የአምላክ እናት መሆን ትልቅ ሥራ ነው

የማርያም ጸሎት (ጸሎተ ማርያም) ሁልጊዜም ፣ በሁሉም ሥፍራ ፣ ለሁሉ የሚጸለይ ታላቅ ጸሎት ነው፡፡ ለመንገደኛው ፣ ለሚሾመው ፣ በአልጋ ላይ ላለው ሁሉ የሚጸለየው ጸሎት ይህ የማርያም ጸሎት ነው፡፡ ሹማምንት ፊት አይተው እንዳያደሉ ፣ ጉቦ ተቀብለው ፍርድ እንዳያጣምሙ የሚጸለይላቸው ጸሎት ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም ነው፡፡ ሰዎች ለሰዎች እንዲያዝኑና እንዲራሩ የሚደገምላቸው ይኼ ጸሎት ነው፡፡ ዛሬ በዓለም ያሉ መሪዎች ክፉዎችና ጨካኞች የሚሆኑት ጸሎተ ማርያም ስለማይደገምላቸው ነው፡፡ ለተሾመውና ለተሻረው ፤ ለሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ለሆነው ሰው ጸሎተ ማርያም የምስክር ወረቀት ዲፕሎማ ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጸሎትዋ እግዚአብሔርን ነው ያመሰገነችው፡፡ ደስታዬ እግዚአብሔር ነው አለች፡፡ ደስታ በኃይል ወይም በጉልበት አይገኝም ፤ ከእግዚአብሔር እንጂ፡፡ ደስታ ከሁሉ ነገር ስለሚበልጥ ሁሉ ሰው ሊደሰት ይፈልጋል፡፡ ሊደሰት የሚችለው ግን በእግዚአብሔር ሲያምን ነው፡፡ በዓለም ውስጥ ብዙ ብልጭልጭ ነገሮች አሉ፡፡ የሚያመጡት ጣጣ ግን ብዙ ነው፡፡ ሰው ከሀብት የተነሣ የገዛ ወገኑንና ዘመዱን ሁሉ ይጠላል፡፡ መደሰት የሚቻለው አንድዬን ሲወዱና እርሱን ሲያምኑ ነው፡፡ እናታችን ነፍሴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል አለች፡፡ እኛስ በምንድን ነው ደስ የሚለን? በሀብት ፣ በሥልጣን ፣ በዕውቀት ፣ በወገን መመካት ነው ደስ የሚለን ወይንስ በእግዚአብሔር? ደስታ ፣ ተድላ ፣ ፍስሓ እርሱ ነው፡፡ የእመቤታችን ጸሎት ታላቅ ጸሎት ነው፡፡

ከእንግዲህ በኋላ የእግዚአብሔር ማደሪያ ፣ ማኅደረ መለኮት ሆናለችና ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ፣ ንዕድ ፣ ክብርት ይሉኛል አለች፡፡ ‘ታላቅ ሥራን ሠርቶልኛልና’ ነው ያለችው፡፡ የአምላክ እናት መሆን ፤ ወላዲተ አምላክ መሆን ታላቅ ሥራ ነው፡፡ ሁሉ በረከሰበት ፣ ሁሉ በተዳደፈበት ፣ ሁሉ በተላለፈበት ሰዓት የአምላክ እናት መሆን በእርግጥም ታላቅ ሥራ ነው፡፡ የአዳም ዘር በሙሉ ያመሰግኑኛል ነው ያለችው፡፡

ዛሬ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ብዙ ሥራዎችን ይሠራልናል፡፡ ነገር ግን ሠርቶልናል ፣ ሠርቶልኛል አንልም፡፡ እንደ እመቤታችን አናመሰግነውም፡፡ ቆመን እንድንሔድ ማድረጉና ጤናን ማደሉ በራሱ ትልቅ ነገር ፣ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ እናመስግነው፡፡

እግዚአብሔር ትሑት ስለሆነ ትሑታንን ይወዳል አለች፡፡ እግር ማጠቡን ታውቃለችና ትሑታንን ከፍ ከፍ ያደርጋል አለች፡፡ እነ ፈርዖንን እንዳሰጠመ ታውቃለችና ትዕቢተኞችን ያዋርዳል አለች፡፡ ትዕቢተኛ ሰው የሰይጣን ፈረስ ነው የሚሆነው፡፡ ገደል ገብቶ ፣ ተሰባብሮ ነው የሚሞተው፡

ስለዚህ ትሕትናን የመጀመሪያ ሥራችን እናድርግ፡፡ የክርስትና ልዩ ምልክት ትሕትና ነው፡፡ የሰይጣን ምልክት ግን ትዕቢት ነው፡፡ ዛሬ ሁላችንም የምንታመም ፣ የምንወድቅ አይመስለንም፡፡ ስለዚህ ሰማይ ሰማይ እናያለን፡፡ ደኃውን ግን እንጸየፋለን፡፡ ዛሬ ምልክታችን ትሕትና ሊሆን ይገባል፡፡ በኪሩቤልና በሱራፌል ላይ የነገሠው አምላክ በመስቀል ላይ ነገሠ፡፡ ስለ እኛ በአህያ ላይ ነገሠ፡፡ ተቀመጠ፡፡ ይህ ሁሉ ትሕትና ነው፡፡ ስለዚህ መታወቂያ እናውጣ ፤ መታወቂያ ይኑረን፡፡ መታወቂያችን የክፋት ፣ የተንኮል ፣ የጭካኔ ፣ የዘረኝነት ፣ የመለያየት አይሁን፡፡ የእኛ መታወቂያ የፍቅር ፣ የሰላም ፣ የይቅርታና የአንድነት መታወቂያ ይሁን፡፡ ይህን መታወቂያ ሁላችንም እንያዝ፡፡ በዚህም ደስ ይበለን፡፡

ግንቦት 27 1985 ዓ.ም. እንዳስተማሩት 

Share your love

5 አስተያየቶች

  1. አሜን በርከታቸው ይደርብን እንዲ ለሀገር የሚያስቡትንም እግዚአብሔር አያሳጣን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *