የአንቀጸ ብፁዓን ተራራ፥ ወንጌል የተጀመረችበት፣ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ መምህርነቱን ለቤተ ክርስቲያን የገለጠበት ስፍራ ነው። ዘጠኙን ብፁዓን በስብከቱ የገለጣቸው በዚህ ተራራ ላይ ነው። ትምህርቱን ለመስማት በጉባኤው ለመገኘት ወደ ተራራው የወጡ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ከሁሉ ይልቅ ቀርበው ይሰሙት ነበር። “ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ” ማቴ 5፥1 እንዲል። እሱ ከተራራ ላይ ወጥቶ ከተቀመጠ ማን ከተራራው በታች ይቀራል ብለው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚነሱ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ወደ ተራራ ወጥተው በተቀመጠበት ስፍራ ሲፈልጉት ይኖራሉ።

ኢትዮጵያ ሀገራችን ፍጹማን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የበዙባት አገር ናት። ብዙዎቹ ዓለምን ንቀው ስብከቱን እየሰሙ ለመኖር ወደ ተራራው ይወጣሉ። እሱ ከፍ ካለው ቦታ ላይ ይቀመጣል። እነሱ ቃሉን ለመስማት እንዲመቻቸው ዝቅ ብለው ተቀምጠው “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው” ሲል ይሰሙታል። ጠቢባን ጥበባቸውን፣ ባለጠጎች ሀብታቸውን፣ የሕዝብ አለቆች ሹመታቸውን ትተው ይከተሉታል። በዚያ ዘመን ከክርስቶስ ጋር ወደ ተራራው ወጥቶ፣ ስብከቱን ሰምቶ ከአይሁድና ከአጋንንት በቀር ወደ ኋላ የተመለሰ የለም ማቴ 4፥10፣ ዮሐ 6፥66።

ከተራራ ወደ ተራራ ያመላልሳቸዋል፤ በትንሹ ተራራ ያስጀመራቸውን ትምህርት ወደ ረዥም ተራራ አውጥቶ ምሥጢሩን ያብራራላቸዋል። በመጀመሪያው ተራራ ላይ ደቀ መዝሙርነትን ያስጀምራቸዋል፤ በመጨረሻ የሚገናኙበት ተራራ ላይ አካሉ ባደረጋት ቤተ ክርስቲያን ላይ ይሾማቸዋል። ትንሹ ተራራ ያልኋችሁ የአንቀጸ ብፁዓን ተራራ ነው። ረዥሙም ተራራ ደብረ ታቦር ነው። የመጨረሻ ክከርስቶስ ጋር የተለያዩበት ተራራም ደብረ ዘይት ነው። በትንሹ ተራራ በአንቀጸ ብፁዓን በቃል የነገራቸውን ወንጌል ምሥጢሩን በዐይናቸው እንዲያዩት ያደረገው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ነው። በቤተ ክርስቲያን ላይ ካህናት አድርጎ በአንብሮተ እድ የሾማቸውም በደብረ ዘይት ነው ሉቃ 24፥50።

የቤተ ክርስቲያን ደቀ መዝሙርነቷ ዛሬም ልክ እንደ መጀመሪያው ነው። አንዳንዶቹ በልባቸው፤ አንዳንዶቹም በእግራቸውም በልባቸውም ከተራራ ወደ ተራራ እየተዘዋወሩ በዕዝነ ነፍሳቸው ትምህርቱን ይሰማሉ። በዚህ ሰሙን መታሰቢያቸውን ያከበርንላቸው አቡነ አረጋዊ ደብረ ዳሞ ወጥተው መኖር የፈለጉት በተራራ ላይ የሰበካትን ወንጌል በልባቸው እያመላለሱ ለመኖር ነው። ከተራራው ጫፍ ወጥተው በተቀመጡ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደርሱ ቀርበው ስብከቱን ሲሰሙ ያገኟቸዋል። ቀርበው ሲሰሙ ይውላሉ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ደብረ ዳሞ ደብረ ታቦርን ይሆንላቸዋል፤ ጌታ ልብሱ ነጭ ሆኖ፣ ሙሴና ኤልያስም ከሱ ጋር ሲነጋገሩ፣ አብ በደመና ሁኖ “የምወደው ልጄ” ብሎ ሲመሰክርለት ይሰማሉ። በተመስጦ ይዋጣሉ። ለሰው ከተደረገው የእግዚአብሔር ፍቅር የተነሣ ደንግጠው ዝም ይላሉ።

በነገራችን ላይ በቅዱስ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነበረባቸውን ቦታዎችና ታሪኩን ሊያስታውሱን የሚችሉ ኩነቶችን ሊገልጡልን የሚችሉ ምሳሌዎችን ማድረግ ለአንዳንዶቹ እንደሚመስላቸው ግብዝነት አይደለም። ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳንድ ነገሮችን ያደረገው ነቢያት ያደርጉት በነበረበት መንገድና ቦታ ነው። ሙሴ ወደ ተራራ ወጥቶ እንደጸለየ እሱም ይህንኑ አደረገ ዘዳ 9፥9፣ ማቴ 4፥1። ኤልያስ በኮሬብ ፈፋ ውስጥ ያድር እንደነበረ እሱም በኤሌዎን ዋሻ ውስጥ ያድር ነበረ። 

ከሁሉም ይልቅ የሚደንቀኝ ጌታ የሞት ፍርሃት በያዘው ሰው አምሳል የጸለየባት የጌቴሴማኒ ምሥጢር ነው። ከረዥም ዓመት በፊት በዚህ ስፍራ ይስሐቅ “አባቴ ሆይ በጉ ወዴት አለ?” ዘፍ 22፥7 ብሎ አብርሃምን የጠየቀው በዚህ ስፍራ ነበር። ተመልከቱ ይስሐቅ የአባቱን ፈቃድ መፈጸሙ አይቀርም፤ ነገር ግን ሞት እንዲቀርለት የፈለገ ይመስላል። ኢየሱስ ክርስቶስም መሥዋዕትነቱ የሚያስፈልገን ስለሆነ እንዳይቀር የሱም የባሕርይ አባቱ የአብም ፈቃድ ነው። ነገር ግን “አባት ሆይ ይህች ጽዋዕ ከኔ ትለፍ” ብሎ ይጣራል። እንዴት ያለ ነገር ነው?

ለማንኛውም የቦታና የሁኔታዎች መመሳሰል የሰውን ልብ በጊዜውና በቦታው እንዳለ ሆኖ እንዲረዳው ስለሚያደርግ ቅዱሳን ወደ ተራራ ወጥተው ገዳም አቅንተው በዐት ሠርተው የሚኖሩበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ከዓለም ተለይተው ወደ ተራራው በወጡ ጊዜ በቀራንዮ ተራራ ላይ ሊቀ ካህናት ሆኖ ያገኙታል። በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሠያሜ ካህናት ሆኖ በካህናት በጳጳሳት ላይ እጁን እየጫነ ሲሾማቸው ይመለከቱታል። ከዚህ መውረድ አይሆንላቸውም። 

ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህ መሆን ለኛ መልካም ነው” ብሎ የጠየቀው ጥያቄ ለነሱ ተፈጽሞላቸው ከተራራው ሳይወርዱ እንደ አባ አረጋዊ ያሉት በዚያው ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሊኖሩ ከሞት ተሸሽገው የሚቀመጡበት መኖሪያቸው ያደርግላቸዋል። ከሰው ለተለዩት ከሰው የተለየ ነገር ያደርግላቸዋል። በዓለም ሳሉ ሞት እንዳያያቸው ይሸሽጋቸዋል። ሄኖክ ከሰዎች ተለይቶ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ እግዚአብሔርም ስለወሰደ አልተገኘም ዘፍ 5፥24። ኢልያስን በእሳት ሠረገላ ቢጭነው፤ ጠላቶቹን እሳት ከሰማይ አውርዶ እንዲያስበላቸው ለማድረግ ሥልጣን ቢሰጠው ከሰው የተለየ ነገር አደረገ ብሎ እግዚአብሔርን ሊወቅሰው የሚፈልግ ማነው? ከሰው ተለይቶ ቢለምኑት እግዚአብሔር ከሰው የተለየ ጸጋን ይሰጣል።

ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ሰኞ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

4 አስተያየቶች

  1. “…ከሰው ለተለዩት ከሰው የተለየ ነገር ይደረግላቸዋል …”
    ቃለ ህይወት ያሰማልን
    የአገልግሎት ዘመንዎን ይባርክልን!

  2. ስለ ሊቀ ሊቃውንት በምትጽፉት ማስታወሻ ላይ “አንቱ” እና “አንተ” የሚል አገላለጽ በተደጋጋሚ በሚቀርቡት ጽሑፎች ላይ ስለሚታይ እሱ ቢስተካከል። ከዚያ በተረፈ የምታቀርቧቸው ጽሑፎች አስተማሪ ናቸው።

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *