የኅብረት ዝማሬ ቢበዛ ደስ ይለኛል

ከመምህር ተስፉ ግርማ ጋር በመዝሙር አገልግሎት ዙሪያ ያደረግነውን የቆየ ቃለ መጠይቅ ሁለተኛ ክፍል እነሆ:: 

መምህር ተስፉ ግርማ ፦ በቁጥር ብዙ ናቸው ፣ ለዘማሪ ምንዳዬ ከቁጥር አንድ እስከ ሦስት ማለት ይቻላል፡፡

‘ቸሩ ሆይ’ 

‘ማርያም እንወድሻለን’ 

‘ምድራዊ ፍስሓ ተድላው ደስታው ቀርቶብኝ’ 

ቁጥር አንድ ሁለት ሦስት ከሠራን በኋላ ደግሞ ብዙዎች የሚሰረጉበትን ‘ቃና ዘገሊላ’ ፣ ‘ሳይገባኝ’ን ሠርቻለሁ፡፡ በተለይ ከቀሲስ ምንዳዬ ጋር የአንድ አካባቢ ልጆች ስለነበርን እንዲህ ቢደረግ እያልን በደንብ እናሻሽለዋለን፡፡ ስለዚህ መዝሙሮቹ ውበት አላቸው፡፡ ‘ለኀዘኔ ደራሽ ነሽ ለጭንቀቴ’ ለዲያቆን ዋኘባቸው ፣ ለተስፋየ ኤዶም እንዲሁ ሠርቻለሁ፡፡ 

መምህር ተስፉ ግርማ ፦ ተስፋዬ ኤዶ ጎበዝ ልጅ ነበር፡፡ ይጥራል፡፡ መጀመሪያ ወደ አገልግሎቱ እንዲገባ ወደ ጅማ ጋብዤው ነበር፡፡ ክራርም ይጫወት ነበር፡፡ ከተስፋየ ኤዶ ጋር የተዋውቅነው በአዲስ አበባ ከተማ የሰርክ ጉባኤ ደምቆ እንዲከናወን ካደረጉት አባ አምሃ ኢየሱስ ዘንድ ነበር፡፡ የጉባኤ ቦታው ሞልቶ እንማር ነበር፡፡ 

  በተለይ በእመቤታችን ቀን እንደ ‘ነይ ነይ እምዬ ማርያም’ ህዝባዊ መዝሙር ይዘመር የለ? የዛኔ ተስፋዬ በጣም ይዘምራል፡፡ የቅድስት ማርያም ጉባኤ ሲበተን የነተስፋየ ኤዶ እዚያ ያለው ማኅበር ውጭ ሆኖ ነበር፡፡ ዝክርም ይዘክሩ ነበር፡፡ በኋላ እኛ ጋር በዓለ ወልድ ጉባኤ እየተጠናከረ መጣ፡፡ በወቅቱ እኔን ‘ተስፉ አንድምታ’ ነበር የሚሉኝ፡፡ የአንድምታ ትምህርት እሠጥ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከትምህርት ቤት ወጣው ሰርክ ጉባኤ ነው የምሔደው፡፡ እኔ ቀድሞም ቅድስተ ማርያም ነው የምውለው ብዪሃለው፡፡ አባ አምኃ ኢየሱስ ሲያስተምሩ ከእግራቸው ሥር ነበርሁ፡፡ ትምህርታቸው ይመስጣል፡፡ እውነት ነውና ታሪክ ነውና የምንናገረው በጣም ይመስጣል፡፡ ስለዚህ እዚያው አዳምጣለሁ፡፡ የመያዝ ችሎታ ደግሞ አለኝ፡፡ ስለዚህ ከእርሳቸውም ከነአቡነ ኤልያስም የተማርኩትን በሒደት ማስተማር ጀመርሁ፡፡

  ከተስፋየ ኤዶ ጋር የተዋወቅነው ቅድስት ማርያም ነበር፡፡ መዝሙር ስለሚሞክር እኔ ቤት ይመጣል፡፡ ከዚያ አገልግሎት ውስጥ እንዲገባ ብዬ ማኅበረ አርድእት የሚባል በ80ዎቹ ውስጥ ትልቅ ጠንካራ ትልቅ ጉባኤ የሚያድርግ የጅማ ኢየሱስ ማኅበር ነበር፡፡ በዕድሜ ልጅ ብሆንም ለመጀመርያ ጊዜ ለአገልግሎት ጠርተውኝ ረጅም ጉዞ የሄድኩት እነርሱ ጋር ነበር፡፡ ጉባኤው የሚደረገው ጊቤ አዳራሽ ውስጥ ነበር፡፡ እዚያም ችግር ስለነበር ሰባት አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት ተሰባስበው ያዘጋጁት ጉባኤ ነበር፡፡  በተለይ ቅድስተ ማርያም የነበሩ ወጣቶች ወጣ ብለው ወደ አጋሮ ቴፒ መስቀል እስከ ማሳለም ደርሰው ነበር፡፡ ያኔ እኔ ሄጄ ካስተማርሁ በኋላ  ይቅርታ ጠይቀው ተመልሰዋል፡፡ በዚህ የማኅበረ አርድእት ጉባኤ ላይ ተስፋዬ ኤዶን እጋብዘው ነበር፡፡ ከዚያ እርሱ ገጠር ገጠሩን ይሔድ ነበር፡፡ ከተማ ውስጥ አታገኘውም፡፡ እስከ ቴፒ ሚዛን እየሄደ ያገለግል ነበር፡፡

መምህር ተስፉ ግርማ፡-  ምንም ክፍያ የለም:: እንዴ በዚያ ሰዓት የነበረውን ሁኔታ ልንገርህ … ቁጥር አንድ ከቀሲስ ምንዳዬ ጋር ሠርተናል ብዬሃለሁ፡፡ በክፍያ አይደለም፡፡ እንደውም ደስ ይበላችሁ ተብሎ ሱፍ እንደተገዛልኝ አስታውሳለው፡፡ ከአምስት መቶ እስከ አንድ ሺህ ነበረ ያኔ፡፡ ምክንያቱም እኛ እዚያ ነገር ውስጥ አልገባንም ነበር፡፡ ‘የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰረው’ የሚለውን እኛ አናውቀውም ነበር፡፡ ስለዚህ መዝሙሩን ነው እንጂ የምንሠራው ክፍያ አልነበረም፡፡ አብዛኛው እኔ የሠራሁት ከገንዘብ ውጪ ነበር፡፡ ተከፍሎኝ የሠራሁት የለም፡፡ 

  ‘ለኀዘኔ ደራሽ ነሽ’ የሚለውን ስንሠራ ሰው ቤት እያደርን ነበር፡፡ ቀሲስ ደጀኔ የሚባሉ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ነበሩ፡፡ እሳቸው ቤት እያደርን ነው፡፡ ዲያቆን ዋኘባቸው የነበረው ልምድ ቅዳሴ ላይ ነበረ፡፡ ስለዚህ ከመዝሙሩ ጋር ቶሎ ሊዋሐድ አልቻለም ነበር፡፡ አጃቢዎቹን ጠብቆ መዘመር ይቸገር ነበር፡፡ አሁን መዝሙሩን ስታዳምጡት ካስተዋላችሁ ተለያይተው ነው የተቀረጹት፡፡ ደጋግመን ነበር የቀረጽነው፡፡ አሁን ስንሰማው ቃናው ደስ ይላል፡፡ ሙሉ ካሴቱን ግን ቁጭ ብለህ ብትሰማቸው በፍቅር  የሚሰሙ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ትዝታ ጥሩ ነው፡፡ እያሰብህ አይደል የሚመጣልህ? በዚህ መዝሙር ቀረጻ ላይ ዋሽንት ነው የምትጫወተው ስንታየሁ ትባል ነበር፡፡ በጣም ጎበዝ ናት፡፡ መንገድ ላይ የኔ ቢጤ ሆና ስትለምን አግኝተናት ነበር የወሰድናት፡፡ በኋላ ግን የማይረሳ ሥራ አብራን ሠራች፡፡

  በዚያን ዘመን የመዝሙር አሳታሚና አከፋፋይ የለም ነበር፡፡ መዝሙር ሲታተምም አድራሻ ስለሌለ ካሴት ላይ ‘ከጊዮርጊስ በስተጀርባ’ ‘ከቀጨኔ መድኃኔዓለም በስተጀርባ’ ወዘተ የሚሉ ነበሩ፡፡ በሒደት ግን ዘማርያን እየበዙ መጡ፡፡ ሙዚቃ ቤቶች ወደ መዝሙር ቤትነት መቀየር ጀመሩ፡፡ ማርስ ሙዚቃ ቤት ወደ አርያም መዝሙር ቤት ተለወጠ፡፡ መቅደላ ሙዚቃ ቤት የነበረው ወደ መዝሙር ቤትነት ተለወጠ፡፡ 

ያን ጊዜ መዝሙር የሚሠራው በፍርሃት ነበር፡፡ ዘማርያን ቢያንስ የሚሠሩትን መዝሙር እዩልኝ የሚሉ ነበሩ፡፡ መዝሙሩ ሲሠራም ችኩልነት አልነበረም፡፡ ድምፅ ስላማረ ብቻ ዘማሪ ለመሆን መጣደፍ አልነበረም፡፡ አዝማቹን ተቀርጾ አቀናብርልኝ ማለት የለም ነበር፡፡ ሁሉም እኔ አውቃለሁ ብለው አያስቡም ነበር፡፡ መዝሙር ሲሠሩ ሱባኤ ይይዛሉ፡፡ መባዕ ልከው ጸሎት ያስይዛሉ፡፡ 

  ቀስ በቀስ የፋንቱ ወልዴ ትውፊታዊ የታቦት መዝሙራት በድንቅ ሁኔታ ተሠርተውም ሲወጡ የመዝሙሩ ዘርፍ እየተነቃቃ መጣ፡፡ በሒደት ግን ተደማጭነት ለማግኘት በሚል ደመቅ ደመቅ እያለ እንዲሔድ የመፈለግ ዝንባሌ መጣ፡፡ በወቅቱ የዜማ መሣሪያ ተጫዋቾችም በቴአትር ቤት የሚሠሩ ነበሩ፡፡ በጣም የሚያስደንቀኝ ደጀን ማን ችሎት የሚባል አስገራሚ መሰንቆ ተጫዋች ነበረ፡፡ በመሰንቆ የሰው ስም እስከ መጥራት ድረስ ችሎታ የነበረው ነው፡፡ ዘውዱ አማረ ደግሞ እጅግ የተረጋጋ መሣሪያ ተጫዋች ነበረ፡፡ በሁለቱም እጁ መሣሪያ የሚጫወት ነበረ፡፡ ዘውዱ ጌታቸውና ኤልያስ ደግሞ መዝሙሮቹን እስከመገምገም የሚደርሱ አገልጋዮች ናቸው፡፡ በከበሮ ደግሞ ዲያቆን ባሳዝነው ኤርምያስና አካሉ ዮሴፍ የተሰኙ የጎላ ሚካኤል ልጆች ነበሩ፡፡

መምህር ተስፉ ግርማ ፦ ለመዝሙር የግጥም ችሎታ ብቻውን በቂ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ችሎታው ሊኖርህ ይችላል፡፡ መዝሙር ግን ሃይማኖታዊ ጉዳይ ስለሆነ ቢቻል የሃይማኖትን ትምህርት በደንብ ቢማር ጥሩ ነው፡፡ ካልተማረም ለተማሩት ማሳየት ይገባዋል፡፡ ደስ ስላለህ ብቻ መዝሙር አድርገህ አትዘምረውም፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋ በአስተምህሮ የማትቀበላቸውን ቃላት ያለባቸው መዝሙራት ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ ዘማርያንም መዝሙሩን ሲቀበሉ ስለ መዝሙሩ ሃሳብ ማወቅ አለባቸው፡፡ ስለሚዘምሩበት ርእስ በደንብ መማር አለባቸው፡፡ ግጥም ትልቅ ሃሳብን በትንሽ ሃሳብ የማስቀመጥ ምጥ ነው፡፡ ስለዚህ ትኩረት ይፈልጋል፡፡

  በመዝሙሩ ዘርፍ ቢሆን ደስ የሚለኝ በሰማንያዎቹ የነበረው የመዝሙር መንፈስ ቢመለስ ደስ ይለኛል፡፡ የተመስጦና የንስሓ መዝሙር ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ እንደ ጸሎት የምትጸልየው ዓይነት መዝሙር ቢሆን ደስ ይለኛል፡፡ ሁለተኛ የኅብረት መዝሙር ቢበዛ ደስ ይለኛል፡፡ ግላዊነትና ፉክክር ውስጥ ከመግባት አብሮ መዘመር ቢበዛ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ስብከተ ወንጌል የሚመሩ ሰዎችም ታዋቂ ዘማሪ እያሉ ጉባኤ መጥራታቸውም ዘማርያኑም ፡፡ ዘማርያኑ ውስጥም ሥጋዊ ፉክክርን አምጥቶአል፡፡  

  የአገልጋዮች ማኅበር በተደጋጋሚ ተቋቁሞ ነበር፡፡ ሁሉም ውስጥ በጸሐፊነትም አገልግዬ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ለጊዜው ማኅበር ይሆንና ይጀመራል ብዙም ግን አይጸናም፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር በኩል ያለው ችግር ልጆችዋን ያለማቀፍዋ ጉዳይ ነው፡፡ የአገልጋዮቹ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱም ችግር ነው፡፡ መከልከል ብቻ ሳይሆን ልጆችዋን መሰብሰብ ያለባት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የመዝሙር ክምችት እንኳን በአግባቡ አይቀመጥም፡፡ ዘማርያን ራሳቸው የራሳቸውን መዝሙር ላያስቀምጡ ይችላሉ፡፡ የሚገርመው እስከ ብዙ ዘመን ድረስ በአንድ ዓይነት የካሴት ከቨር ብዙ መዝሙራት እየተቀያየሩ ይሸጡ ሁሉ ነበር፡፡ የመዝሙሩን ዘርፍ የሚከታተል አካልም የለም፡፡ መዝሙር አይቶ የሚያርምም አካል የለም፡፡ ይህ ሁሉ ትኩረት ሊሠጠው የሚገባ ነገር ነው፡፡ 

  ለመዝሙሩ አገልግሎት ብዙዎች ደክመዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አምላክ ዋጋቸውን ያስባል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት ስለሆነች ሌላውን ሳይቃርሙ ቤተ ክርስቲያንዋን አውቆ የሚያገለግል ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ ሰዓታቱን ኪዳኑን ማሕሌቱን በማወቅ በአባቶች ምስጋና ለማመስገን መጣር አለበት እላለሁ፡፡ 

Share your love

8 አስተያየቶች

  1. ህፃናት ሆነን በእመቤታችን ስም እምንጠጣት ፅዋ ማህበር ነበረችን አሁንም አለች። 30 አመት ገደማ ይሆናታል። ታዲያ ከፀሎት በሃላ ስኳር ሞቅ ያለው ሻይ እስኪሰጠን የ3 ሊትር ቢጫ ጀሪካን እየመታን እምንዘምረው ቸሩ ሆይ፣ ማርያም እንወድሻለን፣ የፅድቅ በርነሽ፣ አይረሳኝም። ጨርሰን ስንወጣ ደሞ 1 ከምሰሽቱ አካባቢ ይሆናል ልክ እምናውቃቸው ዼንጤ ጐረቤቶች በር ላይ ስንደርስ
    ሀሌ በል ሀሌ
    ሀሌ
    1234
    ሀሌ
    ማርያም አማላጅ ናት
    ሀሌ
    567
    ሀሌ
    ዼንጤ ነው የካዳት።
    ሀሌ በል ሀሌ”

  2. በውነቱ ድንቅ ነው! የተገባ ቆይታ እና ቃለመጠይቅ! በጎ አገልግሎት ያበረከቱ በአጸደ ነብስ ያኑርልን!

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *