ቤተ ክርስቲያን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተች ፣ በጥምቀት ልብስ የተሸፈነች ፣ በረድኤተ መንፈስ ቅዱስ ጉልላትነት ከመዓት እሳት ፣ ከቍጣ ዶፍ የተከለለች ፣ በመስቀል ዓላማዋ የታወቀች ናት ። የተገዛችው በወልደ እግዚአብሔር ወርቀ ደም በመሆኑ ምድራዊ ዋጋ አይችላትም ። ወርቅና አልማዝም አይሠፈርላትም ። ዋጋዋንም አሳንሳ በምድራዊ ነገር አትደለልም ። ቤተ ክርስቲያን በግምት የምትጓዝ ፣ ለዛሬ ብቻም የምታቅድ አይደለችም ። በአምስቱ አእማደ ምሥጢራት ላይ የቆመች ፣ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ምድራዊ ተልእኮዋን የምትወጣ ፣ ነገ ላይ የምትጠብቀው ትውልድ ያላት ፣ በጨለማው ዓለም ላይም የተስፋ በር ናት ። የርግማን መጎናጸፊያ የወደቀበት ፣ ልጅነት የተመለሰበት ፣ እንደገና የተወለድንበት ፣ ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ ጋር የተባበርንበት ፣ የክርስቶስ ወገን ፣ የአማንያን ወዳጅ የሆንበት ፣ አሮጌውን ቤተሰብ ጥለን አዲስ ወዳጅነት ያገኘንበት ምሥጢረ ጥምቀት የሚሰጥባት የብርሃን ቤት ናት ።
ምእመናን ከሌሎች ሰራቂነት ብቻ ሳይሆን ከራሳቸውም አለማወቅ የሚድኑት አእምደ ምሥጢራትን ሲያውቁ ነው ። አምስቱ አእማደ ምሥጢራት ምሥጢረ ሥላሴ ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ ፣ ምሥጢረ ጥምቀት ፣ ምሥጢረ ቍርባንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ይባላሉ ። ከሊቅ እስከ ደቂቅ እነዚህን የሃይማኖት መሠረት የሆኑት ምሥጢራት ማወቅና ማሳወቅ ይገባል ። እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ቃል የተብራራ ነው ። የእግዚአብሔር ቃልም የእግዚአብሔር መገለጥ ነው ። ስለ እግዚአብሔር ልናውቅ የምንችለው በቅዱስ ቃሉ በብሉያትና በሐዲሳት እኔ ነኝ ብሎ ራሱን በገለጠበት መንገድ ነው ። ቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት የአስተርእዮ መንገዶች ሲሆኑ ራሱ እግዚአብሔር ወልድም ሥጋ ለብሶ ፣ በምድር ላይ ተመላልሶ ፣ ራሱንም በመስቀል ላይ ክሶ አስተርእዮን ወይም መገለጥን ፍጹም አድርጎታል ። አስተርእዮ በዘመናት እያደገ የመጣ እንደ ጠዋት ፀሐይ ብርሃኑ የጨመረ ፣ ሙሉ ቀን ሆኖም ለቤተ ክርስቲያን ያበራ ነው ። የጠፋው ዓለምም እግዚአብሔርን ሊያውቅ የሚችለው በቤተ ክርስቲያን በኩል በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን የአስተርእዮም ቋሚ አገልጋይ ናት ። ይልቁንም በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ ራሱን የገለጠውን እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በምሥጢረ ጥምቀት ልጅነት ፣ በምሥጢረ ቍርባን የሕይወት መብልነት ፣ በምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ተስፋነት ምእመናንን ወደ ድኅነት ትጠራበታለች ። አምስቱ አእማደ ምሥጢራት የምንላቸው አስተርእዮተ እግዚአብሔር ናቸው ። ከፍልስፍናና ከሰብአዊ እውቀት በላይ ስለሆኑ በእምነት የምንቀበላቸው እንጂ ዘመናዊና በዓይን የሚተመን መለኪያ የምናስቀምጥባቸው አይደሉም ።
እግዚአብሔር ምክንያት በማይሻ ህልውና ከዘላለም ዘመን በፊት ነበረ ። ለቀዳማዊነቱ ጥንት ፣ ለደኃራዊነቱም ድንበር የለውም ። ዓለማት በእርሱ የተፈጠሩ በመሆናቸው ሊወስኑት አይችሉም ። ዘመናትንም ያስቆጠረ እርሱ ነውና የዘመን ቍጥር አይስማማውም ። ፍጥረት ሁሉ በእርሱ አምጪነት ሲመጣ እርሱ ግን ያልተፈጠረ ፈጣሪ ሆኖ የሚኖር ነው ። ይህን ዓለም ሲፈጥር የሚታይና የማይታይ አድርጎ መፍጠሩ የሚታየውንና የማይታየውን የመግዛት ችሎታ እንዳለው ያመለክታል ። በዓለመ ነፍስ ያሉም በዓለመ ሥጋ ያሉም እንዲያዩት የሰጣቸው መነጽር እምነት ነው ። እግዚአብሔር በእውቀት ባሰሱት ቍጥር የሚሰወር ፣ በእምነት ግን የሚገኝ አምላክ ፣ የትሕትናና የደግነት ወዳጅ ነው ። አንድነቱ መከፈል ፣ ሦስትነት መጣፋት ሳይኖርበት ዘላለማዊ ሦስትነትና አንድነት ያለው አምላክ ሁኖ ይኖራል ። ሦስት አካል ነው ስንል እንደ አሕዛብ አማልክት ፣ አንድ አምላክ ነው ስንል እንደ አይሁድ የአንድ ገጽ ትምህርትን እያራመድን አይደለም ። ሦስት ፍጹማን አካላት ፣ አንድ ባሕርይ ያለው አምላክ ነው ። እግዚአብሔርን ብዙ አማልክት ማድረግ ፣ አንድ አካል ብሎ መጥራትም ሁለቱም ከመጻሕፍት እውቅና ውጭ የሆነ ሃይማኖት ነው ።
የእግዚአብሔር መንግሥት ለዘላለም ነው ። ነገሥታት ሺህ ዓመት ይንገሡ ቢባሉ ምኞት ብቻ ነው ። ቢፈልጉና ሰዎችም ቢመኙላቸው ዘመናቸው ከአርባ የማያልፍ ነው ። እርሱ ግን መንግሥቱ ለዘላለም ነው ። ነገሥታት የልጅ ልጆቻቸው ሲገዙ አላዩም ። የልጅ ልጅ ዕድሜም አልገዙም ። እግዚአብሔር ግን ግዛቱ ለልጅ ልጅ ነው ። ዳዊት የሰሎሞንን መንገሥ አየ ፣ በሰሎሞን የግዛት ዘመን ግን አልነበረም ። ሰሎሞንም ሮብዓም ሲገዛ ፣ እስራኤልም ለሁለት ስትከፈል አላየም ። እግዚአብሔር ግን ታሪክን የሚመራ ፣ የኋለኛውን ሺህ ዓመት ፣ የሚመጣውንም ሺህ ዓመት በመዳፉ ላይ የሚያይ ጌታ ነው ። ሁሉም ፍጥረት መለወጥ ሲያጠቃው እርሱ ግን የመለወጥ ሕግ ሳያዝዘው ይኖራል። ሀልዎቱን በተለያየ መንገድ የገለጠ ሲሆን አባቶች እንዳሉት ሐዋርያው ጳውሎስም እንደ ተናገረው እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በፍጥረቱ ይታወቃል ። “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና” /ሮሜ. 1፡20-21።/ ፍጥረታት የእግዚአብሔርን ጥበብና ኃይሉን ያሳያሉ ። ውብ የሆኑት ፍጥረታት ጥበቡን ሲናገሩ ፣ ግዙፍና ጽኑዓን የሚሆኑ ፍጥረታት ደግሞ ኃይሉን ይመሰክራሉ ። ፍጥረታት ሁሉ ስለ ፈጣሪያቸው በዝምታ ይናገራሉ ። ነቢዩ ዳዊት፡- “ሰማያት ይነግራ ስብሐተ እግዚአብሔር ወግብረ እደዊሁ ያየድዓ ሰማያት- ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል” እንዳለ ፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ ፣ ግኝት ሁሉ አስገኚ እንዳለው ይመሰክራል ። /መዝ. 18፡1 ።/ ነገረ ሃይማኖትን የመረመረ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የሰው ልጅ ፍጥረትን በማየት ይህ ዓለም አስገኚ እንዳለው ይረዳል ። ሰው ዝም ቢል እንኳ ግዑዛን ፈጣሪነቱን ሲናገሩ ይኖራሉ ። የሃይማኖት መነሻም የእግዚአብሔርን መኖር ማመን ሲሆን ፍጻሜውም ለእግዚአብሔር መገዛት ነው ።
እግዚአብሔር አምላክ ለፍጥረት የገለጠው ሀልዎቱን ብቻ ሳይሆን ስሙንም ነው ። እስራኤላውያን ያህዌ የሚለውን የእግዚአብሔርን ስም መጥራት በጣም ስለሚያስደነግጣቸው አዶናይ የሚለውን ስም ይጠሩ ነበር ። የእግዚአብሔር ስም የእግዚአብሔር ኃይልና ክብር ያለው መሆኑን ስለሚያምኑ ለስሙ ታላቅ ክብር ይሰጡ ነበር ። በስሙም ፍጡርን መሰየምና በዋዛ ስሙን መጥራትም ታላቅ ቅጣት እንዳለው ያምኑ ያስተምሩ ነበር። እግዚአብሔር ስሙን በተለያዩ ጊዜያት ለሰው ልጆች ገልጧል ። ስሙ የተገለጠላቸው የሰው ልጆችም ከድካማቸው በርትተው ፣ ከኀዘናቸውም ተጽናንተዋል ። ጻድቁ አብርሃም ኤልሻዳይ የሚለው ስም ተገልጦለታል ። /ዘፍ. 17፡1።/ አባታችን አብርሃም በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ ይህ ስም ሲገለጥለት በማይችለው ነገር ላይ እግዚአብሔር ቻይ መሆኑን እንዲያምን ፣ ስሙን የሃይማኖት በትር አድርጎ ሰጥቶታል ። ኤልሻዳይ ማለት ሁሉን ቻይ ማለት ነው ። በዘጠና ዘጠኝ ዓመት መውለድ ለሰው አቅም የሚቻል አይደለም ፣ እግዚአብሔር ሲያስችል ግን ፍጥረት አልችልም ማለት አይሆንለትም ። የሚያስፈልገውም ምን ያህል እችላለሁ ማለት ሳይሆን እግዚአብሔር እንደሚችል ምን ያህል አምናለሁ ማለት ነው ።
እግዚአብሔር አምላክ ሀልዎቱን ስሙን ብቻ ሳይሆን የተቀደሱ ጠባያቱንም ለፍጥረቱ ገልጧል ። እነዚህ ጠባያቱም የእግዚአብሔርነቱ ምስክር ናቸው ። ከጠባያቱም ለሰው ልጅ በጸጋ የሰጣቸው ሲኖሩ በእርሱ ዘንድ ግን በምልአት ይኖራሉ ። ኃይሉና ብርታቱ ከታወቀባቸው ጠባያቱ እግዚአብሔር ፍቅር ነው የሚለው ቀዳሚ ነው ። /1ዮሐ. 4፡10 ።/ ይህን ዓለም እንዲፈጥርም ሆነ ይህን ዓለም እንዲያድን ያስገደደው የገዛ ፍቅሩ ነው ። የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ዓለም የተገኘበትና የዳነበት ምሥጢር ነው ። እርሱ ሁሉንም ይወዳል ። ለሁሉም በጸጋው የሚያስፈልገውን ሰጥቷል ። ፍላጎቱን ከነ አቅርቦቱ በመስጠት በመግቦቱ ሁሉን ያረካል ። ፀሐይና ዝናብን ለሁሉ በመስጠቱ ፍቅሩ አድልኦ እንደሌለበት አሳይቷል ። ከሰጠንም ታላቅ ትእዛዝ የብሉይም የሐዲስም አንቀጽ ቀዳሚውና ዋነኛው ፍቅር ነው ። ማንኛውም ተግባራችን ያለ ፍቅር ከንቱ ነው ። በፍቅር ኃጢአቶቻችን ይቅር ይባሉልናል ። በፍቅርም ኃጢአትን እንተዋለን ። በምድር ላይ የምናያቸው የአባትና የልጅ ፣ የወንድምና የእኅት ፍቅር ሁሉ ከዚህ ታላቅ ፍቅር የተገኙ ናቸው። በፍቅሩ ፍጹም የሆነ ግን እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው።
እግዚአብሔር አምላክ በአንድነትና በሦስትነት የሚኖር አምላክ ነው ። ይህን ታላቅ ምሥጢርም በደረጃ ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ ለሰው ልጆች ሲገልጥ ኑሮ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በሆነ ጊዜ ምልአትን አግኝቷል ። እግዚአብሔር አንድም ሦስትም ነው ። በሥላሴነቱ ጭማሪ ፣ በአንድነቱ ድማሬ የለበትም። የአካላቱም ዳርቻ ሦስትነት ነው ። የአምላክነቱም መገለጫ አንድነት ነው ። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሦስት ስም ፣ ሦስት ግብር ፣ ሦስት አካልና ሦስት ኩነት አሉት ። አብ መባል የአካሉ ስሙ ሆኖ ለዘላለም ሲጠራበት የኖረበት ስም ነው ። ወልድ መባልም የአካሉ ስም ሁኖ ከአካሉ ጋር በዘላለማዊነት የተጠራበት ስም ነው ። መንፈስ ቅዱስም የአካሉ ስም ሆኖ ለዘላለም ሲጠራበት የኖረበት ስም ነው ። ዘላለማዊ አባትነት ዘላለማዊ ልጅ ይፈልጋል ። አብ አባት ተብሎ ለዘላለም ከኖረ ዘላለማዊ ልጅ የሆነው ወልድ አለው ማለት ነው። አብና ወልድ ለቅጽበት እንኳ የዘመን መቀዳደም የለባቸውም ፣ የክብር መበላለጥም አያገኛቸውም ። ልብና ቃል ባሉበት እስትንፋስ እንደማይለይ እንዲሁም አብና ወልድ በነበሩበት ዘመን ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ነበረ ። አብ ወላዲ አሥራጺ ፣ ወልድ ተወላዲ ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ ተብለው በግብር ስም ይጠራሉ ። የሦስቱም አካላት ፍጹማን አካላት ሲሆኑ በአንድ ባሕርይና መንበር አንድ አምላክ ተብለው ሲጠሩ ይኖራሉ ። አብ ልብ ፣ ወልድ ቃል ፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ መባላቸውም የኩነት ስም ነው ። እስትንፋስና ቃል የሌለው ልብ እንደሌለ አብም ወልድና መንፈስ ቅዱስ አሉት ። ልብና እስትንፋስ የሌሉት ቃል እንደሌለ እንዲሁም ወልድ አብና መንፈስ ቅዱስ አሉት ። ልብና ቃል የሌሉት እስትንፋስ እንደሌለ መንፈስ ቅዱስም አብና ወልድ አሉት ።
እግዚአብሔር ሦስት አካላት ቢኖሩትም አንድ አምላክነት አለው ፣ በሦስት ግብራት ቢጠራም በአንድ መንበር ይኖራል ፣ ሦስት ኩነታት አሉት ቢባልም በአንድ ባሕርይ ይጸናል ፣ ሦስት አስማት አሉት ብንልም ጌትነቱ ግን አንድ እንደሆነ እንናገራለን።
ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት የሃይማኖት መሠረት በማድረግ ትመሰክራለች ። ከመናፍቃንና ከከሀድያን ጋርም ልዩነቷን በዚህ የእምነት አንቀጽ ልዩ እንደሆነ ትገልጣለች ። ከዚሁም ጋር ዓለም የዳነበት ፣ ለመዳንም አምላካዊ ደም የጠየቀውን የሥጋዌውን ጉዞ የሃይማኖትዋ መሠረት መሆኑን ታምናለች ። ህልውናዋንም የመሠረተችው በእግዚአብሔር ከለላ እንጂ በምድራውያን ጠባቂዎች ፣ በሰው ጉልበት ላይም አይደለም። ወንጌልንም የምሥራች ብላ በጨለማና በቀቢፀ ተስፋ ላሉ ሁሉ ትሰብካለች። ስብከተ ወንጌል የራቁትን የምትጠራበት ፣ ያሉትን የምታጸናበት ነው ። ያለ ስብከተ ወንጌልም በገንዘብ መበልጸግ ቢኖር እንኳ ትውልድን ማፍራት አትችልም ። ስብከተ ወንጌል ንጹሕ ዘር ሁኖ በምእመናን ልብ ላይ መዘራት ይገባዋል። ስብከተ ወንጌል የሰላም ርእስ እንጂ የሁከት ማስነሻ ሁኖ አያውቅም ። ስለዚህም ጤና የሚሰጠውን ወንጌል በቅዱስ ፍርሃት ማወጅ ፣ የጠፋውንም ዓለም በፍቅር መሳብ ይገባል ።
ከዚሁ ጋር ሕዝብን ለማዳን ክብረ ክህነት እጅግ አስፈላጊ ነው ። እረኛውን የማይሰማ መንጋ በአውሬ እንደሚበላ ፣ ከጠላትም በላይ ራሱን እንደሚጎዳ እንዲሁም የክህነትን ክብር የሚንቅ አባቶቹንም የማይታዘዝ ለሰይጣን ሥራ የተጋለጠ ነው ። ባለንበት ዘመን ወንጌልን መስበክና የክህነት ክብርን ማስጠበቅ እጅግ ያስፈልገናል ። እርስ በርሳችን ስንነቃቀፍና ስንፈራረድ ዓለም ጦር ሰብቆ ይመጣል ። እኛ ስንጣላ መናፍቃን ያለ መሣሪያ ይማርኩናል ። እኛ ስንገፋፋ ለማያምኑ ሰዎች እንቅፋት እንሆናለን ። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየመጣ ያለው ፈተና የእርስ በርስ መናናቅ የሳበው መከራ ነው ። ወደ ውስጥ የሚወራውን ወደ ውጭ በማውራት ፣ በካህናት ጉባዔ ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ሊመከርበት የሚገባውን ለሕዝብ በመዝራት ቤተ ክርስቲያን በትግል ውስጥ እንድትገባ ፣ አጥሯ እንዲነቀነቅ አስተዋጽኦ ማድረግ አይገባምና የራቀውን ለማቅረብ ወንጌል መስበክ ፣ ያለውን ለማጽናት የክህነትን ክብር መመለስ እጅግ ያስፈልገናል ።
ማስታወሻ :- መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጸሐፊ ናቸው::
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ቃለ ህይወትን ያሰማልን!
ቤ/ክ ቅጥሮቿ ተከብረው የቀደመ ሠላሟና አንድነቷ ተመልሶ ለማየት ያብቃን!