የምሥጢራት ምሥጢር 

በግእዙ ምሥጢር  የምንለው በግሪክ ሚስትሪ Mystery ሲባል፤ በላቲን ደግሞ Sacrament  የሚባለው በነጠላ መጠሪያው ነው። 

ምሥጢራት፣ Mysteries (Sacraments) ስንል ደግሞ በብዙ የምንጠራበት ነው። የግሪኩ ሚስቲሪዮን ከላቲኑ ሳክራመንት ጋር አቻ ቃል ነው:: 

ምሥጢር  ማለት ድብቅ፣ሽሽግ፣ለልብ ወዳጅ ለቅርብ ዘመድ ካልሆነ በስተቀር የማይገለጥ ማለት ነው። ምሥጢር ላመኑ እንጂ ላላመኑ የማይሠጥ፣ በዓይን የሚታየው በእጅ የሚዳሰሰው  ነገር በመንፈስ ቅዱስ ሲለወጥ አይታይም፣ ምእመናን በሚታየው አገልግሎት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሲቀበሉ አይታይምና ምሥጢር ነው። 

ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን የሚፈጸሙት በግብር አምላካዊ በመንፈስ ቅዱስ የሚፈጸም ስለሆነ ምሥጢር ተብሏል። “ይህቺ ቀን ምን ያህል የምታስፈራ ናት? መንፈስ ቅዱስ ከሰማየ ሰማያት የሚወርድባት…መሰዋዕቱን የሚሰውርባትና የሚያከብርባት።” እንዲል  መጽሐፈ ቅዳሴ።  

በግእዙ ምሥጢረ ምሥጢራት፣በአማርኛው የምሥጢራት ምሥጢር፣ በላቲኑ Sacrament of Sacraments በግሪኩ ደግሞ Mystery  of Mysteries በማለት የምንጠራው ቃል በሁለት መልኩ ይተረጎማል።

ምሥጢረ ምሥጢራት የሚለው ቃል የመጀመሪያው ለምሥጢረ ሥላሴ ሰጥተን የምንተረጉመው ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ ለምሥጢረ ቁርባን ለአምላካችን ለክርስቶስ ሰጥተን የምናብራራው  ነው። የመጀመሪያውን እንመልከት፦

ምሥጢረ ሥላሴ

___

ምሥጢረ ምሥጢራት ማለት የምሥጢራት ሁሉ የበላይ መጀመሪያ ምሥጢር  ማለት ነው።  ሰማይ፣ ምድር፣  መላእክት፣ ደቂቀ አዳም ከመፈጠራቸው የሚቀድም የማይቀደም( ‘ቀ’ አጥብቅ) ቀዳማዊ ምሥጢር ፤ ምሥጢረ ሥላሴ ነው።

ከምሥጢረ ሥላሴ ከሌሎችም ምሥጢራት በቅድምና መታወቅ ያለበት ሦስትነት አንድነት ነውና ምሥጢረ ምሥጢራት የምሥጢራት ሁሉ የበላይ ምሥጢር ምሥጢረ ሥላሴ ነው።

“መቅድመ ኲሉ ንሰብክ ሥላሴ ዕሩየ ወቅዱስ ዘውእቶሙ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ – ከሁሉ አስቀድሞ በአካል ልዩ በክብር አንድ የሚሆን ሦስትነትን እናስተምራለን። እኒህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው” እንዲል ሊቁ ( ሃይ.አበው ፷ ፥፪ ) ምሥጢረ ሥላሴን ከምሥጢራት ሁሉ ቀድሞ መጀመሪያ መማር ይገባል።

“በእንተ ምሥጢር ዘትትወሀብ ለመንፈሳውያን ሊቃውንት ወትትነገር ለምእመናን በስመ ቅድስት ሥላሴ ዘትዜኑ ምሥጢረ ምሥጢራት ዛቲ ይእቲ”

ትርጉም- ለመንፈሳውያን ሊቃውንት ስለምትገለጽና በቅድስት ሥላሴ ስም አምነው ለሚኖሩ ምእመናን ስለምትናገር ምሥጢረ የምትናገር ከምሥጢራት ሁሉ የምትቀድም ምሥጢር ይህቺ ናት ይህቺውም ምሥጢር፤ ምሥጢረ ምሥጢራት ምሥጢረ ሥላሴ ናት።” እንዲሉ የ”ምሥጢረ ምሥጢራት – ፩ ” መጽሐፍ ጸሐፍያን መ/ር ገብረ መድኅን እንየው እና መ/ር መዝገበ ቃል ገ/ሕይወት ምሥጢረ ምሥጢራት ምሥጢረ ሥላሴ ነው።

የሰው ልጅ በቅድሚያ ለሃይማኖት ያህል ሁሉን ሚያሳውቀውን ሁሉን የሚያውቅ ፈጣሪን ማወቅ ይገባል። የትምህርት፣ የሃይማኖት ፣የምግባር ፣ የትሩፋት መጀመሪያ ሁሉ ስመ ሥላሴ ምሥጢረ ሥላሴን- ምሥጢረ ምሥጢራትን  መማር ነው።     

      ምሥጢረ ቁርባን 

___

የግሪኩ ሚስቲርዮን ከላቲኑ ሳክራመንት ጋር ትይዩ ሲሆን በኦርቶዶክስ ነገረ መለኮት የመለኮታዊ ጸጋ መገለጥ ላለው ለማንኛውም ሥርዓት የሚገባ ቃል ነው:: (Maria Gwyn McDowell, Concise Encyclopedia of Orthodox Christianity , Anthony McGukin, 2014, 329)

ከክርስቶስ ጋር ያለን ኅብረት ዕውን የሚኾነው በምሥጢራት ተሳትፎ ያለበትን ሁኔታ መሠረት አድርጎ ነው። በጥምቀት ያገኘነው ልጅነት፣ በምሥጢረ ቁርባን የምናሳካው ኅብረት (ዮሐ.15፥4-7)፣ እና ሌሎችም በምሥጢራቱ አማናዊነት ላይ ባለን ጽኑ እምነት መነሻ ኦርቶዶክሳዊ ማንነታችን የሚሠራባቸው ናቸው። 

ምሥጢረ ምሥጢራት ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ሁላችንንም ግባችን ወደኾነው ሱታፌ አምላክ (የመለኮታዊ ባሕርይ) ተካፋይነት(2ጴጥ 1፥4) የሚያደርሰን የሕይወት ስንቅ ነው። [Geo Pallikunnel, Elevation to the divine state Through Holy Qurbana, 2016,232]

የቤተ ክርስቲያን አንድነት በምሥጢረ ቁርባን ላይ የተመሠረተ ሲሆን ቅዱስ አግናጥዮስም  ” ቤተክርስቲያን ምሥጢረ ቁርባን  ሲፈጸም ምልዓትዋ ላይ የምትደርስ ቁርባናዊ ማኅበር ናት” እያለ በዚያ ቀዳሚዊ ዘመን  (ኹለተኛው ምዕት ዓመት መጀመሪያ)አስተምሯል። 

በምሥጢራት አማካኝነት ብዙ ስንኾን አንድ እንደኾንን ይነግረናል፣ በዚህም የሰው ዘር ኹሉ የሚተባበርበት የሰላም መሠረት ነው። ” አንድ ስለምታደርግ ሥጋውና ደሙ እግዚአብሔር አንድ ያደርገን ዘንድ “በማለት በቅዳሴ ሰዓት በዲያቆኑ የሚነበበው የሚጸለየው በእንተ ቅድሳት የተባለው ክፍል የሚያስረዳን አንድ የሚያደርገን ምሥጢረ ቁርባን መሆኑን ነው። (በእንተ ቅድሳት፣ መጽሐፈ ቅዳሴ፣ 1984፣22)

በምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በምሥጢረ ቁርባን ብዙዎች ስንሆን አንድ መሆናችንን፦”እንዘ ብዙኃን ንህነ እም ጾታ ዘመን ዘዚአሁ:: ነአምን ሞቶ ወንሴፎ ትንሣኤሁ:: ለእግዚእ ክርስቶስ ለእመ ተኀትመ ጸጋሁ:: መለያልየ አሐደ ይረስየነ ምስሌሁ:: በአጽናፈ ዓለም ይጠባህ አሐዱ ሥጋሁ፤ እንዲሁ ብዙዎች ስንኾን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፣ እርስ በእርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን” (ሮሜ 12፥5) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በተግባር የተረጎመና የሰው ልጅን ኦርቶዶክሳዊ ማንነት በምሥጢራዊ መንገድ የሚያውጅ በምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በኩል የሚፈጸም መሆኑን እንረዳለን ነው።

ከሰማያት የወረደው ኅብስት በአካለ ሥጋ ምድራውያን ለሰማያዊ ዋጋ እንዲበቁለት በመስቀል ላይ ተቆርሶና ተቀድቶ የተሰጠው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው “ሰማያዊውያን መና ምድራውያን በሉ፥ በኃጢአት ትቢያ ከነበሩት በመንፈሳዊው ኅብስት ተወስደው በረሩ፣ በገነትም አበሩ። በዚህ ኅብስት እያንዳንዱ ሰው እንደ ንሥር እስከ ገነት የሚበር ይኾናል። የልጁን ሕይወታዊ ኅብስት የበላ ኹሉ በደመናት ውስጥ ወደ እርሱ ይበራል” እያለ ለመንፈሳዊው ዕድገትና ጥንካሬ ሥጋ ወደሙ ያለውን ከፍተኛ ሚና እንደሚከተለው በዝማሬው ያስተምራል።

“ምድራውያን ሰማያዊውን መና ተመገቡ::

በኃጢአታቸው ምክንያት ትቢያ ሆነው ነበር:: መንፈሳዊው እንጀራ ግን ወደ ገነት አሳርጎ ብሩሃን አደረጋቸው:: የወልድን ሕያው ሥጋ የሚበላ ሰው በደመናት መካከል እየበረረ እንደ ንስር ወደ ሰማይ ይወጣል” [Hymns on the unleaved bread, 17.8-9,12-13.Geo Pallikunnel,Elevation to the divine state through Qurbana,2016,79-80]

የክርስቶስ ሥጋና ደም በረጅሙ መንፈሳዊው ጉዞአችን የሚያስፈልገን ስንቃችን ነው። በዚህ ምክንያት በምግበ ነፍስ፣ ምግበ ሕይወት ደረጃ ዘላለማዊ ሕይወት የሚገኝበት ምሥጢር ኾኖ ነው የቀረበልን።[John D.Zizioulas, The Eucharistic Communion and The World,2011,24 ] የነገረ መለኮት ትምህርት መግቢያ መጽሐፍ ፣መ/ር ግርማ ባቱ ገጽ 239)

በምሥጢረ ቁርባን ውስጥ የምናገኘው ከክርስቶስ ጋር ያለ ሕይወት የሐሳብና የስሜት ደረጃዎችን ያለፈ ኅብረት ነው።ብዙዎች ስንሆን አንድ የሚያደርገን ምሥጢረ ምሥጢራት ነው።

___

ምስጢረ ቁርባን ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት  (ምስጢረ ሥላሴ፣ምስጢረ ስጋዌ፣ ምስጢረ ጥምቀት፣ምስጢረ ቁርባን እና ትንሣኤ ሙታን) አንዱ ሲሆን፤ ምሥጢረ ንስሐ ደግሞ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን  (ጥምቀት፣ ሜሮን፤ ቁርባን፣ክህነት፣ ተክሊል እና ቀንዲል) አንዱ ሆኖ ከ 7 ዓመት በኋላ ላሉ ኦርቶዶክሳውያን ወደ ምሥጢረ ቁርባን ለመድረስ ቅድመ ሁኔታው ራስን ለካህን ማሳያው እና ማስፈቀጃው  መንገድ ነው።

ምሥጢረ ቁርባን የአንዲት ቤተክርስቲያን  ቅድሳት ነው። ሃይማኖታቸው የቀናና እውነተኛ የሃይማኖትን መንገድ ያቀኑ ቀደምት አበው አምስቱ አዕማደ ምሥጢርን በያዘ በዘወትር የጸሎተ ሃይማኖት ክፍላችን ላይ፦ “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት ፤ ትርጉም- ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን።” በማለት ሠልስቱ ምዕት-318  የሃይማኖትን ድንጋጌ አስቀምጠዋል። ያስቀመጡበትም ምክንያትም በአንዲት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ምስጢረ ምስጢራት (የምሥጢራት ሁሉ ማጽኛ ማኅተም) የሆነው ምስጢረ ቁርባን የሚግለጥ ነው።

ሁሉን አንድ የሚያደረግ ቅድስት የእግዚአብሔር ልጅ የክርስቶስ ሥጋና ደም ሥልጣነ  ክህነት ባላቸው  በካህናት እና በምእመናን የኅብረት  ጸሎት አማከኝነት በመንፈስ ቅዱስ አሠራር አማናዊ የክርስቶስ ሥጋና ደም በአንዲት  ቤተክርስቲያን ይፈጸማል ፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴያችንም በበእንተ ቅድሳት ጸሎት ላይ “አንድ ስለምታደርግ  ሥጋው እና  ደሙ ”  እና ” ቅድሳት ለቅዱሳን” በማለት ምሥጢረ ቁርባንን ቅድሳት ልዩ ምሥጢር እንደሆነ ገልጧል።

ምሥጢረ ቁርባን የምሥጢራት የአገልግሎት ሁሉ መክብብ ነው። ይኸውም ምስጢር የሌሎች ምስጢራተ ቤተክርስቲያን (ጥምቀት፣ቁርባን፣ሜሮን፣ክህነት፣ ንስሐ እና ተክሊል) እና ሥርዓተ አምልኮ፣ ሰዓታት ማኅሌት ኪዳን መክብባቸውና መፈጸሚያቸው ምሥጢረ ምሥጢራት ነው፡፡ 

ምሥጢረ ቁርባን ለመንግስተ ሰማያት የተገባን የምንሆንበት የሰው ልጆች ድኅነትን (የዘላለም ሕይወትን) የምናገኝበት፣ በክርስቶስ ቤዛነት ያገኘነውን ነፃነት በሥጋዊ ድካም በኃጢአት ስናሳድፈው ደግሞ ለዘለዓለም ሕያው ከሆነ መስዋዕት በመንፈስ ቅዱስ ጸጋን የምንካፈልበት ታላቅ ምሥጢር ነው።

ምሥጢረ ቁርባን በድቅድቅ ጨለማ የተመሰለ ኃጢአትን ድል አድርገን ለሰርጉ ቤት ለመንግስተ ሰማያት የተገባን የምንሆንበት ታላቁ ምሥጢር ሲሆን ምሥጢራዊ  ዕራት ተብሎም ይጠራል። ግብጾች ዩክሪስት (Eucharist ) ይሉታል፡፡ ይህም ቃል የግሪክ ሲሆን ትርጉሙ ‹‹ምስጋና ማቅረብ›› ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹የጌታ እራት››፣ ‹‹ምስጢራዊው እራት››፣ ‹‹አንድ የመሆን ምስጢር›› በማለትም ምሥጢረ ቁርባን  ይተረጎማል። 

ምሥጢረ ቁርባን  የምሥጢራት ሁሉ ማጽኛ ሲሆን፣ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ከተፈጸሙ በኋላ ማጽኛው ማኅተሙ ምሥጢረ ምሥጢራት (Sacrament of Sacraments) በመባል የሚታወቀው ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡

ምሥጢረ ምሥጢራት ቅዱስ ቁርባን በንስሐ እና በጋብቻ ውስጥ  ያለው ድርሻ ስንመለከት ለምሥጢረ ንስሐ ወደ ንስሐ አባት ቀርቦ ንስሐን የፈጸመ ሰው ንስሐው ሙሉ የሚሆነው የምሥጢረ ንስሐ ማጽኛ የሚሆነው ምሥጢረ ቁርባን ሲፈጸምለት ነው።

ምሥጢረ ጋብቻም  የሚጸናው የሚታተመው አንድ የሚያደርገው ምሥጢረ ምሥጢራት በተባለው በቅዱስ ቁርባን የተፈጸመ እንደሆነ ነው። ቅዱስ ቁርባን የጸጋዎች  ሁሉ አክሊል ነው። አንድ ጊዜ ስለ ዓለም ሁሉ ቤዛ መሥዋዕት ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም አካሉ እንሆን ዘንድ የምንካፈልበት፣ ከክርስቶስ ለቤተክርስቲያን የተሰጠ የጸጋዎች ሁሉ አክሊል ነው፡፡

ምሥጢረ ቁርባን ግሩም የሚያድን እሳታዊ ምሥጢር ሲሆን ይህን ምሥጢር  ደጉ አባታችን አባ ሕርያቆስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በተናገረው የቅዳሴ ማርያም አንቀጽ “ዛሬ በዚህች ቀን በፍቅርና በትሕትና ግሩም በሚሆን በዚህ ምሥጢር ፊት እቆማለሁ በዚህም ማዕድና ቁርባን ፊት…

መንፈሳቸውን ያረከሱ ሰዎች ከርሱ ሊቀምሱ የማይቻላቸው በእውነት ቁርባን ነው፡፡ በበግ በጊደርና በላም ደም እንደ ነበረው እንደ ቀደሙት አባቶች መሥዋዕት አይደለም፤ እሳት ነው እንጂ፡፡ ፈቃዱን ለሚሠሩ ልቡናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው፡፡ ስሙን ለሚክዱ ለዓመፀኞች ሰዎች የሚበላ እሳት ነው፡፡” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 5-7)ብሎል።

በእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት (በምስጢረ ስላሴ) አምነው በክርስቶስ ደም የተዋጁና በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቁ ምዕመናን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በመቀበል ምስጢረ ቁርባንን ይፈጽማሉ፡፡

ጌታም በቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› (ዮሐ 6፡54) ብሎ እንደተናገ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን የሚቀበሉ ምዕመናን የዘላለም ሕይወት አላቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ሳይገባው ይህንን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት›› (1ኛ ቆር 11፡26) ብሎ ገልጿል።ቅዱስ ቁርባን መዳናችን የተፈጸመበትና የታተመበት የምሥጢራት ሁሉ ዘውድ ፣ ማጽኛ፣መክብበ ምሥጢረ ምሥጢራት Sacrament of sacraments ነው።

ምሥጢረ ቁርባንን ያስተማረን በተግባር ፈጽሟ ያሳየን በጸሎተ ሐሙስ  ማታ መጋቢት ሃያ ስድስት  ከአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ አንድ ዓመት በፊት መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ዮሐ.6፥41-60፣ ማቴ. 26፥26-28። 

የምሥጢረ ምሥጢራት ምስጢረ ቁርባን ተካፋይ የሆነ ሁሉ ስለ ቅዱስ ቁርባን ትርጉም፣ አስፈላጊነት፣ አፈጻጸም …ወዘተ ማመንና ማወቅ መፈጸም ይጠበቅበታል። 

Share your love

4 አስተያየቶች

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *