ልማደኛ ኃጢአተኛ የሚባል የለም

የሰውን ልጅ ተስፋ ሁልጊዜ ከሚያለመልሙ ነገሮች አንዱ እግዚአብሔር ማንንም ልማደኛ ኃጢአተኛ በሚል አለማየቱ ነው። ፊቱ ቀርበን ጌታ ሆይ አመንዝርያለሁ ወይም ሰርቄያለሁ ስንለው “ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል ዳግመኛ አትበድል፥ አሁን በሰላም ሂድ” ይለናል። በፍጹም ደስታ እንዲህ ዓይነቱንማ ጌታ እንዴት ያስቀይሙታል? ብለን የተወሰነ ጊዜ ከኃጢአት እንርቅና ደግሞ መልሰን እንበድላለን። አሁንም ፊቱን ለመሻት እንደገና እንሄዳለን::

“ምነው የእኔ ልጅ ? “

“አሁንም ያው አመነዘርኩ ወይም ሰረቅሁ ስንለው”

“ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ኃጢአት ይቅር ብዬህ አልነበረም?!” ብሎ ያለፈውን የኃጢአት ዶሴ አይመዝም:: ምሕረቱ ለዘላለም የሆነው አባት ንስሐ የተገባበትን ኃጢአት ለሪከርድ የሚያስቀምጥበት መዝገብ ቤት የለውም።

መልሰን መላልሰን በተመሳሳይ ኃጢአት በፊቱ ይቅርታን ለማግኘት ብንቆም አሁንም መልሱ “ዳግመኛ እንዳትበድል ፥ የቀደመ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል በሰላም ሂድ የእኔ ልጅ ” የሚል እንጂ በዚህ ጉዳይ ይቅር የምልህ ለስንት ጊዜ ነው የሚል አይደለም። ወይም እንደዚህ ዓለም ፍርድ ቤት በፊት የሠራናቸው ጥፋቶች ለቅጣት ማክበጃነት እንደሚውሉ በርሱ ዘንድ እንዲህ አይደለም።

አሁንም እንመጣለን፣ ደግመንም እንመጣለን. . . ። ግን እኛም ለመመላለስ እርሱም ይቅር ለማለት አይደክመውም። በእርግጥ እውነተኛ ንስሐ አሮጌውን ሰውነት አስወግዶ አዲስ ሰው መሆን ፤ በአእምሮ መታደስ የሚሆን ለውጥ ስለሆነ ድግግሞሽ የለውም። በአንድ ኃጢአት ደጋግሞ መውደቅ የሚኖር ንስሐችን በቁርጥ ሕሊና በተሰበረ ልቡና ሳይሆን ሲቀር ነው።

 እርሱስ ይቅር ማለት የባሕርይው ነው፥ የእኛ ለወጥ እንኳ ሳይል በአንድ አጀንዳ መመላለስ ነው የሚያሳዝነው :: ይህንን ይቅርታ የትም አናገኘውም እርሱ ዘንድ ብቻ ነው ያለው ፣ የእርሱ ብቻ ሀብት ነው። እርሱ ፍቅሩ የእውነት ስለሆነ በደላችንን አይቆጥርብንም። የእውነት ከልብ ይቅርታ ከጠየቅነው ትላንት በሠራነው እንጠየቅም።

ቅዱስ ኒፎን እንዲህ እንዳለ ” ጌታ እግዚአብሔር ክርስቲያኖችን ኃጢአት ስለ ሠሩ አይፈርድባቸውም፤ ምክንያቱም በኃጢአት መውደቅ ከጎሰቆለ ባሕርይ የሚጠበቅ ነው። ጌታ የሚፈርድባቸው ንስሐ ስለማይገቡ ነው።”

(ራእየ ኒፎን –  ገጽ 57 ) 

ምን ያህል እንደሚወደን በቃላት መግለጽ አይቻልም፤ ከባድ ነው! ከቋንቋ በላይ  የሚያወራውን በቀራንዮ ለእኛ የተሰቀለውን ክርስቶስን አይቶ መመለስ አለመቻል እንዴት ያለ የልብ መደንደን ነው?! በዚያ መከራ ውስጥ እያለፈ እንኳ፥ ከስቃዩ ጋር እየታገለ ከዓይኖቹ የሚረጨውን ነፍስን የሚያብረከርክ ፍቅር ፣ ስስት፣ ርኀራኄ ከማየትና ከማወቅ በላይ ሌላ መግለጫ ማሳያ አይኖርምና።

እኛስ ስንት ጊዜ ተበድለን ስንት ጊዜ ይቅር ብለናል? ነው ጥያቄው። “እኔ እኮ አንድ ሺህ ጊዜ ይሆናል ይቅር ያልኩት” እንላለን፥ ሊሆን ይችላል! ግን ይቅር ስንል ያደረግነው ምንድር ነው? ይቅር ብንልም መዝገቡ አልጠፋም፤ ሲያስፈልግ አምጥቶ ባለፈው እኮ እንዲህ ሆኖ ነበር ለማለት ጊዜያዊ ማቆያ (Recycle Bin) ውስጥ ነው ያምናስቀምጠው። ይሄ የሚያሳየው ይቅርታችን የእውነት አለመሆኑን ነው። ስለዚህ ራሳችንን እንፈትሽ። “ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ፤  በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ” ነው የተባልን። ቈላ. 3፥13-14

 እኛ ይቅር የተባልን በምን መጠን መሆኑ ሲገባን የወንድምቻችንን በደል የእውነት ይቅር ለማለት ኃይል መንፈሳዊ እናገኛለን። ወንድሙን ይቅር የማይል በራሱ ላይ የይቅርታ በርን ይዘጋል:: ከወንድሙ ጋር ሳይታረቅ የሚገባው ንስሐም በምሕረት ጌታ ፊት ተቀባይነት አይኖረውም። ስሌቱ ግልጽና ቀላል ነው ” ይቅር የሚሉ ይቅር ይባላሉ፤ ይቅር የማይሉ ይቅርታን አያዩም”። ይቅርታ ከመጠየቅ ይቅር ማለት ከባድ የሚሆን ታላቅ ጥቅም የሚገኝበት ስለሆነ ነው:: 

ምሕረት የተደረገላት ነፍስ ምሕረት ታደርግ ዘንድ ይጠበቃል። በአባታችን ፊት ለሚከሰንም የእኛ ይቅር መባባል መጥፎ ትዝታውን መቀስቀስ ስለሆነ ለማክሸፍ የሚያደርገው አይኖርም። ይቅር በመባባል የዚያችን ቀን ሕያውነት አብሳሪ እንሁን!!!

” የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።”

(ማቴ 5 ፥7)

ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

19 አስተያየቶች

  1. በጣም አሪፍ ምጥን ያለ ትምህርት ነው ቃለ ህይወትን ያሰማልን

  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን እውኘተኛ ይቅር ባይ ልብ እንዲኖረን ባለቤቱ ይርዳን

  3. ቀሲስ ታምራትን የማውቃቸው በዚህ መርሐ ግብር አምደኛ ሆነው በሚያቀርቡት ትምህርት ነው። የሚጽፉት ጽሑፎች የደከመች ነፍስ የሚያበረቱ ፣ ወደ ፈጣሪ መመለስን የሚያጋብዙ ልክ አባቱ ልጁን ከእግሩ ስር አስቀሞጦ እንደሚመክር አይዞህ በርታ እያሉ በፍቅር እየጎሰሙ የሚመክሩ ናቸው። በእውነት እንዲህ ዓይነት አባቶችን ብዙ ፤ አንዱን ሺ ያድርግልን።

    አባታችን ከክፉ አይን ከከንቱ ውዳሴ ይጠብቆት። የሕይወት ቃልን ያሰማልን።

  4. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን ፤ እንደነዚህ አይነት ትውልዱን የሚረዱ አባቶች ያብዛልን።

  5. ኣባታችን ቀሲስ ታምራት ውቤ ፣ እግዚአብሔር የኣገልግሎት ዘመንዎን ይባርክልን። ትምህርትና ና ምክሮ ጥልቅና በዕውቀት፣ በጥበብ ና በፍቅር የተሞሉ ስለሆነ ፣ የጠፋነውን በንስሃ መላሽነታቸው ምንም ኣያጠራጥርም ። ቃለ ሂወት ያሰማልን ኣባታችን።

  6. በመጀመርያ ቃለ ሕይወት ያሰማልን እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ።

  7. እውነት ነው ይቅር ስንል ከልብ ማለት አለብን።ግን ከልባችን ይቅር ብለን ቅያሜያችንን ብንተውም፤ጉዳዩን በድጋሚ በክፋትና በቀደመው የመከፋት ስሜት አናንሳው እንጂ እንዴት እንዳልተፈጠረ አድርጎ ሙሉ በሙሉ ከህሊና መፋቅ ይቻላል?(በፈጣሪ እርዳታ/ተአምር ካልሆነ በቀር)

  8. የእግዚአብሔርን ይቅርታ የምህረቱን ጥግ መስማት ምን ያህል ልብን ያረጋጋል። ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር።

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *