አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና” ከገዳም ከተመለሰ፣ ጉባኤ ሠርቶ ማስተማር ከጀመረ እነሆ ሦስተኛ ቀን ሆነው። በሦስተኛው ቀንም በታናሿ መንደር በቃና ሠርግ ተደረገ። ይህ ሠርግ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይነት የተገለጠበት ሠርግ ነው። ለሐዋርያት ሰውነቱ ከአምላክነቱ፣ አምላክነቱ ከሰውነቱ የማይነጣጠልበት አምላክ ወሰብእ መሆኑን በምሥጢር ገለጠላቸው። እንደ ዮሐንስ መጥምቅ በዮርዳኖስ ተገኝተው አብ በደመና ሆኖ ሲመሰክርለት፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ሲያርፍበት አላዩም። በገዳመ ቆሮንቶስ ሰይጣንን ድል ነሥቶ መምጣቱን አላወቁም። ስለዚህ በዚህ የሠርግ ቤት ተአምር ሰው ሲሆን አምላክ፤ አምላክ ሲሆን ሰው መሆኑን አስረዳቸው።
ሰው መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ከሰዎች እንዳንዱ ተጠርቶ ወደ ሠርግ ቤት ገባ። አምላክ መሆኑም ይታወቅ ዘንድ ውኃውን የወይን ጠጅ አድርጎ አስገረማቸው። ለዚህ ነው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ ክብሩንም ገለጠ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” ዮሐ 2፥11 ያለው። ደቀ መዛሙርቱ ማመን የጀመሩበት ቀን ነው። ከዚህ በፊት ምን አይተው ሊያምኑ ይችላሉ? እንደ ሰብአ ሰገል በኮከብ ተመርተው አልመጡም። እንደ ቤተ ልሔም እረኞች በመልአክ ተጠርተው አልተሰበሰቡም። እንደ ዮሴፍ አረጋዊ በሕልም፣ እንደ ሰሎሜ በተአምራት አልተረዱትም። የባሕርይ አምላክነቱን ሊያስረዳ የሚችል ሥራ ያዩት ዛሬ ነውና ተአምራቱን ባዩ ጊዜ አመኑበት።
ከሐዋርያት በፊት በሰዎች መካከል የገለጠችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። ከሰዎች መካከል ሂዳ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ባለች ጊዜ ከተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ከእርሱ በቀር የሌለውን ወደ መኖር ማምጣት እንደሌለ ከእሷ በቀር ማን ያውቃል? ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣው አምላክ ከዚህ የሠርግ ቤት መካከል መኖሩን ያለ እርሷ ማንም አያውቅም ነበር። እሷ እንደ ነቢያት ብታየው ኖሮ “በማድጋ ካለው እፍኝ ዱቄት በማሰሮም ካለው ጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም” ወይም “ከዘይት ማሰሮ በቀር አንዳች የለኝም” 1ነገ. 17፥12፣ 2ነገ. 4፥2። እንዳሉት ሴቶች ያለ አቀራረብን በመጠቀም ልመናዋን ታቀርብ ነበር እንጅ ባልተለመደ መንገድ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” እንዴት ትለው ነበር? ያልነበረውን ዓለም ወደ መኖር ያመጣ እርሱ የሌላቸውን እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ስለምታውቅ ነው − ልመናዋን በዚህ መልኩ ያቀረበችው።
በቤተ ክርስቲያን ጸሎት ውስጥ “ልመናዋ፣ ክብሯ ይደርብን” የምንላት ልመናዋ ከሌሎች ሰዎች ልመና የተለየ ስለሆነ ነው። እንደ ከነናዊቷ ሴት እየጮኸች እየሰገደች አልለመነችም፤ እንደ ኢያኢሮስ፣ እንደ ኢያሪኮ ዕውራን ወይም በቅዱስ ወንጌል ልመናችውን በክርስቶስ ፊት እንዳቀረቡ ሰዎች ባለ አቀራረብ ልመናዋን አታቀርብም። ክርስቶስም እንደሌሎቹ “እምነትሽ አድኖሻል፣ ይኩንኪ በከመ ተአመንኪ” አላላትም። “ጊዜዬ ገና ነው” ብሎ ነው የመለሰላት። “የሚላችሁን አድርጉ” ብላ ለአሳላፊዎቹ ትዕዛዝ ትሰጣለች፤ አሳላፊዎቹ ውኃውን ይቀዳሉ፤ የቀዱትን ውኃ ወስዳችሁ ለአሳዳሪው ስጡት የሚል ትዕዛዝ ከክርስቶስ አፍ ይሰማሉ፤ ወስደውም ይሰጣሉ። ተአምራቱ በዚህ ሁሉ ሂደት የሚፈጸም እንጅ ነቢዩ ኤልያስ ቃል ብቻ ተናግሮ “ዱቄቱ ከማድጋው ዘይቱ ከማሰሮው አያልቅም” 1ነገ. 17፥14 ብሎ የሚያበረክት አይደለም። ጊዜዬ ገና ነው የሚለው ምላሽ ትርጓሜው የሚጀምረው ከዚህ ነው።
የቃና ዘገሊላ ተአምር የነገረ ድኅነትን ጥልቅ ምሥጢር የያዘ ስለሆነ ነገረ ድኅነትም የተፈጸመው በእግዚአብሔር ፈቃድና በሰው ልጆች ተሳትፎ መሆኑን የሚገልጥ ተአምር ነው − ዛሬ የተፈጸመው። እሷም “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚለው ቃሏ ከሰማያዊ አባቱ ጋር አንድ አድርጓታል። ሰማያዊ አባቱ “ወሎቱ ስምዕዎ” ባለ ጊዜ ክርስቶስ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ነገረን። እመቤታችንም እንዲሁ ተናገረች።
ወደዚህ ዓለም ለመምጣት ምክንያት ያደረጋት እመቤታችን ዛሬ ደግሞ በሠርግ ቤት መካከል ክብሩ እንዲገለጥና ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ እንዲያምኑበት አደረገች። እኛ ሁላችን በእርሱ እናምን ዘንድ ምክንያት የሆነችን ድንግል ማርያም ናት። ኤልሳቤጥን “የጌታዬ እናት” ብላ ትንቢት እንድትናገር ያደረገቻት በርጅናዋ ወራት ከነቢያት እንድትቆጠር ያደረጋቻት እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት። ዮሐንስ በማኅፀን ሳለ ለፈጣሪው እንዲሰግድ ያደረገችውም እሷ ናት። የሕጻኑ በደስታ መዝለል የሰላምታዋን ድምጽ በሰማች ጊዜ መሆኑን ኤልሳቤጥ መስክራለችና። ዮሐንስ መጥምቅ ለአጥማቂነት ሲታጭ ንዋ በግኡ ለእግዚአብሔር ብሎ ሲመሰክር ያኔ እመቤታችን በዚያ ነበረች። ይህንን ምስክርነት የሰጠው ለአጥማቂነትም የታጨው ያኔ ገና በማኅፀን ሳለ ነውና። በደስታ መዝለሉ “እኔ ካንተ ልጠመቅ ይገባኛል” እያለ ነው።
በሰማይ የሚኖረው ኮከብ ከሰማይ ዝቅ ብሎ ሲያበራ በቤተ ልሔም ባለችው ግርግም በቆመ ጊዜ የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች። ነገሥታት ለተወለደው ሕጻን በሰገዱ ጊዜ ዓለም የተገዛላቸው ሲገዙለት ወድቀውም ሲሰግዱለት ከሰዎች ግብርን የሚሰበስቡት እጅ መንሻን ሲያቀርቡለት የጌታ እናት እመቤታችን በዚያ ነበረች። መልአኩ እረኞችን እየመራ በወሰዳቸው ጊዜ ድንገት ከመላኩ ጋር ከሰማይ ነጉደው ሲመጡ የታዩት መላእክት ሲያመሰግኑት ድንግል ማርያም በዚያ ነበረች።
የኢየሱስ እናት ድንግል ማርያም የሌለችበት ጊዜ መች ነበረ? አዳም ከገነት በወጣ ጊዜ እሷ በአዳም ዘንድ አልነበረችምን? እሷን በተስፋ ባያያት ኖሮ ለሞት ያበቃችውን ሴት ሔዋን ብሎ ስም ያወጣላት ነበር? “አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣላት የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና” ዘፍ. 2፥20 እንዲል። በእውነት “የሞት ሞትን ያስፈረደችበት ሴት ይህ ስም ይገባታል? ይህ ስም ከእሷ ስለምትወለደው ስለ እመቤታችን ሲባል የወጣ ስም ነው፤ ሕያዋን ያደረገን ክርስቶስን ወልዳ የሕያዋን ቅዱሳን ሁሉ እናት እሷ ናትና።
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ታላላቅ ሥራዎችን በሠራባቸው ቀኖች ሁሉ የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች። እሷ በሌለችበት የሠራው እኛን የማዳን ሥራ የትኛው ነው? ከሰማየ ሰማያት በወረደ ጊዜ ወደ ምድር በመጣባት በመጀመሪያዋ በዚያች አስደናቂ ሰዓት እሷ ይህ ድንቅ ሥራ በተፈጸመባት በናዝሬት ነበረች። የነቢያት ትንቢት በተፈጸመበት ቦታ ሁሉ እሷ በዚያ ነበረች።
ተሰዶ ከስደት ሊመልሰን ባሰበ ጊዜ ከእሷ ተለይቶ አልተሰደደም። ስደቱ የተፈቀደው ለሕጻኑና ለእናቱ ነው “ሕጻኑንና እናቱን ይዘህ ሽሽ” እንዲል። ዮሴፍና ሰሎሜ ስደተኞችን ሕጻኑንና እናቱን ሊያገለግሉ የተላኩ ናቸው እንጅ ስደታቸው ለስደታችን ቤዛ ሊሆን የሚችል አይደለም። ትንቢቱም የነበረው ሕጻኑ በእናቱ ጀርባ ሆኖ ስለመስደዱ እንጅ ሌሎችን የሚያጠቃልል አልነበረም ኢሳ 19፥1 ይህንን በሚመስሉ የነገረ ድኅነት ሥራዎች ሁሉ እመቤታችን ድንግል ማርያም ነበረች። ለዓለም ሁሉ ድኅነት በቀራንዮ በተሰቀለ ጊዜ የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች ዮሐ 19፥27። እናት የተሰቀለ ልጇን ለማየት እንዴት ትችላለች? ነገር ግን ዓለም በሚቀደስበት በዚህ ሰዓት ከእሱ ጋር እንድትኖር አደረጋት።
እሷ በሌለችበት የተቀበልነው ምንም በጎ ነገር የለም። መንፈስ ቅዱስን በተቀበልንበት ሰዓት እሷ በዚያ ነበረች ሥራ 1፥14። የእግዚአብሔር መንግሥት ለሰው በምትሰጥበትም ጊዜ እሷ በዚያ አለች። ዳዊት እንደተናገረው በቀኙ ቆማ እናያታለን። በዚህ ዓለም ከእሷ ያየነውን ክርስቶስ በሰማይም ከእሷ ጋር እናየዋለን።
የተወደዳችሁ ክርስቲያኖች ሆይ ከክርስቶስ የሚበልጥ ስጦታ የለም። አምላክን ከማየት የሚበልጥ ጸጋም አይገኝም። ይህን ታላቅ ስጦታ የተቀበልነው ደግሞ በእሷ ምክንያት ነው። ኪሩቤል ተሸክመውት ቢኖሩም እንኳን ለእኛ ሊያሳዩን እነሱም ሊያዩት አልተቻላቸውም። ሱራፌል ዙፋኑን ከበው ቢያመሰግኑትም እኛ በዙፋኑ ዙሪያ ቆመን እንድናመሰግን ማድረግ አልተቻላቸውም። ይህን ሁሉ ያደረገችልን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። ቤተ ልሔም ደርሰን እጅ የነሣን ጊዜ እሷንም በዚያ አይተናታል። ግብፅ ብንወርድ እሱን ይዛ በረሀ ለበረሀ ስትንከራተት እናገኛታለን። ቀራንዮ ብንወጣ ከመስቀሉ ሥር አለች።
በኑሯችሁ ሁሉ የኢየሱስ እናት ልትኖርበት ይገባል። ብትነግዱ፣ ብታርሱ፣ ብትቆፍሩ፣ ሚስት ብታገቡ፣ ምናኔ ብትጀምሩ፣ ትምህርት ቤት ብትሄዱ እመቤታችን በዚያ መኖሯን ማረጋገጥ ይገባችኋል። እሷ እሱ በሌለበት ስፍራ ስለማትኖር የእሷ መኖር የእርሱ መኖር ያረጋግጥልናል። የዚህ ሠርግ ባለቤቶችም መጀመሪያ የጠሩት እመቤታችንን መሆኑ “በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሠርግ ነበረ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች” በማለቱ ይታወቃል። ወንጌላዊው ሲጽፍ እሷን ያስቀደመው በሀገራቸው ባህል እናትን ሳይጠሩ ልጅን መጥራት የተለመደ ስላልሆነ አስቀድመው እሷን ጠርተው ቀጥለው እሱን መጥራታቸውን ለመግለጽ ነው።
የሐዲስ ኪዳን ሊቃውንት ይህንን የዮሐንስን ወንጌል ሲተረጉሙ “እናትን ጠርቶ ልጅን መተው አይገባምና እሱንም ጠሩት፤ መምህርን ጠርቶ ደቀ መዝሙርን መተው አይገባምና ብለው ደቀ መዛሙርቱንም ጠሯቸው” ብለው ተርጉመውታል። ወጉ አስቀድሞ እናትን መጥራት፣ ከዚያም ልጅን መጥራት እንደሆነ ያሳያል።
ዛሬ በምንገባንበት በምንወጣንበት ሁሉ የኢየሱስ እናት በዚያ አለች ስለዚህ በጎደለው ነገር ሁሉ አንጨነቅም።
ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆን የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ናቸው::
ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምሕር።
በሕይውት፣ በጤና፣ ፀጋውን አብዝቶ ይጠብቅልን
አሜን አሜን አሜን
ቃለሕይወት ያሰማልን
እሷ በሌለችበት የተቀበልነው ምንም በጎ ነገር የለም። …
እሷ እሱ በሌለበት ስፍራ ስለማትኖር የእሷ መኖር የእርሱ መኖር ያረጋግጥልናል። …
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
ቃለህይወት ያሰማልን!
የሚያጠግብ እጅግ ደስ ሚል ፅሁፍ ነው:-
“የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች”
ቃለህይወትን ያሰማልን መምህራችን
“ዛሬ በምንገባንበት በምንወጣንበት ሁሉ የኢየሱስ እናት በዚያ አለች ስለዚህ በጎደለው ነገር ሁሉ አንጨነቅም”
በኑሯችሁ ሁሉ የኢየሱስ እናት ልትኖርበት ይገባል። ብትነግዱ፣ ብታርሱ፣ ብትቆፍሩ፣ ሚስት ብታገቡ፣ ምናኔ ብትጀምሩ፣ ትምህርት ቤት ብትሄዱ እመቤታችን በዚያ መኖሯን ማረጋገጥ ይገባችኋል። [እሷ እሱ በሌለበት ስፍራ ስለማትኖር የእሷ መኖር የእርሱ መኖር ያረጋግጥልናል።]…
ቃለህይወትን ያሰማልን።
KHY
ስለእውነት እምባ እየተናነቀኝ ነው ያነበብኩት የእምቤታችን ምልጃ ዘውትር አይለን ለመምህራችንም ቃለ ህይወት ያሠማለን
Kalehiywet yasemaln
አባታች ቃለ-ህይወት ያሰማልን በዕድሜ በፀጋ ይጠብቅልን በሰፊው እንደሚመጡልን የማይጠገበውን የእግዚአብሔርን ቃል ደጋግመው እደሚያስተምሩን እንጠብቃለን
እናመሰግናለን
የኔታ
ቃለህይት ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
የኢየሱስ እናት በዚያ አለች ስለዚህ በጎደለው ነገር ሁሉ አንጨነቅም።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን። እንዲህ ያሉትን መምህራን ከ አቡጊዳ ጀምረው አስተምረው ለዛሬ ላበቁልን ለመምህራኖቹ መምህሮች እግዚአብሔር አሰበ መምህራንን ይክፈልልን። እኚህም እነሱን የመሰለ ሳይተኩ እንዳያልፉ እግዚአብሔር ያግዝልን።
የኢየሱስም እናት በእኛ ሕይወት ነበረች ለማለት ያብቃን ፤ ፍቅሯን ያብዛልን፡፡
የሕይወትን ቃል ያሰማልን፡፡
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን።እግዚአብሔር ይስጥልን።
ቃለ ህይወት ያሰማልን
“የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች”
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን መምህራችን!