ከጌታ እግዚአብሔር ጋር የተዋሐዶ ሕይወትን መኖር የሚፈልግ ስብከት ከመስማት፣ መጽሐፍ ቅዱስና አዋልድ መጻሕፍትን ከማንበብ በማያንስ ደረጃ ማንበብ ያለበት ሌላ ትልቅ መጽሐፍ አለ፤ ፍጥረት!

የተሰጣቸው ግዕዛን ከጌታ እግዚአብሔር ጋር ደረጃው ከፍ ያለ ግንኙነት ላጎናፀፋቸው  መላእክትና ሰው ጌታ እግዚአብሔር በፍጥረት ጭምር ሀልዎቱንና ባሕርይውን ከእነርሱም ምን እንደሚጠብቅ ይተርክላቸዋል፡፡

ሰው ፍጥረትን በአምስቱ የአፍአና በአምስቱ የውስጥ ሕዋሳት የመረዳት፣ የመተርጎምና የመተረክ ጸጋ ተሰጥቶታል። በዚህ ጸጋችን ተመርተን ከላይ ስሟ በተጠቀሰ እንስሳ የተቀመጠልንን ምሳሌ እንመርምር።

አንድ መጽሐፍ ስመለከት የምድር ፍጥረት በአጠቃላይ ዔሊ ከምድር ገጽ እንድትጠፋ አድማ ያደርጋሉ። ስብሰባው ሲበተን ከመካከላቸው አንዱ ሀገር አማን ብላ ሣር የምትግጠዋን ዔሊን ያገኛትና እርሷን ለማጥፋት ውሳኔ ከተላለፈበት ስብሰባ መምጣቱን ይነግራታል፡፡ ዔሊ ምንም ጥፋት ሳይኖርባት ይህ በመወሰኑ በመገረም “ለመሆኑ ስብሰባው ላይ ማን ማን ነበረ?” ስትል ትጠይቃለች። ወሬ ነጋሪውም ማንም የቀረ እንዳልነበርና ውሳኔውም በሙሉ ድምፅ መጽደቁን ያረዳታል (አይ ድምፅi ከድምፅ አልፈው ቃል ጋር መድረስ ያልቻሉ መገለጫቸው ይህ ነው፤ ሀሳብ አልቦ ድምፅ ብቻ መሆን፤ ያለ ቃል ማሰብ አይቻልም፤ ያለ ቃል ሀሳብ አይገለጥም)። ዔሊ ትንሽ ከተከዘች በኋላ “ለመሆኑ ስብሰባው ላይ የፍጥረታት ባለቤት እግዚአብሔር ነበር?” ስትል ያልጠበቀውን ጥያቄ ለወሬ ነጋሪው አቀረበች። እርሱም ሳያመነታ “አይ እርሱስ የለም፤ አልተገኘም፤ አላየሁትም ” በማለት በርግጠኝነት ሲመልስ ዔሊ “እንግዲያውስ ተዋቸው!” ብላ ሣር ወደ መጋጧ ተመለሰች።

በአድማው የነበሩት እርሷን ለማጥፋት እያገሱና እየደነፉ ቢፈልጓት ሊያገኟት አልቻሉም፤ የፍጥረታት ጌታ ድንጋይ አልብሷት ነበርና። እንዲያውም ፍለጋው ያደከማቸው ብዙዎች ድንጋይ መስላቸው እርሷ ላይ ዐረፍ እያሉ ማለፋቸው ኋላ በተደረገ ምርመራ ተደርሶበት ተገምግመውበታል:: ዔሊ በፈጣሪዋ ታመነች፤ እንዴት ሊያድናት እንደሚችል በማሰብም ጊዜ ማጥፋት አልፈለገችም፤ ወደ ዕለታዊ ተግባሯ በእምነት ተሰማራች እንጂ። የእኛስ መታመኛችን ማን (ምን) ይሆን?

ሌላው ዔሊ በተሰጣት ተፈጥሮ በጣም ረጋ ብላ የምትኖር ፍጥረት በመሆኗ በምድር ላይ ረዥም ዕድሜ (ከ150 ዓመት በላይ) ለመኖር ከሚችሉ ጥቂት ፍጥረታት አንዷ ናት። በዚህ ዓለም ስንኖር ነገሮችን በእርጋታ ማከናወን ብዙ አደጋ ይቀንሳል። በዚህ ዘመን ሰው መነሻና መድረሻውን፣ ማንነቱን፣ ሕይወት ብሎ የያዘውን፣ የሀሳብ መንገዱን፣ ወዘተ . . . እንዳይመረምር ሕይወቱ በጥድፊያና በውክቢያ የተሞላ እንዲሆን ተደርጓል። ሳያውቅ ኖሮ ሳያውቅ ይሞታል! 

በመንፈሳዊ ሕይወትም እርጋታ (ትዕግስት) ከሕይወት ምንጭ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን ለመጀመር፤ የጀመርነውን የተጋድሎ መንገድም ለመፈጸም ቁልፍ ምሥጢር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትእግስት እንሩጥ ” ዕብ 12፥2 ሲል ይመክራል።  

መንፈሳዊ ሕይወት የጥድፊያ ሕይወት አይደለም። በአንድ ጉዳይ በቶሎ መልስ የምናገኝበት ወይም ውጤቱ በቅፅበት የሚገለፅ አይደለም፤ በልዑሉ ፈቃድ የሚወሰን ነው:: ከክርስቲያን የሚጠበቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በእርጋታና በማስተዋል መኖር ነው፤ እንደ ዔሊ።

ዔሊ የጎረሰችውን ቅጠል እንኳ ስታላምጥ በእርጋታ ነው:: ከፈጣሪያችን ጋርም ሆነ ከፍጡራን ጋር ያለንን ግንኙነት ቀስ ብለን በእርጋታ ማጣጣምን መልመድ ይጠበቅብናል። የምናየውና የምንሰማው ከመብዛቱ፤ አማራጮች ከሚቀርቡበት ፍጥነትም የተነሣ የማጣጣም ዕድላችንን ተነጥቀን ምርጫችን ውሳኔያችን ሁሉ ግብታዊ ሆነ። ኑሯችንም በፀፀት የተሞላ ሆነ፤ ጥድፊያ የፀፀት እናት ናትና።

የመጨረሻው ከዔሊ የምንማረው ከሸክም ጋር መኖርን ነው:: እንደ ክርስቲያን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምንከተል ከሆነ መሥፈርት ተቀምጧል። “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ማቴ 16፥24 በቃሉ መሠረት እያንዳንዱ የሚሸከመው የየራሱ መስቀል አለው።

ዔሊ ከሸክም ጋር መኖሯ ምናልባት እንዳልቧ ለመንቀሳቀስ አግዷት ፍጥነቷንም ቀንሶባት ሊሆን ይችላል። እኛም “ተጭኖ እንደ ልቤ አላንቀሳቅስ አለኝ” የምንለው ብዙ ነገር ሊኖር ይችላል። ጤና ማጣት፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ የመግባባት ክሂሎት አለመኖር ወዘተ . . . እያለን በተሸከምነው መስቀል ልንማረር እንችላለን፤ የተሰጠን ግን በምክንያት ነው::

በመንፈሳዊም ሕይወት ጌታ እግዚአብሔርንና ፈቃዱን ማወቃችን፤ ከፈቃዱ ብናፈነግጥ ኋላ ወደ ፍርድ እንደሚያመጣን መረዳታችን የምንፈልገውን ለማድረግና ለመሆን እንቅፋት ሆኖብናል ብለን ልናስብ እንችላለን። ከሽክማችን የተነሣ ከኋላችን የነበሩ ሲቀድሙን፤ የዚህን ዓለም አቀበት መውጣት ቀሏቸው እኛ ለመውጣት እየታገልን ስናቃስት ቁልቁል ሲያዩን፤ የስኬት ትርጓሜ ተንሸዋሮ እንዳልገባቸው ቂሎች ተቆጥረን መሳለቂያ ስንሆን ያማል፤ ዘላለምን ያስረሳል፡፡ ግን ከልዑላን አባት የሚሰጠን ሸክም እንቅስቃሴያችንን ቢገደበውና እንደ ልባችን እንዳንሆን ቢከለክለንም፤ ሊውጠን ዙሪያችንን ከሚዞረን አውሬ  የምንድንበትና ረዥም ሕይወት እንድንኖር (ዘላለም) የሚያጎናጽፈን ጋሻ ነው። ፍጥነትን የሚገድብ እንጂ ለእርጋታ ሕግ ወጥቶለት አያውቅም፤ ምክንያቱም ጥፋትን የሚቀድመው ፍጥነት ነውና። እርጋታና መንቀርፈፍም አንድ ሆነው አያውቁም።

መስቀልን እንሸከመዋለን፤ ሽክማችን ደግሞ መጠለያ፣ መሸሸጊያ፣ መከለያ ይሆነናል። ምሥጢሩ እስኪገባን ለጊዜው ሊያደክመን ይችላል፤ ደኅንነት ያለ ግን በተሸከምነው መስቀል ሥር ነው:: የዔሊም ተፈጥሮና ሕይወት ለዛሬ ይህን ወሰድን:: ለእኛ ማስተዋል ለዔሊ መልካም ዕድሜ ተመኘሁ!!!

ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

13 አስተያየቶች

  1. እውነት ነው ሁላችንም የየራሳችንን ሸክም በአኮቴት በምስጋና መሸከም እንዳለብን ለጥቅማችን እንደሆነ ተምሬበታለው የሕይወትን ቃል ያሰማልን

  2. “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ማቴ 16፥24 በቃሉ መሠረት እያንዳንዱ የሚሸከመው የየራሱ መስቀል አለው።ቃለ-ህይወት ያሰማልን መምህር ምስጋናዬ የላቀ ነው

  3. “ለመሆኑ ስብሰባው ላይ የፍጥረታት ባለቤት እግዚአብሔር ነበር?” ስትል ያልጠበቀውን ጥያቄ ለወሬ ነጋሪው አቀረበች። እርሱም ሳያመነታ “አይ እርሱስ የለም፤ አልተገኘም፤ አላየሁትም ” በማለት በርግጠኝነት ሲመልስ ዔሊ “እንግዲያውስ ተዋቸው!” ብላ ሣር ወደ መጋጧ ተመለሰች።
    እግዚአብሔር ባልወሰነብን/ባልፈረደብን ነገር ላይ መጨነቅ እንደሌለብን ፣ ሌሎች የሚሉትን ሳይሆን እግዚአብሔር የሚወደውን ማድረግ የክርስትና መልክ መያዝ ነው ።
    እግዘብሔር አምላክ
    እንደ ኢሌ እርጋታን ፣ ማስተዋልን ያድለን

  4. ቃለ ሕይወት ያሰማልን
    ። “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ማቴ 16፥24

  5. “መስቀልን እንሸከመዋለን ፤ ሸክማችን ደግሞ መጠለያ ፣ መሸሸጊያ ፣ መጠለያ ይሆነናል።”
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን!

  6. “ጥቂት በጥቂት አደገ… ” ወንጌል ቅዱስ🙏👏
    “…እለ ይትወሀብ ሎሙ ፯ምክዕቢታት ትምህርት ለኵሉ ፍጥረት ዚአሁ” መጽ. ሄኖክ፴፭፥፴፩

    መምህር ቃለሕይወት ቃለ ጽድቅ ያሰማልን
    ያንደረባው ሚዲያ
    ‘ለሀገራችንን ጥሩ ነገርን ይዛቹ እየመጣችሁ ነው’
    ጸጋውን እድሜውን ያብዛላቹ🙏
    🙏

    ከወደድኩት በጥቂቱ
    “ለመሆኑ ስብሰባው ላይ የፍጥረታት ባለቤት እግዚአብሔር ነበር?” ስትል ያልጠበቀውን ጥያቄ ለወሬ ነጋሪው አቀረበች። እርሱም ሳያመነታ “አይ እርሱስ የለም፤ አልተገኘም፤ አላየሁትም ” በማለት በርግጠኝነት ሲመልስ ዔሊ “እንግዲያውስ ተዋቸው!” ብላ ሣር ወደ መጋጧ ተመለሰች።”

    “ፍጥነትን የሚገድብ እንጂ ለእርጋታ ሕግ ወጥቶለት አያውቅም፤ ምክንያቱም ጥፋትን የሚቀድመው ፍጥነት ነውና። እርጋታና መንቀርፈፍም አንድ ሆነው አያውቁም።”
    ቀሲስ [ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ] ታምራት ውቤ(በቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ ምሩቅ) መምህር ከእሷ ገና ብዙ እማራለን ጸጋውን ያብዛልዎት

    • ቃለ ህይወትን ያሰማልን!
      በሰው ውሳኔ ለይ ሳይሆን በ እግዚአብሔር ሀሳብ ላይ ለመደገፍ የበረታን ያድርገን።

  7. ቃለ ሕይወት ያሰማልን! እኔ በግሌ በብዙ ነገር ኋላ የቀረሁ እንደሆነ ይሰማኛል። ምናልባት እንደተባለው ክርስቶስ እንድሸከም ያዘዘልኝ መስቀሎች ይሆናሉ። ዋናው ግን ይህን አምኖ መቀበልና በጌታ ታምኖ በእርጋታ መፅናት ይመስለኛል። ለዛ የመንፈስ ልዕልና ያብቃን! በድጋሜ ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

  8. መምህር እግዚአብሔር ጸጋውን አብልጦ ይስጥልን። ቃለ ህይወት ያሰማልን!!

  9. እንደ ዔሊ የተሰጠንን እድሚያችን በእርጋታ እንድንኖር ያድርግልን ፣በሁሉ እግዚአብሔር ይቅፕድምልን አባታችን ቃለሕይውት ያሰማልን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *