ብርሃኑ ጎበና – ከትናንት እስከ ዛሬ


“ብዙም የማልጽፈው ከእኔ የተሻሉ ጸሐፊዎች ስላሉ በሚል ነው”

መልአከ አርያም ብርሃኑ ጎበና

“ብርሃኑ ጎበና” በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው ቀደምት መምህራንና ጸሐፍት የአንዱ ስም ነው:: 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኬሚስትሪ ዲግሪያቸውን የሠሩት መምህር ብርሃኑ ጎበና 

“ዐምደ ሃይማኖት” “ፍኖተ ጽድቅ” “አናቅጸ ሲኦል” ወዘተ የተሰኙ በሳል መጻሕፍትን በማበርከትና ይታወቃሉ:: መልአከ አርያም ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና በአሁኑ ሰዓት በሰሜን አሜሪካ … አስተዳዳሪ ናቸው:: በጃንደረባው ሠረገላ ላይ የሚከተለውን ቆይታ አድርገዋል:: 

ጃንደረባው:- ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዴት ገቡ? 

መ/ አ ብርሃኑ ጎበና :- ያደግሁት አዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ ነበር:: ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት የገባሁት በአጥቢያዬ ቅዱስ ዑራኤልና ጊቢ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ:: አንድ ቀን በሰንበት ስንሔድ የመዝሙር ድምፅ ከአንዲት አዳራሽ ሰማን:: አስፈቅደን ገባን:: ዝማሬውን ትምህርቱን ሰማን:: እሑድ እሑድ የትምህርት ሰዓት መሆኑን ሰማንና ተመዘገብን:: 

በዚያም በጊቢ ገብርኤል ሰንበት ተማሪ ሆኜ በሰባዎቹ መጀመሪያ ገባሁ:: በሰንበት ትምህርት ቤትም በርካታ መንፈሳዊ ኮርሶችን የመማርና የትምህርት ክፍሉንም በሰብሳቢነት እስከ መምራት ድረስ አገለገልሁ:: ከዚህም በተጨማሪ ከተማሪዎች የሰበሰብነውን ጥያቄ እየያዝን በወቅቱ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ከነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩና ከተጠያቂው ሊቅ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዘንድ በመቅረብ ጥያቄዎችን እንጠይቅ ስለነበር ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነት ሃይማኖትን በጥልቀት የመማር ዕድል አገኘሁ:: በሒደትም የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢነትም በሰባኪነትም አገልግያለሁ:: 

ጃንደረባው :- ከማኅበረ ቅዱሳን መሥራቾች አንዱ እንደሆኑ ይታወቃል::  እንዴት ተጀመረ? የነበረዎት ቆይታስ ምን ይመስላል?

መ/አ ብርሃኑ ጎበና :- በ1980 ዓ.ም. የካምፓስ ተማሪ እያለን እኛ ባለንበት ዶርም ላይ የሃይማኖት ክርክር ተነሣ:: እኔ ቤተ ክርስቲያን እንደምሔድ ያወቀ ልጅ ወደ ክርክሩ ጋበዘኝ:: በዚያ ውይይት ላይ ከአንድ ሰው ክርክር ገጥመን እያለ ብዙ ተማሪ ቁጭ ብሎ መስማት ጀመረ:: ተከራካሪው ውይይቱን ረግጦ ሲሔድ ከተመልካቾቹ ጋር ለመወያየት ዕድል አገኘሁ:: በዚያም ለምን ሃይማኖታችሁን በአግባቡ አትማሩም የሚል ሃሳብ አነሣሁላቸው:: ከዚያም ተማሪ በሚገኝበት ቀን ቅዳሜ ቅዳሜ ከዐሥር ሰዓት በኋላ በማገለግልበት ጊቢ ገብርኤል እየመጡ መማማር ጀመርን:: 

አንድ ቀን በጊቢ ገብርኤል ዐውደ ምሕረት ሳገለግል የሚያውቀኝ ሰው ዩኒቨርስቲ መግባቴን ሲያውቅ ለምን የጽዋ ማኅበራችን ላይ ተገኝተህ አታስተምርም? አለኝ:: ብዙ ሲንየሮች ያሉበት የዶርም ፅዋዕ ማኅበር ሲሆን አንድ ጊዜ አራት ኪሎ አንድ ጊዜ ስድስት ኪሎ እየሔዱ የሚያካሒዱት ነበረ:: በዚያን ቀን ጊቢ ገብርኤል ጉባኤ መጀመሩን ስነግራቸው እኛም እኮ ምስካየ ኅዙናን ጉባኤ አለን አሉኝ:: ጉባኤውን በትብብር ለማድረግ ተስማማን:: በሒደትም ኮተቤ የሚማሩትን ፣ ሕንፃ ኮሌጅ የሚማሩትን እየጨመረ በሒደት ሁሉንም የሚያስተባብረው ማኅበረ ቅዱሳን ተመሠረተ:: 

በማኅበሩ በሰባኬ ወንጌልነት ፣ በሐመር መጽሔት አዘጋጅነት ፣ በማኅበሩ ሥራ አመራርነትም አግልግያለሁ:: 

ጃንደረባው :- ዐምደ ሃይማኖት እንዴት ተጻፈች?

መ/አ ብርሃኑ ጎበና:- በሰማኒያዎቹ ውስጥ በስብከተ ወንጌል በየአጥቢያው አገለግል ነበር:: በዚያን ወቅት በረከታቸው ይደርብንና አባ ኪዳነ ማርያም በኋላ አቡነ ያዕቆብ የጊቢ ገብርኤል ስብከተ ወንጌል ነበሩ:: እርሳቸው የብፁዕ አቡነ እንድርያስ ተማሪ እንደመሆናቸው ጥልቅ ትምህርት ያስተምሩ ሳለ ቁጭ ብዬ እማር ነበር:: ቀስ በቀስ የሰርክ ጉባኤን በየቦታው ማስተማር ጀመርሁ:: በወቅቱ የነበሩትን የሐሰት አስተምህሮ ለመግታት ዕቅበተ እምነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ትምህርቶች እሠጥ ነበር:: ብዙ ሰዎች በትምህርቱ ቢጠቀሙም በጽሑፍ እንዲቀርብ ይጠይቁ ነበር:: ልጅ ሆኜ የሥነ ጽሑፍ ችሎታውም ስለነበረኝ  በመጀመሪያ በበራሪ ጽሑፍ በኋላ በመጽሐፍ መልክ ዐምደ ሃይማኖትን ለማዘጋጀት ችያለሁ:: ጠቅላላ ሃሳቦችን ከያዘው ከዐምደ ሃይማኖት በኋላ በጥልቀት ጉዳዮቹ ላይ በተናጠል በማተኮር “ኆኅተ ሃይማኖት” “ፍኖተ ጽድቅ” “መራኄ ድኅነት” “አናቅጸ ሲኦል” “ቅዱስ ስምዖንና ሺኖዳ” “ፍጻሜ ዘመን” የሚሉ መጻሕፍትን ልጽፍ ችያለሁ::

ጃንደረባው :- ለስብከት አገልግሎት ከሰንበት ትምህርት ቤት ኮርሶች ባሻገር ከሊቃውንቱ እግር ሥር ቁጭ ብለው የመማር ዕድል ነበረዎት?

መ/አ ብርሃኑ ጎበና :- በጣም ጥሩ ነገር አስታወኸኝ:: ለእኔ የስብከት አገልግሎት ትልቁን መሠረት የጣሉልኝ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ነበሩ:: መምህር ቀጸላ ተብለው በሚጠሩበት ጊዜ የጊቢ ገብርኤልን ሰንበት ትምህርት ቤት የመሠረቱት እኚህ ታላቅ አባት በደርግ ዘመን በጵጵስና ተሹመው ከሚያገለግሉበት የጎንደር ሀገረ ስብከት በቤተ ክርስቲያንዋ በሌለ ሥርዓት  ጡረታ እንዲወጡ ተደርጎ ወደ ጊቢ ገብርኤል ና በአታ የበላይ ጠባቂ ሆነው ተመልሰው ነበር:: ብፁዕ አባታችን በአታ እያሉ ለሁለት ዓመት ያህል ያስተምሩን ነበር:: ከነአርዮስ ከነንስጥሮስ ጀምሮ የሚነሡ ጥያቄዎችን የሚመልስ ጥልቅ ትምህርት ያስተምሩን ነበር:: ማስተማር ብቻ ሳይሆን እሳቸው ባሉበት ቆመን እንድናስተምር ያደርጉን ነበር:: “እኛ ባለንበት አስተምሩ:: የተሳሳታችሁን እናርማለን:: የጎበጠውን እናቀናለን” እያሉ እንድናስተምር ያደርጉን ስለነበር ስለዚህ ሳንፈራ እናስተምር ነበር:: የሚቃና ነገር ካለ አንድ አባባል ነበራቸው “አንተ ጥሬ! እንዲህ በለው” 

ሊቃውንት ባሉበት ማስተማርን እንዳንፈራ አድርገው አሳድገውናል:: በዚያን ጊዜ እንዲያውም አንድ ነገር ገጥሞኝ ነበር:: ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ሳስተምር ርእሴ “ምሥጢረ ሥላሴ” ነበረ:: አንድ አሁን ሊቀ ጳጳስ አባት መጥተው “አንተ ደፋር እንዴት ሊቃውንት እንኳን የማይደፍሩትን ምሥጢረ ሥላሴ ብለህ እንዴት ታስተምራለህ?” ብለውኝ ነበር:: እኔም ከማን ተምሬ ድፍረቱን እንዳገኘሁ ነግሬያቸው ገርሞአቸው ነበር::  

እነአለቃ አያሌው እነ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁንም ለእኛ ትልልቅ መምህራኖቻችን ነበሩ:: የታላላቅ ወንድሞቻችን አስተዋጽኦም ቀላል አልነበረም:: እነጋሽ ታዬ ፣ እነጋሽ ተሰማ ፣ እነጋሽ ግርማ ፣ እነመልአከ ብርሃናት ጌታቸው ደጀኔ ፣ እነ ሊቀ ትጉሃን ጌጡ የኋላሸት በእኔ ሕይወት ውስጥ ብዙ ቦታ ያላቸው ናቸው:: ትምህርታቸውም ሕይወታቸውም በእኛ ዕድሜ ላለነው አስተማሪ ነበረ:: 

ጃንደረባው :- በዚያን ዘመን የነበረውን አገልግሎት ከአሁን ዘመን ጋር እንዴት ያስተያዩታል?

መ/አ ብርሃኑ ጎበና:- ሰማኒያዎቹ በመንፈስ መቃጠል የነበረበት የአገልግሎት ዘመን ነበረ:: በኮሚኒዝም እግዚአብሔር የለም የሚል አስተምህሮ የተነሣ የሆነ ክፍተት (Vaccume) ተፈጥሮ ነበር:: ሃይማኖተኛ መሆን እንደ ኋላቀርነት ይታይ ነበረ:: ሊቃውንቱን የሚያከብርም ወጣት አልነበረም:: የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆነን ዞረን ስንሰብክ ሕዝቡ ላይ ትልቅ ነገር ተፈጥሮ ነበር:: ከእኛ ቀድመው የተመረቁ ተማሪዎችም የእኛን ወጪ ይሸፍኑ ነበር::  ከአዲስ አበባ እየወጣንም እናገለግል ነበር:: በረሃብ በጥም ውስጥ ሆነን በፍቅር እናገለግል ነበረ::

አሁን ያለው አገልግሎት በትጋት የሚያገለግሉ እንዳሉ  ለተርእዮ ለታይታ ለጥቅም የሚያገለግሉም አሉ:: ያን ጊዜ ለመንፈሳዊ ዋጋው ተብሎ የሚገለገልበት ዘመን ነበር:: ለዚህ ዘመን አገልጋዮች  “እናንተ ጽድቁን እሹ ሌላው ይጨመርላችኋል” ተብሎ እንደተነገረ በትጋት ካገለገላችሁ እግዚአብሔር በሥጋ ከምንም ነገር አያሳጣችሁም ለማለት እወዳለሁ:: 

ጃንደረባው:- ከሀገር ከወጡ ወዲያ በአገልግሎት ላይ ምን ድርሻ አለዎት?

መ/አ ብርሃኑ ጎበና:- በኢትዮጵያ ሳለሁ በስብከትና በመጻሕፍት ብቻ በአፍአዊ አገልግሎቶች ላይ እሳተፍ ነበር:: ወደ ሰሜን አሜሪካ ከመጣሁ ወዲህ ግን አፍአዊውን ብቻ ሳይሆም በቤተ መቅደስ ውስጣዊ አገልግሎትም በመሥጠት ላይ እገኛለሁ:: በሜሪላንድ ግዛት የኆኅተ ምሥራቅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ስሆን በዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ደግሞ ዋና ጸሐፊ ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ:: 

የውጪ ሀገር አገልግሎት ብዙ ውጣ ውረዶች አሉበት:: ዝም ብሎ መቀደስ ብቻ አይደለም:: 

በአብዛኛው አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው ሕንፃ ቤተ መቅደስ የላቸውም:: ስለዚህ በሰዓት እየተከራዩ ይገለገላሉ:: ስለዚህ በየቀኑ መቅደስ መሥራትና መልሶ ማፍረስ የአገልግሎቱ አካል ነው:: ዝም ብዬ ሳስበው ከደብተራ ኦሪት የድንኳን አገልግሎት ጋር ይመሳሰልብኛል:: እስራኤላውያን በጉዞ ላይ እያሉ ሲጓዙ ይውሉና ድንኳን ይተክሉ ነበር:: እነርሱ ቢያንስ ትንሽ ይሰነብቱ ነበር:: የውጪው ዓለም ቤተክርስቲያን ግን በየቀኑ ትነቅላለች በየቀኑ ትተክላለች::  ዲያቆንም ቄስም ሰራዒም ንፍቅም ፍም የሚያጠምቅም አንድ ካህን ብቻ ሊሆን ይችላል:: ትልቅ ዋጋ ያለበት አገልግሎት ነው:: አንዳንድ አባቶች “ኢትዮጵያ መች አገለገልን? ያንን ቆጥሮ እዚህ እያስከፈለን ይሆን?” ይላሉ:: በዚያ ላይ በስትረስ ውስጥ ያለ ምክር የሚሻ ሕዝብ አለ:: ለአገልግሎት እንዲመቻቸው ደግሞ ለድጎማ ሥራ ይሠራሉ:: ስለዚህ የውጪው አገልግሎት በብዙ ውጥረት የተሞላ ነው:: 

ጃንደረባው :- ብዙ ጸሐፍት ወደ ውጪ ሲወጡ ብዕራቸው ይነጥፋል ይባላል:: እውነት ነው ይላሉ:::

መ/አ ብርሃኑ ጎበና:- አዎ እውነት ይመስላል:: ከራሴ ብነሣ ኢትዮጵያ ሳለሁ ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ዐሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ ሰባት መጻሕፍትን ጽፌ ነበር:: ወደ ሰሜን አሜሪካ ከመጣሁ ወደ ዐሥራ ስድስት ዓመታት ሆኖኛል:: የጻፍሁት መጽሐፍ የመጀመሪያውን ዐምደ ሃይማኖት የተሻሻለዕትም ብቻ መሆኑ የተባለውን ነገር እውነት ነው ያሰኘዋል:: ዋነኛ ምክንያቱ በውጪ ሀገር ያለው የአገልግሎት ውጥረት ነው:: ለመጻፍ ጊዜና የተረጋጋ ኅሊና ያስፈልጋል:: መጻፍ በራሱ ቀላል ነገር አይደለም:: ጊዜ የሚፈልግ ነገር ነው:: 

እኔ ያለሁበት አካባቢ ደግሞ የሜትሮፖሊታን አካባቢ እንደመሆኑ ብዙ ሐበሾች ይበዛሉ:: ስለዚህ  ቀዳሽነቱ ፣ ሰባኪነቱ ፣ አስተዳዳሪነቱ ፣ አማካሪነቱ ፋታ ያለው ሥራ አይደለም:: ካህን ሁሉ ጸሐፊ ላይሆን ይችላል ሰባኪ መሆን ግን ግዴታው ነው:: ቃለ እግዚአብሔርን ማስተማርና መቀደስ ክህነቱ የሚጠይቀው ሥራ ነው:: ስለዚህ ይህ ትልቅ ሓላፊነት ነው:: ከዚያ ባሻገር የቤተሰብ አስተዳዳሪነትም አለ:: ብዙዎቻችን አገልግሎት ስንጀምር ተቀጣሪ ሆነን ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን እስከምትደራጅ በውጪ ሥራ እየሠራንም ጭምር ነበረ::  አንድ ካህን ብቻ ያለበትም ደብር ይኖራል:: ሁሉንም አገልግሎት የሚፈጽመው እንግዲህ ያው አንዱ ካህን ነው:: ብዕር የሚነጥፈውም ለዚህ ነው::

ከዚያ ውጪ በአሁኑ ዘመን በጥልቀት የሚጽፉ ጸሐፊያን በርክተዋል:: እኔ በጻፍሁበት ዘመን የነበሩ ሊቃውንት ወዲያውኑ መልስ ቢጽፉ ኖሮ እኔ ባልጻፍሁ ነበር:: ሥራዬ ማዳረስ ይሆን ነበር:: እኔ የጻፍኩት ከቅናትና ያለኝን ከመወርወር አንጻር ብቻ ነበር:: አሁን ግን በእውቀት የበለጸጉ ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱንም ጠንቅቀው የሚያውቁ ጸሐፊያን በጣም በዝተዋል:: ይህም ሁኔታ እንዳትጽፍ ያደርግሃል:: “የሚገባው ነገር እየተጻፈ ወደ ሕዝቡ እየደረሰ ነው:: እኔ ምን የተለየ ነገር እጽፋለሁ” ያሰኝሃል:: ውስጥህን የሚያንጸባርቁልህና በተሻለ መልኩ የሚገልጹልህ ጸሐፍት ስታይ ዝም ትላለህ:: ብዙም የማልጽፈው ከእኔ የተሻሉ ጸሐፊዎች ስላሉ በሚል ነው:: የሌሎቹም እንዲህ ይመስለኛል::

Share your love

15 አስተያየቶች

  1. በጣም ድንቅ ቃለ መጠይቅ ነው:: ረጅም ዕድሜ ይሥጥልን:: ቃለ ሕይወት ያሰማልን::

  2. ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና በጣም የምናከብራቸው የምንወዳቸው አባታችንም መካሪያችንም ናቸው በአገልግሎታቸውም እዩኝ እዩኝ የማይሉ የነዋይ ሰው ያልሆኑ አስተምህሮታቸው እና አገልግሎታቸው የሚጣል የሌለው ነው እግዚአብሔር ወዶ እና ፈቅዶ የእርሶ የመንፈስ ልጆዎት እንድሆን ስለረዳኝ እግዚአብሔር ይመስገን የቅዱሳን አምላክ ከነመላው ቤተሰብኦ በህይወት በጤና ይጠብቅልን !

  3. በእውነቱ ለዚህኛው ትውልድ እንዲህ የቀደሙትን የማስተዋወቅ ስራችኹ እጅግ የሚበረታታ የሚደነቅ ነው። መምህራችንን በብዕር ስማቸው እንጂ እንዲኽ በጥልቀት አላውቃቸውም ነበረ። ሌሎች የጻፉትንም መጻሕፍት በተቻለኝ አቅም ፈልጌ ለማንበብ እሞክራለኹ። ምክንያቱም ዓምደ ሃይማኖት ለሌሎቹ ትልቅ መሰሶ አቁማ ሄዳለችና። ብዕር አይደርቅምና እግዚአብሔር ብርታቱን ጽናቱን ሰጥቶ ሌላም እንዲጽፉልን የእግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ይኹን እላለኹ። ቃለ ሕይወት ያሰማልን🙏🙏🙏

  4. የቅዱሳን አምላክ በእድሜ ፣ በጤና ይጠብቅልን። ቃለ ሕይወትን ያሰማልን።

  5. የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ማህበር ዘርፈ ብዙ ክርስቲያናዊ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ከነዚህ መሃከል ደግሞ በጃንደረባው ሚዲያ ላይ የሚወጡ የተለያዩ ሰባኪያነ ወንጌልና ፀሀፍት ከሚያካፍሉን ፅሁፎች በተጨማሪ እንደ መልአከ አርያም ብርሃኑ ጎበና ያሉ አባቶቻችን ክርስቲያናዊ ህይወታቸው እንድናውቃቸውን እና ከእነሱ ተመክሮ ልምድ እንድንካፈል ይረዳልና ይበል የሚያሰኝ ነው።
    ለሁላችሁም ቃለ ህይወት ያሰማልን ፤ አገልግሎታችሁን እግዚያብሄር ተቀብሎ ለበለጠ ስራ እንድትተጉ ይረዳችሁ ዘንድ ፀሎቴ ነው።
    እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

  6. በትውሉዱ ላይ በጎ አሻራ ለማሳረፍ በአለማዊ ትምህርታቸው ለስጋቸው የተሻለ ምቾት ያለውን ስራ ትተው በመንፈሳዊው አለም ለሌላው ወገናቸው ለመትረፍ የደከሙት መምህራችንን የበለጠ እንድናውቃቸው መደረጉ ተገቢነው።

  7. በጣም ደስ የሚል ቃለ መጠይቅ። ለመምህራችን እድሜ ከጤና ጋር ይስጥልን።

  8. ለመምህር ቃለ ህይወት ያሰማልን።
    የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እየሰራችሁት ላለው ትውልዱን ያማከለ ስራ ትልቅ ክብር ይገባቹሀል። ለእናንተ እግዚአብሔር አቅሙን አብዝቶ ይስጣችሁ።

  9. “መ/አ ብርሃኑ ጎበና:- ሰማኒያዎቹ በመንፈስ መቃጠል የነበረበት የአገልግሎት ዘመን ነበረ:: በኮሚኒዝም እግዚአብሔር የለም የሚል አስተምህሮ የተነሣ የሆነ ክፍተት (Vaccume) ተፈጥሮ ነበር:: ሃይማኖተኛ መሆን እንደ ኋላቀርነት ይታይ ነበረ:: ሊቃውንቱን የሚያከብርም ወጣት አልነበረም:: የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆነን ዞረን ስንሰብክ ሕዝቡ ላይ ትልቅ ነገር ተፈጥሮ ነበር:: ከእኛ ቀድመው የተመረቁ ተማሪዎችም የእኛን ወጪ ይሸፍኑ ነበር:: ከአዲስ አበባ እየወጣንም እናገለግል ነበር:: በረሃብ በጥም ውስጥ ሆነን በፍቅር እናገለግል ነበረ:: ”

    ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህራችን ብዙ ነገር ከእርሶ እንማራለን

  10. ዋው ደስ የሚል ነው በእውነት!! ድንግል ማርያም በምልጃዋ ትከተልህ!!!

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *