እመነኩሳለሁ ብዬ ለአንድ አመት ሙሉ መጽሐፈ መነኮሳትን ሳነብ እና ስዘጋጅ ነበር

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ ካሣ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ፣ ደራሲና ተመራማሪ እንዲሁም ካህን ናቸው:: የጃንደረባው ሠረገላ ላይ የዚህ ሰንበት እንግዳ ሆነዋል::

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ ካሣ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ፣ ደራሲና ተመራማሪ እንዲሁም ካህን ናቸው:: የጃንደረባው ሠረገላ ላይ የዚህ ሰንበት እንግዳ ሆነዋል::

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ:- ተወልጄ ያደኩት እዚሁ አዲስ አበባ ኮልፌ አጠና ተራ (እፎይታ) አፄ ኃይለ ሥላሴ ያሠሯቸው የቁጠባ ቤቶች ውስጥ ነው። ፊደል የቆጠርሁትም በዚያው አካባቢያችን ውስጥ ልጆች ሰብስበው ያስተምሩ የነበሩ መምህር ጋር ነው። ከዚያም እዚያው ቤታችን አጠገብ በሚገኘው ኮልፌ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (የአሁኑ ሚሊንየም) ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተማርሁ። ትምህርት ቤቱ ብዙም ጠንካራ አልነበረም። መምህራን ክፍል የማይገቡበት፤ ተማሪዎች በጨዋታ የሚያሳልፉበት ጊዜ ይበዛ ነበር። እኔም ከትምህርቱ ይልቅ ወደ ኳስ ጨዋታው አዘነብል ነበር። ኮልፌ አካባቢ ሱቅ ስለነበረንም ወደ ትምህርቱ ዓለም ለመግባት አካባቢው አይጋብዝም ነበር። በዚህ ምክንያት ትምህርቱን ቸል ብዬው ስለነበር የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ወድቄአለሁ።

አባቴ ግን ከልጅነቴ ጀምሮ ለትምህርት ያለኝን ቀረቤታ ስለሚያውቅ እና በትምህርቱም ከፍ ያለ ደረጃ ላይ እንደምደርስ ተስፋ ያደርግ ነበር። ከዚያም ሰፈረ ሰላም የሚባል የግል ትምህርት ቤት ገባሁ። የሙሉ ቀን ትምህርት ስለነበርና ኳስ መጫወት የሚቻልበትም ግቤ ስላልኾነ ከንግዱ ዓለም እንድወጣና ሙሉ ለሙሉ ትምህርቴ ላይ ብቻ እንዳተኩር የምገደድበት ሁኔታ ተፈጠረ። ጓደኞቼ በወቅቱ ሰፈረ ሰላም ት/ቤት የሚማሩ ጥናት የሚያዘወትሩ ነበሩ። በትምህርት ቤቱ ያሉ መምህራንም እጅግ ኃይለኞች እና የሚጋረፉ ነበሩ። በአጠቃላይ የነበረው ኹኔታ ትምህርቴ ላይ ብቻ እንዳተኩር የሚያስገድደኝ ነበር። ከዛ በኋላ ትምህርቴን በአግባቡ መከታተል ጀመርኩ፣ ከጓደኞቼም ጋር ማጥናቱን ተያያዝኩት። የስምንተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ፈተናንም እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ውጤት (95/100) አምጥቼ ማለፍ ቻልኩ። ይህ ውጤት በውስጤ ከፍተኛ የAcademic ሕይወት መነቃቃት ፈጥሮብኝ ነበር፥ አባቴም እጅግ ደስ ብሎት የማልረሳውን የሸሚዝ ስጦታ አበርክቶልኝ ነበር። ከዛ በኋላ ቢያንስ አባቴን ተስፋ ላለማስቆረጥ በትምህርቴ የበለጠ መጠንከር እንዳለብኝ ወሰንኩ።

ከዛ በኋላ በቀድሞው አጠራሩ ከፍተኛ 7 ወደተባለው ከሰፈረ ሰላም ከፍ ብሎ ወደ አዲሱ ገበያ አከባቢ ወዳለው ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ልዩ ክፍል (special class) ገባሁ። ከዛ በኋላ የደረጃ ተማሪ ሆኜ ነው የቀጠልኩት፥ ዘጠነኛ ክፍል 9ኛ ደረጃ ይመስለኛል የወጣሁት፤ አሥረኛ ክፍል 3ኛ ደረጃ ነበርኩ፤ አሥራ አንደኛ ክፍል 1ኛ ደረጃ ነበር የወጣሁት። ከመምህራኖቼም ጋር ጥሩ ቅርበት ነበረኝ። በተለይ ትምህርቱን በአግባቡ ከማስተማር በተጨማሪ ምክር ይሰጡን የነበሩ እና ቅርብ የሆኑ እንደ ባለ ውለታ አድርጌ ምቆጥራቸው የማትስ (መ/ር ኃይሉ) እንግሊዘኛ (መ/ር ታደለ) እና ኬሚስትሪ () መምህራን ነበሩ። እንደ ታላቅ ወንድም እንደ ወላጅ ሆነው ከትምህርት ባሻገር ይመክሩን ነበር። ስህተታችንን አይተው አያልፉም ነበር። በዚህ አጋጣሚ ልባዊ አክብሮቴን ልገልጽና ላመሰግናቸው እወዳለሁ።

እነዚህ ሦስት መምህራን የ12ኛ ክፍል ፈተናን ክፍለ ሀገር ሄጄ እንድወስድ አጥብቀው መከሩኝ። ለዚህም ያቀረቧቸው ሦስት ምክንያቶች ነበሩ። የመጀመሪያው ከሀረማያ የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ የሚመረቁት መምህራን የሚመደቡት ክፍለ ሀገር ስለኾነና መምህራኑ fresh graduates ስለሆኑ እና ተግተው በደንብ ስለሚያስተምሩ ትምህርታቸውን በደንብ ታገኛለህ። ሁለተኛ ከጓደኛ፣ ከቤተሰብና ከአከባቢ ስትርቅ ማጥናት የምትችልበት ሰፊ ጊዜ ታገኛለህ፣ ሦስተኛ ደግሞ ውጤት ስታመጣ የክፍለ ሀገር ተማሪ ስለሆንክ አዲስ አበባ ትመደባለህ የሚል ነበር። እነዚህ ምክንያቶች እጅግ አሳማኝ ሆነው ስላገኘዃቸው ለአባቴ ሃሳቡን አሳውቄ የአባቴ የቅርብ ዘመዶች ወዳሉበት ወደ ሆሳዕና አገር ሄድኩ። ስለኾነም 12ኛ ክፍል የተማርኩትና ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናውን የወሰድኩት ሆሳዕና ዋቸሞ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር።

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- መንፈሳዊ ሕይወቴ የሚጀምረው ከሆሳዕና በኋላ ነው። ለማትሪክ ፈተና ስድስት ወር ሆሳዕና ተቀመጥኩ፥ በሆሳዕና ግን ብዙ ነገሮች ተቀየሩ። አካዳሚክ ሕይወቴ እንደነበረ ቢቀጥልም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት የገባሁበት እዚያ ሆሳዕና ነው። ሆሳዕና ለእኔ በእርግጥም እንደስሟ ሆሳዕና (መድኃኒት) ናት። በተለይ ሆሳዕና ማርያም ቤተ ክርስቲያን ባለውለታዬ ናት። ከአንድ ደረጄ ከሚባል እንደኔው ማትሪክ ለመፈተን ከክፍለ ሀገር ከመጣ ጓደኛዬ ጋር ቀን ትምህርት ቤት ቆይተን ወደ ቤት እንመለስና ከሰዓት በኋላ አጥንተን ከአሥራ አንድ ሰዓት በኋላ እርፍት እንደማድረግ ብለን የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም እንሄዳለን። በአውደ ምሕረት ላይ የወንጌል ትምህርት ሲሰጥ ሰምተን እንመለሳለን። ወንጌል ከሚሰብኩት ውስጥ አንዳንዶቹ ከእኛ ጋር ቀን ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች ናቸው። ከዛ ውስጤ እኔ ለምንድነው የማላስተምረው? የሚል ጥያቄ ይፍጥርብኝ ነበር። ለካ እነርሱ ዝዋይ ሄደው በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሃይማኖት ትምህርት ሥልጠና የወሰዱ ማስተማር የሚችሉ ዲያቆናት እና መምህራን ነበሩ። እመቤታችን ቤተ ክርስቲያን የማታ ጉባኤ መሳተፍ የዘወትር ተግባራችን ኾነ። በማታ ጉባኤ የምሰማው የወንጌል ትምህርት ለረጅም ጊዜ ውስጤ የተቀመጡ በአእምሮዬ ውስጥ ይመላለሱ የነበሩ ጥያቄዎችን የሚመልሱ ነበሩ።

ከአሥረኛ ክፍል ጀምሮ አእምሮዬ የሚያነሣቸው ነገር ግን መልስ ያላገኘሁላቸው መሠረታዊ የህልውና ጥያቄዎች ነበሩ። ሌሊት ተነሥቼ ለማጥናት ስል በጊዜ እተኛ ነበር። ቶሎ እንቅልፍ ስለማይወስደኝ እራሴን እየጠየኩ እራሴ እመልሳለሁ። ለምድን ነው በጊዜ የምተኛው? ሌሊት ተነስቼ ለማጥናት፣ አጥንቼስ? ውጤት ለማምጣት፤ ከዛስ? ዩኒቨርሲቲ ለመግባት፤ ከዚያስ? ጥሩ ሥራ ጥሩ ደመወዝ ለማግኘት፤ ከዚያስ? ትዳር መያዝ፣ ቤተሰብ ማፍራት፣ መኖር ከዛ መሞት። መጨረሻችን ሞት ከሆነ በዚህ ሁሉ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ለምንድነው ማለፍ ያስፈለገን? የሰው ልጅ መጨረሻው ሞት ከሆነ ለምን መኖር አስፈለገው? ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ? ለምንድን ነው እዚህ ዓለም ላይ የምኖረው? የዚህ ዓለምስ መጨረሻው ምንድነው? የሚሉ ማለቂያ የሌላቸው ጥያቄዎች በአእምሮዬ እያሰላሰልኩ አልጋ ላይ ስገላበጥ ነው ረጅም ሰዓት ሳልተኛ የምቆየው። ግን ማንን ነው ምጠይቀው? ማን ነው ስለ እነዚህ ጥያቄዎች የሚስረዳኝ። ከእነዚህ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ቤት ውስጥ ሲነገር አትሰሚም፤ ት/ቤት ውስጥም አይነሳም። እና እነዚህ ጥያቄዎች ለረጅም ጊዜ በአእምሮዬ ውስጥ እየተመላለሱ ተቀምጠው ነበር።

ሆሳዕና ማርያም ቤተ ክርስቲያን ማታ ጉባኤ ያስተምሩ የነበሩ ሰባክያን በትምህርታቸው እነዚህን ጥያቄዎች ይመልሱ ነበር። መምህራኑ የሚያስተምሩትን ትምህርት ከየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወይም ጥቅሱ ምን እንደኾነ አልይዝም መልእክቱ ግን ሰተት ብሎ ነበር ልቤ ውስጥ ይገባ የነበረው። በማስታወሻዬ ላይ የምጽፈውም ኃይለ ቃሉን ነው። እያንዳንዱ ቃል ስለ ሕይወት ያለኝን አመለካከት ይቀይረው ነበር። የምሰማቸው ትምህርቶች ሁሉ አእምሮዬ የቋጠረውን ጥያቄ ሲፈቱት ውስጤን ሲያሳርፉት ይሰማኝ ነበር። ለካስ አንሞትም፣ ለካስ በከንቱ ተፈጥረን በከንቱ ለመሄድ አልመጣንም፤ ሰው የሆንበት ምክንያት፣ ዓላማና ትርጉም አለው። ለካስ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ የምትሰጠን ሕይወት ሌላ ነው፣ እርሷ ጋር ያለው የሕይወት ትርጉም ሌላ ነው። የራሳችንን ማንነት ማግኘት የምንችለው፤ የሰው ልጅ ከልደቱ እስከ ሞቱ ድረስ ያሉ የህልውና እንቆቅልሾች ሁሉ የሚፈቱት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው። በመጨረሻም ወሰንኩ። መማር ካለብኝ የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ መማር እንዳለብኝ፤ ማገልገል ካለብኝ ቤተ ክርስቲያንን ብቻ እያገለገልኩ መኖር እንዳለብኝ ብዬ ወሰንኩ።

አሁን ዛሬ ላይ ሆኜ የነገረ መለኮትና የፍልስፍና ትምህርቶችን በምችለው መጠን ከተማርሁ በኋላ በዛ የ18ና የ19 ዓመት ልጅ በነበርሁበት እድሜ ላይ ሆኜ አነሳቸው የነበሩትን ጥያቄዎች ሳስታውስ ዛሬም የሚያነሱ ወጣቶች እንደሚኖሩ አስባለሁ። በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከሚሰጡ ትምህርቶች ውስጥ ከሰው ህልውና፣ ከማንነት፣ ከዓለም ምንነት፣ ከሕይወት ትርጉም ጋር የተያያዙ የፍልስፍና ጥያቄዎችን ለሚያነሡ ተማሪዎች መልስ ሊያገኙባቸው የሚችሉባቸው ትምህርቶች እስከዛሬ አለመኖራቸው ወይም በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ አለመካተታቸው በጣም ያሳዝነኛል። ወጣቶች እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልስላቸውና አእምሯቸውን የሚያሳርፍላቸው ሰው ካጡ ምን ያህል ሊጨነቁ ወይም በተሳሳተ መንገድ ሊረዱ እንደሚችሉ ወይም አእምሮቸው እነዚህን ጥያቄዎች ከመጠየቅ ዝም እንዲል ወደ አላስፈላጊ ልማዶች ሊገቡ እንደሚችሉ አስባለሁ። እነዚህን ወጣቶች እኔ የምረዳቸው ይመስለኛል። እንዴት ልደርስላቸው እንደምችል አላውቅም። በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በማስተምራቸው ትምህርቶች የእነዚህን መሠረታዊ የህልውና ጥያቄዎች ለመመለስ እሞክራለሁ።

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- አብሮኝ ትምህርቱን ከሚያጠና እና ወደ ቤተክርስቲያን አብረን ከምንመላለስ ጓደኛዬ ጋር የ12ኛ ክፍል ትምህርታችንን አቁመን የዲቁና ትምህርት ለመማር እስከ መወሰን ደርሰን ነበር። በኋላ ግን ድጋሜ ተማክረን 6 ወር ናት እንደ ምንም ጨርሰን ከዛ በኋላ የቤተክርቲያኑን ትምህርት ለመማር ሰፊ ጊዜ አለን ተባብለን ወደ ትምህርት ገበታችን ተመለስን። አእምሮዬ ግን በዘመናዊው ትምህርት የመቀጠል ፍላጎቱ እያቆመ መጥቷል። እንደውም ከመጓጓታችን የተነሣ በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በጊዜው የሆሳዕና፣ ከንባታና ሀዲያ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ እና እኔና ጓደኛዬ ወደ ብፁዕነታቸው ሄደን ዲቁና መቀበልና ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንደምንፈልግ ገልጸን እንዲፈቅዱልን አናግረናቸው ነበር።

እርሳቸውም መማር እንዳለብን እና ብዙ ነገር እንደሚቀረን ነገሩን። እኛም እውነት ነው ብለን ዓለማዊውን ትምህርት አስቀድመን ለመጨረስ በወሰንነው ውሳኔ ጸንተናን፤ ታግሰን ማትሪክ ወሰድን፤ ጓደኛዬም ወደ መጣበት ሄደ እኔም ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ። ይሄ የሆነው በ1985 ዓ/ም ነበር። ያኔ ለማትሪክ ፈተና ለመቀመጥ ይሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል ትምህርት 6 ወር ጊዜ ስለነበር ከመስከረም እስከ መጋቢት ድረስ በሆሳዕና ቆይቼ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ። የማትሪክ ውጤት በትኩረት ስላልሠራሁ አልጠበኩም 2.8 ነበር ያመጣሁት::

ሆሳዕና ከመሄዴ በፊት በአዲስ አበባ እያለሁ ምንም ዓይነት ሰንበት ትምህርት የመሄድም ሆነ ማንኛውንም ጉባኤ የመሳተፍ ልምድም ሆነ ዝንባሌ አልነበረኝም። ስለተለያዩ ጉባኤያት ስብከቶች ወዘተ ብሰማም አባቴ ትምህርቴ ላይ ብቻ እንዳተኩር ስለሚፈልግ ወደ እነዚህ ቦታዎች መሄድን አያበረታታኝም ነበር። ከሆሳዕና እንደመጣሁ ግን ዐይኔ ስለተከፈተ (ምን መስማት፣ ምን መማር፣ የት መሄድ እንዳለብኝ ስለአወቅሁ) የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የት ነው የማገኘው ብዬ ፍለጋ ነበር የጀምርኩት።

ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- ከዚያ በኋዋላ የሆነው እሱ ነው። የመጀመሪያው ዐይኔ ያረፈው ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ይካሄድ የነበረው ሳምንታዊ የሰንበት ትምህርት ቤት ጉባኤ ነበር። እጅግ የሚገርም ጉባኤ ነበረ። በተለይ የወንጌል አንድምታ ትምህርቱ አይረሳኝም። በየሳምንቱ ጥያቄ ይነሣና አንድ የወንጌል አንቀጽ ይነበባል ያንን የወንጌል አንቀጽ ሁሉም ወደ የቤቱ ወስዶ ተርጉሞ እና በተረዳው መጠን በአንቀጹ ዙሪያ አስቦ በቀጣዩ ሳምንት ይመጣል። ያኔ ሁሉም ምን እንዳሰበ ማንን ጠይቆ ምን እንደተረዳ ውይይት ይደረጋል። በዛ ውይይት የሚነሱ ሀሳቦች እጅግ ግሩም ነበሩ፤ መጨረሻ ላይ ትርጓሜው ወይም ወንጌል አንድምታው ይነበብና በአባቶቻችን የማስተማር ትርጉምና ስልት የተነሱ የተለያዩ ሀሳቦች ታርቀው ሁላችንም አንድ ወጥ የሆነ ግንዛቤ ይዘን እንድንሄድ ይደረግ ነበር። በዚህ መንገድ ነው ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የነበረው። እኔም እጅግ ተጠቅሜበታለሁ።

ሁለተኛው ደግሞ እሑድ ጠዋት ፈለገ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት (መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም) ተከታታይ ትምህርት እማር ነበር። በመደበኛ መልኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ዶግማ፣ የመሳሰሉትን ተምሬአለሁ። ማኅበረ ቅዱሳን በዓታ ግቢ ያዘጋጃቸው የነበሩ የተላዩ ኮርሶችንም እወስድ ነበር። ሥልጠና ይሰጣል ከተባለ ያለበት ሄጄ እማር ነበር። 1987 ዓ.ም. ግን በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ለመቆየት መማር ያለብኝን የአብነት ትምህርት ለመማር ወደ መናገሻ አምባ ማርያም ገዳም ሄድኩ።

ወደ መናገሻ አምባ ማርያም ገዳም ለመሄድ የተነሣሁበት ወቅት በጣም ከባድ ነበር። አስታውሳለሁ በ1986 ዓ/ም ክረምት ወቅት ውስጥ ነው። አባታችን ወንድሞቼንና እህቶችን ጠርቶ ወደፊት ምን ልንሠራ እንደምናስብ ጠየቀን። ወንድሞቼና እህቶቼ መሥራት የሚፈልጉትን ተናገሩ። የቤቱ የመጨረሻ ልጅ ስለሆንኩ ጥያቄው መጨረሻ ላይ እኔ ጋር ደረሰ። ጋሼ ዛሬ ይህንን ነው የምሠራው እንዲህ ነው የምሆነው ብዬ የምነግርህ ነገር የለኝም። ከፈቀድክልኝ ከሁለት ሳምንት በኋላ ላሳውቅህ አልኩት። እርሱም ፈቀደልኝ። ከዛ በማግስቱ ወደ መናገሻ አምባ ማርያም ገዳም ከጓደኛዬ (አሁን ቀሲስ ዮሐንስ ቀለመ ወርቅ ይባላል በአሜሪካ አሪዞና ቤተ ክርስቲያን ያገለግላል) ጋር ሄድኩ። ገዳሙ እንደደረስን ደስ የሚል ስሜት ነው የተሰማኝ። አካባቢውና መልክአ ምድሩ ከዚህ በፊት የማውቀው ያህል ትምህርት ቤት ቅጽሩ ውስጥ ስገባ ያደኩበት ቦታ ያህል ነው ይመስለኝ የነበረው። በዚህም ምክንያት የምናናግራቸው አባቶች እንደሚቀበሉን እርግጠኛ ነበርኩ።

በረከታቸው ይደርብንና የዛሬ አንድ ዓመት አከባቢ ያረፉት የኔታ በቀለ ኪዳነ ማርያም የተባሉ ብዙ ሊቃውንትን ያፈሩ የገዳሙን የአብነት መምህር አገኘናቸው። እዚህ እርሳቸው ጋር መጥተን ተቀምጠን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት መማር እንችል እንደሆነ ጠየቅናቸው። “እናንተ የከተማ ልጆች ናችሁ ምግብ ትቸገራላሁ። ብርዱም ከባድ ነው በዛ ላይ ማደሪያ የለም ጎጆው ሁሉ ተማሪ ይዞታል” አሉን። የከተማ ልጆች ስለሆንን የለመድነውን እንደማናገኝና እንደምንቸገር ገለጹልን። እኛም ችግር የለም እርሶ ብቻ ይፈቀዱልን እንጂ እንደማንኛውም ተማሪ ሆነን እንኖራለን እንችለዋለን ብለን ልናሳምናቸው ሞከርን። የየኔታ መልስ ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር። ለማንኛውም ለመስከረም ማርያም ኑና አዲስ ነገር ካለ እናያለን ብለው ሸኙን። ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ግን ከየኔታ የሰማሁትን ሳይሆን ገዳሙን ገና ሳየው ውስጤ የፈጠረብኝን ደስ የሚለውን ስሜት አድምጬ ለአባቴ ወደ መናገሻ አምባ ማርያም ገዳም መሄድና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት መማር እንደምፈልግ ነገርኩት። አባቴ በወቅቱ ሃሳቤን አልተቀበለውም ነበር።

እኔ ትምህርቱን ለመማር ወደ ገዳም ለመሄድ ወስኜ ቁርጥ አቋም ብይዝም በእናትና አባቴ በኩል ግን የይሁንታ ፈቃድ አላገኘሁም ነበር። ቤታችን ውስጥ የካህን ዘር ስላልነበረ ሊሆን ይችላል የእኔ ቤተ ክርስቲያን የመግባት ዓላማ ምንም አልታያቸውም። እነርሱ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ገብቶኝ ሳይኾን የልጅነት ስሜት አጓጉቶኝ የተነሳሳሁ ነው የመሰላቸው። እኔ ግን ልብሴንና መጽሐፎቼን በሻንጣ ከትቼ ለመሄድ ተዘጋጅቻለሁ። የምጠብቀው ፈቃዳቸውን ብቻ ነበር።

እኔ ለመሄድ ወስኜ ቤተሰቤ እስኪፈቅዱልኝ ድረስ የጠበኩበት ጊዜ በጣም ከባድ ጊዜ ነበር። ፊቴን ወደ እግዚአብሔር አዞርኩ። እግዚአብሔር እኔን ወደዚህ ሕይወት እንድገባ ጠርቶ፤ ይህንን ትምህርትም እንድማር አነሳስቶ ለምን ቤተሰቤ እንዲከለክለኝ ያደርጋል እያልኩ ከእግዚአብሔር ጋር መሟገት ጀመርኩ። በሂድኩበት ቤተ ክርስቲያን ሁሉ ግድግዳውን እንደበር እያንኳኳሁ “ክፈትልኝ፥ ወደ ቤትህ አስገባኝ፣ ላገለግልህ እፈልጋለሁ፤ ፍቃዴ ከአንተ ጋር መኖር ነው፤ እኔ ወደ አንተ እየመጣሁ እነርሱ እንዲፈቅዱልኝ የማታደርገው ለምንድን ነው” እያልኩ እግዚአብሔርን እማጸነው ነበር። 1987 ዓ/ም መስከረም፣ ጥቅምትና ኅዳር እነዚህ ሦስቱ ወራት ለእኔ የደጅ ጥናት ወቅቶች ነበሩ።

የታኅሣሥ በዓታ ዋዜማ ዕለት ማታ ቤተ መንግሥት በዓታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ከደጇ ቆሜ ለእመቤታችን “ዛሬ ግቢሽ አልገባም፥ እዚሁ ከየኔቢጤዎች ጋር ነው የማድረው። ከፈቀድሽልኝ እገባለሁ በዛው እንደገባሁ እቀራለሁ፥ ካልፈቀድሽልኝ ግን እዚሁ ውጪ እንደቀረሁ እቀራለሁ ዳግም አልመለስም” ብዬ በጸሎት ነገርኳት። እዛው ከየኔቢጤዎቹ ጋር አደርኩ እና ሲነጋ ወደ ውስጥ ገብቼ ንግሡን ሳላከብር ከደጃፉ ተመልሼ ወደ ቤት ሂድኩ። ቤት ስሄድ እጅግ በሚገርም ሁኔታ አዲስ ነገር ሰማሁ። ገና ከመግባቴ እናቴ “ወደ ፈለግህበት ሂድ” አለችኝ። ለምን ብዬ ጠየኳት። “ዛሬ አንድ ቀላ ረዘም ያለች ሴት የሆነ ገጠር ቤተ ክርቲያን ይመስለኛል በቤተልሔም በኩል ቆማ ‘ተይው ለምን ትከለክይዋለሽ እኔ ጋር እኮ ነው የሚመጣው ለምንድን ነው የምትከለክይው’ ብላ ስትናገር ሰማኋት። ዛሬ እመቤታችን ነች ብትሄድ እርሷ ጋር ነው የምትሄደው ስለዚህ ወደፈለግህበት ሂድ” አለችኝ።

…. ይቀጥላል

Share your love

9 አስተያየቶች

  1. እግዚአብሔር ባወቀ የምትሰሩት ስራ በጣም ደስ የሚል ነው እርሱ ይጠብቃችው በምትሰሩትም ስራ እንደኔ የጠፋነውን ሁሉ የምትመልሱበት በሰው ሁሉ ልብ ውስጥ መልካም ቅናትን አሳድራችው ወደ እግዚአብሔር የምትመልሱበት ያድርግልን

  2. ትልቅ አስተማሪ መጠይቅ ነው አመቤታችን ለእኛም ወደ ደጅዋ ትመልሰን አሜን።

  3. እጅግ በጣም ጥሩ ነው እግዚአብሔር ያበርታችሁ ከአድማጭ የሚነሱ ጥያቄዎችም ብታቀርብ ጥሩነው።

  4. ለካስ ቤተክርስቲያን ስንገባ የምትሰጠን ሕይወት ሌላ ነው፣ እርሷ ጋር ያለው የሕይወት ትርጉም ሌላ ነው። የራሳችንን ማንነት ማግኘት ምንችለው የመኖር ትርጉም ያለአ ከልደት እስከሞት ድረስ ያሉ እንቆቅልሾች ሁሉ የሚፈቱት ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው።

    ቃለ ህይወት ያሰማልን

  5. በጣም ለመንፈሳዊነት የሚያነሳሱ፥ መንፈሳዊ ግንዛቤን የሚያስጨብጡ ሌሎችንም ብዙ የህይወት ቁምነገሮች እያስያዛችሁን ነው። ስራችሁን በዘመናዊነትና በጥራት ለሠስራት የምታደርጉት ጥረት በጣም ያስደስታል። በሌሎች ቋንቋ ለመድረስ መሞከራችሁ በጣም የሚደነቅ ነው። እግዚአብሔር ይስጥልን!

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *