ይህች ሴት ቤተ መቅደሱን ልታቃጥለው ነው

መልአከ ምክር ቀሲስ ከፍያለው መራሒ የሃያ ሰባት መጻሕፍት ደራሲና ስመ ጥር ካህን ናቸው፡፡ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በጻፏቸው መጻሕፍት ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከትምህርት እስከ አገልግሎት በሔዱበት ረዥም ርቀት ለትውልዱ አርአያ የሚሆኑ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ቅርስ ናቸው፡፡ በዚህ ሰንበት በጃንደረባው ሠረገላ ላይ ያደረጉት ቆይታ ክፍል አንድ ይህን ይመስላል፡፡

መልአከ ምክር ቀሲስ ከፍያለው መራሒ ፦ የተወለድሁት ጎንደር ጋይንት ጉና ቅዱስ ሚካኤል ከስመ ጥሩ የቅኔ ሊቅ አለቃ መራሒ በየነና ከወ/ሮ ዘውዲቱ ያለው በታኅሣሥ 29 ቀን 1936 ዓ.ም ነበረ፡፡ ወላጆቻቼ እግዚአብሔርን ፈሪ ፣ ሰው አክባሪ ደጎች ነበሩ፡፡ 

       እናቴ የነበሩት ወይዘሮ ዘውዲቱ ያለው እኔን ነፍሰ ጡር ሆና ሳለ እንደ ባህላችን በእናትዋ ቤት ለመውለድ በበቅሎ ሆና ታላቅ እኅቴን አቅፋ ስትጓዝ አባቴ ደግሞ ለእመጫት መታረሻ የሚሆነውን ዱቄት በአህያ ጭኖ ከኋላ ሲከተል ከአፋፉ ላይ ሲደርሱ ገዴ አሞራ ከዛፍ ላይ ድንገት ብድግ ብላ ስትበር በቅሎዋ ደንብራ መንገድ ሰብራ ስትሮጥ የተፈናጠጠችው ሕጻን ተፈንጥራ ከቁጥቆጦ ላይ ወደቀች፡፡ ነፍሰ ጡር እናቴ ግን እንድ እግርዋ ከእርካብ ላይ ሳይላቀቅ ከመሬት ላይ እየተጎተተች የተወሰነ ርቀት እንደሔደች አለቃ መራሒ የይድረሱልኝ ጥሪ ሲያሰሙ በአካባቢው የተገኙ ሰዎች በቅሎዋን አረጋግተው ይዘው የነፍሰ ጡርዋን እግር ከእርካብ ላይ አላቀው በቅርብ ወደሚገኝው መንደር ሕጻኗንም ጭምር  ወስደው ያሳርፏቸዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ወይዘሮ ዘውዲቱ በሕይወት ትተርፋለች ብሎ የገመተ ሰው አልነበረም ሆኖም ሦስት ቀናት እንደቆዩ ሕፃን ከፍያለውን (እኔን) በእግዚአብሔር ቸርነት በሰላም ተገላገለች፡፡

       አባቴ አለቃ መራሒም የተከሰተውን አደጋና ተአምር በማሰብ ‹‹ተደመ›› ተደነቀ ከሚለው ግሥ በመነሣት ‹‹መድምም›› አስደናቂ ልጅ ተወለደ በማለት ‹‹መድምም›› ብለው ስም አወጡልኝ፡፡ የደብሩም ካህናትም አባቴ ባወጡልኝ ስም ይጠሩኝ ነበር፡፡

       ትምህርት ያልቀመሰችው  እናቴ ደግሞ ይህ ልጅ  በተዓምራት  የተገኘ ነውና  ትልቅ ሰው ይሆናል  ብላ ‹‹ከፍያለው›› ብላ ጠራችኝ፡፡ የሁለት ስም ባለቤት ስለነበርሁ ሰውም በሚቀናው ይጠራኝ  ነበር፡፡ ካደግሁ በኋላ ግን ከክፍለ ሀገር  ወደ አዲስ አበባ ስመጣ መድምም የሚለው ስሜ ለከተማው ሕዝብ ግራ ሲገባው በማየቴ ከፍያለው የሚለውን ስም እንደ አማራጭ ስነግራቸው ይሄ ይሻላል ስላሉኝ ዘመናዊው ትምህርት ቤት ስገባም ‹‹ከፍያለው›› በሚለው ስም ተመዘገብሁ፡፡ በዚህ የተነሣ እናቴ ያወጣችልኝ ስም ጸደቀ፡፡

       የሰባ ዓመት ልጅ እንዳለሁ እናቱ በወሊድ ምክንያት ደም ፈስሷት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡ምንም እንኳን ልጅም ብሆን እናቴን አስታውሳት ነበር፡፡ ዘለግ ያለች ጠይም ዓሳ መሳይ ጠጉረ መልካም ፣ ሁል ጊዜ ሹሩባና ቁንዳላን የምትሠራ እንደነበረች ትዝ ይለኛል፡፡ የእናቴን ጡት ጠብቼ ከማደጌ በስተቀር ፍቅሯን ባላውቀውም ካደግሁ እና ነፍስ ካወቅሁ በኋላ ግን የእናቴ ፍቅር ይሰማኝና ትዝታዋ ይመጣብኝ ነበር፡፡ አባቴ አለቃ መራሒም በዚያን ወቅት የባለቤታቸውን የአርባ ተዝካር ካወጡ በኋላ ጋይንት ነገላ ወረዳ ከሚገኘው አካለ ክርስቶስ ገዳም ሄደው መንኩሰው ወደ ቤታቸው ተመለሱ ልጆቻቸውንም ለብቻቸው ያለ እናት ማሳደግ ጀመሩ፡፡

       አባቴ ደግ የጸሎት ሰው ነበሩ፡፡ ሌሊት ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እንቅልፍ አያውቁም በቃል የሚያውቁትን ሲጸልዩ ያድሩና ጠዋት ሲነጋ ከቤት አጥር ግቢ ውስጥ ክንፍዋን በተፈጥሮ የዘረጋች ግራር ዛፍ ነበረችና ከዛፉ ሥር ትልቁ ነጭ አጉዛ ተነጥፎላቸው የጸሎት መጻሕፍቶቻቸውን ተራ በተራ ቆመው ሲደክማቸው ቁጭ ብለው ሲጸልዩ ይውሉ ነበር፡፡ የግራርዋንም ዛፍ ‹‹ቤተ ማርያም›› ብለው ሰይመዋታል ቤተሰቡም ሆነ የመንደሩ ሕዝብ የአለቃ መራሒ ጸሎት ቤት ‘ቤተ ማርያም’ እያሉ ይጠሯት ነበር፡፡

አለቃ መራሒ የበቁ የጸሎትና የማሕሌት ሰው ስለነበሩ ከዕለታ በአንድ ቀን  ከዕድሜና ከሙያ ጋደኞቻቸው የጉና ሚካኤል ሊቃውንት ጋር የሰኔ ማርያም ጉና ማሓሌት ተቁሞ ከመልክዓ ማርያም ‹‹ሰላም ለእስትንፋስኪ›› የሚለው ተጸንጽኖ እና ተመርግዶ ሲያበቃ አለቃ መራሒ ‹‹ጽንሕኒ ውስተ ሠናይ ወሠውርኒ እሞት …..›› የሚለውን ወርበው ሲያሸበሽቡ መሪጌታ መርሻ የተባሉ የድጓ መምህር እግረ ልምሾ ስለነበሩ ከከበሮ ላይ ተደግፈው ማሕሌት ቆመው ሳሉ አንዲት ሴት ወይዘሮ ችቦ እያበራች ከመቅደስ ወደ ማሕሌት ስትመጣ መሪጌታ መርሻ ያዩትና ደንግጠው አለቃ መራሒን ጠርተው “ኸረ  ይህቺ ሴት  ቤተ መቅደሱን ልታቃጥለው ነው” ብለው ይጮሃሉ አለቃ መራሒም ‹‹የት አለች መሪጌታ›› ብለው ቀና ሲሉ ከመሪጌታም ከዓይናቸው ተሰወረች ፡፡ እመቤታችንን በወረብ የጠሯት አለቃ መራሒ ነበሩ ስሟን ሲጠሩዋት ልትባርካቸው የመጣችውም እርሳቸውን ነበር፡፡ የታቻቸውም መሪጌታ መርሻም የበቁ ሰው ኖረዋል ድንቅ ነው፡፡

መልአከ ምክር ከፍያለው መራሒ ፦  ትምህርቴን ከፊደል ጀምሮ እስከ ዳዊት ድረስ በቤቴ ውስጥ አባቴ አለቃ መራሒ በሚገባ ካስተማሩኝ በኋላ፣ የቅኔውንም መንገድ እንዲሁ ከእርሳቸው ተምሬያለሁ፡፡ ሆኖም ቅኔውን መቀኘት አለብኝ ብሎ በማሰቤ፣ ስማዳ ወደተባለ ወረዳ ሃዶ እንጉዳዳር ኪዳነ ምሕረት የቅኔ መምህር ከነበሩት ከመሪጌታ ዓለሙ በሥነ ሥርዓት ተምሬ ተቀኝቻለሁ፡፡ የዜማ ትምህርቴንም ወደ ዋድላ ሄጄ መለይ ማርያም፣ ከመሪጌታ ዳዊት ጾመ ድጓ ደጋግሜ በመማር ያስተምህሮ ድጓ እንደጀመርኩ ብዙ ሳልገፋ ወደ አንዳ ቤት ደረባ መርቆሬዎስ ከመሪጌታ ፍቅረ ማርያም፣ በኋላም የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም የአቋቋም መምህር ከነበሩት ክብረ በዓልና መዝሙር ተማርኩ፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትምህርቴን በምማርበት ጊዜ ሁሉ በዘርና በመከር ወቅት ወደ ቤተ ሰቦቼ እየተመለስሁ እረዳቸው ነበር፡፡ በጠቅላላው የእርሻውንም ሆነ የአጨዳውን ተግባር ሰው በሚፈለግበት ጊዜ ወደ ቤተሰቦቼ እየሄድሁ ስረዳቸው አባቴ ይደሰቱና ይመርቁኝ ነበር፡፡ 

       አንዳቤት በአቋቋም ትምህርት ላይ እንዳለሁ  ቤተ ማርያም ከተባለች ደብር አንድ ጸጋ እግዚአበሔር ያደላቸው አባ ዋሴ የተባሉ መንፈሳዊ አባት መኖራቸውን በመስማቱቴ ወደ እርሳቸው ለማማከር ሄድሁኝ፡፡ አባ ዋሴም ገና ሲያዩኝ  “ለምን መጣህ ማሙሽ? ” አሉኝ፡፡ በዚያን ጊዜ የ19 ዓመት ጎልማሳ ነበርሁና፤ “ሕግ ልግባ ወይስ ልመንኩስ?’ ብዬ ያማከርኳቸው፡፡

አባ ዋሴም ሳቅ ብለው ማሙሽ “ወደ አዲስ አበባ ትሄዳለህ ፣ ትልቅ ሰው ትሆናለህ ፣ ዘመናዊ ትምህርትም ትማራለህ፣ በዘመነ ዮሐንስ ወደ ውጭ ሀገር ትሔዳለህ ፣ ተመልሰህ የትልቅ ሰው ልጅ በዘመነ ዮሐንስ ታገባለህ፣ አምስት ወንዶች ልጆች ትወልዳለህ፣ ባለቤትህ ስድስተኛ ሴት ልጅ ትፀንሳለች ፤ በዚያን ጊዜ ለእናቲቱ ያሰጋታል ያቺ ሕፃን ባትወለድ ይሻላታል’  አሉኝ፡፡ ይህንንም ትንቢታቸውን ከሰማሁ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ወሰንሁ፡፡

መልአከ ምክር ቀሲስ ከፍያለው መራሒ ፦ ልመጣበት ነው፡፡ ጥር 29 ቀን 1958 ዓ.ም.

ከጋይንት ተነሥቼ ይኄይስ ገላዬ የተባለ አንድ የቤተ ክርስቲያን ልጅ አስከትዬ ወደ አዲስ አበባ የእግር ጉዞ ጀምሬ እስቴ ወረዳ ከአጎቴ ከአቶ ይባቤ በየነ ቤት አርፎ ፣ ሲነጋም አጼ ፋሲል ባሠሩት ድልድይ ዓባይን ተሻግሬ ሞጣ ገብቼ አደርሁ። ወቅቱ ዘመነ መርአዊ ቅበላ ስለነበር ሠርጉና ተዝካሩ በደረሱበት የተትረፈረፈ ስለነበር፣ ምንም የረሀብ ችግር ሳይገጥመኝ እየበላሁና እየጠጣሁ ፣ ዕረፍትም እያደረግሁ ዐቢይ ጾም ሰኞ ሊገባ ቅዳሜ ዕለት ደብረ ወርቅ ገዳም ገባሁ፡፡

       የካህን እንግዳ ስለሌለው እሑድ ሌሊት ማሕሌት ቆሜ አደርሁ ፣ ጠዋት ቅዳሴው እንዳበቃ በደብሩ ሥርዓት የቅኔው መምህር ቅኔውን ይቀኛል፣ እኔም ቅኔ እንድመራ ተጋበዝሁ ፣ ቅኔውንም በቅኔ ይትበሃል ስመራ፣ ድመፀ መልካም ስለነበርሁ የቅኔው መምህር መልስ እያሉኝ ደጋግሜ ተቀኘሁ። ሥርዓተ ማኅሌቱ እንዳበቃ ስንክሳር አንብቤ ከታረገ በኋላ ሊቃውንቱ ስለወደዱኝ የት ልትሄድ ነው ብለው ጠየቁኝ፡፡ ‘ወደ አዲስ አበባ መሄዴ ነው’ ብላቸው ፤ ‘አዲስ አበባ ምን ያደርግልሃል፤ ይቺ ደብር ትልቅ ናት እዚሁ እንቅጠርህና እመቤታችንን አገልግል’ አሉኝ፡፡  እኔም ‘የተወለድኩበትም ታላቅ ደብር ነበር፣ ልቤ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ስለተነሣ ነው መንገድ የጀመርኩትና አይሆንም’ አልኋቸው። ከዚያም ደጀ ሰላም የሰንበት ምሳ ተጋብዤ ወደ አዲስ አበባ ጉዞዬን ቀጠልሁ፡፡

       ከአንድ ሳምንት በኋላ ደብረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም ደረስሁ፡፡ በቆሎ ትምህርት ቤት እንግዳ ማስተናገድ የተለመደ ስለሆነ፣ ከእኔ ቀደም ብሎ መጥቶ እንጦጦ ማርያም የቆየ ዲያቆን ናሁ ሠናይ ጽጌ የተባለ ወንድም አገኘሁ። እርሱም አስተናገደኝ፡፡ ከዚያ ቀስ በቀስ ወደ ከተማው ወርጄ ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ደረስ፣ የማውቀውን አብሮ አደጌ የሆነውን ዕርቁዬ ዘነበ የተባለ የመጽሐፍ ተማሪ አገኘሁ። እርሱም የመቃብር ቤት ቦታ ፈልጎ አስጠጋኝ፡፡ ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም የተማረ ሰው ይወደዳል፣ ወሩ ዓቢይ ጾም ስለሆነ ምዕራፍ ጾመ ድጓ ይቆማል፤ ቀስ በቀስ ከሊቃውንቱ ጋር ተዋወቅሁ፣ ሊቃውንቱም መጨኔውን (የደጀ ሰላም ኃላፊውን) አስጠርተው ይሄ ሰው የተማረ ሰው ስለሆነ አዚህ እያገለገለ ደጀ ሰላም እንዳትከለክሉት ብለው መመሪያ ሠጡልኝ፡፡

መልአከ ምክር ቀሲስ ከፍያለው መራሒ ፦ ዓቢይ ጾም እንዳለቀ የግንቦት ባለወልድ ዕለት ቤተ ከርስቲያን መኖሩን ጠይቄ ለመሳለም ስሔድ አራት ኪሎ ባለወልድ ማኅሌት ተቁሞ ደረስሁ፡፡ ከዚያም የካህን እንግዳ የለውምና ወደ ማሕሌቱ ጠጋ ብዬ ሳገለግል ፣ ቅኔ እንድመራ ተጋበዝሁ ፣ ቅኔውን ተመርቼ ስጨርስ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ከቤተ መቅደስ ሆነው ያዳምጡኝ ኖሯል፡፡ ሕዝቡ ከተሰናበተ በኋላ ‘ያቺ ቅኔ የተመራችውን ልጅ ጥራልኝ’ ተብሎ ተጠራሁ፡፡ ከዚያም ከየት እንደመጣሁ ጠይቀውኝ የመጣሁበትን ነገርኳቸው፡፡

ለምን ወደ አዲስ አበባ እንደመጣሁ ቢጠይቁኝ ‘ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ፈልጌ መምጣቴን’ ነገርኳቸው፡፡ ሊቀ ሥልጣናትም ‘በዲቁና ተቀጥረህ እየሠራህ መማር ትችላለህ’ ሲሉኝ እጅ በመንሳት ምስጋናዬን አቀረብሁ፡፡ በ1958 ዓ.ም. በሰኔ ወር አሥራ አምስት ብር እየተከፈለኝ በዲቁና እንዳገለግል ተቀጠርሁ፡፡ ሆኖም ቅጥሩ በዲቁና ይሁን እንጂ አገልግሎት የምሠጠው በድብትርናም ጭምር ነበር፡፡

በተጨማሪም ዘመናዊ ትምህርት የመማር ፍላጎቴ ከፍተኛ ስለነበር በ1959 ዓ.ም. ትምህርቴን ከ3ኛ ክፍል ጀመርሁ፡፡ በተለይም በክብረ በዓል ቀን በሐምሌ ሥላሴ እና በጥር ሥላሴ እንዲሁም ለዘመን መለወጫ ፣ ለልደትና ለትንሣዔ ጭምር ወረቦቹን ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር እንድወርብ በሊቀ ጠበብቱ እታዘዝ ነበር። በማስረገጡም ጥበብ እጅግ የተመሰገንሁ አገልጋይ ስለነበርሁ ሊቀ ጠበብቱና አጋፋሪውም ሆነ ብለው ከግርማዊነታቸውና ከፓትርያርኩ ፊት ይመድቡኝ ነበር።

       አንድ ጊዜ የጥር ሥላሴ እየተከበረ ሳለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ወረብ ስወርብ ትኩር ብለው አዩና “ይሄ ልጅ እንደ ውኃ ዋና እኮ ነው የሚሳበው ከየት መጣ?” ብለው ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያምን (ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ) ጠየቋቸው፡፡ ሊቀ ሥልጣናትም ‘በዘመናዊውም ትምህርት ጎበዝ ነው፡፡ አባታችን የጉኔ መኮንን ዘር ነው’ አሏቸው፡፡ ከዚያ በኋላም በጸሎተ ቅዳሴውም ጃንሆይ ሲመጡ ተመርጠው ከሚቀድሱ ዲያቆናት አንዱ አድርገውኝ ነበር፡፡

ይቀጥላል

Share your love

17 አስተያየቶች

  1. ጃንደረባው ለኔ ይሔን እየጠፋ ያለ ትውልድ ሊታደግ ከ እግዚአብሔር የተላከ ይመስለኛል …እግዚአብሔር ያበርታችሁ እንደ ማህበረ ቅዱሳን ያለ ትልቅ እንዲሆን ምኞቴ ነው … የመላከ ምክርን የመሰሉ የተደበቁ የብፁዐን ከዋክብት ሊቃውንትን ታሪክ ስለምታጋሩን እናመረግናለን ይቀጥል

    • ስለ እውነት ይበል የሚያስብል መልካም ስራ ነው።

      ልዑል እግዚአብሔር ማስተዋሉንና ጥበቡን ያድልልን። ወደፊት ልክ እንደ ሚስጢሪን ላካፍላችሁ (ማህበረ ቅዱሳን): እነዚህን ግለ ታሪኮች በመጽሐፍ መልክ እጠብቃለሁ።
      በርቱ የብዙ አስተማሪ ታሪክ ያላቸውን በህይወት ያሉ እናቶችንና አባቶችን ወንድሞችንና እህቶችን ታሪክ እንደምታጋሩን ተስፋ አደርጋለሁ። ቃለ ህይወት ያሰማልን።

  2. እጅግ በጣም ድንቅ ፣ ደስ የሚል እና አስተማሪ ታሪክ ነው። ቀጣዩን ክፍል በጉጉት እጠብቃለሁ::

  3. የጃንደረባው ቤተሰቦች ከልብ እናመሰግናለን!ብዙ ልናውቃቸው የሚገቡ መመህራን እንዳሉ አመላክታችሁናል!

    • የእውነት ቀልብ የሚገዛ ቃለ ምልልስ ነው፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች ትውልዱ በሂወት ካሉ አባቶች እጅ ብዙ እንዲማር እና በቁም እያሉ እንዲያመሰግናቸው ያደርጋል እናመሰግናለን

  4. እግዚአብሔር ይስጥልን ብዙ የማናውቃቸውን ሊቃውንት እንድናቅ ስለረዳችሁን

  5. ቀጣይ ክፍል ዘገየ፡፡ትልቅ አገልግሎት ነው፤ ለትልቅ ደረጃ ያድርስልን፡፡እንደነዚህ ያሉ አባቶችን ታሪክ ማንበብ እንዴት ይናፍቃል

  6. በጣም እናመሰግናለን በጉጉት እየጠበቅናችሁ ነው ይህን አስተማሪ ታሪክ ጨርሱልን፡፡

  7. እጹብ ድንቅ ነው ሌላ ቃል ስለሌለኝ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለህ ።

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *