በዚያ መንገድ ዳግመኛ አትመለሱ (ዘዳ. 17፥16)

የዓለም መድኅን የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደቡባዊ የይሁዳ ክፍል ልዩ ስሟ ቤተ ልሔም በተባለችው ስፍራ፣ ሄሮድስ በነገሠበት ዘመን ተወለደ፡፡ ሰብአ ሰገል ለተወለደው ሕፃን ለንጉሥ የሚገባውን እጅ መንሻ ሊያቀርቡለት መጡ፡፡  ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፡፡ በኢየሩሳሌም ከእርሱ ጋር የካህናትንም አለቆች የአሕዛብንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንደሚወለድ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “አንቺ ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ በይሁዳ ከነገሡ ነገሥታት ከቶ አታንሽም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢዩ ሚክያስ ነግሧልና ቤተ ልሔም” ነው አሉት (ሚክ. 5፥2)፡፡

ሄሮድስ የካህናት አለቆች የሕዝብ ጻፎች የነገሩትን ከያዘ በኋላ ሰብአ ሰገልን (የጥበብ ሰዎች) በስውር ጠርቶ ኮከብ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፡፡ ወደ ቤተ ልሔም እነርሱን ልኮ፤ ሒዱ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው፡፡ ሊሰግድለት ፈልጎ አይደለም ሊገድለው ወዶ ነው እንጂ፡፡

ሰብአ ሰገልም ንጉሡ ሄሮድስን ሰምተው ሔዱ፡፡ እነሆም በምሥራቅ ያዩት ኮከብ (መልአኩ) ሕፃኑ ባለበት ቦታ ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር፡፡ ኮከቡን መልአኩን ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው፡፡ የሁለት ዓመት ጎዳና መርቶ ኢየሩሳሌም ሲገቡ ከሄሮድስ ጋር ሲገናኙ ተሰውሯቸው ነበርና አሁን ሲታያቸው ደስ ተሰኙ፡፡ 

ከዚያም ወደ ቤተ ልሔም የከብቶች በረት ግርግም ውስጥ ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፣ ወድቀውም ሰገዱለት ሳጥናቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ አቀረቡለት፡፡ ሰብአ ሰገል የጥበብ ሰዎች የሁለት ዓመት መንገድ ተጉዘው እጅ መንሻን አቅርበው የተወለደውን ሕፃን ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክነቱን ከተረዱ በኋላ ወደ ንጉሡ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ከመልአኩ ተረድተው “ወነገሮሙ በሕልም ከመ ኢይግብኡ ኀበ ሄሮድስ ” እንዲል ” በሄሮድስ በኩል እንዳይመለሱ በራእይ ተነገሯቸው በሌላ መንገድ በሌላ ጎዳና ወደ ሀገራቸው” ተመልሰዋል፡፡ማቴ.2፥12

ሰብአ ሰገል ሁለት ዓመት ፈጅቶባቸው ወደ ቤተልሔም የመጡትን መንገድ ሲመለሱ ግን ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አግኝተው ለእርሱ ሰግደው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ (ሲሔዱ) በሌላ መንገድ ኃይል ተሰጥቷቸው ፵ ቀን ብቻ ነው የፈጀባቸው፡፡ የይሁዳ ንጉሥ እያሉ መጥተው አምላክ እያሉ ተመልሰዋል ሲል (በማቴ. 2፥1-12 ትርጓሜ ወንጌል) ይገልጥልናል፡፡

በመጡበት መንገድ አለመመለሳቸውን እና በሌላ መንገድ (ፍና ካልዕ) መሔዳቸውን ወደ ሄሮድስ አለመመለሳቸውን “And being warned of God in a dream that they should not return to Herod, they departed into their own country another way.”  Matthew 2፥12 (KJV) (Fr.Tadros Y.Malaty) የግብፅ ቤተ ክርስቲያን አባት ታድሮስ ያዕቆብ  ማላቲ የማቴዎስ ወንጌልን በተረጎሙበት መጽሐፍ የቀደምት ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ትርጓሜ በመጥቀስ ስለ ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) የሚከተለውን ብለዋል።

ሰብአ ሰገል ለአማኞች ለኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ለበዓል አከባበርና ለሥርዓተ አምልኮ አርአያ ምሳሌ ናቸው፡፡ በቤተ ልሔም በኤፍራታ የተወለደውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ማክበር ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት ነውና እርሱን ካገኙ በኋላ በሄሮድስ በጊዜያዊ ገዥ በሰይጣን መንገድ መመለስ ፤ በዓላትን ክርስቲያናዊ ባልሆነ መንገድ ማክበር እንደማይገባን አስተምረዋል።

ቅዱስ አንብሮስ ዘሚላን  እና ታላቁ ጎርጎርዮስም በአዲሱ መንገድ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሊጓዙ፣ ሊመላለሱ፣ በዓላትን ሊያከብሩ እና  ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚወስደውን መንገድ ሊይዙ እንደሚገባ ገልጸዋል። በሄሮድስ መንገድ መመለስ፣ በዓላትን በኦርቶዶክሳዊ መንገድ አለማክበር (እንደ ክርስቲያን አለማክበር) በቤተልሔም የተወለደውን፣ በቀራንዮ የተሰቀለውን አዳኙን መሲሑን ኢየሱስ ክርስቶስን ዳግመኛ መስቀል እና ለቤዛ ቀን የታተምንበትን  ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ማሳዘን ነው(ዕብ.10፥28-30፣ኤፌ.4፥30)

በዓለ ልደቱን ስናከብር እግዚአብሔርን እና ሰዎችን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ሊሆን ይገባል እንጂ ፤ ድሆችን ፣ ጠያቂ የሌላቸውን በየአብያተ ክርስቲያናት ደጅ የሚጠኑትን በመዘንጋት መሆን አይገባም ፡፡ በዓለ ልደት አካላዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ሆኖ የተወለደበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡ ይህም የሰውን ዘር ለማዳን የተደረገ  ደገኛ በዓላችን ነው። 

የጌታችንን የልደት በዓል በማክበር የሚገኘውን ጥቅም “እመቦ ዘአክበረ ልደተ እግዚእ ይከውን ክብሩ ምስለ ሰብአ ሰገል፤ የጌታችን በዓለ ልደት የሚያከብር ሰው ቢኖር ክብሩ (በተወለደ ጊዜ ተገኝተው መብአ ሰጥተው እንዳከበሩት) እንደ ሰብአ ሰገል ይሆንለታል” እንዳለ ትርጓሜ ወንጌል ከበዓለ ልደቱ ጥቅም በረከት ለማግኘት የሚጠበቅብን ባልተገባ መንገድ ባለመመላለስ እና በዓሉን በሚገባ ማክበር ነው፡፡

ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከተገናኙ፣ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከተወለዱ፣ ወደ ቤቴል ቤተ እግዚአብሔር ከመጡ በኋላ  ወደ ኋላ መመለስ የቀደመውን ያልተገባ አኗኗር መከተል ውጤቱ ሞት የሆነ ከእግዚአብሔር መለየት ነው የሚሆነው። በቤተልሔም የተወለደውን ሕጻን ከአገኘን በኋላ  ከኃይል ወደ ኃይል ለመሸጋገር የኋላውን እየተውን የፊቱን ለመያዝ ይበልጥ መትጋት ወደፊት መራመድ ይጠበቅብናል (ፊል.3፥13፣ ሉቃ. 21፥31፣ ሮሜ.8፥6)፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በጻፋቸው ቀዳማዊና ካልአይ መልእክቱ በሃይማኖት ለወለዳቸው በምግባር ላሳደጋቸው ክርስቲያኖች ቀድሞ በሥጋ ፈቃድ እንደ አሕዛብ በሥጋ ምኞት ይኖሩ የነበረበትን የቀደመውን የሥጋ ምኞት ተከትለው በሚያመጣው ወጥመድ እንዳይወድቁ ከክፉ ምኞት እንዲርቁ፣ ከኃጢአት እንዲጠበቁ በምኞት እንዳይወድቁ፣ በመጡበት መንገድ እንዳይመለሱ ከክፉ ምኞት ባርነት እንዲላቀቁ “አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ” በማለት ጽፎላቸዋል (1ኛ ጴጥ. 1፥14)፡፡

ከዚያ በማስቀጠልም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ  ብርቱዎችና ትጉሃን ምእመናንን አይቶ ደግሞ የጀመሩትን በጎ ትጋትና በጎ ቅንነት ሳይነቅፍ በቀጣይ ኑሮአቸው የያዝነው ይበቃናል ሳይሉ የበለጠ እንዲተጉ፣ እንዲበረቱ፣ እንዲያስቡ ወንድሞቹን ሲያጸና “ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ” በማለት ጽፏላቸዋል። (2ኛ ጴጥ. 1፥10)፡፡ 

ነብዩ ሆሴዕ የአምላካችን የእግዚአብሔር በዓላትን ማክበር በተመለከተ “በእግዚአብሔር በዓላት ቀን ምን ታደርጋላችሁ? (ሆሴ.9፥5) ብሎ ሕዝበ እስራኤልን እንደጠየቀው፤ እኛም እስራኤል ዘነፍስ የተባልን በሐዲስ ኪዳን ያለን  ኦርቶዶክሳውያን በዓላትን ስናከብር እንዴት እንደምናከብር ይጠይቀናል!?፤ የሥርዓት መጽሐፍችን ፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ ገጽ 259 እና 263 ስለ በዓላት አከባበርን በተመለከተ መንፈሳዊ ተድላ ደስታ ልናደርግ እንደሚገባን ሲገልጽ  “ረብህ ጥቅም የሌለውን ነገር ልትናገሩ፣ የማይገባ ሥራ ልትሠሩ አይገባም፣ ይልቁንም መንፈሳዊ ተድላ ደስታን ልታደርጉበት ይገባል ‘እንጂ’… ልደት እና ትንሣኤ ከጾም በኋላ ስለሆኑ የተቻለው (ከቅ

ዳሴ መልስ) ያልተቻለው ደግሞ በነግህ (ሲነጋ) ጾምን በመብልና በመጠጥ ማሰናበት አለበት በዚህም ፈጽሞ ደስ ይበላቸው” ይላል፡፡ 

ምንም እንኳን መብል መጠጥ የሚያፋቅር ደስ የሚያሰኝ  መሆኑ ቢታወቅም ፤ ክርስቲያኖች በሚያከብሯቸው በዓላት ላይ ከመብልና ከመጠጥ ይልቅ በዋናነት በጸሎት፣ በማኅሌት፣ በምሥጢራት፣ በትምህርት፣ በተዘክሮና በመሳሰሉት መንፈሳዊ ተግባራትን በማከናወን ማክበር ይገባል፡፡ መንፈሳዊ በዓላት – መንፈሳዊ ሐሴት የሚገኝባቸው ናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት  “በቃለ አሚን ወበትፍሥሕት ደምፁ እለ ይገብሩ በዓለ፣ በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና የምስጋና ቃል አሰሙ” (መዝ.42፥4) ያለው መንፈሳዊ በዓልን በመንፈሳዊ ደስታና በምስጋና ማክበር እንደሚገባ ጽፎልናል።

የእግዚአብሔር በዓላት በፍጹም ደስታ ሊከበሩ ይገባቸዋል፡፡ ደስታውም የሥጋ መሻትንና የዓይን አእምሮትን በማሟላት ሥጋዊ ደስታን በመደሰት ብቻ ሳይሆን፤  ፈሪሃ እግዚአብሔር ባልተለየው መንፈሳዊ ሐሤት ከማኅበረ ምእመናን ጋር በፍጹም መንፈሳዊ ደስታ ማክበር ይጠበቃል፡፡ሠለስቱ ምእትም “የጌታችን በዓላት እናከብር ዘንድ፣ ተአምራቱንም እንገልጥ ዘንድ እንዲሁም ምስጋናውንም እንናገር ዘንድ” አዝዘዋል (ፍት.ነገ. ትርጓሜ. ገጽ.260)፡፡

በ፲፭ ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ርቱዐ ሃይማኖት ስለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዜና ልደቱን ለመጻፍ ሲጀምር “አቤቱ የፈቀድህላቸው ይሰሙ ዘንድ ስለ መወለድህ እንድናገር የድርሰትን መንገድ አቅናልኝ” ብሎ ጸሎትን ልመናን ካስቀደመ በኋላ የበዓሉን ታላቅነት እና እንዴት ማክበር እንደሚገባን በግሩም ጽሑፉ

“ቤተልሔም ዛሬ ሰማይን መሰለች፣ አህያና ላም፣ ዮሴፍና ሰሎሞን የአርባዕቱ እንስሳ ምሳሌ ናቸው፡፡ በረት ክርስቶስ አምላክ በውስጧ ስለተገኘባት በኪሩቤል ሰረገላ ትመስላለች፡፡ ድንግል ልጇን በቀኟ የያዘች የአብ ምሳሌ ናት። ጌታ የተወለደበትን ዕለት በምድር ይህ ሁሉ የተደረገባት ይህች ዕለትም የተከበረች ናት ደስ እንሰኝባት” እያለ የጌታችንን ተአምራቱን ይገልጣል፡፡ 

ክርስቶስ የተወለደባት ይህቺን ዕለት እንዴት ማክበር እንደሚገባን ርቱዐ ሃይማኖት  ሲገልጥ፡- “በምንም መንገድ ኀዘን ከእኛ ሊኖር አይገባም፡፡ በክርስቶስ በዓላት ማልቀስ ኃጢአት እንደሆነ፣ ክርስቲያንም ሆኖ በሕማማት የሚደሰትም ታላቅ በደል ይሆንበታል፡፡ መልካምን በማድረግ ይደሰት፣ በሕማማት የሚያለቅስም ያልቅስ፡፡ በዚህች ዕለት (ጌታችን በተወለደባት ዕለት፣ እግዚአብሔር በሥጋ የተወለደባት ዕለት ናትና በዘመዶቹ ሞት፣ በበሽታ፣ በሀብቱ መጥፋት የሚያዝን የሚያለቅስ ሰው በሰማያት ደስታ የለውም፡፡ በወንድሙ ቂም በቀል የያዘ የተጣላ በዚህችም ዕለት ይቅር ያላለ ይህ ዐሥራ አራት እልፍ ከአራት ሺሕ ሕፃናት የገደለ የሄሮድስ ወንድም ነው” ይላል፡፡ 

ምክንያቱን አክሎ ሲገልጥም  “ሄሮድስ የመሲሕ ክርስቶስን ልደት በሰማ ጊዜ ሕፃናቱን ይገድል ዘንድ አዘዘ፡፡ ዐሥራ አራት ዕልፍ ከአራት ሺሕ ሕፃናትን ገደለ፣ ዘካርያስንም ስለ ልጁ ስለ ዮሐንስ ገደለው፡፡ በዚህም የተረገመ ሄሮድስ ተደሰተ፡፡ መድኃኒታችንን ያገኘው መስሎት ነበርና፡፡ ሰነፍ ሄሮድስ ሆይ ነፋስን ትይዘው ዘንድ ቀንንም ታስቀርበው ዘንድ ይቻላልን!?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ስለዚህም ያለፈውን በይቅርታ በመተው፤ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊና ሀገራዊ ኑሮአችን ማስተካከል እንደሚገባን ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል።

ኦርቶዶክሳውያን በዓላትን ስናከብር ይልቁንም የጌታችን ልደት እንደ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን በመሰብሰብ፣ ምሕረትን ይቅርታን በማድረግ እና በመጣንበት በዚያ በኃጢአት መንገድ ባለመመለስ፤ ከገቢረ ኃጢአት በመራቅ ገቢረ ጽድቅ መልካም ሥራ በመሥራት ልናከብረው ይገባናል፤ ስለዚህም “ወደ ቤቴል- ቤተልሔም (ቤተክርስቲያን) በመጣንበት መንገድ አንመለስ” 1ነገ. 13፥1፤ በዚያ በኃጢአት መንገድ ዳግማኛ አንመለስ ዘዳ.፲፯፥፲፮ ፤ ይልቁንም በቤተልሔም የተወለደውን በቀራንዮ የተሰቀለውን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር ስጋውን ቅዱስ ደሙን እንቀበል እና  ” ስብሐት ለእግዚአብሔር በስማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ -ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ።” ሉቃ.2፥14 በማለት በዝማሬ በምስጋና ሕይወት እንኑር! ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣የሰብአ ሰገል የመንፈሳዊ ጉዟቸው በረከት አይለየን!

Share your love

5 አስተያየቶች

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *