጥናት ላይ የመስቀል ጦረኞች ክስተት ትኩረቴን ስቦት ነበር፡፡ ብዙ ታሪኮች የሚጀምሩት በምዕራብ አውሮፓ የነበሩ ሥነ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወደ መስቀል ጦረኝነት እንዴት እንዳመሩ የነበረ ሲሆን የሲቴቨን ሩንሲማን ባለ ሦስት መድበል ታሪክ ግን ከእስልምና መስፋፋት በፊት ስለነበረው የምሥራቅ ክርስቲያኖች ውዝግብ እና በለዘብተኞች [should be ምስራቃውያን አገሮች (ሊባኖስ, ሶርያ, ጆርዳን, እስራኤል, ፍልስጤም, ቆጵሮስ እንዲሁም የድሮዋ አርመንያ)]ላይ ስላመጣው ጉዳት በመተንተን የሚጀምር ነበረ፡፡  

ይህም በምሥራቅና ኦሪየንታል ክርስትና እና በነገረ መለኮት ውዝግቦች ዙሪያ ጥልቅ ፍላጎት እንዲያድርብኝ አደረገ፡፡ በመጨረሻ በኮፕቲክ ኢንሳይክሎፔዲያ ላይ በኢትዮጵያ ስለነበሩ የነገረ መለኮት ውዝግቦች የሚተነትኑ የአቶ ጌታቸው ኃይሌ የመግቢያ መጣጥፎች ጋር ተገጣጠምን፡፡ እና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የበለጠ ለማንበብ ፍላጎቴ ጨመረ፡፡ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የክርስትና ታሪክ ጥናት ፍቅርም ወደቅሁኝ።

ጃንደረባው :- የግእዝ ቋንቋን ስለተማርህበት ሁኔታ መስማት የሚያጓጓ ነገር ነው፡፡ ግእዝ ለመማር ያስቸገሩህ ሁኔታዎችስ ምን ነበሩ? እንዴትስ ተወጣሃቸው? የኢትዮጵያን ታሪክ ፣ ባሕልና ሥነ ጽሑፍ ለማጥናት ግእዝ ቋንቋ ምን ያህል ረዳህ?

አውግስጢኖስ ዲከንሰን:- ከእኔ የእይታ መነጽር ግእዝን በምማርበት ወቅት ትልቁ ተግዳሮት ቀድሞ ስሠራባቸው ከነበሩት ቋንቋዎች ጋር እጅግ ሰፊ ልዩነቶች ካሏቸው የግእዝ አገላለጾች ጋር መተዋወቅና መግባባቱ ላይ ነበር፡፡ 

የግእዝ የቃላት ሥርዓት ከዚያ በፊት በትምህርት ቤት ስማራቸው ከነበሩት ለምሳሌ ከፈረሳይኛ ፣ ከላቲን እና ከግሪክ ቋንቋዎች እጅግ በጣም የተለየ ነው፡፡ የተለየ ድምፅ ያላቸውን ቃላት በመያዝ ወይም የተለየ ቅደም ተከተሎችን በማወቅ ዙሪያ ሳይሆን በግእዝ ቋንቋ ውስጥ ነገሮች የሚገለጹበትና የማይገለጹበት ልዩ የሆነ መንገድ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር መሠረታዊ ልዩነት ያለው አድርጎታል፡፡ 

ስለዚህ አንድ ሰው ግእዝን ለመመርመር በመጀመሪያ እንዴት ማንበብ እንዳለበት ዳግም መማር ይኖርበታል፡፡ ይህን እውነታ ግን ሰዎችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አይደለም፡፡ እንዲያውም እጅግ ውብ የሆነ ነገር ነው፡፡

ጊዜና ልምምድ እንደሚያስፈልገውና መቻኮል የማይፈልግ ቀስ ያለ ሒደት እንደሆነ አምኖ ለተቀበለ ሰው ግእዝን በአግባቡ ማንበብ በእርግጥም የሚቻል ነገር ነው፡፡ ራሱን ፊሎሎጂስት ብሎ እንደሚጠራ ሰው ግእዝን መማር እጅግ አስፈላጊና የኢትዮጵያን ታሪክና ባሕል ለመረዳት ወሳኙ ነገር ይመስለኛል፡፡ በእኔ አስተያየት ታሪክን በትክክል ለመረዳት የሚቻለው አንደኛው በቀጥታ ማስረጃዎችን በመመርመር ነው፡፡ ያሉት እውነተኛ የማስረጃ ዓይነቶች ደግሞ ጽሑፋዊና ከርሰ ምድራዊ ናቸው፡፡

ስለዚህ አስፈላጊ የሆኑትን ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን ለማንበብ የግድ ግእዝን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ስነ ጽሑፎቹ ሲጻፉ የነበሩበትን ሁኔታ (ዐውድ) ለመረዳትና በጽሑፎቹ ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ ህጸጾችን ወይንም መለያየቶችን ለማስታረቅ በቂ አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ይጠይቃል።

ጃንደረባው:- ስለ ማስተርስ መመረቂያ ጥናትህ ትንሽ ብትነግረን? ጥናትህ በንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ድርሳናት ላይ ስላለው በጊዜው ስለነበረው አስማትን ውድቅ የማድረግ ክስተት ላይ ያተኮረ ነው። ይህን ርእስ እንዴት ልትመርጠው ቻልክ?

አውግስጢኖስ ዲከንሰን:- የጥናት አማካሪዬ በአስማት ታሪክ ላይ አተኩረው የሚያጠኑ ፕሮፌሰር መሆናቸውና የኔም በዘመኑ (በመካከለኛው ዘመን ፣ ከ5ኛው መቶ/ክ/ዘ – 15ኛው መቶ/ክ/ዘ) የነበሩትን ሃይማኖታዊ ውዝግቦች ለማጥናት የነበረኝ ፍላጎት መገጣጠሙ ይህ ርእስ እንዲመረጥ መንገዱን ጠርጓል። 

በዚያ ዘመን በነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እጅግ ብዙ ጥናቶች ቢሠሩም አሁንም ገና የመጀመሪያዎቹን የማዕዘን ድንጋዮች የማስቀመጥ ያህል ብቻ መሥራት እንደጀመርን ይሰማኛል። ተጨማሪ ከጥፋት የተረፉ ግልጽ ማስረጃዎች እንዲኖሩ ብንመኝም አሁን ያሉንን ያህል በመገኘታቸው ራሱ እድለኞች ነን። የተገኙት ማስረጃዎች ብቻ እንኳን ገና ብዙ ሥራ መሥራት ያስችላሉ::

ጃንደረባው :- የኢትዮጲያን ቋንቋዎች፣ ታሪክና ባሕል ጥናት ከጀመርክ በኋላ ያስተካከልካቸው ስለኢትዮጲያ በሰፊው የሚታመኑ የተሳሳቱ ሃሳቦች ነበሩህ? ካሉ ምን ምን ነበሩ? ስለሃገሪቷና ህዝቦቿ ይበልጥ ስታውቅ ስለኢትዮጵያ ያለህ አረዳድ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ አመጣ?

አውግስጢኖስ ዲከንሰን :- ከሁሉም የሚበልጠው “ኢትዮጵያ ከሌሎች ተነጥላ የምትኖር የክርስቲያን ሀገር ናት” የሚለው ነው። ይህም ብዙ ጊዜ ታዋቂ በሆኑና ሰፊ ተቀባይነት ባላቸው ምንጮች ተደጋግሞ ሲባል የኖረና ለማንኛውም ጉዳዩን በገረፍታ ለሚያይ ሰው ምክንያታዊ መስሎ ሊታየው የሚችል ነገር ነው። 

“ኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ባልሆኑ ሀገራት ተከብባ ከኖረች በእርግጠኝነት ከሌሎች ተገልላ ያለምንም ውጪያዊ ተጽዕኖ ኖራለች ማለት አይደለምን?” የሚል ሰው ይኖራል:: ይሁንና ያለው ማስረጃ የሚያሳየው ግን ከዚህ ተቃራኒና እጅግ የሚደንቅ ታሪክን ነው:: ኢትዮጵያ በዓለም አሉ ከሚባሉት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ጋር ግንኙነት ነበራት። በግብፅ ያሉ ገዳማት ቢሉ፣ በኢየሩሳሌም፣ በሶርያ (እንደ ሳይድናያ) እንዲሁም በሮም ካሉ ክርስቲያኖች ጋር የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ግንኙነት ነበራቸው፤ ሥነ ጽሑፍ እና ሥእላትም በየጊዜው ይለዋወጡ ነበር።

ጃንደረባው:- አዲስ ባሕልን ማጥናት አስደሳችም አስቸጋሪም ሊሆን ይችላል። እንደ አንድ የውጭ ሀገር ሰው ስለ ኢትዮጵያ ሲጠና ሊያጋጥም ይችላል የምትለውን ከሁሉም የሚበልጥ ከባድ ፈተና ልትነግረን ትችላለህ? አንተስ ይህን እንዴት አለፍከው?  

አውግስጢኖስ ዲከንሰን:- ለተጓዦች ያስቸግራሉ ብዬ የማስበው የማይጠብቋቸውን ትንንሽ ነገሮች ናቸው። ለትልልቆቹ ልዩነቶች ለመዘጋጀት ይቀላል። ምን መጠበቅ እንዳለብን ስናውቅ ነገሮች ይቀልላሉ። 

ቀላል የሚመስሉና በሁሉም ዘንድ የሚታወቁ ናቸው ብለን የምናስባቸው ነገሮች ወይንም ደግሞ ኢትዮጵያውያን በሁሉም ዘንድ የሚታወቁ ናቸው ብለው የሚያስቧቸው ነገሮች ናቸው አስቸጋሪ የሚሆኑት። ለምሳሌ ወደ ቤታቸው የጋበዙኝ ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን ምስጋናዬን ለማሳየት ትንሽ ሥጦታ ይዤ ባለመሔዴ ተቀይመውኝ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጲያውያን እጅግ እንግዳ ተቀባይና ደግ ሕዝብ መሆናቸው አለመግባባቶችን ለመፍታት ያግዛል።

ጃንደረባው :- የመመረቂያ ጥናት ርእስን ምርጫ ግለሰቡ ላይ የሚመሠረትና በዝንባሌው፣ ስለ አንድ ርእስ ለማወቅ ባለ ጉጉትና ፍላጎት ላይ ተመርኩዞ የሚደረግ ነው። በተለይ ስለ መልክእ ሥነ ጽሑፍ ለማጥናት ምን እንደሳበህ ልትነግረን ትችላለህ? በተጨማሪም በመልክ ስነ ጽሑፍ ጥናትህ ላይ የምታተኩርበት ርእሰ ጉዳይ ይኖር ይሆን?

አውግስጢኖስ ዲከንሰን:- ገና ስለ መልክእ ከሰማሁበት ጊዜ ጀምሮ የተሰማኝ እጅግ የመደነቅና የአክብሮት ስሜት ነበረ:: ሁሌም ላነብባቸውና ስለእነርሱ ልማር ብፈልግም ከኔ አቅም በላይ እንደሆኑ ይሰማኝ ነበር። ከግእዝ ንባብ ጋር እየተላምድኩኝ ስመጣ ግን በትክክለኛው ልምምድና ቁርጠኝነት ምንም ነገር ማንበብ እንደምችል አወቅሁኝ። 

ይህን ማለቴ ግን ዋጋውን ያሳንሰዋል ወይንም ምስጢራዊነቱን ያስቀረዋል እያልኩኝ አይደለም፤ እንደውም ይበልጥ በተረዳነው መጠን ያለን ክብርና አድናቆት ይጨምራል:: በምዕራቡ ዓለም የትምህርት ተቋማትም መልክእ የሚገባውን አይነት ቦታ እንዳልተሠጠው እረዳለሁ። እንዲህ ያለ እጅግ ብዙና ውብ የሆነ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ችላ ተብሏል:: አንዳንዴም በትክክል የሚረዳው ሳይኖር ቆይቷል። ስለዚህም ይህ ጉዳይ ላይ ጥናት ማድረግ የሚያስኬድ ጥሩ እድል እንደሆነና እኔም በርከት ያለ አስተዋጽኦ ላደርግበት የምችልበት ርእስ እንደሆነ አሰብኩኝ።

ስለመልክ በጣም ከሚያስገርሙት ነገሮች አንዱ ምን ያህል ከኢትዮጲያ ባህልና ክርስትና ጋር የተዋሐደ እንደሆነ ነው። ለየግላቸው ተነጥለው ሊጠኑ የሚችሉ ጉዳዮች ሲኖሩ፣ መልክ በጸሐፊው ዓለም ያሉ ብዙ ርእሰ ጉዳዮችን በአንድ አዋድዶ ለማንሳት የሚያስቻል አቅም አለው። ከገድላት፣ ከተአምራት እንዲሁም ከሃይማኖታዊ የስነ ጽሑፍ ስራዎች ጀምሮ ከማይጠበቁ ምንጮች ሁሉ ሃሳቦች ሲነሱ እናገኛለን። ለምሳሌ መልከ ኢየሉጣ ላይ በተአምረ ማርያም ላይ የሚገኝ ተአምር ተጠቅሶ እናገኛለን። እንስሳት የሚጠቀሱባቸው ቦታዎችም ፊሳልጎስ ከተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኙ ምሳሌዎችን ሲያጣቅሱ ይስተዋላል። ቁጥሮች ላይ እንኳን አስር ጣቶቻችንን የአስርቱ ትእዛዛት፣ ሁለቱን ወርቾች የሰለሞን ቤተ መቅደስ ምሰሶዎች ምሳሌ ተደርገው ሲነሱ እናያለን። እነዚህ ሁሉ ጠባያት በሰዋሰውና በቃላት አጠቃቀም በሚራቀቅ አስደናቂ የግጥም አጻጻፍ ዘዴ ወደአንድ ይመጣሉ። ቢያንስ በእኔ አስተያየት ይህ እንዲሁ ተራ የሆነ ትግል ሳይሆን [ለሚያጠናው ሰው] በስተመጨረሻ ትልቅ እርካታን የሚያጎናጽፍ ሽልማት ያለው ነው። ስለምናነበው የጽሑፍ አካል ብቻ ሳይሆን ስለሚጠቅሳቸው መጻሕፍት፣ ስለሚጠቀምባቸው ቃላት ወዘተ. እንማርበታለን።  

ጃንደረባው :- በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያጋጠሙህን ልምዶችህን ብታካፍለን፤ ወደዚህች ቤተ ክርስቲያን የሳበህ ምንድነው? 

አውግስጢኖስ ዲከንሰን:- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለጸጋ እና ውብ ቤተ ክርስቲያን ናት። ብዙ ጊዜ ቤተ እምነቶች ላይ ከቆይታ በኋላ አንድ ወደ መምሰል የመምጣት አዝማሚያ ይታያል:: ይህ ያለምንም ተጽእኖ ብቻ ሳይሆን የቤተ እምነቱ አባላት በሚያደርጓቸው ጫናዎች ምክንያት የሚመጣ ነው። ቅዳሴን እንደምሳሌ ብናነሳ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ወደሮማዊነት መልክ እንዲሁም የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቅዳሴ ወደባይዛንታይን መልክ ብዙ ምእት ዓመት የተሻገሩ ስርአቶችን በመተው (መሥዋዕት በማድረግ) እንዲቀየሩ የተደረጉበትን ሁኔታ ማንሳት ይቻላል። 

ወደምንጩ ስንመለስ እጅግ አስገራሚና ውብ የሆኑ ልዩ ልዩ ነገሮችን (ሥርአቶች፣ ጽሑፎች ወዘተ.) በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን እናገኛለን፤ በእርግጠኝነት አሁን ዘመን ላይ ባለን የመመሳሰል ፍላጎት የምናዳፍናቸው ልዩ ልዩ ሃብቶች ነበሩ:: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው ብዝኃነት ያለው ትውፊትና ሥርዓት በጣም አስደሳችና ልዩ ሲሆኑ ለምሥራቃዊ ኦርቶዶክስ ክርስትና ሀብትም አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድም በውስጧ በሚገኘው ብዝኃነት ያለው ትውፊትና ሥርዓት እንዲሁም ሲሰፋ ደግሞ ለምሥራቃዊው ኦርቶዶክስ ክርስትና በምታበረክተው ሀብትዋ ምክንያት የተለየች ናት! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓቶች ከብዙ የኢትዮጵያ ባሕሎች ፣ ከቄስ ት/ቤቶቹ፣ ከስብከትና ዝማሬዎቹ፣ ከማኅበረሰቡና ከበጎ አድራጎቶቹ ጋር ያላቸውን ትስስር ስንመለከት ስለቤተ ክርስቲያኗ ሥርዓት ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ሳያውቁ የብዙ ኢትዮጲያውያንን ባህላዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ ሃይማኖታዊና ፓለቲካዊ ዐውድ ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመረዳት አስቸጋሪ መሆኑን እንረዳለን።

ጃንደረባው:- የመልክእ ሥነ-ጽሑፍን እንደሚያጠና ተማሪ፥ አንተም መልክእ እንደምትደርስ ሰምተናል። እስቲ ከደረስከው መካከል ቀንጭበህ ለአንባቢዎቻችን አጋራልን።

አውግስጢኖስ ዲከንሰን:- 

ሰላም፡ ለለ፡ ዐይነ፡ ዚአኪ፡ ምንዱባነ፡ ዓለም፡ እንተ፡ ትሬኢ፨
ወለአእዛንኪ፡ ሰላም፡ ቃለ፡ መልአክ፡ አንቲ፡ ትሰምዒ፨
ጣዕዋ፡ ማርያም፡ እክለ፡ ኂሩት፡ ትሬዒ፨
ንዒ፡ ሠናይትየ፡ ኀቤየ፡ ንዒ፨
ምስለ፡ ጊዮርጊስ፡ ከራድዮን፡ ፍጡን፡ ረዳኢ፨

ሰላም፡ እብል፡ ለመላትሕኪ፡ ወለአእናፍኪ፡ እሳለማ፨
ለከናፍርኪ፡ ሰላም፡ ወለአስናንኪ፡ ጽዱላነ፡ ግርማ፨
ማርያም፡ ድንግል፡ ጽጌ፡ ሐና፡ ቅድስት፡ እማ፨
ባልሕኒ፡ እምጻዕረ፡ ሲኦል፡ በእንተ፡ አንብዕኪ፡ ዘዘንማ፨
ከመ፡ ታነሥኦሙ፡ ለደቂቃ፡ ኦፍ፡ ጰልቃን፡ ዘስማ፨

ሰላም፡ ለልሳንኪ፡ ወለቃልኪ፡ ኑዛዜ፡ ለነዳይ፡ ብእሲ፨
ለእስትንፋስኪ፡ ሰላም፡ ወለጕርዔኪ፡ ሐዳሲ፨
ማርያም፡ ድንግል፡ ወላዲተ፡ አምላክ፡ ነጋሢ፨
አንጽሕኒ፡ እምነ፡ ርኵስ፡ በማየ፡ በረክትኪ፡ ቀዳሲ፨
ከመ፡ ሀየል፡ ያውፅኦ፡ ለፀሩ፡ ከይሲ፨

ሰላም፡ ለክሳድኪ፡ ላዕለ፡ መታክፍት፡ ዘዘዚአኪ፨ 
አምላክ፡ መኖቅሪጥስ፡ ቀርበኪ፡ ወኀይለ፡ ልዑል፡ ጸለለኪ፨
በዕንቍ፡ ተሰርጎኪ፡ ማርያም፡ ወበአልባሰ፡ ወርቅ፡ ተዐጸፍኪ፨
ጐሥዐ፡ ልበ፡ ዚአየ፡ በከመ፡ ዳዊት፡ ይቤለኪ፨
ፈተወ፡ ንጉሥ፡ ሥነኪ፡ እስመ፡ ውእቱ፡ እግዚእኪ፨

ሰላም፡ ለዘባንኪ፡ ጸዋረ፡ ሕፃንኪ፡ በጊዜ፡ ጕያ፨
ወለእንግድዓኪ፡ ሰላም፡ አረፍተ፡ ቅድስት፡ አቅሌስያ፨
ማርያም፡ ብርጋና፡ ወክርስቶስ፡ ባሕርያ፨
ታብርህ፡ ለፍኖትየ፡ ውስተ፡ ዓለመ፡ ጽልመት፡ ንያ፨
በብርሃንኪ፡ ወርኀ፡ ገሃህ፡ ዘተሰመየት፡ አሶንያ፨

Share your love

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *