በብዙ ጥንታውያት መዛግብት እና የሊቃውንት ትርጓሜያት ውስጥ ከዮሐ 7፡53-8፡11 ያለው የወንጌል ንባብ ተዘልሏል። ታሪኩ ተፈጽሟል አልተፈጸመም የሚለውን አኹን በዝርዝር የምናየው አይደለም። ለመጠቆም ያህል ግን ይህ የወንጌል ክፍል የሌለ መኾኑን ብዙዎች ይናገራሉ። አንዳንዱቹ ታሪኩን በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በሌላ ቦታ ሲያደርጉት፤ አንዳንዶች ደግሞ ወደ ሉቃስ ወንጌልም ውስጥ የሚከተቱ መኾኑን ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በዮሐ 7፡53-8፡11 ያለው ክፍል በኋላ የተጨመረ እንጂ በቀደመው ቅጂ ውስጥ የነበረ አይደለም የሚሉ ሐሳቦችንም የሚያነሡ አሉ።
በኛ ግን ታሪኩ በወንጌል የተጻፈና የታመነ መኾኑ በጉባኤ ቤትም በትርጓሜ የሚሰጥ መኾኑን በግልጽ ከአንድምታ ትርጓሜው መረዳት ይቻላል። እንደ አባ ጄሮም፣ ሊቁ አምብሮስ እና አውግስጢኖስ ታሪኩን በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ያደርጉታል። ሊቁ አባ ጄሮም በብዙ የጥንት የዮሐንስ ወንጌል ቅጂዎች ውስጥ ታሪኩን ማግኘቱንም ያወሳል። ዲዲመስ አይነ ስውሩ ደግሞ በዮሐንስ ወንጌል ባይኾንም በወንጌል ውስጥ ታሪኩን ማግኘቱን ይናገራል። በዲድስቅልያ ውስጥም ታሪኩ መገኘቱን ልብ ይሏል። Did. apost. 7; transl. by Arthur Vööbus። ሊቁ አውግስጢኖስ እንዲያው ታሪኩን ያጠፉት ትንሽዬ እምነት ያላቸው ባሎች መኾናቸውን ይናገራል። ምክንያቱም ሚስቶቻቸው ታሪኩን ሰምተው ሊያመነዝሩ ይችላሉ ብለው ስለሚፈሩ ነው ይለናል። “men of slight faith” deleted it because they were afraid that their wives might commit adultery after hearing about the woman” (On Adulterous Marriages 7.6)።
የተለያዩ አሥራው መጻሕፍትን በተለያዩ ቀደምት አበው የትርጓሜ ስብስብ አድርጎ በማዘጋጀት በጉልህ የሚታወቁት ግብጻዊው ታድሮስ ያዕቆብ ማላቲን ይህን ታሪክ በዮሐንስ ወንጌል ማብራሪያ መጽሐፋቸው ላይ የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅንና የአውግስጢኖስን ትርጓሜ መሠረት አድርገው ያብራራሉ። (Tadros Malaty, Commentary on John part 1, p 381-385)። እንደ መግቢያ ይህን ከተመለከትን ታሪኩ በኛም በዮሐንስ ወንጌል የሚገኝ ታሪክ መኾኑ የታመነ ስለ ኾነ መልእክቱን ወደ ማየት እንግባ።
በዮሐ 8፥1 የተጻፈው የወንጌል ክፍል የሚያስረዳን ቁም ነገር ከፈሪሳዊነት አስተሳሰብ መውጣት እንዳለብን ነው። ፈረሳዊነት የራስን አመንዝራነት ማየት አለመቻል ብቻ ሳይኾን ራስንም አጽድቆ መሞገትም ጭምር ነውና። ፈሪሳዊነት ከትሕትና የተራቆተ ማንነት የሚንጸባረቅበት ሕይወትም ነው። እነዚህ ሰዎች አመንዝራዋን ሴት ስታመነዝር አገኘናት ብለው ልቡናት ያመላለሱትን ኩላሊታት ያጤሱትን ወደሚያውቅ ማእምረ ኅቡዓት ወደ ኾነው ጌታ መጡ። ሴቲቱ ማመንዘሯን ተቃውመው የመጡ ያስመስሉ እንጂ የመጡት በቀጥታ የማይፈተነውን ጌታ እንፈትነው ብለው ነወ። በዚህም በራሳቸው ሥራ ራሳቸው የዲያብሎስ መኾናቸውን ምንም ቅሉ ባይረዱትም በተረዳ መንገድ ገለጹ። ሴቲቱን ስታመነዝር አገኘናት ካሉ ስለምንድን ነው አብሯት በዝሙት የወደቀውን ወንዱን ልጅ ይዘውት ያልመጡት? በእውን በሕግ የተጻፈው አመንዝራይቱ እና አመንዝራው ይገደሉ የሚል አይደለምን? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን አመጣጣቸው ጌታን እንፈትነዋል በሚል ስለ ኾነ፥ ለመፈተን ይመቸናል በሚል መንገድ ቀረቡ። በእርግጥ በሙሴ ሕግ ስታመነዝር የተገኘች ሴቷ ብቻ ትገደል አልነበረም የሚለው ይልቅስ አመንዝራውም አመንዝራይቱም ይገደሉ ነበር እንጂ የሚለው።
ሲጀመር ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሙሴን ሕግ ሊነግረው የሚችል ይኖር ይኾን? በእነርሱ አስተሳሰብ ጌታችን ትገደል ቢል ጨካኝ ነው ሊሉት አትገደል ደግሞ ቢል የሙሴን ሕግ ይሽራል ብለው ሊከሱ ነበር። የመጡት የሕሊናቸውን በር ዘግተው፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስንኳን የክስ ምክንያት ብናገኝ ብለው ነበር። በትርጓሜ ወንጌል “… ትወገር ቢል የእግዚአብሔር ወገን ነኝ ይላል፤ የሰው ጥፋት አያሳዝነውም እንለዋለን ብለው ነው፤ አትወገር ቢል “አንሰኬ ለኲነኔ ዝንቱ ዓለም መጻእኩ” ይላል አንድ ጊዜ እንዲህ ይላል ነገሩ ቀዋሚ አይደለም እንለዋለን ብለው ነው።” ብሎ ያትታል። (ቃለ ሕይወት በዛ (መ/ሐ፣ የመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም የሐዲሳትና የሊቃውንት ምስክር መምህር)፣ ወንጌል ቅዱስ ትርጓሜ፣ ገጽ 657)። ይህ እንደምን ያለ መታወር ነው! የሕጉን ባለቤት በሕጉ ይፈትኑት ዘንድ ይችላሉን? ለሙሴ ሕግ ሠርቶ የሰጠውን ጌታ በራሱ ሕግ ይፈትኑት ዘንድ ሞከሩ። ከእውነተኛ አኗኗር እየወጣን ስንሄድ የተገላበጠ ነገር እስከማድረግ ድረስ ዝቅ እንላለን። በኃጢአት ጣዕም የሰከረች ልቡና ዕውቀቷ ከስካሯ የተነሣ ጠማማ ስለሚኾንባት የማይፈተነውን ጌታ እፈትነዋለሁኝ እስከማለት ትደፍራለች። ውድ ወንድሞችና እኅቶች ሆይ እንደ ፈሪሳውያን የኾንባቸው የሕይወት አጋጣሚዎች የሉምን? እስኪ ለአንድ አፍታ ቆም ብላችሁ ሕይወታችሁን መርምሩት!
ፈሪሳውያኑ ላቀረቡት ጥያቄ ጌታችን የመለሰውን መልስ አውግስጢኖስ በብዙ መንገድ እያደነቀ ይገልጻል። “ከዚያን ጌታ ኢየሱስ ምን መልስ ነው የመለሰላቸው? እውነቱንስ እንዴት አድርጎ መለሰ? እንዴት አድርጎ በጥበብ መለሰ? የውሸት ክስ በቀረበ ጊዜ ያን ተቃውሞ ጽድቁን እንዴት መለሰ? በድንጋት አትወገር አላለም፥ እንዲያ ቢል ሕጉን ተቃርኖ ይናገራልና። ትወገርም አላለም፡ ምክንያቱም እርሱ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግ እንጂ የተገኘውን ሊያጠፋ (ሊያጣ) አይደለምና። ታዲያ ምን ብሎ መለሰ? እንዴት ጽድቅን፣ ቅንነትንና እውነትን እንደተመላ ተመልከት! “ኃጢአት የሌለበት በመጀመሪያ ይውገራት አለ!” ኦ የጥበብ መልስ! እንዴት እነርሱን ወደ ራሳቸው እንደላካቸው!” እያለ አውግስጢኖስ ያደንቃል። Tractates on the Gospel of John (Augustine) Tractate 33። ሕጉን እናስጠብቃለን የሚሉ እነርሱ ራሱ ሕጉን አፍራሾች ነበሩ።
ብዙዎቻችን ልክ እንዲህ ነን፤ እኛ ትዕቢተኞች ናቸው ብለን ያሰብናቸውን ትዕቢተኞች እያልን እንከሳቸዋለን፥ ነገር ግን እኛ ከተከሳሾቹ ይበልጥ በትዕቢት እሾህ ተወግተን የተጎዳን ነን። የሌሎች ስሕተት ወዲያው የሚታየን ነገር ግን እኛው ራሳችን የስሕተት ብዛት የተሸከምን ነን። ስለዚህ ጌታችን በመጀመሪያ ራሳችንን እንድናይ ስለሚፈልግ ወደ ራሳችን ይመራናል። መጀመሪያ ራሳችሁን አጥሩ ይለናል። መጀመሪያ በራሳችሁ ላይ ራሳችሁን ከሳሽ አድርጉ እና ከተያዛችሁበት የኃጢአት እሥር ውጡ። በየኃጢአት ምሽጋችን ውስጥ ተወሽቀን ሳለ እንዴት ሌላውን ልንከስ እንዳዳለን! እንዴትስ ራሳችንን ንጹሕ አድርገን ለማስቈጠር እንጥራለን? እንዴት እንዲህ ኾኑ ከሚለው በላይ እንዴት እንዲህ ኾንኹኝ የሚለውን ልንመልስ ይገባናል።
እነዚህ ሰዎች በኃጢአታቸው በመጽናታቸው ምክንያት መድኃኒታቸውን የሚያዩበትን ዐይን አባታቸው ዲያብሎስ ስላሳወረባቸው ክርስቶስን እንደ ዲያብሎስ ሊፈትኑት ይዳዳሉ። ዕሩቅ ብእሲም አድርገው ይቆጥሩታል። ወደ ሕይወት ውኃ ወደ ክርስቶስ የነፍሳቸውን ጥም ሊያረኩ መምጣት ሲገባቸው የሕይወት ውኃን ይገፉት ነበር። ባለማወቅ ወደ እርሱ ዘንድ መጥተው ባለማወቅ ከእርሱ ዘንድ ርቀው ሄዱ፤ ቅዱስ ይስሐቅ ዘሶርያ “ሰይጣን እግዚአብሔርን አይቶታልን? እግዚአብሔርን የሚመለከቱት ልበ ንጹሐን ብቻ ናቸው። ሰይጣን ንጹሕ ልብ አለው ሊል የሚችል ወገን ማነው? ነገር ግን ይፈራል ይንቀጠቀጥማል።” ይላል። (ታደለ ፈንታው (ዲን፣ ተርጓሚ)፣ የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት ታድሮስ ያዕቆብ ማላቲ እንዳስተማሩት፣ 2005 ዓ.ም፣ ገጽ 84)። እንግዲህ ወደ ሰይጣን እየቀረብን ስንሄድ የልቡና ንጽሕናችንን እያጣን፡ በሰዎች ላይ ክስን በመመሥረት ብቻ የበቀናን የነቃን እንደኾን አድርገን ራሳችንን ለማስቆጠር የምንጥር እንኾናለን። ይህ እጅግ አሳዛኝ የኾነ የዕለት ተዕለት የሕይወት ጉዟችን ነጸብራቅ ነው። እንደ ፈሪሳውያን ከትዕቢት ተጣብቀን እንኳ ቢኾን ወደ ጌታ በፍቅርና በተአምኖተ ኃጢአት ውስጥ ኾነን በተሰበረ ልብ ብንቀርብ ትዕቢታችን ከእኛ ተነቅሎ ይወድቃል።
በእርግጥም እርሱ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትዕቢታችንን የሚነቅልልን መኾኑን አምነን የምንሄድ ከኾነ። ይህ ካልኾነ ግን ለራሳችን ጥፋት ራሳችን በራሳችን ላይ ምክንያት እንኾናለን። እግዚአብሔር ትሕትናን ሲተክልብን በንዝኅላልነታችን ምክንያት ዲያብሎስ ይነቀልብንና ከእርሱ ጋር የሚያወዳጀንን ትዕብትን ይዘራብናል። ትዕቢተኛ ሰው የዲያብሎስ ማኅበርተኛና የቅርብ ወዳጁ ነው። በዚህም ምክንያት ከብርሃን ክርስቶስ ርቆ በጨለማ (አለማስተዋል) በተባለ በዲያብሎስ ቤት ውስጥ ይኖራል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደውም “ትዕቢት ከዝሙት ወይም ከማመንዘር በላይ እኛን ያቆሽሻል። ለምን? ያልከኝ እንደ ኾን ምንም እንኳ ዝሙት ንስሓ ካልገቡበት ሥርየተ ኃጢአት የሌለው በደል ቢኾንም በዝሙት የቆሸሸ ሰው ንስሓ ለመግባት ቅርብ ነው። በትዕቢት የታመመ ሰው ግን እንዲህ እንደ ዘማዊው ያለ ዐቅምን አያገኝም። ስለዚህ ትዕቢት እጅግ አደገኛ ደዌ ዘነፍስ ነው ብዬ እነግርሃለኁ” በማለት ስለ ትዕቢት ከባድነት ይገልጻል። (ገብረ እግዚአብሔር ኪደ (ተርጓሚ)፣ ሰማዕትነት አያምልጣችሁ እና ሌሎች፣ 2007 ዓ.ም፣ ገጽ 39-40)። ማንኛውም ሰው የትዕቢትን ጫማ ተጫምቶ ወደ ክርስቶስ ቢመጣ የሕይወትን ውኃ ቀድቶ ይጠጣ ዘንድ አይችልም።
ፈሪሳውያን በሥራቸው ምንም የዲያብሎስ ኮፒ ፔስቶች ቢኾኑም ክርስቶስ ወደ እርሱ መጥራቱንና ፍቅሩን አላቋረጠም ነበር። አመንዝራ ናት ትገደል ብለው ሲከሷት የሙሴን ሕግ ጠቅሰው ነበር፤ በእውን ለሙሴ ሕግን የሰጠ እርሱ መኾኑን ቢያውቁ ኖሮ እንዲህ ያደርጋሉን? አለማወቃቸውን ቢያውቁ ኖሮ ወደ ማወቅ ይሸጋገሩ ነበር፤ ነገር ግን አለማወቃቸውን የማያውቁ ብቻ ሳይኾኑ አለማወቃቸውን ማወቅም የማይፈልጉም ጭምር ነበሩ ይህ ደግሞ ከዕቡይነት የተገኘ ዲያብሎሳዊነት ነው። ፈሪሳውያን የሚሉትን ባያውቁትም እኛ ዲያብሎስን እንደ መሰልን እናንተም እኛን ምሰሉን ብለው እየሰበኩ መኾናቸውን በሥራቸው መጽሐፍነት ማንበብ እንችላለን።
ፈሪሳውያን ላቀረቡት ክስ የአምላካችን መልስ ራሳችንን የምናይበት መስታወት ነበር። ጎንበስ ብሎ በምድር ላይ ይጽሕፍ ነበር። በጨቀጨቁትም ጊዜ ከእናንተ መካከል ኃጢአት የሌለበት በድንጋይ መትቶ ይግደላት አለ። በምድር ላይ ዝቅ ብሎ ይጽሕ የነበረው የፈሪሳውያንን ኃጢአት ነበር፤ ጌታ በምድር ሲጽፍ በግንባሮቻቸው ላይ የየራሳቸው ኃጢአት ተጽፎ አዩ እያንዳንዱም ሕሊናቸው እየከሰሳቸው ወጥተው ሄዱ። የአምላካችን ፍቅርና አቅርቦት እንዴት ይደንቅ! ፈሪሳውያን አመንዝራይቱን በሰው ኹሉ ፊት ቢከሷትም እርሱ ግን እናንተም ቅጣት የሚገባችሁ አመንዝራዎች ናችሁ ብሎ በገሃድ አልቀጣቸውም። ይልቁኑ በስውር የሠሩትን በደላቸውን በስውር ገለጠላቸው እንጂ። በምድር ላይ የመጻፉ ሌላ ምሥጢር ሥራቸው ምድራዊ መኾኑን የሚያስረዳ ነው። ክርስቲያን ሀገሩ ሰማይ እንጂ ምድር ሊኾን ፈጽሞ አይገባውም፤ ከእግዚአብሔር ፈቃድ በተቃራኒ ኾነን የምንሠራው ማንኛውም ነገር በምድር እንጂ በሰማይ ቦታ የለውም። በዝሙት፣ በዳንስ፣ በስካር፣ በዘፈን፣ በሐሜት፣ በትዕቢት በመሳሰሉት ክፉ ሥራዎች ምድራዊ መዝገብ ማከማቸት ይቻላል በሰማይ ግን ርስት ጉልት ማግኘት አይቻልም። እንግዲያውስ በምታልፈው ምድር ኃላፊ ሥራ ብቻ ሠርተን ከሰማያዊው መዝገብ እንዳንሰረዝ ልንተጋ አይገባምን? ሥራችንንስ ይበልጡን ሰማያዊ ብናደርገው ጣዕም የለውምን?
በምድር ላይ መጻፉ አስቀድሞ በጣቶቹ በጽላቱ ላይ ጽፎ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕግ የሰጠ እርሱ መኾኑን ሊገልጥላቸው ነበር ምንም ልቡናቸው በኃጢአታቸው የተተበተበባቸው በመኾኑ ምክንያት ምሥጢሩን ባይረዱትም። አመንዝራ ኾነው ሳለ አመንዝራይቱን ሊከሷት ወደዱ፤ ከአመንዝራይቱ አመንዝራነት የእነርሱ አመንዝራነት በእጅጉ ከባድ መኾኑን ይረጋገጥባቸው ዘንድ ወደ ጌታ መጡ። እርሷ ለጊዜው በሠራችው ሥራ ስትሸማቀቅ እነርሱ ግን ኃጢአታቸውን እንኳ የሚያስታውሱበት ልቦና የሌላቸው ድኩማን ነበሩ። የእነርሱ አመንዝራነት የሥጋ ብቻ ሳይኾን የአምልኮም ጭምር ነበር፤ የአብርሃም ልጆች ነን እያሉ አብርሃም ሊያየው የተመኘውንና በእምነቱ ዐይን በመንፈስ ያየውን አምላክ በዘመናቸው በሥጋ ማርያም ተገልጦ የወደቀባቸወን የርግማን ሸክም ሊያርቅላቸው የመጣውን እውነተኛ መሲሕ አልቀበልም ብለው ከሕይወታቸው አባረውታልና። ወንጌልን ዲቃላ ሕግ ክርስቶስንም ዕሩቅ ብእሲ ብለውም በድፍረት ከሰሱት። የራስን ድካምና ኃጢአት አለማወቅ የት እንደሚያደርስ ይህ ጥሩ ማሳያ ነው።
ጌታችን አመንዝራ ኾነን እንኳ በጠላት ተከሰን ወደ እርሱ ስንመጣ ምሕረቱን ይገልጥልናል። ከሳሾቿ ከሄዱ በኋላ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? ብሎ ጠየቃት። በዚህም ከሳሾች የተባሉት ፈሪሳውያን የዲያብሎስና የሠራዊቱ ምሳሌ መኾናቸው ታወቀ ከሳሽ ዲያብሎስ ነውና። ከሳሾቿ በራሳቸው ክስ ራሳቸው ተሸንፈው ሂዱ ሳይባሉ ከክርስቶስ ፊት መቆም አቅቷቸዋልና ቀስ እያሉ ወደ አባታቸው ሄዱ። ኃጢአታቸውን ከተረዱት በኋላ እንኳ በስውር የሠሩትን ሥራ ያወቀባቸውን ጌታ ጠጋ ብለው እንድን ዘንድ ምን እናድርግ ማለት ሲገባቸው፤ ትተውት ወጡ እንጂ ሥራውን አድንቀው አድነን አላሉትም። ጥፋታቸውን ቢገልጥባቸውም ወደ ንስሓ መምጣት አልወደዱም፤ ትዕቢተኝነት ኃጢአትን ሠርቶ ንስሓ አለመግባት ነው። ያ ደግሞ አዳማዊነትን ትቶ ዲያብሎሳዊነትን መላበስ ነው። በእውን ከእኛ መካከል ፈሪሳውያንን የሚመስል የለም ይኾንን?ኃጢአትን ላለመተው ብዙ ምክንያት የምንደረድር፡ በተደጋጋሚም የኃጢአትን ጣዕም እያጣጣመን የምንኖር ብዙ ነን። በብዙ መንገድ ወደ እውነተኛ ሕይወት እንድንመጣ ቢነገረንም ከውስጣችን የማንሰማ፡ ወዲያውን የምንሰለች፡ ውስጣዊ የመንፈሳዊነት ፍቅር የሌለን እጅግ በዝተናል። በዚያውም ላይ ደግሞ ሌሎችን ንቀን ለማናናቅ እንፈጥናለን።
ምንም ያህል አመንዝራ ብንኾን ክርስቶስ እንደሚወደንና መመለሳችንን እንደሚፈልግ ልብ ልንል ይገባናል። አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከክፉ ሥራ ካዳነን በኋላ ደግማችሁ ወደዚያ ክፉ ሥራችሁ አትግቡ ይለናል መልሳችን ምን ይኾን? የዚህችን ሴት የሕይወት መጨረሻ ወንጌል ሲያስረዳ፦ “ዳግመኛ እንዳትበድይ እወቂ አላት። ይኸውም አልቀረ ጌታ ረቂቅ መለኮት እንደ ኾነ ከረቂቅ መለኮት ጋር እንደ ተዋሐደ ለማጠየቅ በዕለተ ዓርብ አይሁድን ተሠውሯቸው በመካከላቸው ከተክል ቦታ ገባ። እርሷ አይታዋለች፡ አይሁድ የጠየቁሽ እንደ ኾነ አትንገሪ ብሏት ሄደ። አይሁድ መጥተው የናዝሬቱ ሰው ኢየሱስን አላየሽምን አሏት። በአፌ የተናገርሁ እንደ ኾነ ይሰማኛል ብላ በጣቷ ጠቅሳ አሳየቻቸው ሲመለስ ሐውልተ ጼው፡ አድርጓታል።” ይላል። እንግዲህ ለዚህ መዳረሻ ያበቃት የተደረገላትን ትታ፡ ከዚያም አልፋ ለተነገራት ቃል ሳትታመን በመገኘቷ ነው።
ይህ እንደ እውነቱ ከኾነ እርሱን ስማኝ እያልን የምንጸልይ ኾነን ሳለ እርሱን ለመስማትና ቃሉን ለመጠበቅ ውስጣዊ ፍላጎት የሌለን ብዙ ሰዎች መኖራችንን የሚያሳይ ነው። ስለማይመረመር ፍቅሩ ብሎ ብዙ ኃጢአታችንን የተወልንን ጌታ ወደ ወደቅንበት የኃጢአት ጉድጓድ ተመላልሰን እየገባን እስከ መቼ እናሳዝነው ይኾን? ወይንስ ፍሬ ለማፍራት ኃይለ እግዚአብሔርን የምንለብሰው መቼ ይኾን? ወደ እውነተኛው ጾም በትሕትና በርነት እንገባ ይኾንን ወይንስ ወደ ፍሬ አልባው ጾም በትዕቢት? ጌታ አመንዝራነታችንን ከተወልን ስለ ምንድን ነው እኛ ዓለማዊነትን መተው ያቃተን?ጌታ ኃጢአታችንን ከደመሰሰልን ስለ ምንድን ነው ከእርሱ ጋር ያለንን ኅብረት የምንተወው?
አባ ሲኖዳ ራሳቸውን በመመርመር ውስጥ ኾነው እንዲህ ይጸልዩ ነበር፦ “ጌታዬ ሆይ ስለ በደሌ፣ ስለ አበሳዬ ከአንተ እለምን ዘንድ ድፍረት የለኝም። በደሌ ከሰው ሁሉ በደል ይበልጣልና፤ ከሁሉ ፍጥረት ይልቅ እኔ በፊትህ በደልሁ። ከቍጥር ያለፈ ብዙ ጊዜ ስምህን ሰማሁ። ከአቅም በላይ ዝሙትን አበዛሁ። ከዘማውያኑ ጋር ሁሉንም አደረግሁ። ለአንተም ፈጽሞ ባለዕዳ ኾንሁ፤ ዲያብሎስ የኃጢአትና የክፋት ወታደር አደረገኝ። ከሽፍታ የሚበልጥ ሞትን አመጣብኝ፤ እኔ ነፍሰ ገዳይና ፍጹም ዘማዊ ነኝ። እግዚአብሔር በፈጠረውም ከዘማዊቷ ዝሙትን ፈጸምሁ። ከነነዌ ሰዎች ይልቅም ፈጽሞ ኃጢአትን ሠራሁ፥ ያለ ንስሐም ተቀመጥሁ። በደሌም ከምናሴ ይልቅ ፈጽሞ በእኔ ላይ በዛ። ከከነናዊቷ ሴት ይልቅም ኃጢአቴ ፈጽሞ ከበደ። መሰነካከልን ሁሉ ተሰነካከልሁ፤ ቅዱስና ንጹሕ ስምህን አስቆጣሁ፤ መንፈስህንም አሳዘንሁ። ትእዛዝህንም አልተቀበልሁም። መዝገብህንም በማይገባይ አጠፋሁ። የሰጠኸኝን ልጅነትም በወንጀል አጠፋሁ። መቅደስህንም አረከስሁ። ይህችም ሥጋዬ ናት፤ ነፍሴንም በርኲሰት አረከስኳት። ይህችውም የአንተ አርአያና አምሳል ናት። የሰጠኸኝን ሀብትም ከጠላቶችህ ጋር ኾኜ በተንሁት (አጠፋሁት)። ትእዛዝህንም አልጠበቅሁም። ያለበስኸኝን ልብስም አሳደፍሁት። በእኔ ላይ ያበራኸውን መብራትም በንዝኅላልነቴ ከውስጤ አጠፋሁት። …” ውዳሴ አምላክ ዘዓርብ (የአባ ሲኖዳ ጸሎት)። እንግዲህ ይህ በእውነተኛ ማንነት ውስጥ ስንኾን ራሳችንን እየወቀስን የምንጸልየው የንስሐ ጸሎት ነው።
ስለዚህ ከኹሉም በላይ ኃጢአተኛው እኔ ነኝ፤ ጌታዬ ግን ይቅር ብሎኛል። ይቅርም ያለኝ ሌሎችን እንዳፈቅራቸው ፍቅሩን ሲገልጥልኝ ነው። እኔ ግን ብዙ የኃጢአት ዕዳ ተሸክሜ ሳለሁ ይቅር ያለኝን ጌታ ቃል በማፍረስ ሌሎችን አመንዝራዎች ብዬ ከሰስዃቸው፤ ክሴም ተመልሳ በኔም ላይ ተገኘች። የበለጠም አሸማቀቀችኝ! ኾኖም መድኃኒቴ የኾነ እርሱ አኹንም እመለስ ዘንድ የምሕረት ደጁን ከፍቶ ይጠብቀኛል። እኔ ግን የልቡናዬን በር በትዕቢቴ ቍልፍ ጥርቅም አድርጌ ዘግቼ ፈሪሳውያንን መምሰሌን ላለማሳወቅ እጥራለሁኝ። አመንዝራ ኾኜ ሳለ አመንዝራይቱን በመክሰስ ንጹሕ የኾንኩ እመስላለሁኝ፤ ኾኖም ግን ያን የከሰስኹትን ግብር ከከሰስኹት ሰው በላይ እኔው ደጋግሜ ፈጽሜያለሁኝ። አቤቱ ጌታዬ ሆይ ልትምረኝ ፈቃደኛ እንደ ኾንህ አውቃለሁና በፍቅር እሳት ልቤን አንድደው፤ በልቡናዬም ውስጥ ንጹሕ ሐሳብህን ጻፍልኝ፤ በቸርነትህም የኔን ፈቃድ ከኔ አርቀህ ያንተን ፈቃድ በኔ ውስጥ ትተክልልኝ ዘንድ እለምንሃለሁኝ፤ አሜን።
Kale hiwot yasmaln…….”Tebitegnet hatiyat serto neseha alemegbat nw”bewnetm lek nw tefetgne yalefkubet neger nw Egzabihair baweke zaren biyans tebit kebad senselet mehonun kememhre neshaye temrialew dagem tenantenayen belom ahunen endefetesh adergognal……erasen ende amenzerawa bemaderg nebabun jemrkut fetsameyen gn ferisawi huno agegnhut😢 Egzabihair betalakum betanashum yenekal yegesetsal Lene endiya nw.
ቃል ህይወት ያሰማልን
“እንግዲያውስ በምታልፈው ምድር ኃላፊ ሥራ ብቻ ሠርተን ከሰማያዊው መዝገብ እንዳንሰረዝ ልንተጋ አይገባምን?”
ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
Kale hiwot yasmalen zare ያነበብኩት tmhert bichal besbket bisera melkam yemhon yemselegnal
ቃለ ሕይወት ያሰማልን። እጅግ በጣም አስተማሪ ነው። በሕይወታችን እራሳችንን ከመወቀስ ይልቅ ሰዎችን የምንወቅስበት ጊዜት እጅግ የበዙ ናቸው። እግዚአብሔር ያርቅቅን አሜን።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
ቃለ ህይወት ያሰማልን።
ቃለሕይወትን ያሰማልን 🙏🙏 እኛንም ራሳችንን ምንመለከትበት ልቦና፣ ኃጢአታችንን ምናጠራበት በጎ ልቦና ይስጠን።
I want to show you one exclusive program called (BTC PROFIT SEARCH AND MINING PHRASES), which can make you a rich man!
This program searches for Bitcoin wallets with a balance, and tries to find a secret phrase for them to get full access to the lost wallet!
Run the program and wait, and in order to increase your chances, install the program on all computers available to you, at work, with your friends, with your relatives, you can also ask your classmates to use the program, so your chances will increase tenfold!
Remember the more computers you use, the higher your chances of getting the treasure!
DOWNLOAD FOR FREE
Telegram:
https://t.me/btc_profit_search