በሥጋ ማርያም ተገልጦ፥ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በአይሁድ ምድር ሲመላለስ “አምላካቸውን ያዩት ሰዎች እንዴት ታድለዋል?” የሚል ነገር አንዳንዴ ውል ይልብኛል:: (ይሄ ዘወትር የምንደነቅበት ነበር መሆን ያለበት)።
ተመልከቱ ቅዱስ ሉቃስ “እንደልማዱ በሰንበት ወደ ምኩራብ ገባ” ይለናል። (ሉቃ 4፥26) በዕለተ ሰንበት ስትሄዱ መጽሐፉን ገልጦ የሚያነበው ዓለምን በቃሉ የፈጠረው ፥ በእጆቹ የፈጠረን አምላክ ነው። ግን እኔስ በዚያ ዘመን ብኖር ከአይሁድ የተለየ ለጌታዬ ቦታ እሠጠው ነበር? ለዚያውም ዘወትር በሰንበት ወደ መቅደሱ የማልሄድ ከሆነ ፈጽሞ አላየውም።
በቤተ ሳይዳ የጠበሉ ስፍራ ስትሄዱ ሠላሳ ስምንት ዓመታት አልጋ ታቅፎ የኖረን ሰው አንድ በሠላሳዎቹ መጀመሪያ ያለ ወጣት እያናገረው ነው፤ ከዛ በሚደንቅ ተአምር አልጋህን ይዘ ተነሥ ሲለው ታያላችሁ ፤ ያያችሁትን ማመን ቢከብዳችሁም ያን ሰው ግን፣ ያ አጃቢ ያላስከተለውን፣ የወየበ ልብስ የለበሰን ሰው፣ ያ በለሰለሰ ድምጽ የሚናገርን ሰው እንዴት አምላክ ብላችሁ ትወስዱታላችሁ?
በዚያ ላይ በኑሮ ወጥመድ ተወጥራችሁ፣ እከሌ አየን አላየን፣ ማን ነው መጀመሪያ ጠበል ውስጥ ዘልሎ የገባው የሚለው ወሬ አካባቢውን ወጥሮት እንዴት ይኼንን ሰው ዓይኖቻችን ይየው? ስለአምላክ ያላችሁ፣ ስለሚመጣው መሲህ የሰማችሁት ትንታኔ እና የተወሩ ወሬዎች ሁሉ ዓይናችን ሥር ሆኖ ምስኪኑን መጻጉዕ የሚያናግረውን አምላክ የሚያገልል ነበር።
ያ ዘመን ዛሬ ቢሆን እኔ ከአገለሉት፣ ሲገደል ከተደሰቱት ወይም ግድ ካልሰጣቸው ሰዎች ተርታ የምመደብ እንደምሆን እራሴን እጠረጥራለሁ።።
እስቲ በዚሁ ወደ ሰማርያ እንለፍ። ወደ ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራት። “ወደ ሰማርያ ሊያልፍ ግድ ሆነበት” ይለናል ዮሐንስ። ብዙም ሳይዘገይ “በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ” ይለናል። ለምን በሰማርያ ሊያልፍ ግድ እንደሆነበት ሲነግረን። ከዛ አንዲት በኃጢአት የደከመች፣ በሃይማኖቷ ግን “ክርስቶስ የሚባል መሲሕ ይመጣል የዛኔ እሱ ሁሉን ይነግረኛል” ብላ በልቧ የምትጠብቅ ምስኪን ሴት የውኃ እንስራዋን አዝላ ከነመቅጃዋ መጣች።
“ውኃ ሥጪኝ አላት” ያ የማይጠማው ከሷ ኃጢአት የተነሳ ግን ደክሞት የተጠማው ሰው። የተሰመረን መስመር መሲሑ መጥቶ ምክንያቱን እስኪነግራት የምታከብረው ያቺ ሴት ግን አይሁዳዊ ሲሆን ከሳምራዊት ሴት ውኃ ሥጪኝ ማለቱን አልወደደችም። እሱ ግን አላት “የሚጠይቅሽን ብታውቂ አንቺ ነበር ውኃ የምትጠይቂው” ግራ ገባት። በአንድ በኩል የሚቀልድ መሰላት፣ ስለዚህም በምክንያት እና በማሾፍ ሞገተችው “የታለ መቅጃኸ?” አለችው፣ በሌላ በኩል ይሄ ሰው ሥርዓት አለው፣ እንደሌሎች የምታውቃቸው አይሁድ አልመስላት አላት፣ አይሁድ ሆኖ ሳለ ከሳምራዊት ሴት ጋር ማውራቱ ሳያንስ አነጋገሩ በሥልጣን ነበር። ቸል ብለው የማያልፉት ነበር። ይሄም ከቃሉ የተነሳ ብቻ አልነበረም። ከሁኔታው፣ ከመልኩ፣ ከሞገሱ፣ ዓይን ብቻ የሚገባው ቃላት የማይገልጸው የእውነት ውበት በማየቷ ጭምር እንጂ፣ ይሄ ግን አካላዊ ውበት እንዳይመስላችሁ፤ ከኃጢአት ድካም ማረፍን የናፈቀች ነፍስ ብቻ የምታውቀው፣ ስታየው ግን የማታልፈው ልዩ ውበት እንጂ። ። በመኃልየ መኃልይ ጠቢበኛው ሰሎሞን የገለጻት ነፍስ ስታየው የምታውቀው ፥ ውዷን ከመፈለጓ የተነሳ የደከመችው ያቺ ሴት ስታየው የምታውቀው ውበት ያለው ነበር እንጂ። ለዚህ ነው “ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ” ያለችው። ንግግሩ ብቻ ስላልሆነ ነው “አያለው” ያለችው።
አምስት ባሎች የነበሯት አሁን አብራው ካለችው ጋር ባልተቀደሰ ጥምረት የተሳሰረችው ያቺ ሴት ግን ክርስቶስን ግድ ያስባለ የሃይማኖት ውበት ነበራት። ያም ተስፋ ነበር። “አንተ ከአባቶቻችን ትበልጣለህ፣ አንተ ከያዕቆብ ትበልጣለህ፣ ደግሞ ይመጣል ያ መሲሒ፣ ይመጣል ክርስቶስ ሊነግረን ሁሉን” ትለው ነበር ለራሱ ለክርስቶስ። በኃጢአት ብዛት ቀጥና በአባቶቿ እምነት ተስፋ ግን ሳትሰበር ያለችው ያቺ ጌታን ግድ ያሰኘች ነፍስ።
ሲ ኤስ ሉዊስ እንዲህ ይላል “በዚህ ምድር ላይ ተራ ሰዎች የሉም። ከሟች ሰው ጋር በሕይወታችሁ አውርታችሁ አታውቁም።” ተፈጥሮ፣ ሀገራት፣ ባህሎች፣ ጥበቦች፣ ስልጣኔዎች እነዚህ ናቸው ሟቾች። እነዚህ ናቸው አርጀተው የሚጠፉት። የእነዚህ ሕይወት ነው ለእኛ ጥቅም፣ ለእኛ እንደ ትንኝ መሆን ያለባቸው። የምናወራው፣ የምንቀልደው፣ የምንሰራው፣ የምንጋባው፣ የምንበዘብዘው፣ የምናሰቃየው፣ የምንጨቁነው ግን ዘላለማዊን ነው። ከዘላለማዊው ጋር ነው የምንጋፋው። የምንተቃቀፈው። ጌታችን ያን ሁሉ ሰዓት በውሃ ጉድጓድ ዳር ተቀምጦ የጠበቃት፣ በእኛ ዓይን ብትሆን ባል የማይበረክትላት ተብላ የተገፋች፣ በማንኛውም ሰው ዓይን መሙላት የማትችለው ያቺ ዘላለማዊ ነፍስ ያላት አንዲት ሳምራዊት ነበረች። አንዲት ሳምራዊት። የምታየውን ወንድምህን ካልወደድክ እግዚአብሔርን ወዳለው ማለት ውሸት ነው ይለናል ሐዋርያው ዩሐንስ በመልዕክቱ፣ ምክንያቱም እግዚአብሔርን አላየኸውምና። (1ዮሐ 4፥20)። ይሄ ማለት አጠገብኽ ያለው ዘላለማዊው ወንድምኽ ነው ያላየኸው አምላክ መገለጫ። እሱን ውደደው፣ ግድ በለው፣ ለምነው ውሃ ላጠጣ ብለህ፣ የሚያስፈልገውን ለምኖ አይደለም ለምነኽ ስጠው እያለን ነው። ዘላለማዊውን ወንድማችንን ስንረዳ ዘላለማዊው ውሃ፣ የፍቅር ውሃ፣ የዚህን ዓለም ውሃ የማያስጠማው ውሃ ፥ የሕይወት ምንጭ መፍለቅ ይጀምራል ከውስጣችን። ክርስቶስ ግድ የተሰኘባትን ነፍስ ያልናቅን ለታ፣ ያን ጊዜ ነው ጌታችንን መውደድ የምንጀምረው። ያቺ ነፍስ በኃጢአት የደከመች ቢሆን እንኳ፣ ያቺ ነፍስ እኛን የሚያበሳጭ እና የሚያናድ ነገር ከመሥራት የማትቦዝን ቢሆን እንኳ፣ ያቺ ነፍስ ቀን በቀን ብታቆስለን እንኳ ከጌታችን ሥጋና ደም ቀጥሎ በዚህ ምድር ላይ ያቺን ነፍስ ነው ልናከብረው የሚገባው። ይሄ ነው የክርስቶስ ፍቅር። የሱ ፍቅር ያለ ቅድመ ሁኔታ አይደለም። ምክንያቱም “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን” (ዮሐ 14፥23) ብሎናልና። የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቅ፣ እወድኸለው ስላልከኝ ብቻ አልመጣም እያለን ነው፣ ቃሌን የሚጠብቅ ግን ይወደኛል፣ እኔም አባቴም እንመጣለን። እንመጣለን በሱ ውስጥ መኖሪያ ልናደርግ። በቁመተ ሥጋ ተወስኖ በአይሁድ ምድር ሲመላለስ በእጆቹ የመዳሰስ፣ ቀሚሱን የመንካት፣ እንደ ዮሐንስ ደረቱ ላይ የመተኛት ዕድሉን ላላገኘን ሁሉ በእውነት ግን ይሄን ዕድል ለምንመኝ፣ በእናንተ ውስጥ ከአባቴ ጋር መኖሪያዬን ላደርግ እመጣለሁ አለን። ቃሌን ከጠበቃችሁ።
ለሰማሪያዊቷ ሴት እንዳላት የዘላለም የውሃ ምንጭ በውስጣችን ሊያፈልቅ ይመጣል። ያ የውሃ ምንጭ በውስጡ የፈለቀለት ቅዱስ ጳውሎስ ይሄን አለን “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? … ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ …
ከጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” (ሮሜ 8፥ 35-39)። “መቅጃ የለህም” በማለት እንስራ እና መቅጃ ስላላት ውሃ መጠጣት፣ በመጠጣትም መርካት የምትችል የመሰላት ያቺ ምስኪን ሴት፣ አሁን መቅጃዋን አይደለም እንስራዋን ሳይቀር ትታ ወደ ከተማ ሄደች። ሌሎች ለዘላለም መንግስቱ እንዲሆኑ “ኑ ፥ ያን አንዲት ምስኪን ሴትን ለማዳን የደከመውን እዩ” ብላ ከከተማው ሰዎችን ጠራች። አገኘውት እያለች በንዳድ ፀሐይ የደከመች ዋላ ውሃ ስታገኝ እንደምትዘለው እየዘለለች ወደ ከተማ ገባች። አገኘውት ውዴን እያለች። ኑ እዩት ውዴ እንደ በረዶ ንጹሁ ነው ፥ ኑ እዩት ውዴ ስለእኛ በደም ተለውሶ ቀይ ነው። ኑ እዩት አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው ይነግራችኋል ከሁሉ የተሰወረውን ታሪካችሁን፣ መልኩም ለነፍሴ ያማረ ነው። ኑ ሳምራውያን ሆይ ፥ ውዴ ይህ ነው ፥ ይመጣል ያልነው ክርስቶስ ይህ ነው ፥ ባልንጀራዬም ይህ ነው። (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 5፥ 10-16)።
በዚህ ምድር ላይ የሚገጥመን ሰው ሁሉ ጌታችን በመስቀል ላይ ደሙን ያፈሰሰለት ነው። ያለእሱ ፈቃድ በዚህ ምድር ሊመላለስ ይቅርና ከጸጉሩ አንድ እንኳ ያለአምላካችን ፈቃድ አትነቀልም። ያ ሰው ክርስቲያን ሲሆን ደግሞ ክብሩ ልዩ ነው። በዚህ ምድር ላይ ባልጀራችን ነው አምላካችንን የመውደዳችን መገለጫ። ለእኛ በጣም ቅርቡ እሱ ነው። በሰማርያ ለአንዲት ኃጢአተኛ ያን ሁሉ የደከመ ጌታችን፣ በጎልጎቷ የመስቀልን መራራ ሞት የተጎነጨላትን ያቺን ነፍስ እናክብራት። ስልጣኔ እንጂ ሟች ፥ የሰው ልጅ አይደለም።
እውነት ነው መምህራችን ቃለህይወት ያሰማልን፡፡ለኛም ፍቅሩን ያድለን፡፡
በሰማርያ ለአንዲት ኃጢአተኛ ያን ሁሉ የደከመ ጌታችን፣ በጎልጎቷ የመስቀልን መራራ ሞት የተጎነጨላትን ያቺን ነፍስ እናክብራት፡፡
እግዜር ይስጥልን
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
ስልጣኔ እንጂ ሟች ፥ የሰው ልጅ አይደለም።
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን መምህር!
ድክመቴን በዚህ ጽሁፍ እንድመለከት ያደረገኝን እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ!
ይቅርታ እንድጠይቀው ያደረገኝ መልዕክት ነው! አመሰግናለሁ መምህር🙏
Kale hiwot yasemaln
አሜን ቃለህይወት ያሰማልን
ጌታዬ ሆይ ለእንደኔ አይነቱ በባለንጀራው ላይ ለሚታበይ ይቅርታህ እና ቸርነትህ አይለየኝ::
ቃልህን በልቤ አትምልኝ በንፁህ ፍቅርህ እጠበኝ!!!
Amen
በእውት ቃለሕይወትን ያሰማልን