ምሥጢር የሚገልጡት አሌፋት

የእስራኤላዊያን የሃይማኖት፥ የባሕልም ሆነ የቋንቋ ትምህርት መሠረት ፊደሎቻቸው ናቸው። በሀገራችን ሊቃውንት ዘንድ፥ የዕብራይስጥ ፊደላት “አሌፋት” በመባል ይታወቃሉ። አሌፋት የተባሉትም የመጀመሪያ ፊደል የሆነውን ‘አሌፍ’ መሠረት በማድረግ ነው። በሌላው ዓለም ፊደሎች ድምጾችን የሚወክሉ ሥዕላዊ መግለጫዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። በእስራኤላዊያን ዘንድ ግን አሌፋቱ ድምጾችን የሚወክሉ ሥዕሎች ብቻ አይደሉም። አንዳንድ ሰዎች ፊደሎች ተገጣጥመው ‘አሳብን ማስተላለፊያ’ ብቻ ሆነው እንደሚያገለግሉ ያምናሉ። ለእስራኤላዊያን ግን የአሌፋቱ ሚና አሳብን ከማስተላለፍም ይሻገራል። 

እስራኤላዊያን አሌፋቶቻቸውን ኦቲዮት የሶድ (אוֹתיּוֹת יְסוֹד) ይሏቸዋል፤ ‘መሠረት የሆኑ ፊደላት’ ማለት ነው። ‘መሠረት የሆኑት ለምንድር ነው?” ካለን “ለፍጥረታት ሁሉ” የሚል መልስን ይሰጡናል። በእርግጥ አሳቡ ለእኛ ትውፊት እንግዳ አይደለም። የኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ዓለም የተፈጠሩባቸውን ቋንቋዎች “አንድም ዕብራይስጥ፥ አንድም ሱርስት” ብሎ ያስቀምጣል። ምንም ስንኳ አሌፋቱን ‘የፍጥረታት ሁሉ መሠረት’ እስከማለት ድረስ ባንሄድም ስንኳ በውስጣቸው እጅግ ብዙ ምስጢራትን የያዙ መሆናቸውን ግን አንክድም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትውፊት መሠረትም ለአሌፋቱ የሚሠጠው ቦታ ከፍ ያለ ነው። እያንዳንዱን ፊደል ከአይሁድ ትርጓሜ አንጻር በማናበብ ብዙ ለማለት ቦታ ቢገድበንም፤ ምሥጢርን ስለተሞሉት አሌፋት ግን ጥቂት ሃሳቦችን ለመመልከት እንሞክራለን። 

የአሌፋቱ መገለጥ 

አሌፋት የራሳቸው የሆነ ቅድመ ተከተል አላቸው። በአይሁድ ዘንድ ቅድመ ተከተሉ በራሱ በእግዚአብሔር የተዘጋጀ መሆኑ ይነገራል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአሌፋቱን ስም እና ቅድመ ተከተላቸውን የምናውቅበት አንደኛው መንገድ መዝሙረ ዳዊትን በመመልከት ነው። 

በመዝሙር 118 (119) ላይ መዝሙረኛው ዳዊት ‘አሌፍ’፥ ‘ቤት’ እያለ በዕብራይስጡ ፊደላት መሠረት ጸሎቱን አዋቅሯል። ብዙዎች ከዕብራይስጡ ፊደላት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚተዋወቁት ይህንን መዝሙር በሚጸልዩበት ጊዜ ነው። እነዚህ ፊደላት ግን እንደ ድንገት የመጡ አይደሉም። የራሳቸው የሆነ ምንጭ፥ እኛም ጋር የደረሱበት የራሳቸው መንገድ አላቸው። በመዝሙረ ዳዊት አንድምታ ትርጓሜ ላይም ምንጫቸውን ሲያስቀምጥ አንዲህ ይላል፦ 
“ይህንም አሌፋት አዳም በገነት ሳለ ሰባት ዓመት ሲጸልየው ኑሯል። ኋላ ዕፀ በለስን በላ፥ ሳተ፤ ተሰውሮታል። ከዚያ ወዲህ የተነሱ አበው ደመ አቤል ያስጥመን እያሉ የሚምሉ ሆነዋል። ጌታ በዕሩቅ ብእሲ ደም አይማሉ ብሎ ለሔኖክ በጸፍጻፈ ሰማይ ጽፎ አሳየው፤ በብርት ቀርጾ አኑሮታል”

በአንድምታ ትርጓሜያችን ላይ አዳም አሌፋቱን ይጸልይ እንደነበረ፥ ከዚያም ዕፀ በለስን በልቶ እንደተሰወረው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አሌፋቱን ለሔኖስ በሰማይ ላይ ጽፎ እንዳሳየው ተጽፏል። ይህ ትውፊት ከሞላ ጎደል በአይሁድ መጻሕፍት ውስጥም ይገኛል። አይሁዶች ሚድራሽ በተሰኘ የትርጓሜ ስብስብ መጻሕፍታቸው ውስጥ እንደሚገልጹት ከሆነ፤ እግዚአብሔር ለአዳም አሌፋቱን፥ የእያንዳንዱን ትርጉም እና በመሐላቸው ያለውን ሒሳባዊ ግንኙነት ሳይቀር አስተምሮታል። አዳምም እውቀቱን ወስዶ ለልጆቹ አስተማረ። በዚህ አይነት መንገድ እየተቀባበሉት ሄደው ያዕቆብ ጋር ሲደርስ፥ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ እንዳስተማረው እና ዮሴፍም የፈርዖንን ሕልሞች መፍታት የቻለው አሌፋቱን ቀመር አድርጎ በእግዚአብሔር እርዳታ እንደሆነ ይናገራሉ። አንዳንድ ዝርዝሮች ላይ ልዩነት ቢኖርም፥ አሌፋቱ በእግዚአብሔር ለአዳም ተገልጠዋል የሚለው ላይ ግን ትውፊታችን ከአይሁድ ትውፊት ጋር ይስማማል። 

አሌፋቱ እንደ ጸሎት

በአይሁዶች ዘንድ የሚነገር አንድ አፈ-ታሪክ አለ። በአንድ ወቅት አንድ ረቢ (በዕብራይስጥ መምህር ማለት ነው) ሉሪያ የተባሉ መምህር ጸሎታቸው የልብ አድርስ እንደሆነ ተሰማቸው እና ጥቂት ተኩራሩ። በዚህ ጊዜ አንድ መልአክ ተገልጦ “ከአንተ እጅግ የሚበልጥ ጸሎት ያለው ሰው አለና፤ ወደ እርሱ ሒድ” ብሎ ተናገራቸው። እኚህም ረቢ ተነስተው ከእርሳቸው የተሻለ ጸሎት አለው የተባለውን ሰው ለማየት ሄዱ። ሰውየውን ሲያገኙት ግን ተራ ሰው ሆነባቸው እና ተደነቁ። “ለመሆኑ ለሮሽ ሃሾናህ (አይሁድ ዓለም የተፈጠረበት ቀን ብለው የሚያከብሩት) ምን ብለህ ጸለይክ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም ፈራ ተባ እያለ፥ “ረቢ፥ እና የተማርኩ ሰው አይደለሁም። ሁሉንም አሌፋት ስንኳ አላውቃቸውም። ስለዚህ የበዓሉ እለት የምችላቸውን አሥሩን ፊደሎች ከጸለይኩ በኋላ ‘አምላኬ ሆይ፥ እነዚህን ፊደሎች ውሰድና ለአንተ ደስ የሚያሰኝህን ጸሎት አድርጋቸው’ ብዬ ጠየቅሁት። ቀኑን ሙሉም ፈጣሪዬን እንዲህ እያልኩ ስማጸነው ዋልኩኝ።” አላቸው። ረቢውም የትሑት ሰው ጸሎት በፈጣሪ ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት እንዳለው ተረዱ ይባላል። 

በእርግጥ አንድምታችን አሌፋቱ ጸሎት ስለመሆናችን አዳም ይጸልየው ነበር በማለት ከላይ ባየነው የመዝሙረ ዳዊት አንድምታ ክፍል ላይ ይገልጻል። ሁሉም ፊደል ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የሚገልጸው ብዙ ነገር ስላለው፥ ምስጢራቸውን እያሰቡ በተመስጦ ፊደሎቹን ማለት ታላቅ ጸሎት ተደርጎ ይወሰዳል። አንዳንዶች ደግሞ ቀስ ብለው በተመስጦ ፊደሎቹን ይጽፋሉ፥ ስለ እግዚአብሔር የሚናገሩትን ነገርም ያስባሉ። በአይሁዶች ዘንድ የፈጣሪን ቃል የሚያስተምሩ መምህራን በአሌፋቱ መሠረት የተዋቀረውን መዝሙር 118 (119) ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ እንዲጸልዩ የተቀመጠ ትእዛዝ የሚገኘው አንድም ከዚህ አንጻር ነው። 

አሌፋቱ እንደ ምጢራት ቁልፍ

እስራኤላዊያን አንዲት አጭር ጸሎት አለቻቸው። “ባሩክ ሃመላሜድ ኤት ያዲ ለሳፔር ኤት ሃኦቲዮት” ትላለች። “አሌፋትን እጽፍ ዘንድ እጄን ያሰለጠነው እርሱ የተመሰገነ ይሁን” ማለት ነው። ጸሎቱን አይሁዶችም ሆነ በክርስቶስ የሚያምኑ አይሁድ (Messianic Jews) ይጸልዩታል። “ፊደል ለማጥናት ጸሎት ይጸልያሉ?” ብለን ልንደነቅ ልንችል ይሆናል። መልሱ “አዎ” ነው። ፊደል ሲያጠኑም ሆነ በተማሩት ፊደል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ምስጢርን ሲያገኙበት እድሜ ልካቸውን በዚህች ጸሎት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው ታላቅ የምስጢራት መክፈቻ ቁልፍ ተደርገው ስለሚታሰቡ ሁሌም ፈጣሪን ስለ አሌፋቱ ያመሰግናሉ።

በዕብራይስጥ ፊደል ለማለት ኦት (אוֹת) የሚለውን ቃል እንጠቀማለን። ሆኖም ግን ቃሉ ‘ምልከት’ እና ‘ድንቅ’ ተብሎም ይፈታል፤ ፊደላቱ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ ፍጥረቶቹ በውስጣቸው የያዟቸው ምልክቶች፥ የሚገልጡትም ድንቅ ነገር እንዳለ ለማመልከት ነው። ለዚህ ማሳያነት ሊውሉ የሚችሉ እጅግ ብዙ ምሳሌዎች ቢኖሩም፤ ከእነዚህ መካከል አንዱን ብቻ እንደ ማሳያ እንውሰድ። የኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያ ዐረፍተ ነገር እንደሚከተለው ይላል፦ 

בְּרֵאשִׁ֖ית בָּרָ֣א אֱלֹהִ֑ים אֵ֥ת הַשָּׁמַ֖יִם וְאֵ֥ת הָאָֽרֶץ
(በሬሺት ባራ ኤሎሂይም ኤት ሃሸማዪም ቨኤት ሃአሬትዝ)

ከላይ ባለው ዐረፍተ ነገር ላይ ብቻ፥ ወደ ሌላ ቋንቋ ሲተረጎም የሚጠፉ፥ በዕብራይስጡ ሲሆን ግን የሚታዩ ነገሮች አሉ። ለአብነት ያህል በዐረፍተ ነገሩ ላይ አሌፍ (א) የተሰኘችው ፊደል ስንት ጊዜ ተጠቅሳለች ብንል መልሱ ስድስት ነው። ለመሆኑ አሌፍ ስድስት ጊዜ ለምን ተጠቀሰች ብንል፥ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ፍጥረታቱን አጠቃልሎ ፈጥሮ እንደሚጨርስ አስቀድሞ የገለጸው ዘፍጥረት 1፡1 ላይ መሆኑን በአይሁድ ትርጓሜ ላይ ተጠቅሶ እናገኛለን። ሌላው (אֵ֥ת) የሚለው ቃል ነው። ይህ ቃል በሌላ ቋንቋ አቻ ያለው ቃል ስላልሆነ አይተረጎምም። ሆኖም ግን የገባበት የራሱ የሆነ ሰዋስዋዊም ሆነ ምስጢራዊ ምክንያት አለው። 

ከትርጓሜ አንጻር (אֵ֥ת) የሚለው ቃል በዕብራይስጥ የመጀመሪያውን አሌፍ (א) እና የመጨረሻውን ታው (ת) ፊደል በማጋጠም የሚሠራ ነው። ይህ ሲተረጎም አንድም “ከአሌፍ እስከ ታው” ያሉትን ፊደላት ፈጠረ ማለት እንደሆነ ያስረዳሉ። አንድም ደግሞ “ከአሌፍ እስከ ታው” ማለትም “ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ” ያሉትን፤ ማለትም ፍጥረትን ሁሉ ፈጠረ ማለት እንደሆነ ያመሰጥራሉ። አንድም ደግሞ “ከአሌፍ እስከ ታው” የሚለው ጊዜን የሚጠቁም ስለሆነ፤ እግዚአብሔር ጊዜን ፈጠረ የሚል ትርጉም አለው የሚሉ አሉ። 

በዕብራይስጥ አሌፋት እንደ ፊደል ብቻ አያገለግሉም፤ የቁጥር አቻም አላቸው። አይሁድ የአሌፋቱን የቁጥር አቻ በመጠቀም ትርጓሜ የሚያራቅቁበት ገሜትሪያ የተባለ ስልት አላቸው። ይህ ስልት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፥ አባቶቻችን በትርጓሜ ውስጥ ይህንን የገሜትሪያ ስልት እንዴት እንደተጠቀሙት ለማወቅ በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 13 ቁጥር 18 የዕብራይስጥ ፊደሎችን እና የቁጥር አቻቸውን በመጠቀም የሰሩትን ስሌት እንድትመለከቱ እጋብዛለሁ። 

ማስታወሻ:- መምህር ፍሬሰንበት ገብረ ዮሐንስ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የዕብራይስጥ መምህር ሲሆኑ የጃንደረባው ሚዲያ ቋሚ ዐምደኛና ማኔጂንግ ኤዲተር ናቸው::

Share your love

2 አስተያየቶች

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *