የብቸኝነት መስቀል

መድኅን ክርስቶስ በቸርነቱ የፈወሰው መጻጉዕ አንዱ የደረሰበት መከራ ለ38 ዓመታት ታሞ በአልጋው ላይ መኖሩ ነው፡፡ ሌላው መከራው ደግሞ ሰው የለኝም ያስባለው ብቸኝነቱ ነው (ዮሐ 5፡ 1 – 14) በብዙም ወይም በጥቂቱ ብቸኝነት ለብዙ ሰዎች የማይቀር ውስጣዊ ሕመም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ብቸኝነት ጥልቅ እና ትርጉም ያለው ግንኙነትን በማጣት ምክንያት የምንራበው ረሀብ ነው፡፡ ጥልቅና ትርጉም ያለው ግንኙነት መጀመሪያ ከእርሱ ቀጥሎም ከፍጥረት ጋር እንዲኖረን አድርጎ የፈጠረን እግዚአብሔር ነው፡፡ በአርአያ ሥላሴ የመፈጠራችን አንዱ መገለጫ በባሕርይ (በሰውነት) ከሚመስለን ከሌላው ሰው ጋር የሚኖረን የጥልቅ ግንኙነት ናፍቆት እና ተግባራዊ አንድነት ነው፡፡ ሰው ከአምላኩ እና ከሌላው ሰው ጋር ሊኖረው የሚገባውን ጥልቅ አንድነት ካላገኘ እየጠወለገ ይኖራል፡፡ ፍርሃት (Anxiety) እና ድባቴ (Depression) ከብቸኝነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጨማሪ ጉዳዮች መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሥነ ልቡናዊ ገጹን ለባለሙያዎች በመተው መንፈሳዊ መልኩን ለማየትና ለማሳየት መሞከር ነው፡፡ ሁለቱም ገጻት ብቸኝነትን ሕመም ብለው ዐውቀውት ሐኪም ይፈልጉለታል፡፡ እንደ ክርስቶስ ያለ ሐኪም (ባለ መድኀኒት) ይገኝ ይሆን? በፍጹም አይገኝም፡፡ በሌላ በኩልም በዚህ ጽሑፍ ብቸኝነት ብለን የምንገልጸው ሰዎች ጥልቅ የሆነ ግንኙነት ጎድሎባቸው የሚቀበሉትን መከራ እንጂ ከሰው ተለይተው በበአት ተከተው የሚኖሩ የአባቶች ሕይወትን ለመግለጽ አይደለም፡፡ እነርሱ ምንም እንኳ ከሰው አንጻር ብቸኛ ቢባሉም በረቂቅ ከእግዚአብሔርና ከወዳጆቹ ጋር የሚኖሩ ናቸውና፡፡ ስለሆነም የብቸኝነትን መንፈሳዊ ገጽ ምን እንደሚመስል አስተውለን ወደ መድኀኒቱ ለመድረስ እንሞክር፡፡

ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ የተፈጠረ አይደለም፤ ሌላውን ይሻል፡፡ ሌላውን መሻቱ በሥላሴ ዘንድ ባለች ፍቅር አምሳል ሌላውን በመውደድ ሕይወት እንዲኖረው ነው፡፡ ራሱን ለሌላው እየሰጠ ራሱን ለዘለዓለም እንዲያተርፍ ነው፡፡ በቅዱስ ወንጌል ነፍስን ልታገኛት ብትሻ ተዋት (ጣላት) የሚለው ተቃርኖ የሚመስለው መርሕ እዚህ ላይ ይመጣል (ማቴ 10፡ 39፤ ማር 8፡ 35)፡፡ ለሌላው ራስን በመስጠት ራስን ለሕይወት ማትረፍ፡፡ ነገር ግን ሰው ሊያገኘው የሚገባው ጥልቅ እና ትርጉም ያለው ግንኙነት በበደል ምክንያት ተበላሸ፡፡ ኀጢአት ራሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር ርቆ ራስን መውደድ ስለሆነ፤ ሰው እውነተኛ ስጦታውን (እርሱነቱን) ለመስጠት ስስት እና ፍርሃት አሸነፈው፡፡ ስለዚህ የእርሱ የሆነውን የሰጠ ቢመስል እንኳን፤ ራሱን ለመስጠት ግን አስቸጋሪ ሆነበት፡፡ ሰው ራሱን ሙሉ ለሙሉ መስጠት የሚቻለው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው፡፡ ስለሆነም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ካላስተካከለ፤ አካሄዱን ከፈጣሪው ጋር በሚገባ ካላደረገ ራሱን የሚሰጥበት ዐቅም አይኖረውም፡፡ በዚህ ምክንያት በብቸኝነት ጨለማ ውስጥ ይኖራል፡፡ በሲዖል ስለሚኖሩ ነፍሳት ልሳነ ወርቅ ዮሐንስ በተግሳጽ መጽሐፉ ላይ ያስቀመጠውን እናስተውል፡፡ ሊቁ እንዲህ ይላል፡-

“ወዳጄ በወዲያኛው ዓለም የሚደረገውን የመከራ ጽናት ዕወቅ፤ ተረዳ፡፡ ከሌባ ከወንበዴ ከነፍሰ ገዳዮች ጋር በባሕረ እሳት ሰጥመን እንኖራለንና፡፡ እነርሱ አያዩንም፤ እኛም አናያቸውም፡፡ ከእኛ ጋር እንደ እኛ ብዙ ሰዎች ሳሉ ብቻችንን ያለን ይመስለናል እንጂ፡፡ እርስ በእርሳችን እንተያይ ዘንድ ጨለማ አይለቀንምና፡፡ አንዱም አንዱ ብቻውን ያለ መስሎት መከራውን ይቀበላል እንጂ”

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሲዖል ያሉ ነፍሳት ምንም እንኳን ብዙ ጉባኤ ቢሆኑም ብቻቸውን እንዳሉ ሆነው ፍጹም የብቸኝነት ስሜት እንደሚሰማቸው፤ አንዱ ሌላውን እንደማያይ ሁሉም በየራሳቸው ብቻቸውን መከራ እንደሚቀበሉ በግልጽ ያስተምረናል፡፡ ምንም እንኳን ብቸኝነት ከሰው በደል በኋላ የመጣ ሁኔታ ቢሆንም እንኳን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት እንድናስካክል፤ ወደ እርሱም እንድቀርብ በመግቦታዊ ፈቃዱ (Providential will) ብቸኝትን ሊያመጣብን ይችላል፡፡ በሃይማኖታችን የጸናን፤ በምግባራችን የቀናን ባንሆን ብቸኝነት ይመጣብናል፡፡ በሰዎች ተከበን ሊሆን ይችላል፡፡ ከሚሰማን ብቸኝነት ለመሸሽ ራሳችንን በብዙ ሥራዎች ወጥረን ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአንድ በኩል ስናየው ብቸኝነት የአንድ ትልቅ ጉዳይ ምልክት ነው፡፡ እርሱም በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለው አምልኮታዊ ግንኙነት መስተካከል ያሻዋል የሚል ምልክትን የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ስንል በብቸኝነት የሚታመሙት ላይ ለመፍረድ አይደለም፡፡ ሕሙምን አዝነው አብረው ይታመሙለታል እንጂ አያዝኑበትም፡፡ ይልቁንስ ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ ርኅራኄን እናገኝ ዘንድ ለሌሎች መራራት ይገባናል፡፡ ቢሆንም ወደ እውነተኛው መድኀኒት ለመድረስ ሕመማችንን ለይቶ ማወቅ ይገባናል፡፡ እንዲያ ከሆነ የአሁን ብቸኝነት ለወደፊት ከእግዚአብሔር እና ከሰው ጋር በሰላም እና በፍቅር ለምንኖረው ሕይወት በጎ መሠረት የሚሆንበት ዕድል አለ፡፡ ከእግዚአብሔር ጸጋ ጋር ሆነን ካስተዋልነው የአሁን ብቸኝነት በማታ እንደሚሰማ ነገር ግን ወደ ንጋቱ ደስታ የሚያደርስ ልቅሶ ይሆናል፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ መዳረሻው መስቀሉ እንደሆነ እንዲሁ በመንፈሳዊ አኳኋን ለሚመለከቱት ብቸኝነትም እንዲሁ ነው፡፡ ብቸኝነት የእግዚአብሔርን የምሕረት ፊቱን እየፈለጉ በትዕግሥት የሚሸከሙት መስቀል ነው፡፡ ብቸኝነት ደጉ ሳምራዊን ተስፋ እያደረጉ የሚታመሙት የነፍስ ሕማም ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው ሰው ለሚሰማው ስሜት እግዚአብሔርን እየወቀሰ የሚኖር ከሆነ ወደ መፍትሔው መድረስ ሳይቻለው ይኖራል፡፡ ቀድሞም እግዚአብሔርን እንዲያማርር (እርሱ ላይ እንዲያጉረመርም) ያደረገው ጠላት ሰይጣን የመጨረሻውን የማይገባ ውሳኔ እንዲያስብና እንዲወስን ሊያደርገው ይችላል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህን በራስ ሕይወት ላይ የመጨረሻውን ጉዳት የማድረስ ድርጊት በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ እዚህ ደረጃ ድረስ ለደረሱ ሰዎች ማዘን፤ ለሌሎችም መጠንቅና መራራት እጅጉን ይገባናል፡፡

Share your love

10 አስተያየቶች

  1. በእውነት ገና ላነበው ስል ነው ያለቀብኝ፡፡ እጅግ በጣም አስተማሪ ጸሑፍ ነው፡፡
    እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
    ብዙ ብዙ ብዙ እያስተማራችሁን ነውና በርቱልን

  2. ቃለ ህይወትን ያሰማልን መምህራችን። አብዛኛውን ጊዜ የብቸኝነት ስሜት ወደ ከፍተኛ ጭንቀት፣ ድባቴ ወይም ይህን የመሰለ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስና የዕለት ከዕለት ኑሮአችን ላይ ተጽዕኖ ሲፈጥር ወደ ንስሐ አባት ከመሄድና ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡንን፣ ጭንቀታችንንም የሚያስረሱንን መንፈሳዊ ትሩፋቶች ከማከናወን ይልቅ ወደ ሀኪም ጋር ለመሄድ መቸኮል ይቀናናል። ሁልጊዜ ለብቻችን ስንሆን የምናሳልፈውን ጊዜ መጠንቀቅ አለብን ባይ ነኝ። በተለይም የአዕምሮ ጤንነትን መታወክን ከተለመደው የተለየ ስሜት ሲሰማን፣ በዕለት ከዕለት ኑሮአችን ተጽዕኖ ሲያመጣ፣ አልፎም የባህሪ መለዋወጥን በማስተዋል ራሳችንን መመልከት እንዳለ ሆኖ መንፈሳዊ ህይወታችን ያለበት የእድገት ደረጃና ወደ እግዚኣብሔርን በማመን ውስጥ ያለ መቅረብንም አብዝተን ልንለማመደው የሚገባ ይመስለኛል። ዘመናችን በተለየ አሁን በቴክኖሎጂ መስፋፋት ያለው ጥቅም እንዳለ ሆኖ በመገናኛ ሚድያዎቻችን አጠቃቀም ግን አብረን ሳለን ብቸኝነት እየተሰማን፣ በተጨማሪ ሳናውቀው ስሜቶቻችንን እንዲሁም ኑሮአችንን ባለመመርመር ያልጠበቅነው ደረጃ ላይ ስንደርስ እንነቃለን። ጭንቀትም ሆነ ሌሎች የአዕምሮ ጤና መታወኮች ባለንበት ጊዜ እጅጉን የተስፋፉ በመሆኑ ለራሳችንም ሆነ ባጠገባችን ላሉ ሰዎች ትኩረት ልንሰጥ ይገባናል። በተጨማሪም ለሌሎች ሥራዎች ጊዜ እንደምንሰጠው ሁሉ መንፈሳዊ እድገታችንንም መመርመር ይገባል እላለሁ።
    ይህ ጭንቀትን የመሳሰሉ ሌሎችም የአዕምሮ ጤንነትን የተመለከቱ ጉዳዮች በመንፈሳዊ እይታ ምን እንደሚመስሉ ለምዕመናኑ በማቅረብ ሰፊ ሥራም ይጠበቃል ባይ ነኝ።
    በድጋሚ መምህራችን እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ህይወትን ያሠማልን 🙏🙏🙏

  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር። መጻጉ ከጠየቀው ጥያቄ ዋናው የሚረዳው ሰው እንደሌለ የተናገረው ነው። እኛ ወደብቸኝነት የሚወስደን ካጠገባችች ብዙዎች እያሉን እራሳችን በምንፈጥረቅ መገለል የብቸኝነት ስሜት ይሰማናልና። መጀመሪያ ከዚህ ወጥተን ቤተ ክርስቲያንን፣የንስሃ አባትን፣ቅዱሳትመጻህፍትን ሌሎችም አጠገባችን ያሉትን ልንመለከት ይገባናል።
    በድጋሚ ቃለህይወት ያሰማልን። ጃንደረባው ሚዲያ ለምታደረወጉት ጥረት እጅግ እናመሰግናለን እግዚአብሔር ይስጥልን።

  4. ተባረክ!!
    የሚሰማኝን ስሜት ነዉ የጻፍከው። በተለይ ”ሰዎች በሞሉበት ብቸኛ መሆን” እና መናፈቅ እራስህን ለመውቀስ እና መጥፎ የሚባሉ ዉሳኔዎችን አንድትወስን ያደርግሐል።

  5. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን መምህር። በእውነት ስለ ብቸኝነት መንፈሳዊ አተያየት በተመለከተ ትልቅ ትምህርት ነው ያስተማሩን። በድጋሚ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን🙏💐

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *