የዛሬው ጹሁፍ በውሳኔ አሰጣጥ ጉዳይ እና በሕይወት ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን ስንወስን የሚገጥሙን የሥነ ልቡና ዝንፈቶችን (cognitive dissonance) ይዳስሳል።
ስለ ውሳኔ ስናስብ ስለ ራሳችን ማሰብ ግድ ይለናል። ምክንያቱም ለራሳችን ያለን ግምት ነው በውሳኔ አሠጣጥ ሒደታችን ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድረው። ስለራሳችን ያለን በጎ አመለካከት ለአእምሮም ሆነ አካላዊ ጤናችን እና በሕይወት ላለን ደስታ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
ለዚህም ነው ስለ ራሳችን በጎ እና የማይለዋወጥ ምስል (consistent self-image) እንዲኖረን ብዙ ነገሮችን ስንሠራ የምንታየው።
ይሄን የማንነት ምስል ለመጠበቅ ስኬትን ለራሳችን የመውሰድ ጠንካራ ዝንባሌ ሲኖረን ውድቀትን ደግሞ ለሌሎች እንሠጣለን። ገና ልጅ እያለን በቋንቋችን ሳይቀር የሚዋሐደን ይሄ አስተሳሰብ ነው። ጥሩ ውጤት በትምህርት ስናገኝ “አገኘሁ!” እንላለን። መጥፎ ውጤት “ሲ” ወይም “ዲ” ስናገኝ “አስተማሪው ሠጠኝ” ነው የምንለው። ይሄ ውድቀትን ለራስ ባለመሥጠት ሥነ ልቡናዊ ማንነታችንን እየጠበቅን ነው። በዚህም ራሳችንን ከተራ ሰዎች የተሻልን እንደሆንን እናምናለን፣ በእውቀት፣ በውበት፣ በባህርይ ፣ በጥረት እና በችሎታ ከብዙ ሰዎች እኛ የተሻልን እንደሆን እናምናለን ወይም ማመን እንፈልጋለን።
ይሄ ስለ ራስ ያለ የተጋነነ በጎ አመለካከት በጥቂት ሰዎች ላይ የሚስተዋል ሳይሆን ብዙ ሰዎች ያላቸው ማንነት ነው። አንዳንዴ ግን ሕይወት ይሄን ስለራስ ያለንን ግምት ይቀደዋል (smash it)። ከሥራ እንባረራለን ፣ ሰዎች ይተዉናል ፣ ለማግኘት ተስፋ ያደረግነውን ነገር እናጣለን ወይም በሰዎች ፊት ከፍተኛ ነቀፋ ይደርስብናል ፥ እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ደግሞ ለራሳችን ከሠጠነው ግምት ተቃራኒ የሆኑ ውሳኔዎችን እንወስናለን።
ይሄ ስለራስ ባለ ልዩ እና ከእውነታው የተለየ ምስል ምክንያት ፊት ለፊት ያለን ሐቅ ለመቀበል እንቸገራለን። በዚህም ቀላል እና ጊዜያዊ የነበሩ ችግሮቻችን ሥር ይሰድዳሉ። ይሄን ስሱ (fragile) የሆነ ስለራስ ያለን ግምት ለመጠበቅ ጊዜያችንን ባልሆኑ ነገሮች እናባክናለን ፣ አላስፈላጊ እና ጊዜ አባካኝ ክርክሮች ውስጥ እንጠመዳለን ፣ አንዳንድ ሰዎች ወደ ሱስ ወይም ለእነሱ የማይመጥን ግንኙነቶች ውስጥ ይነከራሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የቶልስቶይ ወንጀለኞች ለዚህ አመለካከት ገላጭ ምሳሌዎች ናቸው። ቶልስቶይ በልቦለዶቹ ወንጀለኞቹ ሁለት ዓይነት ሥነ ልቡና እንዳላቸው ያሳየናል።
የመጀመሪያው እውነትን ይሸሹታል ፥ በመካድ፤
መካድ የሚከሰተው ስለሕይወት ኃያል እውነት ፊትለፊት ሲገጥመን እና ያን ከመቀበል ይልቅ መካድን ስንመርጥ ነው። ለምሳሌ ልጆቿቸው ከመስመር እየወጡ እና ያልሆነ ሕይወት ውስጥ እየገቡ የሚመለከቱ ወላጆች ይሄን ወዳጆቻቸው ሲነግሯቸው የመጀመሪያው ግብረ መልሳቸው መካድ ነው። እነዛ ያሳደጓቸው ልጆች፣ ከምንም ነገር በላይ የሚወዷቸው ልጆቻቸው በመጥፎ ሕይወት ውስጥ ተገኝተዋለ ብለው ማሰብ አይፈልጉም። ስለዚህ ወሬውን ያመጡላቸውን ሰዎች መንቀፍ ወይም መቀየም ይቀላቸዋል እውነታን ከመጋፈጥ ይልቅ።
በተመሳሳይ ቆዳችን ላይ የሆነ ጥቁር ነጥብ ቢወጣ፣ መጀመሪያ ሊያስደነግጠን ይችላል። ከዛ ግን እንረሳዋለን። ከሳምንታት በኋላ ስናየው የበለጠ ጠቆረ እንጂ የተለወጠ ነገር የለም። ምንአልባት ከዚህ ከሳምንታት መካድ በኋላ የበለጠ መጥቆሩ ከመካድ ሊያወጣን ይችላል። የመጀመሪያው ግብረ መልሳችን ግን መካድ ነው። እንዲሁ እንደወጣ እንዲሁ እንዲጠፋ መመኘት ነው።
ልጃቸው ወደጦርነት የሄደ እና ከዛ ያልተመለሰ ቤተሰብ አውቃለሁ። ጦርነቱ ካለቀ ረጅም ጊዜ ቢሆንም የልጃቸው አለመመለስን ሞቶ ነው ብሎ መቀበል አይፈልጉም፤ ሰው ሁሉ ያን ቢያምንም። ይሄ እውነታ የሚነግረኝ በጣም የምንወደው ነገር ሲሆን በዛ ነገር ላይ የደረሰ ክፍ ነገርን መቀበል ይከብደናል። በጣም የምንጠላው ነገርም ሲሆን ያ ነገር በጎ ነገር እንዳለው መቀበል እንቸገራለን። ስለዚህ ጠንካራ ስሜቶች ሁልጊዜ መካድ ይከተላቸዋል። ለምሳሌ ሂትለር ሕጻናትን የሚወድ እና ለሕጻናት ስሱ ልብ እንዳለው መቀበለ ይከብደናል። ምክንያቱም ሂትለር በብዙ ነገር ክፉ እና አረመኔ ስለሆነ። አንድ የሚሊተሪ ስትራቴጂስት “ጠላቴን አልጠላውም፣ ምክንያቱም ጥላቻ ጠላቴን እንዳላይ ይከልለኛል” ይላል። ጥላቻ የወረረው አዕምሮ ፈጽሞ ስትራቴጂክ ውሳኔዎችን መወሰን አይችልም። ፍቅርም የወረሰው አዕምሮ እውነታን የመጋፈጥ አቅም የለውም።
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሱስ (addiction) ነው። የሰው ልዩ ባህሪው ራሱን ፍጹም መውደዱ ነው። በዚህም ማናችንም ደደብ እንደሆንን እና የሆኑ ነገሮችን ማድረግ እንደማንችል መቀበል ይቸግረናል። ለዚህ ነው በሌሎች ላይ ውበት ስናይ የሚቀናን መተቸት ወይም የሚነቀፍ ነገር መፈለግ የሚሆነው። ምክንያቱም ያ ሰው ከኛ የሚያንስበትን ነገር ነው የምንፈልገው። ሱስ ከዚህ የሚመነጭ ነው። ሱሰኛ ሰዎችን ተመልከቱ። (በርግጥ በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ማን ሱሰኛ ያልሆነ አለ?) ሁሉም በማንኛውም ሰዓት ያን ሱስ ማቆም እንደሚችሉ ነው የሚያምኑት። ምክንያቱም አልችልም የሚለው ስሜት በከፍተኛ ደረጃ ለራሳቸው የሰጡትን በጎ ስሜት (self-iamge) ይጎዳዋል። ስለዚህ ሰው ሁሉ የሚያውቀውን እውነት ይክዱታል። ከሱ መውጣት እንደከበዳቸው።
ሾፐናወር ለሰው ልጅ መቀበል ከሚከብደው አሉታዊ ስሜት ከሆኑት ትልቁ “ደደብ ነኝ የሚለው ስሜት ነው” ይላል። ይሄ ያለመቻል ስሜት ለራሳችን የሰጠነውን የተጋነነ ስሜት፣ ራስን ከመውደድ እና ስሱ (frgile) የሆነውን ማንነታችን እንዳይጎዳ ከመጠበቅ የመጣ ፍላጎት ስለሆነ ፊት ለፊት ያለውን ሀቅ እንሸሻለን፣ እንክደዋለን። ይሄ የጥሩ ውሳኔዎች ሁሉ የመጀመሪያው እንቅፋት ነው።
ሁለተኛው የቶልስቶይ ወንጀለኞች ባህሪ ምክንያት መስጠት (self-justification) ነው፤
የቶልስቶይ ወንጀለኞች ወንጀል ከፈጸሙ በኋላ ያን ወንጀል በዛ ሁኔታ (context) ውስጥ ወይም በእነርሱ ላይ ከደረሰባቸው አንጻር ተገቢ እንደሆነ ምክንያት ይሰጣሉ። ጉቦ የሚሰጥ ሰው ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት ጉቦ ከሚቀበለው ልዩነት የለውም። ሁለቱም ካለጉቦ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል ነው የሚናገሩት። ጉቦ ተቀባዩ ያለጉቦ የኑሮ ውጣ ውረድን ማሸነፍ እንደማይችል ሲናገር ፥ ጉቦ ሰጪውም የቢሮክራሲውን ውጣ ውረድ ያለጉቦ ማለፍ እንደማይችል ነው የሚገልጸው።
ሁለቱም ወንጀል እየሰሩ እና በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቃቸውን አስነዋሪ ተግባር እየሰሩ መሆናቸውን ማመን አይፈልጉም። ይልቁስ ከመሠረታዊ እምነታቸው ጋር እንዳይጋጭ ለዛ ምክንያት ይሰጣሉ።
ምክንያት የመስጠት (justification) ትልቁ መገለጫ ማቆም ነው። ለምሳሌ ሲጋራ ለማቆም ጥሮ ያልቻለ ግለሰብ የሚያደርገው ሲጋራ መጥፎ ነው ብሎ ማመን ያቆማል። ይልቁስ ሲጋራ እያጨሱ እስከ 90 እና 80 ዓመት የኖሩ ጥቂት ሰዎችን መጥቀስ ይጀምራል ወይም “ሕይወት ማለት ካላጨስክ እና ካልጠጣክ ምኑን ሕይወት ሆነ?” ማለት ይጀምራል። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአገቱኒ መጽሐፉ የነገረን የዚህ ባህሪ ተጠቂ መሆኑን ነበር። አቆመ። ቤተክርስቲያን መሄድ እና ማስቀደስ አቆመ። ንጉሱ “ለምን አቆምክ?” ብለው ሲጠይቁት የመለሰው “መጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላኛውን አዙርለት ይላል፤ እኔ ግን መልሼ ነው የምመታው። ለነገ አትጨነቁ ይላል፣ እኔ ደግሞ ልጆች አሉኝ አለመጨነቅ አልችልም። ስለዚህ አቆምኩኝ” አለ። አለመጨነቅ ጥሩ መሆኑን ሳይሆን ፥ ለመጨነቁ ምክንያት መስጠት ተያያዘ። መታገሰን ገንዘብ ከማድረግ ይልቅ ፥ ታገሱ የሚለውን ስብከት መስማት ማቆም የቶልስቶይ ወንጀለኞች ባህሪ ነው።
በሕይወታችሁ ጥሩ ውሳኔ ለመወሰን ትፈልጋላችሁ? በተቻለ መጠን እውነታን ተጋፈጡ። ሲ ኤስ ሉዊስ ለኦክስፎርድ ተማሪዎቹ የሚላቸው ይሄን ነበር “እውነታን በጥቂቱ ካሳየናችሁ ፥ እውነትን የማየት ድፍረት በጥቂት ከሰጠናችሁ፤ ያን ጊዜ ስኬታማ ፕሮፌሰሮች እንባላለን። የኛ ዓላማ እውነትን የሚያዩ እና ያዩትን እውነት የመናገር ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ማፍራት ነው።”
እውነታው ከምናስበው በላይ ደደቦች ነን። እውነታው ብዙ ነገሮችን ማቆም አንችልም። እውነታው ስሜታዊ ነን። እውነታው ፈሪዎች ነን። እውነታው ከመጠን በላይ በሰዎች መወደድ እንፈልጋለን። እውነታው እንደምናስበው ጥሩዎች አይደለንም። እውነታው ሰንፎች ነን። እውነታው አድሎአዊ እና ዘረኞች ነን። ይሄን ስለራስ መቀበል ያማል፣ ግን ይሄን በጊዜ እንደመቀበል ምንም ፈጣን የመፍትሔ እና የለውጥ መንገድ የለም። አዎ ለዚህ ብዙ ምክንያቶችን መስጠት እንችላለን፤ ግን እውነታውን አይቀይሩትም።
ቻርሊ መንገር ስለወዳጁ ልጅ እና አባቱ ስላለው ነገር እዚህ ጋር ማንሳቱ በጣም ጠቃሚ ነው። ልጁ ከአባቱ የሳንቲም ማጠራቀሚያ “በኋላ እተካለሁ” እያለ ሁልጊዜ ይወስዳል። ይሄን ባህሪ ያስተዋለ አባት “ልጄ! ግድ የለህም ስትወስድ በኋላ እተከዋለሁ እያልክ ተደብቀህ ከምትወስድ ፥ በወሰድክ ቁጥር ሁሉ ራስህን ሌባ እያልክ ጥራ” አለው። ያ ልጅ ዛሬ አድጎ እና ተለውጦ የካሊፎርኒያ ቢዝነስ ስኩል ዲን ሆነ። መጥፎ ነገር ስናደርግ ራሳችንን በዛ ስም እንጥራው። አዎ፣ “ዝሙት እየሠራሁ ነው። እየሰረቅሁኝ ነው። ወንጀል እየሠራሁ ነው” እንበል። በውሸት ምክንያት የተገነባን የራስ ምስል (self-iamge) ከመጠበቅ ይልቅ፤ ራሳችንን ለዛ ጠባይ ተገቢ በሆነ ስም እንጥራው። ከዛ ጠባይ ለመላቀቀ ትልቅ እርዳታ ይኖረዋል። ከዐሠርቱ ትእዛዛት ሁለተኛው “የተቀረጸ ምስል ለራስህ አታኑር” የሚል ነው። ይሄ የተቀረጸ ምስል አንዱ የራስ ምስል (self-image) ነው።
በምክንያት የምንጠብቀው፣ እውነትን በመካድ ያቆምነው፣ ይሄ ስሱ ምስል (fragile self-image)፣ የሰዎችን መጥፎ ንግግር እና ነቀፋ መቋቋም የማይችለው ፣ በተግሳጽ እና በአሉታዊ ኮሜንት የሚፈርሰው ፣ ላይክ እና አስመሳይ የማሽሞንሞን ቃሎች የሚያለመልሙት የተቀረጸው የራስ-ምስል (carved self-image) ለጥሩ የሕይወት ውሳኔ ሁለተኛው እንቅፋት ነው።
የ ምትጽፏችው ጽሑፎች በጣም አስተማሪና ቁምነገር አዘል ናች
Thank you for sharing 🙏🏽
አሪፍ ነው 👏👏👏👍
ይቀጥል
ጽሁፉ ለማንበብ ከባድ ነው ነገር ግን ራሴን የቱ ጋር እንዳለሁ እንድመለከት ተረድታችሁኛል አመሰግናለሁ
በርቱ።
ጥሩ የውሳኔ ሰውም ያድርገን።
እናመሰግናለን
እግዚአብሔር ያክብርልን።
Enamesegnalen
እናመሰግናለን መምህር
እጅግ በጣም ጥሩ ነው ….
ግን ይህ ስሜት ለኩን ሲያልፍስ ለራስ ጥፋት እራስን ጥፋተኛ ከማድረግ አልፎ ለሰውም ጥፋት ራስን መውቀስስ እንዴት ይታያል (ለራሳችን ያለን አሉታዊ ስዕለ)።
ምትሉኝ ነገር ካለ🙏
True nw gin it needs tirgum
እራሴን ነው ያየሁት
እናመሰግናለን ወንድማችን
በጣም ቆንጆ ነው ፤ ከሥነ ሰብእ እና ሥነ ሕይወት ጋር በተያያዘ እንደዚኹ ቀጥሉበት።
It’s a great essay (Note)
Always hating rebuke no matter our failure. Psalm 49 says, “Why do you hate my discipline and speak my law?”
እግዚአብሔር ይስጥልን በጣም ገንቢ ምክር ነው በርቱልን
የገባኝ ነገር ቢኖር በዚህ ዘመን ሚዲያዎች ላይ ሰለራስህ ጥሩ ነገር ይኑርህ/ ይኑርሽ (Self image) ብለው የሚጠሩት እና በሰፊው የሚሰብኩት ነገር የትእቢት እና የቁልቁለት መንገድ መሆኑ ነው:: ለኔ በጊዜ ነው የደርስክልኝ::
ቃለህይወትን ያሰማልን::
When a false self-image gets destroyed, it can be a challenging but ultimately liberating experience. It often involves a period of self-reflection, reevaluation of one’s beliefs and values, and potentially confronting uncomfortable truths about oneself.
This process can ultimately lead to personal growth, increased confidence, and a deeper sense of fulfillment.
Thank you for the essay, it was quite an eye opener 🙏🏾
እግዚአብሔር ይስጥልን::
ጥሩ እና አስተማሪ ፅሁፍ ነው እግዚአብሔር ያበርክትልን 🙏
ደስ የሚል ገንቢ ጽሑፍ ነው። ነገር ጥያቄ በዚህ መንገድ ኹሉ ጊዜ የጥፋተኝነት ስሜት መሰማትስ ጤነኝነት ነው ወይ?
ከዐሠርቱ ትእዛዛት ሁለተኛው “የተቀረጸ ምስል ለራስህ አታኑር” የሚል ነው። ይሄ የተቀረጸ ምስል አንዱ የራስ ምስል (self-image) ነው።
…
ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
እጅግ በጣም ጥሩ ነው እግዚአብሔር ይስጥልን
በጣም ዐይን ከፋች (eye-opening) የሆነ ፅሁፍ ነዉ። ከዚህ በኋላ በምወስናቸው ውሳኔዎች ዉስጥ የነገሩን እውነታ ለመፈተሽ እጥራለው ።
ቃለ ህይወት ያሰማልን። በርቱ!
እግዚአብሔር ያክብርልን
እግዚአብሔር ይስጥልን
Tnku Tnku Tnku betammm ketlubet🙏🙏🙏
” ከዐሠርቱ ትእዛዛት ሁለተኛው “የተቀረጸ ምስል ለራስህ አታኑር” የሚል ነው። ይሄ የተቀረጸ ምስል አንዱ የራስ ምስል (self-image) ነው። ”
እንደሁልጊዜው በጣም አስደናቂ ጽሑፍ ነው፣ ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን