የፍቅርና የጥላቻ መሥዋዕት

በሰው አማካኝነት በቤተ ክርስቲያን ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ሁለት ዓይነት መሥዋዕት ሲቀርብ ኖሯል፤ የፍቅርና የጥላቻ መሥዋዕት:: ይህ እንደምን ነው? ቢሉ ታሪኩን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደባት ከቤተልሔም ጀምረን እንመዛለን። 

የጌታችንን በቤተልሔም መወለዱን የእንስሳት እረኞች “እንደ እንስሳ ሆነ” ተብሎ የተነገረለትን ሰውን ለመጠበቅ በሚላኩ ሰማያዊ እረኞች (መላእክት) ብሥራት ሲያውቁ፤ በንግሥና ወንበር የተቀመጡም በነገሥታት ማዕረግ በሚኖሩ በሰብዓ ሰገል አማካኝነት “የተወለደው የአይሁድ ንግሥ ወዴት ነው?” በሚል ሰሙ። የንጉሡ ልደት ለነገሥታት በነገሥታት ተበሰረ። 

እነዚህ ነገሥታት በቤተልሔም ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ የፍቅር መሥዋዕት አድርገው ሲያቀርቡ ሄሮድስ በበኩሉ የሕፃናቱን ደም የጥላቻ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ጌታችን ግን የሁለቱንም ሳይሆን ሁለቱንም ተቀበለ። ወርቅ ንጽሕናን፣  ዕጣን ምዑዘ ምግባርን፣ ከርቤ ፍቅርን በክርስቶስ ያመኑ እንዲያቀርቡ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ሲያመለክት፤ የሕፃናቱ በቤተልሔም መታረድ የክርስቲያኖችን የሰማዕትነት ሕይወት የሚጠቁም ሆነ። 

አይሁድ የመሲሑን ፍለጋ በፍና ትንቢት እየተከተሉ መክሰሳቸውን (ማሳበቃቸውን) ሄሮድሳውያንም ደም ማፍሰሳቸውን ከዚያ ቀን ጀምሮ አላቆሙም:: በቤተልሔም የተወለደው ንጉሥ በየት ነው ሲባሉ ደሙን ለማስፈሰስ እንደ ጠቆሙ፤ በመጨረሻም በቀራንዮ ለስቅላት አሳልፈው የሰጡት “ንጉሥ ነኝ ” ይላል ብለው በመክሰስ ነው፡፡  በቤተልሔም የጀመሩትን በቀራንዮም ፈፀሙት። ይህን ሁኔታ ቅዱስ ኤፍሬም “በቤተልሔም ፍቅር ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ ስትሠዋ፤ ጥላቻ ደግሞ የሕፃናትን ደም መሥዋዕት አድርጋ አቀረበች” ሲል ይገልፀዋል።

በቀራንዮ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን የፍቅርና የዕርቅ መሥዋዕት አድርጎ ሲያቀርብ አይሁድ ግን በጥላቻ ደሙን አፈሰሱ። እርሱ በፈቃዱ ስለ ፍቅር እነርሱ ደግሞ በጥላቻ ሆነው ያፈሰሱት ደም ግን ዘላለማዊ መሥዋዕት ሆኖ ቅድመ እግዚአብሔር ቀረበ። 

መሲሐውያን የሆኑ ሁሉ ከሁለቱ በአንዱ መሥዋዕት ሆነው መቅረብ ከእምነት በሆነ ፍቅር የሚጠበቅ ነው፡፡ ራሳቸውን በመካድና ፈቃዳቸውን በመሠዋት መነኰሳት በምናኔ፣ ካህናት በአገልግሎት፣ ምዕመናን በፍቅር በሆነ አንድነት እንደ ወርቅ ንጹሕ፣ እንደ ዕጣን ምዑዝ፣ እንደ ከርቤ በፍቅር በሆነች አንድነት ዕለት ዕለት አምሃ ሆነው ይቀርባሉ። በጥላቻ የተሞሉ ደግሞ የክርስቲያኖችን ደም ሲያፈሱ ምሥክር እንዲሆን የደም መሥዋዕት ያቀርባሉ። ሰማዕታቱም ደማቸውንና ሰውነታቸውን የተወደደ መሥዋዕት አድርገው በማቅረብ በአባታቸው ፊት ይቆማሉ። ቅዱስ ጳውሎስ “ሰውነታችሁን ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለው ” ያለው ይህን ሲያመለክት ነው። ሮሜ 12፥1 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ” ያለ ይህን ነው:: ከሁለቱ በአንዱ መንገድ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ የማይችል ግን የክርስቶስ ተከታይ ነው ተብሎ ለመጠራት የሚበቃ አይደለም። 

የመጀመሪያዎቹን መምህራነ ወንጌል ካህናት በፍቅር በቃለ እግዚአብሔርና በምሥጢራት መሥዋዕት አድርገው ሲያቀርቧቸው ፤ ሁለተኞቹን ማለት ሰማዕታትን ግፈኞች በእሳት በሰይፍ ስለት መሥዋዕት ያደርጓቸዋል። 

ጌታ እግዚአብሔርም የሁለቱን ሳይሆን ሁለቱንም ይቀበላቸዋል፡፡ በቅዳሴ እግዚእ “አምላክነ ሥመራ ለነፍሰ ዚአነ” አቤቱ ጌታ ሆይ ሰውነታችንን ውደዳት እንዳለ ከሁለቱ በአንዱ መንገድ መሥዋዕት ሆነን እንቀርብ ዘንድ አምላካችን ሰውነታችንን ይውደዳት፤ አሜን!

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

6 አስተያየቶች

  1. ቅዳሴ እግዚእ
    “አምላክነ ሥመራ ለነፍሰ ዚአነ”
    “አቤቱ ጌታ ሆይ ሰውነታችንን ውደዳት”

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *