የጌታን ቃል ማን ያምነዋል? የመልዕክተኞቹን ምስክርነትስ ማን በሚገባ ይቀበለዋል? ለዚህም ነው ከነቢያት እስከ ሐዋርያት ድረስ “እግዚኦ መኑ የአምነነ ስምዐነ፤ አቤቱ ብንናገርስ ምስክርነታችንን ማን ያምነናል?” እያሉ የተናገሩት። ከነቢያት ኢሳይያስ ከሐዋርያት ዮሐንስና ጳውሎስ ይህንን ቃል ጠቅሰውታል። ኢሳ  53፥1፣ ዮሐ 12፥38፣ ሮሜ 10፥16

ከመጀመሪያዎቹ እስከመጨረሻዎቹ የእግዚአብሔር መልዕክተኞች ድረስ ይህ ቃል ደጋግሞ መጠቀሱ ለምን ይመስላችኋል? ቃሉን ከመስማት የመልዕክተኞቹን ምስክርነት አምኖ ከመቀበል መዘግየታችንን የሚያሳይ አይመስላችሁም?

ቃሉን ለማንበብ ብንፈጥንም ቃሉን ለማመን ግን የዘገየን መሆናችንን ከሚረጋገጥባቸው አንዱ “እናንተስ አስቀድማችሁ ጽድቁንና መንግሥቱን ፈልጉ ይህ ሁሉ ይጨመርላችኋል” ሉቃ 12፥31 የሚለው ነው። ይህ ትምህርት ከተሰበከ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝን በመርሳታቸው የገሠጻቸው የመሰላቸው ቀን ነበረ ማቴ 16፥7 በእንጀራ ምክንያት ጉባኤው እንዲፈታ ሀሳብ ያቀረቡበትም ጊዜ ነበረ ማቴ 14፥15 ከተጠሩት ሰዎች መካከልም አንዳንዶቹ ወደ ንግዳቸው፣ አንዳንዶችም ወደ እርሻቸውና ልባቸው ወደ ፈቀደው መሄዳቸው የተነገረው ይህን ትምህርት በመርሳት ነው ማቴ 22፥5

የተወደዳችሁ ወንድሞችና እኅቶች ሆይ! እውነቱ ግን እንዲህ ነው፦ እኛ የታዘዝነውን ስናደርግ እግዚአብሔርም የተናገረውን ማድረግ ይጀምራል። ነገሮችን ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ከመውረስ አንጻር ስናደርጋቸው እግዚአብሔር ምድርን ጨምሮ ያወርሰናል። አብርሃም ያመነው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንዲቆጠርለት እንጅ ዘሩ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ እንዲበዛለት ፈልጎ አልነበረም። እግዚአብሔር ግን ለአብርሃም ያደረገውን ተመልከቱ መቆጠር የማይችል ዘር እንዲኖረው አደረገ። እኛ የሰማዩን ክብር ፈልገን ቃሉን ማድረግ ስንጀምር ያልፈለግነው ምድራዊ ክብርም ተከትሎ ይመጣል። ሐዋርያት “ሑሩ ወመሀሩ” ያላቸውን ለመፈጸም እንጅ ይህንን አስበው ወደ ልስጥራን የገቡ አልነበረም እግዚአብሔር ግን በልስጥራን ከተማ ከሰው የተለዩ አማልክትን መስለው እንዲታዩ አደረጋቸው ሥራ 14፥11

ቢያስፈልግ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ይጨምራል። ሙሴ በግብጽ ሲኖር የፈርዖን የልጅ ልጅ ነበረ ከግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ሲመጣ ግን የፈርዖን አምላክ ሆነ ዘፀ 7፥1። ከነበረው ይልቅ የተጨመረው ነገር አይበልጥም? የመታዘዝን ጥቅሙን የማመንን ዋጋውን ተመልከቱ። መንግሥተ ሰማያትን ፍለጋ ወጥተው ይህ ዓለም የተጨመረላቸውን ሰዎች አስቡ። አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ሞተሎሚ ከተማ የገቡት ወንጌልን አስተምረው ለሐዋርያት ከተዘጋጀው በረከት ለማኘት እንጅ የዳሞት ንጉሥ ሊሆኑ አልነበረም ነገር ግን ከተደረገው ተአምር የተነሣ ንጉሡ የመንግሥቱን እኩሌታ እስከመስጠት ቃል ገብቶላቸው እንደነበረ በገድላቸው ላይ ተጽፏል። የምንፈልገው የላይኛውን ከሆነ የታችኛው ተጨምሮ የሚሰጥ ስጦታ ነው። እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ብቻ ያዘጋጀው ስጦታ የላይኛው ነው የታችኛው ለሁሉም የተሰጠ ነው። የሰዎችስ ይቅርና ለእንስሳት ሳይቀር የሰጠውን ዓለም ቢሰጥህ ምን ይገርማል? የዚህ ዓለም ገዥዎች የትኛውንም ያህል የተፈሩ የተከበሩ ቢሆኑ የአንበሳን ያህል ክብርና ግርማ የላቸውም። 

አንባሳ ዐዋጅ ነጋሪ ሳይልክ ተዋጊ ሠራዊትም ሳያሠማራ አራዊት ሁሉ ተገዝተውለት የሚኖር ፍጥረት ነው። የምድር ነገሥታት ቢጨንቃቸው ምልክታቸውን የአንበሳ ምስል ያደርጋሉ። በፈረስ ተጭነው እየሄዱ የአንበሳ ምስል አሠርተው እንደ አንበሳ እንድንፈራቸው ይፈልጋሉ።

ለማንኛውም ወንድሜ በዚህ ዓለም የትኛውም ክብር ቢሰጥህ እንዳይገርምህ ምንም ብታውቅ እንደ እባብ ራስህን የምታድስበት ጥበብ የለህም። ምን ሀብት ብታከማች የሞት መድኃኒት መግዣ አይሆንህም። እጅግ ያማረ መኝታ ላይ ብትጋደምም ከአስፈሪ ሕልም ነጻ አያደርግህም። የተሰጠህን ነገር በሙሉ መርምረው ከእንስሳት ከአራዊት የበለጠ ስጦታ ካለህም የሚኖርህ አንድ ነገር ብቻ ነው፥ እሱም ሰማያዊነትህ ብቻ ነው። 

ከዚያ ውጭ ያለውን ተወው ካንተ የተሻለ ለሌሎችም ፍጥረታት ተሰጥቷቸዋል። ያማረውንና ጌጠኛውን ብትለብስ ከእንስሳት ወይም ከምድር እጸዋት አዘጋጅተህ ነው። በወርቅና በብር ብታጌጥ ከምድር ውስጥ አውጥተህ ነው። ይህ ሁሉ እግዚአብሔር ሊጨምርልን ካሰበው ነገር ጋር ሲነጻጸር ጥቂት ነው። ይህንን ማድረግም ለኛ የተከለከለ አይደለም ይልቁንም ስለምንበላውና ስለምንጠጣው እንዲሁም ስለምናጌጥበትና ሰልሽልማታችን ስንጨነቅ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መትጋት እንዳይቀርብን ነው እንጅ።    

ይልቁንም ጽድቁንና መንግሥቱን ስንፈልግ ሳለን ያላሰብነው ጸጋ ሲጨመር ለኛም ለሌሎችም አስደናቂ ሆኖ ይኖራል። በእግር መራመድ ለሁሉም የተፈቀደ ነው፤ ጽድቁንና መንግሥቱን ፍለጋ ስትጀምር ግን በክንፍ መብረር ይጨመርልሃል። በሰው ልሳን መዘመር ስትጀምር በመላእክት ልሳን ማመስገን ይሰጥሀል። ዛሬ እንደምንም ብለህ ከፍቅረ ንዋይ ራስህን አውጥተህ ምጽዋት ብትጀምር መጥዎተ ርዕስ {ራስን መስጠት} ይጨመርልሀል። አንጢላርዮስ እንኳን ራሱን፥ ገንዘቡን የማይሰጥ ንፉግ ባለጠጋ ነበረ። ከዕለታት በአንድ ቀን ገንዘቡን መስጠት ቢጀምር ራሱን እስከ መስጠት አደረሰው። ገንዘቡን መጽውቶ ሲጨርስ ራሱን ሽጠው ነዳያን እንዲካፈሉት ፈቀደላቸው።

ክርስትና ፍጹምነትን የምታመጣው እንዲህ ስትሆን ነው። የክርስቶስ ደቀ መዝሙርነትን ስትጀምር ክርስቶስን መምሰል ይጨመርልሀል። በእግር መከተል ስትጀምር በግብር መምሰል ይሰጥሀል። በተራራው ስብከት ጉባኤ ላይ ስትገኝ በጽዮን ተራራ ሲገለጥ በክብር መገለጥ ይፈቀድልሀል። በሐሙስ ምሽቱ የጌታ ራት ላይ ከይሁዳ የተለየህ ሁነህ ከተገኘህ በመጨረሻው ቀን በሚደረገው የበጉ ሠርግ ላይ መጋበዝህ አይቀርም ራዕ 19፥7። ከተሰጠን ይልቅ የሚጨመርልን ይበልጣል። ከዕውቀትም ዛሬ የምናውቀው የተከፈለ ነው በኋላ የሚጨመርልን ዕውቀት ምን ዐይነት እንደሆነ ዛሬ ባናውቀውም ያንጊዜ ተከፍሎ የነበረው ሁሉ ይሻራል 1ቆሮ 13፥9። ዛሬ በድንግዝግዝ እንደሚያይ ሰው እናያለን በኋላ ግን ዙፋኑን በፊት ለፊት ማየት ይጨመርልናል።  

እኛ ግን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንዳስተማረው ቃሉን ለውጠን ተቸግረናል። ዋናውን ስጦታ ፍለጋ ላይ ሳንሆን ተጨማሪውን ነገር ፍለጋ ላይ ነን። በዚህ ዓለም ያለው ማንኛውም ክብር ሁሉ ሹመትም ቢሆን ሽልማትም ቢሆን በምድር ላይ ክብር ሁሉ ቢጨመርልን የምንቀበለው እንጅ መደበኛ አድርገን የምንፈልገው ስጦታ አልነበረም።  ለዚህ ነው ሊቁ ዕብራውያንን መልዕክት በተረጎመበት ድርሳኑ እንዲህ ብሎ ያስተማረው፦ “ንሕነሰ ወለጥነ ትምህርተ እግዚእነ ዘይቤ አንትሙሰ ኅሡ መቅድመ መንግሥቶ ወጽድቆ በእንተዝ ኢንረክባ ለይእቲ ወኢንረክባ ለእንታክቲ፤ እኛ ግን ጌታ እናንተስ አስቀድማችሁ ጽድቁንና መንግሥቱን ፈልጉ ያለውን ትምህርት ለወጥን ስለዚህ ይህችንም ያችንም አናገኛትም” አለ።

አምላካችን ለቃሉ የታመነ ነው። በመጽሐፍ የተጻፈውን ፈቃዱን ለሚያደርጉ ሁሉ በመጽሐፍ የተጻፈውን በረከት ይጨምርላቸዋል። ከሰው ጉልበት የእግዚአብሔር በረከት ይበልጣል። ሙሴ በበትሩ ብቻ የጠበቃቸውን ሕዝቦች የዛሬ መሪዎች በዘመናዊ የተራቀቀ መጠበቂያ ሊጠብቋቸው አልተቻላቸውም። ኢያሱ የጠላት አጥር ጥሶ ያወረሳቸውን አገር ጠላት አጥራቸውን አፍርሶ ወሰደባቸው። ይህን ምድር እስከ ደም ጠብታ ድረስ ብንፈልገውም ጽድቁንና መንግሥቱን መፈለግን ከረሳን ይህንንም ያኛውንም እናጣለን። ይልቁንም ይሄኛው ለበጎ አገልጋይ በደመዎዙ ላይ ጉርሻ እንዲጨመርለት አጥብቀን በምንፈልገው ሰማያዊ ስጦታ ላይ የሚያስፈልገን፥ ነገር ግን አስቀድመን ያልፈለግነው ምድራዊ ጸጋ እንዲጨመርልን አስቀድመን ጽድቁንና መንግሥቱን እንፈልግ። ይህ ሁሉ ይጨመርልናልና።    

ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ሰኞ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

12 አስተያየቶች

    • ”ነገሮችን ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ከመውረስ አንጻር ስናደርጋቸው እግዚአብሔር ምድርን ጨምሮ ያወርሰናል።”
      ቃለ ሕይወት ያሰማልን 🙏

  1. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
    ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥልን
    ልብስ የሚያድስ መንፈስን የሚያስደስት ትምህርት ነው።

    • ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
      ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥልን
      ልብን የሚያድስ መንፈስን የሚያስደስት ትምህርት ነው።

  2. የሕይወትን ቃል ያሰማልን
    እጅግ ጥኡም ትምሕርት ነው የምንፈልገውን ሳይሆን የሚያስፈልገንን አስተምረውናል
    በእድሜ በጤና ይጠብቅልን ሰኞን እንድናፍቅ ሆኛለው

  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህራችን
    ይህን የመሠለ ትምህርትም ከዚህ በፊት ዓውደ ምሕረት ላይ አስተምረው ነበረ እና video ላይ ብዙ ጊዜ ሰማዋለው በብዙ እንዳስብ እና ‘ ተስፋቹን ለዩ ‘ እንዳሉት ለካስ የኛ ተስፋችን አክሊል( መንግሥተ ሰማያት) ናት ብዬ እንዳስብ አርጎኛል ።
    እግዚአብሔር ይስጥልኝ

  4. ”ነገሮችን ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ከመውረስ አንጻር ስናደርጋቸው እግዚአብሔር ምድርን ጨምሮ ያወርሰናል።” 🙏
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን ያነበብነውን ለመኖር ያትጋን 🙏

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *