የአንድ ኃጢአተኛ ሰው ጸሎት

አቤቱ “በጎውን ነገር ማን ያሳየናል?” የምንልበት ዘመን አይደለም፤ እንኳን በእኛ ዘንድ ይቅርና ወንጌል በአሕዛብ ዘንድ ሳይቀር የተሰበከበት ዘመን ነውና። ነገር ግን የተሰበከውን ቃል በልቤ አኑሬ ሕይወቴን ሳልለውጥበት ብዙ ዘመናትና ዓመታት አለፉ። ቃልህን ሰምቶ አለማድረግ በአንተ መዘባበት መሆኑን አውቃለሁ፤ ቃልህን የምሰማ እንጅ የምፈጽም ባለመሆኔም ምክንያት በድቡሽት ላይ እንደተሠራ ቤት ሆኛለሁ። ጥልቀት በሌለው አኗኗር ላይ የተገነባው መንፈሳዊነቴ ጎርፍ በጎረፈ፣ ነፋስ ባለፈ ጊዜ የሚናወጥ ደካማ ሆኖብኛል።

 ዓለምን ለማሳለፍ ዳግመኛ መምጣትህን ባሰብሁ ጊዜ እደነግጣለሁ። ጻድቃን “አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና” እያሉ የምትመጣበትን ቀን ሙሽራዋን እንደምትጠብቅ ሴት በተስፋ ይጠባበቃሉ፤ እኔ ግን አሁንም ለንስሐ ዕድሜ እንድትጨምርልኝ እለምናለሁ። ለንስሐ ብየ የለመንሁትን ዕድሜ አሁንም ማለቂያ ለሌለው ፍላጎቴ ባውለውም አንተ ግን የለመንሁትን ዕድሜ ሰጥተህ አጠገብኸኝ። ሰው ምን ቢቸግረው ነው የሠርጉን ቀን የሚያራዝመው? የደስታ ቀኑ እንዳትደርስ የሚከላከል ሰው ማለት እኔ ነኝ። አንተ የምትመጣበት ቀን ከዓለም አስቀድሞ ያጨኻትን የጻድቃንን ነፍስ እንደ ሴት ሙሽራ በአፍህ መሳም ስመህ መኃ 1፥2 የምትቀበልበት ቀን ነው። 

ፀሐይና ጨረቃ በማያስፈልጓት ከተማ ለመኖር ጻድቃን ራሳቸው እንደ ፀሐይና ጨረቃ የሚያበሩበትን ያንን ቀን በቶሎ እንዲመጣ አለመለመን እንዴት ያለ ሞኝነት ነው? ያንጊዜ ታላቅ ደስታ ይደረጋል፤ ሙታንን የሚያነቃቸው ታላቁ ዝማሬ በሰማያውያን መላእክት ይጀመራል፤ መላእክት “ቅዱስ እግዚአብሔር” ሲሉ ምድራውያን ጻድቃንም “ቅዱስ ኃያል…….”  እያሉ ያንን ዝማሬ ሊቀበሉ ከመቃብራቸው ይወጣሉ። ሞት ያንን ምስጋና ሰምቶ ይደነግጣል። ዲያብሎስ ይገሠጻል። 

በእውነት የዚያን ቀን የሚደረገው ተድላ ደስታ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስካሁን አልተደረገም። እመቤታችን “ተፈሥሒ” የሚለውን የምስጋና ቃል በሰማች ጊዜ ያገኘችውን ደስታ ጻድቃን ያንጊዜ ያገኙታል። ያችን የደስታ ቀን ባለመዘጋጀቴ መድረሷን እየቸኮሉ ከሚጠባበቁት ውስጥ አይደለሁምና አዝናለሁ። 

ጌታዬና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ያንን ቀን በደስታ እንድጠብቅ እንጅ ባሰብሁት ጊዜ ከመደንገጥ አውጣኝ። አውቃለሁ ጌታዬ ዛሬ ቃልህን ሰምተው ደስ የማይላቸው ሰዎች ያንጌዜ “ንዑ ኀቤዬ” የሚለውን ቃልህን ሰምተው ደስ አይላቸውም። ያንጊዜም ደስታን የሚሰጠን ዛሬ የምንሰማው ቃልህ ነው። 

ይህንንማ በመካከላችን ስብከትን በጀመርህባት ቀን “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” ባልኸን ጊዜ ገልጠህልን ነበር። መንግሥተ ሰማያት ብለህ የጠራሃት ቃልህን መሆኑን መምህራኖቻችን፥ “መንግሥተ ሰማያት፡− ሕገ ወንጌል፣ ሕገ ወንጌል፡− ተስፋ፣ ተስፋ፡− እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብለው ተርጉመው ነግረውን ተረድተን ነበር። መንግሥተ ሰማያትን በመካከላችን ያኖርህልን ሆይ! ቃልህን በሰሙ ጊዜ የማር ወለላ እንዳቀረቡላቸው ሕጻናት ሳስተው እንደሚሰሙህ ወዳጆችህ እንድሆን እርዳኝ። 

ደፍሬ ስምህን መጥራቴን ሳስብ አንዳንድ ጊዜ ፍርሃት ይይዘኛል፤ ደግሞ “ሰውን የምትወድ ሆይ” ብለው ካህኑ በቅዳሴ ጊዜ ሲጠሩህ ስሰማ ፍርሀቴን ያርቅልኛል። አንተ በምትከብርበት መቅደስ ውስጥ ገብቼ መቆሜንም ሳስብ በቅዱሳን ጉባኤ መካከል የአንድ ኃጢአተኛ የእኔ መገኘት ያስጨንቀኛል፤ ነገር ግን ካህኑ በቅዳሴው መካከል “ወንጌል” ብለው ወጥተው “ኃጥአንን ለንስሐ እንጅ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም” የሚለውን ቃልህን ሲያነቡ በሰማሁ ጊዜ በሰጠኸኝ ዕድል ድምጼን ከፍ አድርጌ አመሰገንሁህ። 

ሰዎች እስኪገርማቸው ድረስ በእኔ በቀራጩ ቤት መዋልህ ለምንድነው? በፊትህ በድለው ከማያውቁ መላእክት ይልቅ የእኔን ምስጋና ለመስማት መምጣትህ ለምንድነው? ሰውን መውደድህ ያስደንቃል! 

ከተግሣጽህ ይልቅ ፍቅርህ ማርኮኝ መጥቻለሁ። ደዌ ከጸናበት ሰው በቀር ሀኪሙን በብርቱ ፍለጋ ማን ይፈልገዋል? እኔም ደዌ ነፍስ ቢጸናብኝ ኃጢአት ቢያስጨንቀኝ መጥቻለሁና ፈውሰኝ። ላገለግልህ ብወድም እንደ ሐማተ ጴጥሮስ ሳልፈወስ ላገለግልህ አልፈቀድሁም። ለአንተ ምን ይሳንሃል? ከለምጼ ልታነጻኝ ብትወድ ይቻልሃል። 

ከአልጋዬ ልታነሣኝ ብትወድስ ማን ይከለክልሃል? ፈውሰኝና ዕድሜዬን በሙሉ አገልጋይህ አድርገኝ። ሳልፈወስ ባገለግል ደዌዬ ወደ ሌሎችም እየተዛመተ ብዙዎችን ይበክላል። ይሁዳ ባዛመተው ገንዘብ መውደድ፣ አፍኒንና ፊንሐስ በጀመሩት የመቅደስ ውስጥ ድፍረት፣ ዳታንና አቤሮን ባቀጣጠሉት ዘረኝነት፣ ሲሞናውያን ባሳዩት ጉቦኛነት ተይዘው ያልተፈወሱ ብዙ ናቸው፤ የእኔም ተጨምሮ የፈውስ ጊዜአችንን እንዳያርቅብን ስለምፈራ ፈውሰኝና አገልጋይህ ልሁን። 

እኔ ሥጋህንና ደምህን የምቀበለው ዝቅ ብለህ አጥበህ እንዳነጻሓቸው እንደ ሐዋርያት ንጹሕ ሆኜ አይደለም፤ እንዲያውም ስቆርብ ያዩኝ ሰዎች ገርሟቸው “ይሄ ኃጢአተኛ ሰው ቆራቢ ለመባል ብሎ ነው እንጅ አምኖበት ነው?” ብለው ተሳለቁብኝ። በሽታ የጸናበት ሰው መድኃኒቱን የሚወስደው ደዌው እንዲለቀው እንጅ ደዌው ከለቀቀው በኋላ ነውን? እኔስ ይህ ቍርባን ፈራጅ እንደሆነ ባውቅም ማኅየዊ እንደሆነም አምናለሁ። 

ሐዋርያት “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” 1ዮሐ 1፥7 ብለው ያስተማሩት ትዝ ይለኛል። የምትፈርድብኝ ፍርድ ሳይሆን “እንካችሁ ብሉ ሥጋዬን፣ እንካችሁ ጠጡ ደሜን” ብለህ ወደ እኔ የዘረጋሃት እጅህን አያታለሁ። ስለዚህም አፌን ከፍቼ እቀበልሃለሁ። 

ዛሬ “በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ አንተን በመፍራትም ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ” ዳግመኛ በምትመጣ ጊዜም በምሕረትህ ብዛት በሚያስፈራና በሚያስደነግጥ ዙፋንህ ፊት እቆማለሁ። ጭብጥ አፈር ወደ ባሕሩ ቢወረወር ባሕሩን ያደፈርሰዋልን? የእኔ የኃጢአተኛው ወደ መቅደስህ መግባትስ ያንተን ባሕርይ ያሳድፈዋልን? በእውነት በስምዖን ቤት መዋልህ ስምዖንን ያነጻዋል እንጅ አንተን አያረክስህም። ማርያም ኃጥዕት እግርህን ያጠበችበት እንባ እሷን አነጻት እንጅ አንተን አላረከሰህም። ደም የሚፈሳት ሴት ልብስህን በመንካቷ ካንተ የወጣው ኃይል እሷን ጎበኛት እንጅ አንተን አልለወጠኸም። እኔም ወደ ቤትህ የምገባው ይህንን እያሰብሁ ነው። 

በተራራው ስብከት ጊዜ ተገኝቼ ስታስተምር ባልሰማህም፤ በደብረ ታቦር በተገለጥህ ጊዜ ክብርህን ካዩት መካከል ባልሆንም፤ በደብረ ዘይት እጅህን ጭነህ ከሾምኻቸው ውስጥ ባልመደብም አንተ ግን ለእኔ ምሕረት ማድረግን አትሰለችም። ወደ አንተ ባልመጣ እንኳን በተኛሁበት መጥተህ “ልትድን ትወዳለህ?” ማለትህ አይቀርም። 

ከሰማይ የወረድህልኝ ሆይ! ኢያሱ ለእስራኤል ርስታቸውን እስኪያወርሳቸው ፀሐይን እንዳቆምህለት በምድር ላይ ያለን ኃጥአን ልጆችህ ሰማያዊት ርስትህን ሳንወርሳት ፀሐይ አትጥለቅብን፤ ዕድሚአችን አይለቅብን። 

አሜን!

Share your love

27 አስተያየቶች

    • ቃለ ህይወትን ያሰማልን የኔታ…በእርሶ ጦማር ምክንያት ዘወትር ሰኞን በጉጉት የምጠብቅ ሆኛለሁ… ብዕርዎ አይንጠፍ የኔታ….ጌታ ሆይ! እኔ ኃጥእ ልጅህ ሰማያዊ ርስትህን ሳልወርስ ፀሀይ አትጥለቅብኝ፣ እድሜየ አይለቅ

  1. ቃለ ህይወትን ያሰማልን የኔታ…በእርሶ ጦማር ምክንያት ዘወትር ሰኞን በጉጉት የምጠብቅ ሆኛለሁ… ብዕርዎ አይንጠፍ የኔታ….ጌታ ሆይ! እኔ ኃጥእ ልጅህ ሰማያዊ ርስትህን ሳልወርስ ፀሀይ አትጥለቅብኝ፣ እድሜየ አይለቅ

  2. እጅ የሚደንቅ ሕይወታችንን የሚኒካ ፤ እኛን ራሳችንን የሚገልጥ ጽሑፍ ነው:: ይህ ድርሰት ብቻ ሳይሆን ጸሎት ነው:: ቅዱስ ቁርባን ከመቀብላችን አስቀድመን ከምንጸልየው ከመቶ አለቃው ጸሎት ቀጥሎ ብንጸልየው ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። (የግል አስተያየት ነው።)

    ሊቀ ሊቃውንትን ሕይወት የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ያሰማዎ ።
    ጥሩ የነፍስ ምግብ እያቀረባችሁልን ነውና ፤ ጀንደረባው ሚዲያን እግዚአብሔር ይስጥልን (ያቆይልን) ።

  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን በተለይ በዚ ዘመን ላለን ወጣቶች እጅግ ጠቃሚ ፀሎት ነው

  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን በተለይ በዚ ዘመን ላለን ወጣቶች እጅግ ጠቃሚ ፀሎት ነው

  5. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፣ ክርስቶስ መንግስቱን ያውስልን።የኔታ

  6. ቃለ ህይወትን ያሰማልን የኔታ
    ዘወትር ሰኞን በጉጉት የምጠብቅ ሆኛለሁ
    “በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ አንተን በመፍራትም ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ”

  7. “ሰዎች እስኪገርማቸው ድረስ በእኔ በቀራጩ ቤት መዋልህ ለምንድነው? በፊትህ በድለው ከማያውቁ መላእክት ይልቅ የእኔን ምስጋና ለመስማት መምጣትህ ለምንድነው? ሰውን መውደድህ ያስደንቃል!”

    “በተራራው ስብከት ጊዜ ተገኝቼ ስታስተምር ባልሰማህም፤ በደብረ ታቦር በተገለጥህ ጊዜ ክብርህን ካዩት መካከል ባልሆንም፤ በደብረ ዘይት እጅህን ጭነህ ከሾምኻቸው ውስጥ ባልመደብም አንተ ግን ለእኔ ምሕረት ማድረግን አትሰለችም። ወደ አንተ ባልመጣ እንኳን በተኛሁበት መጥተህ “ልትድን ትወዳለህ?” ማለትህ አይቀርም።”

    በእውነት እኔው ራሴ የጻፍኩት መሰለኝ!
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!!

  8. ሳልፈወስ ባገለግል ደዌዬ ወደ ሌሎችም እየተዛመተ ብዙዎችን ይበክላል። ይሁዳ ባዛመተው ገንዘብ መውደድ፣ አፍኒንና ፊንሐስ በጀመሩት የመቅደስ ውስጥ ድፍረት፣ ዳታንና አቤሮን ባቀጣጠሉት ዘረኝነት፣ ሲሞናውያን ባሳዩት ጉቦኛነት ተይዘው ያልተፈወሱ ብዙ ናቸው፤ የእኔም ተጨምሮ የፈውስ ጊዜአችንን እንዳያርቅብን ስለምፈራ ፈውሰኝና አገልጋይህ ልሁን።

  9. ምህረትህን ከ እኔ ያላራቅክ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለ ንስሀ አብቃኝ🙏

  10. Ye midenk new masibewun new ezi tihemert wust Menfeskidus yasitemaregn edime yistot
    ዓለምን ለማሳለፍ ዳግመኛ መምጣትህን ባሰብሁ ጊዜ እደነግጣለሁ። ጻድቃን “አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና” እያሉ የምትመጣበትን ቀን ሙሽራዋን እንደምትጠብቅ ሴት በተስፋ ይጠባበቃሉ፤ እኔ ግን አሁንም ለንስሐ ዕድሜ እንድትጨምርልኝ እለምናለሁ። ለንስሐ ብየ የለመንሁትን ዕድሜ አሁንም ማለቂያ ለሌለው ፍላጎቴ ባውለውም አንተ ግን የለመንሁትን ዕድሜ ሰጥተህ አጠገብኸኝ። ሰው ምን ቢቸግረው ነው የሠርጉን ቀን የሚያራዝመው? የደስታ ቀኑ እንዳትደርስ የሚከላከል ሰው ማለት እኔ ነኝ። አንተ የምትመጣበት ቀን ከዓለም አስቀድሞ ያጨኻትን የጻድቃንን ነፍስ እንደ ሴት ሙሽራ በአፍህ መሳም ስመህ መኃ 1፥2 የምትቀበልበት ቀን ነው

  11. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን የኔታ, ጽሑፎትን ሳይ “ዛሬ ደግሞ እግዚአብሔር ምን ሊለኝ ይሆን” ያው መቼም እኔ እርስዎ እንዳሉት “ወደ አንተ ባልመጣ እንኳን በተኛሁበት መጥተህ “ልትድን ትወዳለህ?” ማለቱ አይቀርምና ብዬ ነው የማነበው፤ ልብ ድረስ ይገባል እጅግ ያስተምራል እና የኔታ ዕድሜ እና ጤና ይስጥልን
    ለእናንተም ጃን ሚዲያዎች ብርታቱን ይስጥልን ቃለ ሕይወትን ያሰማልን

  12. ቃለ ህይወትን ያሰማልን መምህራችን በእድሜ በፀጋ ይጠብቅልን። ስለ እዉነት በዚህ ጊዜ እንደናንተ አይነት መምህራንን አያሳጣን እኛንም ለንስሀ የተዘጋጀ ልብን ያድለን።

  13. Endet yemimesit ena yemitafit Tshuf nww …. Min elalew… Qale hiywet yasemalin…. Yagelgilot zemenotn yibarklin yeneta

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *