ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ላይ ከተጠራ በኋላ በአገልግሎቱ የተመረጠ ዕቃ በመሆን ሲያሳድድዳቸው ለነበሩት የክርስቶስ በጎች ሊሰጥ የሚችል የተመረጠ ፤ ጌታውን የሚመስል ኖላዊ(እረኛ) ሆኖ ስሙን ተሸክሟል፡፡ (ሐዋ. 9:3) ከማሳደድ ወደ መጠበቅ ሲሸጋግር ለተሠጡት በጎች መጸለይን አልተወም፡፡ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ “ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም” ይላቸዋል፡፡ ለመሆኑ ሐዋርያው የሚጸልየው ምንድነው ? ምንስ ብሎ ስለ በጎቹ ያሳስብ ይሆን ?
ራሱ ይመልሳል :-
“የክብር አባት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብን የመገለጥን መንፈስ እንዲሠጣችሁ እለምናለሁ:: ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንደሆነ በቅዱሳንም ዘንድ ያለውን የርስት ክብር ባለጠግነትም ምን እንደሚሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉን ታላቅነት ምን እንደሆነ ታውቁ ዘንድ ነው” (ኤፌ 1: 16-18)
የመጀመሪያው በጸሎቱ የሚያሳስበው ጉዳይ ክርስቲያኖች በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ የተሰጠውን ጥበብ እንዲያውቁ ነው፡፡ ይህ ጥበብ የእግዚአብሔርን አንድነቱን ሦስትነቱን ማወቅ ነው፡፡ጌታ የሠጠን ቃል እኛን ከቅድስት ሥላሴን ኅብረት የሚያሳትፈን ሲሆን ለቅድስት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረቷ ነው፡፡ (ዩሐ 17:14) ይህ ጥበብ “የተሰወረውን የእግዚአብሔርን ምሥጢር መናገር” ሲሆን ክምችት ያላቸውን ጽንሰ ሀሳቦች ማመላለስ ብቻ አይደለም:: (1ኛ ቆሮ 2:7)
ስለ እግዚአብሔር የምንሰማው በሙሉ ስለ ራሳችን እና ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነት የምንሰማው ነው፡፡ ነገረ ድኅነት ማለት አንድ ክፍለ ትምህርት ሳይሆን ከአጠቃላይ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ የሚገኘው ሕይወት ነው፡፡ የመንፈሳዊ ዕውቀቱም ግብ አማኙ እግዚአብሔርን እንዲያውቅ ማድረግ ነው፡፡ የምናምንበት እንቀጸ ሃይማኖት የክርስቲያናዊ ሕይወታችን ምንጭ ነው፡፡ ማወቅ እና መኖር አንድ ናቸውና ሐዋርያው እየጸለየላቸው ያለው ስለ ዕውቀት ክምችታቸው እንዳይደለ እንገነዘባለን፡፡ አባቶቻችንም በትምህርቶቻቸው ኖላዊያዊ እና ድኅነታዊ መሠረቱን ያልለቀቀ ደረቅ ምሁራዊነት የሌለበት ትምህርት በመሥጠት እውነተኛውን አምላክ በማምለክና በማወቅ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ አድርገውናል፡፡
ሁለተኛው ጸሎቱ የሚያሳስበው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ኖላዊያዊና ድኅነታዊ መሠረቱ በሐዋርያት ምስክርነት ላይ ስለሆነ ሐዋርያት አይተው ሰምተው ቀምሰው ባወቁት ኢየሱስ ክርስቶስ እኛም ተመሳሳይ ዕውቀት እንድንይዝ በጥሪያችን ተስፋ እንድንኖር ነው፡፡
ወደ ጌታ ደረት የተጠጋው ሐዋርያ
“ስለ ሕይወት ቃል ከመጀሪያው የነበረውን የሰማነውን በዓይናችን ያየነውን የተመለከትነውን በእጃችን የዳሰስነውን እናወራለን (1ዮሐ 1:1) ይለናል፡፡ የልባችን ዓይን ብሩህ ሲሆን ወደ ሃይማኖት የመጠራታችን ተስፋ እናውቃለን፡፡ ተስፋችን በቅዱሳን ሕይወት የተመለከትነው በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠውን የማዳኑን ኃይል ነው በእኛም መግለጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ክብር መግለጥ የትምህርታችንም የህይወታችን ምግብ ነው፡፡
በዚህ ሕይወት ውስጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን መክፈት ማንበብ ማጥናት መነጋገር መመራመር መወያየት ትልቅ ድርሻ አላቸው:: (ሉቃ 24: 15) መንፈሳዊ ዕውቀት የምናገኘው ቅዱሳት መጻሕፍትን በመክፈት ነው፡፡ የቅዱስ ፊልጶስ መጽሐፍን መሠረት ያደረገ ምስክርነት ኢትዮጵያዊው ጃንደረባን ወደ ሕይወት መርቶታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከመጻሕፍት እንዳመለከቱት እርሱ የተቀበለውን ሠጥቷልና ወደ እዚህ እውቀት እንዲደርሱ በተመሳሳይ ሁኔታ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ያስተምራል፡፡( 1ኛ ቆሮ 15) ጌታ የኤማሁስ መንገደኞችን ወደ እውነተኛው ማየት እና ማወቅ ያደረሳቸው ሲወያዩና ሲመራመሩ በመካከላቸው እንደ እንግዳ ሆኖ ተገኝቶ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመተርጎሙ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሠጠን ለባዊነትም አያስፈልግም ተብሎ የሚጣል ሳይሆን ማወቅ እስከሚችለው ድረስ በቅዱሳት መጽሐፍት የተገለጠውን እውነት ለማስተዋል የምንጠቀምበት ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ደረቅ እና ሕይወት አልባ አለመሆኑን እንዲሁም ቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር ስለ እግዚአብሔር እንደምንናገር ከጸሎትና ከአምልኮት በመነሳት መምህራን ያስተምሩናል፡፡ ስለ እግዚአብሔር መናገር የሚጀምረው በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት በመቆም ነው፡፡
በእግዚአብሔር ሕልውና ያመነ ፤ በፊቱ የሚቆምና አምልኮትን የሚፈጽም እግዚአብሔርን ማወቅ ጀምሯል፡፡ ቀርቦም በማነጋገር አማኝነቱን በመግለጽ ከአምላኩ ፊት በፍርድ ቆሞ ፍጹም ኃያል እና ንጹሕ ለሆነ አምላክ ራሱን በትሕትና ያቀርባል፡፡ ራሱ ላይ የፈረደን እግዚአብሔር በምሕረቱ ይቀበለዋል፡፡ ማር ይስሐቅ “አእምሯችን በጨለማ ከተዋጠ ነፍሳችን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አትችልምና የመጀመሪያ ፈተናዋን ለጸሎት ከመቆም ጋር ትግል ማድረግ ነው” ይለናል፡፡ ይህንን ትግል አልፎ ንጹሕ ሀሳብን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ግን የተረጋጋ ሕይወትን ከአምላኩ ጋር ይመሰርታል፡፡ እግዚአብሔርን ማወቅ ከአምልኮት ይጀምራል ማለት እግዚአብሔር እየተመራመርን የምንተነትነው ቁስ ወይም የምንመዝነው ሀሳብ ሳይሆን አብረን በመኖር የምናውቀው ሕይወት ስለሆነ ነው፡፡ (Mystical treaties St Issac of Nineveh pp 22
በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማለት የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ፣ በተቀደሰ ዜማና ሁልጊዜ አዲስ በሆነ የቃል ምስጋና ፣ሰማየ ሰማያት በሚደርስ የዕጣን መሥዋዕት ፣ በቅዱሳት ሥዕላት ተከብበን በክርስቲያኖች መካከል ቆመን በአንድነታችን ውስጥ የምንኖረው ሕይወት ነው፡፡ በኅብረት አምልኮታችን ውስጥ እውነተኛ መንፈሳዊ ዕድገትን እንጀምራለን፡፡ ግላዊው አእምሮአችን በዚህ ኅብረት ተዋሕዶ የተዋጠ ይሆናል፡፡
በዚህ ቅዱስ ኅብረት መካከል የሚመጣ ማንኛውም ችግርም ህክምና የሚያገኘው ከኅብረቱ በሆነው የቅድስት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ነው፡፡ ስለዚህ ከኅብረቱ በአፍአ ያለ ፈራጅ ሳይሆን አማኞች በየዕለቱ እንዴት ክርስትናን ሊኖሩት እንደሚችሉ የሚያስረዳ፤ የሚረዳ አልፎም ችግርን የሚፈታ ህይወት የሆነ ህክምና ይሆናል ፡፡ ለዚህም ነው በመንፈሳዊው ዓለም ያለን ልምምድ ኅብረታዊ ስለሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን እንዲሆን ሁለትም ሦስትም መሆን የተጠበቀብን:: (ማቴ 18:20)
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋ የሚቀዳው ከዚህ ነው፡፡ ወደ ባልንጀራዬ የማደርገው ተልዕኮ በተሰጠኝ ጸጋ በኅብረቷ ውስጥ ባለኝ ሱታፌ የድርሻዬን እንድሠራ ነው፡፡ የወንድሜ ሕመም (ኃጢአት) የእኔም ጉዳት ነው፡፡በመካከላችን ያለ ማንኛውም ውድቀት (crisis) በኅብረቱ ውስጥ ያለ በመሆኑ የጋራ ነው፡፡ ራሴን ነጻ የማደርገው የኅብረታዊው ህልውና አካል የለም፡፡
የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ደረቅና ምሁራዊ ብቻ እንዳይሆን በተልዕኮ ኖላዊያዊ ሆኖ ለሁሉም እውነተኛ የድኅነት ዕውቀትን የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ ይህ የምስክርነት አገልግሎት ውስብስብ ለሆነው ማህበረሰባዊ ስሪቶች ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮቻችን የሚሰጥ ትክክለኛው መድኅኒት እና ህክምና ነው፡፡
እውነተኛ አስተምህሮ ላይ የሚኖረን ታማኝነት ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያልተቀዱ ትምህርቶችንና አካሄዶችን በኅብረቷ ቢገኝ ድል እንደሚያደርግና እንደሚያክም በማመን የምንሰጠው መድኃኒት ነው፡፡ ባለንበት ዘመን ለሁሉም ነገር ተቀያሪ አካሄድ መኖሩ የተጋረጠብን ችግር ቢሆንም እውነተኛ የሥነ መለኮት ሕይወት “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ” እስኪሆን በተልዕኮ የምንተጋ መሆን አለብን፡፡( 2ኛ ቆሮ 4:6)
እግዚአብሔር በጸጋ በየዘመኑ ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት የሚያስፈልጋትን ኖረው የሚጽፉ ቅዱሳን አስነሥቷል፡፡ አሁንም አብሮን የሚሠራ አምላክ ክርስቲያኖች የሚኖሩበትን ሕይወት እየተረጎምን የቅድስት ቤተክርስቲያንን ትውፊት እንድናስተምራቸው ራሳችን የሚሳተፍበትን ህይወት በተግባር እንድናውቀው አብሮን ይሰራል፡፡ ታዲያ ይህን መንፈሳዊ ተልዕኮ እንድናሳካ ” የእውነትን ቃል በቅንነት የምንናገር የማያሳፍር ሰራተኛ ሆነን የተፈተነውን ራሳችንን ለእግዚአብሔር ልናቀርብ ልንተጋ ይገባል”፡፡ ( 2ኛ ጢሞ 2:15)
በዚች ዓለም ላይ ባለን ህይወት ክርስቲያኖች የምንኖርበትን ዘመን መዝነን አክመን ተልዕኳችንን ስንፈጽም እኛ ልንኖረው ከሚገባው ተግባራዊ ሕይወት በመቀጠል በዘመኑ ያለውን ችግር በሚገባ የተረዳን መሆን አለብን፡፡ ይህ ከሌለ እንደ ተልዕኮ መግባባትም ስለማንችል የደረስንበት ግላዊ መረዳት መፍትሔ አቅራቢ ሆነን ከአንድ ህብረት የወጣን ግን ብዙ መፍትሔ አቅራቢዮች መሆንን ያመጣል፡፡ ስለዚህ ወደ ማንኛውም ድምዳሜ ከመድረሳችን በፊት ራሳችንን ወደ ኅብረቱ አእምሯችንን የሚመልሰው ጥያቄዎችን ልንጠይቅ ይገባል፡፡
” የሀሳብ አጥሮቼን ተላልፌ ይሆን? ለሐዋርያዊው ትውፊት ታማኝ ነኝ? ከያዝኩት ሀሳቤ ጋር የቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርት ይስማማል? ከዚህ በፊት ከነበረው የአባቶች አእምሮ ጋር አብሮ ይሄዳል? በዚህ ሀሳብ ከቤተ ክርስቲያን የተለየ አቋም መያዝ ያስፈልገኛል? ልጸልይበት ይገባል? ለመንፈሳዊ አባቴ ይህን ሀሳብ ይዤ ልቅረብ? ሙሉ በሙሉ ስለዚህ ጉዳይ ማሰብ ማቆም አለብኝ?”(Thinking orthodox 109)
በባሕርይው ኖላዊያዊ የሆነ ትውፊት እና የአባቶች አስተምህሮ ያለን ጥሪ በትሕትና እና ጥልቅ በሆነ አስተውሎት የምንቀበለው ነው፡፡ ስለዚህ ዘወትር ወደ ውስጥ ልንመለከት ራሳችንን ልንመዝን እና አማናዊ ንስሐ ያስፈልገናል፡፡ ይህን ካደረግን በሌሎች ላይ ከመፍረድ እና ራሳችን በራሳችን ላይ ከምናስተላልፈው የፍርድ ቃል ይጠብቀናል፡፡ (ማቴ 7:2)
ደረቅ ምሁራዊነትን አስቀርተን ወደ ሕይወት ትምህርት የምናደርገው ጥልቅ ጉዞ የሐዋርያት ምስክርነት ድንጋጌ ፣ አባቶች አስተምረውበት በጸሎት ጀምረነው በአምልኮት ኖረነው ከሕይወት ስንቀምስ የምናገኘውን በተልዕኮ የምናውቀውን ተግባራዊውን ዕውቀት ይሰጠናል፡፡ ለዚች ዕውቀት ያድርሰን፡፡
እግዚአብሔር ይስጥልን መምህር የኔ ጥያቄ ኤፌ 1-16 ላይ የለው ሃይለ ቃል ነው።ይህም “የክብር አባት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ……ይህን ብታብራሩኝ።እግዚአብሔር ይስጥልን።አሜን
“ደረቅ ምሁራዊነትን አስቀርተን ወደ ሕይወት ትምህርት የምናደርገው ጥልቅ ጉዞ የሐዋርያት ምስክርነት ድንጋጌ ፣ አባቶች አስተምረውበት በጸሎት ጀምረነው በአምልኮት ኖረነው ከሕይወት ስንቀምስ የምናገኘውን በተልዕኮ የምናውቀውን ተግባራዊውን ዕውቀት ይሰጠናል፡፡ ለዚች ዕውቀት ያድርሰን፡፡” አሜን አሜን ለዚህ ያድርሰን 🙏