በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፉ ቃላት መካከል ሕይወት አልባ የሆኑ ቃላት የሉም:: ሁሉም ሕያዋንና ሕይወት ቀጥል ናቸው:: ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንደጻፈው ፣ ቅዱስ ያሬድ በድጓው እንዳዜመው “ከአንዱ ኮከብ ክብር የአንዱ ኮከብ ክብር ይበልጣልና” ለእኔም እንደ ከዋክብት ከሚያበሩት ቃላቶች መካከል ይህ ቃል ሳበኝ።
ፀሐይ እና ከዋክብት ያበሩት በቃል ነው:: ብርሃን የበራው በቃል ነው:: አዳም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ከሥላሴ ዘንድ ቃል ወጥቷል:: ከድንግል ዘንድ መልአኩ የሚስደነግጠውን የሚደንቀውን የሚረቀውን ነገረ ሥጋዌን ይዞ መጥቶ ያስረዳው በቃል ነው። የቃል ጥቅም ብዙ ነው:: ከላይ ያለው ቀጭን ትእዛዝ ግን የኢትዮጵያውያንን አኗኗር የቀየረ ትእዛዝ ነው:: ኢትዮጵያ አካሉን ሳታይ በጥላው ብቻ እንዳትቀር ፣ አካላዊ ቃልን ታውቅ ዘንድ የተሠጠላት አጭር የቃል ትእዛዝ ይህ ነው::
ወደዚህ ሰረገላ ቅረብ !
አዎ ይህ ቃል ብሉይን ይዛ ለነበረች ሀገር ሐዲስ ኪዳን ተጨምሮላታል:: ግዝረትን ለተቀበለች ጥምቀትን ሸልሞአታል::: ጥላውን ላየች ዓይን አካሉን አስተዋውቋታል:: በሠረገላ ስንኳን ሲሄድ ለአፍታ ዓይነ ሥጋው ከንባብ ዓይነ ልቡናው ከምሥጢር ፈቀቅ በማይልበት ልጇ ፤ የሠረገላው መጓዝ ከንባቡ ባልረበሸው በትጉሕ ልጇ አማካኝነት ብዙ በረከት ያገኘችው “ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” በሚለው ቃል ምክንያት ነው::
እመቤታችን “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ” ባለችው ቃል ሰማይ እና ምድር ታርቋበታል:: “ወደዚህ ሰረገላ ቅረብ” በሚለው በዚህ ትእዛዝ ደግሞ ጥላው አካሉን ምሳሌው እውነቱን ትንቢቱ ፍጻሜውን አግኝቷል:: በዚህ ቃል መሠረት ፊልጶስ “ወደ ሰረገላው ቀረበ” ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ልጇም ትሑት ነውና ተማረ ፣ ጠየቀ ፣ አወቀ ፣ ተጠመቀ::
ይገርምሃል ወዳጄ ዛሬ የሚተረጎመው ወንጌል ዛሬ የምታየው ሥርዓት እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው በሰረገላ ውስጥ ስብከት ተጀምሮ ነው:: በጥቂት ሰዓታት በጥቂት ቃላት በጥቂት ስብከት።
ወዳጄ እኔና አንተስ መቅረብ ያለብን ወደ የትኛው ሰረገላ ይሆን? ለማስተማር ሳይሆን ለመማር ወደ ሰረገላ መቅረብ የለብን ይሆን? እመነኝ ወደ ሰረገላ ቅረብ እንጂ የፈለከውን ታገኛለህ:: ከዚያ “ነፍሴ የወደደችውን አገኘች” እያልኽ መዘመር ትቀጥላለህ።
“አዎ ና ወደ ጸሎቱ ሰረገላ እንሳፈር” በጸሎት ሰረገላ ውስጥ ጌታህን ታገኘዋለህ:: ና ተሳፈር ቀርበህ ጠይቀው ፈጥኖ ሔዶ ቢቀድምህም እንኳን ከኋላው ሆነህ ጥራው:: አዎ እንደ በርጤሜዎስ “የዳዊት ልጅ ሆይ” በለው ይሰማኻል:: ከብዙ ጩኸት መሃል ቆሞ ይጠብቅሃል።
አዎ ወደ ሰረገላው ቅረብ “አረቦነ መንግሥተ ሰማያት” ተብላ በምትጠራው ቤተ ክርስቲያን ሰረገላ ላይ ተሳፈር:: በዚያ ሰረገላ ላይ ጌታን ከነእናቱ ሐዋርያትን ከነስብከታቸው ነቢያት ከነትንቢት አዝመራቸው ታገኛቸዋለህ አዎ ና እንሳፈር ።
ቤተ ክርስቲያን ለምን ቆየህ? የት ሰነበትህ? እንዴት እንዲህ አረፈድህ? አትልህም እጆችዋን ዘርግታ ታቅፍሃለች:: “በጉ ይታረድ” ትላለች ጫማህን ታጫማሃለች ኩፌት ኩፋሩን ትሰጥሃለች ቀለበቱን ዘንጉን ታስጨብጥሃለችና ወደዚህ ሰረገላ እንቅረብ ና ወዳጄ !
ቃለ ህይወት ያሰማልን እኛንም ወደሰረገላው ምንቀርብበትን ትሁት ልቦናን ይስጠን
እግዚአብሔር ይስጥልኝ!
ቃለ ህይወት ያሰማልን