“ብፁዕ አቡነ ገብርኤል  ቅርባችን የነበረ ሥዕለ መድኃኔዓለምን እየጠቆሙ “ሂድና እዚያ ጋር ሦስቴ ስገድ” አሉኝ”

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ:- እናቴ በሕልም ስላየችው ነገር በነገረችኝ በዚያው ቅጽበት ደግሞ እኅቴ ወደ ቤት እናቴን እየተጣራች ገብታ በዛው ዕለት ያየችውን ሕልም ነገረቻት፥ “የሆነ ገጠር ቦታ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ተቀምጠን በሰፌድ የእንጀራ ፍትፍት ነገር እየበላን ሳለ አንድ አረጋዊ ካህን ከመካከላችን መዝገበን እጁን ይዘው ሲሂዱ አየሁ” ምን ማለት ነው? አለቻት። እናቴም ይሄ የእግዚአብሔር መልዕክት ነው መሄድ ትችላለህ ብላ ፈቀደችልኝ። እኔም የዛው ዕለት ታኅሣሥ 3 ቀን 1987 ዓ/ም ሳልውል ሳላድር ተነስቼ ወደ መናገሻ አምባ ማርያም ገዳም አቀናሁ። ይገርምሻል አባቴም ያረፈው 2012 ዓ/ም የታኅሣሥ በዓታ ዕለት ነው።

አስቀድሜ ሻንጣዬን አዘጋጅቼ መጽሐፌን ሸክፌ ስለነበር ከአንድ የጽዋ ማኅበርተኛ ወንድሜ (ዮሴፍ እርገጤ ይባላል) ጋር ተነሥተን ወደ መናገሻ ሄድን። እንደነገርኩሽ በክረምት ወቅት የመጣን ጊዜ የኔታ ማረፊያ የለም ብለውናል። የምናርፍበት እንኳን ሳይኖር በቃ እመቤታችንን ተስፋ አድርገን ነበር የተነሣነው። በተሳፈርንበት መኪና ውስጥ ግን እንደ አጋጣሚ የገዳሙ አበምኔት የአባ ሐረገወይን የወንድም ልጅ ወደ ገዳም ለመሄድ ከእኛ ጋር ተሳፍራ ነበር። እየተጫወትን ከሄድን በኋላ ከተማው ጋር ደርሰን ስንወርድና ወደ ገዳሙ ስናቀና ዓይታ ማን ጋር እንደምሄድ ጠየቀችን። እኛም እመቤታችን ጋር ብለን መለስንላት። “እሱማ እውነት ነው” አለችና “ግን ማን ጋር ነው የምታርፉት ማለቴ ነው” አለችን። እኛም የምናርፍበት እገሌ የምንለው ሰው ስለሌለን “እመቤታችን ጋር ነው የምንሄደው” አልናት።

በሉ ከአባታችን (ከአበምኔቱ) ጋር አገናኛችኋለሁ ብላ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ከተሳለምንና ጸሎት ካደረግን በኋላ አባ ሐረገወይን ጋር ወስዳ አገናኘችን። እርሳቸውም ማንነታችንን፣ ከየት እንደመጣን፣ ለምን እንደመጣን፣ ሃይማኖታችንን በደንብ ጠይቀው ከተረዱ በኋላ እዛው ገዳሙ ውስጥ እንድቀመጥ ለጊዜው የገዳሙ መጋቢ አባ አድነው የሚባሉ አባት ቤት እንድቀመጥ፣ በየዕለቱ እደገዳሙ አባላት ድርጎ (ዳቤና ንፍሮ) እንዲሰጠኝ አዝዘው ገዳሙ ውስጥ እንድቀመጥና እንድማር ተፈቀደልኝ። ከአዲስ አበባ ወጥቼ፣ ዘመናዊ ትምህርትን ትቼ፣ 12ኛ ክፍል ከጨረስኩ በኋላ እራሴን እመቤታችን ገዳም ቆሎ ትምህርት ቤት ውስጥ አገኘሁት፤ የአባቶቼን ሃይማኖት ለመማር አዲስ መንገድ፣ አዲስ ጉዞ ጀመርኩ።

መናገሻ አምባ ማርያም ገዳም የቆየሁት ሁለት ዓመት ነው። ትምህርቴን የግእዝ መጻሕፍትን ከማንበብ ነው የጀመርኩት፣ ዳዊት መድገም፣ የቃል ትምህርቶችን (ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብፁዓን፣ መልክአ ማርያም፣ መልክአ ኢየሱስ)፣ የቅዳሴ ትምህርትንና ገዳማዊ ሕይወትን ተምሪአለሁ። የሁለት ዓመት ቆይታዬ ለእኔ ገነት ውስጥ እንደነበርሁ ነበር የተሰማኝ። ከአብነት ትምህርት ባሽገር መነኮሳትን እየረዳን ገዳማዊ በሆነ ኑሮ ነበር የቆየነው። እናድርባት የነበረችው ጎጆም የኔታ ቤት ግቢ ውስጥ ስለነበረች የኔታ ነጻ በሚሆኑባቸው ጊዜያት ሁሉ አጠገባቸው ጠጋ እያልን እንማር ነበር። ጎጆዋ ቤት ውስጥ ይኖር የነበረው ነፍሱን ይማረውና አንድ ዲያቆን ዓቢይ የሚባል ወንድማችን ነበር። ዘመናዊ ትምህርት ጨርሰን ከከተማ የመጣን ተማሪዎች መሆናችንን ሰምቶ አብረን እንኑር እኔ የአብነት ትምህርቱን አስጣናችኋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ዘመናዊ ትምህርት ታስጠኑኛላችሁ ብሎን ተስማምተን አብረን መኖር ጀመርን። የጨጓራ ሕመምተኛ ስለነበር ወደ ካንሰር ተቀይሮበት አረፈ። እኔና ጓደኛዬ ዮሐንስ እዛው ጎጆ ቤት መኖር ጀመርን። ምግባችንን እራሳችን እያበሰልን፣ ቀን እየተማርን ማታ እየቀጸልን ቆየን።

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከመግባቴ በፊት ዝዋይ ገዳም ለመማር ከአንዴም ሁለቴ ሄጄ ነበር። በሁለቱም ወቅት ወባ በኃይለኛው የተነሣችበት ወቅት ስለነበር አሁን በሕይወት ያሉት አቡነ ጎርጎርዮስ አሁን ወቅቱ ጥሩ አይደለም ብለውኝ ተመልሻለሁ። ከዛ በኋ ነው ወደ መናገሻ ገዳም የሄድኩት። መናገሻ የሄድኩት ቅድስት ሥላሴ ለመግባት ቀድሜ መማር የነበረብኝን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለማሟላት ነው። ከዚያ በ1988 ክረምት ወቅት ላይ ገዳሙ ለአንቦ ሀ/ስብከት ጽፎልኝ፤ ሀ/ስብከቱ ደግሞ ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ጽፎልኝ በአምቦ ሀገረ ስብከት በኩል በ1989 ዓ/ም ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገባሁ።

የዲቁና ክህነት የተቀበልኩት እዛው መናገሻ አምባ ማርያም ገዳም በወቅቱ የምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል ነው። የትምህርተ መለኮት ትምህርቴንም እንድማር ደብዳቤ ጽፈው ያስገቡኝ ብፁዕነታቸው ናቸው። ያኔ ከየሀ/ስብከቱ የተላኩ ተማሪዎች ተመዝግበው አርብ ምዝገባው አልቆ ሰኞ ትምህርት ሊጀመር እኔ ረቡዕ ነው መስከረም ወር ላይ ገዳሙ የጻፈልኝን ደብዳቤ ይዤ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ጋር የመጣሁት። መልአከ ሰላም ዳኛቸው ካሳሁን የታወቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ኮሌጅ መግባት እንደምፈልግ ነግሬያቸው ስለነበር “አንተ እዚያው በመናገሻ ተቀመጥ እና ትምህርትህን ተማር እኔ የመንፈሳዊ ኮሌጁ ምዝገባ ሲጀመር አሳውቅሃለው” ብለውኝ እኔ ሀሳቤን እርሳቸው ላይ ጥዬ እዛው ገዳም ትምህርት ላይ ነበርኩ። እና እሳቸው ኮሌጁ መከፈቱን ሰምተው አሳወቁኝና ሙሉ የትምህርት ማስረጃዬን ይዤ ወደ አቡነ ገብርኤል ሄድኩኝ።

ብፁዕ አቡነ ገብርኤልም “ነገ የመግቢያ ፈተና ተፈትነው አርብ ውጤታቸውን አውቀው ሰኞ ትምህርት ይጀመራል? ምን ላድርግህ? ጊዜው ሄዶብሃል ከአሁን በኋላ አምቦ ሄደህ ደብዳቤ አስጽፈህ መምጣት እንዴት ይሆናል አትደርስም” አሉኝ። እኔም “ግድየለም ይጻፉልኝና ዕድሌን ልሞክር” ብያቸው ከገዳም የተጻፈልኝን ደብዳቤ ሰጠኋቸው። ከዚያም ወደ አምቦ ሀ/ስብከት መሩት። እኔም የዛው ዕለት ተነሥቼ ወደ አምቦ አቀናሁ።

አምቦ ስደርስ የማስታውሰው የሀ/ስብከቱ ጽሐፊዎች ቅኖች ስለነበሩ “የሊቀ ጳጳሱ ደብዳቤ ነው አስተናግዱት” ብለው አንዷ ለሆስፒታል የሚሆነውን አንዷ ደግሞ ለቅድስት ሥላሴ የሚሆነውን ደብዳቤ አዘጋጅተው ረቡዕ ዕለት ወደ ማምሻ ላይ ጨረስኩ። ግን በዛ ሰዓት አውቶቡስ ስለማይወጣ ሌላም ትራንስፖርት ስላልነበረ እዚያው ለማደር ተገደድኩ። ግን የት ነው የማድረው? ከዚህ በፊት ወደ አምቦ ከተማ መጥቼ አላውቅም ማደሪያ የምጠይቀው የማውቀው አንድም ሰው አልነበረም። የሚገርመው ነገር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ አብረን የተማርን አሁን አርፏል ነፍሱን ይማረውና ብዙነህ የሚባል ጓደኛዬ የእርሻ ኮሌጅ ለመማር አምቦ ገብቶ ነበር። ለካ እዚያ መንገድ ላይ የት ነው የማድረው እያልኩ ሳስብ ከፊቴ ቆሞ አየሁት “እንዴ መዝጌ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለኝ። ከብዙ ዓመት በኋላ መገናኘታችን ገርሞኝ የማውቀን ጓደኛዬን በማግኘቴም ደስ ብሎኝ ሰላም ተባብለን የመጣሁበትን ጉዳይ አስረዳሁት። እርሱም “በቃ ከኛ ጋር ታድራለህ” ብሎ ወደሚማርበት እርሻ ኮሌጅ ይዞኝ ገባ። ወደ ተማሪዎች ዶርም ከሄድን በኋላ እነርሱ ዶርም ማደር እንደምችል ነገረኝ። እራት ለመመገብም የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ ይዞኝ ገባ። ለተማሪዎቹ ሁሉ ቄስ ነው እያለ አስተዋወቀኝ። እነርሱም እራታቸውን በአንድ ላይ አድርገው አምጥተው ጸሎት አድርገን አሉኝ። ያኔ ገና ዲያቆን ብሆንም እንደ ቄስ ጸሎት አድረጌ ማዕዱን በጋራ በላን።

ሐሙስ በጠዋት ተነስቼ ወደ አዲስ አበባ መጣሁና ለብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሰጠኋቸው። እሳቸውም ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብቼ እንድመዘገብ ደብዳቤው ላይ ፊርማቸውና ቲተራቸውን አኖረው ሰጡኝ፤ ተመዘገብኩ፥ ዓርብ የመግቢያ ፈተናውን ተፈተንን። ሰኞ ደግሞ ውጤቱ ተለጠፈ እኔም ለዲግሪ መርሐ ግብር አለፍኩኝ። ከዚያ ለብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሄጄ ነገርኳቸው። እርሳቸውም በጣም ደስ ብሏቸው ቅርባችን የነበረ ሥዕለ መድኃኔዓለምን እየጠቆሙ “ሂድና እዚያ ጋር ሦስቴ ስገድ” አሉኝ እኔም ሰግጄ ወደ እሳቸው ስመለስ “ጌታችን ዐሥር ለምፃሞችን ፈውሶ ነበር። ከፈወሳቸው ለምፃሞች ውስጥ መዳኑን ለጌታችን መጥቶ የተናገረ አንዱ ብቻ ነበረ። አንተም እሱን ትመስላለህ ለብዙ ልጆች ደብዳቤ ጽፌ ነበር ካለፉት መካከል ግን ማለፍህን መጥተህ የተናገርክ አንተ ብቻ ነህ” ብለው መርቀውኝ፣ ምክራቸውንም ለግሰውኝ መስቀላቸውን ተሳልሜ ወጣሁ።

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አምስት የትምህርት ዓመታትን አሳልፌአለሁ። እንደምፈልገው አልነበረም በኮሌጁ የነበረው ትምህርት አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም። እኔ ስገባ ኮሌጁ በ1987 ተከፍቶ ገና ሁለተኛ ዓመቱ ነበር። ስለዚህ ብዙም የጠነከረ አልነበረም፥ መማር ማስተማሩ የዳበረም አልነበረም። ቢሆንም የተለያዩ መጻሕፍትን ከቤተ መጻሕፍት በመዋስ እናነብ ነበረ። ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን የነ አቡነ ሺኖዳ፣ የአቡነ ታድሮስን የነአቡነ ሙሳ መጻሕፍትን እናነብ ነበር። አራት ኪሎ ስለነበርን ለእኛ እጅግ አመቺ ነበርና ወደ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲና ቤተ መዘክር እየሄድን መጻሕፍትን እየተዋስን እናነብ ነበር። በዚህ መልኩ የተማርነውን በንባብ በደንብ አድርገን አጠነከርን።

አንድ ዓመት ከተማርን በኋላ ወደ የመጣንበት ሀ/ስብከት እንመለስና ክረምቱን እያገለገልን እንቆይ ነበር። እኔም ወደ መናገሻ አምባ ማርያም ገዳም ተመልሼ ነበር። እንዳጋጣሚ አንድ ቀን ሳስተምር ሱባኤ ሊይዙ ከመጡ ሰዎች አንድ እናት ትምህርቴን በስፒከር ሰምታ ዛሬ ማን ነው ያስተማረው ጥሩልኝ ብላ አስጠርታኝ ሱባኤ የያዘችበት ቤት ወሰዱኝ (አንቺ የምላት እንደ እናት ስለሆነችኝ እንጂ ትልቅ ሰው ናት በወቅቱ በግምት 60ዎቹ እድሜ ውስጥ ትሆናለች)። ምን እደሆንኩ ከየት እንደመጣሁ የት እንደምማር ጠየቀችኝ አስረዳኋት። በጣም ነው የተገረመችው።

ቴዎሎጂ የሚባል ትምህርት እንዳለ እንደማታውቅ ነገረችኝ። በምትችለው ሁሉ ልታግዘኝ እንደምትፈልግ ቃል ገብታ ሱባኤው ሲያልቅ አዲስ አበባ ስትመለስ እንድደውልላትና ቤቷ እንደምትወስደኝ ገልጻልኝ ወጣሁ። በቀጠሯችን መሠረት ሱባኤው ካለቀ በኋላ አዲስ አበባ አራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተገናኘን። ካሳንችስ ወደ ሚገኘው ቤቷ ወሰደችኝ። ነፍሷን ይማረውና ወ/ሮ ሣራ ሳህሌ ትባላለች። በወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ኃላፊ የነበሩት የመሐመድ ሳሌም አህመድ ሳሌም ጸሐፊ ነበረች። የተማሪነትን ችግር እንደምታውቅ፣ በሚያስፈልገኝ ሁሉ ልታግዘኝ ቃል ገባችልኝ፣ በቃሏም መሠረት በቀሪው የአራት ዓመት የኮሌጅ ቆይታዬ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገችልኝ፤ በተለይ መጽሐፍ ፎቶ ኮፒ እያደረገችልኝ፤ በምንም ነገር እንዳልቸገር እየረዳችኝ ትምህርቴ ላይ ብቻ እዳተኩር አድርጋኛለች።

መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብቼ ከመናገሻ አምባ ማርያም ገዳም እርቄአለሁ ብዬ ነበር የማስበው እመቤታችን ግን ሱባኤ ለመያዝ ደጇ ላይ ወድቃ የነበረችን ሴት አገናኝታ በልጇ ስትንከባከበኝ ደግሞ አየሁ። በኮሌጁ የሚሰጠውን ትምህርት እየተከታተልኩ፤ የጎደለውን ከመጻሕፍት ለማሟላት እየሞከርኩ፤ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት (በተለይ ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለምና ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን) በማታ ጉባኤና በሰንበት ትምህርት ቤት እያገለገልኩ፤ ትምህርቴን በማዕርግ አጠናቅቄ በ1993 ዓ/ም በነገረ መለኮት የመጀመሪያ ዲግሪዬን ያዝኩ። ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተመረኩ በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የውጪ ግንኙነት መምሪያ ውስጥ ለአንድ ዓመት የሥነ ጽሑፍና የምርምር ረዳት ኤክስፐርት ሆኜ ሠርቻለሁ። የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የእንግሊዘኛ ንግግሮችን ያዘጋጁ የነበሩት አምባሳደር ጥበቡን አግዝ ነበር።

በዚህ መሀል በፊት በዚህ ወቅት ኮሌጅ ለመግባት ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን ያገኘሁበት መኖሪያ ቤት አሁን ሆሳዕና አግኝቻቸው የነበሩት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የሚኖሩበት ቤት ነበር። በጊዜው ደግሞ ምሁር ኢየሱስ ገዳምን ለማሠራት ምዕመናንን ከተለያዩ የዓለም ክፍል በማስተባበር ላይ ነበሩ። እኔም ጠዋት ጠዋት አምባሳደር ጥበቡን ሳግዝ እቆይና ከሰዓት በኋላ ለእርሳቸው ወደ ውጭ የሚላኩ ደብዳቤዎችን አዘጋጅላቸው ነበር። ከብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ጋር ቅርበታችን በጣም የጠበቀ ነበር። የቅቤ ቡና ሁሉ ያስለመዱኝ እርሳቸው ናቸው። የቅስና ክህነት የተቀበልኩትም ከብፁዕነታቸው ነው።

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- ከባለቤቴ ጋር ለረጅም ጊዜ በርቀት እንተዋወቃለን። በቅርበት በሕይወት ጓደኛነት የተዋወቅነው ግን በ1994 ዓ/ም። እሷ Constraction and Business Bank ነበረ የምትሠራው። ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋሽ ግርማ የተባለ ትልቅ መምህርና የሥራ ባልደረባዋ ዘንድ የባንኮች ጉባኤ ትሳተፍ ነበር። ጋሽ ግርማ ካረፈ በኋላ በእርሱ ፈንታ ኅብረት የሺጥላ (አሁን ቀሲስ) የተባለ መምህር ተተካ። ከዛም በኋላ እርሱ ወደ ደብረ ሊባኖስ ለትምህርት ሲሄድ እኔ ተመደብኩኝና እዚያ ጉባኤ ላይ ማስተማር ጀመርኩ። በዚያው ከእርስዋ ጋር ተዋወቅን።

ለመጋባት ስለተፈቃቀድን ቤልጅየም የእስኮላርሺፕ ፎርም ስሞላ አግብቻለሁ ብዬ ሞላኋት። ስኮላርሺፑ ተሳክቶ ትምህርት ቤቱ እንደተቀበለኝ ሲያሳውቀኝ ቶሎ ወደ ጋብቻ አመራንና በ1994 ዓ/ም ሐምሌ 21 ማክሰኞ የእመቤታችን ዕለት ተጋባን። ሥርዓቱም የተፈጸመው ብሥራተ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ነበር። የጋብቻ ሥርዓታችን በጣም አጭር የቁርስ ዝግጅቱ የደብሩ አለቃ ቢሮ ውስጥ ተፈጽሞ ምሳ የእኔ ቤተሰቦች አዘጋጅተው ከቤተ ክርስቲያን በኋላ ወደ እኔ ቤተሰብ ቤት ሄድን። ምሳ አብረን ከርሷና ከእኔ ቤተሰቦች ጋር በልተን በቃ ሠርጉ አለቀ፤ በማግሥቱ ሁለታችንም ወደ ሥራ ገባን። ከዛን በኋላ መስከረም 27 ቀን 1995 ዓ/ም ወደ ቤልጄም ሄድኩኝ። አስቀድሜ ፎርሙ ላይ ሞልቻት ስለነበረ ከ5 ወራት በኋላ ባለቤቴ ወደ ቤልጅየም መጣች። ከዛም ሁለት ሴት ልጆችን አፈራን። ሥርጉት መዝገቡ እና ከነዓን መዝገቡ ይባላሉ። አሁን የ18ና 16 ዓመት እድሜ ልጆች ናቸው። እግዚአብሔር ይመስገን።

በነገራችን ላይ ወደ ምንኩስና ሕይወት የመግባት ሃሳብ ነበረን። አምስት የምንሆን ወንድሞች እንመነኩሳለን ብለን ኮሌጅ የቆየንበትን የመጨረሻውን አምስተኛ ዓመት አባ ዘድንግል (አሁን የጉራጌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ) ዶርም በየሳምንቱ አርብ አርብ እየሄድን መጽሐፈ መነኮሳትን እናነብና እንማር ነበር። የሚሆነው ግን እኛ የፈለግነው ሳይሆን እግዚአብሔር የፈቀደው ነው።

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- ቤልጄም ከገባሁ በኋላ የአየር ሁኔታው ከባድ ነበር። የሌሊቱ መርዘም፣ ለአገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ በመሆኔ ቶሎ ወደ ትምህርቱ መስመር አልገባሁም። ትምህርት ከተጀመረ ከሁለት ሳምንት በኋላ ስለደረስኩ፣ የመኖሪያ ቤት ለማመቻቸት ላይና ታች ስል ቆይቼ ትምህርት ከተጀመረ ከወር በኋላ ነው ክፍል መግባት የጀመርኩት። የትምህርቱ ሥርዓት የተለየ መሆኑ ታክሎበት የመጀመሪያው ሲሚስተር ከብዶኝ ነበር። ቀስ እያልኩ እየለመድኩ ከሲስተሙ ጋር እየተግባባሁ መጣሁና የመጀመሪያ MA Degreeዬን በReligious Studies ለሁለት ዓመት አጠናሁ። ከዛም ሁለተኛ MA Degreeዬን በቴዎሎጂ ለሁለት ዓመት ተከታተልኩኝ። በአጠቃላይ አራት ዓመት ስቆይ በገንዘብ ይረዱኝ የነበሩት Aid to the Church in Need የሚባል የጀርመን ውስጥ የሚገኝ ድርጅት ነው። ለድርጅቱ ደብዳቤ የጻፉልኝና ያስፈቀዱልኝ በረከታቸው ይደርብንና በወቅቱ የኮሌጁ ዋና ዲን የነበሩት ብፅዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ነበሩ። ብፁዕ አባታችን አቡነ ጢሞቴዎስ ገና ከመሄዳችን በፊት Catholic Near East Walfare Association (CNEWA) ሽሮ ሜዳ አካባቢ የሚገኝ ድርጅት አነጋግረውና ደብዳቤ ጽፈው ለቅያሪ ልብሳና ለሻንጣ፣ ለአየር ቲኬትና እዛ ስንደርስ ለታክሲ እንዳንቸገር የገንዘብ ድጋፍ እንድናገኝ ሁሉ አድርገውልናል። አሁንም ጠቅልዬ ስመጣ ኮሌጁ ውስጥ በአስተማሪነት እንዳገለግል የቀጠሩኝ ብፁዕነታቸው ናቸው። ብፁዕ አቡነ ጤሞቴዎስ ትልቅ ባለውለታዬ ናቸው።

የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ውጤቴ ጥሩ ስለነበር PHD ፕሮግራም መቀጠል የምችልበት እድል አገኘሁ። የገንዘብ ድጋፍ ግን አላገኘሁም ነበር። ወደዚህ መጥቼ ብጠይቅ እዛም ብፈልግ የትምህርቱን ውጪ ሸፍኖ ሚያስተምረኝ አካል ማግኘት ተቸግሬ ነበር። የዓለም የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤንም ጠይቄ ነበር አልተሳካም። ያኔ በወቅቱ የነበረው እሳቤ አንድ ሰው አውሮጳ ከገባ በኋላ ሠርቶ እራሱን መደገፍ ይችላል የሚል ስለነበር ያመለከትኩባቸው ቦታዎች ሁሉ አዎንታዊ መልስ አልነበራቸውም ። በዚህ ምክንያት ትምህርቱን አቋርጬ ከማውቃቸው ካህናት አባቶች ጋር ተነጋግሬ ወደ ሰሜን አሜሪካ ለመሄድም ወስኜ ነበር። በዚህ ጊዜ እዛው ቤልጂየም ያሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች “ወደ አሜሪካ ሄደህ ስታገለግል የሚከፍሉህ ምዕመናን ናቸው። እዚም እኛም እንደዚህ ማድረግ እንችላለን ስለዚህ አንተ ሄደህ አገልግሎቱ ከሚቋረጥ፣ ቤተ ክርስቲያን ከምትዘጋ አራት ዓመት ስትማር አንድም ቀን አስቸግረኸን ከእኛም ተቀብለህ አታውቅም አሁን ግን እዚሁ ቅር እና እኛ ለትምህርትህ ሚሆነውን እንክፈልህ ትምህርትህንም አታቋርጥ አሉኝ”

እኔ ቤተ ክርስቲያን እንጂ ምዕመናን ተቸግረው እንዲያዋጡ አልፈልግም ብላቸውም፤ እርሱ አንተን አያስጨንቅህ እኛ እንደሚሆን እናደርገዋለን ብለው አሰባስበው ለአንድ ዓመት አከባቢ በሚከፍሉኝ የገንዘብ ድጋፍ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገልኩ ትምህርቴን ቀጠልኩ፥ ባለቤቴም ሥራ አግኝታ ትሠራ ጀመር፥ እኔም ቆይቶ ሥራ አገኘሁ። ቀስ እያሉ ነገሮች መስመራቸውን እየያዙ እስኪስተካከሉ ግን እጅግ ብዙ ውጣ ውረድ ነበረው።

በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች መሃል ግን ትኩረቴን ከትምህርቴ አላነሳሁም። የPHD ትምህርቴንም በ5 ዓመት ቆይታ ጨርሻለሁ። በሁለተኛ ማስተርስ ዲግሪዬ ላይ የጀመርኩትን ርዕስ ነበር በጥልቀት አስፍቼ PHD የሠራሁበት፥ Christian Moral philosophy ወይም Theological ethics ነው የሚባለው። ከ10ኛ ክፍል ጀምሮ ውስጤ የነበረው ሀሳብ እና ጥያቄ እስከመጨረሻው እንዲመለስልኝ ብሎ ሳይሆን አይቀርም እዛው ፍልስፍና የሚቦካበት ምድር ውስጥ 9 ዓመት በትምህርት የቆየሁት።

በቆይታዬ ማንበብ የምችላቸውን መጻሕፍት ሁሉ በምችለው መጠን አንብቤያለሁ፣ መሳተፍ የምችልባቸውን academic ውይይቶች እና ክርክሮች ተሳትፌያለሁ። በምችለው መጠን አእምሮዬ ያነሳቸው ጥያቄዎችን መመለስ በምችልባቸው መድረኮች ተሳትፌያለሁ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን እነዚያ ሰንበት ትምህርት ቤተ የተማርኳቸው basic የሆኑ ኮርሶች፣ መናገሻ ገዳም ሳለሁ የኔታ ያስተማሩኝ እና ልቤ ላይ ያስቀመጡት ትምህርት እና ቅድስት ሥላሴ እየተማሩኝ የመልአከ ሰላም (ጋሽ) ታዬ አብርሃም ትምህርቶች በአውሮጳ ዘመናዊ ትምህርት እንዳልወሰድ አጽንተው ይዘው አቆይተውኛል።

የአውሮጳውያኑን ከእግዚአብሔር የተላቀቀ ሰው ባለው የማሰብ አቅም ላይ ብቻ የተመሰረተውን ፍልስፍና በትችት ዐይን ነበር እመለከተው የነበረው። ያኔ ፍልስፍና ተግዳሮቴ ስለነበር እዛ እንማር የነበረው ከግሪኮ-ሮማን ፈላስፎች ጀምሮ በጥልቅ የዳበረው የምዕራቡ ዐለም Godless ፍልስፍናም የነበረኝን እምነት የመሻር አቅም የነበረው ስለነበረ ከባድ ነበር። ግን ተቋቁሜ ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ እምነቴንና ማንነቴን ጠብቄ መመለስ ችያለሁ።

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- በቆይታዬ ማንበብ የምችላቸውን መጻሕፍት ሁሉ በምችለው መጠን አንብቤያለሁ፣ መሳተፍ የምችልባቸውን academic ውይይቶች እና ክርክሮች ተሳትፌያለሁ። በምችለው መጠን አእምሮዬ ያነሳቸው ጥያቄዎችን መመለስ በምችልባቸው መድረኮች ተሳትፌያለሁ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን እነዚያ ሰንበት ትምህርት ቤተ የተማርኳቸው basic የሆኑ ኮርሶች፣ መናገሻ ገዳም ሳለሁ የኔታ ያስተማሩኝ እና ልቤ ላይ ያስቀመጡት ትምህርት እና ቅድስት ሥላሴ እየተማሩኝ የመልአከ ሰላም ጋሽ ታዬ ትምህርት በአውሮፓ ዘመናዊ ትምህርት እንዳልወሰድ አጽንተው ይዘውኛል፥ የአውሮፓውያኑን ከእግዚአብሔር የተላቀቀ ሰው ማሰብ ላይ ብቻ የተመሰረተውን ፍልስፍና በትችት ዐይን ነበር እመለከተው የነበረው። ያኔ ፍልስፍና ተግዳሮቴ ስለነበር እዛ እንማር የነበረው ከግሪኮ-ሮማን ፈላስፎች ጀምሮ በጥልቅ የዳበረው የምዕራቡ ዓለም Godless ፍልስፍናም የነበረኝን እምነት የመሻር አቅም የነበረው ስለነበረ ከባድ ነበር።

መሃል ላይ ሳላነሳው የቀረሁት እዚህም ቅድስት ሥላሴ ፋዘር ማቲው በሚባል መምህር ፍልስፍና ስማር የእግዚአብሔርን መኖር የምጠራጠርበት ቅጽበት ውስጥ ገብቼ ተረብሼ ነበረ:: ለዚህ ደግሞ መፍትሔዋ ቤተ ክርስቲያን ናት:: ቤተ ክርስቲያንን ደግሞ ጥያቄ ውስጥ ከትቼያት ነበር :: ስለዚህ በጣም ተጨነቅሁ:: አሁን ካናዳ የሚኖር ፍስሓ ታደሰ የሚባል ያኔ ሰቃይ ሆኖ አስተማሪ ሆኖ የቀረ ወዳጄ ነበረ:: እርሱን ሳማክረው ሳቀና “እኔም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞኝ በአታ ሔጄ ነው የመጣሁት” ብል እሱም ተመሳሳይ ተግዳሮት እንዳለበት ነገረኝ:: የቭላድሚር ሎስኪ “Mysticism and Theology (Mystical Theology” የሚል መጽሐፍ ሠጠኝ:: የአራተኛ ዓመት ተማሪ በነበርኩበት በዚያን ጊዜ ያ መጽሐፍ ሕይወትን በMystical መንገድ ወይንም በኦርቶዶክሳዊ እይታ እንዳይ ያ መጽሐፍ ረዳኝ:: ቀድሞ ከነበረኝ የሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት ፣ የጋሽ ታዬ ትምህርት ፣ የአብነቱ ትምህርት ጋር Purely acadamic በሆነ መንገድ ደግሞ የቭላድሚር ሎስኪ መጽሐፍ ጥግ አስያዘኝ:: አሁን የራሴን position define አድርጌያለሁ:: ፕላቶ ቢሉ አርስቶትል ቢሉ ኢማኑኤል ሊቪናስ ፣ ሃይዲገር ቢሉ የማንም ፍልስፍና ቢመጣ የምመለከተው በኦርቶዶክስ እይታ ስለማየው እኔ ላይ ምንም ያመጣው ነገር የለም::

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- መመረቂያዬን ለመሥራት በጣም ምቹ የሆነ የመጻሕፍትና የመረጃ አቅርቦት ያለበት ቦታ ነበር:: የምትፈልገው መጽሐፍ ባይኖራቸው እንኳን ከአሜሪካን ድረስ ያስመጡነበር:: አምስት ዓመት ሙሉ የደከምሁበት ሲሆን በየስድስት ወሩ የደረስኩበትን ለክፍል ማቅረብ ነበረብኝ:: አስተያየት ተቀብሎ ደግሞ የማስተካከል ሥራ ነበረ::

የመመረቂያዬ ትኩረት ፍልስፍናን መሠረት ያደረገ ሥነ ምግባራዊ መርሕ ሲሆን በማኅበረሰብ ላይ ተጽእኖ የፈጠረን የሥነምግባር ዘውግ የትኛው እንደሆነ ስፈልግ ያገኘሁት ነበረ:: የራስ ወዳድነት ሥነ ምግባር ተብሎ የሚጠራ ነው:: በሰሜን አሜሪካ ያደጉ ማኅበረሰቦች Ayn Rand የምትባል objectivist ልብወለድ ጸሐፊ አለች:: The Fountainhead , The Atlas Shrugged የተሰኙ ልቦለዶችዋን ብዙ ሰዎች እንደመጽሐፍ ቅዱስ እያነበቡ ያደጉ ናቸው:: ለጥናት ቴክሳስ በሔድኩበት ጊዜ በአጋጣሚ በእርስዋ ላይ ዐውደ ጥናት ተዘጋጅቶ ደርሼ ነበር:: የጥናቱ ርእስ “Ayn Rand the best in us” (በውስጣችን ያለች ምርጥዋ አይ ራንድ) የሚል ነበር:: ይሄንን ያህል ውስጣቸው ዘልቃ ገብታ ነበር:: አቋምዋ ግን ሙሉ በሙሉ ግለኛ (egoistic) ነበረ:: እርስዋን በዚያ ደረጃ ማግዘፋቸው ሰዎች ከእምነት ሕይወት ወጥተው በቁሳዊነትና በራስ ወዳድነት ዐውድ ውስጥ ጥግ የደረሱ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው::

አይ ራንድ በ1985 ብትሞትም ታራ ስሚዝ የምትባል ፊሎዞፊ አስተማሪ ነበረች:: ራስ ወዳድነት ራሱ ሥነ ምግባር ነው የሚል ሃሳብ ታቀነቅን ነበር:: ይህ ሃሳብ በጽሑፌ ላይ ብዳስሰውም ገና በደንብ አልተመታም:: በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ego በጣም የፈጠጠበት ዘመን ላይ ነን:: እንደ ቤተሰብም እንደ ማኅበረሰብም እንደ ሀገርም ሁሉም የየግሉን ጥቅም ለማሳካት የሚሻኮትበት ባሕል ውስጥ ነው የገባነው:: የዚያ ተጽእኖ እስከ አሁንም እኛ ላይ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ በደንብ ሊቃኝ ይገባል:: በዲዘርቴሽኔ ላይ ብሠራውም በደንብ ተተንትኖ ወደ ማኅበረሰቡ መቅረብ እንዳለበት ግን አምናለሁ::

ሁለተኛው ርእሴ “Ethics of responsibility” Responsibility (ተጠየቃዊነት) የምዕራቡን የፍልስፍናና የቴዎሎጂ መሠረት በጠበቀ መልኩ የተደራጀ ሊገዝፍ የሚገባው ሥነ ምግባራዊ ምልከታ ነው:: William Schweiker የሚባል የቺካጎ ዲቪኒቲ ትምህርት ቤት መምህርን ብዙ መጻሕፍትን የሠራ ሰው ነው:: እርሱን በማግኘት የእርሱን ሥራዎች መነሻ አድርጌ የሠራሁት ነበር:: በሌላ መልኩ ደግሞ የምሥራቃውያን ኦርቶዶክስን ምልከታ ደግሞ ለብቻ መቃኘት ነበረብኝ:: እነዚህን ሦስት ነገሮች ጨምቆ አንዳች የሥነ ምግባር ምልከታ ( ethical paradigm) መፍጠር ይቻል እንደሆነ የሚያስቃኝ ሥራነበር የሠራሁት::

የእኛ የሥነ ምግባር ምልከታ Theanthropic Ethics (የአምላክ ወሰብእ ሥነ ምግባር ወይም ሥግው ቃል ሥነ ምግባር) በመባል ይታወቃል:: በዚህ ላይ ብዙ የጻፉ ሊቃውንት ስላሉ በዚያ ላይ በማጥናት Theanthropic Ethics in Conversation with Autonomy and Heteronomy በሚል የሠራሁበት ርእስ ነው:: ያ ጊዜ ለመማር የሚሻ ማንነቴ ሙሉ እርካታ ያገኘበት ወቅት ነበረ::

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ:- ልክ ነው። እንዲያውም እዚህ ዲግሪ ተመራቂዎች እያለን ጓደኛዬ መብራቱ ኪሮስ “የመመረቂያ መጽሔት ላይ ከፎቶ ሥር የሆነ ነገር ማለት አለብህ” ብሎኝ ነበር።

በነገራችን ላይ ከዶ/ር መብራቱ ጋር ነፍስና ሥጋ የምንባል በጣም የምንቀራረብ ጓደኞች ነን። በሊተርጂ ዙሪያ እጅግ ብዙ የሠራ ሰው ነው። እንዲያውም የማልረሳው ገጠመኝ ዶግማቲክ ቴዎሎጂ የሚባል ኮርስ ሉቨርን ዩኒቨርስቲ ስንማር “የኦርቶዶክስ አቋም Monophysite ነው” እያለ ፕሮፌሰሩ ሲያስተምር ሰማሁትና “አይደለም የምሥራቁ አቋም Miaphysite ነው” ብዬ ተቃወምሁት። “ልታብራራው ትችላለህ?” አለኝ። “እድሉን ከሠጠኸኝ አዎን እችላለሁ” አልሁት። ከዚያም ለዶ/ር መብራቱ “Miaphysite Christology: An Ethiopian Perspective የተሰኘውን የማስተርስ መመረቂያህን ላክልኝ” አልሁት:: ያንን መመረቂያ ወደ ዐሥር ገጽ ጨምቄ ዋና ዋና ማሳያዎቹን ለፕሮፈሰሩ ላክሁለት።

በሚቀጥለው ሳምንት “ክፍል ውስጥ አስተምረው” አለኝና ሙሉ ሰዓቱን ለቀቀልኝ። ለተማሪዎች አንድ ሰዓት አቀረብሁት። በሁለተኛው ሰዓት ደግሞ በጥያቄና መልስ ተወያየንበት። የተሰማኝ ኦርቶዶክሳዊ ድል ከፍተኛ ነበረ:: ይኼን ማድረግ የቻልኩት መብሬ በሠራው ሥራ ነበረ። በነገራችን ላይ አስተማሪው ከ20 ውጤት 19 ሰጠኝና final exam መውሰድ አያስፈልግህም ብሎኝ ባቀረብኩት ጥናታዊ ጽሑፍ ብቻ ውጤት ሰጥቶኛል።

እና እዚህ ተማሪ እያለን መመረቂያ መጽሔት ፎቶ ስር ምን እንደምጽፍ ሲጠይቀኝ የመለስሁት “ከትምህርት ረሃብ አልጠገብሁም” ብዬ ነበር። ምክንያቱም ገና ልቤ ላይ አልደረሰም ነበር። ውጪ በትምህርት ከቆየሁ በኋላ ግን ከዚህ በኋላ አስተማሪ ማየት አልፈልግም እስከምል ድረስ ተማርሁኝ። ልክ ነው እውቀት በቃኝ አይባልም። ነገር ግን የምንችለውን ያህል እንወስድና እየተማርን ዘመን ላለመጨረስ የያዝነውን እያቀበልን እንሔዳለን።

…. ይቀጥላል

ጃንደረባው ሚዲያ ከቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ ጋር ያደረገው ዘለግ ያለ አካዳሚያዊ ውይይት በቀጣይ ሳምንት በሰፊው ይቀጥላል::

Share your love

7 አስተያየቶች

  1. አስተማሪ ቃለ መጠይቅ

    ይህ ሃሳብ በጽሑፌ ላይ ብዳስሰውም ገና በደንብ አልተመታም:: በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ego በጣም የፈጠጠበት ዘመን ላይ ነን:: እንደ ቤተሰብም እንደ ማኅበረሰብም እንደ ሀገርም ሁሉም የየግሉን ጥቅም ለማሳካት የሚሻኮትበት ባሕል ውስጥ ነው የገባነው:: የዚያ ተጽእኖ እስከ አሁንም እኛ ላይ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ በደንብ ሊቃኝ ይገባል:: በዲዘርቴሽኔ ላይ ብሠራውም በደንብ ተተንትኖ ወደ ማኅበረሰቡ መቅረብ እንዳለበት ግን አምናለሁ::

    ይሄን ፅሁፍ ብናነበዉ ብዙ ትምህርት እንወስድ ነበር።

  2. ደስ ይላል መምህር የተለያዩ ደብሮች ላይ አዬታለሁ ፀጋዎን ያብዛው እንደው ሚገኙበት አድራሻ ባገኝ

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *