የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ | ክፍል ፪

የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ

ክፍል ፪

ወጥመድ የሌለበት የሕይወት መንገድ ያጋጠመው ከፍጡራን መካከል ማንም የለም። በመላእክት ዘንድ ሳጥናኤል ነበረ። በሰዎችም ዘንድ የእድሜ ልክ ጠላትነት ካለብን ከሰይጣን ዘንድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይታጠፍ ተዘርግቶ የሚኖር ወጥመድ አለ። ለዚህ ነው ቅዱስ መጽሐፍ “ወጥመድ በአንተ ላይ አለ” ኤር. 48፥43 ሲል የተናገረው። 

በክንፍ የሚበሩ ባሕሩን ገደሉን የሚሻገሩ የሰማይ አዕዋፍ በምድር ላይ በተጠመደ ወጥመድ መያዛቸው ግን የሚገርም ነገር ነው። ተራራ ሳይጋርዳቸው ከአንዱ ቦታ ወደሌላ የወደዱት ቦታ መሄድ ይቻላቸዋል፤ ባሕርና ገደል አያስጨንቃቸውም፤ ነገር ግን የአዳኞች ወጥመድ ይይዛቸዋል። ነቢዩ ዳዊት ወጥመድ በሕይወቱ የገጠመችውን ሰው የገለጠው አዳኞች ባጠመዷት ወፍ ምሳሌነት ነው። “ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች” መዝ 128 በሚለው ዝማሬ ውስጥ የወፎችን በወጥመድ ውስጥ መውደቅ ይገልጻል። 

ወፎችን በወጥመድ ውስጥ የሚጥላቸው ምንድነው? ቢሉ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ ዋናው ግን መጽሐፍ የመሰከረላቸው ወጥመዳቸው በመብል ምክንያት ነው።

የሥጋ ለባሽ ሁሉ ወጥመድ ምክንያቱ ምንድነው ቢባል ከሆድ የሚቀድም ያለ አይመስለኝም። ለዚህ ነው ማር ይስሐቅ “ነቅዐ ኩሎን ዕከያት፤ የኃጣውዕ ሁሉ መነሻ” በማለት የሚገልጸው። ለወፎችም ወጥመድ ውስጥ መውደቅ ምክንያቱ እሱ ነው። ምንም እንኳን በሰማይ ቢበሩ የሚበሉትን ፍለጋ ወደ ምድር መምጣታቸው አይቀርም። 

አዳኞች ይህንን ስለሚያውቁ ወጥመዳቸውን አዘጋጅተው ይጠብቃሉ እንጅ ወፎቹ ሲበሩ አብረው አይበሩም። 

ወንድሜ ደካማ ጎንህን አዳኞች ካወቁብህ ወጥመዳቸውን ዘርግተው አንተን መጠበቅ አይሰለቻቸውም። በሰማይ ብትበርም አንድ ቀን ይወርዳል ብለው ወጥመድ ማዘጋጀታቸውን አይተዉም። የኛ አዳኞቻችን አጋንንት ናቸው፤ ደካማ ጎናችንን ሳያጠኑ ለሕይወታችን ወጥመድ የማይዘረጉ ጠንቃቃ አዳኞች ናቸው። 

እስኪ ልብ በሉና ተመልከቱት አጥማጆች እኮ ለሁሉም ለየራሱ ለሚያጠምዱት ነገር ሁሉ ልዩ ልዩ ማጥመጃ አላቸው። ዓሣ በሚያጠምዱበት ወጥመድ ወፎችን አያጠምዱም። ጦጣና ዝንጀሮ በሚያጠምዱበትም ቆቅና ዥግራ አያጠምዱም። አጥማጆች ለሁሉም የሚገባውን ወጥመድ ማዘጋጀት ያውቁበታል። 

ዲያብሎስም ጠንቃቃ አጥማጅ ነው ሁሉንም የመንግሥተ ሰማያት መንገደኞች በተመሳሳይ ወጥመድ የሚያጠምድ እንዳይመስላችሁ ለሁላችንም ደካማ ጎናችንን አጥንቶ ወጥመዱን ያዘጋጃል። ደናግሉን በዝሙት፣ መነኮሳቱን በስስት፣ ባለትዳሮችን በቅንዓት፣ ካህናቱን በትዕቢት፣ ሴቶችን በትውዝፍት፣ ወንዶችን በነጽሮ ብእሲት ሊያጠምድ ይሞክራል። አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገዳም ቢያገኘው ባህታዊነቱን አውቆ ገዳማውያንን በሚያሸንፍበት ፈተና ነው የፈተነው። 

በጾም በጸሎት የሚኖር አንድ ገዳማዊ ሰው በስስት ቢፈተን ለመውደቅ ቅርብ እንደሆነ ስለተረዳ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል” ማቴ 4፥3 አለው። ለተራበ ሰው ሌላ ምን ወጥመድ ሊዘጋጅለት ይችላል? ዲያብሎስ መጀመሪያ ያደረገው ደካማ ጎኑን ማጥናት ነበረ እሱም እንደተራበ አወቀ። “ከዚህ በኋላ ተራበ” ብሎ ወንጌላዊ ማቴዎስ እንደነገረን። በሌላ ጊዜ በቤተ መቅደስ ሲያገኘው ወጥመዱን ቀይሯል − የትዕቢት ወጥመድ አዘጋጅቷል ማቴ 4፥5። በካህናት መካከል ሊጠመድ የሚችል ወጥመድ ይህ ነዋ! በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላ ነው ማቴ 4፥8።

ዲያብሎስ በዚህ ልክ ወጥመዱን ለማዘጋጀት የሚተጋ ከሆነ እኛም ነፍሳችንን ከአዳኙ ወጥመድ ለማዳን በጥበብ መመላለስ ይገባናል። የሰማይ ወፎች ክንፍ ኖሯቸው እየበረሩ ከወጥመድ ካላመለጡ እኛም በምድር ላይ እየተርመሰመስን የምንኖር ለወጥመዱ ምን ያክል የቀረብን እንሆን ይሆን? እንጃ! ይህ ነገር ከባድ ነው። ከአጥማጁ ለመዳን እንኳን ያልተፈቀደልንን የተፈቀደልንንም ቢሆን ልንተው ይገባናል። ብጹዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተናገሩት እና በገድላቸው ተጽፎ የሚገኘው ይህ ቃል ሁል ጊዜ ይገርመኛል። “የሚጣፍጥ ምግብን መውደድ ኀጢአትን ያመጣል፤ ሞትን ያስከትላል፤ክንፍ ያላቸው የሰማይ ወፎች እንኳን በመብል ምክንያት ይጠመዳሉ ምግብንም በመሻት ከምድር ላይ ይወድቃሉ በወጥመድም ይያዛሉ የሰው ልጅም ምግብን በመውደድ በኃጢአት ይወድቃልና እኔስ ለሰውነቴ መብል መጠጥን አልፈልግም ልብስም አልሻም ዕራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን እንደወጣሁ ዕራቁቴን ወደ ምድር እመለሳለሁ እንጂ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም በተለየሁ ጊዜ መብል መጠጥንና ልብስን ማን ያመጣልኛል”  ብለዋል። 

የሚጣፍጠውን በልቶ ያማረውን የደመቀውን ለብሶ እግዚአብሔርን ማመስገን የተፈቀደ ቢሆንም በዲያብሎስ ወጥመድ ላለምያዝ ግ ን የተፈቀደላቸውንም ሳይቀር በመተው ነፍሳቸውን የሚጠብቁ እንደዚህ ያሉ ቅዱሳን ብዙ ናቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ”1ቆሮ 9፥27 ያለው እንዲህ ባለ ጉሰማ ነውና በሃይማኖት ውስጥ ስንኖር ጉሰማ ካልተጨመረበት የሥጋ ነጻነት ነፍሳችንን ወደ ባርነት ይመልሳታል። 

የሰማይ ወፎች የሚታይ መብል በማይታይ ወጥመድ ውስጥ ተበትኖ ይጠብቃቸዋል። በመብረር ላይ ሳሉ አቆልቁለው ሲመለከቱ መብሉ እንጅ ወጥመዱ አይታይም። ወርደው ሊበሉ ሲጀምሩ የሚታየውን መብል ሳይቀምሱት የማይታየው ወጥመድ ይይዛቸዋል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ፍጻሜአቸው ይሆናል። እኛም በሚታይ የዓለም ሥርዐት ውስጥ ብዙ የማይታዩ ኃጢአቶች እንዳሉ መርሳት የለብንም። የሚታየንን ብቻ ሳይሆን የማይታየንንም መመርመር ይገባናል። ልንበላው የቀረበልን እንጀራ ለሰይጣን ወጥመድ የማያስይዝ መሆኑን እንመርምረው። የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ በሚለው ትምህርት ውስጥ ይህንንም እናስተውላለን።

Share your love

27 አስተያየቶች

  1. አባታችን ቃለህይወት ያሰማልን
    እግዚአብሔር ከክፋ ወጥመድ ይጠብቀን በቤቱ ያፅናን

  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን በእድሜ በጤና ያቆይልን
    እኛም ለነብሳችን ከተጠመደልን ወጥመድ ለማምለጥ ቸሩ አምላካችን ይርዳን::

  3. ቃለ ሕይወትን ቃለ በረከትን ያሠማልን አባታችን በእድሜ በፀጋ ጠብቆ ያቆይልን

  4. ቃለ ሕይወትን ቃለ በረከትን ያሠማልን አባታችን በእድሜ በፀጋ ጠብቆ ያቆይልን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *