‘ይህች ድሃ መበለት አብልጣ ጣለች ፤ ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና’ ማር. 12፡41-44
ዛሬ ብዙ ገንዘብ የሌላት በዕድሜ የገፋች ድሃ መበለት ያላትን ስትሠጥ ብዙ ሀብታሞች ደግሞ ከትርፋቸው ብዙ ሲሠጡ አይተናል፡፡ እግዚአብሔር ‘ትልቅ ነው ፣ ትንሽ ነው ፣ ሀብታም ነው ፣ ደሃ ነው’ አይልም፡፡ አያበላልጥም፡፡ ሰው ግን ያበላልጣል ፣ ያዳላል፡፡ እግዚአብሔር አድሎአዊ አይደለም፡፡ ድሃውን ድሃ ነውና አልሠጠም ብሎ አይኮንነውም ፤ ሀብታሙንም ሀብታም ነውና ሠጥቷል ብሎ አያጸድቀውም፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅና ትንሽ የሚሆነው በሥራው በምግባሩ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታ ይህችን ድሃ መበለት የተመለከተው፡፡ የሃሳቧን ትልቅነት እንጂ የሠጠችውን ገንዘብ ማነስ አልተመለከተም፡፡ ይህ ማለት ግን የሃብታሞቹን አልተቀበለም ማለት አይደለም፡፡ ይህች ድሃ መበለት ግን የምትበላው ሳይኖራት በሳንቲሟ ዳቦ መግዛት ስትችል ያላትን ሳንቲም አምጥታ ሠጠችው፡፡
ዛሬ ብዙዎች ካልተረፋቸው አይሠጡም፡፡ ከትርፋቸውም የማይሠጡ አሉ፡፡ ጌታ የእኛን ትራፊን አይቀበልም፡፡ ለእግዚአብሔር መሥጠት የመጀመሪያውን ነው፡፡ አባቶቻችን ድሮ የሚያደርጉት እንዲህ ነበር፡፡ ወላጆች የመጀመሪያውን ልጃቸውን ፣ ገበሬው ከእርሻው የመጀመሪያውን እሸት ፣ ደመወዝተኛም ከደመወዙ የመጀመሪያውን የሚሠጡት ለእግዚአብሔር ነበር፡፡ እናቶች ከማዕዳቸው ሳይቀምሱ የመጀመሪያውን የሚያቀርቡት ለጌታ ነበር፡፡ እነዚያ ሀብታሞች ግን የእኛ ጌታ [በሥጦታቸው] የሚደነቅ መስሏቸው ቀይ ቀዩን እየመዘዙ ጣሉ ፤ ጉረኞች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የትርፋችን መጣያ አይደለም፡፡ ሲሠጠኝ እሠጣለሁ የሚሉም አሉ፡፡ ለእግዚአብሔር መሥጠት ያለብን ስናተርፍ ከትርፋችን አይደለም ፤ ያለንን እንጂ፡፡ ጌታ እኮ ድሃ አይደለም፡፡ እርሱ ደሃ የሆነው እኛ እንድንበለጽግ እንጂ አጥቶ ፣ ቸግሮት አይደለም፡፡ በእውነትም ድሃ ሆኖ አይደለም፡፡ ስለዚህ ያለንን ፣ ልባችንን እንሥጠው፡፡ ምጽዋት መሥጠት እንደዚህች እናት ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ፣ ብዙ ሀብታሞች አንድ ነገር ያደረጉ እንደሆነ በድምጽ ማጉያ ሀሎ ሀሎ ተብሎ በሕዝብ ፊት ካልተለፈፈላቸው ያኮርፋሉ፡፡ ስለዚህ ዳግመኛ አይሠጡም፡፡ ይገርማል! የሚሠጡት ለሰው ነው ማለት ነው፡፡ ጌታ ያስተማረው ግን በሥውር የሠጣችሁትን በግልፅ እቀበላለሁ ብሎ ነው፡፡ እነዚያ ሀብታሞች ያቺን ድሃ መበለት የምትሠጠው ምንድን ነው ብለው አንጓጠዋት ነበር፡፡ ጌታ ግን ተቀብሏታል፡፡ ዛሬም እንደዚህ የምናንጓጥጥ አለን፡፡ ጌታ ግን ከልብ እንደምትወደው ስላወቀ ተቀብሏታል፡፡ እኛ ግን ብዙ እያለን ፣ ተርፎን እያለ ምንም ልንሠጠው አልወደድንም ፤ አልሠጠነውም፡፡ ከሠጠነው እርሱ አብዝቶ ይሠጠናልና እንሥጥ፡፡
እግዚአብሔር ይባርካችሁ ፤ እግዚአብሔር ይጠብቃችሁ፡፡
ሚያዝያ 18 1985 ዓ.ም. እንዳስተማሩት
ከአያሌው ዘኢየሱስ የግል ማስታወሻ እንደተወሰደ
ማስታወሻ :- በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በድንቅ ስብከቶቻቸው እና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሠረቷቸው ገዳማትና ትምህርት ቤቶች ፣ ባፈሯቸው መምህራንና መነኮሳት ለዘላለም የሚታወሱ ሊቀ ጳጳስ ናቸው::
ጃንደረባው ሚድያ የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን የቆዩ ወደ ጽሑፍ የተቀየሩ ስብከቶች ዘወትር አርብ ይዞላችሁ ይቀርባል::
፡ እኛ ግን ብዙ እያለን ፣ ተርፎን እያለ ምንም ልንሠጠው አልወደድንም ፤ አልሠጠነውም፡፡ ከሠጠነው እርሱ አብዝቶ ይሠጠናልና እንሥጥ፡፡
“ጌታ የእኛን ትራፊ አይቀበልም። ለእግዚአብሔር መስጠት የመጀመርያውን ነው።” ቃለ ሕይወት ያሰማልን አባታችን።
አሜን አሜን አሜን በረከታቸው ይደርብን