የተዋጀንበት ምሥጢር

በሉቃ 15 ላይ በወንድሙ መመለስ አኩርፎ የነበረው ልጅ አባቱን እኔ ዘመኔን ሁሉ አገለገልሁህ ግን አንዲት የፍየል ጠቦት (በፈለጋችሁት ሥጦታ መስሉት) እንኳ አልሰጠኸኝም ሲለው “የእኔ የሆነ ሁሉ የአንተ ነው” በማለት የእርሱ ዋጋ አብሮ በመኖር እንጂ በሥጦታ የተወሰነ እንዳልሆነ በመንገር አጽናንቶታል። ሰው የሆነበትን ዋና ምክንያት ሲያጠይቅም “እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ” ብሏል። ዮሐ .10፥10

በዚህ ዓለም ያለ የልባችንን ምድራዊ ምኞት ለመፈጸምም አልመጣም። እንዲያውም የእርሱ የሆኑት በዓለም ሀሳብ ራሳቸውን አያጠላልፉም። በማኅፀን ያለ ጽንስ በእናቱ ማኅፀን ሳለ የሚያስፈልገውን በእትብት አማካኝነት ያገኛል። አንዳንድ ጊዜ ከእናቱ ጋር የተሳሰረበት እትብት በአንገቱ ተጠምጥሞ አንቆ ይገድለዋል። ስለዚህ አዋላጆች የመጀመሪያ ሥራቸው ልጁ ከማኅፀን ሊወጣ ሲል ጣታቸውን ሰደድ አድርገው አንገቱ ላይ እትብቱ እንዳልተጠመጠመ ማረጋገጥ ነው:: እኛም እንዲሁ በሕይወት እንዳንኖር አንዱ የሚያንቀን ኃጢአት ያልሆኑ ከዕለታዊ የኑሮ ሁኔታ የሚመደቡ ማነቆዎች ናቸው። መብልና መጠጥ፣ ትዳር፣ የቤተሰብ ኃላፊነት፣ ሥራ፣ ወዘተ. . . ። ልጁ ከማኅፀን በሰላም ከወጣ ሰፊ በሆነችዋ፤ ወላጆቹንና ቤተ ሰዎቹን ለማወቅ ዕድል በሚያገኝባት ዓለም ላይ ለመኖር እትብቱ በመቁረጥ በማኅፀን ላይ ካለው ጥገኝነት እንዲላቀቅ ይደረጋል። ከነ እትብቱ መኖር ፈፅሞ አይታሰብም። እናስተውል! እኛም የአዳም ማኅፀን ከሆነች ከምድር ጋር የሚያጣብቀን እትብት (ስለ ምድራዊ ኑሮ አብዝቶ ማሰብ) ተቆርጦ ካልተጣለ እንደ ወላጅ ሥላሴን፤ እንደ ቤተ ሰዎች እመቤታችንን፣ ቅዱሳን መላእክትንና በሰማይ የሚያድሩ ቅዱሳንን የማየትና ከእነርሱ ጋር የመኖር ዕድል አይኖረንም። በቅዳሴ “በሰማይ የሃሉ ልብክሙ” ልባችሁ በሰማይ ይሁን የሚል ለዚህ ነው:: 

የሲዖልም አሰተሳሰብ ከዚሁ የሚመደብ ነው። ሰው ሲዖልን በሁለት መንገድ ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያው በዚህ ዓለም ሳለ በፍርሃት መንፈስ፤ ሁለተኛው መዳረሻው እዚያ ሲሆን በአካል ነው። በአብዛኛው ጸሎታችን፣ ትምህርታችን፣ ሀሳባችን ሁሉ ስለ ሲዖል የሆንን አለን። ቅጣት እንዳለ ማወቅና ያን በፍርሃት መንፈስ እያሰቡ ተጣብቆ መኖር የተለያዩ ነገሮች ናቸው:: ካለበለዚያ “መዝገባችን ባለበት ልባችን በዚያ መሆኑን ” ያሳያል። ማቴ 6 

እግዚአብሔርን የማወቅና የመምሰል ምሥጢር ታላቅ ነው። ያም የተገለጠ በልጁ ነው:: እኛም ልናውቀው የምንችለው “እርሱ በእኛ እኛም በእርሱ ስንኖር” ነው። ሁሉን ማድረግ ያለብንም ያን ለማሳካት መሆን ይኖርበታል። የብርሃን አምላክ የሕይወት መገኛ የእውቀት መጀመሪያ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር የመኖርን ምሥጢር ይገልፅልን ዘንድ ፈቃዱ ይሁን! 

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

8 አስተያየቶች

  1. አሜን ።ቃለ ሕይወት ያሰማልን ቀሲስ
    ጽሑፉ ግን ቴሌግራም ላይ ከተለቀቀው(ጃንደረባው ሚዲያ) እና ወደዚኽ ከሚመራው የመግቢያ ጹሑፍ ጋር ፈጽሞ አይገናኝም ያን ማስተካከል ቢቻል መልካም ነው።

  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን አባታችን በዛውም ትርጉሙን ቢነግሩን የህይወት ቃል ምንድነው በ ህይወት የምንኖረው ቃል ነው ወይስ ወደ ህይወት ምንገባበት ቃል ነው እንዴት፣? የት?ነው ምንሰማው

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *