ዛሬ ሰምቼው በጣም የወደድኩትና ሁልጊዜ ከማሰላስለው ሀሳብ ጋር የሚሄድ አንድ ቁም ነገር ላካፍላችሁ መልካም መስሎ ታየኝ። ታሪኩ እንዲህ ነው።
አንድ የአራዊት ማቆያ ሥፍራን መጎብኘት የሚወድ ሰው የፈጣሪ ድንቅ ሥራ የሆኑ እንስሳትና አራዊትን እየተመለከተ ሲዘዋወር ትዕይንት (circus) ለማሳየት የሰለጠኑ እጅግ በጣም ግዙፍ የሆኑ ዝሆኖች በጣም በትንሽ ችካል ላይ በቀጫጭን ገመድ ታስረው ሳይንቀሳቀሱ ቆመው ያያል። እነዚህ በምድር ላይ ካሉ እንስሳት (አራዊት) እጅግ ግዙፍ የሆኑ ዝሆኖች አንድ በጣም ደካማ የሚባል ሰው እንኳ በቀላሉ ሊነቅላት በሚችል ትንሽ ችካል ላይ በተቋጠረች ቀጭን ገመድ ታሰረው አለመንቀሳቀሳቸው የሚገርም ነገር ነበር። ይህ ጎብኚ በዚህ ሁኔታ እየተደነቀ ሳለ እነዚያን ግዙፍ ፍጥረታት የሚንከባከበውን ሰው በቅጥሩ ውስጥ ስላየ ምሥጢሩን ጠይቆ ለመረዳት ወስኖ ቀረበ።
“ሰላም ለአንተ ይሁን ወንድሜ! በእንስሳት ማቆያው ውስጥ አራዊቱን እያየሁ ስዘዋወር እነዚህ በግዝፈታቸውም ሆነ በጉልበታቸው በምድር ላይ ከሚመላለሱ ፍጥረታት ተወዳዳሪ የሌላቸው ዝሆኖች በዚች ትንሽ ችካል ላይ በቀጭን ገመድ ታሰረው ተመለከትሁ። ዝሆኖቹ በቀላሉ ገመዱን በጥሰውና ችካሉን ነቅለው በነፃነት እንደ ፈለጉ መንቀሳቀስ ሲችሉ በተቃራኒው ከእነርሱ ጉልበት ጋር ፈፅሞ በማይነፃፀር ማሠሪያ ተሸብበው መቅረታቸው አስደንቆኛል፤ ምሥጢሩ ምን ይሆን?” ሲል ጠየቀ።
አራዊቱን የሚንከባከበው ሰውም “ወንድሜ ጥሩ አስተውለሃል! እውነትህን ነው እነዚህ ግዙፍ ዝሆኖች የታሠሩት እነርሱን በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ ሊያቆማቸው ጨርሶ አቅም በሌለው ችካልና ቀጭን ገመድ ነው። ችካሉን መንቀልም ሆነ ገመዱን መበጠስ ለእነርሱ በጣም ኢምንት ነገር ቢሆንም ግን ፈፅሞ አይሞክሩም። ምክንያቱም ገና በልጅነታቸው ልናሳድጋቸው ስናመጣቸው ወደ ፊት የሚኖራቸውን ኃይልና ጉልበት በምንም ልናቆመው እንደማንችል ስለምናውቅ አስቀድመን በጣም ጠንካራ በሆነ ችካል ላይ እጅግ ወፍራምና ጥብቅ በሆነ ገመድ እናስራቸዋለን። እነርሱም ለብዙ ጊዜያት ያን ገመድ ለመበጠስና ችካሉን ለመንቀል ብርቱ ትግል ያደርጋሉ፤ ግን ያቅታቸዋል። ስለዚህ ችካሉን መንቀልም ሆነ ገመዱን መበጠስ እንደማይችሉ አምነው ይቀበላሉ። አንድ ጊዜ ይህ “አልችልም” የሚል የተሸናፊነት መንፈስ በውስጣቸው ከሠረፀ በኋላ ምንም እንኳ ችካሉ ደካማና ገመዱም ቀጭን ቢሆንም ለመታገል አይሞክሩም፤ ተቀብለውት ይኖራሉ” በማለት ምሥጢሩን አብራራለት።
ይህን ታሪክ ሳነብ በአእምሮም በመንፈስም ጨቅላ በነበርንባቸው ዓመታት በአንድም በሌላም መንገድ የሰማናቸው፤ አሁን በአእምሮና በመንፈስ ጎልምሰን እንኳ ልንነቅላቸው ስንችል ያቆሙን ችካሎች፤ ልንበጥሳቸው አቅሙ እያለን ያሰሩን ገመዶች ታዩኝ። ከልማድ መውጣት፣ ከቀደመ ጠባያችን መፈታት፣ አዲስ ሕይወት መኖር ለመሞከር “አልችልም፤ ክርስትናን መኖር ከባድ ነው” በሚል የመንፈስ ዝለት ታሰርን።
ግን ለመሆኑ ሰው ኃጢአትን መኖር ከቻለ ጽድቅን መኖር ለምን ያቅተዋል? ክፉ መሆን ከቻለ መልካም ለመሆን ምን ይሳነዋል? መጥላት ካላቃተው ማፍቀር እንዴት ያቅተዋል? መቀየም ከቀለለው ይቅር ማለት ለምን ይከብደዋል? ከፍርድ ለመዳን የሚማፀን በሌላ መፍረድ እንዴት ይስማማዋል? ድንቁርና ያልጎፈነነው እውቀት እንዴት ያቅረዋል? በደካማ ምሪት ክፉ መሆን ከቻለ ሁሉን በሚችለው አምላክ ምሪትና እርዳታ የተሻለ መሆን የማይቻለው ለምንድር ነው? መልሱ ስለ ታሰርንና የታሰርንበት ማሰሪያ በእኛ ውስጥ ካለው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አንፃር ኢምንት መሆኑን አምነን ስላልተቀበልን ነው::
በነፃነት መንፈስ በጌታ እግዚአብሔር ፊት እንድን መላለስ በመጀመሪያ የሌለውን ምስል ስለንና ቅርፅ ሰጥተን በፊቱ አልችልም በሚል መንፈስ ከቆምንበት የቀደመ ሕይወት ልማድ፣ እውቀት፣ ወዘተ. . . ሁሉ መፈታት ይኖርብናል።
በሥልጣነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ እማዕሰረ ልማድ፣ እማዕሰረ ክፋት፣ እማዕሰረ ጥላቻ፣ እማዕሰረ ቅያሜ፣ እማዕሰረ ፍርድ፣ እማዕሰረ ድንቁርና፣ እማዕሰረ አለመቻል . . . እግዚአብሔር ይፍታ!!! አሜን!
“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ” ገላ 5፥1
ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::
https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL
ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::
አሜን
አሜን አሜን አሜን 🙏🏼
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን እግዚአብሔር ይስጥልን አባታችን
“በደካማ ምሪት ክፉ መሆን ከቻለ ሁሉን በሚችለው አምላክ ምሪትና እርዳታ የተሻለ መሆን የማይቻለው ለምንድር ነው? መልሱ ስለ ታሰርንና የታሰርንበት ማሰሪያ በእኛ ውስጥ ካለው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አንፃር ኢምንት መሆኑን አምነን ስላልተቀበልን ነው::”
ይፍቱኝ/ን
አሜን
አሜን ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
ይፍቱኝ!
አሜን🙏
የህይወትን ቃል የመላእክትን ዝማሬ ያሰማልን፤ጸጋውን ያብዛልዎ🙏
በሥልጣነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ እማዕሰረ ልማድ፣ እማዕሰረ ክፋት፣ እማዕሰረ ጥላቻ፣ እማዕሰረ ቅያሜ፣ እማዕሰረ ፍርድ፣ እማዕሰረ ድንቁርና፣ እማዕሰረ አለመቻል . . . እግዚአብሔር ይፍታ!!! አሜን!
አሜን አሜን አሜን አባታችን ይፍቱን! ቃለ ህይወት ያሰማልን የአገልግሎት ዘመን ያርዝምልን በእርሶ ቻናል በሚዳሰሱ ትምህርቶች እየተጠቀምንባቸው ነው ለዚህም እግዚአብሔር ይስጥልን እናመሰግናለን
Amenn
ቃለ ህይወት ያሳማልን እኛም ከታሰርንበት የሀጥያትና የእርኩሰት እስራት አምላከ ቅዱሳን ይፍታን
አሜን
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን እግዚአብሔር ይስጥልን