ጳውሎስና ሲላስን በመሣሪያ ያጀባቸው ሰው አልነበረም

የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ – ጃን ያሬድ በሚል ርእስ በመዝሙር ዘርፍ ለሚሠራው አገልግሎት ምክረ ሃሳብ (Proposal) በሚሠራበት ወቅት ካነጋገራቸው በአማርኛ መዝሙር ዘርፍ የካበትተ ልምድና እይታ ያላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች መካከል መምህር ተስፉ አንዱ ስለነበረ ከጃንደረባው ትውልድ የጃን ያሬድ ምክረ ሃሳብ አዘጋጆች ጋር ዘለግ ያለ ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር:: ከቃለ መጠይቁ በኋላ መምህር ተስፉ ወደ አምላኩ ቢጠራም ለመዝሙር አገልግሎት ያለውን በጎ ህልም ግን ለዚህ ትውልድ ከአደራ ጋር ጭምር አጋርቶ ነበር:: 

የመምህር ተስፉ ሃሳቦችና ጥቆማዎች አንዳንዶቹ በሥራ ሊታዩ የሚገባቸው የዝማሬን አገልግሎት ከትናንት ጋር የሚያስተሳስሩ ጥቆማዎች ሲሆኑ ትምህርት አዘል ትንታኔዎችም የሠጡባቸው ይበዛሉ:: ወደ አእላፋት ዝማሬ እየገሰገስን እንደመሆናችን በዚህ ሰንበት የጃንደረባው ሠረገላ ላይ ከመምህር ተስፉ ግርማ ጋር “በመዝሙር አገልግሎት ታሪክ” ዙሪያ ጃን ያሬዶች ካደረጉት ቆይታ ለአንባቢያን የሚሆኑትን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል:: 

መምህር ተስፉ ግርማ :- እኔ ልጅ በነበርሁበት ዘመን ከነበረኝ ትውስታ ልጀምር፡፡ በሰማንያዎቹ ውስጥ እየሰማን ያደግነው በገና እና ዘለሰኛ ነበር፡፡ መዝሙር ካሴት ስላልተስፋፋ በዐቢይ ጾም በሬድዮ ዜና ሊቀርብ ሲል ‘አንድ መዝሙር እንጋብዛችሁ’ ተብሎ አስቀድሞ ይለቀቅ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደግሞ እኔ ባደግሁበት አምስት ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በር ላይ አንድ መዝሙር የሚሸጥበት ቆርቆሮ ቤት ነበር፡፡ እዚያ መዝሙር ሲከፈት ነበር የምንሰማው፡፡አሁንም ድረስ ቃናቸው በሕሊናዬ ይመጣብኛል፡፡ የነ አቶ ደምሴ ፣ የነ ዓለሙ አጋ ፣ የነ ዓለማየሁ ፈንታ መዝሙራት ነበሩ፡፡ የቀረጻው ጥራት ላይ ብዙም አናተኩርም፡፡ መልእክቱ ላይ ግን እናተኩር ነበር:: ቀጥሎ ደግሞ የመሪጌታ ፀሐይ ፣ ሊቀ መዘምራን ኪነ ጥበብ በፒያኖ የሚዘምሩት ዝማሬ እናዳምጥ ነበር፡፡

መምህር ተስፉ ግርማ :- እንደሚመስለኝና በወቅቱ እንደ ሰማሁት በቤተ ክርስቲያንዋ ጥያቄ በስድሳዎቹ ጊዜ የምድር ጦር አንደኛ ክፍለ ጦር በኦርኬስትራ መዝሙር ያቀርብ ነበረ፡፡ እንዲያውም በሆነ ጊዜ በ1960 አንደኛ ክፍለ ጦር ሙዚቀኞች እነ አርቲስት ብዙነሽ በቀለ የዘመሩት ‘ጊዜዬ እስኪደርስ’ ‘ልመናዬን ስማኝ’ የሚል መዝሙር ሁሉ ነበረ፡፡ በኋላ የእነርሱን መዝሙራት እነ ዘማሪ መገርሳ እነ ዲያቆን ታደለ ፊጣ በመንፈሳዊ መዝሙር መልክ ዘምረውታል፡፡  

በወቅቱ ሌሎች እምነቶች የሙዚቃ መሳሪያን በመጠቀማቸው ወጣቱ እየተሳበ ከቤተ ክርስቲያን እየወጣ ስለነበረ እሾህን በእሾህ ለመዋጋት በሚል ወደ ሌላ ካምፕ እየሔደ ያለውን ወጣት ለመመለስ በሚል የተጀመረ ይመስለኛል፡፡ ቅዳሴ ላይ ‘እስመ ኃያል አንተ’ ሲባል ፣ ‘እስመ ለዓለም’ ሲባል ይታጀብ ነበር፡፡ ፒያኖውን በመዝሙር ላይ ሲጠቀሙ ያን ያህል መሣሪያው ከዘማሪው ድምፅ በላይ ጎልቶም አይሰማም ነበር፡፡ ለስለስ ያለ ብቻ ነበር እንጂ መሣሪያውም ጉልሕ አልነበረም፡፡ በሒደት ግን እንዲቀር ተደርጓል፡፡ የሰባተኛና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ፡፡ የመሪጌታ ፀሐይን ‘ዐውደ ዓመቱን ባርኪልን’ ፣ የሊቀ መዘምራን ኪነ ጥበብን ‘የሲና ሐመልማል’ ‘መሠረተ ዜማ ወጠነ’ የሚሉ መዝሙራት ለመስማት እዚያች መዝሙር ቤት ከትምህርት ቤት መልስ እንሔድ ነበር፡፡ 

  ጃንደረባው :- በቤታችሁ በቴፕ መስማት አትችሉም ነበር? 

የሚገርመው መዝሙር ቤት ባዶ የክር ካሴት ይዘህ ስትሔድ መቅጃ መሣሪያ ስለሌለ አንድ ሰዓት ሙሉ ቁጭ ብለህ መዝሙሩን ከቴፑ ላይ አስቀድተህ ነበር የምትወስደው፡፡ ተቀርጾ የሚሠጥህ ቁጭ ብለህ አዳምጠህ ነበር፡፡ ይህ ትውልድ ላያውቀው ይችላል እንጂ መዝሙሩን ለመስማት ይህ ሁሉ ነገር ነበረ፡፡ ካሴቱ ቤት ሔዶ ካልሠራ ወይ ትደበድበዋለህ አለዚያም በእስክሪፕቶ ታሽከረክረዋለህ፡፡ የምትፈልገው መዝሙር ላይ ለማሳለፍም እንዲሁ ማሽከርከር ያስፈልግ ነበር፡፡ ለመዝሙር ካለን ፍቅር የተነሣ ብርቅ ሆኖብን እንሰማ ነበር፡፡ መዝሙር ወደ ቤትም ወስደን እንደ ቅዳሴ አክብረን በጸሎት መንፈስ እንሰማው ነበር፡፡   

መምህር ተስፉ ግርማ :- የካሴት መዝሙር መታተም የተጀመረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በኩል ነበር፡፡ አስታውሳለሁ የካሴቶቹ ሽፋን ቀይ ሽፋን የነበረው ካሴት ነው፡፡ መዝሙር ቤት ስላልነበረ በመምሪያው በኩል ይታተማል፡፡ ሰው ኮፒ እያደረገ ይወስድ ነበረ፡፡ ሽያጭም አልነበረም፡፡ ቀስ በቀስ ነው መዝሙር ቤቶች እንደ አርያም መዝሙር ቤት እንደ ቅዱስ ገብርኤል መዝሙር ቤት (የዘማሪት ፋንቱ ወልዴ) ዓይነት መዝሙር ቤቶች የመጡት:: 

የኅብረት ዝማሬ የተጀመረው በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ሰርክ ጉባኤ ላይ ወጣቶች የምስጋና ልብስ ለብሰው በኅብረት ዝማሬ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ እሱንም ለማዳመጥ እኔም እሔድ ነበር፡፡ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ትምህርት ቤት ማኅበረ ክርስቶስ ከቅዳሴ በኋላ ጉባኤ ያደርግ ነበር፡፡ እዚያም አኮርድዮን ነበረ፡፡ የኳየር መዝሙር ይዘመር ነበር፡፡ ጳጳሳትም ይገኙ ነበር፡፡ በቅድስት ሥላሴ ዘማርያን በሃይማኖተ አበው ፣ በኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት በሚያደርገው ጉባኤ ላይ ይዘምሩ ነበር፡፡

መምህር ተስፉ ግርማ :- ልክ ነው:: መጀመሪያ እነ ኪነ ጥበብ እነ መሪጌታ ፀሐይ በፒያኖ ሲዘምሩ መዝሙሩ ጎልቶ ይሰማል እንጂ መሣሪያውን ከነመኖሩ ራሱ አትሰማውም ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ዘመናዊውን መሣሪያ ከባሕላዊ መሣሪያዎች ጋር በማጣመር ወደ መዘመር ተሔዶም ነበረ፡፡ ይህም ትውልዱን በዘመናዊ መሣሪያ ተስቦ እንዳይወሰድ ለመመለስ በሚል ነበረ፡፡ 

በኋላ ላይ ግን ነገሩ እጅግ ፈር እየለቀቀ መጣ፡፡ 

አንደኛ መካነ ኢየሱስ የሚዘመሩ የፕሮቴስታንት መዝሙሮች መሳሪያውን ተገን በማድረግ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውስጥ መዘመር ተጀመሩ፡፡ ሁለተኛ የሙዚቃው መሣሪያ ከዘማሪው በላይ ገንኖ መሰማት ጀመረ፡፡ ሰውም ቃሉን ብሎ ዝማሬውን ከማዳመጥ ይልቅ መሣሪያውን ወደማጣጣምና ወደ መደሰት እየተሸጋገረ መጣ፡፡ ደስታና ተመስጦ ደግሞ ይለያያል፡፡ መዝሙር መመሰጥ ነው ያለበት እንጂ ሥጋዊን ደስታ መፍጠር ዓላማው አይደለም፡፡ ሦስተኛ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በሌላ እምነት ተከታዮች መወረር ጀመሩ፡፡

እንግዲህ እኔ ተወልጄ ያደግሁት እዚያው ቅድስት ሥላሴ ፊት ለፊት ነው፡፡ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ የሠፈራችን ሰዎችን በደንብ እናውቃቸዋለን፡፡ የት ነው የምናገኛቸው? ቅድስት ሥላሴ አዳራሽ ውስጥ! ከራሳቸው አንደበት የምንሰማው ፉከራ ‘ቅድስት ሥላሴ እኮ የእኛ ቅርንጫፍ ነው’ የሚል ቃል ነበር፡፡ ምክንያቱም መዝሙሩም አገልግሎቱም ያው እየሆነ ነበር፡፡ 

ሳሪስ አካባቢ እንዲሁም በክፍለ ሀገራት በተለይ በምሥራቅ ኢትዮጵያ እስከ ገለምሶ ድረስ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በዚህ መሣሪያ መገልገል ጀምረው ነበር፡፡ ይህም የመሣሪያ አጠቃቀም መመሳሰል የሃይማኖቱን አጥር እያፈረሰውና የእኛ ናቸው ወደማለት መመጣት ተጀመረ፡፡ ስለዚህ ፈር ለቀቀ፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋን አስወረራት፡፡ የሚገርመው ቤተ ክርስቲያንዋ ለሕዝባዊ መዝሙር በፈቀደቻቸው በዋሽንትና መሰንቆ የሚዘመሩትንም መዝሙራት ወደ ሙዚቃ መሣሪያ እየቀየሩ መዘመር ተጀመረ፡፡ ለምሳሌ የዘማሪ ምንዳዬን መዝሙር ውጪ ያሉ ሰዎች በሙዚቃ መሣሪያ አሳትመው መሸጥ ጀምረው ነበር፡፡  

መምህር ተስፉ ግርማ :- ልመጣልህ ነው:: እንዲያውም ከቅድስት ሥላሴው የሚብሰው ሁኔታ በማኅደረ ስብሐት ልደታ ሰንበት ትምህርት ቤት  የነበረው እንቅስቃሴ ነበር፡፡ እንዲያውም ቅዱስ ሲኖዶስ በ1986 ዓ.ም. ዝማሬ ላይ ደንብ እንዲያወጣ ያስገደደው ልደታ የወጣው ዝማሬ ነበር፡፡ ጭራሽ ከአኮርድዮን አልፎ ድራምና ኦርጋን ሳይቀር ያለበት ደንበኛ ሙዚቃ የሆነ ‘መዝሙር’ አወጡ፡፡ ያን ጊዜ ነው ቅዱስ ሲኖዶስ እንደዚህ ዓይነቱ አካሔድ ወጣቱን ለማዳን በሚል ተጀምሮ የበለጠ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊያጠፋ ስለሚችል ‘ከእንግዲህ ወዲህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በምን መሣሪያ ይዘምሩ? መዝሙሩስ ምን መምሰል አለበት?’ የሚለውን የደነገገው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ በዚህ አኩርፈው ከነ ዕቃቸው የወጡ ብዙዎች ነበሩ፡፡

መምህር ተስፉ ግርማ :- መዝሙር የጸሎት አንዱ ክፍል ነው፡፡ ጸሎት ደግሞ ተመስጦ ያስፈልገዋል፡፡ ቢቻል ቢቻል መዝሙሮች ሁሉ ሌላ መሣሪያ ሳያጅባቸው ቢዘመሩ የተሻለ ነው፡፡ ለምሳሌ ከጸሎት ሁሉ ትልቁ ጸሎት ቅዳሴ ነው፡፡ ቅዳሴ የሚከናወነው ያለ መሣሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ ማሕሌቱ በከበሮና ጸናጽል ይታጀባል፡፡ ከበሮና ጸናጽል ግን ብቻውን ዜማ አይሠጥም፡፡ የኅብረት ዝማሬውን እኩል ለመዘመር እንዲችሉ የሚረዳ ነው እንጂ ከበሮ ብቻውን ብትመታው ፣ ጸናጽሉን ዝም ብለህ ብትመታው የሚሠጠው ዜማ የለውም፡፡ የሚፈለገው ሰዎቹ በቃላቸው ምስጋናውን እንዲያቀርቡ ነው፡፡ የመሣሪያ ጥላቻ ሳይሆን የጸሎትን ተመስጦን እንዳይረብሽ ነው፡፡ መሳሪያ ሥጋዊ ደስታን ይሠጣል እንጂ ተመስጦ ውስጥ ስለማያስገባ አባቶቻችን ከልክለዋል፡፡ 

በሐዲስ ኪዳን ጌታ በምሴተ ሐሙስ የመጀመሪያውን ቍርባን ሲያደርግ ‘መዝሙር ዘመሩ’ ይላል፡፡ የዘመሩት ግን ያለ ምንም መሣሪያ ነው፡፡ ጳውሎስና ሲላስንም በዜማ መሣሪያ ያጀባቸው ሰው የለም፡፡ 

ባሕላዊ የምንላቸው መሣሪያዎች ባሕላዊ ይባሉ እንጂ መሠረታቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ በገናን ፣ መሰንቆን ፣ እንቢልታን ተጠቅሰው እናገኛቸዋለንና ተፈቅደዋል፡፡ እነርሱም ቢሆኑ ለቤተ መቅደስ ውስጥ አገልግሎት አይውሉም፡፡ ምክንያቱም ራሳቸውን የቻለ የዝማሬ ድምፅ ስለሚያወጡና ሰውዬውን ወክለው ስለሚዘምሩ ሰውዬው ከማመስገን ውጪ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ መሰንቆ ለብቻው አንድን ዜማ ማዜም ይችላል፡፡ ድምፁንም ትሰማዋለህ፡፡ እንደ ከበሮና ጸናጽሉ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ከፍላ ወስናለች፡፡ ሕዝባውያን ባልደመቀ ሁኔታ መንፈሳዊነትን ፣ ተመስጦን በማያስረሳ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተጠቀሱት መሣሪያዎች ይገልገሉ፡፡ ካህናቱና የውስጥ አገልግሎት ግን በራሳቸው ዜማ በሌላቸው ዕቃዎች ብቻ ይገልገሉ፡፡ ይህም ዕቃው በራሱ ቅዱስ ወይም የረከሰ ስለሆነ ሳይሆን መንፈስን የማይረብሽ ወደቃሉ የሚመራ እንዲሆን ነው፡፡

መምህር ተስፉ ግርማ :- ይህንን ጊዜ ሰዉ ወደ ሁለት ጎራ መከፈል ጀመረ፡፡ የአባቶችን ውሳኔ የሚያከብሩ ማኅበራትም ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች መብዛት ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ ማኅበረ ቅዱሳን ‘ለጌታዬ ለእግዚአብሔር’ የሚለው ቁጥር አንድን መዝሙር አወጣ፡፡ ማኅበረ ሥላሴ ደናግላን ‘ለማርያም’ የሚለውን ዝማሬ አወጣ፡፡ በባሕላዊ ደግሞ ማኅበረ ፊልጶስ ‘ገና ደስታችን’ ‘ቡሄ በሉ’ የሚሉትን አወጡ፡፡ ይህም የነበረውን ፈተናና ማሸነፍና የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ማስከበር ቻለ፡፡

  በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ግን የሙዚቃ መሣሪያውን የሚደግፉ ሰዎች በቤተ ክህነትም በቤተ መንግሥትም ትልቅ ተቀባይነት የነበራቸው ሰዎች ስለነበሩ በቀላሉ ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም፡፡ ይህንን ችግር ለመዋጋት የአጥቢያው ወጣቶች ማኅበረ በዓለ ወልድ (ፈለገ ሠለስቱ ምዕት እግዝእትነ ማርያም ማኅበር) የሚል ማኅበር አቋቋምን፡፡ በዚያን ጊዜ አፈር ላይ ቁጭ ብለን ጉባኤያቸውን ስንታደም የነበርን ሕፃናት ስንሆን የጉዳዩ አቀንቃኞች ደግሞ በዕድሜም በደረጃም ትልቅ ነበሩ፡፡ ብንናገር የሚያዳምጠንም የለም፡፡ 

የተጠቀምነው ሥልት መረጃ ለመውሰድ ውስጣቸው መግባት እና እነሱን መስሎ መረጃ መያዝ ነበር፡፡ በጎን ደግሞ ማኅበራችንን አጠናከርን ፣ የሌላ እምነት የሆኑ ሰዎችንና እዚህም እዚያም ወጣ ገባ የሚሉ ልጆችን ዝርዝር የድምፅ ፣ የፎቶ መረጃ መሰብሰብ ጀመርን፡፡ ከዐምደ ሃይማኖት ፣ ከጊቢ ገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋርም በስውር መቀናጀት ጀመርን፡፡ 

  ይህንን ዝርዝር መረጃ ለካቴድራሉ አስተዳደር ስናቀርብም በዕድሜ ሕፃን ስለሆንን የሚያምነን አልነበረም፡፡ ከፖለቲካ ጋር ያገናኙብን ነበር፡፡ ያለን ብቸኛው ምርጫ ኦርቶዶክሳዊ የሆነ መንፈሳዊ መዝሙር መሥራት ነበረ፡፡ 

በ1987 ዓ.ም. ‘ትሕትናሽ ግሩም ነው’ የተሰኘውን የማኅበር መዝሙር ሠራን፡፡ ገቢውን ለነዳያን የዋለ የካሴት ሽያጭ አደረግን፡፡ መጽሔት አሳተምን፡፡  

ከብዙ ድካም በኋላ ግን የደብሩን አስተዳዳሪ ማሳመን ችለን ሰንበት ትምህርት ቤቱ እንደ አዲስ ተቋቋመ፡፡ የማኅበረ በዓለ ወልድም ልጆች በዚህ አገልግሎት ላይ ተካተቱ፡፡ ይህ ድል መገኘቱ በምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ የነበረውን ተመሳሳይ እንቅስቃሴም እንዲገታ አድርጎታል፡፡

መምህር ተስፉ ግርማ :- በዚያን ጊዜ በአራት ኪሎ ዙሪያ ከነበሩ ወጣቶች ጋር ማኅበረ በዓለ ወልድን ካቋቋምን በኋላ ማክሰኞ ሐሙስና ቅዳሜ እየተሰበሰብን መማር ጀመርን፡፡ ከዚያ ውጪም ኮከበ ጽባሕና ምኒልክ ትምህርት ቤት ስማር በዕረፍት ሰዓት እሰብክ ነበረ፡፡

ያንን ተማሪም ቀስ በቀስ ወደ ማኅበረ በዓለ ወልድ አመጣሁት፡፡ በወቅቱ የሠርክ ጉባኤ ስላልነበረ ቅድስት ማርያም እየሔድሁ ከጳጳሳት እማር ነበር፡፡ በአታ እየሔድሁም ከቀለም ቀንዱ ከአቡነ ኤልያስ ዘንድም እንዲሁ እማር ነበር፡፡ የሰርክ ጉባኤ መድመቅ የጀመረው በቅድስት ማርያም ባሕታዊ አባ አምኃ ኢየሱስ ማስተማር ከጀመሩ በኋላ ነበር፡፡ ይህን ጊዜ ምንም ጉባኤ ባልነበረበት ጊዜ በማኅበራችን አስተባባሪነት በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያንም በሃያ ዘጠኝ እና በስምንት በአርባዕቱ እንስሳ በዓል ቀን ጉባኤ ማድረግ ጀመርን፡፡ ይህንን እንዳናደርግ እጅግ ብዙ ፈተናዎችን ከኦርጋን አቀንቃኞች ጋር ብዙ ፈተና ደርሶብን ነበር፡፡ የፖለቲካ አባል ናቸው እስከመባል ሁሉ ደርሰን ነበር፡፡ 

መምህር ተስፉ ግርማ :- መዝሙር ስንሠራ የተነሣነው የሙዚቃው መሣሪያን ተጽዕኖ መቃወምን አስበን እና  እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ባሕታዊ ሞተው ስለነበር በኀዘን ስሜት ሆነን ነበር የዘመርነው፡፡ ተስፋዬ ኢዶ ፣ ምንዳዬ ብርሃኑን የመሳሰሉ ዘማርያን ጋር ሁለት ትዕግሥቶች ፣ ስንታየሁ የሚባሉ አጃቢዎች ጋር በፍርሃት ውስጥ ሆነን ነበር፡፡  

መሐሙድ ስቱድዮ በሚባል የቀረጻ ቦታ ላይ ነበር፡፡ የመዝሙር ሥራ እንደ አሁን አልነበረም አንዱ ከተሳሳተ ሙሉው ድጋሚ መቀረጽ ነበረበት፡፡ ሆኖም በፍርሃትና በፍቅር ስለነበር ተሳክቶ ነበር፡፡ ሁሉም አዋቂ ነኝ ሳይል አላዋቂ ነኝ በሚል ስሜት ውስጥ ነበረ፡፡ ጸልየን እናደርገው ነበር፡፡ በመሣሪያ ያጀቡት ፈለቀች ፣ ስንታየሁ የሚባሉ ሴቶች እንዲሁም ዮሴፍ ገዳሙ የሚባል ባለ መሰንቆ ፣ አካሉ ዮሴፍ በከበሮ ተሳትፈው ነበር፡፡ ‘ትሕትናሽ ግሩም ነው’ ‘የምሥራች እንበል’ ‘ዝማሬ ዳዊትን’ ወዘተ የሚሉ መዝሙራት ነበሩ፡፡

መዝሙሩን ስንሠራ ‘ዘማሪ እገሌ’ የሚል ነገር ሳይሆን የማኅበር ነበረ ፣ መዝሙር ጥናት ላይ አንድ ሰው አርፍዶ እንኳን አይመጣም ነበር ፣ በጥናት ጊዜ በፍርሃት እንጂ በሳቅ ስላቅ ውስጥ ሆነው አያገለግሉም፡፡ ሁሉም ለመማር እንጂ አዋቂ ነኝ ብሎ የሚመጣ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ ሁሉም ሰው ወደ አገልግሎት ሲመጣ በፍርሃት ነበር፡፡ እንደ ዛሬ ቤተ መቅደሱን ቢሮ አላደረግነውም ነበር፡፡ መሰልቸት እንኳን የለም ዝማሬው እስኪያምር ድረስ ይደከምበት ነበር፡፡ 

መዝሙር ሲጠና የተቀረጸውን ብትሰማው የስቱድዮ ይመስላል፡፡ መቼ መዝሙሩን ጨርሰን ታትሞ ነዳያን በተመገቡ የሚል ብቻ ፍላጎት የነበረበት ነው፡፡ ካሴቱ ላይ እንኳን ፎቶግራፍ አልነበረም፡፡ ፎቶግራፍ በአንድ በኩል ጥሩነት አለው ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎችን ወደ ሥጋዊ ነገር ወደ እውቅና ፣ ከእግዚአብሔር የመቅደም ፣ ከአገልግሎት የመቅደምንም ነገር አምጥቶአል፡፡ ያንጊዜ ግጥምና ዜማ ሠጥተን እንኳን ስማችንን እንኳን አናጽፍም ነበር፡፡ ጥሩ ነው በማለት ወይም መጥፎ ነው በማለት አይደለም የምመዝነው፡፡   

ይቀጥላል …

Share your love

5 አስተያየቶች

  1. በጣም አስተማሪ ቃለመጠይቅ ነው::ቀጣዩን በጉጉት አንጠብቃለን:: ነፍሳቸዉን በ አፀደ ገነት ያኑርልን

  2. እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ደስ ይላል እኔ በጣም ከበፊትም ጀምሮ ማውቅ የምፈልጋቸው ነገሮች ተመልሰውልኛል ( ማን ይንገር የነበረ ማን ያረዳ የቀበረ ) ነውና አምላከ ቅዱሳን ነፍስ ይማርልን ለናንተም እድሜ ይስጥልኝ

  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን ብዙ ማወቅ የምፈልገወረን በዚህ ቃለ መጠይቅ ተረድቻለሁ ነብሱን በአፀደ ገነት ያሳርልን ጃንያሬድን እናመሰግናለን የአገልግሎት ዘመን ያርዝምልን

  4. አስተማሪ ቃለ መጠይቅ ነው።እኛ ጋር እንዲደርስ ላያደረጋችሁት ሁሉ እግዚአብሔር ይስጥልን።

    ነብሳቸውን በአፀደ ገነት ያሳርፍልን!

  5. እግዚአብሔር ይስልጥልን። ቀድማችሁ ደርሳችሁ እንዲህ ብዙ እንዲያስተምሩን ስላደረጋችሁ እናመሰግናለን።
    ነፍሳቸውን ከቅዱሳን ጋር ይደምርልን።
    እንዲህ ቃላቸውን ልንሰማ የሚገቡ ብዙዎች አሉና በርቱልን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *