በእግዚአብሔር ፊት በቆምህ ጊዜ የምታቀርበው ጥያቄ ምንድነው? “ለምኑ ይሰጣችኋል፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ የለመነ ሁሉ ይቀበላልና፤ የፈለገም ሁሉ ያገኛልና፤ መዝጊያ ለሚያንኳኳ ሁሉ ይከፈትለታል” ማቴ 7፥7 ብሎ በፊቱ ልመናን እንድናቀርብ ስለፈቀድልን ጸሎትና ምልጃን ማቅረብ እንችላለን።

ነገር ግን ጥያቄህን አታሳንሰው፤ የቆምኸው በንጉሥ ፊት ነውና። ቢያሻህ እንደ አስቴር ለወገኖችህ ሁሉ መዳን የሚሆን ተስፋን የምታገኝበት፤ አለበለዚያም ደግሞ እንደ ነህምያ የፈረሱ ከተሞችን መልሶ መገንባት የሚያስችል ዕድል የምታገኝበት ቦታ ላይ መቆምህን አስብ። ነቢዩ ናታን በንጉሥ ዳዊት ፊት በቆመ ጊዜ ለኢየሩሳሌም ጥበብና ማስተዋል የተሞላውን ሰው ሰሎሞን እንዲነግሥ የለመነው ከዕለታት በአንድ ቀን በንጉሥ ፊት በቆመ ጊዜ ነበር 1ነገ 1፥23። ብላቴናው ዳዊት በእስራኤል ቆነጃጅት ዐይን የገባውና ዕልፍ ገዳይ የሚል ሙገሳ ከሴቶች አፍ የቀረበለት በጎቹን ትቶ አንድ ቀን በንጉሥ ፊት በመቆሙ ነበር። አንተም ልመናህን አታሳንሰው፤ በየቀኑ የምትቆመው በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት መሆኑን አትርሳ። ስለምድራዊ ኑሮ ብትለምን፥ በሞት የሚገታ ነው። በምድር ላይ ሰፊ ማደሪያ እንዲኖርህ ብትጠይቅ፥ ከምድር ስፋት የተነሣ የጠብታ ውኃ ያህል ትንሽ ነው። ሥልጣንም ይሻራል፤ ኃይልም ይደክማል፤ ባለጠግነትም ይጠፋል እነዚህን ሁሉ ብትለምን በእግዚአብሔር ፊት ትንንሾች ናቸው።

አንተ ግን በፊቱ ልመናህን እንድታቀርብ ስለተፈቀደልህ ልመናህን ከፍ አድርገው። እንደ አብርሃም ልጆች በሁለቱ ወንዞች መካከል ተሰብስበህ የምትኖር ሳትሆን ዘፍ 25፥20 አራቱ አፍላጋት የሚፈሱባትን ገነትን ወርሰህ እንድትኖር “ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ” ሉቃ 23፥43 ተብሎ ተፈቅዶልሃል።  

አንድ ቤት ሳይሆን አንድ ከተማ እንዲሰጥህ የምትለምን እንኳን ቢሆን ልመናህ ታናሽ መሆኑን አስብ። አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ማግኘት የምትችልበትን ጸሎት ለአንድ ከተማ ብቻ አታድርገው። ይሄኛው አልፎ በዚያ ትኖር ዘንድ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የምትቀበልበት ጊዜ ይመጣል።  በዚያውም ላይ ምጽዋት የሚጠይቅ ሰው የሚቆመው ከበር ውጭ ነው፤ አንተ ግን የቆምኸው ቤተ መቅደስ ውስጥ ነው። ለዚህ ነው ልመናህን ከፍ አድርገው የምልህ። በፊትህ ያለው አምላክ ዘካርያስ ካየው መልአክ ይበልጣል። ነገር ግን የማይገባ ንግግር ብታቀርብ እንኳን አይቆጣም። ምክንያቱም ልጁ ነህና። የዘካርያስ ጥያቄ ልጅ እንዲሰጠው ነው፤ ጥያቄው ትንሽ ነው። አንድ ሊቀ ካህናት መካኒቱ ሐና የለመነችው ልመና ላይ መገኘት አልነበረበትም። ከዚያ አልፎ እንደ አረጋዊው ስምዖን ዐይኖቹ በሰው ሁሉ ፊት ያዘጋጀውን የእግዚአብሔርን ማዳን ያዩ ዘንድ መጸለይ ይገባዋል። ልብ በሉ! ትልቅ ጥያቄ የሚኖረን እምነታችን ታላቅ የሆነ እንደሆነ ነው።

የክርስቲያን ጥያቄ እንደ መጻጉዕ ለፈውስ፣ እንደ ጤሜዎስ እያዩ ለመመላለስ፣ እንደ ሁለቱ ወንድማማቾች ለሹመት ማቴ 20፥21 ሳይሆን እንደ ባለ ሽቱዋ ሴት ያለ ነው ˉ መሆን ያለበት። የሷ ጥያቄ የዘለዐለም ሕይወት ነው እንጅ ሌላ ጥያቄ የላትም። ለዚህ ነው እግሩን ይዛ በእንባዋ ስታጥበው ምንም አልከለከላትም። ሌሎቹ ሰዎች ያቀርቡት በነበረው ጥያቄ ላይ መልሱ ይዘገይ ነበር። ሁለቱ ዕውራንና ሲሮፊኒቃዊቷ ሴት ለዚህ ማሳያ ይሆኑኛል ማር 7፥26፣ ማቴ 20፥31። አብዝተው እስኪጮሁ ድረስ ፈጥኖ አልመለሰላቸውም። የዚህችን ሴት ልመና ግን ሳትነግረው አወቀላት። እሷ ሃሳቧን በዕንባዋ ነገረችው፤ ዕንባን እንደ መጽሐፍ የሚያነብ ጌታ ምን እንዳሰበች በእንባዋ ተረድቶ ያደረገችው ሁሉ ለምን እንዳደረገችው ተናገረላት “ይህንን ለመቃብሬ አደረገች” አለ። ሳትናገር የፈለገችውን አወቀላት።  የሚቃወሟት አንዳንድ ሰዎች ቢኖሩም ገሠጸላት፤ ማርያም መግደላዊት ሰባት አጋንንት አድረውባት ብትቸገር ወደ እርሱ መጥታ፥ ሽቱ ቀብታ፥ እግሩ ሥር ወድቃ ለመነችው። አላዘገያትም። ልመናዋን ፈጥኖ መለሰላት ማር 16፥9።

ከሷ ይልቅ የሚገርመኝ በጌርጌሴኖን የመቃብር ሥፍራ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ነገር ነው። ያደረባቸው ጋኔን ከመጮሁ በቀር ሰዎቹ ምንም አልተናገሩም ነገር ግን ተፈውሰዋል ማቴ 8፥32። ሳይነግሩት የሚሰማው ልመና እንደዚህ ያለ ነው። በመጽሐፈ ኪዳን “ሳንለምነው የምንሻውን አውቆ ይሰጠናል” የተባለው እንዲህ ያለው ልመና ነው። ጌታ የሚወደው ልመና የነፍሳችን መዳን ጉዳይ መሆኑን ልብ በል። ኃጢአትና ሰይጣን ከጠፉልን ሌላውን እኛ እናደርገዋለን። እግዚአብሔር ፊት መቆም የሚያስፈልጉን ልመናዎች እነዚህን ማጥፋትና የዘለዓለም ሕይወትን ማግኝት ናቸው። አንዳንድ ሰዎች ዕድሉን ካገኘሁ ብለው የዘለዓለም ሕይወትን ጉዳይ እንደ ሣምራዊቷ ሴት ተራ ነገር አድርገው ይመለከቱታል። ለዘለዓለም ስለማያስጠማው ውኃ ሲነግራት ከውኃ መቅዳት ማረፏን ብቻ ነበር የታያትና “ጌታ ሆይ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ” አለችው። እሱ የነገራት በርሱ በማመን ስለምታገኘው የዘለዓለም ሕይወት ነው እሷ ደግሞ እየጠየቀችው ያለ እንስራ ተሸክሞ ከመመላለስ እንዲያድናት ነው። ገና ጥያቄዋ ትንሽ ነው። በታላቁ አምላክ ፊት መቆማችንን ካላወቅን እኛም ከዚህ ያለፈ ላንጠይቅ እንችላለንና ልመናችንን በልዑል አምላክ ፊት እንደ ሚቀርብ በማሰብ ማቅረብ ይገባናል።

በመጽሐፍ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ካልገባን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆመ ሰው መናገር አንችልም። እርሱ ግን አባት ነውና ሁሉንም በፍቅር ይቀበለናል እንጅ ዐጼ ቴዎድሮስ እንደ ቀጡት አዝማሪ የንግግራችንን ስንፍና ተመልክቶ ሊቀጣን አይፈልግም። ዐጼ ቴዎድሮስ ከደጃች ጎሹ ጋር ጦርነት ላይ በነበሩ ጊዜ የደጃች ጎሹ አዝማሪ

“ያንጓብባል እንጅ መች ይዋጋል ካሳ፤

ውርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ”

ብሎ ገጠመ። በኋላ ደጃች ጎሹ ሲሸነፉ አዝማሪውም ተማርኮ በንጉሡ ፊት ስለገጠመው ግጥም ሲጠየቅ አዝነው የሚተዉት መስሎት

“አወይ የእግዜር ቁጣ አወይ የአምላክ ቁጣ፤

አፍ ወዳጁን ያማል ሥራ ሲያጣ፤

ሽመል ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ”

ብሎ ገጠመ። ንጉሡም እንደተናገረው አድርጋችሁ ግደሉት ብለው በሽመል አስደብድበው አስገደሉት። እግዚአብሔር እንዲህ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ለራሳችን የሚጎዳ ልመና ያቀረብንበት ቀን ስንት ነበር? ነቢዩ ኤልያስ “ጌታ ሆይ ነፍሴን ውሰድ” ብሎ በለመነበት ቀን ነፍሱን ቢወስዳት ኖሮ ዮርዳኖስን ማን ይከፍልልናል፤ እሱስ ቢሆን በእሳት ሠረገላ ተጭኖ መኖር ከመሞት አይሻለውም? በእሳት ሠረገላ ተቀምጦ ወደ ሰማይ ሊወጣ ዕድል የተሰጠው ሰው ነፍሴን ውሰድ ብሎ ይለምናል? አየህ የኛ ልመና ከእግዚአብሔር ስጦታ በእጅጉ ያነሰ ስለሆነ ልመናህን በቅጥ አድርገው። ትንሽ ነገር አትለምን። ልመናህ ሁሉ ስለዘለዓለም ሕይወት ይሁን። “መንግሥትህ ትምጣ” በል። በአባቶቻችን ልመና ክርስቶስ ተወለደልን በኛ ልመና ደግሞ መንግሥቱን እንወርሳለን።

አሜን!

ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ሰኞ የሚነበቡ ይሆናል:: 

Share your love

16 አስተያየቶች

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህራችን
    ሁሌም በጉጉት ነው ምጠብቀው የእርሶን ፁሁፍ

    “በመጽሐፍ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ካልገባን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆመ ሰው መናገር አንችልም።”

  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን። ዓይነ ልቦናችን ያብራልን ። እንደ ክርስቲያን ማሰብን ከቅዱሳን ህይወት ስንማር ለነገሮች ያለን እይታ እንደ ክርስቲያን ይሆናል።እንደ ክርስቲያን ማሳብ ስንጀምር እንደ ክርስቲያን መጠይቅ እንጀምራለን።ስለዚ አብዝተን ቅዱሳን መጻሕፍትን እናንብብ። #እንዳላነብ የሚከለክለኝ ምንድነዉ?

  3. kale hiwot yasemalin…. መምህር…..#እንዳላስትውል የሚከለክለኝ ምንድነዉ?

  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር ምንም አንብቤ ተግብሬ ለዚ በቅቼ አምላክ ፊት ባልምቆምም እንደ እርሶ ያሉ ሰው በዚ ዘመን በመኖርዎ ተስፋ አረጋለው እግዜር እረጅም እድሜ ይስጦት እንደው ሚያነቡት ከሆነ በ አንድ ቀን ጸሎቶ ብስራተ ገብርኤል ብለው ያስቡኝ አባቴ።

  5. የህይወት ቃል ያሰማልን መምህር ፅሁፉዎ በጣም ልዩ ነው እና ሁሌም በጉጉት ነው ምጠብቀው።

  6. በጣም ደስ ይላል ። በተለይ የ መግደላዊት ማርያም ታሪክ ሁሌም ያስገርመኛል ።
    ቃለ ህሕይወትን ያሰማልን።

  7. አሜን መምህር ቃለህይወት ያሰማልን፤ እንደ እርሶ ያለ ሰው ያላሳጣን እግዚአብሔር ደተመስገነ ይሁን!!@ እረጅም እድሜ ከጤናጋ አምላክ ያድልዎ።

  8. ቃለ ሕይወት ያሰማልን።ረጅም ዕድሜና ጤናን ሰጥቶዎች የተበተኑ የባዘኑ መንጎችን በመሰብሰብ ለመንግሥቱ የታጩ ይሆኑ ዘንድ ያበርታዎት።
    ትምህርቱ ቆም ብለን በፈጣሪ ፊት ስንቆም ምን መለመን እንዳለብኝ የተማርኩበት ነው።

  9. ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር ያገልግሎት ዘመኖን ይባርክልን እድሜ ከጤና ያድልልን።

  10. ቃለ ህይወት ያሰማልን ረጅም እድሜ እና ጤና ይስጥልን …ስለ ፀሎት ጥሩ ትምህርት አግኝቼበታለሁ አመሰግናለሁ

  11. ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር ! እድሜ ከጤና ያድልልን።

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *